ኢትዮጵያ | ሙስና፤ ሙሰኞች፤ ኣሞሳኞችና የሙስና ተከላካዮች

(ጆሲ ሮማናት)

ባለፈው ሳምንት የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ነጋዴዎችን በሙስና ጠርጥሮ እንዳሳሰረና ፍርድቤት እንዳቀረበ ኣይተናል[1]፡፡ ጉዳዩ በጥርጣሬ ደረጃ ያለና በፍርድ ቤት የተያዘ ስለሆነ ስለዛ ሳናወራ ኣሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የሙስና ኣደጋና ለሙስና ኣመቻች የሆኑ ጉዳዮችን ኣንድ ሁለት እንይ፡፡ በርእሱ ንደተገለፀው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ ሙስና የሙሰኛች፤ ኣሞሳኞችና፤ የሙስና ተከላካይ ኣካላት ኣስተሳሰብና ድርጊቶች ውጤት ነው፡፡

ሙሰኞች

ኣብዛኞቹ ሙሰኞች ከከፍተኛ እስከ ታችኛው የመንግስት እርከን ውስጥ ትብዛም ትነስም ስልጣን የተቆናጠጡ ወይም ህዝብን ለማገልገል ደሞዝ ተቆርጦላቸው የተቀመጡ ሰራተኞች ናቸው (ከመንግስት ተቀጣሪ ሰራተኛ ቁጥር ኣንፃር ትንሽ ቢሆንም)፡፡ እነዚህ ሰዎች ባላቸው የስራ ሃላፊነት (ባብዛኛው ያገኙት በሹመት ነው) ምክንያት ወደ ሙስና እንዲገቡ የሚያበረታቷቸው/የሚገፋፏቸው በርካታ ምክንያቶች ኣሉ፡፡

ኣንደኛ ድህነት ነው፡፡ ያ ያደጉበት ድህነት ተመልሰው ላለማየት በማንኛዉም መንገድ ሃብታም መሆንን ይመኛሉ፡፡ ሁለተኛ የማህበረሰብ ተፅእኖ ነው፡፡ ህዝባችን ስልጣንና ሙስና ለያይቶ ኣያይም፡፡ ኣብዛኛው ሰው የሚያስበው ኣንድ ሰው ባለስልጣን ሆነ ማለት ይሞስናል- ኑሮውን ያሻሽላል ነው፡፡ ሙስናን የሚፀየፍ ባህል የለንም፡፡ ኣሁን ኣንቺ ኣንድ ደህና ሙስና ይሰራበታል ተብሎ የሚታመን (ለምሳሌ ጉምሩክ ወይ ከመሬት ጋር ተያያዥነት ያለው የመንግስት ስራ ወይም ማንኛዉም NGO) ቦታ ላይ ሆነሽ ሙስና ባትሰሪ “ጅል” ወይም ደግሞ “ኣትበላ-ኣታስበላ ገገማ” ልትባይ ትችያለሽ፡፡ ከበላሽ ግን “ወንድ ነች” ነው የሚሉሽ – ይሄው ነው:: በመብላትሽ የሚቃወሙ ሰዎች ካሉ ያንቺን ቦታ ይዘው መብላት የሚፈልጉት ናቸው – ሆዳሞች፡፡

