በኢትዮ-ኤርትራ የወሰን ግጭት መፍትሄ ዙርያ

(አማኑኤል አለማየሁ (ደጀና)

የኤርትራ መንግስት ኢትዮጲያን የወረረው የመሬት ይገባኛል ጥያቄው በንግግር ወይንም በድርድር ቢበዛም በአለማቀፍ ገላጋይ አካል ስለማይፈታ አይደለም፡፡ በኤርትራ ውስጥ እየተነሱ የነበሩትን የፖለቲካ (የዴሞክራሲ)፣ የህግ የበላይት እንዲሁም የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች በገዥው ፓርቲ ህ.ግ.ደ.ፍ. በተለይም ደግሞ በድርጅቱ ባለቤት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ላይ የፈጠረውን ጫና ወደ ጎን ማዞር (diverte) የሚያስችል ቋሚ ፀብ መፍጠርና አገሪቱን በጦርነት ሰበብ አግቶ መያዝ እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ስለታየው የገባበት ጦርነት ነው፡፡

ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በፊት የኤርትራ መንግስት ቋሚ ጠላት ፍለጋ ከየመን ቀጥሎ ከሱዳን ከዛም ከጅቡቲ ጋር መለስተኛ ጦርነቶችን አድርጓል ነገር ግን እንደታሰበው ወደ ለየለትና ወደ ቋሚ ጦርነትና ጠላትነት ሊገቡለት አልቻሉም፡፡

ኤርትራ እንደ የጣልያን ቅኝ ግዛት ስትመሰረት ቅኝ ገዥዋ ጣልያን እግሯን ኤርትራ ውስጥ እንዳሳረፈች የወሰደችው አንደኛ እርምጃ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ ተወላጆችን በባንዳነት (በጣሊያን ታጣቂነት) መመልመልና ለቅኝ ግዛት መስፋፋት ፍላጎቷ መጠቀም ነበር፡፡ በጥቁር ሸሚዝ ለባሽነት የሚታወቁት ኤርትራ የተመለመሉ አስካሬዎች (ወታደሮች) በሊብያ ትሪፖሊ እንዲሁም በምቃዲሾ በወቅቱ የሃገሪቱ ተወላጆች ለነፃነታቸው ያደርጉት የነበረውን ትግል ለመደፍጠጥ ዘምተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ጣልያን ከሌሎች ቅኝ ግዛቶችዋ በተለየ በርከት ያሎ ወታደሮች ያሉበት ከፍተኛ ጦር ምንጭ የሆነ ግዛት ፈጥራ ነበር፡፡ ስለዚህ በኤርትራ የተፈጠረው የጦር ምንጭነት ታሳቢ የተደረገ ቅኝግዛት ምስረታ ከሌሎች የጣልያን ቅኝ ግዛቶች በተለየ የትምህርት ደረጃው እስከ 4ኛ የሚደርስ እንዲሁም በከፍኛ የንፅፅር ፕሮፓጋንዳ ስለነፃነቱ የማያስብ ይልቁን በጣልያን በመገዛቱ ካካባቢ ህዝቦች በተለይ ከደቡብ አዋሳኞቻቸው የበለጠና የሰለጠኑ እንደሆኑ እንዲያስቡ በሚያደርግ አስተሳሰብ ህብረተሰቡን ገንብቶ ነበር፡፡

ይህ የቅኝ ግዛት እሳቤን መሰረት ባደረገ እና የኤርትራን ህዝብ አግቶ መያዝ የሚያስችል፤ አቶ ዮሴፍ ገ/ሂወት እንደሚለው የቅኝ ገዥዎች ቦታ ለመተካት የሚጥርና ካርታ (ወሰን) አምላኪ ፖለቲካዊ ልሂቅ ተፈጥሮ ኤርትራን ወደ ትልቅ እስርቤት ቀይሯት ይገኛል፡፡ ከዚህ አይነቱ ልሂቅ ጋር የሚደረግ ማንኛውም ውል ይሁን ድርድር ሊታይ የሚገባው በጥንቃቄ እንዲሁም በወትሮ ዝግጅነት (vigilantly) መሆን አለበት፡፡ ምክያቱም ዋና አላማው በስሩ ደፍጥጦ የያዘውን ህዝብ የዘልአለም ተገዥ ማድረግ እንጂ አገራዊ ጥቅም ፍለጋ አይደለም፡፡

