መጅሊሱ በአዲስ መልክ ከተመረጠ ጥቂት ወራትን አስቆጥሯል፡፡

መጅሊሱ ሕዝበ ሙስሊሙን እንዲያገለግል፣ እንዲያረጋጋ፣ ወደተሻለ አቅጣጫም እንዲመራ፣ በመካከሉ ያሉ አለመግባባቶችን ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ እንዲችል ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የልማቱ ግንባር ቀደም ተሰላፊና ተጠቃሚ እንዲሆን አመቺ ሁኔታን እንዲፈጥር ይጠበቃል፡፡ አብዛኛዎቹ አመራሮችም እንሞክረው፣ ኢስላማዊ ኃላፊነታችንን እንወጣ በሚል እንጅ የተሻለ ገቢ ለማስገኘት በሚችል ሥራ ላይ ለመሳተፍ የሚችሉ ናቸው፡፡ ሁሉም የየራሳቸው የሆነ የተረጋጋ የግል ሕይወት ነበራቸው፡፡ ዘው ብለው፣ ተገፍትረው የገቡት ግን እንደሸረሪት ድር ከተተበተበ፣ መውጫውና መግቢያው ከማይታወቅ፣ ደግሞም ጠንካራ ከሆነ ኃላፊነት ውስጥ ነው፡፡

በአብዛኛው በመጅሊስ አመራር ማለትም በሕዝበ ሙስሊሙ አመራር የጠለቀ ልምድ የላቸውም፡፡ አንዳንዶቹም ከሰው ፊት ወጥተው መናገር የሚፈሩ ናቸው፡፡ ሌሎቹም ቁርዓንና ሐዲስን ማስተማር እንጅ ከፖለቲካው መዘውር (ማሽን) ጋር አይተዋወቁም፡፡ አንዳንዶቹም አዘዋወሩን ካልቻሉበት፣ የፖለቲካው መዘውር ከግራም ከቀኝም፣ ከውስጥም፣ ከውጭም ሲያላጋቸው ከጎናቸው የማይለያቸውን ቁርዓንና ኪታብ አንግበው ወደ መድረሳቸው ለመመለስ ምንም ነገር የማይመልሳቸው ናቸው፡፡ ለነዚህ ሰዎች ደሞዝም፣ ሥልጣንም፣ ፕሮቶኮልም ለነሱ ምንም ማለት አይደለምና፡፡

አዘዋወሩን የሚችሉበት ቢሆም ውስጣዊውና ውጫዊውን ተጽዕኖ ተቋቁመው ለማለፍ ራሳቸውን ካላዘጋጁ በስተቀር የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል አይሆንም፡፡ ይልቁንም የተመረጡበት ተጨባጭ ብሔራዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታ በቀኖናዊና በዘመናዊ፣ በአሸባሪና ተሸባሪ፣ በአክራሪና ተከራሪ፣ በተቀባይና በተከራካሪ፣ በጽንፈኛና ለዘብተኛ፣ አመለካከት መካከል ከፍተኛ ፉኩቻ የሚካሄድበት ጊዜ በመሆኑ በዚህ የባሕር ሞገድ ዋኝተው መውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ወደፊት ጠንካራ መጅሊስ ይኖር ዘንድ ሕዝበ ሙስሊሙ ጥቃቅን ልዩነቶቹን ወደ ጎን በመተው ካልተባበራቸው፣ መጅሊሱን የመረጠው ኅብረተሰብ ጽኑ የጀርባ አጥንት ሆኖ በሁሉም ነገር ካልተባበረው የሚጠብቃቸው ሞገድ በእርግጥም ከፍተኛ ነው፡፡ ሁሉም «እስቲ በመጀመሪያ እንደሌሎቹ ጠንካራ መጅሊስ እንኳን ይኑረን» የሚል ቅን አመለካከት ዛሬ ቢኖረው ወደፊት በልዩነቶች ላይ የጠለቀ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል ድባብ መፍጠር ይቻላል፡፡

ያም ሆነ ይህ አዲሶቹ የመጅሊሱ ተመራጮች፣ መጅሊሱን እንደ ሃይማኖታዊ ተቋም በአንድ በኩል ራሱን እያደረጀ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበረው የመጅሊስ አመራር የተጀመሩትን ሥራዎች ከራሱ ዕቅድ ጋር በማገናዘብ መሥራት ጀምሯል፡፡ ዕቅዱንም በመላው አገሪቱ የሚገኙ የመጅሊስ አመራር አባላትን በመጥራት አስተዋውቋል፡፡ እንዴት በተግባር ሊውል እንደሚችልም መመሪያዎችን አስተላልፏል፡፡ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ አመራር አባላትም ጠቃሚ ሐሳብ ተቀብሏል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በልዩ ልዩ ሙያ የተካኑ ሙስሊሞችን በመጋበዝ የምክክር ጉባኤ ለመጥራት የመጀመሪያውን ምዕራፍ ነድፏል፡፡ ይህም ማለት መጅሊሱ የሚመራው በፈጣሪ መልዕክተኛ የምክክር መንገድ (ሹራ) መሆኑ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱም «ነገ ፈጣሪ ፊት እራቁታችንን የምንቆም ስለሆነ ዛሬ በሐቅ እንሠራለን፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙን በሐቅ እንመራለን፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙም ቅን ፍላጎታችንን አይቶ ከጎናችን ሊቆም ይገባል፡፡ ብቻችንን ለመሥራት ፍላጎት የለንም፡፡ ብንፈልግም አንችልም፤» የሚል አቋም አንጸባርቀዋል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ ሰላሙን ተጎናጽፎ የዕለት ተዕለት ተግባሩን ያለአንዳች ሕውከት እንዲሠራም ምኞት አላቸው፡፡ ከእርሳቸው ጋር የሚሠሩትም እንደዚሁ፡፡ ይህ በእጅጉ ደግ ጅምር ነው፡፡ በቅንነት መሥራት ዋናው ጉዳይ ነው፡፡ ሙስሊም ሐቅን ፈላጊና በሐቅ ተመሪ መሆኑን የሚያረጋግጠው ከሠራ በኋላ ብቻ ሳይሆን ለመሥራት አስቦ፣ ተመኝቶ፣ ዓልሞ፣ ቃል ገብቶ ሲሠራ ነው፡፡ ፈጣሪም የሚመለከተው ቅን ልቦናን ነው፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ከተቋቋመ ግማሽ ዓመት ቢሆንም በነዚህ ወራት ጊዜያት ጠቃሚ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ ካከናወናቸው ተግባራት ውስጥም ልዩ ልዩ የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ያካተተ የምክክር መድረክ ማቋቋሙ ይገኝበታል፡፡ ይህ መድረክ በአጭር ጊዜ እንዲሠሩ ከነደፋቸው መርሃ ግብሮች ውስጥም የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

