የግብርና ምርት ዕድገት እንደዓምና «ወገቡን እንዳይዝ» እየተመከረ ነው

ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የሰብል ምርት ውስጥ ከ 30 እስከ 35 በመቶ የሚሆነው የሚመረተው በአማራ ክልል ነው ። በ2003 /2004 የምርት ዘመን በክልሉ 75 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ መሰረት በ 2004/2005 የምርት ዘመን ለማሳካት የታሰበው 109 ሚሊዮን ኩንታል ቢሆንም የምርት መጠኑ ወደ 74 ነጥብ 96 ሚሊዮን ኩንታል ዝቅ ብሏል። በክልሉ በአገዳና በብርዕ እህሎች የ38 በመቶ፣ በጥራጥሬ ሰብሎች የ20 በመቶ እና በቅባት እህሎች የ29 በመቶ የምርት ጉድለት ተከስቷል።

በኦሮሚያ ክልል በ2004 /2005 የምርት ዘመን 146ሺ 542 ኩንታል ለማምረት ታቅዶ 113ሺ 316 ኩንታል ብቻ ነው የተገኘው። በምርት ዘመኑ በዋና ዋና ሰብሎች በአማካይ በሄክታር 25 ነጥብ 6 ኩንታል ለማምረት የታቀደ ቢሆንም የተመረተው ግን 20 ነጥብ 33 ኩንታል ብቻ ሆኗል።

በሁለቱ ክልሎችም ሆነ በሌሎቹ የአገሪቱ አካባቢዎች የግብርና ምርት ምጣኔ ዝቅተኛ መሆኑን ነው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የቅድመ ምርት መረጃ የሚያመለክተው። ይኸው ጉዳይም በአሁኑ ወቅት የግብርናው ዘርፍ አነጋጋሪ አጀንዳ በመሆኑ በተለይም የግብርና ሚኒስቴርና የክልል ግብርና ቢሮዎች በጋራ ምክክር መድረካቸው እየተነጋገሩበት ይገኛሉ።

ከትናንት በስቲያ ጀምሮ በአክሱም ከተማ ሳቢያን ሆቴል እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ወቅት እንደተመለከተው፤ የምርት እድገት ምጣኔው መቀነሱ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠውና በቀጣይነትም ከፍተኛ ጥንካሬን የሚጠየቅ ነው።

የአማራ ክልልን የበልግ ሥራዎች ማጠቃለያና የመኸር ሥራዎች ዝግጅት በተመለከተ ገለፃ ያደረጉት የክልሉ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አምላኩ አስረስ እንደተናገሩት፤ ከተቀመጡ ግቦች ውስጥ በተፈጥሮ ሀብት ልማት የታየውን የተደራጀ ሠራዊት በሰብል ልማቱም መገንባት የመጀመሪያው ነው ። በክልሉ በአሁኑ ወቅት ማዳበሪያ የሚጠቀመው አርሶ አደር 25 በመቶ ብቻ ሲሆን፤እንዲሁም ምርጥ ዘር ደግሞ የሚጠቀሙ እስከ 15 በመቶ ናቸው። ስለዚህ የማስፋት ሥራውን ማጠናከርም ትኩረት እንደተሰጠው ተናግረዋል ።

በፍፃሜውም በዋና ዋና ሰብሎች አጠቃላይ የምርት መጠንን በሄክታር አሁን ካለበት አማካኝ 17 ኩንታል ወደ 34 ኩንታል በማሳደግ ጥቅል ምርቱን 135 ሚሊዮን ኩንታል የማድረስ ግብ መቀመጡንም ነው ዶክተሩ የገለፁት።

በአማራ ክልል ለምርቱ እድገት መቀነስ የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ። ማሳን ደጋግሞ ማረስ ለምርታማነት ማደግ ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አምላኩ፤በክልሉ በአሁኑ ወቅት ሰብል እየተመረተበት ካለው አራት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ ሦስት ጊዜ ደግሞ እየታረሰ የሚመረትበት መሬት አንድ ሚሊዮን ሄክታር ብቻ ነው።

እንደ ዶክተር አምላኩ ገለጻ፤ በክልሉ ሁለት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬትን በመስመር በመዝራት መሸፈን የሚቻል ቢሆንም አሁን ግን በመስመር እየተዘራ ያለው 570 ሺ ሄክታር መሬት ብቻ ነው። በተጨማሪም በክልሉ አንድ ሚሊዮን ሄክታር የኮትቻ መሬት ያለ ሲሆን እየተንጣፈፈ የሚዘራበት ግን 200 ሺ ሄክታር ብቻ ነው።

ከኦሮሚያ ከልል ግብርና ቢሮ ሪፖርት እንደተመለከተው፤ በመጪው የመኸር ወቅት 5 ነጥብ 95 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመሸፈን 177 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት እቅድ ተቀምጧል።

