የዋሽንግተን ዲሲና አካባቢዋ ተጋሩ የአቋም መግለጫ (+ video)

በዋሽንግተን ዲሲ እና ኣካባቢዋ ተጋሩ የተካሄደ ህዝባዊ ስብሰባ ተከትሎ የተሰጠ የአቋም መግለጫ

እኛ በዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢዋ የምንኖር ኢትዮጵያዊያን የትግራይ ክልል ተወላጆች ጃንዋሪ 27, 2018 ላይ በወቅታዊ የክልላችን እና የሀገራችን ጉዳይ በማስመልከት ስብሰባ አካሂደናል። ይህንን ስብሰባ ስናካሂድ የሚከተሉትን እውነታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ነው።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከ26 ዓመታት በፊት ከነበረችበት የእርስ በርስ ጦርነት እና አስከፊ ሁኔታ ለማውጣት በተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የትግራይ ህዝብ ከፍተኛ የህይወት መስዋእትነት እና የአካል ጉዳት ከፍሏል። ከዚህ ሁሉ መራራ የህይወት መስዋእትነት እና የአካል ጉዳት በኋላ፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲተከል፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መብት እና እኩልነት እንዲከበር የተከፈለው መስዋእትነት እንደ አንድ ሀገራችንን ከነበረችበት አስከፊ ሁኔታ እንድትወጣ እና እንደ ሀገር እንድንቀጥል የተደረገ አስተዋጽኦ እንጂ የትግራይ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለየ መልኩ ጥቅም እንዲደረግለት በማሰብ ስላልነበረ የከፈለውን መስዋእትነት በክብር ተቀብሎታል።

ከዚህ ሁሉ መራራ ትግል በትግራይም ኾነ በመላው ኢትዮጵያ በተካሄዱ ውጊያዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ የነበረው አካሉ የጎደለ፣ ብሔርን ለማመጣጠን ሲባል ከአገልግሎት የተቀነሰ ታጋይ እና የተሰዉ ታጋዮች ቤተሰብ የህዝባችን ክፋይ በጦርነት በወድመ የትግራይ ክልል ኢኮኖሚ ላይ ሲጫን፣ የትግራይ ህዝብ፣ “ልእኩልነት የተከፈለ መስዋእትነት ነው” በማለት ከባድ ሸክም ተሸክሟል። ይህ ያደረገው እንደ ማንኛውም ህዝብ እኩል መብቱ ተጠብቆለት፣ የመሰለውን የፖለቲካ ፓርቲም ኾነ አመለካከት እንዲደግፍ እና እንዲቃወም በትግሉ የጨበጠው መብት እንጂ ማንም በችሮታ የለገሰለት እንዳልኾነ ከምንም ነገር በላይ ይገነዘባል።

የትኛውንም ሀይል “እኔን ደግፈኝ፤ እገሌን መደገፍ ደግሞ አቁም፤ ካልኾነ ወዮልህ!” በማለት ሊመጻደቅበት አልነበረም፤ ምክንያቱም ይህ አይነቱ አስተሳሰብ በመሰረቱ ጸረ ዲሞክራሲያዊ እና የትግራይ ህዝብ ደግሞ እዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ፣ የአስተሳሰቡ አራማጆች እና ጌቶቻቸው ከ26 ዓመታት በፊት ባካሄደው መራራ ትግሉ ለአንዴና ለመጨረሻ አስወግዷቸዋልና።

ከዚህ ሁሉ የትግራይ ህዝብ የከፈለው መስዋእትነት በኋላ፣ አሁን በተፈጠረችው አዲሲቷ ኢትዮጵያ የብሔር ብሔርሰቦች እኩል ተሳትፎ ባሳየ አኳሀን ባለፉት አስርት አመታት ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንደተመዘገበ ማንም የማይክደው ሐቅ ነው። ይሁን እንጂ፣ ባለፉት አመታት የተመዘገበ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እንደተጠበቀ ኾኖ፣ ከዚህ እውነታ ጎን ለጎን የተስተዋለ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ አድልዎ፣ ሙስና፣ የፍትሕ መጓደል፣ የዲሞክራሲ እጦት እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ ህዝብም በከፋ ሁኔታ በደል ሲደርስበት ነበር ብለን አስቀምጠናል።

Photo - Tigrayans meeting in Washington DC, Jan 27, 2018
Photo – Tigrayans meeting in Washington DC, Jan 27, 2018

እንግድያውስ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱ ተጨባጭ የሀገራችን እና የክልላችን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት የህዝባዊ ስብሰባው ተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ካካሄድን በኋላ የሚከተለውን ባለ ስምንት (8) ነጥቦች የአቋም መግለጫ ስጥተናል።

1. በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት የሰፈሩ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የመስራት እና የመኖር መብት የሚከበርበት፤ የሕግ የበላይነት በሰፈነበት መልኩ አጥፊዎች በሕግ የሚጠየቁበት እና ተገቢው ቅጣት የሚቀጡበት አሰራር በፌደራል መንግስት እና በክልሎች እንዲሁም እነዚህ የመንግስት መዋቅሮች የሚመራው ኢህአዴግ እና በውስጡ ያቀፋቸው አራቱ አባል ድርጅቶች እንዲሁም አጋር ድርጅቶች የሚያስተዳድሯቸው ክልሎች ላይ በአፋጣኝ እንዲተገበር እንጠይቃለን።