•    ሕዝበ ሙስሊሙ አሁን ካለበት ጊዚያዊ ችግር እንዲወጣ ከሚመለከተው የሙስሊሙ ኅብረተሰብ አካላትና ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ኃይላት ጋር በመሆን የማረጋጋት ተግባር ማከናወን፤
•    የሙስሊሙን አንድነት በማጠናከር ለሀገሩ ሰላምና ለልማት ጠንክሮ የሚሠራ ኅብረተሰብ እንዲሆን የሚቻለውን ያህል ጥረት ማድረግ፤
•    ወጣት ሙስሊሞች በእምነታቸው ጠንክረው በማንኛውም ሥፍራ ለአገሪቱ ልማት ንቁ ተሳትፎና አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ አመቺ ሁኔታን መፍጠር፤
•    ጠባብ አመለካከቶችን በመዋጋት ሕዝበ ሙስሊሙ በመቻቻል፤ በሰላም አብሮ መኖር፤ በመከባበር አብሮ መኖር አማራጭ የሌለው መርህ መሆኑን፤
•    አሁን የሚታየውን የአመለካከት ልዩነት ለማጥበብና ሕዝበ ሙስሊሙ እርስ በርሱ ተከባብሮ እንዲኖር የሚያስችል ሁኔታ ማመቻቸት፤
•    የሙስሊሙ ታሪክ፣ ባህል፣ ልምድ እንዲጠና በማድረግ በማንነቱ የኮራ ሙስሊም ኅብረተሰብ  መፍጠር፤
ይሁንና መጅሊሱ የሚገጥሙት ፈተናዎች ምንድን ናቸው? እነዚህንስ ከባድ ፈተናዎች ለማለፍ ምን ማድረግ አለበት? ለመሆኑ የአገራችን ችግር ከሌሎች አገሮች ችግር የተለየ ወይስ ተመሳሳይ ነው? ከዚህ ድምዳሜ የሚያደርሰንስ ምንድን ነው?

ትውስታ
የመጅሊሱ ምርጫ በተካሄደበት ሳምንት የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በዚህ ጋዜጣ ላይ የሚከተለውን አስተያየት ሰጥቶ ነበር፤ ለመሆኑ ይህ ዛሬ ምን ያህል ተለውጧል? ራሳችንን እንገምግም፤

«ባለፈው መስከረም 27 ቀን በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው ሕዝብን ያሳተፈ የኢስላማዊ ጉዳዮች ምክር ቤት (መጅሊስ) ምርጫ ተካሂዷል፡፡ የምርጫውን ሂደት የተቀበሉ እስከ ቀበሌ ምርጫ ጣቢያዎች የመረጡ እንዳሉ ሁሉ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ያልሄዱም ይኖራሉ፡፡ ወደፊትም የዞኖችና የክልሎች ምርጫዎች በመጨረሻም የከፍተኛው ምክር ቤት አባላት ይመረጣሉ፡፡ በተከታታይም ከቆየው ምክር ቤት ኃላፊነታቸውን ተረክበው መሥራት ይጀምራሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ምርጫውን ተቀብለው የመረጡትንም ሆነ ያልመረጡትን እስከ ጭራሹም «መጅሊሱ አይወክለንም» ያሉትንም በቅንነት በታማኝነት፣ ያለአድልዎ ምናልባትም የበለጠ ተጠቃሚ በማድረግ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ማለት ነው፡፡

«ነገሩ ኢስላማዊ መሆኑ ይቀርና ፖለቲካ ይሆንና፣ ያም ፖለቲካ በሌሎች ግፊት የበለጠ ይቀጣጠልና፣ ኢስላማዊ ሳይሆን የአገራችንን የአንዳንድ ችኮ መንቻኬ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፈለግ ይከተልና፣ በጎ ጅምሮችን ሁሉ መቃወም ይጀምራል፡፡ አንዳች ገደብ እስኪደረግለት ድረስ በጁምዓ ሶላት ወቅት በአንዳንድ ኢማሞች መሪነትና በተከታዮቻቸው አለሁ ባይነት ትርምሱ ይቀጥላል፡፡ ወይም የሰላማዊ ኢማሞችን ማይክሮፎኖች እየተነጠቁ ሰላማዊው አማኝ በስጋት ውስጥ ሊወድቅ፣ ወደዚያ መስጊድ መጥቶ በመስገዱ ሊቆጨው፣ በሌሎች ዳፋ ችግር ላይ የሚወድቅ ሊመስለው፣ ምዕራባውያን ጋዜጠኞች ደግሞ ስለኢትዮጵያ መልካም ገጽታ ማሳየት ይቸግራቸው እንደሆነ እንጅ ገንዘብ የሚያገኙበት እስከሆነ ድረስ «ተመስገን የሚበላበት ሥራ አገኘን» ብለው እያጋነኑ ያቀርቡታል፡፡

