ግጭትና ምሁራን፤ ባለሁለት ገጽታ ፍላጎት (The ambivalent interest)

(ገ/መድህን ሮምሃ (ዶ/ር)

የህዝብ ዥንጉርጉነት፤ ማስወገድ አይቻልም፡፡ ከሰፊው ህዝብ ውስጥ፤ ጥቂት ስለህዝብ የሚሠው ይፈልቃሉ፡፡ በአንጻሩ ከሰፊው ህዝብ ውስጥ፤ ጥቂት ግለ ሰቦች ለራስ ጥቅም የሚሸነፉ፤ ህዝብ ሊያጠፉ የሚችሉ ይፈጠራሉ፡፡ የግጭት ወይም የጦርነት ተዋናዮች ቢያንስ አንዱ ግንባር ወይም አንዱ ተጋጣሚ ህዝባዊነት ስሜት አይኖረውም፡፡ አንዳንዴ እንደዕድል ሆኖ ሁለቱ ግንባር የህዝባዊነት ስሜት የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ጦርነት ወይም ግጭት የሚለኰሰው ለራስ ጥቅም በማሰብ ብቻ ሊሆን ይችላል ወይም ለህዝብ ድህንነት ተብሎም ጦርነት ይታወጃል፡፡ ያም ሆነ ይህ፤ በመጨረሻ ህዝቡ በአሸናፊው ኃይል መዳፍ ውስጥ ይወድቃል፡፡ እንደኢትዮጵያ የመሳሰሉት ሀገሮች ማለትም ብዙ ባህላዊ ልዩነቶች ያላቸው ህዝቦች ያሏቸው እና ብሔረ መንግስት ግንባታ ያላጠናቀቁ ሀገሮች፤ ዜጎቿ በአንድነት ለሰላምና ለመለወጥ ካልቆሙ፤ ህዝቦች ይበታተኑና በድህነት ወደ ታጀበ ጦርነት ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ በተለይ በዙህ ረገድ የመንግስትና የምሁራን ሚና ከፍተኛ ይሆናል፡፡

አሁን በሃገራችን እየተከሰተ ያለው ብሔር ተኰር ግጭት ወይም ብጥብጥ፤ ግብአት የሚያገኘው ከሁለት ግንባር መሆኑን ጥርጥር የለውም፡፡ ከመንግስትና ከሌሎች ሃይሎች፡፡ መንግስት፤ ብሔር ተኰር ህገ መንግስትና ፖሊሲ እንደሌለው የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን የአንድን ሀገር ህገ መንግስት ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ቢያሟላም፤ ያለተዋናይ የ‘ቅዱሳን’ ድርሳን ከመሆን የዘለለ ትርጉም አይኖረውም፡፡ የቅዱሳን ድርሳን፤ ቅዱሳን ራሳቸው ከማሞገስና ማወደስ አልፎ ለህዝብ ጥቅም አይሰጥምና ወይም የህዝብ ችግር አይፈታምና፡፡ በመሆኑ ይህ ለህዝብ ስልጣን የሰጠ ህገ መንግስት ስላለን ብቻ ከችግር ሊያስተርፈን አይችልም፤ አላስተረፈንምም፡፡ ህግ መንግስታችን ብዙኀኑ የሚስማሙበት ቢሆንም፤ መንግስት (ገዢ ፓርቲው) ራሱ ይፋ እንዳደረገውም፤ በተፈጠረው የአፈጻጸም ችግር፤ ግጭት እንዲከሰት በር ከፍቷል፡፡ መንግስት፤ ግጭትን መከላከል ሆነ መቆጣጠር አልቻለም (የመንግስት ሚና እንተወውና ወደ ርእሰ ጉዳያችን እንለፍ)፡፡

ዛሬ ብሔር ተኰር ግጭት እንዲፈጠር ቅስቀሳ የሚያደርጉ ሃይሎች ከተለያየ አቅጣጫ ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህ ሃይሎች በብሔር ግጭት ቅስቀሳ ላይ የተሰማሩ፤ የመንግስት ድክመትን በመጠቀም ነው፡፡ ዛሬ፤ በርከት ያሉ ምሁራንና የፖለቲካ ‘አክቲቪስቶች’፤ የእነዚህ ሃይሎች ፖሊሲ ሲያንጸባርቁ በገሃድ ይታያሉ (እዚህ ጋር ሊሰመርበት የሚገባው፤ አወንታዊ አስተዋጽኦ ያለው ምሁር የለም ማለቴ እንዳልሆነ ነው)፡፡ ብሔር ተኰር ግጭት እንዲፈጠር ቅስቀሳ እያደረጉ ነው፡፡ በተለይ አሁን ላይ እየተንጸባረቀ ያለው የምሁሩ ባለሁለት ገጽታ ፍላጎት (The Ambivalent interest)፤  ህዝቡ በማዳናበር ለግጭቱ መንስኤ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ ይህ፤ ባህርይ በፖለቲከኞችም በአያሌው እየተንጸባረቀ ነው፡፡ ዛሬ በሃገራችን በህዝቡም እንደባህል ተጋብቶበት ይስተዋላል፡፡

‘ባለሁለት ገጽታ ፍላጎት’ ያልኩበት ምክንያት፤ ምሁሩ በአንድ በኩል ስለኢትዮጵያዊነት ይሰብካል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔረ ሰቦች እርስ በእርሳቸው የሚያጋጭና የሚለያይ መርዙ ይረጫል፤ ባለሁለት ገጽታ ፍላጎት፡፡ የመጽሐፉን አሉታዊ ጎኑን ለግዜው እናቆየውና፤ ሞቲ ቢያ (2009) ‘የኦሮሞ ጥያቄና ፈተናዎቹ’ በተሰኘ መጽሐፉ፤ የዚህ ዓይነት ባህርይ ‘የአንድነት ስም እየጠሩ ለበላይነት ለቅሶ’ በማለት ገልጾታል፡፡ ባለሁለት ገጽታ ፍላጎት ነጸብራቅ ያላቸው ሰበካዎች ጥቂት እንደአብነት ወስደን እስቲ እንይ፡፡

የምሁራኑ ትችት፤ እውነታ ይኑረው አይኑረው ከፖለቲካዊ ድርጅት ጋር የተያያዘ ብቻ ከሆነ፤ እዚህ አላካትትም፡፡ የጽሁፉ ዓላማ እስካልሆነ ድረስ፡፡ እዚህ ለመዳሰስ የፈለግኩት ከህዝብ ጋር ንኪኪ ያላቸው ብቻ ጥቂቶቹ በማንሳት ነው፡፡ እዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተካተቱ የምሁራኑ ትችት፤ በግዜ ቅደም ተከተል ለማስቀመጥ ተሞክሯል፡፡