በኔ እይታ ኤርትራ ኢትዮጲያን የወረረችው ቋሚ ጠላት ፍለጋና ህገመንግስት፣ መብት፣ እድገት ወዘተ የመሳሰሉ የሰለጠነ ማህበረሰብ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች የኤርትራ ህዝብ ቢያነሳ “አገሪቱ ጦርነት ላይ ስለሆነች አትመልስላችሁም” የሚል ፖለቲካዊ እሳቤ ተይዞ የተደረገ ወረራ ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጲያና  የኤርትራ ግጭት ሊያበቃ የሚችለው፡-

1/ የኤርትራ መንግስት ማንነቱን ቀይሮ ሰላማዊ ከሆነ (በኔ እምነት የኤርትራ መንግስት የመጀመሪያ ምርጫ አይደለም)

2/ የኤርትራ መንግስት ወርዶ ሌላ ከጎረቤት አገሮች ጋር በሰላም የሚኖር መንግስት ከተመሰረተ

3/ የኤርትራ መንግስት ማንነቱን ሳይቀይር ነገር ግን በኢትዮጲያ መንግስት፤ በአለማቀፍ ማ/ሰብ እና በዲፕሎማሲያዊ ማህረሰብ ጫና ውስጥ ከገባ ብቻ ነው፡፡

በተራ ቁጥር 1እና 2 ያስቀመጥኳቸው ይሆናሎች (scenarios) ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት ስለሚመቹ በትልቁ የሚጠበቀው የኢትዮጲያ መንግስት አሁን ካለው የኤርትራ መንግስት ባሻገር (post PFDJ) በማሰብ በለውጥ ሂደቱና በዝምድና ግንባታው ላይ ሚና ሊኖረው ይችላል፡፡ በመሆኑም በዚህ ፅሁፌ ብዙም ትኩረት ልሰጥባቸው የምፈልግ ኩነቶች አይደሉም፡፡

ነገር ግን የኤርትራ መንግስት ተገዶ ወደሰላም አማራጭ ሊመጣ የሚችው፡-

1/ የኢትዮጲያ መንግስት በአለማቀፍ ማበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያለውና የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ህብረትን ያካተተ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ሲችል

2/ የኢትዮጲያ መንግሰት ሃይሉን አደራጅቶ አስገዳጅ ወታደራዊ ጫና መፍጠር ሲችል (ይህ አማራጭ የኢትዮጲያ መንግሰትም ይሁን የአለማቀፍ ማህረሰብ ሊመርጡት የሚችሉት አማራጭ አይመስኝም)

3/ በተራ ቁጥር 1 የጠቀስኩት እንዳለ ሆኖ የኢትዮጲያ መንግሰት (ኢህአዲግ) በአልጀርስ ስምምነት መሰረት ችግሩን ለመፍታት መንቀሳቀስ ሲችል

ኢትዮጲያ ኤርትራ እና የአልጀርስ ስምምነት ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የኤርትራ መንግስትን ሊያስገድዱ ከሚችሉ አማራጮች ውስጥ በአልጀርስ ስምምነት መሰረት ተግባራዊ ለማድረግ መንቀሳቀስና አለማቀፋዊ ተፅእኖ እንዲጨምር በማድረግ ግጭቱን ወደ አስገዳጅ መፍትሄ እንዲያመራ ማድረግ ነው፡፡

የአልጀርስ ስምምነት በዋናነት ያሰፈራቸው ተደራሽ አላማዎች፡-

1/ ግጭትን ማስወገድ (cessation of hostilities)

2/ በጦርነቱ የተፈናቀሉት ሰዎች መልሶ ማቋቋምን(resettlement of displaced persons)