በሩቁ ያሉት ወገኖቻችን ደግሞ የአገራቸውን ውድቀት የሚመኙ ባይሆኑም ለሕዳሴዋ የቆሙ እየመሰላቸው በምዕራባውያን ቅኝት በተቃኘ የዴሞክራሲ ከበሮ እየደለቁ ስለተጣሰው ልቦለድ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይነግሩናል፡፡ ያንን ወርቃማ ጊዜአቸውን፣ ያንን ከፍተኛ ኃይል ያለውን የድምፅ ሞገዳቸውንና የሕትመት ውጤቶቻቸውን በጥላቻ ሳይሆን በፍቅር፣ በተቀናቃኝነት መንፈስ ሳይሆን በአንድነት መንፈስ፣ በአፍራሽ መልኩ ሳይሆን በገንቢ መልኩ፣ ኃይል በተሞላበት ስሜት ሳይሆን ብልህነት በተሞላበት ስሜት እየተመሩ በጎውን በጎ፣ ስህተቱን ደግሞ ስህተት ስለሆነ በዚህ መልኩ መታረም ይኖርበታል በሚል አንድ አስተማሪ ለተማሪው በሚነግረው መንገድ በመንገር ሲኖርባቸው መስደብ ለውጥ የሚያመጣ መስሏቸው ሁሉንም ድርጊት ማንቋሸሽ ያዘወትራሉ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል የራሳቸውን ባንዴራ ትተው በሰው አገር ባንዴራ ሥር ተንበርክከው በቅንነት እናገለግላለን ወይም ከዚያ ጋር የሚመሳሰል ተግባር በታማኝነት እንፈጽማለን ያሉና አገራቸውን ሁለተኛ አገር ያደረጉ ይገኙባቸዋል፡፡
በደረሰባቸው ኪሳራ ዳግም ወደ አገራቸው እንደማይመለሱ ተስፋ በመቁረጥም የአገርና የወገን ናፍቆታቸውን በመንግሥትና በሕዝብ ስድብ የቀየሩ አሉ፡፡ ለመሆኑ እንደዚህ ላሉ ሰዎች እንዴት አድርጎ ነው ስለአገር ፍቅር ማስተማር የሚቻለው? ወይም የበለጠ ግልጽ ይሆንላቸው እንደሆነ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ኦባማ ከተቀናቃኛቸው ጋር ሲከራከሩ «ማንኛውም ሰው የሚያስታውሰው ድልን ነው፡፡ ነገር ግን በመንገድ ላይ የሚያጋጥማቸውን እንቅፋት አያስታውሱም፡፡ ነገሮችን ካለፉ በኋላ ዘወር ብለን ስንመለከታቸው በጎ ይመስላሉ በመካከል ግን ሁሉንም ዓይነት ስህተቶች ፈጽመናል፡፡ ተሳስተናል፣ ተሞኝተናል፣ ተጃጅለናል፡፡ ነገር ግን የአሜሪካ ሕዝብ (ከዚህ ሁሉ ጋር) ወደፊት እንድንገፋ አድርጎናል፤» ያሉትን ማስረዳት የሚቻለው እንዴት ነው?

የቸገረውኮ «ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ» እንደሚባለው እየሆነ ነው፡፡ እስቲ ፍረዱ አንድ ለኩሊነት የሄደ ሰው ምንም ሳይማር የፖለቲካ ሊቅ ሆኖ የሚያስረዳው፣ የሚሟገተው፣ ስለአገራችን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች የሚነግረን እንዴት ነው? ይልቅ እየሸቀለ የሚያገኘውን ብር ቢልክ አይሻል? የሚባለውም «አኝከህ፣ አኝከህ ወደ ዘመዶችህ ዞረህ ዋጥ» ነው፡፡ የኛዎቹ «ግራ የገባቸው ግራዎች» በዚህ ረገድ ምን ያደርጋሉ? ይውጣሉ ወይስ ምን ያደርጋሉ?

ያም ሆነ ይህ የሚጠቅመን የኛው ጉዳይ በኛው መፍታት ስለሆነ ወደ ጉዳያችን፣ በተለይም ወደ ልዩነቶቻችንና መፍትሔዎቻቸው በድጋሚና በተደጋጋሚ እንሂድ፡፡ ለመሆኑ ዓይነተኛ ችግሮቻችን ምንድናቸው? ለጊዜው አንዱና ዋነኛው የአመለካከት ልዩነት ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ ጉዳይ በጥልቀት እንመልከተው፡፡

በኢስላም ሁሉም የአንድ ዓይነት እምነት ተከታይ እንዲሆን አልተፈቀደም
በመሠረቱ ቅዱስ ቁርዓን በተለያዩ ምዕራፎች «ተዋቸው፣ የተለያየ እምነት እንዲኖር ያደረግሁት እኔ ነኝ፣ አንተም እምነት አለህ እነርሱም አላቸው፣ የምቀጣቸው እኔ ነኝ፤» ይላል፡፡ ከዚህ መለኮታዊ አስተምህሮት በስተጀርባ ሌላ ተልዕኮ ከሌለ በስተቀር ሁሉም እኔን ካልመሰሉ አልተዋቸውም፤ እጨፈጭፋቸዋለሁ፤ አጠፋቸዋለሁ፤ ሰላማቸውን እነሳቸዋለሁ፤ ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት እምነት ይኖረው ዘንድ ዓላማዬ ነው፣ እኔም እርሱም በአንድ ዓይነት እምነት መመራት አለብን ማለት ሕገ ወጥነት ነው፡፡ እርግጥ ነው ክርስቲያኑም (ኦርቶዶክሱም፣ ካቶሊኩም፣ ወንጌላዊውም) ሁሉም ሰው ክርስቲያን ሆኖ ከፍርድ ቀን ቃጠሎ እንዲድን ሊመኝ ይችላል፡፡ በዚህ ረገድ የቡድሂስቱም፣ የዞሮአስተሩም፣ የታኦይስቱም፣ የይሁዲውም፣ ራዕይ በዚህ ዓይነት ምኞት ሊመራ ይችላል፡፡ ችግሩ ግን ከበጎ ምኞቱ ላይ አይደለም፡፡ ከራሱ በስተቀር ሌላውን ከመጥላቱ፣ የሌላውን ስም ከማጥፋቱ፣ ከሌላው የበለጠ ሐቀኛና ታማኝ መስሎ ከመታየቱ ላይ ነው፡፡

