ወቅታዊና ውጤታማ የፖለቲካ ጥገኝነት ስትራተጂ

(በጆሲ ዘ ሮማናት)

ቅዳሜ ግንቦት 06/2003 ኣ.ም. ኣዲስ ኣበባ ከሚገኘው የረጅም ጊዜ ወዳጄና የቁርጥ ቀን ሰው የሚከተለው ኢሜይል ደረሰኝ፡፡

“ይድረስ ለማከብርህ ዲያስፖራው ወዳጄ፡፡ እንደምታውቀውና ሁሌም እንደምታስታውሰው ዩኒቨርሲቲ ከነበርንበት ከ 1990ዎቹ መጀመርያ ጀምሮ ወደ ውጪ ኣገር የመውጣት ፍላጎቱ ኣለኝ፡፡ ይህ ፍላጎቴ እዛ ያላችሁ ጓደኞቼን ባስታወስኩ ቁጥር እያደገ እያደገ መጥቶ በቅርቡ የመሰረታዊ ሸቀጦች ዋጋ መጨመርን ተከትሎ እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ስለዚህ እዛ ካንተ ጋር ያሉ ጓደኞቻችንን ኣነጋግረህ ከዚህ ኣገር የምወጣበትን ኣንድ ዘዴ ብትፈጥሩ፡፡ በዲቪ ተስፋ ቆርጫለሁ፣ እንኳን ኣሁን ኮምፒተሩ መሳሳት ጀምሮ ድሮው በትክክል እየሰራም ኣልሆነልኝም- ኣሁን ዲቪ ሰልችቶኛል” ፡፡

እኔም በተባልኩት መሰረት እሁድ እለት ጓደኞቻችንን ሰብስቤ የጉዳዩን ኣሳሳቢነት ከገለፅኩላቸው በኋላ በጉዳዩ ላይ ኣብዝተን ተወያየን፡በመጨረሻም የጓደኛችንን ፍላጎት ለማሟላት ማንኛውም የትግል ስልት እንደምንጠቀምና ኣሜሪካ ወይም ካናዳ የሚገባበትን መንገድ እንደምናመቻች በኣንድ ድምፅ ተስማማን፡፡ ለዚሁ የሚያስፈልግ ወጪም ኣብረን ለመሸፈን፡፡

ቀጥሎም የተለያዩ ስትራተጂዎችን በመንደፍ ኣንድ በኣንድ ተወያየንባቸው፡፡ መጀመረያ የቀረቡት ኣማራጮች የሚጠየቀውን ክፍያ ኣሟልተን በትምህርት፣ በጋብቻ፣ በጉብኝት፣ ኮንሰርት ለማቅረብ ወዘተ እያንዳንደቸው በጥልቀት መከርንባቸው፡፡ ሆኖም የጓደኛችንን ባህርይና ሁኔታ ስለምናውቀው ሁሉም ኣማራጮች ዉድቅ ኣደረግናቸው፡፡ በመጨረሻ ግን ኣንድ ጥሩ ሃሳብ መጣ- የፖለቲካ ጥገኝነት፡፡ ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ የፖለቲካ ጥገኝነት ለማግኘት ስለማያመች ለየት ያለ ምክንያት መፍጠር የግድ ይላል፡፡ እውነቱን ለመናገር በኣሁኑ ዘመን የፖለቲካ ጥገኝነት ለማግኘት ወይ የ ኤርትራ ወይ የ ሲፒጂ (CPJ) ዜግነት ሊኖርህ ይገባል፡፡

በዚሁም መሰረት ጓደናችን ወደ ኬንያ፣ ሱዳን ኣሊያም ግብፅ ሄዶ በኤርትራ ስደተኝነት እንዲመዘገብ ሃሳብ ቀረበ፡፡ ሆኖም ስናስበው የኣሁኖቹ የምእራባውያን የኢሜግሬሽን ጉዳይ ፈፃሚዎች (Immigration officers) ሁኔታዉን ዉስብስብ እያደረጉት ነው፡፡ ኤርትራወያኖቹ ራሳቸው ብዙ ውስብስብ ሂደት ማለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ባለፈው ተሳክቶለት በሱዳን በኩል በስደተኝነት የመጣ ኣንድ የኣዲቀይሕ (ኤርትራ) ልጅ እንደነገረን ከሆነ ሰዎቹ ትግርኛ ቋንቋን ኣቀላጥፈው መናገር ጀምረዋል ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ የኤርትራ ሰፈር ያውቁታል፡፡ እንደዉም ልጁ በ ኢንተርቪው ጊዜ የተጠየቀው ጥያቄ “በቅርቡ ከ ኣዲቀይህ ሙሉ ለሙሉ ልጆቻቸውን ኣስከትለው ወደ ሱዳንና ኢትዮጵያ ከኮበለሉ ታዋቂ ነዋሪዎች ውስጥ ኣምስቱን ጥራ” የሚል ነበር፡፡ …. ስለዚህ ይሄ ዘዴ ለጓደኛችን ኣይሰራም፡፡

