ግልፅ ደብዳቤ ለክቡር ጠ/ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አሕመድና ለኢትዮጵያ ህዝብ

(ዋስይሁን)

የኢትዮጵያ ህዝቦች በደማቸውና አጥንታቸው የገነቡት ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ፣ ወደውና ተፋቅረው ያፀደቁት የሉዓላዊነታቸው መገለጫ የሆነው ህገ መንግስት በጠራራ ፀሀይ ያለምንም ስጋት ሲጣስና ሲቀደድ ማየት፣ አንዱን ህዝብ በሌላውን ህዝብ እንዲነሳሳ እና ግጭት ውስጥ እንዲገባ የሚያደርግ አፍራሽ ተግባሮች መፈፀም የመጨረሻው ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ለእርስዎ ይከብዳል የሚል እምነት የለንም፡፡

ላለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት እንደዚህ በመሰለ አፍራሽና ፀረ ህዝብ ተግባር በተለያዩ አካባቢዎች ስንት ወገኖች እንዳለቁና እንደተጎዱ ከመኖሪያ ቦታቸውና ከንብረታቸው እንደተፈናቀሉና እንደተዘረፉ ፣ ለእርስዎ የተሰወረ ነገር አልነበረም፡፡ አሁን መቋጫ እያገኘ ነው መባል በተጀመረበት ወቅት ደግሞ ትላንትና አውሮፕላን ይዘው ሲጨፈጭፉ የነበሩ ወገኖችና ሀይሎችም ተጨምረውበት ብቀላ በሚመስል መልኩ ብሄርን ያነጣጠረ ጥቃት ቀጣይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ስራ መስራትና ለዚህም በግልፅ የተፈቀደ በሚመስል መልኩ የህዝብ ሉዓላዊነትና ህዝባዊ አንድነት ባረጋገጠ ህገ መንግስት ላይ ጥሰት ሲካሄድ ዝም ብሎ ማለፍና ማየት ለሁላችን ወገኖች ስጋት ላይ እንዲጥል ምክንያት ሆነዋል፡፡ሉዓላዊነታችን ባረጋገጠ ህገ መንግስት ላይ ጥቃት መፈፀምና ግዝአታዊ አንድነትን የሚያስቀድም መፈክር ወደፊት አምጥቶ ቀሮሮ ማሰማት ትላንትናም ለአገሪቷ አልጠቀመም ነገም አይጠቅምም፡፡ ስለ ሰላምና ስለ ፍቅር እየተዘመረ ስለ ህዝቦች አንድነትና ሀይማኖታዊ እኩልነት እየተነገረ ባለበት ሰዓት የእኩልነታቸውና አንድነታቸው መገለጫ የሆነውንና በህገ መንግስታችን ያረጋገጥነውን ባንዴራ እያቃጠሉና እየረገጡ ግዛታዊ አንድነትን የሚገልፅ ባንዴራ እያውለበለቡ ቀረሮ ማሰማት በኢትዮጵያ ህዝቦችና ብሔር ብሔረሰቦች ላይ ያላቸውን ንቀት በግልፅ ያስመሰክራል፣

የኤርትራ መንግስትና የግብፅ መንግስት የፌዴራል ስርዓቱ ዋና ሀይል ወያነና የትግራይ ህዝብ ነው በዚሁ ሀይል ላይ ጥቃት ከፈፀምን ፌዴራል ስርዓትና ኢትዮጵያ የምትባል አገር ትበተናለች፣ ህዳሴ ግድቡም ይቆማል፣ የሚል የተሳሳተ እስትራቴጂ ተነድፎ ስራ ላይ መዋል ከጀመረና ሰፊ ዘመቻ መካሄድ ከጀመረበት 5 ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ ይህንን የውጭ የጠላቶች ሴራ የራስን እቅድ በማድረግ ለተግባራዊነቱም ላይና ታች እያለ ያለውን የስርዓቱ አመራርና ሀይል አወቀም አላወቀም እቆምልሃለህ ፣ እሞትልሃለህ እያለው ላለው ህዝብም ፍፁም እንደማይጠቅመው ገሀድ ሆኖ ይታያል፡፡

ትላንትና በትግራይ ህዝብና በቅማንት ህዝብ ላይ ፍፁም አስቀያሚ ጭፍጨፋና ግፍ የፈፀመ አመራር በፈፀመው ግፍና ጭፍጨፋ ላይ ተጠያቂነት የማይታይበትና ጠያቂ የሌለው ስርዓት በማግኘቱ ተኩራርቶ ራሱን ለቀጣይ ጭፍጨፋና የህዝቦች መተላለቅ እያቅራራ ያለው አመራርና የጠላቶች መሳሪያ የሆነውን ሀይል፣ አገሪቷ ወዴት ሊወስዳት እንደሚችልና ለሁላችን እያንዣበበ ያለውን አደጋ ለእርስዎም ከፍተኛ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ሳይገነዘቡት ይቀራል የሚል እምነት የለንም፡፡