የአንዳንድ ሙስሊሞች አመለካከት ከዚህ አንጻር የተቃኘ ቢሆን የማይገርመውም ለዚህ ነው፡፡ ዳሩ ግን፣ ኢስላም ሁሉም ሰው አንድ ዓይነት እምነት እንዲከተል እንደማያስገድድ በብዙ የቁርዓንና የሐዲስ አንቀጾች ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ሁሉም አንድ ዓይነት እምነት እንዲከተል በማስገደድ ፈጽሞ ሊሳካ እንደማይችል ደግሞ ባለፈው አንድ ሺሕ ዓመት ታሪካችን ታይቷል፡፡ ኢስላም ማለት ሰላም መሆኑን የሚያምን፣ ባያምን ነገ በፍርድ ቀን ተጠያቂ እንደሆነ የሚያውቅ የሌሎችን የመኖር ሰላም ሊያደፈርስም ሆነ ሊነካ አይችልም፡፡ አይገባም፡፡ በመሬትም በሰማይ ቤትም አደጋም አለው፡፡ በአገር ልማት ላይ በጎ አስተዋጽኦ የሚያበረክተውን ትውልድንም በጠማማ አቅጣጫ በመውሰድ አምራች፣ ፈጣሪ፣ ተማሪና ተመራማሪ እንዳይሆን ያደርጋል፡፡

ወጣቶች ወጣቶች በመሆናቸው ወይም ባለማወቃቸው ወይም የሌሎች መሠሪ ኃይሎች ሳያውቁ መሣሪያ በመሆናቸው ወይም በባህሪያቸው ለውጥ ፈላጊ በመሆናቸው ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ በሕይወታቸው ስህተት በመፈጸማቸው ምክንያት ግን መጥላት ወይም በጥቅሉ መፍረድ ግን ኢስላማዊ አይደለም፡፡ ኢስላማዊው መንገድ ማስተማር፣ መውደድ፣ ማፍቀር፣ አፍቃሪ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ በአሉታዊ አመለካከት እንዳይሞሉ መከላከል ነው፡፡ ወደ ኢስላም የበለጠ እንዲሳቡ ማገዝ ነው፡፡ ለመሆኑ በስድብ፣ በትችት፣ በጥላቻ፣ በማራቅ፣ በአሉባልታ፣ በሀኬት ወደ በጎ ተግባር የተሳበው የትኛው ነው? ስለሆነም ስህተት መፈጸም ያለ ስለሆነ ስህተቱን ለማባባስ ከመሞከር ይልቅ ለማረም መጣር ያስፈልጋል፡፡

እዚህ ላይ ኢትዮ-ተርክሽ ትምህርት ቤት አምና ግንቦት 20 ቀን 2004 በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ በተካሄደው ጉባኤ ዓብዱላህ ቲ አንቴፒ የተባሉ ምሁር ኢስላምንና መቻቻልን በሚመለከት ያደረጉትን ንግግር መጥቀስ የሚያስፈልግ ይሆናል፡፡ እኚህ ምሁር እንዳሉት «ብዙ የቁርዓን አንቀጾችም ፍትሕንና ሰላምን በሚመለከት በውስጣቸው አካተዋል፡፡ ሁለቱም ዛሬ ዘመናዊ ሕጋዊ ሥርዓት የሚከተለውን (ፍትሕና ሰላም) ሕይወትን፣ ሀብትን (ካፒታልን)፣ ማባዛትን (ማፍራትና ማራባትን) ለመጠበቅ አሠራር ባህርይ ያለባቸው ናቸው፡፡ «እናንተ ያመናችሁ ሆይ! ለአላህ ቀጥተኞች በትክክል መስካሪዎች ሁኑ፡፡ ሕዝቦችንም መጥላት ባለማስተካከል ላይ አይገፋፋችሁ፣ አስተካክሉ፣ እርሱ (ማስተካከል) ለአላህ ፍራቻ በጣም የቀረበ ነው፡፡ አላህንም ፍሩ፡፡ አላህ በምትሠሩት ሁሉ ውስጥ አዋቂ ነው፡፡» ቁርዓን (5፡8) ፣በማለት (መልካም ነገር እንድንሠራ፣ ሌሎች የሚጠቀሙበትን የጥላቻ መንገድ እኛ ተከትለነው በመሄድ ወደ ስህተት ስተት ብለን እንዳንገባና ከፍትህ መንገድ እንዳንርቅ ያዘናል፡፡ ትክክለኛ (ፍትሐዊ መሆን)  ከቅዱስነት ቀጥሎ የሚገኝ መሆኑንም ይመክረናል) (ቁርዓን 5፡8) አንድ ሰው ሌላውን ሰው፣ ካልገደለ ወይም በመሬት ላይ አስጸያፊ ተግባር ካልፈጸመ በስተቀር፣ ሁሉንም ሕዝብ እንደቆጠረ «በዚህም ምክንያት በእስራኤል ልጆች ላይ እነሆ ያለ ነፍስ (መግደል) ወይም በምድር ላይ ያለማጥፋት፤ ነፍስን የገደለ ሰው ሰዎቹን ሁሉ እንደገደለ ነው፡፡…» በሚል ሰፍሯል፡፡ (ቁርዓን 5፡32) ጠላት ወደ ሰላም ካዘነበለ እናንተም ወደሱ አዘንብሉ፤ አላህን እመኑ እርሱም ሁሉንም አዋቂና ሁሉንም ሰሚ ነውና (ቁርዓን 8፡61) ::  እናንተ ያመናችሁ ሆይ!  ሁላችሁም በመታዘዝ ውስጥ ግቡ፤ የሰይጣንንም እርምጃ አትከተሉ፤ እርሱ ለእናንተ ግልጽ ጠላት ነውና (ቅዱስ ቁርዓን 2፡208) በማለት በሙሉ ልብ ወደ ሰላም እንድንገባና ጠላታችን የሆነው ሰይጣን እግር ተከትለን እንዳንሄድ ያስጠነቅቀናል፡፡

