ኣቶ መለስ ከሞቱ ኣራት ወር ሆኗቸዋል፡፡ የኣቶ መለስን እረፍት ተከትሎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የታየው ለውጥና የኣቶ መለስ ኣመራር ትሩፋቶች (legacies) ምን ይመስላሉ? ኣቶ መለስ በድርጅታቸው በኢህኣዴግና በመንግስት ጉዳዮች ላይ የነበራቸው ሚና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሄዱ ካለፉት ጥቂት ኣመታት ወዲህ በህዝቡ ዘንድ ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግስት የኣንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ ናቸው የሚል ኣመለካከት እንዲሰርፅ ኣድርጓል፡፡ ይሄ ኣመለካከት ለብዙዎች በተቃዋሚነት ጎራ የተሰለፉ ወገኖች የኢህኣዴግ ጥንካሬ የኣቶ መለስ ጥንካሬ ነው፣ ኣቶ መለስ የኢህኣዴግን የመሪነት ቦታ የለቀቁ ቀን የድርጅታቸው ጥንካሬ ኣብሮ ያበቃል የሚል የተሳሳተ እምነት የነበራቸው ሲሆን ቀላል የማይባሉ የኢህኣዴግ ደጋፊዎችም ተመሳሳይ ኣስተያየትና ስጋት ሲታይባቸው ነበር፡፡ ኣቶ መለስ ታመዋል በተባለ ጊዜም በሁለቱም ጎራዎች የታየው ይሄው የተቃዋሚዎች ተስፋና የደጋፊዎች እልህ የተቀላቀለበት ስጋት ነው፡፡ እናስ የኣቶ መለስን ሞት ተከትሎ ምን ክስተቶች ተፈጠሩ?

የህዝቡ ስሜትና የኢህኣዴግ ምላሽ

የኣቶ መለስ ሞት ደስታ የፈጠረባቸው ዜጎች የሉም ለማለት ቢከብድም ኣብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶት ሃዘኑንና ለመሪው የነበረው ኣድናቆትና ክብር ገልጧል፡፡ ኣንዳንድ በውጪ የሚገኙ የተቃዋሚ ሚድያዎች ህዝቡ ሃዘኑን የገለፀው ተገዶ ኣሊያም ተከፍሎት ነው ቢሉም ኢትዮጵያ ውስጥ ለነበረና ሁኔታውን በቅርበት ለተከታተለ ሰው እውነታው ሌላ ነው፡፡ ማንም ሊጠብቀው ባልቻለ ሁኔታ የኣቶ መለስ ሞት ታላቅ ሃዘንና ቁጭትን ፈጥሯል፡፡ በርግጥ ኣንዳንድ ቦታዎች ላይ ኣንዳንድ ኣስመሳይና ኣድርባይ የኢህኣዴግ ካድሬዎች ህዝቡ ላይ ከውስጥ ፈንቅሎ የወጣውን ሃዘንና ቁጭት እንደ የራሳቸው የፕሮፐጋንዳ ውጤት ኣስመስለው ከሌሎች ቦታዎች/ካድሬዎች የተሻሉ የህዝብ ንቅናቄ የፈጠሩ መስለው ለመታየት ሞክረዋል፡፡ ይሄ ተግባራቸውም ድርጅታቸውን ይጎዳው እንደሆነ እንጂ የተረፈው ፋይዳ ኣልነበረም፡፡ ለምሳሌ በኣንዳንድ መስሪያ ቤቶች (ዩኒቨርሲቲዎችም ጭምር) ሃዘኑን ኣስመልክቶ ሲለጠፉ የነበሩ ማስታወቂያዎች በራሱ ፈቃድ ከውስጡ ሲያዝን ለነበረ ሰው ተጨማሪ ንዴትን የፈጠሩ ሲሆን በውጪ ኣገር ሆነው ህዝቡ ለለቅሶ የወጣው በግድ ነው ሲሉ የነበሩት የኢትዮጵያ የተቃውሞ ሚድያዎች እንደ ማስረጃ ተጠቅመውባቸዋል፡፡