3/ አገሮቹ ከጦርነቱ እንዲያገግሙና ሰላም እንዲያመጡ (rehabilitation and peace building in both countries)

የሚሉ መሰረታዊ አላዎች ያሉት ሲሆን ፤ ከላይ የተጠቀሱት አላማዎች ለማሳካትም በስምምነቱ አንቀፅ አንድ መሰረት ወታደራዊ ግጭቶችን እንዲያስወግዱ እንደዚሁም ለስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ተገዥ በመሆን ፀብ አጫሪነትን እዲያቆሙ ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም በግጭት መንስኤ ነው ተብሎ በአንድ ወገን (በኤርትራ መንግስት) የቀረበው የወሰን ግጭት መርምሮ እልባት የሚሰጥ የድንበር ኮሚሽን (boundary commission) እንዲቋቋም ሲጠይቅ ወረድ ብሎም በግጭቱ ወቅት የደረሰውን የማህራዊና ኢኮኖሚያዊ መናጋትን መሰረት በማድረግ ገምግሞ መፍትሄ/ ካሳ የሚወሰን የካሳ ኮሚሽን እንዲያቋቋም ይጠይቃል (ተስምምተዋልም)::

ስለዚህ የአልጀርስ ስምምነት ዋና አላማው በሁለቱ አገሮች ሰላም መፍጠር እንዲችሉ ነው፡፡ ሰላም ሲፈጠር የተበደለ ይካሳል የተወሰደ መሬት ካለ ይመለሳል በመሆኑም አገሮቹ ህዝቻቸውን ወደ መልካም ጉርብትና (nominalization) እንዲያመጡ ያለመ ስምምነት ነው፡፡

ይህን የአልጀርስ ስምምነት ተከትሎ የተቋቋመው የድንበር ኮሚሽን በተቀመጠለት መሰረት ወይንም ከተቀመጠለት ውጭ በመሄድ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ የተላለፈውን ውሳኔ የኢትዮጲያ መንግስት በከፊል ባለመቀበሉ ምክንያት እስከ አሁን ሲጓተት ቆይቶ አሁን ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተቀበለው ለመሆኑ ገልጧል፡፡ (ይህን ፅሁፍ አስከምፅፍበት ጊዜ የኤርትራ መንግስተ ይፋዊ መግለጫ አልሰጠምም)

ኢትዮጲያ የአልጀርስን ስምምነት መሰረት በማድረግ የድንበር ኮሚሽን ውሳኔ በመቀበሏ ሊፈጠሩ የሚችሉ ይሆናሎች (scenarios)

1/ የኤርትራ መንግስት ኢትዮጲያ የኮሚሽኑን ውሳኔ መቀበሏን አምኖ ወደ ሰላም ሂደቱ በመግባት የወሰን ማስከበር ሂደት ውስጥ መሳተፍ

2/ የኢትዮጲያ ውሳኔ ባለመቀበል ወደ ሰላም ሂደቱ አለመግባት

3/ ተቀብያለሁ ወይንም አልተቀበልኩም ሳይል መቆየት ናቸው፡፡

1)  የኢትዮጲያ ውሳኔ መቀበል

ከላይ በመግቢያየ እደገለፅኩት የኤርትራ መንግስት ህልውና የሚንጠለጠለው ባለው ዴሞክራሲያዊ ባህሪ ልማታዊነት ወይንም የመልካም መንግስትነት ባህሪ አይደለም፡፡ ነገር ግን በቋሚ ጠላት መኖር ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጲያን ውሳኔ ተቀብያለሁ ካለና ወደ ሰላም ሂደቱ ውስጥ የሚገባ ከሆነ፡-

* ከጦርነቱ ጥቂት አመታት በፊት ጀምሮ የሚያካሂደውን የማያቋርጥ የውትድርና አገልግሎት (conscription) እንዲያበቃ ከህዝብ ከፍተኛ ግፊት ይመጣበታል