በመጀመርያ ስለፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌ ጽሑፎች፤ የተወሰኑትን እናንሳ፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው ስለኢትዮጵያ አንድነት ያላቸው ጥልቅ ስሜት በተለያዩ ጽሑፎቻቸው ይገልጻሉ፡፡ ለአብነት የኤርትራ መገንጠል በሰሙ ግዜ ስሜታቸው የገለጹበት ስንመለከት፤ ‘መላይቱን ኢትዮጵያ ‘እናት ሀገር’ ካልኩና ካደረግሁ በኋላ ኤርትራ ተገነጠለች ማለትን ስሰማ መርዶ የሰማሁ ነው የመሰለኝ፡፡ ስሜቴን ደጋግሜ ጻፍኩ፤ ሐዘኔን ማንገፍ ግን አልቻልኩም’ (ጌታቸው ሃይሌ፤ 2006) በማለት በኤርትራ ምክንያት ጥልቅ ሐዘናቸው ይገልጻሉ፡፡ ፕሮፌሰር ጌታቸው የኢትዮጵያ ህዝቦች ልዩነትን አስወግዶ የጋራ ብሔራዊ ማንነት በመገንባት፤ እንዴት አብሮ መኖር እንደሚችል ያስገነዝባሉ፡፡ ተስፋ ያልቆረጠ በሚመስል አንጀታቸው፤ ወደ ፊት ኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የምትቀላቀልበት መንገድ ያሳያሉ፤ አባታዊና ምሁራዊ ምክር ጭምር በመለገስ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ፕሮፌሰር ጌታቸው፤ ብሔረ ሰቦችን በማቃቃር፤ ግጭትና ብጥብጥ የሚያነሳሱ ጽሑፎች ያሰራጫሉ፡፡ ‘ወያኔን በኢትዮጵያውያን ህዝብ ፊት የምቃወምበት መድረክ ስቸገር አቶ ኤልያስ ክፍሌ የሚባል ወጣት ስልክ ደውሎ ኢትዮጵያን ሪቪው (Ethiopian rieview) የሚባል የፖለቲካ መጽሔት ማቋቋሙን፤ ከአማካሪዎቹ አንዱ እንድሆን መፈለጉን፤ እንድጽፍም ነገረኝ፡፡ የሚያወጣቸው ዜናዎች ትኩሶች፤ ድርሰቶቹ የሚመሰገኑ ሆነው አገኘኋቸው፡፡ ከዚህ የተሻለ መድረክ ከየት ይመጣል? እያከታተልኩ መጻፍ ጀመርኩ’ (ጌታቸው ሃይሌ፤ 2006)፡፡ የጽሑፉ ርዕስም ‘Violation of Human Rights of Ethiopians by the Tigray People’s Liberation Front’ ይላል፡፡ ቀጥሎ ባለው ዌብሳይት (http://www.ethiopians.com/getachew.html) ሰፍሮ የሚገኘው ጽሑፍ ግን ወያኔን የሚቃወም ብቻ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያጣላና የሚያጋጭ ጭምር ነው፡፡ የጽሑፉ ይዘት ቀጥለን እንመልከት፡፡

‘…ባለፈፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ (ጽሑፉ የታተመው በ1989 ዓ.ም አከባቢ መሆኑን ነው)፤ ኢትዮጵያ በህወሐት መሪነት፤ በጥቂት ቡድን ኢትዮጵያውያን ከተወሰኑ የቀድሞ ኢትዮጵያውያን ጋር በመተባበር ዕርቃኗ እስክትወጣ ተዘርፋለች፡፡ ህወሐት፤ የሌሎች የሁሉ ኢትዮጵያውያን ጥረት ውጤት የሆነውን የሀገሪቷን ሃብት፤ ከኢትዮጵያ ህዝብ ነጥቆ፤ ለግብረ አበሮቹና ለትግራይ ወሰደላቸው፡፡ ለራሱም ወሰደ…፡፡’ የቀድሞ ኢትዮጵያውያን እና ግብረ አበሮቹ የተባሉት ኤርትራውያን መሆናቸው ነው፡፡

ፕሮፈሰር ይቀጥላሉ፤ ‘…በደርግ የተወረሱ ቤቶች፤ ህወሐት በትግራይ ለባለቤቱ መልሰዋል፡፡ የአብዛኛውን የሌሎች ክልሎች ህዝብ ግን አልተመለሰም፡፡ በመንግስት ምስራቤቶች ቅነሳ በማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቀጣሪዎች አባሯል፡፡ ነገር ግን ከጥቂት ቀኖች በኋላ ለትግሬዎችና ለኤርትራውያን ብቻ ስራቸው መልሰው ሰጧቸው፡፡ ባንዲት አፍሪካዊት ሀገር በህክምና ትምህርት ቤት የሚያስተምር ጓደኛየ እንደነገረኝ፤ ከኢትዮጵያ ለህክምና ትምህርት ስኮላርሺፕ የተላኩ የሁሉም ተማሪ ስም የትግሬዎች ነበር፡፡ ከሌሎች ብዙ ሀገሮች ተመሳሳይ ሪፖርት ደርሶኛል፡፡ የህወሐት የኢትዮጵያ ትምህርት ዓላማ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ትግሬዎች ብቻ ለማሰልጠን ነው፡፡ ህወሐት ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያን ዳኞች በማባረር፤ በምትካቸው ትግሬዎች ብቻ ቀጥረዋል…’ ይሉናል ፕሮፌሰር፡፡

ሁለተኛው ምሁር፤ ከላይኛው ተመሳሳይ ጽሑፍ ያሳተመ፤ ዳንኤል ክንድየ (2003) ነው፡፡ የመጣጥፉ ርዕስ፤ ‘The Causes of the Failure of the Present Regime in Ethiopia’ ሲሆን፤ የታተመው ደግሞ በ‘International Journal of Ethiopian Studies’ በሚል መጽሔት በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ጽሑፉ፤ በመጀመርያ የኢትዮጵያ ታሪካዊ አመጣጥ ከህዝቡ አንድነት ጋር እያገናኘ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔረ ሰቦች ለኢትዮጵያውያን አንድነት ያበረከቱት አስተዋዕጽኦ በበጎነት ይሰብካል፡፡ ዳንኤል፤ የኢትዮጵያውያን አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ከጽሑፉ መረዳት ይቻላል፡፡ የዛሬ ገዢ ፓርቲ ፖሊሲ የሆነውን ብሔረ ሰብ መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም፤ ‘ለአንድነታችን ጠንቅ ነው’ የሚል ጽኑ እምነቱ ይገልጻል፡፡ ይህ ፖሊሲ ለስርዓቱ ውድቀት ዳርጎታል ብሎ ይከራከራል፡፡ በመጨረሻ፤ ለወደፊት የኢትዮጵያውያን አንድነት ሊያስቀጥል የሚችል መንገድ ያሳያል፡፡ እነዚህ ሁሉ በአዎንታዊ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ዳንኤል ቀጥሎ ምን አለ? መጣጥፉ የታተመው፤ ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ከ12 ዓመታት በኋላ መሆኑን ነው፡፡ በመጀመርያ ልክ እንደ ፕሮፌሰር፤ ዳንኤልም እስከአሁን የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ‘ህወሐት’ እያለ ይጠረዋል፡፡ እንደዳንኤል እምነት ባለፉት አስራሁለት ዓመታት (መጣጥፉ እስኪታተም ድረስ) በኢትዮጵያ አንዲት በጎ ነገር አልተሰራችም፡፡ ሁሉም ነገር መጥፎ ነው፡፡ ሐላፊነቱ ደግሞ ጠቅልሎ ለህወሐት ይሰጠዋል፡፡ ከፖለቲካዊ ፓርቲ ጋር የተያያዙ ቢሆኑም፤ እንደዚህ ዓይነቶች ከሐቅ የራቁ ፕሮፖጋንዳዎች ከግጭት አያስተርፈንም፡፡ ነገር ግን ከላይ ለመጠቆም እንደሞከርኩት፤ እዚህ መዳሰስ የተፈለገው ከህዝብ ጋር ንኪኪ ያላቸው ብቻ ስለሆነ፤ ወደ ጉዳያችን እንለፍ፡፡

ትምህርት በተመለከተ፤ በፊት በትምህርት ገበታ የነበሩ ልጆች፤ ኢህአዴግ (እንደሱ አባባል ህወሐት) ወደስልጣን እንደመጣ፤ ከትግራይ ውጭ የሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ልጆች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ትምህርት ማቋረጣቸው ይገልጻል፡፡ አንዱ ምክንያት፤ የመማርያ ቋንቋ በብሔረ ሰቡ ቋንቋ በመሆኑ ልጆች ከትምህርት ማቋረጣቸው ይገልጻል፡፡ የቁሳቁስ ችግር እንደነበረም ያመለክታል፡፡ በትግራይ ግን በአንጻሩ ‘መንግስት (ህወሐት ማለቱ ነው) ብዙ ማራኪ የሆኑ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች ገንብተዋል፡፡ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ደግሞ ኮምፒተር ገብቶላቸዋል’፡፡

