ተቃዋሚዎች እና ‹የጠፋው ኣስር ሺ ቶን ቡና› ወግ

(በጆሲ ሮማናት)

ባለፉት ጥቂት ኣመታት የኢትዮጵያ የግብይት ስርኣት ዘመናዊ ለማድረግ ታስቦ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዴርጅት (ECX) መቋቋሙ ይታወሳል፡፡ ይሄንን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት ማንኛውም ኤክስፖርት የሚደረግ ቡና ግብይት የሚደረገው በዚሁ ድርጅት ዉስጥ ብቻ መሆን እንዳለበት መመሪያ ኣወጣ፡፡ ይሄ ማለት በዚሁ ንግድ ውስጥ ያለ ሁለት ኣካላት፣ ማለትም ቡና ኣቅራቢዎችና ኤክስፖርተሮች የሚረካከቡት እዚሁ ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡ ይሄ የተደረገበት ምክንያትም ኣንደኛ እቅራቢዎቹ በጨረታ የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ሲሆን ሌላውና ዋናው ምክንያት ደግሞ ኣገሪቱ ከቡና የምታገኘውን የውጭ ምንዛሪ በኣግባቡ ለመቆጣጠር ታስቦ ነው፡፡ ይሄ ማለት ኣንድ ኤክስፖርተር ምን ያህል ቡና ወደ ውጪ እንደላከ ስለሚታወቅ የሚገኘው ዶላር ይታወቃል ማለት ነው፡፡

ታዲያ በዚሁ ስርኣት ለመሄድ የተስማሙት ነጋዴዎች በኣንድ ወቅት በዚሁ በ ECX በተደረገ ጨረታ ኤክስፖርት እናደርገዋለን ብለው በጨረታ የገዙትን ቡና ወደ ዉጪ ኣገር መላክ ሲገባቸው የኣለም ኣቀፍ የቡና ዋጋ ዝቅተኛ ስለነበረ በኣገር ውስጥ መሸጡ ያዋጣቸው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት የተወሰኑ ነጋዴዎች ለኤክስፖርት የተዘጋጀውን ቡና በጨረታ ገዝተው ከ ECX ካወጡ በኋሊ ኣንዳንዶቹ ባገር ውስጥ ገበያ ሲሸጡት ኣንዳንዶቹ ገበያ እስኪሻሻል ድረስ በማለት በመጋዘኖቻቸው ኣሽገው ኣስቀምጠዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም በወቅቱ ሃገሪቱ ከቡና ማግኘት የነበረባትን የውጭ ምዛሪ ቀንሶባታል፡፡

ይህንን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነጋዳዎችንና የ ECX ሃላፊዎችን ሰብስበው ካወያዩ በኋላ ከነዚሁ ነጋዴዎች ውስጥ 10000 ቶን ቡና ወደ ውጭ መላክ ሲገባቸው ሳይልኩ የቀሩትን “ቡናው ተኖም ከሆነ እንወቀው”- “ለኣሁኑ እንተወው ከኣሁን በኋሊ ግን እንደዚህ ኣይነት ተግባር ላይ የሚሳተፍ ኤክስፖርተር እጁ ይቆረጣል”- “ማለትም የቡና ኤክስፖርት ፍቃዱ ይሰረዛል” ብለው ነበር፡፡ ይሄንን ውይይት በኢትዮጵያ ቴላቪዥን ሁላችንም ተከታትለነዋሌ፡፡ ይሄ የሆነው 2010 ላይ ነው፡፡

ዘግየት ብሎ ታዲያ  February 2011 ላይ Ethiopian Review የተባለውና በዋናነት በኢትዮጵያ ላይ መጥፎ ስሜት ያላቸው ኤርትራውያን የሚጎበኙትና ኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ቁጣና ጥላቻቸውን የሚተነፍሱበት ድረገፅ የኢትዮጵያ መንግስት ኣስር ሺ ቶን ቡና ጠፋበት የሰረቁትም የኣቶ መለስ ባለቤት ናቸው ብሎ እንደ ትልቅ ዜና ይዞ ወጣ፡፡ ይሄ ኣልገረመኝም በዛ ዌብሳይት ሌላም ነገር ስለሚባል፡፡ እኔ የገረመኝና ለመጻፍም ያነሳሳኝ ግን ኣሜሪካ ውስጥ ያሉ ኣንዲንድ ተቃዋሚ ነን ባዮች ይሄ ጉዲይ በሌላ ተርጉመው እንደ ትልቅ የፖለቲካ ኣጀንዲ ማንሳታቸው ነው፡፡ ለምሳሌ፣-