2. በትግራይ ህዝብ ላይ የሚደረግ ብሔር መሰረት ያደረገ ጥቃት አጥብቀን እናወግዛለን። በህዝቦች መሀል የተፈጠረ ግጭት ነው ብለን አናምንም። ኾኖም ግን ይህንን ተግባር በግላጭ እና በሕቡእ ብህዝብ ላይ ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት በመፈጸም እና ቅስቀሳ በማካሄድ የተሳተፉ ወደ ሕግ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን። ጥቃት ለደረሰባቸው፣ ለተፈናቀሉ እና ቤት ንብረታቸው ለወደመባቸው ዜጎች የፌደራል እና የክልል መንግስታት አስፈላጊውን የሞራል እና የንዋይ ድጋፍ እንዲያደርጉላቸው እናሳስባለን።

3. በትግራይ ህዝብ ላይ የሚካሄድ በሚዲያ የተደገፈ የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ (campaign) አጥብቀን እናወግዛለን። በዚህ ተግባር በቀጥታ ተዋናይ የኾነው ኢሳት (ESAT) የተባለ የቴሌቪዥን ጣብያ በውስጡ የሚሰሩ የጥላቻ መልእክተኛ ግለሰቦች እንዲሁም በተዘዋዋሪ ደግሞ እንደ Voice Of America አማርኛ አገልግሎት ላይ የመሳሰሉ የውጭ መንግስታት የሚዲያ ተቋማት ተቀጥረው የሚሰሩ ግለሰቦች በህግ እንዲጠየቁ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፤ የትግራይ ህዝብ መብቱ እና ድህንነቱ እንዲከበር ለማድረግ የሚመለከታቸው በአካባቢያችን የሚገኙ የሕግ ተቋማት መሰረት በማድረግ ህዝባዊ ዲፕሎማሲ እንዲጠናከር እንሰራለን።

4. ማንም ጤናማ እና ሐላፊነት የሚሰማው ኢትዮጵያዊ በወንድም እና እህት ህዝብ የመጠቃቃት ዘመቻ እንዲካሄድ መፍቀድ የለበትም። በተለይ በማሕበራዊ ሚዲያ ሐሰተኛ ስም (pseudonym) በመጠቀም ተደብቀው ጥላቻ እና ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ የውጭ ሀይሎች ፍላጎታቸው ለማሳካት፣ ሀገራችን ተበታትና ለማየት ካላቸው የቆየ ምኞት እርስ በራሳችን እንድንጨራረስ የሚያደርጉት ቅስቀሳ በሚገባ አስተውለን ወደ አዘጋጁልን ወጥመድ እንዳንገባ መጠንቀቅ እንዳለብን እናሳስባለን።

5. በሀገር ውስጥ ያሉ ሚዲያዎች በተለይ ህዝብ ሊያገለግሉ የተቋቋሙ የሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የህዝብ ምሬት እና የሚደርስበት በደል በማስተጋባት እንዲሰሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

6. በውጭ የሚገኝ ትግራዋይ በማህበራቶቹ በኩል የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በማጠናከር የትግራይ ህዝብ በተለየ መልኩ እንደተጠቀመ እና እንደለማ በማስመሰል የሚቀርብ የሐሰት እና ጥላሸት የመቀባት ቅስቀሳ እሱን ተከትሎ በሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወንድሞቹ እና እህቶቹ የተነጠለ በማድረግ ለጥቃት ዒላማ የማድረግ ዘመቻ ለማስቆም እና ለማርከስ የሚያስችል እውነተኛ የህዝቡን ሁኔታ የሚይሳይ የሚዲያ ተቋም ለማቋቋም ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

7. ዘርን መሰረት ያደረገ በማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ላይ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ የንብረት ማውደም መፈጸሙ በእጅጉ አዝነንል፤ ድርጊቱን አጥብቀን እናወግዛለን።

8. በሀገር ውስጥም ኾነ በውጭ የሚኖሩ የተለያዩ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወላጆች በሀገራችን የተፈጠረውን አሳሳቢ ሁኔታ በተለይ ማንነት መሰረት ያደረገ ጥቃት አስነዋሪ መኾኑን በመረዳት ለማንም ህዝብ የማይጠቅም ይልቁንስ ሁኔታው ወደ ከፋ ደረጃ ከተሸጋገረ ብሔር በማይለይ መልኩ መላውን ህዝባችን የሚጎዳ እንዲሁም የሀገራችን ህልውን ወደ አደጋ የሚከት መኾኑን ተገንዝበን ማንነት መሰረት ያደረገ የጥላቻ እና የማጥቃት ቅስቀሳ ለመመከት በምናደርገው ሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ በጋራ እንድንሰራ ጥሪያችንን እናቀርባለን።

የኢትዮጵያ ህዝቦች ትብብር ይጠንክር! ሰላም እና ብልጽግና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ!
——–

የዋሽንግተን ዲሲ እና አካባቢዋ ተጋሩ ህዝባዊ ስብሰባ ተሳታፊዎች

ጃንዋሪ 27፣ 2018 (ዋሽንግተን ዲሲ)

 

ቪዲዮ (link):-

—-

Avatar

Guest Author

more recommended stories