የጠ/ሚ አብይ አህመድ የመቐለ ንግግር ሙሉ ትርጉም

(ትርጉም በዳንኤል ብርሃነ)

ክቡራት ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፤
(ረጅም ጭብጨባና ፉጨት)
ክቡራት ታጋዮችና የሰማዕታት ቤተሰቦች፤
(ረጅም ጭብጨባ)
ክቡራት የሀገር ሽማግሌዎች (ጭብጨባ) እና የተከበራችሁ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች፤ (ጭብጨባ)
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች (ጭብጨባ)
ክቡራንና ክቡራት።

ከሁሉም በላይና በፊት በዚህች ጥንታዊና ውብ በሆነችው ሰሜናዊት ኮከብ መቐለ ተገኝቼ ከናንተ ጋር ለመወያየት በመቻሌ የተሰማኝን ደስታ ልገልጽ እወዳለሁ። (ረጅም ጭብጨባ)

ትግራይ ማለት የሀገራችን ታሪክ እንደእንጀራ ተቦክቶ የተጋገረባት እና የውጭ ወራሪዎች ብዙ ግዜ ሀፍረት ተጎንጭተው የተባረሩባት የሀገራችን ክፍል ናት።(ጭብጨባ)

በዚህች የጥንታዊት ኢትዮጲያ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የዛሬዋም ኢትዮጲያ ማገር በሆነች ክልል ስራ በጀመርኩ ማግስት ተገኝቼ ከናንተ ጋር ለመወያየት በመቻሌ የተሰማኝ ደስታ ወሰን የለውም።(ጭብጨባ)

ብዙዎች እንደሚስማሙበት ትግራይ የኢትዮጵያ እትብት የተቀበረባት ምድር ናት።(ጭብጨባ)

ትግራይ የሀገራችን ታሪክ ኩራትና የስልጣኔያችን ምንጭ የሆነው የአክሱም ሃውልት የሚገኝባት ምድር ናት።(ጭብጨባ)

ትግራይ ከሀይማኖትነት አልፈው የማንነታችን መገለጫ ለመሆን የበቁት የክርስትናና የእስልምና ሀይማኖቶች ወደሀገራችን በአክሱምና በነጃሺ አድርገው ለመጀመሪያ ግዜ የገቡባት ክልል ናት። (ጭብጨባ)

ትግራይ የመላው ጥቁር ህዝብና የመላው የነጻነትና የእኩልነት ደጋፊዎች ኩራት የሆነችው የነጻነታችን መሰረት አድዋ የምትገኝባት ክልል ናት። (ጭብጨባ)

በቅርቡ ደግሞ ከ3 ሽህ ዓመታት በላይ እድሜ ያላት ከተማ ሽሬ ማይ አድራሻ አካባቢ የተገኘባት መሆኗ፤ ሀገራችን ከአለም ከተሞች ቀዳሚ ለመሆኗ ማስረጃ ነው። (ጭብጨባ)

ትግራይ የማህሌታዊ ያሬድ እና እንደነ ዘርዓ-ያዕቆብ የመሰሉ ፈላስፎች ምንጭ ናት። (ጭብጨባ)

Photo - PM Abiy Ahmed speaking in Mekelle, Martyr's hall, April 13, 2018
Photo – PM Abiy Ahmed speaking in Mekelle, Martyr’s hall, April 13, 2018

ትግራይ ለፍትህና ለእኩልነት ሞትን ተጋፍጠው ክቡር መስዋዕትነት የከፈሉ፤ ለኢትዮጲያን ግንባታ ቤዛ የሆኑ ጀግኖች፣ እንደነስሁል (ወደ ስሁል ፎቶ እየጠቆመ)፣ ሙሴ፣ ዋልታ፣ ሀፍቶም፣ ቀለበት፣ ሀየሎም፣ ብርሀነ መስቀል፣ ቀሽ ገብሩ፣ አሞራ፣ ጥላሁን ግዛው፣ በተለይ እንደጓድ መለስ ዜናዊ ያሉ (ጭብጨባ)፤ በአጠቃላይ ደግሞ ተቆጥረው የማያልቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ጀግኖችና ታጋዮች ሀገር ናት። (ጭብጨባ)