«በሐዲስ ውስጥም ነቢዩ ሙሐመድ «ሙስሊሞች ማለት ሌሎቹ ከምላሳቸውም ሆነ ከእጃቸው ጥቃት የሚጠብቁ ናቸው» በማለት አንድ ሙስሊም በምላሱም ሆነ በእጁ እንዳያደርስበት ያስገነዝባሉ፡፡ በሌላ አነጋገር ሌሎቹን ከምላሳቸውም ሆነ ከእጃቸው ጥቃት ጥበቃ የማይከላከሉና ለሌሎች የማይታመኑ ከሆኑ ሙስሊም ለመሆናቸው ራሳቸውን እንደገና መጠየቅ ይኖርባቸዋል ማለት ነው፡፡ በሌላ ሐዲስ እንደተጠቀሰውም ነብዩ ሙሐመድ «ከሙስሊም ድርጊቶች ሁሉ የላቀው የቱ ነው?» ተብለው ሲጠየቁ  «ሲበሉ ሌሎቹን ከነሱ ጋር እንዲበሉ የሚጋብዙ፣ እና ፍጽም አግኝተዋቸው የማያውቋቸው ቢሆንም እንኳን ሰላም የሚሉ ናቸው» በማለት መልሰዋል፡፡ (ኢማም ቡኻሪ 4፣5/ኢማም ሙስሊም 64፣65) ይህም የነብዩ ሙሐመድ መልስ ከዚህ ከምንወያይበት አርዕስተ ጉዳይ ጋር እንደሚስማማ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

«በኢስላማዊ ታሪክ ላይ ምርምር የሚያደርጉ ሙስሊሞች፣ በጠቅላላው፣ የሰላምና የታማኝነት ተወካይ ሆነው ያገኟቸዋል፡፡ ስለሆነም ኢስላምን ከአመጽና ከሽብር ጋር ለማያያዝ መሞከር በእኔ ግንዛቤ ሐቅን ማፋለስና ፍትሕ አልባ መሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ታሪክ የማይረሳው ከፍተኛ አለማወቅ ነው፡፡

«ስለሆነም አንድ ሰው በሙሉ ልብ በማንኛውም መለኪያ ቢታይ ፍትሐዊ የማይሆን የኃይልና የተስፋፊነት እርምጃ በኢስላማዊ ዘርፍ መሥራቾች ተካሂዷል፡፡ በዚህ ረገድ ማንኛውም ሰው ወይም ፓርቲ ወይም መንግሥት እንደዚህ ያለውን ድርጊት ከፈጸመ ሙስሊም አይደለም፡፡ ሙስሊምም እንዲህ ያለውን ድርጊት አይፈጽምም፡፡  ትክክለኛ የሆኑ መረጃዎችን ለሚያጠናም ኢስላምና ጸብጫሪነት ወይም በቂ ምክንያት የሌለው አመጽ እንደ ጥቁርና ነጭ ወይም እንደ ክረምትና በጋ የተለዩ ናቸው፡፡» በማለት አቅርበው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ለመሆኑ ይህ አመለካከት በኅብረተሰቡ እንዲሰርጽ ምን ያህል ጥረት ተደረገ? በተለይም የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በራሳቸው ስሜት እየተመሩ ሳይሆን በሙስሊም ሊቃውንት በመታገዝ ለመሥራት ምን ያህል ጥረት አድርገዋል፡፡ ስለሆነም ወደፊት ምን ይደረግ?

ኢትዮጵያዊ ችግሮቻችንን በኢትዮጵያ ዓይን እያየን እንፍታ
ኢትዮጵያ አገራችን በርካታ ችግሮች አሉባት፡፡  አንዱና ለዕድገት ጸር ሆኖ የቆየው ችግር ግን «ችግርን በእኔ መንገድ እንፍታ» የሚለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንዶቹ ሃይማኖቶች ለመንግሥት ከሌሎች የቀረቡ እነርሱ ራሳቸው መሆናቸውን ለማሳየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ አንዳንድ ጊዜም ተልዕኳቸው መለኮታዊ ሳይሆን ዓለማዊ፣ ነፍሳዊ ሳይሆን ሥጋዊ ሆኖ የሚታይበት ሁኔታ አለ፡፡ የመንግሥት ሹመት እያጓጓቸው መለኮታዊ ሹመቱን ይረሱታል፡፡ መለኮታዊውን የፍቅር ቃል በዓለማዊ ጥላቻ ያጠቁሩታል፡፡ ሐሜት፣ አሉባልታ፣ ምቀኝነት፣ ሸረኝነት፣ ተንኮለኛነት፣ ሆዳምነት ይፈታተናቸዋል፡፡ ነገሮችን በኢትዮጵያ ዓይን ማየት ሲገባቸው በራሳቸው ስግብግብ ፍላጎት እያዩ አገርና ወገንን የሚጎዳ ተግባር ይፈጽማሉ፡፡ ለአላፊ ጠፊ መናኛ ጥቅም ብለው የዘላለም ቤታቸውን ይንዳሉ፡፡
ታማኝነታቸውን ያፈርሳሉ፡፡ የሚበላ ነገር ተከትሎ ወደማረጃ ቦታው ሰተት ብሎ እንደሚገባ አሳማ በግል ጥቅም ተገዝተው ወደ አስፈላጊ ያልሆነ መስመር ጥልቅ ብለው ይገባሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም መለኮታዊ ቃላትን እያጣመሙ ለራሳቸው አርቲቡርቲ እኩይ ዓላማ ያውሏቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንድ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን እንዲሁም ዋቢ ያደረጓቸውን ማየት ይቻላል፡፡