የግዛት አንድነት አራማጅ ሀይል ስለ ኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት ፣ እኩልነትና ተፈቃቅሮ መኖር ደንታው እንዳልሆነ በግልፅ እያየን ነው፡፡ ቤተ አማራ በሚል የግዛት አንድነት ካርታው እንደተመለከትነው ከሆነ ስለ ኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሶችና ህዝቦች ያላቸውን ንቀት በግልፅ ገሀድ ሆኖ እናየዋለን፡፡ ቤተ አማራ ብሎ ሲያስብ አሁን ካለችው የትግራይ ክልል ከግማሽ በላይ ወደ ቤተ አማራ ያካተተ፣ ሙሉ ዓፋር በቁጥጥሩ ስር ያደረገ፣ ምፅዋዕና ዓሰብን ይዞ ሸዋ ክ/ሀገር ሲባል የነበረ በሙሉ አካቶ በምስራቅ እስከ ድሬዳዋ ፣ በደቡብ እስከ አዋሳ ፣ በደቡብ ምዕራብ ደግሞ እስከ አምቦና ቤንሻንጉል ጉምዝ የሚባለው ክልል ሙሉ በሙሉ በግዛት አንድነቱ የማጠቃለል ፍላጎት እንዳለው ገሀድ አድርገዋል፡፡

ሌላው ቀርቶ እርስዎ በአሁን ሰዓት የጀመሩትን መሰረታዊ ለውጦች ህዝቡ ከጎንዎ መሆኑ በሚገልፅበትና ከጎንዎ መሆኑ በሚያረጋግጥበት ወቅት ትላንትና በአደባባይ የህዝቦች ህይወት እንደቅጠል ሲቀጥፉ ከነበረው የፋሽሽት ስርዓት መሪ መንግስቱ ኃይለማርያም ጎን ጋር ፎቶግራፍዎ ዘርግተው ድጋፋችን እየገለፅንልዎት ነን ሲልዎት ፀረ ህዝብ ሀይሎች ፤ በመፈቃቀድ ወደንና ተማምነን የገነባነውን ፌዴራላዊ ስርዓት ለማፍረስ ምን ያህል ቆርጠው እንደተነሱ በግልፅ የምናይበት ሁኔታ እንዳለን ገሃድ አድርጎልናል፡፡

ድህነትን ለመቅረፍ አባይ የሚል ግድብ በመስራቱ የስርዓቱ ዋና ሀይል ወያነና የትግራይ ህዝብ እንደ ዋና ጠላት ተወስዶ በሻዕቢያ መሀንዲስነትና በግብፅ ፋይናንሳዊ ድጋፍ ሲካሄድ የነበረ ዘመቻና አገርን የማፈራረስ ሂደት አሁንም በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የቦርደር ጉዳይ አሁን አጀንዳ መሆን የለበትም በሚል የሻዕቢያ (የማነ ገብረአብ እና ፕ/ኢሳያስ አፈወርቂ) ስትራቴጂ አፍራሽና በታች ሀይሉ አዲስ አበባ ኮማንድ ፖስት መስርቶ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ያቀደው ስትራቴጂ ዞሮ ዞሮ የህዝቦች መተላለቅ ሊያስከትል እንደሚችልና በዓለም ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ጥፋት ሊያመጣ እንደሚችል እርስዎም ከአሁኑ ጀምሮ በአግባቡ መረዳት ያለብዎት ይመስለናል፡፡

በተለያዩ መድረኮችና የህዝብ ውይይቶች ሊያደርጉት የነበረ ንግግር ሁሉ ስናየው ለአገሪቷ ጥሩ እሳቤ ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ የሚያሰፍን ለሁሉም ህዝቦች እኩል የሚመለከት፣ ጥላቻና መቃቃርን የሚያስወግድ መፈቃቀርና መዋደድን የሚያሰፍን ንግግር እንደሆነና በዚሁ ልክም የእርስዎ እሳቤ ልባዊ እሳቤ እንደሆነ አድርገን እንመለከተዋለን፡፡