በርግጥ በመጀመርያዎቹ ጥቂት ቀናት ኢህኣዴግም የህዝቡ ሃዘንና ቁጭት ከጠበቀው በላይ የሆነበት ይመስላል፡፡ የዚህ ስሜት መገለጫዎችም ለምሳሌ ከታሰበው ጊዜ በላይ የተራዘመ የሃዘን ጊዜ እንዲኖር የተደረገ ሲሆን ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስቴር ለመምረጥ/ለመመመደብ/ለማሳወቅ ከተገለፀበት ጊዜ እንዲራዘምና ሃዘኑ ላይ ትኩረት እንዲሰጥበት መደረጉ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ በመንግስት ሚድያዎችና በባለስልጣናት ስለ ኣቶ መለስና መንግስታቸው ላይ ስለለነበራቸው ሚና/ተፅእኖ ይነገር የነበረው ነው፡፡ ኣንዳንድ ሰዎችም “ይሄ ሁሉ ስራ ጠ/ሚኒስትሩ ብቻቸውን ይሰሩት ከነበረ ሌሎቹ ባለስልጣናት ምን ይሰሩ ነበር? ኣሁንስ ከሳቸው ውጪ ይሰሩታል ወይ?” እስከማለት ደርሰዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ መጨረሻው ህዝቡ ላይ የነበረው የሃዘን ስሜትና ቁጭት ኢህኣዴግ የድርጅቱን ተቀባይነት ለማደስና መንግስት የነደፋቸው “የልማትና ትራንስፎርሜሽን እቅዶችን” ለማሳካት ተጨማሪ ሞቅታና ንቅናቄ እንዲፈጠር ኣቅጣጫ ኣስቀምጦ እየሄደበት ይመስላል፡፡ ለዚህም በየሚድያውና በየስብሰባው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሚናና ራእይ በማጉላት ከሁለት ኣመት በላይ እንደ መፎክር ሲገለፅ የነበረው “የኣምስት ኣመት የልማትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ እናሳካለን” የሚለውን ኣባባል የተካ እስኪመስል ድረስ “የመለስን ራእይ እናሳካለን” ወደሚል ተቀይሮ ህዝቡና የድርጅቱ ኣባላት ትኩረታቸው እዛ ላይ እንዲሆን ኣድርጓል፡፡

ኣንዳንድ የኢህኣዴግን የውስጥ ፖለቲካ ያልተረዱ የፖለቲካ ተንታኞች ኣቶ መለስ ታመው በነበረበት ወቅትና ከሞቱ በኋላ ሲገልፁት የነበረው ያለ ኣቶ መለስ ኢህኣዴግ ጥንካሬ እንደማይኖረው፣ኢህኣዴግን በመሰረቱ ኣራቱ ድርጅቶች የስልጣን ሽኩቻ እንደሚፈጠር ወይም እንደተፈጠረ፣ ኣገሪቱ የሰላምና መረጋጋት ኣደጋ እንደሚጋረጡባት …. ወዘተ ወዘተ ቢተነትኑም ተፈጠሩ የተባሉት የኣመራር ክፍተትና የስልጣን ሽኩቻ ኣገር ውስጥ በሚኖር ህዝብ ላይ የፈጠሩት ተፅእኖም ስጋትም ኣልታየም፡፡ እንዲያውም በስተመጨረሻ ኣንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶችና ተንታኞች ከጠበቁት በተላቢጦሽ ኢህኣዴግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ህዝቡ ላይ የተፈጠረውን ሃዘንና ቁጭት ኣሁን ኢህኣዴግ እያካሄደባቸው ባሉ የልማትና የፖለቲካ እንቀስቃሴዎች ላይ ንቅናቄዎችን ለመፍጠር ተጠቅሞበታል፡፡ በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ሁኔታም ሰላማዊ የመሪ መተካት ስራ ሰርቷል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ይህ ሽግግር ለመጀመሪያ ጊዜ የኣገሪቱ የመሪነት ቦታ ከደቡባዊው የሃገሪቷ ክፍል በፈለቁ ፖለቲከኛ እንዲያዝ ሆኗል – ይህ በራሱ ታሪካዊ ነው፡፡

የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች ምላሽ

ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ሁለት ኣስርት ኣመታት ተቃዋሚች ነን የሚሉ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ሲቋቋሙና ሲፈርሱ ብናይም ለሃገሪቱ ፖለቲካ በበጎ መልኩ ያበረከቱት ኣንዳች ኣስተዋፅኦ የለም፡፡ በሃገሪቱ ፋይዳ ያለው የተቃዋሚ ድርጅት እንዳይኖር ያደረገው ኢህኣዴግ ነው የሚል ወቀሳ የሚሰነዝሩ ሰዎች ቢኖሩም በኔ እምነት ኢህኣዴግና የህዝቡ የፖለቲካ ኣስተሳሰብ የራሳቸው የሆነ ሚና ቢኖራቸዉም ትልቁ ጉድለት የራሳቸው የተቃዋሚዎች ድክመት ነው፡፡ በተግባር እንዳየነው ኣብዛኞቹ ድርጅቶች በውስጣቸው ዲሞክራሲያዊ ኣስተሳሰብ ሳይኖራቸው፣ በግለሰቦች ኣምባገነንነት ታፍነው ሲሞቱ ሎሎች ደግሞ የህዝቡን ታሪክ ኣኗኗርና የፖለቲካ ኣስተሳሰብ ያገናዘበ የፖለቲካ ፕሮግራም መቅረፅ ተስኗቸው በራሳቸው ጊዜ የከሰሙ ናቸው፡፡ በኣንፃሩም ጥቂት ድርጅቶች ቀና ኣስተሳሰብና መጠነኛ ፕሮግራም ይዘው ባለው የፖለቲካ ሜዳ ለመጫወት ቢሞክሩም ሃሳባቸውን የሚረዳቸው ጠፍቶ ኣሊያም በቂ ጉልበትና ወኔ ኣጥተው ከሞቱት በላይ ካሉት በታች ሆነው እየቀጠሉ ያሉ ድርጅቶች ኣሉ፡፡ በኣጠቃላይ ትርጉም ያለው የፖለቲካ ፕሮግራምና ኣደረጃጀት ይዞ ህዝቡ ዘንድ እስከ ገጠር ድረስ ሰርፆ ገብቶ ተቀባይነት ያገኘ የተቃዋሚ ድርጅት ስላልነበረ የኣቶ መለስን ሞት ተከትሎ ትርጉም ያለው ስራ ይሰራሉ ብሎ መጠበቅ ኣይቻልም ነበር፡፡ በመሆኑም ባለፉት ወራት እንደ ሁልጊዜው በሚድያ የሚነሱ ጉዳዮች ላይ ብቅ እያሉ የውግዘት መግለጫ ከማውጣት ያለፈ የሰሩት ስራ የለም፡፡ ሰሞኑም የተለመደው የምርጫ ጊዜ ጩከታቸውን እያሰሙ ነው፡፡