ለማንኛውም ወደሌሎቹ አንገታችንን ቀና ከማድረጋችን በፊት በሙስሊሙ መካከል ያለውን ችግር እንመልከት፡፡ እንደሚታወቀው በሙስሊሙ ኅብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ አመለካከቶች በአንድ ላይ ሰብሰብ ብለው ሲታዩ ኢስላማዊ አመለካከቶች እንጅ ሌላ አይደሉም፡፡ በዚህም መሠረት ማለት አይቀርምና ሁሉም በየበኩላቸው የሙስሊሙን ኅብረተሰብ አንድነት ይሻሉ፡፡ ሁሉም ለሙስሊሙ ኅብረተሰብ አንድነት ይሰብካሉ፡፡ ሁሉም በአንዱ ሙስሊም ኅብረተሰብ ላይ የሚደርስ በደል ቢኖር ያወግዛሉ፡፡ ነገር ግን «ድር ቢያብር አንበሳ ያስር እንዲሉ አንድ እንሁን» ሲባሉ «አዎን አንድ መሆን ጥሩ ነው፤ ነገር ግን አንድ መሆን የምንችለው በእኔ መንገድ መሆን አለበት፤» ብለው እርፍ ይላሉ፡፡ አንዳንዶቹም ይህን የሚያደርጉት «ውርድ ከራሴ በበኩሌ ሞክሪያለሁ» በማለት ከደምስራቸው የቀረበ ፈጣሪያቸውን ለማሞኘት፣ ለመሸንገል፣ ለመደለልና የለበጣ ተግባር ለመፈጸም የሚሞክሩ ይመስላሉ፡፡ በዚህ ምክንያት በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሩቅ ምሥራቅና በሌሎቹም ቦታዎች የደረሰው ጥፋት እንዲህ በዋዛ የሚገለጥ አይደለም፡፡

በመሠረቱ በአገራችን ይህን ያህል የሚጋነን ልዩነት የለም፡፡ ቢበዛ ሦስት ወይም አራት ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ግን ክፍፍሉ በመቶዎች ይቆጠራል፡፡ ከሁሉ አስቀድመን፣ ይህን በአገራችን ላይ ቢሆንስ ብለን እናስብ፡፡ «የማን ቤት ጠፍቶ የማን ሊበጅ፤ ያውሬ መፈንጫ ይሆናል እንጅ» የሚያስብል እንደሚሆን አያጠያይቅም፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ ከአሁኑ በቂ ዝግጅት ካላደረግን በስተቀር የአገራችን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በከፍተኛ ፍጥነት በተራመደ ቁጥር ኢስላማዊ አስተምህሮቱም በዚያ መጠን እያደገ እንደሚሄድ አያጠያይቅም፡፡ ምን ይደረግ? የኢኮኖሚ ልማት ብቻውን አይመጣማ! ብዙ አጀቦችና አጃቢዎች አሉታ! በከፍተኛ የዕድገት ሒደት ባለ አገር ሌላ ነገር (ሃይማኖት፣ ባህል፣ ልምድ ወዘተ) አብሮ እንዳይገባ በርን ጠርቅሞ መዝጋት አይቻልማ! ስለዚህም እንደግሪክ ኦርቶዶክስ፣ እንደአርመን ኦርቶዶክስ፣ ወይም ቁጥራቸው እስካሁን ከ30 በላይ እንደደረሱት ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የሱኒ፣ የሰለፊ፣ የሺዓ፣ የሙዕተዚላይት፣ የሱፊ፣ አህሉል ሱና ወል ጀምዓ፣ አሽዓሪ፣ ራፊዒያ፣ ኢማምያ፣ ራሺዲያ፣ ሙከረሚያ፣ ሙርጂዒያ ወዘተ የተባሉና ሌሎች ዘርፎች መስጊዶችና መድረሳዎች የማይከፈቱበት ምክንያት የለማ! ስለሆነም የሚሻለውና የኛ ጥሩ ነው ብለን የምናስብ ከሆነ ልጆቻችን በማስተማር ለዚህ ሁሉ ራስን ማዘጋጀት ነው፡፡