ይህ እንዳለ ብንወስደውም የህግን የበላይነት ከማረጋገጥና ከማስፈን አንፃር ግን የራሱ ክፍተት እንዳለው አድርገን እናየዋለን፡፡ በመሆኑም ነፃነት ማለት ህገ መንግስትን መጣስ ፣ የህዝቦች እኩልነትና አንድነት ያረጋገጠውን ህገ መንግስት በጠራራ ፀሀይ መርገጥ፣ አንዱን ህዝብ በሌላው ህዝብ እንዲነሳና ጥቃት እንዲፈፅምበት ማድረግ አድርጎ የተገነዘበ ሀይል ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብም ከፍተኛ ስጋት ሆኖ እንዳለ እርስዎም በአፅንኦት ማየት ያለብዎት ይመስለናል፡፡
ስለሆነም ክቡር ጠ/ሚኒስተር ለለውጥ መነሳትዎ ለፍቅር ለአንድነት መቆምዎ፣ ጥላቻና ቂም በቀልን ማስወገድዎ፣ ሁሉም ወገኖች በአገራቸው በህዝባቸው ጉዳይ ላይ በሰላማዊ መንገድ ያገባናል ብለው እንዲያስቡ እንዲታገሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲወዳደሩ ማድረግዎ እጅግ የሚበረታታና የሚደገፍ ነው፡፡ ለዚሁም ከምንም በላይ ከጎንዎ እንቆማለን፡፡

ለውጥ በንግግር ብቻ አይመሰረትም፡፡ ለውጥ በእቅድና በፕሮጀክት ፣ ለውጥ በመርሀ ግብር በትራንስፎርሜሽን ፣ ተመስርቶ ይካሄዳል፡፡ ይህ ሲሆንም በተደራጀ መልኩና ህዝብን ያሳተፈ ለውጥ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ስለሆነም ጥሩ እሳቤዎና ፍላጎትዎ የተደራጀና ህዝብን ያሳተፈ ለውጥ እንዲሆን በእቅድ የተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበና ተጨባጭ ለውጥን የሚያመጣ ከምፅአታዊ ለውጥ የፀዳ ለውጥ እንዲሆን አድርገው ቢመሩት ውጤታማ ለውጥ እንዲሆን ያደርገዋል አንላለን፡፡

መምጣት ያለበት ለውጥ መነሻና መድረሻ ያለው ለውጥ ቢሆን ህዝቦች በሂደቱና አካሄዱ ያለውና ሊኖረው የሚችል አመለካከት የተስተካከለ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

ይህ ማለት የለውጡ መነሻ ፌደራል ስርዓቱና ህገ መንግስቱ ሆኖ መድረሻው ደግሞ አስተማማኝ ሰላም፣ አስተማማኝ የህዝቦች እኩልነት ፣ አንድነትና ነፃነት፣ የጋራ ተጠቃሚነትና ልማት፣ ከአድልዎ ስርቆትና ሌብነት የፀዳ ፈጣን የህዝብ አገልግሎት የሚያረጋግጥ ስርዓት፣ ፍቅር ፣ አንድነትና ውህደት የሰፈነባት ኢትዮጵያ ፣ ጥላቻ፣ መቃቃር፣ ቅናት ፣ የማይታይባት ኢትዮጵያ፣ በሆነ ይሁን ጊዜ የህግ የበላይነት የሰፈነባት ሰላማዊት አገር ፣ ዜጎች በየትም ቦታ በሰላም ሰርተው የሚኖሩባት ኢትዮጵያ፣ ከውጭ ጣልቃ ገብነት የፀዳች ሉዓላዊነት አገር የመመስረት መዳረሻ ሊኖርዎት ይገባል፡፡ ይህንን ሲሆን ደግሞ ከአገሪቷ አራቱ ማዕዝኖች ድጋፍዎ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል ልናረጋግጥልዎት እንወዳለን፡፡

የአመራርዎ እምብርት ግልፅ መደባዊ ይዘት ያለው አመራር እንዲሆን በአፅንኦት ይጠበቃል፡፡ እስካሁን ባለው አካሄድ ሁሉም ለማስደሰት ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ብቻ ተመልክተናል፡፡ በአንድ ፖለቲካዊ ስርዓት ውስጥ ሁሉም ማስደሰት ቢፈለግና ቢታሰብም ዞሮ ዞሮ ግን መደባዊ ይዘት ያለው ሂደት መሆኑ ፍፁም የማይቀየር ነው፡፡ የፕረዚዳንት ትራምፕ አመራር ዋና መደባዊ ይዘቱ ካፒታሊስቱን በዋናነት መጥቀም ነው፡፡ ለዚህ ሲሉ ያላቸውና የሌላቸው ሀይልና አቅም በሙሉ አሟጠው ሲጠቀሙ ይታያል፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ካፒታሊዝም የመገንባት እቅድ ፍላጎት ቢኖረውም ዋና ይዘቱ ነፃ ኢኮኖሚ በመገንባት ሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚ እያደረገ የሚገነባ ካፒታሊዝም የመገንባት እቅድ እንደነበረው በግልፅ ያስቀምጣል፡፡ የእርስዎ አካሄድም ሁሉም ለማስደሰት አስበው ቢሰሩም እምብርት ያለው አካሄድ እንዲሆን ግን በግድ ይፈለጋል፡፡