የመጨረሻውና የተሻለ ኣማራጭ የ ሲፒጂን ዜግነት ማግኘት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ሰዎች ይሄ ዘዴ ተጠቅመውበት ውጤታማ ሆኗል (ማንነታቸውን ኣንገልፅም ምክንያቱም ከኣንዳንድ ዌብሳይቶች ጋር መጣላት ኣንፈልግም)፡፡ እኛም ይሄንን ለማስፈፀም ስትራተጂ የነደፍን ሲሆን ኣፈፃፀሙም እንደሚከተለው ይሆናል፡፡

1. ኣንደ ኣንድ ሺ ዶላር ኣዋጥተን ለጓደኛችን እንልካለን፣

2. ጓደኛችን ኣዲስ አባባ ውስጥ የግል ሳምንታዊ ጋዜጣ ለማሳተም ከሚመለከተው የመንግስት ኣካል ፍቃድ ያወጣል፡፡ ራሱን በዋና ኣዘጋጅነት ያስመዘግባል፣

3. በተከታታይ ሁለት እትም መንግስትን በጣም የሚሳደቡ፣ የፕሬስ ህጉን የሚፃረሩ ፅሁፎችን ያትማል (የሚታተሙት የጋዜጣ ብዛት ትንሽ ይሆናሉ- ባይሸጡም ግድ የለም)፣

4. በሶስተኛው እትም የመንግስት ሚድያዎች እየተቹት እንደሆነ፣ ያልታወቁ ሰዎች በስልክ እንዳሰፈራሩት፣ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች እየተከታተሉት መሆኑን በዋናው ገፁ ያስነብባል፡፡ በርእሰ ኣንቀፁም “የምፅፈው ስለ እውነትና ስለ ኢትዮጵያ ኣንድነት ነው” ፣ “መታሰርን ኣልፈራም” ፣ “እየፃፍኩኝ እሞታለሁ” ብሎ ያትታል፡፡

5. እኛም ይሄንን ዘገባ ተቀብለን በኣንዳንድ የተቀዋሚ ሚድያዎች እንዲወጣ እናደርጋለን (ለምሳሌ: Addis Neger, Ethiomedia, Ethiopianreview, VOA Amharic, … etc)፡፡

6. በመቀጠል የተቀዋሚ ሚድያዎቹን ዜና በመጥቀስ ጉዳዩ ሲፒጂ እንዲከታተለው በ ኢሜይል ማጨናነቅ ፡፡ (እርግጠኞች ነን በሚቀጥለው ቀን ሲፒጂና ተዛማጅ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የፕሬስ ኣፈናና ወከባ ኣስመልክተው መግለጫ ያወጣሉ፣ ለዚህም የጓደኛችንን ጉዳይ በኣባሪነት ይጠቅሳሉ)፡፡

7. ጓደኛችን በ ሶስተኛው እትሙ ከላይ የተገለፁ ሚድያዎች የዘገቡትንና ሲፒጂና ሌሎች “የሰብኣዊ መብት ተቆርቋሪዎች” ያወጡትን መግለጫ በፊት ገፁ በሰፊው ይዘግበዋል፡፡ በርእሰ ኣንቀፁም “የሚደረግብኝ ከትትል ቀጥሏል” ፣ “መፃፌን እቀጥላለሁ” ይላል፡፡ “የመኖርና የመሞት ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ኣገሬን ለቅቄ ኣልወጣም” ብሎ ቢጨምርበትም ጥሩ ነው፡፡

8. ጋዜጣውን ባሳተመ በሶስተኛው ቀን ኣገርን ለቆ ለጉብኝት ወይም ለቢዝነስ ብሎ ወደ ኬንያ ኣሊያም ወደ ሱዳን ይወጣል፡፡ እዛ እንደደረሰም ኣገር ውስጥ ያለው የፕሬስ አፈና ኣሳስቦት ሸሽቶ እንደመጣ መግለጫ ይሰጣል፡፡ ከዛ በኋላ ያለው ሁኔታ ሲፒጂ ስለሚከታተለው ከኣሜሪካ መንግስት የፖለቲካ ጥገኝነት ለማግኘት ሳምንታት ብቻ በቂ ናቸው፡፡

9. በመጨረሻም እኛም እረፍት እናገኛለን ጓደኛችንም የ CPJ Fellowship,….. ምናምን ምናምን እያለ የሲፒጂ ኑሮዉን ይመራል፡፡ ………………………

ተፈፀመ

Jossy Romanat

more recommended stories