ትግራይ በሀገራችን ለውጥና ዲሞክራሲ እንዲመጣ የታገሉ የተለያዩ ሀይሎች ህዝባዊ ድጋፍና ከለላ ያገኙባት፤ የኢህአዴግ ድርጅቶችን ከጠላት ደብቃና ደግፋ አሁን ለደረሱበት ደረጃ ያደረሰች ናት። (ጭብጨባ)

ትግራይ ያለኢትዮጲያ ኢትዮጲያ ያለትግራይ፤ ሞተር እንደሌለው መኪና ትርጉም አልባ ነው። (ጭብጨባ)

የትግራይ ወጣቶች፤
ይህን ታላቅ የአባቶቻችሁ ታሪክና አደራ እንድትገነዘቡና እንድትጠብቁ አሳስባለሁ። እንደአባቶቻችሁ ጽናትና ህዝባዊ ፍቅርን ያዙ። የሀገራችንና የሀገራችሁ ዋልታ ሁኑ። ድህነትንና ኋላቀርነትን ታሪክ ለማድረግ ታገሉ። (ጭብጨባ)

የተበራችሁ ተጋባዥ እንግዶች፤
ክቡራንና ክቡራት፤

የትግራይ ህዝብ ሀገሩን ከልቡ አውጥቶ የማያውቅ በመልካም ሆነ በክፉ ግዜ በኢትዮጲያዊነቱ የማይደራደር ህዝብ ነው። ገዢ መደቦች ጨቁነውትና ረግጠውት በነበረበት ክፉ ዘመን እንኳን በኢትዮጲያዊነቱ ፍጹም ሳይወላውል ከሌሎች ኢትዮጲያዊ ወንድሞቹ ጋር በመሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹን ገብሮ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የታገለ ጽናትና ሀቀኝነትን በደሙ የሰነቀ ህዝብ ነው። (ጭብጨባ)

ትላንት በአንዳንድ የኦሮሚያና የአማራ አካባቢዎች ለተፈጠሩ ችግሮች በጣም እያዘንን፤ መንግስታችን ያ ድርጊት እንዳይደገም ከህዝብ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ያደርጋል። (ጭብጨባ)

ምንም እንኳን አንዳንድ ጥቂቶች አስፈላጊ ያልሆነና ኢትዮጲያዊ ያልሆነ ተግባር ቢፈጽሙም አብዛኛው ህዝብ ግን አልተቀበለውም። ኦሮሚያ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥቃት ለማድረስ በሚሞከርበት ግዜ የኦሮሞ ህዝብ እኛን ሳትገድሉ እነሱን አታጠቁም በማለት በዛች ፈታኝና መጥፎ ወቅት ለትግራይ ወንድሞቹ ያለውን ፍቅርና መከታነት አስመስክሯል። (ጭብጨባ)

ዓምና በትግራይና በአማራ ክልል መሀል አንዳንድ ችግሮች ተፈጥረው በነበረ ግዜም ተመሳሳይ ፍቅርና መከታነት ታይቷል። ምንም እንኳን ህዝባችን ከእጅ ወደአፍ የሚኖር ቢሆንም ማተቡን አክብሮ ተፈናቃይ ትግራዋይ ባለንጀራውን ምርት አጭዶና ሰብስቦ ተፈናቃዮች ወደተጠለሉበት ቦታ ድረስ ወስዶ አስረክቧል። (ጭብጨባ) ይህ የአንድ አማራ ገበሬ ታሪክ ነው። እንደዚህ ያሉ አብነቶች ብዙ ናቸው።
ህዝባችን ለማመን የሚቸግር ፍቅር መቻቻል አብሮ የመኖር ፍላጎት የሚያሳይ ባህል ያለው ህዝብ ነው። (ጭብጨባ)

ማነው ከማን ጋር ያልተዋለደ? ይቺ የሁላችን መኖሪያ የሆነች ኢትዮጲያ በአሸዋ ላይ የቆመች ሳትሆን በማይነቃነቅ ጽኑ መሰረት ላይ የቆመች ናት። (ጭብጨባ) ይህን ደግሞ ልንከባከበው ይገባል። ሚዲያዎቻችንም ይህን የሚያኮራ ታሪክ እና የህዝባችንን አብሮ የመኖርና የመደጋገፍ ባህል ለማጎልበት ሊሰሩ ይገባል። (ጭብጨባ)