እርስዎ እርቅና ሰላም ለመፍጠር፣ ፍቅርና አንድነት ለማስፈን፣ ጥላቻና ቂም በቀልን ለማስወገድ አስበው የሚሰሩት ስራ እጅግ በጣም የሚደገፍና የሚበረታታ ቢሆንም በዚህ መፈክር በዙርያዎ እርስዎን መጠቀምያ ለማድረግ የሚያንዣብብ ፣ የውሸት ወሬ የሚረጩ፣ ያልተደረገ፣ ያልተወራ፣ ያልታሰበ ነገር እንደታሰበ፣ እንደተደረገ እንደተወራ አድርገው የሚያስወሩ፤ ጥላቻን የሚጭሩ፣ እርስዎ በተሳሳተ መንገድ የሚመሩ፣ እርስዎን መጠቀሚያ የሚያደርጉት ጥገኞች በዙርያዎ እንዳያንዣብቡና ገና የለውጥ ሂደቱን እሳት እንዳያስገቡበት ፣ ያሰቡትና ያቀዱት ገና ሳይጀመር ጥላሸት እንዳይቀቡት ከጅምሩ ሁሉም ስራዎችዎ በጥንቃቄና በተደራጀ መንገድ እንዲመሩት ከሁሉም በላይ በህዝብ ተሳትፎና ግሩፕ ስራ ትልቅ ቦታ እንዲሰጡት ከአደራ ጭምር እናሳስብዎታለን፡፡ ከአሁኑ ጀምሮ አማካሪ ነኝ ፣ ፕሮጀክት አሰጥሀለህ ፣ ሚኒስተር አስደርግልሀለህ እየተባለ በጠራራ ፀሀይ እየተዘረፈ ያለውን ገንዘብ ለእርስዎም መረጃው ሳይደርስ ይቀራል የሚል እምነት የለንም፡፡

እርቅና ሰላምን ለማውረድ ጥላቻና ቂም በቀልን ለማስወገድ ሲሉ ትላንትና በመስቀል አደባባይ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች የቀጠፈ የደርግ ባለስልጣኖችም ምህረት አስገብቷል፡፡ ሰላም፣ ፍቅር ለቀጣይ ህዝባዊ አንድነት ሲባል ሁሉ ሰው እየደገፈ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ የኔ ተቀናቃኝ ናቸው ስለኔ እንዲህ ብሎ አውርቷል ወዘተ ብለው ወደ ቂም በቀል የሚወስድ እርምጃ እየሄዱ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ የተናገሩትን ንግግር ቀለሙ ሳይቀር ወደ እንደነዚ እርምጃ መሄድ አያስፈልግም ነበር በኛ እምነት በጀመሩት አካሄድ ቢቀጥሉ ይመረጣል እንጂ እርስ በእርሱ የሚጣረስ ተግባር መፈፀም እርስዎን ግምት ውስጥ ይከታል እንላለን፡፡

ከሁሉ በላይ በአፅንኦት ልንመክርዎት የምንፈልገው ነገር ቢኖር በአሁኑ ሰዓት ለዚህ ህዝብና ለዚች አገር ጦርነት ፍፁም አያስፈልገውም፡፡ ማን ያሸንፋል ማን ድል ያስገኛል የሞኞች እሳቤ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት እያንዳንዷ እንቅስቃሴዎ እንደ ጀመሩት ፍቅርን ሰላምን የሚያሰፍን ጦርነትን የሚያስርቅ እንጂ ህዝቦች ወደ ጦርነትና ግጭት የሚያስገባ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይጠይቆታል፡፡ እያንዳንዷ እንቅስቃሴዎ ደግሞ ከሁሉም ህዝቦች ብቃትና ህዝባዊ ውግንና ያላቸው አማካሪዎች ቢያደርጉ እሳቤዎና ምኞትዎ ይቃናል፣ ይሳካልም ብለን እናምናለን፡፡

