የስማበለው አባልነትና መዘዞቹ

(ብርሃነ ሓዱሽ)

ባለፉት ሶስት ዓመታት ሃገራችን ሰላምዋን አጥታ መቆይተዋን ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ በኔ እይታ አሁን ላለንበት ሀገራዊ ቀውስ ዋነኛው ምክንያት የኢሃደግ የስራ ድስፕሊን እየዘቀጠ መምጣቱ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ደግሞ በተለያዩ የመንግስት፣ ድርጅትና የህዝብ መድረኮች ተገምግሞ መፍትሄ ሳይበጅለት እየቀጠለ ያለው “የፓርቲው” (ግንባሩ) የስማበለው የአባላት ምልመላ እና ወልዶት የመጣው የጥራት ችግር ነው፡፡ በድርጅቱ ልምድ የማእከላይ ኮምቴዎች፣ ጉባኤዎች፣ መሰረታዊ ድርጀቶች፣ ህዋስ በጠንካራ ድስፕሊን በፅኑ ግምገማ ከዛም በወጣ አመራር መመራት ብዙ ለተዘመረለት ውጤትና ድል አብቅቶ ነበር፡፡ ይሁንና ቀን እያለፈ ቀንን ሲተካው ያ ቀርቶ በስማበለው አባልነትና ጥልቅ “ግምገማ” ተተካ፡፡

ለምሳሌ በ2000 ዓ/ም የአንደኛ ዲግሪ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ እያለሁ የኦሆዴድ ድርጅት አባላት በክረምት ወቅት በስመ ስልጠና በሁለት ቀናት ከ2000-3000 ብር ይሰጣቸው እንደነበር የኦሆዴድ አባላት ጋደኞቼ ይነግሩኝ ነበረ፡፡ እነዘህ ሰዎች ትክክለኛ የድርጅቱ አባላት ቢሆኑ ቅር ባላለኝ ነበር፡፡ በብዛት የአነግ ሃሳብና ባንዲራ አቀንቃኝ ነበሩ፡፡ አሁን ያሉት የድርጅቱ አባላት ከተራ አባል አስከ ከፍተኛ አመራር በዚህ አካሄድ የመጡ ናቸው። በዚህ ሁነታ የተደራጀ የፖለቲካ ድርጅት ምን ኣይነት ቁምና እንደሚኖረው ለመገመት አያስቸግርም። ኦሄዴድ ቀድሞ አፌ ገባና እንደምሳሌ አነሳሁ አንጂ በሌሎች የኢሃደግ እህት ድርጅቶችም ይህ የተሞካሸ ተግባር የለም ለማለት ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግም፡፡ ለዚህም ነው የት ይደርሳል የተባለ ጥጃ ከብት ተራ ተገኘ አንዲሉ ወይም ወጣ ወጣና እንደ ሸንበቆ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ ዓይነት ተክለ ቁመናና ባህሪ ዛሬ ተላበሰው፡፡ ለዚህ ነው እንግዲህ አሁን አባላቱ በድርጅቱ በአባልነት የመቀጠልና ያለመቀጠል ፍላጎት የውሃ ላይ ኩበት ይመስል ወደ ነፈሰፈበት የሚነፍሰው፡፡