ሌላው፤ 42 የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች /መምህራን/ ያለ ምንም ምክንያት፤ የሌሎች ብሔረ ሰቦች አባላት ስለሆኑ ብቻ፤ ከስራቸው ተባረዋል፡፡ ‘አዲስ የስራ መዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም በመጠቀም፤ ከትግሬዎች ውጭ ብዙ ኢትዮጵያውያን ከስራቸው ተባረሩ፡፡ ከነዚህ ውስጥ፤ 10,000 የትምህርት ቤት መምህራን፣ 10,061 የኢትዮጵያ ህንጻ ግንባታ ባለስልጣን ቅጥረኞች፣ 3,400 የቤቶች ባለስልጣን፣ 56,000 ስቪል ሰርቫንት፣ 300,000 የመከላከያ አባላት እና የመሳሰሉትን ናቸው፡፡ …ከአለማቀፋዊ ማህበረ ሰብ በብድርና ስጦታ ለኢትዮጵያ የተሰጠ ሚልዮኖች ዶላሮች ተጠልፎ፤ ለመሪዎች ወይም ለትግራይ ልማት ይውላል’ ይለናል ዳንኤል፡፡

ቀጥለን፤ ሞቲ ቢያ (2009) ‘የኦሮሞ ጥያቄ እና ፈተናዎቹ’ በተሰኘ መጽሐፉ የሰነዘረው ትችት ባጭሩ እንመልከት (የሞቲ ሞያ መጽሐፍ የታተመው በ2009 ዓ.ም ቢሆንም፤ ጽሑፎቹ በ1980ዎቹና በ1990ዎቹ በመጽሔት መውጣታቸው በመጽሐፉ መግቢያ ተገልጿል)፡፡ ሞቲ ቢያ፤ እንደላይኞቹ ጠንከር ያለ የአንድነት (የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረ ሰቦች አብሮ መኖር) ስሜት በጽሁፉ አያንጸባርቅም፡፡ የአንድነት ፍላጎቱ ብልጭ የሚልበት፤ ኦነግ መንግስትነት ከተረከበ ብቻ ነው፡፡ እንደ ሞቲ ቢያ እምነት፤ ዛሬ የኦሮሚያ ህዝብ በህወሐት ተጨቁኖ የሚኖር ህዝብ እንጂ የኦሮሚያ ህዝብ የሚወክል ፓርቲ በሀገሪቱ የለም፡፡ በመሆኑ ህወሐትን ልክ እንደ ቅኝ ገዢ አድርጎ በመቁጠር፤ የህወሐት ድርጊትና የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነትን እንዲህ ሲል ያወግዛል፡፡

‘…ከኦሮምያ የስኳር ምርት ከመቶ ፐርሰንት በላይ እያተረፉ በብዙ ቢልዮን ብር በልዩ ባንክ የሚያስቀምጡና የክልላቸውን ልማት በማጣደፍ ላይ የሚገኙ የፖለቲካ አገዛዙ ‘የእንጀራ አባቶች’ ናቸው፡፡ የኦሮምያን ከተሞች በድቅድቅ ጭለማ ተውጠው እያሉ፤ ከኦሮምያ ወንዞች በተገኘ ሃይል በክልላቸው የታላላቅ ዘመናዊ እንዱስትሪ የኤሌክትሪክ ፓዎሮችን እየተከሉ ያሉ ‘ስትራተጂክ ዘራፊዎች’ ናቸው፡፡ …በትግራይ ልማት ማለት ትላልቅ ዩኒቨርስቲዎችን መገንባት፤ ኢንዲስትሪ አምራች እንዱስትሪዎችን መትከል፤ ከመሬት መንቀጥቀጥ የአደጋ ክልሎች የፀዱ የከፍተኛ ኃይል የኤሌክትሪክ መስመሮችን መዘርጋት፤ ለትግራይ ተወላጆች ከቢሮክራሲዊና ከባንክ ነፃ የሆነ የፋይናንስ ብድር አገልግሎት መስጠት…ወዘተ ሲሆን፤ በኦሮምያ ክልል ሌላ ነው፡፡ በኦሮሚያ ትልቁ ልማት የገጠር ጤና ጣቢያዎችን መገንባት ሲሆን፤ በትግራይ የጤና ኮሌጆችን መሥራት ነው፡፡ …በትግራይ የወርቅ ማዕድናት የተጠናከሩ ፍለጋዎችን ማካሄድ ልማት ሲሆን፤ በኦሮሚያ ‘የተበታተነ አኗኗር ለወንበዴዎች የተመቸ ነው’ በማለት የገበሬ ጎጆዎችን ማፍረስና የገጠር መንደሮችን መመሥረት ነው፡፡ በቅርጽ ያሸበረቀ፣ ግልብና ተራው ልማት ለኦሮሚያ ተመድቧል…’ እያለ፤ ሞቲ ቢያ ነቀፌታውን ያዥጐደጕደዋል፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፤ መንግስት ወይም አንድ ገዢ ፓርቲ፤ በልኩ መሰረት እየተቹ መስመር በማስያዝ ወይም ከስልጣን በማውረድ፤ የህዝብ አለኝታ ከመሆን ባሻገር ጠንካራ ስርዓት ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረግ ምሁራዊ ግዴታ እንደሆነ እስማማበታለሁ፡፡ ከላይ እንደአብነት የተጠቀሱ የምሁራን ስራዎች፤ ስለትግራይ ህዝብ በተመለከተ የሰነዘሩት ትችቶች ግን፤ ለኢትዮጵያውያን መርዳት ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ጉዳት ብቻ ሳይሆን ህዝብ ወደ እርስ በእርስ ግጭት በመጋበዝ ሀገርና ህዝብ የሚበታትን ነው፡፡ እዚህ ጋር መታወቅ ያለበት፤ ኢህአዴግ (እንደምሁራኖቹ አባባል ህወሐት) እንደመንግስት፤ ምሁራኖቹ በገለጹት ዓይነት በህዝቦች መካከል አድሎ ቢፈጽም ኖሮ፤ እንደእኔ ዕይታ፤ የምሁራኖቹ ትችት የሚደገፍ ነበር፡፡ ህልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርምና ግጭት ተፈርቶ የሚተው ጉዳይ ስላልሆነ፡፡

ነገር ግን የተነሱ ጉዳዮች ፍጹም ከሐቅ የራቁ በመሆናቸው፤ በዚህ ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ምክንያት አንዱ ብሔር በሌላው ብሔር በሚሰነዝረው ጥቃት፤ በመካከላቸው የቂም ሐውልት ይገነባና የወደፊት የህዝቦች አብሮ መኖር ጠንቅ ይሆናል፡፡ ዛሬ በህወሐት አሳብቦ በትግራይ ህዝብ ላይ ጥቃት እየተፈጸመ ነው፡፡ ይህ ጥቃት የነዚህ ጽሑፎችና መሰሎቻቸው የሐሰት ፕሮፖጋንዳ የግባቸው ውጤት ነው፡፡ ይህ ከሐቅ ፍጹም የራቀ ፕሮፖጋንዳ፤ አሁን ላለው ግጭትም እንደዋነኛ መንስኤም ሆኗል፡፡ በትግራይ ህዝብም ላይ ከባድ ጥቃት እየደረሰ ነው፡፡ በሌሎች ብሔረ ሰቦች መካከል ግጭት አልተከሰተም ማለቴ አይደለም፡፡ እነሱም የዚህ ዓይነቶችና ከታሪክ ጋር ትስስር ያላቸው ፕሮፖጋንዳ ብልጭ ሲሉ እንደሚከሰቱ ግልጽ ነው፡፡