በኛ እምነት በአሁኑ ሰዓት እርስዎን የሚያግዙና ራእይዎ በማሳካት ከጎንዎ የሚቆሙ ሰዎች ነገሮች በነቀፌታ ዓይን የሚያዩ ሰዎች ቢሆኑና እርስዎም እንደዚህ የመሰሉ ሰዎች ቢመርጡ ለውጤትዎ አጋዥ ይሆናሉ የሚል እምነት አለን፡፡ ለእርስዎ ጥሩ እየመሰሉ ከበስተጀርባዎ ደግሞ ሌላ ስራ የሚሰሩ ሰዎች መምረጥ ኢህአዴግም ለውድቀት የዳረጉት እንደዚህ ዓይነት “Yes Men” ሰዎችና ወረበሎች ናቸው፡፡ ከማንም ጊዜ በላይ አደራ የምንልዎት ከነዚህ የመሰሉ አስመሳዮች ምንም ዓይነት ስብእና የሌላቸው ወሬኞችና ወረበሎች መራቅ ነው፡፡

አጀማመርዎ ለህዝቦች እያስደሰተ ነው፡፡ አጀማመርዎ ፍቅር ነው፣ ሰላም ነው፣ መዋደድ ነው፣ ይቅር ይቅር መባባል ነው፡፡ ኢኮኖሚውም በዚህ ልክ ቢሆን ፤ የተራበ እንዲበላ ቢደረግ፤ ስራ ያጣ ስራ እንዲያገኝ ቢደረግ፤ የኑሮ ውድነቱ መልክ ቢይዝ፤ አጀማመርዎ እንዳማረ ሁሉ አጨራረስዎ ያማረ እንዲሆን እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በጥናቃቄ ቢመራ ያምራል እንላለን፡፡

ክቡር ጠ/ሚኒስተር

ሌላውን ህዝብ የሚንቅና የሚያንቋሽሽ አመራር የራሱን ህዝብ ሊጠቅምም ፍፁም አይችልም፡፡ እንደ ትላንትናው የደርግ መፈክር “እፍኝ” የማይሞሉ የሚል የተሳሳተ የሰነፎችና ደካሞች አባባል ያነገቡና በትምክህት የተወጠረ አመለካከት ያለው ሀይል ለውጡ ሳይጀመር ሌላ እሳት እንዳይጭርብን ለ27 ዓመት ያገኘነውን ሰላም ሌላ ጦርነት ውስጥ እንዳይከተን ነገሮች በጥንቃቄና በበቂ ችሎታ ልንመራውና ልንከታተለው ይገባል፡፡ በዛም በዚህም ከአሁኑ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉ አካሄዶችና አመለካከቶች ምልክታቸው አደገኛና ትላንትናም ለከፍተኛ ፍጅት የዳረገን አመለካከት ነው፡፡ እርስዎን በመደገፍ ስም ህገ መንግስቱን በጠራራ ፀሀይ የሚንድ አካሄድ መሄድ፣ ህዝቦችን የሚንቅ አመለካከት ፣ የግዛት አንድነትን ለማስመለስ የሚቋምጥ አካሄድ በሆነ ይሁን መለኪያ ነገና ከነገ ወዲያ የእርስዎ ስልጣን ለመንጠቅ ያሴራ ሀይል እንጂ እርስዎ ላነገቡት ለውጥ ፍፁም ሊደግፍ አይችልም፡፡ ስለሆነም ስንዴውና እንክርዳዱ ተደበላልቆ አደጋ ውስጥ እንዳያስገባን በጥንቃቄ እንዲያዩትና እንዲመሩት በአፅንኦት ምክራችን እንለግሳለን፡፡

የተከበራችሁ የፌደራል ስርዓቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት

የፌደራል ስራአቱ ሉዓላዊነት የኢትዮጲያ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ህዝቦች የኢትዮጲያ ሉአላዊ ስልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ህገ መንግስቱ ደግሞ የሉዓላዊነታቸው መገለጫ ነው፡፡ ሉዓላዊነታቸው የሚገለጸው ደግሞ በዚህ ህገ መንግስት መሰረት በሚመርጧቸው ተወካዮችና በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ነው፡፡ ህገ መንግስቱ ደግሞ የአገሪቷ የበላይ ህግ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ማንኛውም የአገሪቷ ዜጋ፣ የመንግስት አካላት፣ የፖለቲካ ድርጅቶች ፣ሲቪክ ማህበራት ፣ማንኛውም ባለስልጣን ህገ መንግስቱን የማስከበርና ለህገ መንግስቱ ተገዥ መሆን እንዳለበት ህጉን ይደነግላል፡፡