ሌላው ምክንያት በተለይ ኣሁን ኣሁን ኣልፎ ኣልፎ የሚታየው በሃላፊነት ቦታ የሚቀመጡ ሰዎች የፖለቲካ ተሳትፎ ብቻ እየታየ በማይመጥናቸው ቦታ ይሾማሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ለስራው ብቁ ኣለመሆናቸው ያውቃሉ – በስራው በራስ የመተማመን መንፈስ የላቸዉም፡፡ ደግሞም በማንኛዉም ሰኣት ሊወርዱ እንደሚችሉም ያስባሉ፡፡ የባሰው ደግሞ ከዛ ቦታ ቢነሱ ባላቸው እውቀትና ችሎታ የትም መድረስ እንደማይችሉ ይገነዘባሉ፡፡ ስለዚህ ያለው ኣማራጭ መሞሰን ነው፡፡ እንዲህ ኣይነት ሰዎች በመጀመርያም ወደ ቦታው ሲመጡ ምንም ሞራል ስለሌላቸው ቢሰርቁ ምንም ቅር ኣይላቸዉም – ኣይከነክናቸዉም፡፡ 10 ሚልዮን ብር በጀት ተመድቦለት በጥራት ተሰርቶ 30 ኣመት እንዲያገለግል የታቀደን ትምህርት ቤት ወይም ክሊኒክ ጉቦ ተቀብለው ጥራቱ ሳይጠብቅ በ6 ሚልዮን ብር ቢሰራና 6 ኣመት ብቻ ቢያገለግል ግድ የላቸዉም፡፡ እነሱ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የፖለቲካ ቃላትን እየወረወሩ፤ እየገመገሙ – እያስገመገሙ – “ልማታዊ ሰራዊት እየገነባን ነው” እያሉ እያስመሰሉ መቆየት ይችላሉ፡፡ በቢሮኣቸዉ መግቢያ ላይም “የኣቶ መለስን ራእይ እናሳካለን” የሚል ትልቅ ፖስተር ይለጥፋሉ – ኣስመሳዮች፡

ኣሰራራቸውን ለመፈተሸና ለመዘገብ የሚመጣ ጋዜጠኛ ኣያስተናግዱም፡፡ በተኣምር መረጃ ቢገኝ እንኳን ያንን ዘገባ ለማስተላለፍ የሚሞክር ዜጋ ወይም ጋዜጠኛ በፀረ-መንግሰትነትና ፀረ-ልማትነት ይፈርጁታል፡፡ ለነገሩ እነሱ እዚህ ላይ ብዙ ጥረት ኣያስፈልጋቸዉም- በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ውስጥ ያሉ ኤዲተሮች እንደዚህ ኣይነት ዘገባ የድርጅትንና የመንግስትን ገፅታ ያበላሻል ብለው ስለሚያስቡ (ወይ ስለሚነገራቸው ሊሆን ይችላል) እንደዚህ ኣይነት ወሬዎችን ኣይዘግቡም – ምናልባት ኣንድ ዘመቻ እስኪጀመር ድረስ፡፡ ሙሰኞቹ ችግራቸው ይታውቅብናል ብለው ከሰጉና በጣም “ብልህ” ከሆኑ ደግሞ ጋዜጠኞችን ጠርተው በመስሪያቤታቸው ስላለው “ኣበረታች ለውጥ” መግለጫ ይሰጣሉ – ለማስቀየስ፡፡ ኣየህ ያ ቅድም ችግር ኣለ ሲባል ኣላስዘግብም ያለው ኤዲተር ኣሁን ዘና ብሎ ዘገባውን እንዲተላለፍ ይወተውታል፡፡

ኣሞሳኞች

ሙሰኞቹ ስራቸውን ለመስራት ከሚያስፈልጓቸው ነገሮች ኣንዱ ጉቦ ለመስጠት የተዘጋጀ ሃይል መኖር ነው – ኣሞሳኝ፡፡ ባገራችን ደግሞ በዚህ ምድብ ውስጥ ያለው ኣብዛኛው ነጋዴው ነው፡፡ የኛ ኣገር ነጋዴ ከማህበረሰቡ የወጣ እስከሆነ ድረስ የሙስና መንፈሱ ጠንካራ ነው፡፡ ኣንድ ተራ ጉዳይ ኣንድ መስሪያቤት ሄዶ ሁለት ሰኣት ወረፋ ጠብቆ በክብር ተስተናግዶ ጉዳዩ ከሚያስፈፅም ይልቅ ሃላፊውን ወይም ሰራተኛዉን በስልክ ኣናግሮ፤ ጉቦ ሰጥቶ- ሁለት ሶስት ቀን ደጅ ጠንቶ ቢያስፈፅም የሚያረካው ሰው ብዙ ነው፡፡ ኣንድ የመንግስት መስሪያቤት ጋ ሄዶ ኣንድን ኣገልግሎት መብቴ ነው ብሎ ተከራክሮ ከማስፈፀም ይልቅ የተጠየቀውን ጉቦ ከፍሎ መጨረስ የሚፈልግ መኣት ነው፡፡ ኣንድን ኣገልግሎት ለማግኘት ህፃናት፤ እናቶችና ሽማግሌዎች ተሰልፈው ወረፋ እየጠበቁ እያየ በዘመድ፤ በትውውቅ፤ ወይም በገንዘብ የማይገባውን ኣገልግሎት ወይም ወረፋ ኣግኝቶ ቀድሞ ለመጨረስ የሚተጋ ሰው በጣም ብዙ ነው – ደግሞም ምንም ቅር ኣይለዉም፡፡