* የኤርትራ ጦር ከጦርነቱ ጀምሮ ባለማቋረጥ በምሽግ ውስጥ የመኖር ልምድ ብቻ ያለውና  በከፍተኛ የልብስ፣ የቀለብ እንዲሁም የትጥቅ እጥረት ጫና ላይ ያለ ወታደር ስለሆነ፣ ከምሽግ ወጥቶ በካምፕ እንዲኖር ቢጠይቅ በገፍ ሰፈሩን ለቆ በመሄድ አገሪቱ ወታደር አልባ የመሆን እጣ ፋንታ ስለሚገጥማት የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ የሰራዊት እጥረት ውስጥ ይገባል፡፡ በመሆኑም ለተቃዋሚ ሃይሎች ጥቃት በቀላሉ ይጋለጣል ውድቀቱንም ያቀላጥፋል፡፡

* የኤርትራ ህዝብና የኤርትራ ጦር እስካሁን በእግት (hostage) ውስጥ እንዲኖር ያደረገው መሬታችን በወያኔ (በኢትዮጲያ) ስለተወረረብን ነው እየተባለ ነው፡፡ ነገር ግን ይህን ጉዳይ ከተፈታ የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጲያ ጋር ባለው ግጭት እያሳበበ መኖር ስለማይችል ህዝቡ የመብት፣ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና የህገመንግስታዊ ስርዓት መመስረትን መንግስቱን አጥብቆ ስለሚታገለው ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይወድቃል፡፡

ስለዚህ የኢትዮጲያ መንግስት የድንበር ኮሚሽኑን በአልጀርስ ስምምነት መሰረት መቀበልና ይህን ተከትሎ የኤርትራ መንግስት የኢትዮጲያን ውሳኔ ተቀብሎ ወደ ሰላም ሂደቱ መግባት የባህሪ ለውጥ አድርጎ ሊቀበለው ይችላል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ተቀብሎ ለመሄድ ከሞከረም ለኤርትራ የለውጥ ሃይሎች ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ ስለሚፈጥር በኤርትራ መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ ያበረታታል፡፡

(ይህ ሂደት በኢትዮጲያ መንግስት ላይም ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ በሚቀጥው ፅሁፌ እመለስበታለሁ)

2/ የኤርትራ መንግስት የኢትዮጲያን ውሳኔና ጥሪ አለመቀበ

የኤርትራ መንግሰት የአልጀርስን ስምምነት መሰረት በማድረግ የኢትዮጲያ መንግስት መቀበሉን በመግለፅ ያቀረበው የሰላም ጥሪ አልቀበልም ሊል ይችላል፡፡ ጥሪውን ላለመቀበል ከሚያስቀምጣቸው ምንያቶች ውስጥ በመዘግየቱ ምክንያት ጉዳት ደርሶብኛል በማለት ነው፡፡ ቢሆንም ግን ግጭቱ እልባት አግኝቶ ወደ ተለመደ ሰላማዊ ሂወት መመለስ የሚፈልገው የኤርትራ ጦር መንግስት በወትድርና ለማቆየት ሲል የፈጠረውና ችግር መፍታት የማይፈልግ መሆኑን ሲያውቅ ምሽግ ውስጥ ድንበር መጠበቁን እየተወ የመፍረስ እድሉ ይጨምራል፡፡ ከህዝብ በኩልም ከፍተኛ ጫና ይደርስበታል፡፡ ከነዚህ ሁሉ በበለጠ ግን የኢትዮጲያ መንግስት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ድል በሚያገኝበት መንገድ ሊንቀሳቀስበትና የኤርትራን መንግስት አሁን ካለበት መገለል ተጨማሪ ጫና ውስጥ እዲገባ ማድረግ ይችላል፡፡ ኤርትራ መንግስት የሰላም ሃይል አለመሆኑንም ስለሚያሳይ በተለይ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤት ኢትዮጲያ ያላትን ተሰሚነትና ወንበር በመጠቀም ተጨማሪ ጠንከር ያለ ማእቀብ እዲጣልባት ለመስራት ልትጠቀምበት ትችላለች፡፡ በተመሳሳይ በአፍሪካ ህብረትምና ከአካባቢያዊ መንግስታት(IGAD) ተፅእኖ በተጨማሪ የኤርትራ መንግስትን ጫና ውስጥ መክተት ይቻላል፡፡