ስርዓቱና ህጉ ግልፅ በሆነበት አገር ላይ የህዝብ ሃላፊነትና ስልጣን የያዙ ሃይሎችና አመራሮች ህገ መንግስቱ በግልፅ ሲንዱትና ሲጥሱት ዝም ብሎ መመልከት ለናንተ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትም የሞራልና የህሊና ቁስል ነው፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ተገዥነታችሁ ለህገ መንግስቱ ለህዝቡና ለህሊናችሁ በሆነበት ወቅት ህገ መንግስቱ ሲጣስና የህዝብ ሉዓላዊነት ሲናድ ዝም ብሎ ማየትና መስማት አገሪቷ ዋስትና ወደ ሌለው መንገድ እየሄደች እንደሆነ ፤ አነሰም በዛም ወደ ሌላ የእርስ በርስ ጦርነት እየተመራች እንደሆነ ማወቁና መረዳቱ የግድ ይላል፡፡

ስለሆነም የያዛችሁት የህዝብ ውክልና ተጠቅማችሁ ህገ መንግስቱ እንዲከበር ፣ የህዝብ ሊዓላዊነት እንዲከበር ፣ ህገ መንግስቱና ስርዓቱ ሲጣስ ህገመንግስቱን የጣሱ ሃይሎች ፣ አመራሮች፣ ባለስልጣኖች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ ህዝቦች በአገራቸው ላይ ሰብአዊና ፖለቲካዊ መብታቸው እንዲከበር፣ በማንኛውም የአገሪቷ ክልል ተዘዋውረው የመስራት መብታቸው እንዲጠበቅ፣ አገራችን የጀመረችው የሰላም፣ የልማትና የዴሞክራሲያው አንድነት መንገድ እንዲጠበቅ፤ እናንተም በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባልነታችሁ በህሊናችሁ ለመረጣችሁ ህዝብ ስትሉ ዘብ እንድትቆሙ፣ ከአደራ ጭምር ትጠየቃላችሁ፡፡

መላ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ህዝቦች፡

ትላንትና በደማችሁ እና በአጥንታችሁ አስከፊውን የደርግ ስርዓት በማስወገድ ወዳችሁና ተፈቃቅራችሁ ፌዴራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መስርታችኋል፡፡ መብታችሁና ጥቅማችሁ ሉዓላዊነታችሁ አንድነታችሁና ነፃነታችሁ የምታረጋግጡበት ህገ መንግስት መስርታችኋል፡፡ በሆነ ይሁን ጊዜ ይህ ህገ መንግስት የሁላችን ህዝቦች ዋስትና ነው፡፡ ማስተካከልና ማሻሻል ካስፈለገም በገዛ ፍቃዳችንና እምነታችን እንጂ በማንም ሀይል አስገዳጅ ፍፁም ሊቀየር አይችልም፡፡ ስለሆነም ይህንን ህገ መንግስት የሁላችን ህዝቦች ዋስትና እንደመሆኑ መጠን ከማንም ጥቃትና አፍራሽ እንቅስቃሴ በንቃት በተደራጀና በተዋሃደ መልኩ ልንጠብቀው ይገባል፡፡ የግዛት አንድነት አራማጆች ሽንፈታቸውን ባለመቀበል የድሮ ስርዓታቸውን ለማስመለስ እየቋመጡብን መሆናቸው በአመክሮ ልንመለከተው ይገባል፡፡ በሆነ ይሁን ጊዜ ደግሞ ቅንጣት ታክልም ለግዛት አንድነት አመለካከታቸውና ተግባራቸው እድል ልንሰጥ አይገባም፡፡

የተከበራችሁ የኢህአዴግ አመራሮች

አገራችን ከአስከፊው የደርግ ስርዓት ተላቃ የህዝቦች እኩልነት፣ ነፃነት፣ አንድነትና የጋራ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ከጀመረች 27 ዓመት አስቆጥራለች፡፡ እንዲህ በሆነበት ወቅት ከህዝቡ ጥቅም በፊት የራሱን ጥቅም ማስቀደም የመረጠውን አመራር ራሱን ወደ ገዢ መደብ በመቀየር የህዝቦችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በመርገጥ፣ የያዘውን ስልጣን ለኢፍትሃዊ አድላዊ አካሄድ፣ ለስርቆትና ለቅጥፈት ሲጠቀምበት ቆይቷል፡፡