ከዚህም ኣልፎ ከሙሰኞቹ ጋ ተመሳጥሮ በኣጭር ጊዜ ውስጥ ሃብታም መሆን የሚፈልግ ኣለ፡፡ እስኪነቃበት ድረስ “ልማታዊ ባለሃብት” እየተባለ ከዛም ኣልፎ “ሞዴል” ተብሎ እየተሸለመ ይኖራል – ተነቅቶበት እስር ቤት እስኪወረወር ድረስ፡፡ በኣጠቃላይ ለሙስና የተመቻቸ ማህበረሰብ ኣለ፡፡ ብትፈልግም ባትፈልግም እንድትሞስን ይገፋፋሃል – ኣሞሳኝ፡፡

የተለጠጠ ስልጣንና ያልተሟላ ህግ

ኣንዳንዴ ለባለስልጣናት በህግ የሚሰጡ ስልጣን (የመወሰን ሃይል) ከሚገባ በላይ ይሆንና ችግር ይፈጥራሉ – ለሙስናም ክፍተት ይሰጣሉ፡፡ በተለይ በትላልቅ የመንግስት ስልጣን የሚቀመጡ ዋና የድርጁቱ ሰዎች ናቸው – ታማኝና ቁርጠኛ ኣገልጋይ ናቸው ተብሎ የታሰበ በሚመስል መልኩ መያዝ ካለባቸውና መሸከም ከሚችሉት በላይ የመወሰን ስልጣን በህግ ይቸራቸዋል፡፡ ለምሳሌ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የገቢ ኣሰባሰብ ስርኣቱን ለማሻሳል ተብሎ ኣዲስ ህግ ይወጣና ለባለስልጣኑ ዳይሬክተር ከተገቢ በላይ የሆነ ስልጣን ያሸክማቸዋል፡፡ ለምሳሌ በኣንድ ወቅት የባምቢስ ሱፐርማርኬት ባለቤት መክፈል የሚገባቸው 91 ሚልዮን ብር ሳይከፍሉ ስለተገኙ ድርጅቱ ታሽጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ሆኖም ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ከባለስልጣኑ ሃላፊዎች ጋር በመደራደር 38 ሚልዮኑ ተቀንሶላቸው 53 ሚልዮን ብቻ እንዲከፍሉ እንደተወሰነ ፎርቹን ጋዜጣ በወቅቱ ኣስነብቦናል[2]፡፡