‘የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት ዘርፎ ለትግራይ ህዝብ እየተሰጠ ነው’ የሚል የጭፍን አመለካከት ፕሮፖጋንዳ፤ አሁን የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ እምነት እየሆነ መጥቷል፡፡ የምሁራኖቹ አባባል አንድ ነገር አስታወሰኝ፡፡ በትግራይ ባህል መሰረት ለባለቤቴ የገዛሁላት የወርቅ ሽልማት ያዩ የሌሎች ብሔረ ሰቦች ጓደኞቼ በመደነቅ፤ ‘የትግራይ ሴቶች በመንግስት ወርቅ እንደሚገዛላቸው የሰማነው እውነትነቱ አረጋግጠናል’ ሲሉኝ የቀልድ መስሎኝ ነበር፡፡ በኋላ ግን የብዙዎች እምነት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በሌላ ግዜም፤ ከዲላ ዩኒቨርስቲ የተሰባበሩ ወንበሮችና ጠረጴዛዎች በመኪና ተጭነው ሲወጡ ያዩ ሰዎች፤ ‘ንብረታችን ወደ ትግራይ እየወሰዱት ነው’ ብለው በስሜት ሲናገሩ የሰማ ሰው መጥቶ ነገረኝ፡፡ ከዚህ ግዜ በኋላ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ፤ በትግራይ ህዝብ ላይ እየገነባው ያለው እምነት ለመገንዘብ ሞክሬያለሁ፡፡ በየግዜው በትግራይ ህዝብ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ደግሞ የአጥቂው የእምነቱ መገለጫ መሆኑ ጥርጥር የለውም፡፡  አቶ ሃብታሙ አለባቸው (2009)፤ ህዝቡ በህወሐትና በትግራይ ህዝብ ላይ የነበረውና አሁንም ያለው እምነት በደንበ የተረዳው ይመስላል፡፡ ‘…ግማሹ ሌላውን አገር ዘርፈው ትግራይን ሊጠቅሙ ነው ሲል ሌላውን ደግሞ፤ የኤርትራ ጉዳይ አስፈጻሚ ናቸው ብሎ ማመኑ እንኳን ያኔ ከድላቸው በኋላም አልተወም…’ ይለናል አቶ ሀብታሙ፡፡ በተጨማሪም፤ በትግራይ ያለው ዕድገት ዘገምተኛ ቢሆንም፤ በሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተያዘ አስተሳሰብ ግን ‘ትግራይ ተጠቃሚ ነች’ የሚል እነደሆነ ጆን ያንግ (1994) ይገልጻል፡፡

ከላይ የተጠቀሱና ሌሎች በዚህ ጉዳይ የሚጽፉ ምሁራን፤ ህወሐት ‘ከኢትዮጵያ ህዝብ እየዘረፈ ለትግራይ ህዝብ እየሰጠ ነው’ ሲሉ፤ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢህአዴግ እንጂ ህወሐት ስላልሆነ፤ ‘መንግስታዊ ስህተት አለ’ ቢባል እንኳ ለተፈጸመው ስህተት፤ ህወሐትን ብቻ ተጠያቂ ማድረግ፤ ከመጥፎ ወገኝተኝነት የጸዳ አመለካከት አለመሆኑን ያሳያል፡፡ በመቀጠል ምሁራኖቹ ለጥናታቸው መነሻ እንዲሆናቸው፤ ስለተቀባዩ የትግራይ ህዝብ የተወሰነ ምልከታ ቢያደርጉ (ሆን ብለው ህዝብ ለህዝብ የማጋጨት አጀንዳ ከሌላቸው በቀር) ስህተት ባልሰሩ ነበር፡፡ ጤናማ መንግስታዊ ናሙናም መጠቀም ይችሉ ነበር፡፡ ‘የሌሎች ኢትዮጵያውያን ሃብት፤ ህወሐት ሰርቆ ለትግራይ ህዝብ ይወስዳል’ የሚል የምሁራኖቹ የውሸት ፕሮፖጋንዳ ለኢትዮጵያወያን በአያሌ የሚጎዳ ነው፤ የህዝቦች ሞራልም የሚነካ ነው፡፡ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናልና፤ አንድ ህዝብ ወይም ብሔር ‘ንብረትህንና ገንዘብህን እየተዘረፈ ለትግራይ ህዝብ እየተሰጠ ነው’ የሚል ፕሮፖጋንዳ ሲሰማ፤ ‘የሰራነውና ያፈራነው፤ በጉልበተኛ ከተዘረፈ እማ….!’ በማለት የስራ ሞራሉ ከመውደቁ በተጨማሪ አሁን እንደሚታየው፤ ወደአላስፈላጊ ብቀላ ይሰማራል፤ ተሰማርቷልም፡፡ በሌላ በኩል፤ ህወሐት ‘ከኢትዮጵያ ህዝብ እየዘረፈ ለትግራይ ህዝብ እየሰጠ ነው’ ሲባል፤ ለትግራይ ህዝብም ‘የሌባ ተቀባይ ሌባ ነህ’ ከሚል ስድብ ባሻገር ‘ራስህ ሰርተህ መኖር አትችልም’ እየተባለም እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ በተጨማሪም፤ የትግራይ ህዝብ እንደህዝብ፤ ለሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የማያስብና ለአብሮ መኖር ዕንቅፋት እንደሆነ ተደርጎ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ እየተረጨ ነው፡፡

ያም ሆነ ይህ፤ ዛሬም የትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነቱ ከማንም ኢትዮጵያዊ ብሔረ ሰብ በታች ነው፤ ወይም ደግሞ ዝቅተኛ ተጠቃሚ ከሚባሉ ብሔረ ሰቦች አንዱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ፤ ዛሬ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው ህዝብ በአማካይ 22% ሲሆን፤ የትግራይ ህዝብ ግን 27% ከድህነት ወለል በታች ይገኛል፡፡ በትምህርት ጥራት፤ ትግራይ ዝቅተኛ አፈጻጸም አላት፡፡ የወጣቶች ስራ አጥነት በተመለከተ፤ የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ አጀንሲ (2016 ዓ.ም.ፈ) እንደሚያሳየው፤ በኢትዮጵያ የወጣቶች ስራ አጥነት 16.9% ሲሆን የትግራይ ግን 20.6% ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን በመንግስት ፖሊሲ ሆን ተብሎ ሳይሆን፤ በመንግስት የአፈጻጸም ችግር ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ተጠያቂ ደግሞ የክልሉ መንግስት ወይም ህወሐት ነው፡፡ የህዝቡ እምነትም ይሄ ነው፡፡ ለምሳሌ የአምባስነይቲ ወረዳ ህዝብ፤ ለክልል ምክር ቤት የወከላቸው በሰለጠነ መንገድ በሰላማዊ ሰልፍ በአደባባይ ወጥቶ ‘አትወክልኑም’ በማለት ድምጹ አሰምቷል፡፡ ስለትግራይ ህዝብ ተጎጂነት የፌደራል መንግስት የሚመለከቱ ጉዳዮችም አሉ፡፡ በፌደራል ምስራቤቶች (ለምሳሌ በዩኒቨርስቲዎች) ካየነው፤ የትግራይ ተወላጅ ክፉኛ አድሎ ይደርስበታል፡፡ ለምን ቢባል፤ ከላይ በጠቀስኳቸውና የመሳሰሉትን ፕሮፖጋንዳዎች ምክንያቶች፡፡ ዛሬ በሌሎች ክልሎች ጥቃት እየደረሰበት ያለው የትግራይ ህዝብ፤ የፌደራል መንግስት እርዳታ ያስፈልገው ነበር፡፡