የኤርትራ መንግሰት በአልጀርስ ስምነት መንፈስ መሰረት ሰላም ሊፈጥር የሚችለውን ጥሪ እና እርምጃ ባለመቀበሉ ምክንያት በማድረግ የኢትዮጲያ መንግሰት ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ውድቅ (null and void) መሆኑን በማወጅ እስካሁን የተሰራውን ስህተት ከማረም ጀምሮ ሂደቱን እንደ አዲስ ወደ ነበረበት የመመለስና በተስተካከለ መንገድ የመውሰድ እድል ያገኛል፡፡ ይህን ውሳኔ ለመወሰን ከፍተኛ ዲፕሎማሲ እንደዚሁም የተጠናከረ ራስን የመከላከል አቅም የመግንባት ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡

3/ የኤርትራ መንግስት መልስ ሳይሰጥ በዝምታ መቆየት መምረጥ

ይህ አጋጣሚ ሊኖር የሚችል ይሆናል ሲሆን ነገር ግን የኢትዮጲያ መንግሰት ተጨማሪ ጥረቶችን በማድረግና የጊዜ ገደብ እንዲሁም አስገዳጅ እርምጃዎች በመውሰድ የኤርትራ መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ይቻላል፡፡ ከነዚህ ውስጥ የኢትዮጲያ መንግስት ከተባበበሩት መንግስታትና ከአፍሪካ ህብረት ለተወጣጣ ሞግዚት (care taker team) ባድመን እንደሚያስረክብና የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክርቤትና የአፍሪካ ህብረት የሰላም ሂደቱን በማፋጠን እንዲሁም በአልጀርስ ስምምነት ወቅት በእማኝነት የፈረሙት አገራት በኤርትራ መንግስት ላይ ጫና እንዲፈጥሩ መጋበዝና ተፅእኖ ጨዋታው አካል እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ (ይህ ውሳኔ ለመወሰን የኢትዮጲያ መንግሰት ድፍረቱና ማስተዋሉ ሊኖረው ይገባል)

በተጨማሪም የኤርትራ ተቃዋሚ ሃሎችን በከፍተኛ ደረጃ በማገዝና ተደራጅተው አማራጭ ኤርትራ መንግስት የመሆን ተስፋቸው እንዲጠነክር በማድረግ የኤርትራ የስደት መንግሰት (exile government) እንዲያቋቁም በማድረግ በኤርትራ መንግስት ላይ ወታደራዊ፣ ፓለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ማሳደር ብሎም የኤርትራ መንግሰት መውደቁ ስለማይቀር መንግስት አልባ አገር ተፈጥሮ በኢትዮጲያ ላይ ሌላ የሶማሊያዊ ጫና (somalization) እንዳያጋጥም አስቀድሞ መከላከል ወይንም ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይሆናል፡፡

ለማጠቃለል

አሁን በቅርቡ የኢህአዴግ መንግስት በወሰደው ውሳኔ መሰረት ከተሄደ የጨዋታው ኳስ ከኢትዮጲያ ተለግታ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ እግር ስር ትገኛለች፡፡ ከላይ የዘረዘርኳቸው ሶስቱም ይሆናሎች የኤርትራን መንግስት አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት የአቶ ኢሳያስን መንግስት ውድቀት በማፋጠን ለአካባቢው ብሎም ለኢትዮጵያን ስላም በዘለቄታው ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በመሆኑም የኢትዮጲያ መንግስት ቀጣይ ሊሆኑ የሚችሉ የሆናሎች (possible scenarios) በመገምገም ራሱን ለዘላቄታዊ መፍትሄ ማዘጋጀት ያለበት ይመስለኛል፡፡

*********

Guest Author

more recommended stories