የትግራይ ክልል ግብርና ቢሮ እንደገለፀው፤ በተለይም በበጋው ወቅት ለተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፤ ለተፋሰስና ለመስኖ ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መጠነ ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል። በዚህም 100ሺ ሄክታር መሬት ለመሸፈን ታቅዶ 113ሺ 831 ሄክታር መሬት ለምቷል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኪሮስ ቢተው እንደተናገሩት፤ የልማት ሠራዊት ግንባታው በተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ በተሳካ መልኩ የተፈጸመ ሲሆን፤ በመስኖ ልማትም በተመሳሳይ ተደግሟል። «የሁለቱን ተሞክሮ በመቀመርም በሰብል ምርት ላይ የመተግበር ዝግጅቱ ተጠናቋል» ብለዋል።

እንደ አቶ ኪሮስ ገለጻ፤ በዘንድሮው የበጋ ሥራ ወሳኝ ትኩረት በተሰጠው የመስኖ ልማት ሥራ በክልሉ ከ85 በመቶ በላይ የሚሆነው አርሶ አደር ቢያንስ አንድ የመስኖ አማራጭ እንዲኖረው ተደርጓል። 73 በመቶ የሚሆነው አርሶ አደርም ቢያንስ በአማካይ ዜሮ ነጥብ ሦስት ሄክታር መሬት እየለማ ይገኛል።

በሰብል ምርታማነት በኩል በእቅድ የተቀመጠው ግብ በሙሉ ባይሳካም በዋና ዋና ሰብሎች በአማካኝ በሄክታር 26 ኩንታል ምርት ተገኝቷል። ግብርናውም የስድስት ነጥብ ሁለት በመቶ የእድገት ምጣኔ አሳይቷል። በመጪው የምርት ዘመን የሰብል ምርታማነቱን በ30 በመቶ በማሳደግና አማካኝ ምርታማነትንም በሄክታር 36 ኩንታል በማሳደግ የሁለቱን ዓመታት ያጣመረ አጠቃላይ እድገት ለማስመዝገብም ዝግጅት እየተደረገ ነው።

የደቡብ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በመስኖ ልማት ዝግጅትና በበጋ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት በተከናውኑ ተግባራት ጠንካራ የልማት ሠራዊት በመገንባት፤ በአመለካከትና በክህሎት ረገድ ሰፊ ክፍተቶች ተስተውሏል።

በጋራ የምክክር መድረክ ወቅት ክልሎች በቀጠዩ ክረምትና በተከታዮ የመኽር ወቅት ሊሳኩ የሚገባቸውን ወሳኝ የሰብል ልማት ግቦች አስቀምጠዋል። ግብቹን ለማሳካትም የሰብል ምርት እድገት የህልውና ጉዳይ መሆኑ የታመነበት የአመለካከት አንድነት መፍጠር ትኩረት እንደሚሰጠው ነው ክልሎቹ የገለፁት። የባለሙያውንና የአርሶ አደሩን የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የተሻሻሉ አሰራሮችን በስፋት የመተርጎም ክህሎት ውስንነትም ማስወገድ አለበት። የአደረጃጃትና የአሰራር ማነቆዎችን ለይቶ ማስተካከል፤ የክትትልና ድጋፍ ሥርዓትን መዘርጋትና የግብዓት አቅርቦትን በወቅቱ በማሟላትም የመጪውን መኸር የምርት እድገት መጨመር እንደሚቻልም ነው ክልሎች የገለጹት።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድይራድ ማንደፍሮ በበኩላቸው እንደገለጹት፤በመጪው ዓመት ምርታማነትን በአማካይ በ20 በመቶ የማሳደግ እቅድ ተቀምጧል። ለስኬቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት አገር አቀፍ «ኮማንድ ፖስት» ተቋቁሞ አፈጻጸሙን በየ15 ቀን እየገመገመ ነው፤በግብርና ሚኒስትሩ የሚመራና ተጠሪ መሥሪያ ቤቶችን ያካተተ ተመሳሳይ «ኮማንድ ፖስት»ም ተቋቁሟል። በተጨማሪም በየክልሉ በየደረጃው ተመሳሳይ «ኮማንድ ፖስት» ተቋቁሟል።

የጋራ ምክክር መደረኩን በንግግር የከፈቱት የግብርና ሚኒስትር አቶ ተፈራ ደርበው እንደተናገሩት ፤ የቀጣይ የምርት እድገትን በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መሠረት እንዲፈፀም አመራሩ ፤ ባለሙያውና አርሶ አደሩ በተለወጠ አመለካከት መንቀሳቀሳ አለበት።

**********

Source: Addis Zemen – April 21, 2013. Originally titled “ግብርና እንደ አምና «ወገቡን እንዳይዝ» እየተመከረ ነው”, authored by Abraham Ayalew.

Daniel Berhane

more recommended stories