በአጠቃላይ ‘ህወሐት የኢትዮጵያ ህዝብ እየጎዳ፤ የትግራይ ህዝብ እየጠቀመ ነው’ የሚለው የምሁራኖቹ ፕሮፖጋንዳ፤ ቢያንስ በሦሥት ከባባድ ችግሮች የተበተበ ነው፡፡ አንደኛ፤ መንግስት የወሰደው እርምጃ ወይም የፈጸመው ስህተት በሙሉ ሆን ተብሎ ከትግራይ ህዝብ ጋር ለማገናኘት ስለተፈለገ ብቻ ለህወሐት መስጠት፡፡ ለምሳሌ፤ በፕሮፌሰር ጌታቸውና ዳንኤል ዕይታ፤ በአዲሱ የመንግስት አወቃቀር ፕሮግራም መሰረት፤ የሌላ ብሔር ሰራተኞች ተባረው፤ ትግሬዎች እንዲቀጠሩ ወይም በስራቸው እንዲቀጥሉ ተደርጓል ይላሉ፡፡ ይህ አዲስ መዋቅር የትግራይ ተወላጅ ለመጥቀም ሆን ተብሎ ታስቦበት እንደተሰራም ምሁራኑ አንጸባርቋል፡፡ ምሁራኖቹ፤ ለዚህ ዋና ተጠያቂ የሚያደርጉት ደግሞ ህወሐትን ነው፡፡ ሆን ተብሎ በህሊናቢስነት ከትግራይ ህዝብ ለማገናኘት ካልሆነ በቀር በአማራ ክልል ይህንን ከተደረገ፤ ህወሐትን ጥፋተኛ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ዳንኤል ክንዴ፤ ኢህአዴግ እንደገባ፤ አንድ ሚልዮን ተማሪዎች በተለያዩ ክልሎች በተለያዩ ምክንያቶች ትምህርት ማቋረጣቸው ሲነግረን በትግራይ ግን ትምህርት ቤቶች በኮምፒተር እንደተንበሸበሹ ይገልጽና፤ ተጠያቂ ህወሐትን ያደርጋል እንጂ የየክልሉ መንግስት ወይም ፖለቲካዊ ድርጅት ተጠያቂ አያደርግም፡፡

ሁለተኛው የእነዚህ ምሁራን ስራዎች ችግር፤ የቀረቡ መረጃዎች ግምታዊ ናቸው፡፡ በማስረጃዎች የተደገፉ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ሃብት ወደ ትግራይ ተወሰደ ሲባል፤ የተወሰዱ ሃብቶች በማስረጃ የተደገፈ ምን ምን እንደሆኑ ማቅረብ፡፡ በሌላው የኢትዮጵያ አከባቢ የሌለ፤ ነገር ግን በትግራይ የተሰሩ መሰረተ ልማቶች፤ ዝም ብሎ በበሬ ወለደነት ‘ቪርችዋል’ /virtual/ ትግራይ መፍጠር ሳይሆን በእውን በመሬት ላይ ያሉ በመጻፍ ማሳየት መቻል ይጠበቅባቸዋል፤ ምሁራኖቹ፡፡ የትግራይ ተማሪዎች ብቻ ለስኮላርሺፕ ስለመላካቸውም እንዲሁም፡፡ ፕሮፌሰር፤ ትግሬዎች ለመቅጠር 400 ዳኞች ኢትዮጵያውያን እንደተባረሩ ነግረውናል፡፡ ነገር ግን የተቀጠሩ ትግሬዎች በኢትዮጵያ ፍርድቤቶች ተቋማት ስለሚገኙ፤ ስለተቀጠሩ ሰቦች ማንነትና በአድሎ ስለመቀጠራቸው ማስረጃ ካልቀረበ ተአማኒነት የለውም፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ግን አለ፡፡ ዛሬ በብሔር ቀርቶ በቤተ ሰብ ደረጃም አድሎ እንዳለ የሚካድ አይደለም፡፡ ይህ ድርጊት የሚፈጸም ግን በግለ ሰቦች ደረጃ እንጂ በፖለቲካዊ ድርጅት ደረጃ አይደለም፡፡ በእርግጥ፤ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች በግለ ሰቦች የሚፈጸሙ፤ በፖለቲካዊ ምህዳሩ ቀዳዳ ምክንያት እንደሆነ አይካድም፡፡

ዳንኤል ክንዴ፤ በትግራይ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ኮምፒተር ገብቶላቸዋል ሲል፤ የኢትዮጵያውያን የእምነት ባህል በውስጡ የለም እንድል አስገድዶኛል፡፡ እሱ የሚለው ደግሞ ኢህአዴግ ወደስልጣን እንደመጣ የመጀመርያዎች ዓመታት፡፡ የዳንኤል ጥናት የታተመበት ግዜ ማለትም በ2003 ዓ.ም.ፈ አከባቢ (1996/+1/ ዓ.ም) እኔ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ፤ በትምህርት ቤታችን አንድ ኮምፒተር አልነበረም፡፡ የኮምፒተር ትምህርት ተምረን፤ ኮምፒተር በአካል የምናይበት ዕድል ፍጹም አላገኘንም፡፡ የትምህርት ቤቱ ጸሐፊም ኮምፒተር እንዳልነበራት በደንብ አስታውሳለሁ፡፡ ዳንኤል ክንዴ የዛሬ 20 ዓመት በኮምፒተር ተጥለቀለቁ የሚላቸው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችም፤ እስከአሁን ኮምፒተር እንደሌላቸው ለመረዳት ችያለሁ፡፡ ከሞቲ ቢያ የሚሰነዘሩ ትችቶችም ‘በሬ ወለደ’ ዓይነት ናቸው፡፡ ለምሳሌ፤ ሞቲ ቢያ ‘ለትግራይ ተወላጆች ከቢሮክራሲዊና ከባንክ ነፃ የሆነ የፋይናንስ ብድር አገልግሎት ይሰጣቸዋል’ ሲል የትግራይ ተወላጆች ከክልላቸው ውጭ ‘ኢንቨስት’ የሚያደርጉበት አንዱ ምክንያት በአድካሚ ቢሮክራሲ ተማረው እንደሆኑ፤ መረጃው አጥቶት ሳይሆን ስላልፈለገው ነው፡፡ ሌላው፤ ሞቲ ቢያ ከኦሮምያ ወንዞች በተገኘ ሃይል በትግራይ ታላላቅ ዘመናዊ እንዱስትሪ የኤሌክትሪክ ፓዎሮችን እንደተተከሉ፤ ኢንዱስትሪ አምራች እንዱስትሪዎችን እንደተገነቡ እና ከመሬት መንቀጥቀጥ የአደጋ ክልሎች የፀዱ የከፍተኛ ኃይል የኤሌክትሪክ መስመሮችን እንደተዘረጉ እየተረተ ‘ቪርችዋል’ /virtual/ ትግራይ ፈጥሮልናል፡፡

ሦሥተኛው የምሁራኖቹ ችግር፤ በመንግስት የአፈጻጸም ችግር ምክንያት በሌሎች ኢትዮጵያውያን የደረሰው ችግር መረዳትና መቆርቆር እንጂ በትግራይ ህዝብ የደረሰው ችግር አለመገንዘብ እና ለማወቅም ፍላጎት አለመኖር፡፡ ዳንኤል ክንዴ፤ በአዲሱ የስራ መዋቅር ማስተካከያ ፕሮግራም ምክንያት ትግሬዎች ያልሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን ከስራቸው እንደተባረሩ ይነግረናል፡፡ ስለትግሬዎች መባረር አለመባረር ግን የሚመለከተው ጉዳይ አይመስልም፡፡ አንድ ልንገነዘበው የሚገባን ጉዳይ ግን የተባረሩ የመከላከያ አባላት፤ የሌሎች ብሔሮች ሳይሆን የትግራይ ተወላጆች ብቻ ናቸው፡፡ እስከ 1983 ዓ.ም የህወሐት ታጋዮች የነበሩ በኋላ የመከላከያ አባላት የሆኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች፤ ከ1986-1987ዓ.ም ለማመጣጠን ተብሎ ከመከላከያ ተሰናብቷል፡፡ በምትካቸው የሌሎች ብሔሮች በመከላከያ አባልነት ተቀጥሯል፡፡ ምሁራኖቹ፤ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች የተነሱ ጉዳዮች፤ በሌሎች ኢትዮጵያውያን የደረሰው ችግር በርካታ ጉዳዮች ቢያነሱም፤ በትግራይ ህዝብ ስለደረሰ ምንም ማንሳት አልፈለጉም፡፡ በአንጻሩ ግን በሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፤ ለትግሬዎች ምቾት ተብሎ እንደሆነ በህሊናቢስነት ይገልጻሉ፡፡