እዚህ ላይ በወቅቱ የባለስልጣኑ ሃላፊዎች ድርጅቱ ለከተማው ከሚያበረክተው ኣገልግሎት ኣንፃር እና ባለሃብቶችን ላለማስደንገጥ ወዘተ ወዘተ በሚሉ ምክንያቶች ቀንሰውላቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን በዛ ቦታ ላይ የሚቀመጥ ሰው መሞሰን የሚፈልግ ሰው ከሆነ ሁኔታው የተመቻቸ ነው፡፡ ሃላፊዎቹ ኣምስት ሚልዮን ብር ጉቦ ወስደው ባለሃብቱ ኣስር ሚልዮን ብር ብቻ ለመንግስት እንዲከፍሉ ቢያደርጉ ማን ይከለክላቸዋል? እንዴትስ ማረጋገጥ ይቻላል? ደግሞም እንደዚህ ኣይነት ኣሰራር በመካከለኛ ሃላፊዎች ዘንድ የተለመደች ናት- – በግብር መጠን ላይ መደራደር፡፡ እንደዚህ ኣይነት ክፍተቶች ብዙ ህጎች ላይ ይታያሉ – ብዙ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ ንፁህ የሆነ ሃላፊ ቢኖር እንኳን እሱን ለማሞሰን የተዘጋጁ ኣሞሳኞች እስካሉ ድረስ እና የህግ ክፍተት እስካለ ድረስ ወደ ሙስናው ሊገፋፋ ይችላል፡፡ ስለዚህ መንግስት ሙስና ከበሉ በኋላ ማሰርና ንብረት ማስመለስ ብቻ ሳይሆን እንደነዚህ ኣይነት ያሉ ለሙስና የሚያጋልጡ የህግ ክፍተቶችን መሙላት ይገባዋል፡፡ ይሄ ማለት እንደዚህ ኣይነት ቅሬታ መታየት ያለባቸው በፍርድቤት መሆን ኣለበት:: ግልፅነትንና ተጠያቂነትን ማስፈን ማለት ነው፡፡ የስልጣንን ገደብ መወሰን ማለት ነው፡፡

ደካማ ህግ ኣስከባሪዎችና ኣስፈፃሚዎች

መንግስት የሃገሪቱን ህግ ተላልፈው ወንጀልና ጥፋት የሚፈፅሙ ዜጎችን ተከታትለው ማስረጃ ኣሰባስበው ለህግ እንዲያቀርቡ ያቋቋማቸውና በህግ ሙሉ ስልጣን የተሰጣቸው ኣካላት ኣሉ፡፡ ለምሳሌ የፖሊስ ኣካለትና የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን፡፡ ሆኖም እነዚህ መስሪያቤቶች ስልጣናቸውን በኣግባቡ ኣይጠቀሙም፡፡

ለምሳሌ በኣንድ ወቅት በኢትዮጵያ ለኣመታት የተንሰራፋውን የቅጂ መብትን በተመለተ ሲማረሩ የቆዩት የኣገራችን ኣርቲስቶች ከቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ጋር ከተወያዩ በኋላ በፖሊስና ሌሎች የፍትህ ኣካላት ከፍተኛ ዘመቻ ተካሂዶ ዘፈኖችን በህገወጥ መንገድ እየቀዱ ሲሸጡ በነበሩ ሰዎች ላይ እርምጃ ተወስዶ ነበር፡፡ ብዙ ሲዲዎችን ሲቃጠሉና ወንጀለኞቹ ወደፍርድ ሲቀርቡም በኢቲቪ ኣይተን ነበር፡፡

በወቅቱ በቴሌቪዝን እየቀረቡ ስለእርምጃው መግለጫ ሲሰጡ የነበሩት ዝሆንን የሚያካክሉ የፍትህና የፖሊስ ሃላፊዎች “እርምጃውን የወሰድነው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከኣርቲስቶቻችን ጋር ከተወያዩ በኋላ እርምጃ እንዲወሰድ በሰጡት ትእዛዝ መሰረት ነው” እያሉ በተደጋጋሚ ሲያወሩ ሰምተናል፡፡ ሰሞኑም በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩት ባለስልጣናትና ነጋዴዎች ላይ ክትትል የጀመርነውና እርምጃ የወሰድነው ጠ/ሚ መለስ 1 ኣመት 10 ወር በፊት በሰጡት ትእዛዝ ነው ተብሏል[3]፡፡ ጎበዝ እነዚህ ሰዎች እኮ ህግን የተላለፈ ማንኛውም ሰው ላይ ወደ ፍርድ የማቅረብ ሃላፊነት ኣለባቸው፡፡ ለምንድነው ሁሉም ትእዛዝ ከጠ/ሚኒስትሩ የሚጠብቄት? “ጠ/ሚኒስትሩ ስራቸውን ይስሩ እናንተም ስራችሁን ስሩ” ሊባሉ ይገባል፡፡ ኣለበለዚያ እዛ ቁጭ ብለው ትእዛዝ የሚጠብቁ ከሆነ በቋሚነት መቀጠራቸው ኪሳራ ነው፡፡

እና ምን ይጠበስ ?