የተበራችሁ ተጋባዥ እንግዶች፤
ክቡራንና ክቡራት፤

በትጥቅ ትግል ወቅት ሆነ ከዛ በኋላ ከታጋዮች ጋር የሰራ ወይም በማናቸውም አጋጣሚ ትግራይን ያየ የህዝቡን ማንነትና እሴት ለመረዳት አይቸገርም። (ጭብጨባ) የትግራይ ህዝብ ከየትኛውም የሀገራችን ጫፍ የሚመጣ እንግዳን ሀገሩን ሳይጠይቅ እንደራሱ ልጅ ተንከባክቦ የሚይዝ፤ ያለውን አካፍሎ አብልቶ አጠጥቶ የሚሸኝ የትግል ወኔን የሰነቀ ህዝብ ነው። (ጭብጨባ) የትግራይ ህዝብ ዘር ሳይመርጥ ከሁሉም ህዝቦች ጋር መልካም ወዳጅነት ያለው እና ሀገራዊ ማንነትን እየፈጠረ የመጣ ህዝብ ነው። (ጭብጨባ)

ሌሎች የኢትዮጲያ ህዝቦችም እንዲሁ ከሁሉም ብሔሮች ጋር ተዋልደዋል። የኢትዮጲያ ህዝብ እርስ በርሱ እንዲፋቀርና እንዲተሳሰብ የሚያስችሉ ጸጋዎች እንጂ እርስበራሱ እንዲጠራጠርና እንዲጋጭ የሚያደርግ ሁኔታና ታሪክ የለውም። (ጭብጨባ) አሁንም እነዚህ ጸጋዎቻችንን ልንከባከባቸው ይገባል። (ጭብጨባ)

የትግራይ ህዝብ ከተራራ ጋር እየታገለ ተራቁተው የነበሩ ቦታዎችን በለምለም እጽዋት እንዲሸፈኑ እያደረገ ያለ ታታሪ ህዝብ ነው። (ጭብጨባ) ይህ ታሪካዊ ስራ ነገ እንደአክሱም እና እንደአብርሃ ወ አጽብሃ ኪነ-ህንጻዎች የሚዘከር ተጋድሎ ነው። (ጭብጨባ) ይህ የልማታችን ውጤት ነው። ይህም ሆኖ ግን በትግራይ በፍጹም ድህነት የሚገኙ ወገኖች ብዙዎች ናቸው። ይህን ለመቅረፍ መንግስትና የትግራይ ህዝብ እየተረባረቡ ነው። የትግራይ ህዝባችንም ከመንግስትህ ጎን ሆነህ ልትረባረብ ይገባል። (ጭብጨባ) ለዚህ ደግሞ ኢህአዴግና የፌዴራል መንግስት የሚቻላቸውን እንደሚያደርጉ ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ። (ረዘም ያለ ጭብጨባ)

በቅርቡ በተፈጠሩ ችግሮች ሳቢያ ተዘዋውረው የመስራት መብታቸው የተጣሰ ተጋሩ መኖራቸው ይታወቃል። ይህን ለመቅረፍና ተጋሩ እንደሌሎች ኢትዮጲያውያን ሁሉ በማናቸውም ቦታ ተዘዋውረው የመስራት መብታቸው ሊከበር ይገባል። (ጭብጨባ) ይህ መብት እንዲረጋገጥ እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር የፌዴራል መንግስት ጠንክሮ ይሰራል። (ጭብጨባ) በተጨማሪም የትግራይ ሕዝብ ከወንድሞቻችን የኤርትራ ሕዝብ ጋር ያለው ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ፥ ከኤርትራ መንግስት ጋር ያለንን ልዩነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት መንግስታችን የሚያደርገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል። (ረዥም ጭብጨባ)

በመጨረሻም ለኔና ለልዑካን ቡድኔ ለተደረገልን ደማቅና ልባዊ አቀባበልና መስተንግዶ ከልቤ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ። (ጭብጨባ)

ዘላለማዊ ክብርና ሞገስ ለጀግኖች ሰማዕታት። (ጭብጨባ)

ያክብርልኝ አመሰግናለሁ። (ጭብጨባ)

አመሰግናለሁ (በአማርኛ)። ገለቶማ (በአፋን ኦሮሞ) (ረዥም ጭብጨባ)

********

Daniel Berhane

more recommended stories