ሌላው ‘ቪርችዋል’ /virtual/ ትግራይ ፈጥሮ ተረት የሚያወጋን፤ ማቴው ጀ ማክራከን ይባላል፡፡ የመጣጥፉ ርዕስ ‘Abusing Self-Determination and Democracy: How the TPLF Is Looting Ethiopia’ (2004 ዓ.ም.ፈ) የሚል ነው፡፡ ይህ ግለ ሰብ የላይኞቹ ደራሲያን ፕሮፖጋንዳ በሚገባ ያስተጋባል፡፡ ግለ ሰቡ በስሙ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አይመስልም፡፡ ከኢትዮጵያና ከኢህአዴግ ጋር ትውውቅ እንደሌለውም፤ ከጽሑፉ መረዳት አያዳግትም፡፡ ቀጥለን የማክራከን ጽሑፍ እንይ፡፡ ‘…አንድ ሰው ህወሐት/ኢህአዴግ ለብሔረ ሰቦች በህገ መንግስቱ የመገንጠል መብት ለምን ልትፈቅድ ቻለች? ብሎ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ መልሱ ግን ቀላል ነው’ ይልና ራሱ ይመልሳል፤ ማክራከን፡፡ ‘…ህወሐት/ኢህአዴግ፤ በህገ መንግስታቸው የመገንጠል መብት ሊያካትቱ የቻሉ፤ ህወሐት የኢትዮጵያ ሃብት በመጠቀም ትግራይ ለማልማትና ለማስፋት እንዲችሉ እና በመቀጠልም ትግራይን ለመገንጠል ነው’፡፡ ሆኖም ግን ህወሐት ለግዜው ድብቅ አጀንዳ አላት ብሎ ማክራከን ያምናል፡፡ ይሄም፤ ‘በምስጢር የኢትዮጵያ ሃብት መስረቅ ነው’ ይላል፡፡ ህወሐት የኢትዮጵያ ሃብት ለመስረቅ እንጂ ትግራይን ይገነጥላሉ ብሎ ያመነበት ምክንያት፤ ሦሥት ነገሮች ያቀርባል፡፡ አንደኛ የ1976 ዓ.ም.ፈ ማኒፈስቶ ታላቅዋ ሪፓብሊክ ትግራይ ተብሎ ይታወቅ እንደነበር ይገልጻል፡፡ ሁለተኛ፤ በትግራይ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ያለው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወይም ልማት ለስርቆቱ ማስረጃ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሦሥተኛ፤ በኢትዮጵያና ኤርትራ ስለነበረው የድንበር ክርክር ነው፡፡

ማክራከን፤ በትግራይ ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ያለው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወይም ልማት ከስርቆት ጋር እንዴት ለማገናኘት የሚያቀርባቸው ማስረጃዎች እንይ፡፡ ‘…ከ1983 ዓ.ም በፊት፤ ትግራይ ኢኮኖሚዋ ውሱንና ያላደገ ነበር፡፡ ከ1983 ዓ.ም በኋላ ግን ትግራይ ሰፊ የኢኮኖሚና የንግድ ዕድገት አሳይታለች፡፡ ኢህአዴግ ወደስልጣን እንደመጣ በኢትዮጵያ ገንዘብ ትግራይን ለመጥቀም፤ ብዙ የኢኮኖሚ ፕሮግራሞች ተቀርጿል፡፡ በጦርነት ለተጎዳ መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም መሰረት፤ ህወሐት/ኢህአዴግ የኢትዮጵያ መንግስት ትልቅ ሃብት ወደትግራይ እንዲዞር አደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከአለማቀፋዊ እርዳታ ሰጪዎች ያገኘው ትልቅ እርዳታ፤ ወደ የህወሐት ፕሮግራሞች እንዲዞር ተደርጓል፡፡ ለዚህ ዋንኛው ማረጋገጫ ደግሞ ትግራይ በጣም ከፍተኛ /radical/ የንግድ ዕድገት ስታሳይ፤ ሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ግን ባሉበት ቆመዋል፡፡

‘ትግራይ ለመገንባት ሲባል፤ ህወሐት/ኢህአዴግ “ትእምት”ን /EFFORT/ አቋቋመ፡፡ “ትእምት” ከመንግስት ትልቅ ድጎማ ያገኛል፡፡ በ“ትእምት” አማካኝነት የተገኘ ገንዘብ፤ ህወሐት የትግራይ ከተሞችን ያለማበታል፡፡ ለምሳሌ፤ ዓዲግራት የመድሐኒት ፋብሪካ፣ አድዋ ጨርቃጨርቅ፣ መቀሌ ስሚንቶ ፋብሪካ እና ለገበሬዎች ብድር፣ ዘርና ትራክተሮች የሚሰጥ ጉና፡፡ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች በተለየ መልኩ፤ የትግራይ ኢኖሚያዊ ጥቅሞች የሚያፋጥኑ፤ ብዙ የመንግስት ያልሆኑ ድርጅቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ፤ የትግራይ ልማት ማህበር ወይም ማሕበር ልምዓት ትግራይ /ማልት/ እና የትግራይ እርዳታ ሰጪ ወይም ማሕበር ረድኤት ትግራይ /ማረት/ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሃብት ወደ ትግራይ መጥለፍ በዚህ አያበቃም፡፡ በግልጽ ባይታወቅም፤ በከፍተኛ ኢንቨስትመንት እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፤ በመቀሌ ሦሥት ኮሌጆ ተገንብቷል፤ የቢስነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት፣ የህክምና ትምህርት ቤትና ኢንጂነሪንግ ትምህርት ቤት ናቸው፡፡ በተጨማሪም፤ በእነአክሱም የመሳሰሉት የትግራይ ከተሞች የመዝናኛ ሆቴሎች ተገንብቷል፡፡ ከዚህ ባሻገር፤ ብዙ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው የቢሮ ህንጻዎች በትግራይ ከተሞች ተገንብቷል፡፡ የሚገርመው ግን ብዙ ህንጻዎች ባዶ ናቸው፡፡ አንዳንድ ግምቶች እንደሚሰነዘሩ ከሆነ ግን፤ የህወሐት ዕቅድ እነዚህ ህንጻዎች፤ ትግራይ ከተገነጠለች በኋላ የንግድ ማዕከሎች እንደሚሆኑ ነው’ ይለናል ማክራከን፡፡