ከነፃ ኢኮኖሚ ጋር አብሮ የሚመጣው ነፃ አመለካከት፣ ነፃ አስተሳሰብና ነፃ እምነት አስቀድሞ የተረዳው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት አንቀጽ 11 መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን በግልጽ አስቀምጦታል፡፡ በዚሁ አንቀጽ በንዑስ አንቀጽ አንድም መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል፡፡ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ደግሞ የመንግሥት ሃይማኖት የለም ይላል፡፡ ንዑስ አንቀጽ ሦስት መንግሥት በሃይማኖቶች ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ ይገልጻል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 27 ደግሞ የሃይማኖት፣ የእምነትና የአስተሳሰብ ነጻነት እንደተረጋገጠ ያመለክታል፡፡ የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ አንድ እያንዳንዱ የሐሳብ ነፃነት፣ የሕሊና ነፃነትና የሃይማኖት ነፃነት እንዳለው አስቀምጧል፡፡ ይህ መብት የመረጠውን  ሃይማኖት ወይም እምነት መያዝን ወይም ተቀብሎ በሚያመቸው መንገድ ማሳደግን፤ ቢፈልግ ብቻውን፣ ወይም ከሌሎች ጋር ማኅበረሰብ ሆኖ፣ ሕዝብ በተሰበሰበበት፣ ወይም በግል ማካሄድን፤ ሃይማኖቱን በይፋ በማሳወቅ ወይም በልቦናው በማመን፣ ስብከቱ በሚካሄድበት ቦታ በመካፈል፣ በማዘውተርና በማስተማር መተግበርን ያካትታል፡፡ ንዑስ አንቀጽ ሁለትም በአንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ ሁለት መሠረት የተጠቀሰውን ሳይተላለፉ፣ አማኞች እምነታቸውን ለማስፋፋትና ለማደራጀት ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤቶች፣ አስተዳደሮች ማቋቋም እንደሚችሉ ያወሳል፡፡ ንዑስ አንቀጽ ሦስትም አማኙ የመረጠውን እምነት እንዳይዝ ሊያግደው ወይም ወይም በሌላ መንገድ ሊከለክለው እንደማይችል ይናገራል፡፡ ንዑስ ምዕራፍ አምስት ወይም ሃይማኖትን ወይም እምነትን የመግለጽ ነጻነት የሚገደበው ሕጋዊና አስፈላጊ ነው ተብሎ በሕግ   በተደነገገው መሠረት የሕዝብ ደህንነትን፣ ሰላምን፣ ትምህርትን፣ የሕዝብ ሞራልን፣ መሠረታዊ መብቶችን፣ የሌሎች ነፃነትን፣ የመንግሥት ከሃይማኖት ነፃ መሆንን የሚጻረር ከሆነ ነው፡፡ አንቀጽ 90 ንዑስ አንቀጽ ሁለት ትምህርት ከሃይማኖታዊ፣ ከፖለቲካዊ ቡድኖች (ፓርቲዎች)፣ ከትምክህተኛ የባህል ተጽዕኖ ነፃ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

የእኩልነት መብትን የሚያረጋግጠው አንቀጽ 25፣ ሁሉም ሰው በሕግ ፊት እኩል ሲሆን ያለአንዳች ልዩነት የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል በማለት ያስቀምጣል፡፡ በዚህ ረገድ፣ ሕጉ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ ወይም በተገኘበት ማኅበረሰብ፣ በቀለም፣ በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከት፣ በሀብት፣ ከሌላ አገር በመወለድ በትውልድ ሳይለይ ለሁሉም ሰው ሕግ የተጠበቀ እንደሆነ ያረጋግጣል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ይህን የሚል ከሆነ ዜጎች ደግሞ ሕገመንግሥቱንና ሕጎቹን አክብረው መኖር አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ከሆነ «ሕገወጥ» ይሆናል፡፡ በሕጉ ይጠየቃል፡፡ በሕጉም ይዳኛል፡፡ ሕጉ በአገሪቱ ሕግና ደንብ የሚቃኝ ስለሆነ አሜሪካዊ ወይም እንግሊዛዊ፣ ወይም ዓረባዊ፣ ወይም ሌላ መሆን ከቶ አያስፈልገውም፡፡ ማንም አገርም፣ ወይም ዜጋ እንዲህ አድርጉ ብሎ አይነግረንም፡፡ የሚነግረን፣ የሚያስገድደን፣ እንደፈለገ የሚያደርገን ሕዝቦችም ልንሆን አይገባም፡፡ ይህች አገርኮ ማንም የሚያስገድዳት አለመሆኗን ደጋግማ ያረጋገጠች፣ ለማረጋገጥም ሀብቷን፣ ጥሪቷን፣ ሥልጣኔዋንም ጭምር መስዋዕት ያደረገች አገር ናት፡፡

የችግራችን ጥልቅ ምሥጢሩ ምንድን ነው?
አንድ ዓይነት ሃይማኖት፣ አንድ ዓይነት ቋንቋ፣ አንድ ዓይነት ምንትስ እንደማያዋጣ የተገነዘበው ኢሕዴግ የሕዝቦች እኩልነትን የሚያረጋግጥ ሕገመንግሥት አውጥቷል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥትም የሚሻሻል ከሆነ የሚሻሻለው በሕዝቡ ነው፡፡ በማን አለብኝነት መደፍረስ፣ መነካካት፣ መበላሸት፣ መበስበስ፣ መሻገት የሌለበትም ለዚህ ነው፡፡ የዛሬ አስርና አሥራ አምስት ዓመት ለኢሕአዴግ ክርስትናም፣ እስልምናም፣ አይሁድነትም የግለሰብ እምነቶች እንጅ የዲሞክራሲ፣ የሰላም፣ የልማት እንከኖች አልነበሩም፡፡ ከኢሕአዴግ ጎን የተሰለፈውም ሃይማኖት፣ ጎሳ፣ ዘር ለይቶ አልነበረም፡፡ እውነትን በእውነት እንጅ እውነትን ከውሸት ለማግኘት ጥረት ይደረግ እንዳልነበረም ይታወቃል፡፡ «ኢሕአዴጎች ነገራቸው ግልጥ ነው፡፡ አንድ ነገር ምስጢር ነው ብለህ ስለአንድ ሰው ብትነግራቸው ከሰውየው ፊት ለፊት ያጋጥሙሃል» የሚል መልካም እሴት ነበራቸው፡፡ በዚህ ረገድ ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከማንኛውም መንግሥት በላይ ድጋፉን ሰጥቷቸዋል፡፡ አግዟቸዋል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስና የትግል ጓደኞቻቸው በእስልምና ላይ የነበራቸው አመለካከት በአዎንታዊነት የተሞላውም በውስጣቸው አሉታዊ አመለካከት የሚያራምድ ስላልነበረ ሳይሆን አቋማቸው በሕዝባዊ መሠረት የታነጸ ስለነበር ነው፡፡