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ገብተው ህዝቡን ኣሳምነው የፖለቲካ ድጋፍ ማግኘትና በኢትዮጵያ ኣጠቃላይ የፖለቲካና የኣስተዳደር ለውጥ ማምጣት ያቃታቸው እነዚህ ተቃዋሚዎች እስከመጨረሻው ኢህኣዴግን በምርጫ መጣል እንደማይችሉ ራሳቸውን ኣሳምነው ኣንዳንች ተኣምር የሚጠብቁ ይመስላል፡፡ ስልጣን መያዝ የሚቻለው ኢህኣዴግ ራሱን ካጠፋ ወይም ደግሞ የዋህ ልቦና ሰጥቶት ምርጫ ገለ-መለ ሳይል በድርድርና ብሄራዊ እርቅ ስም ስልጣን ለማጋራት ፈቃደኛ የሆነ ቀን ነው ብለው ያሰቡም ይመስላል፡፡ ለመሆኑ ኢህኣዴግ ፍትሃዊም እንበለው ኢ-ፍትሃዊ በምርጫ ስልጣን እስከያዘ ድረስ ለምን እንዲደራደራቸው እንደሚጠብቁ ኣይገባኝም፡፡ ኢህኣዴግ ጫካ ገብቼ ህይወት ከፍዬ ያመጣሁት ስልጣን ነው ሳይሆን እያለ ያለው በትጋት ሰርቼ በማሳየቴ ህዝቡ በምርጫ የሰጠኝ ስልጣን ነው- ነው የሚለው፡፡ ስለዚህ በዛ መንገድ መታገል ነው፡፡ ሕዝቡ ጋ ተጨባጭ ነገር ይዞ መግባትና ስልጣኑን ከኢህኣዴግ መንጠቅ – በሰላማዊ መንገድ፡፡ ሆኖም ግን ከኣቶ መለስ በኋላም ተቃዋሚዎች በዚህ ረገድ ያሳዩት የፖለቲካ ኣደረጃጀት ለውጥ የለም – በቅርቡ ለውጥ ያመጣሉ ብሎ መገመትም ኣይቻልም፡፡ ስለሆነም ኢህኣዴግ ራሱ እንደሚለው “በኣውራ ፓርቲነት“ መቀጠሉ የግድ ነው፡፡

የዲያስፖራው የተቃውሞ ምስቅልቅል

በተለያዩ ጊዜያት ኣንዳንድ ፖለቲከኞች ኣንዴ “ሁለ-ገብ ትግል ጀምረናል እና በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ወያኔን እንጥላለን” ሲሉ፣ ሌላ ጊዜ የት እንዳሉ ከማይታወቁ ድርጅቶች ጋር “ጥምረት ፈጥረናል የወያኔ ሞት ደርሷል” እያሉ በየግዛቱ እየዞሩ ሲደሰኩሩ፣ ከዛም ሲመቻቸው “ሻእቢያ ሊረዳን ነው እና ማሸነፋችን ኣይቀርም” ሲሉ፣ ሞቅ ሲላቸውም ደግሞ “ወያኔ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ እንሚወድቅ በመንፈስ ስለተገለጸልን የሽግግር መንግስት ኣቋቁመናል” እያሉ ሲሰብኩ ቢቆዩም በኣሁኑ ሰኣት የዲያስፖራ የተቃውሞ ፖለቲካ በሂደት እየከሰመ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ሞቷል ሊባል በሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የኣቶ መለስን ሞት ተከትሎም ተራ ኣሉባልታና “እኔ ነኝ የኣቶ መለስን መታመም ቀድሜ ያበሰርኩት” “እኔ ነኝ በስብሰባ ቦታ ጮኬባቸው የታመሙት” እያሉ ከመናቆር ውጭ ሌላ የታየ ፋይዳ ያለው ነገር ኣልነበረም፡፡ ከዚህ ውጭ ግን እንደ ዋና ኣጀንዳ ሲነሱ የነበሩት – ወ/ሮ ሱዛን ራይስ በኣቶ መለስ ቀብር ላይ ያደረጉትን ንግግር መቃወምና ማውገዝ፣ ኢህኣዴግ በስልጣን ሽኩቻ እየፈራረሰ ነው እያሉ ኣጉል ተስፋና ምኞትን ማራገብ በኣንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የኢህኣዴግ የስልጣን ኣሰጣጥ ህገ-መንግስቱን የተከተለ ኣይደለም እያሉ የህገ-መንግስቱ ጠበቃ ሆነው መታየት ነበር፡፡