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከግንባሩ እህት ድርጅቶች ለምሳሌ ከህወሓት አባልነት ለመውጣት ያለው ቢሮክራሲ እጅግ በጣም ከርፋፋ ነው፡፡ በቢሮከራሲው የተማረሩ አባላት የስንብት ደብዳቤ ከማግኘት ይልቅ የመግንስተ ሰማያት መግብያ ትኬት ማግኘት ይቀላል ይላሉ፡፡ በድርጅቱ መመረያ መሰረት አንድ አባል ከድርጅቱ ለመውጣት ሂደቱ በጣም በጣም አጭርና ግልፅ ነው ፡፡ ነግር ግን በየእርከኑ ያሉ “አመራሮች” በሚፈጥሩት ውስብስብ ቢሮክራሲ ሰው ሰልችቶት በቃ ገንዘቡን ይውሰዱት እኔ ግን አባልነቴን ሰርዣለሁ ድሮም በስማበለው ነው የተቀላቀልኩት አሁንም በስማበው ለመውጣት እየተጠባበቁ ነው የሚሉት፡፡ ከአባላት ጥራት ጋር አንድ የቅርብ ወዳጄ ከኔ የተሻለ መረጃ ስላለው ድርጅቱ ለምን ድ ነው በአባለት ጥራት ላይ የማይሰራው ብዬ ስጠይቀው የሰጠኝ ምላሽ አሳፋሪ ነው፡፡ የአባላት ጥራት ላይ ከሰራን ማ ድርጅቱ ባዶ ይቀራል ብሎኝ እርፍ!!! ለዚህ ማሳያ ሰሞኑን ከሁለት ክልልና መስራቤቶች ካገኘሁት መረጃ እንደተራጅሁት ከ4 ወር በፊት 20 አባላት ከድርጅቱ ለመልቀቅ በፅሁፍ ማማልከቻ ቢያስገቡም የሚሰማቸው አጥተው እየተማረሩ ብጉልበት በስማበለው አባልነታቸው ቀጥለዋል፡፡ በእውነተ ይህ ሂደት በእጅጉ ግራ ያጋባል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል ቢሮዎች የሚሰሩ ሰራተኞች የአባለነት ክፍያ በግዲታ እንደሚከፍሉ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ መምህራን፡ሃኪሞች፣ የግብርና ባለሙያዎች የሀገሪቱ ሙያተኛ ናቸው፡፡ በፍላጎታቸው የፖለቲካል ፓርቲ አባል መሆን አይችሉም አላለኩም፡፡ ነገር ግን ከፍላጎታቸው ውጪ ከደሞዘቸው የኦሆዴድ፡ ብአዴን፡ህወሓትና ደኢሀደን አባልነት ወርሃዊ መዋጮ እንዲከፍሉ ማድረግ እጅግ አደገኛ ሲያልፍም የህግ ጥስት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ጨክነን ወደ ፍርድ ቤት ከሄድን ክፍያችን እንደሚቋረጥ እናቃለን። ነገር ግን እማን ላይ ቁመሽ ማንን ታሚያለሽ ሆነባችዋል።

ስለዘህ አንድ የፖልቲካ ድርጅት በራሱ አባላት ለሚነሱት ጥያቄዎች መመለስ ካቃተው የተወሳሰበ ፍላጎት ያለው የ100 ሚሊዮን ህዝብ ፍላጎት ማርካትም ሆነ የመምራት ተክለ ቁመናና ሞራልም ጭምር ያጣል፡፡ ለኔ ይህ ጉዳይ በሰከነ መንፈስ በስትራትጂና በጥብቅ የስራ ድስፕሊን ካልተፈታ በስተቀር ሃገሪቱን ወደ ባስ ብጥብጥና ሁከት የሚመራ ነው መስሎ የሚሰማኝ፡፡ አሁን ያለንበት ጊዜ ሞገድ የጠፋበት ሬድዮ ነው። ስለዘህ ከላይ በጠቀስኩት ሂደት የገቡና በሃይል በድርጅቱ የቆዩ አባለት የድርጅቱን ርእዮተ አለምና የድርጅቱ የፖለቲካ ፕሮግራም ተረድትው ድርጅቱን ረዢም ርቀት ይወስዱታል ብሎ ማመን የዋህነት ነው። ልብ ብለን ማየት ያለብን ጉዳይ ለምንድ ነው አባላቱ ከድርጅቱ ለመውጣት የሚፈልጉት የሚል ጥያቄ ነው። ምንም እንኳን የመውጣታቸው ምክነያት የክፈያ መብዛት ቢመስልም ሃቁ ግን ወድያ ነው፡፡ ከታች እስከ ላይ ያለውን ፍሬ አልባ ወሬዎቸ ፡ ኔትወርክ፣ የጓድነት መንፈስ መላላት፣መጠላለፍ፣መጠቃቃት፣መርህ አልባ ግንኙነት፣ እርስበርስ የመበላላትና ንትርክ እጅጅ ስላላችው ነው፡፡ በተጨማሪም አባል በመሆን የሚያገኙት የፖልቲካ አቅም ግንባታ ስልጠናም ሆነ ጥቅም የለም፡፡ ድርጅቱ ከአባላት የሚፈልገው ገንዘብ ብቻ ነው። እንግዲህ አባታችን ኢህድግ ሆይ በፅናት በወደቁ የትግሉ ሰማዕታት ወደ ስልጣን እንደመጣህ ሁሉ የሰዎች ስብስብ ነህ ና በስማበለው በፈረሃቸው አባላቶችህ ብርቱ ጥርት ወደ መቃብር መውረጃህ እንደተፋጠነ ላንተም የተሰወረ እይመስለኝም፡፡ ብርግጥ ያልዘሩት አይበቅልምና ይሄ አይደንቅም !!!!

ከማን ነው ያልክ አንደሆነ ማነው ብለህ ጊዜ አታጥፋ ፣ ከራስህ ነው!!

ሰኔ 2010

******

Guest Author

more recommended stories