ኣንደኛ – ሙሰኞች ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገቢ ነው፡፡ ሆኖም የሚሰሩት ስራዎች (የሙስና መከላከልም ሆነ የሌላ ሴክተሮች) በዘመቻ መስራቱ ቢቆምና ተከታታይና በሂደት እየተገመገመና እየጠራ የሚሄድ ኣሰራር ቢኖር ይበጃል፡፡ የኣንድ ሰሞን ሞቅታ ብቻ እንዳይሆን፡፡ ሁለተኛ – ህግ ሲወጣ ለመንግስት ሃላፊዎች ተገቢ ያልሆነ (በተለይ በፍርድ ቤት ሊታዩ የሚገባቸውና ለሙስናና ድርድር ክፍተት የሚሰጡ ነገሮች) መሰጠት የለበትም፡፡ ስልጣናቸው ተመጣጣኝና ደረት ያለው ቢሆን የከፍተኛ ደረጃ ሙስናን ኣደጋ መቀነስ ይቻላል፡

ሶስተኛ – ኢህኣዴግ በ9ኛው ጉባኤው ላይ “ኣድርባይ” ብሎ የፈረጃቸውን ኣባላቶቹን ይመርምር፡፡ ብዙ ሃቀኞች እንዳሉ ሁሉ በርካታ ኣጥፊዎችም ኣሉ፡፡ ድሮውም የሚሰማ ጠፍቶ ነው እንጂ ህዝቡ’ኮ ኣስቀድሞ ነቅቶባቸው እየተናገረ ነበር፡፡ በኣሁኑ ሰኣት ብዙ ሰው ወደ ኢህኣዴግ ኣባልነት የሚገባው ሊታገል ሳይሆን ኑሮን ሊያሻሽል ነው ተብሎ ይታመናል – በበርካታ ኣባላትም ጭምር፡፡ ዞሮ ዞሮ ምንም እንኳን ቢዘገይም መጨረሻ ላይ ችግሩን በግልፅ ማውጣቱ ጥሩ ነው፡፡ ሆኖም ግን ችግራችን “ኣድርባይነት ነው” ብሎ ማወጁ ብቻ ለውጥ ኣያመጣም፡፡ ይሄ ችግር መወገድ ኣለበት፡፡ ኣራተኛ – የመገናኛ ብዙሃን ግልፅና ተገቢ የሆነ መረጃ የማግኘትና ችግር ሲኖርም ለህዝቡ የማሳወቕ መብታቸው ይከበር፡፡ ኣንድ ማዘጋጃ ቤት ውስጥ ያለ ተራ ሰራተኛ የፈፀመው ሙስና ወይም ወይም ተገቢ ኣገልግሎት ኣለመስጠት ቢዘገብ የመንግስትን ስም ያበላሻል ተብሎ እንዲታፈን ኣይደረግ፡፡ የንደዚህ ኣይነት ሰዎች መጋለጥ በዋናነት የሚጠቅመው መንግስትን ነውና – ከዛም ኣልፎ ህዝቡ፡ በመጨረሻም – ህግ ኣስከባሪዎችና ስራ ኣስፈፃሚዎችም የተሰጣችሁን ስራና ሃላፊነት ለመወጣት ሁሌ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ትእዛዝ ኣትጠብቁ – እባካችሁ ሃላፊነታችሁን ተወጡ፡፡

—–
ማጣቀሻ፡-
[1]. Court report: Melaku Fenta et al corruption suspects – first day
[2]. Bambis Pays 19m Br in First Instalment to Tax Auth
[3]. በባለሀብቶች ላይ ምርመራው የተጀመረው በቀድሞው ጠ/ሚኒስትር መመርያ መሆኑ ተገለጸ

*************
The author Jossy Romanat in a co-blogger in this blog. He is a social scientist residing in Canada and can be reached at [email protected].

Daniel Berhane

more recommended stories