በመሰረቱ፤ ማክራከን የላይኞቹ በደንብ ከማስተጋባት አልፎ ሌላ አዲስ ነገር አላመጣም፡፡ አንዳንድ ለየት ያሉ የሚመስሉ ነገሮች አብራርተዋል፡፡ ለምሳሌ፤ መንግስት ለትግራይ ህዝብ ሆቴሎች እንደሚሰራለት ለማብራራት ሞክሯል፡፡ “ትእምት”ን /EFFORT/  እና የትግራይ ልማት ማህበር፤ የትግራይ ህዝብ ለመጥቀም ተብሎ እንደተቋቋመ ይገልጻል፡፡ የሰውየው አረዳድ ግምታዊ ቢሆንም፤ መንግስት ለእነዚህ ድርጅቶች ገንዘብ ከሰጠ፤ የትግራይ ህዝብም በመንግስት ላይ ጥያቄ ይኖረዋል፡፡ ማክራከን፤ የሀገሪቱ ወይም ደግሞ የኢህአዴግ ሁኔታ ስለማያውቅ ነው እንጂ ለትግራይ ህዝብ የኢኮኖሚ ጥቅሞች ያመጣሉ ብሎ የዘረዘራቸው ድርጅቶች ሁሉ በሌሎች ክልሎችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፤ የልማት ማህበሮች፤ በክልል ቀርቶ በዞን ደረጃም የትም ቦታ አሉ፡፡ የትግራይ ልማት ማህበር በትግራይ፤ የኦሮሚያ ልማት ማህበር በኦሮሚያ፣ የአማራ ልማት ማህበር በአማራ፣ ወዘተ፡፡ ግለ ሰቡ፤ ሦሥቱ ኮሌጆች የመቀሌ ዩኒቨርስቲ መሆናቸው የተረዳ አይመስልም፡፡ ሰውየው፤ ዛሬ በኢትዮጵያ በአንድ ትልቅ ከተማ፤ የሦሥት ኮሌጆች መገንባት ተአምር የሆነበት ምክንያት ከእንግዳነቱ የተነሳ ይመስለኛል፡፡ ማክራከን ማን እንደላከው ባላውቅም፤ ትግራይ ቀርቶ ኢትዮጵያን እንደማያውቃት በሚገባ አሳውቆበታል፡፡ የትግራይ ሴቶች መንግስት ወርቅ ይገዛላቸዋል እንደተባለ ሁሉ፤ ህወሐት ለትግራይ ህዝብ ሆቴሎች ይሰራለታል ብሎ ማሰብ፤ ጨቅላነት ነው፡፡

ጆን ያንግ (1994) ‘የገበሬዎች አብዮት በኢትዮጵያ’ በሚል የፒ.ኤች.ዲ የመመረቂያ ጽሑፉ ላይ ከላይ የተገለጹ ሐሳቦች ትክክል አለመሆናቸው ይገልጻል፡፡ ጆን ያንግ፤ ለመመረቂያ ጽሑፉ የሚሆን ናሙና (data) ለመሰብሰብ ለአንድ ዓመት ያህል ብዙ የትግራይ ወረዳዎች እየተዘዋወረ ጎብኝቷል፡፡ አሁን ባለው ስርዓት ስለየትግራይ ህዝብ ተጠቃሚነት፤ ጆን ያንግ ትዕዝብቱን እንዲህ በማለት ይገልጻል፡፡ ‘ሺ እንኳ …‘ትግራይ የከፍተኛ እርዳታ /fund/ ተጠቃሚ ነች’ ተብሎ ከትግራይ ውጭ ያለው በሰፊው ህዝብ የተያዘ አስተሳሰብ ቢሆንም፤ በክልሉ ያለው ዕድገት ግን ዘገምተኛ ነው’፡፡ ጆን ያንግ ለትግራይ ዕድገት ወይም ልማት ‘ዕንቅፋት ናቸው’ ብሎ ከሚያቀርባቸው አንዱ አዲስ አበባ ያሉ የመንግስት ቢሮክራቶች፤ ስለክልሉ ያላቸው የግንዛቤ ችግር እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ያንግ፤ በመቀጠል በአጼ ሃ/ሰላሴና በደርግ መንግስታት ግዜም ከማዕከላዊ መንግስት ባጀት ለማንቀሳቀስ ችግር እንደነበር በማስታወስ፤ ዛሬም በተመሳሳይ መልኩ ማዕከላዊው መንግስት በአማራ የበላይነት ስለተያዘ፤ የመንግስት እርዳታ ወደ ትግራይ እንዳይሄድ ስልጣናቸው በመጠቀም እንደሚከለክሉ ይጠቁማል፡፡ በ1992 ዓ.ም.ፈ ትግራይ ላይ ከቢሮክራቶች ጋር ጦርነት እንደነበር በመግለጽ፤ ‘በዚህ ጦርነት ምክንያት፤ ብዙዎች ትግራይ እየጠፋች እንደሆነች ተሰምቷቸዋል’ ይላል ጆን ያንግ፡፡

ዛሬ በኢትዮጵያ፤ በብሔረ ሰቦች መካከል ከባድ ግጭትና ብጥብጥ ተከስቷል፡፡ በመሆኑ፤ ዛሬ በኢትዮጵያውያን ብሔረ ሰቦች መካከል መቻቻል አለ አይባልም፡፡ እርስ በእርስ እየተናከሰ ነው፡፡ ለመጠፋፋትም እየከጀለው ነው፡፡ መንግስት፤ በዚህ ደረጃ ላይ ለደረሰ የብሔሮች ግጭት፤ በጥንቃቄ በማጥናት፤ በጥንቃቄ መፍትሔ ሊያበጅለት ይገባል፡፡ የግጭት ጉዳይ ለመንግስት ብቻ የሚመለከት ጉዳይ አይደለም፡፡ ለመንስኤውም ለመፍትሔውም የተለያዩ የህብረተ ሰብ ክፍሎች የየራሳቸው ሚና አላቸው፡፡ ባላደጉ ሀገሮች፤ ህዝቡ የፖለቲካ ንቃተ ህሊና ስለሚያንሰው፤ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ህዝቡ የምሁሩ ጥገኛ በመሆን ምሁሩ የተጓዘበት አቅጣጫ እንደሚከተል የማይካድ ሐቅ ነው፡፡ ግጭት ሲከሰትም፤ አሉታዊ ተጽዕኖው በማጉላት፤ በሰው ሂወት አደጋ እና የመሰረተ ልማት ውድመት እንዳይደርስ ለህዝቡ ማስተማርና መምራት ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም፤ ሳይንሳዊ ምርምር በማካሄድ የግጭቱ መንስኤና መፍትሔ ለመንግስት መንገዱን ማሳየት ይኖርበታል፡፡ የደቡብ ምስራቅ ኤስያ ሀገሮች፤ ባላቸው ብሔረ ሰባዊ /ጎሳዊ/ እና ሃይማኖታዊ ክፍፍል፤ ይከሰቱ ለነበሩ ግጭቶችና ብጥብጦች፤ የእነዚህ ሀገሮች ምሁራን አወንታዊ ተሳትፎ የሚመሰገን ነበር፡፡ ለምሳሌ፤ እንዶኖዥያ በሦሥት መቶ ደሴቶች የሚኖር ህዝቧ፤ ከሁለት መቶ በላይ ብሔረ ሰባዊ /ጎሳዊ/ እና ሃይማኖታዊ ክፍፍል አለው (ትሪጆኖ፤ 2004)፡፡ ነገር ግን ዛሬ በእንዶኖዥያ የህዝቦች የጋራ ሀገራዊ ማንነት በመገንባት፤ ባህላዊ ማንነት (ለምሳሌ ብሔረ ሰባዊና ሃይማኖታዊ ክፍፍል) መሰረት አድርጎ ይከሰት የነበረው ግጭት በመፍታት ረገድ መንግስት የአንበሳ ድርሻውን ቢወስድም (ፉኩያማ፤ 2014)፤ የምሁራን ሚናም የማይናቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይገለጻል (ትሪጆኖ፤ 2004)፡፡

