ፌዴሬሽን፡- ለዋልያዎች መቀጣት መንስኤው ‹ዝንጋታ› ነው

(ሰይፉ አለምሰገድ)

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምንያህል ተሾመ ሁለት ቢጫ ካርድ አይቶ ሳለ ሰኔ 1/2005 ከቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን ጋር በተደረገው ጨዋታ መሰለፉ ስህተት እንደሆነ አመነ፡፡

ፌዴሬሽኑ ብሄራዊ ቡድኑ ከደቡብ አፍሪካ አቻው ጋር ከመጫወቱ በፊት ችግር ስለመፈጠሩ ፊፋ አሳውቆት እንደነበር ገልጿል፡፡

ሆኖም ይህ ችግር በቡድኑ ተጫዋቾችና በደጋፊዎች ላይ ያልተፈለገ የመንፈስ ጫና እንዳይፈጥር በመስጋት መረጃውን ይፋ ሳያደርግ ቆይቷል፡፡

ፌዴሬሽኑ በፈጠረው ችግር ዙሪያ ዛሬ ሰኔ 11/2005 ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ መሰረት ፊፋ ተጫዋቹ ሁለት ቢጫ ካርድ በማየቱ የተነሳ ከቦትስዋና ጋር በተካሄደው ጨዋታ እንዳይሰለፍ የሚገልፅ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ ልኳል፡፡ ይሁንና የፌዴሬሽኑ አመራሮችና አሰልጣኝ ይህን የፊፋ ውሳኔ በመዘንጋታቸው ተጨዋቹን አሰልፈውታል፡፡

የፌዴሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለችግሩ ተጠያቂ ያላቸውን ግለሰቦች ዝርዝርም ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህ መሰረት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንትና የብሄራዊ ቡድኑ ቡድን መሪ አቶ ብርሀኑ ከበደ፣ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው፣ አሰልጣኝ ስዩም ከበደ፣ የቡድኑ ተጨዋች ምንያህል ተሾመ፣ የስራ አስፈፃሚ አባልናየቡድን መሪ የነበሩ አቶ አፈወርቅ አየለ እና የፌደሬሽን ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አሸናፊ እጅጉ በጥፋተኝነት ተፈርጀዋል፡፡

በፊፋ ህግ መሰረት ተገቢ ያልሆነ ተጨዋችን ማሰለፍ በጨዋታው የተገኘውን ነጥብ የሚያሳጣና ተጨማሪ የገንዘብ ቅጣትም የሚያስጥል ነው፡፡

በዚህ መሰረትም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 3 ነጥብና 6 ሺህ ስዊስ ፍራንክ እንደሚቀጣ ፊፋ ያስታወቀ ሲሆን በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን እስከ ሰኔ 14/2005 ዓ/ም ምላሽ እንዲሰጥም በፃፈው ደብዳቤ አስታቋል፡፡

አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በተፈጠረው ስህተት የተሰማቸውን ሀዘን ገልፀው ጳጉሜ 2/2005 ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር ለሚካሄደው ጨዋታ ከወዲሁ መዘጋጀት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጨዋታ አሸንፈን ወደ መጨረሻው የአለም ዋንጫ ማጣሪያ እንደምናልፍ እርግጠኛ ነኝ ብለዋል አሰልጣኙ፡፡ለዚህም የቡድኑ አባላት ዝግጁ መሆናቸውን አሰልጣኙ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ በበክላቸው በአሰራር ክፍተት የተፈጠረው ችግር አሳዛኝና ሊከሰት የማይገባው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፌደረሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥፋተኞቹ ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንደሚገባቸው የተስማማ መሆኑን በመግለፅ በአጭር ጊዜ ውስጥ የቅጣት ውሳኔውን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ በተፈጠረው ችግር ከፍተኛ ሀዘን እንደተሰማው ገልፆ ለኢትዮጵያ ህዝቦችም ይቅርታ ጠይቋል፡፡

*************

Source: ERTA – June 18, 2013, titled “ፌዴሬሽኑ የፊፋን ክስ አመነ”.

Daniel Berhane

more recommended stories