በኣሁኑ ሰኣት በፖለቲካ ድርጅት ስም ስብሰባ ጠርተው የሚመጣላቸው ሰው እንደሌለ ከምንም ጊዜ በላይ ስለተረዱም የተቃውሞ ወይም በፖለቲካ ፓርቲ ስም ስብሰባ ለመጥራት ኣይሞክሩም፡፡ ኣሁን ያለችው ብቸኛ ኣማራጭ በኢሳት ቴሌቪዥን የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ስም መሞከር ነው፡፡ ኑሮኣቸውን በዚህ የፖለቲካ ቁማር የሚገፉ ጥቂት ሰዎችና ወንድሞቻቸው የተሰባሰቡበት ኢሳት – ራሳቸው ጋዜጠኛ፣ ራሳቸው የኢሳት እንግዳ፣ ራሳቸው የፖለቲካ ተንታኝ፣ ራሳቸው የቦርድ ኣባል፣ ወዘተ ወዘተ ሆነው የሚቀርቡበት ጣቢያ የብር ስጡኝ ዘመቻው በተለያዩ ከተሞች እየሞከረ ይገኛል፡፡ በሚጠሩዋቸው “የኢሳት ገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች” በጣት ለሚቆጠሩ ተሰብሳቢዎች የሚናገሩት የፖለቲካ ፕሮግራም በኣንድ ጉዳይ ላይ ያተኮሩ ናቸው– የዘር ጥላቻና ፖለቲካ ይደሰኮርና ማጠቃለያው “እኛ በኢሳት ቴሌቪዥን ታግለን ኢትዮጵያን ከወያኔ ኣገዛዝ ነፃ ስለምናወጣት ዶላር ኣምጡ” ነው፡፡

ይሄ የኢሳት ጉዳይ ቀጣይነቱ ስለማያስተማምን ሰሞኑን ኣንድ ነገር ይዘው ብቅ ያሉ ይመስላል – “የግንቦት ሰባት ህዝባዊ ሃይል” የተባለ ተዋጊ ቡድን ኣቋቁመናል ብለዋል፡፡ እንደተለመደው ይሄ ኣዲስ ነገር ይዞ መምጣት እንደ ስትራተጂ እንደሚጠቀሙበት ቢታወቅም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኣንዳንድ ኣስቂኝ የሆኑ ነገሮች ኣሉበት፡፡ ይሄ “ተዋጊ ሃይል” በኣካል የት እንደሆነ ኣይታወቅም፡፡ የግንባሩ ኣባል ነኝ ያሉና ለኢሳት ቃለመጠይቅ በስልክ ያነበቡት ኣቶ ዜና ተብለው የተገለፁና በኣካል (በምስል) ያልታዩ ሰውዬ (የኢሳት ጋዜጠኛ ድምፅም ሊሆን ይችላል ኣልታወቀም) የዚህ ተዋጊ ሃይል ትክክለኛ ቦታ የት እንደሆነ ተጠይቀው የት እንደሆነ መናገር እንደማይፈልጉ ገለፁና “ግንባሩን መቀላቀልና መዋጋት የሚፈልግ ሰው እንዴት ያግኛቹ?” ሲባሉ “ዌብሳይታችን ይመልከት ፣ ኢ-ሜይል ያድርግልን ወይም በኣድራሻችን ስልክ ይደውልልን ብለዋል (ስልኩ የለንደን ቁጥር ነው)፡፡ የዲያስፖራ የተቃውሞ ፖለቲካ በእንደዚህ ኣይነት ጨዋታ ይቀጥላል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ማጠቃለያ ፡ የኣቶ መለስና የድርጅታቸው ዋናው የትግል ትሩፋት (ሌጋሲ)