ኢትዮጵያ አሁን በርከት ያለ የተማረ የሰው ሃይል አላት፡፡ ይህ፤ የተማረ ሰው ፖለቲካዊ ግንዛቤው ከሌላው የህብረተ ሰብ ክፍል ላቅ ብሎ እንደሚገኝ ጥርጥር የለውም፡፡ ስለሆነም፤ ይህ የተማረ የህብረተሰብ ክፍል፤ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶች ምርምር በማስደገፍ መንግስትና ህዝብ መርዳት ነው፡፡ የመንግስት ክፍተት ካለም፤ መንግስትን በመሞገት ለህዝብ ጥብቅና መቆም መቻል ነው፡፡ ግጭትንና ብጥብጥን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችሉ ዘዴዎች እያበጀ ምሁራዊ ግዴታው መወጣት ይችላል፡፡ አሁን በሃገራችን እየተከሰተ ላለው መጥፎ ድርጊት ማለትም የሰው ህይወት ማጥፋትና ንብረት ማውደም፤ በኢሰብአዊነቱ የሚወገዝ ብቻ ሳይሆን ዕድገትን የሚጋታና ሃገር ሊያፈርስ እንደሚችል ምሁሩ በብዕሩ መግለጽና ሰፊው ህዝብ ማስተማር ይችላል፤ ከውስጥ የአብሮነት ስሜት ካለ፡፡ ነገር ግን ከላይ ባጭሩ ለመዳሰስ የተሞከሩ የምሁራኖቹ ጽሑፎች የመጨረሻ ዓላማቸው (ultimate goal) ምንድ ነው? እነዚህ ምሁራን የህወሐት ጥላቻ ነው ወይስ የትግራይ ህዝብ ጥላቻ ነው እያንጸባረቁ ያሉ?

የኔ አረዳድ፤ በጽሑፎቹ የተንጸባረቁ የምሁራኖቹ አስተሳሰብና አመለካከት፤ የትግራይ ህዝብ ጥላቻ እንጂ የህወሐት ጥላቻ አይደለም፡፡ ህወሐት ከትግራይ ህዝብ በመለየት መተቸት ተስኗቸው አይደለም፡፡ ምክንያቱም ህወሐት የገዢው ፓርቲ (ግለ ሰቦቹ በጽሑፎቻቸው ኢህአዴግና የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ማንሳት ባይፈልጉም) ከኢህአዴግ እህት ድርጅቶች አንድ እስከሆነ ድረስ እንደገዢ ፓርቲ ወይም እንደመንግስት ጥፋት ይኖረዋል፡፡ ያንን ጥፋት የትችታቸው ትኩረት ማድረግ ይችሉ ነበር፡፡ ሆኖም ግን የትግራይ ህዝብ ስለተፈለገ ብቻ ህወሐትን የማይገልጹ መጥፎ ድርጊቶች በመፍጠር ከህዝቡ ጋር በማገናኘት፤ ህዝቡ የጥቃት ትኩረት ለማድረግ ስለታሰበ ብቻ ነው፡፡ በሌላ አገለላጽ ህወሐትን ተጠቅመው የትግራይ ህዝብ ማጥቃትና ማስጠቃት ነው ዓላማቸው፡፡ ከላይ ከቀረቡ ጽሑፎች ሁለቱ በሳይንሳዊ መጽሔቶች (scientific journals) የታተሙ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ሁለቱ መጣጥፍ የውሸት ናሙና (data) ተጠቅመዋል፡፡ ስህተት ወደ ሆነ ድምዳሜ (conclusion) ላይ ደርሷል፡፡ ይህ ግን ሆን ተብሎ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት በተጨባጭ እንደተከሰተው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በማደናበር በትግራይ ህዝብ ላይ እንዲዘምት ማድረግ ነው፡፡ በሌላ አባባል፤ የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ህዝብ እንዲጠላ ተደርጎ ጦርነት እንዲታወጅበት ነው፡፡ በሌላ ግዜ የምናየው ይሆናል እንጂ እንደነእስክንድር ነጋ መሳይ መኰነን የመሳሰሉ ኢትዮጵያውያን፤ በትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት እርምጃ እንዲፈጸም ለኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሃገራችን በህዝቦች መካከል ግጭትና ጦርነት አዲስ አይደለም፡፡ ካለፈ ታሪካችን መማር ባንችልም፤ ግጭትና ጦርነት ረዥም ዕድሜ ያለው የታሪካችን መጥፎ ገጽታ ነው፡፡ እስከአሁን በሃገራችን የተካሄዱ ግጭቶችና ጦርነቶች ህዝቡ ባለው ልዩነት ሳይሆን፤ ጥቂት ግለ ሰቦች ለግል ጥቅማቸው ብለው የሚለኰሷቸው ናቸው፡፡ የእነዚህ ግጭቶችና ጦርነቶች ውጤት፤ እንደህዝብና ሃገር ዛሬ ላለንበት ደረጃ አብቅተውናል፡፡ እንደህዝብ ከላይ ወደታች ወርደናል፡፡ ህዝብ ካልተጠቀመ፤ በግለ ሰቦች ደረጃም ተጠቃሚ አይኖርም፡፡ ቢያንስ የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን አያመልጥም፡፡ ስለዚህ፤ ከላይ ጽሑፎቻቸው የተዳሰሱ ግለ ሰቦችና መሰሎቻቸው፤ በመጀመርያ ለህዝብ አንድነትና ዕድገት ሲባል ለግል ጥቅም በመሸነፍ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ግጭቶችና ጦርነቶች ከመፍጠር በመቆጠብ፤ ዛሬም ባለፈው ታሪክ ውስጥ ላለመኖር ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ሌላው፤ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ህዝብ፤ የትግራይ ህዝብ እንደህዝብ የማንም ጥቅም የማይነካ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለአብሮነት የሚተጋና ለሃገሩ ዋጋ የሚከፍል ህዝብ ነው፡፡ ነገር ግን እነዚህ ግለ ሰቦች፤ የትግራይ ህዝብ ጠላት የነበሩ የጥቂት ቀደምት ኢትዮጵያውያን ባህርይ የተላበሰ አመለካከት ያላቸው ይመስላል፡፡ አመለካከት ደግሞ እምነት ነውና ያረጀ የወላጅ እምነት መተው ላይቻላቸው ይሆናል፡፡ ሆኖም ግን እነዚህ ግለ ሰቦች፤ ዛሬ ህዝቡ የማንም ኢትዮጵያዊ ብሔር መብት የሚያከብር ህገ መንግስት ባለቤት መሆኑን ከዘነጉት በማስታወስ፤ ዛሬ ለግል ጥቅማቸው ሲባል ጨቋኝ እና ህዝቦች የማጣላትና የማጋጨት ያረጀ የወላጆቻቸው መሳርያ መጠቀም እንደማይችሉ ሊያውቁ ይገባል፡፡

ማጣቀሻ

  1. ጌታቸው ሃይሌ (ፕሮፌሰር) (2006). አንዳፍታ ላውጋችሁ.
  2.  ሞቲ ቢያ (2009). የኦሮሞ ጥያቄ እና ፈተናዎቹ.
  3. Getachew Haile (Professor) (no year of publication). Violation of Human Rights of Ethiopians by the Tigray People’s Liberation Front. Human rights week observance and electronic mail conference. http://www.ethiopians.com/getachew.html.
  4. Daniel Kendie (2003). The Causes of the Failure of the Present Regime in Ethiopia. International Journal of Ethiopian Studies,  1: 177-213.
  5. Mathew J. McCracken (2004). Abusing Self-Determination and Democracy: How the TPLF Is Looting Ethiopia. Case Western Reserve Journal of International Law, 36፡183-222.
  6. Lambang Trijono.Structural-Cultural Dimensions of Ethnic Conflict: Toward a Better Understanding and Appropriate Solution In Managing Ethnic Conflict. In “The Making of Ethnic and Religious Conflicts in Southeast Asia: Cases and Resolutions” (2004).
  7. John Young (1994). Peasants and Revolution in Ethiopia.
  8. Fukuyama F (2014). Political Order and Political Decay.
  9. CSA. (2016). Central Statistical Agency.

 

*********

* ጸሀፊው ዶ/ርገ/መድህን ሮምሃ  [email protected] ሊገኙ ይችላሉ።

Avatar

Guest Author

more recommended stories