ይህንን የበሰበሰ አካሄድ ራሳችሁም አምናችሁም የተቀበላችሁት መሆኑ የሚታይ ቢሆንም በውስጣችሁ ያለው የገማ አካሄድ የመጨረሻው ውጤት ወደ ህዝቦች መተላለቅና ፍጅት እየመራችሁት መሆኑ በግልፅ እየታየ ነው፡፡ ህዝቦች በውስጣቸው ምንም አይነት ቅራኔ የለም፡፡ በየትም ጊዜም ኖሮ አያውቅም፡፡ ተፈቃቅሮ ተከባብሮ አንድነቱን ጠብቆ ሲኖር የነበረ ህዝብ በኋላ ቀር አመለካከትና ዘርአዊ ቅስቀሳ ህዝቦችን ለማፋጀት እየቋመጣችሁ መሆናችሁ እየታየ ነው፡፡
ይህ የተሳሳተ አካሄድ ፍጅቱ በህዝቦች ብቻ የሚቆም ሊሆን አይችልም፡፡ እናንተንም ጭምር የሚያቃጥላችሁ ፍጅት ሊሆን እንደሚቻል ከአሁኑ ጀምራችሁ ልትገነዘቡት ይገባል፡፡ ቢሆን ቢሆን ለስልጣን ብላችሁ ህዝቡን ከምታፋጁት በገዛ ፍቃዳችሁ ስልጣኑን ለህዝብ አስረክባችሁ የህዝቡን ሰላምና የልማት ጉዞ እንዲቀጥል ብታደርጉት ለናንተና ለቤተሰባችሁም ተጠቃሚ እንደሚያደርጋችሁ የሚጠፋችሁ አይመስለንም፡፡

ስለሆነ ከማፋጀት ሰላም ብትመርጡ፣ ለግላችሁና ለሆዳችሁ ከምታስቡ ለህዝብና ለአገር ብታስቡ፣ ከመቃቃርና ጥላቻ መቻቻልና በጋራ መስራት ብታስቀድሙ ፣ ወንጀለኞች በህግ ተጠያቂ ብታደርጉ፣ መጥፎ መስራት ለአገርና ለህዝብ ጥፋት ካልሆነ በስተቀር የሚያተርፈው ነገር እንደሌለ ተረድታቹ፤ ጥሩ በመስራት ስማችሁና ክብራችሁ አስጠብቃችሁ በህዝባችሁም ተከብራችሁ ብትኖሩ ይመረጣል እንላለን፡፡

የተከበራችሁ የትግራይ ህዝብ ሆይ

በአስር ሺዎች የሚቆጠር መስዋእት ከፍለህ የህዝቦች እኩልነት፣ አንድነትና ነፃነት የጋራ ተጠቃሚነት ያለው ስርዓት መመስረትህ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያውቁታል፡፡ ሁሌም ለመስዋእትህና ለከፈልከው ዋጋና ክብር ይሰጡታል፡፡
በመስዋእትህ የተገነባውን ስርዓት ለማፍረስና የከፈልከውን መስዋእት ዋጋ ቢስ ለማድረግ አንተም አበሳጭተው ወደ አልተፈለገ ግጭት ሊያስገቡህ ላለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት ያልተፈለገ መስዋእት ዳግም እንድትከፍል እያደረጉህ እንደሆነ በግልፅ ታይቷል፡፡

እጅግ በጣም የሚገርመው ግን በነሱ ሴራና ጥላቻ ሳትበገር የከፈልከውን መስዋእት ታሳቢ በማድረግ ያሳየኸውን አስተዋይነት፣ ቻይነትና ታጋሽነት የታላቅነትህ ምስክር መሆኑ ገሀድ የሚያደርገው ነው፡፡ ጠላቶችህ ማንነትህና የማድረግ ችሎታህ በአግባቡ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ አሁን በደካማ አስተሳሰባቸውና ቀቢፀ ተስፋ እምነታቸው የማይጫር ነገር ቢጭሩ እንደወትሮህ ታጋሽነትህ ፣ ቻይነትህ፣ ታላቅነትህ አሳያቸው፡፡ ይህንን ስታደርግም ራስህን አደራጅተህ ፣ ውስጣዊ አንድነትህን ጠብቀህ ፣ እያንዳንዷን እንቅስቃሴ በጥንቃቅ በአፅንኦት እየተመለከትክ ፣ ከሌላው ወንድምህ ኢትዮጵያዊ እየተደጋገፍክ ፣ ለሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መፍትሄ ቅድሚያ ሰጥተህ ፣ ታጋይነትህና ጀግንነትህ ግን እንደወትረው ጠብቀህ የግዛት አንድነት ሀይሎች ከሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ ሆነህ መክታቸው፡፡