ባለፉት ሳምንታት የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜን ኣሜሪካ ባደረጋቸው ስብሰባዎች ከሌላ ጊዜ በተለየ ሁኔታ ጨርቁን የጣለ –  ሰው መስሎ በተለያዩ ድረገጾች ያየነው ኣቶ ታማኝ በየነ በኢትዮጵያ ኣለ ብሎ ከገለጻቸው ችግሮችና የኣባይ ግድብ መሰራት የለበትም ለሚለው ተቃዉሞዉ በ VOA እንደ ምክንያት ያቀረበው ‘ኣስር ሺ ቶን የመንግስት ቡና ጠፍቶ (ተሰርቆ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንለፈው ኣሉ’ የሚል ነው፡፡

ሼክፔር የተባለ የሲያትል ነዋሪና በኣሁኑ ሰኣት ወደ ፖለቲካው መጣሁ መጣሁ እወቁኝ እያለ ያለ ሌላ ሰው ደግሞ ኣውራምባ ታይምስ ለተባለው ጋዜጣ በሰጠው ኣስተያየት ተመሳሳይ የሆነ (የኣስር ሺ ቶን ቡና) ጉዳይ ኣንስቷል፡፡

ሌሎች የነዚህ ሰዎች ተከታዮችም ተመሳሳይ ነገር ሲፅፉ ኣያለሁ::

ስለዚህ ኣቶ ታማኝና ሌሎቻችሁ እባካችሁ ከመናገራችሁ በፊት እነዚህን ነገር ብታስተውሉ፤

1. በመሰረቱ መንግስት ቡና ኣይሸጥም፡፡ ስለዚህ የመንግስት ቡና ኣልጠፋም፣

2. ነጋዴዎቹ የወሰደት የራሳቸው በጨረታ የገዙትን ቡና ነው፡፡ ችግሩ የተፈጠረው ኤክስፖርት ማድረግ ሲገባቸው ስላላደረጉት ነው፡፡ በዚህም መገኘት የነበረበት የውጭ ምንዛሪ ስለቀረ ብቻ ነው፣

3. ከመናገራችሁ በፊት ስለምታወሩት ነገር ኣድማጮቻችሁ በደንብ ሊያውቁ ይችላሉ ብላችሁ ብታስቡ- ቢያንስ ለክብራችሁ፣

4. የኢትዮጵያን መንግስት ለመቃወም የሚያስችሉ ብዙ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ኣሉ፡፡ የናንተ ከፍተኛ ጥያቄ እንደነዚህ ኣይነት የሰፈር ወሬ (ወይም ደግሞ በሰለሞን ተካልኝ ኣባባል የ Starbucks ወሬ) ከሆኑ ለኛም ኣይጠቅሙንም ለናንተም የትም ኣያደርሷችሁም፡፡ እና ራሳችሁን በፖለቲካ ብታንፁ ወይም ደግሞ ለሚችሉ ሰዎች ብትተዉት፣

5. ኣቶ ታማኝ በ VOA እሰጥ-አገባ ላይ ከኣቶ መኮንን ጋር ያደረግከው ክርከር ላይ ምንም ኣይነት የፖለቲካ ብስለትም ኣቅምም እንደሌለህ ያየንበት ነውና እንደ ድሮው ማይክሮፎኗን ይዘህ ቀረርቶና ሽለላዋ ላይ ጠበቅ ኣርገህ ብትይዝ ብዬ ወገናዊ ምክሬን እለግሰሃለሁኝ፡፡

Jossy Romanat

more recommended stories