በመሠረቱ ከአምስት ዓመት በፊት በነበሩት የአገር ውስጥ ጉዳይ አመራሮች እንዲህ ያለው የሃይማኖት ትርምስ አልታየም፡፡ ከዚያ በፊትም እንደዚሁ፡፡ አሁን ግን አለ ለምን? ምናልባት ችግራችንን ውጫዊ ልናደርገው ይሆን? ነገር ግን ውስጣዊ እንጅ ውጫዊ ተጽዕኖ አንበርክኮን እንደማያውቅ የምንሞግት ከሆነ ዛሬ ችግሩ የመነጨው ከውስጣችን መሆኑን መቀበል ይኖርብናል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የሚያቀርበው ሐሳብ ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን «በእርግጥም የዕውቀትም፣ የችሎታም፣ የአቅምም፣ የቅንብርም ችግር ይኖር እንደሆነ ጓዳን መፈተሸ ብልህነት ነው፡፡ የሚቀርብ ጥናት ሁሉ፣ የሚቀርብ ሪፖርት ሁሉ እውነት ነው ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም የፈረንጆች ምክሮች፣ አስተያየቶችና ሥልጠናዎች ከአገራቸው እንጅ ከአገራችን አንጻር ያልተቃኙ ከሆኑ የሚያስከትሉት መዘዝ ቀላል ላይሆን ይችላል፡፡ መረዳት ያለብን ፈረንጆች ምንጊዜም በማንኛውም መንገድ ይቅረቡ የሚያስቀድሙት የራሳቸውን ጥቅም መሆኑን ነው፡፡ ልማታችንን በማፋጠን በአፍሪካና በተቀረው ዓለም የተሻልን ሁነን እንዳንገኝ ርስ በርስ እንድንራኮት የሞት ሽረት ትግል የሚያደርግ ኃይል ጓዳችን ውስጥ ገብቶበት እንደሆነም መፈተሽ ሊኖርብን ይችላል፡፡ የአንድ ብልህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓይነተኛ ሥራ ደግሞ ቤቱን መፈተሽ፣ ለውጥ የሚያስፈልገው ከሆነ መለወጥ ነው፡፡

ማጠናከር የሚያስፈልገውንም ማጠናከር ይገባል፤» ብሎ አስተያየት ከመስጠት የሚከለክለው ኃይል የለም፡፡  ያለ አንዳች ጥርጥር ባለሥልጣኖቹ ገንቢ ሐሳብ ሲቀርብላቸው «እኛ የምናደርገውን እናውቃለን፤ እናንተ ደግሞ አርፋችሁ ተቀመጡ» የሚሉ ዓይነት መሆናቸውንና አለመሆናቸውን መፈተሽ አለበት፡፡ ሕውከት የሚያስከትለው እንደዚህ ያለው በእብሪት የተሞላ አስተሳሰብ ነውና! አንድ ችግር «እንደህ ግሞ ግሞ የተቃጠለ እንደሆን» ለማቀዝቀዝ፣ ለማብረድ፣ ለማጥፋት፣ መሞከር አስቸጋሪ ነው፡፡

ማጠቃለያ
ችግሮቻችንን አንስተን ውለን አንስተን ብናድር ብዙዎች ናቸውና ማለቂያ የላቸውም፡፡ ይህም ሆኖ አዲስ የተመረጠው መጅሊስ ራሱን በማጠናከርና በማደራጀት በምድር ሰዎች በሰላም፣ በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመተሳሰብ፣ አብሮ ለመኖር እንዲችሉ፣ በሰማይ ደግሞ ወደ ዘላለማዊ እሳት እንዳይገቡ ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ማዳን ነው፡፡ ይህን ሁለት ስለት ያለው ሥልጣን በአግባቡ ለመወጣት ይችል ዘንድ የጀመረው የምክክር አካል የማቋቋምና የማደራጀት ሥራ ጠንክሮ እንዲቀጥልበት መሠረቱ ጥልቀት ያለው እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ዋናው መሠረታዊ ጉዳይ ሙስሊሙም ሌሎችን ሳይቃረን፣ ሌላውም ሙስሊሙን ሳይቃረን በሰላም ለመኖር ከመቻሉ ላይ ስለሆነ ውጥኑን ከዳር ለማድረስ የሌት ተቀን ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ ይልቁንም «እስላም ጠላ ሆዴ» ብለው ለተነሱ ኃይሎች እንከን የለሽ የሰላም መንገድ መሆኑን ለማሳየት መጣር አለበት፡፡

ከዚህም ሁሉ በላይ መንግሥትና የመንግሥት ተቋማት በተለይም መገናኛ ብዙሃንና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች ግንባር ቀደም ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ጉዳይ በጥንቃቄ መያዝ ያለበት መሆኑን ከዘነጋና አንዳንድ ችግሮችን አስወግዳለሁ ብሎ አያያዙን ካላወቀበት፣ የሃይማኖት ተቋማት በፈጣሪ መልዕክት በትክክል መመራት ትተው የግል ስሜታቸውና ፍላጎታቸው የሚያሸንፋቸው ከሆነ፣ የአገር ሽማግሌዎች ችግሩን እያዩ እንዳላዩ የሚያልፉት ከሆነ አደገኛ ነው፡፡ አደጋውንም ከኢትዮጵያ የረዥም ዓመታት ጦርነት ታሪክ፣ በጦርነቱም ከወደቀው ሥልጣኔያችን የበለጠ መረጃ ከቶ ሊኖር አይችልም፡፡ ስለሆነም ነገሩ «የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች» እንደሚባለው እንዳይሆንም ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡

**************

* Originally published on the Ethiopian Reporter, on March 10, 2013, titled “መጅሊሱ እንዴት ሰነበተ?”, authored by Teshome Berhanu Kemal ([email protected])

Daniel Berhane

more recommended stories