የተከበራችሁ የኤርትራ ህዝብ ሆይ

አስከፊው የደርግ ስርዓት ከወንድምህ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በጋራ ሆነህ ከገረሰስከው በኋላ ከወንድምህ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመተባበር ሰላምና የጋራ እድገት ይመጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ጊዜ እብሪትና ጦርነት የሚናፍቃቸው አመራሮች ከወንድምህ የኢትዮጵያ ህዝብ በቦርደር ስም ወድ ጦርነት ማግደውህ ከሁሉም ህዝቦች በአስር ሺዎች የሚቆጠር ወጣት አልቀዋል፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት ደግሞ ሰላምና ጦርነት የሌላቸው አገሮች እንደሆኑ አድርገውሃል፡፡
ሰላም፣ ወንድማማችነት፣ የጋራ ተጠቃሚነትና ወንድማዊ መደጋገፍ ለሁላችን ህዝቦች ይጠቅማል፡፡ ከማንም ግዜ በላይ ደግሞ አሁን ያስፈልገናል፡፡

ይህንን ፍላጎት የተረዱ የተወሰኑ አመራሮችህ የህዝባቸውን ፍላጎት በማስቀደም በአሁን ወቅት ከኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ደግሞ ከትግራይ ህዝብ ትክክለኛ እርቅ ያስፈልገናል ሲሉ ይሰማል፡፡ ይህንን ፍላጎት የሌላቸው እንደነ ፕረዚዳንት ኢሳያስ እና የማነ ገብረአብ የመሰሉ ግን ከትክክለኛውና የህዝብ እርቅ ወጥተው ከግዛት አንድነት ሀይሎች በሚስጥር እየደለቱና እየተማከሩ የትግራይ ህዝብን ከጫወታ ውጭ በማድረግ ቁማር እየተጫወቱ መሆናቸውን በግልፅ እየተመለከትን ነው፡፡ ይህንን የተሳሳተ አመለካከት ግን ላንተው ይሁን ለወንድምህ የኢትዮጵያ ህዝብ አንዳች ጥቅም የለውም፤ ፍፁምም አይኖረውም፡፡

ስለሆነም ትክክለኛው እርቅ እየተመኙ ያሉ አመራሮችህን እየደገፍክ ከወንድምህና የቅርብ ቤተሰብህ ሰላምህን ፈጥረህ አፍራሽ ሴራና እንቅስቃሴ እያደረጉ ያሉ ሰይጣን አመራሮችህ እየተቃወምክ መልካም ጉርብትናህን ወንድምነትህን ወደ ድሮ ቦታው መልስ፡፡ ወንድምህና መልካም ጉርብትናህ የሚመኘው የኢትዮጵያ ህዝብም እንደወትረው እጁ ዘርግቶ እየጠበቀህ ይገኛል፡፡

በስተመጨረሻ ኢትዮጵያ አገራችን በአሁኑ ወቅት ከሰላምና ልማት መንገድ ውጭ ሌላ ምርጫ ሊኖራት አይገባም፡፡ ጦርነት ለህዝባችንና ለአገራችን ያለው ፋይዳ በአግባቡ ጠንቅቀን የምናውቅና የተረዳን ህዝቦች ነን፡፡ ከዴሞክራሲያዊ አንድነት፣ ከሀይማኖታዊ ብሄር ብሄረሰብ ነፃነት ውጭ ሌላ ምርጫ ይኖረናል ብሎ ማሰብ ከንቱ ምርጫ ነው፡፡ በሆነ ይሁን ጊዜ ፍፁም ተቀባይነት የማይኖረው ምርጫ ነው፡፡ እንኳን አሁን ድሮም ቢሆን ከከፍተኛ ኪሳራ ውጭ የፈየደ ነገር የለም፡፡
ስለሆነም ህዝቦች በሀይል ገዝቶና አንበርክኮ መኖር ፍፁም እንደማይቻል ማወቅና መረዳት የግድ ይላል፡፡ በመሆኑም በስልጣን ያላችሁና ለስልጣን የምትቋምጡ ወገኖች ሀይሎች በሙሉ ዘመን ያለፈበት ሴራ አንግባችሁ ሌላ ሽንፈት ከመከናነብ ትክክለኛውን የህዝብ ምርጫ ይዛችሁ ሰላምና ልማቱ ብታስቀጥሉ ለናንተም ጠቃሚ ምርጫ ነው ልንላችሁ እንወዳለን፡፡ ይህንን ሳይሆን ሲቀር ግን ሊያስከትለው የሚችል አደጋ ቀላል ሊሆን እንደማይችል በአፅንኦት ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ ሰላምዋን ያብዛልን!

**********

Guest Author

more recommended stories