ኢህኣዴግ የደርግን ስርኣት ጥሎ ስልጣን ከያዘ ወዲህ በሃገሪቱ በርካታ የኣስተሳሰብ የመሰረተ-ልማት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ የታዩ ቢሆንም የፌዴራል ኣወቃቀርንና የብዝሀ ፖለቲካ ሰርኣትን ያወጀውና በ 1987ዓ/ም የፀደቀው ህገመንግስት ከምንም በላይ ነው፡፡ ያ ህገመንግስት በተለያዩ ሰዎችና ኣልፎ ኣልፎም በመንግሰት የሚጣስበት ኣጋጣሚዎች ቢስተዋልም ዞሮ ዞሮ በኢትዮጵያ የተረጋጋና ጤናማ የፖለቲካ ስርኣት እንዲኖር ከተፈለገ ብቸኛው ኣማራጭ ህገመንግስቱን ማክበርና ማስከበር ነው፡፡ ባለፉት ኣመታት ኢትዮጵያ የተጎናፀፈችው የፀጥታ መረጋጋትና ይሄንንም ተከትሎ የታዩት የመሰረተ-ልማትና የኢኮኖሚ መሻሻሎች ህገመንግስቱ ለዘመናት የኢትዮጰያ ህዝብ ሲታገልባቸው የነበሩ መሰረታዊ ጥያቄዎች በመመለሱ ብቻ ነው፡፡ ኢህኣዴግ ብቁ የሆነ የወታደራዊና ፖለቲካዊ ኣመራር ልምድ ቢኖረዉም ህገመንግስቱ የመለሳቸው መሰራተዊ ጉዳዮች በተለይም የፌዴራል ኣወቃቀርና ይሄንን ተከትሎ የተረጋገጡት የማንነትና ራስን በራስ የማስተዳደር መብቶች ሳይረጋገጡ በተረጋጋ ሁኔታ ሌሎች ፖሊሲዎችን መተግበር ይችል ነበር ብሎ ማሰብ ኣስቸጋሪ ነው፡፡

ህገመንግሰቱ ከኢህኣዴግ በላይ ነው – ህገ-መንግሰቱ ከግለሰቦች በላይ ነው፡፡ ኣንዳንድ ሰዎች ህገመንግስቱ የሚጎድለው ነገር ኣለ የተሟላ ኣይደለም ወይም ኣላስፈላጊ ኣንቀፆች ኣሉበት ብለው ለመቀበል ቢያንገራግሩም በኔ እምነት ህገመንግሰቱ የሚሻሻልበት ስርኣት እስካስቀመጠ ድረስ ሙሉ ነው፡፡ ህገ-መንግስቱ በሁሉም ዜጋ እስተከበረ ድረስ ዉሎ ኣድሮ የዜጎች ሰብኣዊም ፖለቲካዊም መብት መጠበቃቸው የግድ ነው፡፡ የህገ-መንግሰቱ ኣስፈላጊነትና ውጤታማነት ከታየባቸው ክስተቶች ኣንዱ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ በሚባል ሁኔታ የተካሄደው ሰላማዊ የመሪነት ሽግግር ነው፡፡ ኣገር ውስጥ ያለው ህብረሰተሰብ ለኣፍታ እንኳን የኣመራር ክፍተት ይፈጠራል ብሎ ሳይሰጋ ጊዜውንና ትኩረቱን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃዘን ላይ ኣድርጎ ማየት ህገመንግሰቱ ላይ ካለው እምነትና ተስፋ የመነጨ ከመሆኑ ውጪ ሌላ ሊመጣ የሚችል ትንታኔ የለም፡፡ በውጭ ኣገር ያሉ በርካታ ዜጎች የስልጣን ሽግግሩ ላይ እንከን ይኖራል ብለው በኣንድ በኩል የሰጉ በሌላ በኩል የተደሰቱ ሃይሎች ቢኖሩም ስጋታቸውንና ተስፋቸውን የተሳሳተ እንደነበር ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ ኣልወሰደባቸውም፡፡ በህገመንግስቱ ከተካተቱት መብቶች ኣንዱና ዋነኛው ዜጎች በሰላማዊ የፖለቲካ መድረክ ራሳቸውን ኣደራጅተው ሃሳባቸውን ለህዝብ ገልፀው በህዝብ ይሉኝታ ስልጣን የሚይዙበትና በህዝቡ ከስልጣን የሚባረሩበት ስርኣት ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ኣንድና ብቸኛው መንገድ ሊሆን ይገባል፡፡

**************

Please check the archives for more on the issues raised above.

* This article is part of the “Post-Meles 2012″ Special Edition of this blog.

Jossy Romanat

more recommended stories