​የትውልዱ ትግል እና ኢህአዴግ ሊከተለው የሚገባው ቀጣይ አቅጣጫ

(ሀብቶም ገብረእግዚያብሄር)

እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች ከጠቅላላው ህዝብ የበለጠውን የሚይዘው ወጣቱ ትውልድ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በእንደዚህ አይነት ሀገሮች ላይ የፖለቲካ ስልጣን የሚይዙ ሃይሎች ይህንን ያለማቋረጥ የሚፈጠረውን ብዙ ነገር ሊፈጠርለት የሚገባን አዲስ ሃይል እና ትውልድ ፍላጎት ቀድሞ የሚተነብይ እና ለመሟላቱም የሚተጋ ሊሆን ይገባል፡፡ 

ይህ ሁኔታ በማይሟላበት እና ከዚህ በተቃራኒ በሚሆንበት ጊዜ ይህ ትኩስ ሃይል ፍላጎቱን ለማሟላት ምንም ከማድረግ የማይመለስ ተፈጥሮዋዊም አለማዊም ብቃት ያለው ሃይል ነው፡፡ የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅም ጥቅሙን ለማስከበር የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ሃይል ነው፡፡ 

ይህንንም እውነታ ለመረዳት የመጀመሪያው ዲሞክራሲያዊ አብዮት በደርግ ከተጠለፈ በሗላ በሀገራችን ሁለተኛውን ዲሞክሪያሳዊ አብዮት ያቀጣጠሉትን እና በወቅቱ የመሩትን መላው የሀገራችንን ወጣቶች ታሪክ ማየት በቂ ነው፡፡ 

የህዝብ ጥያቄ እና የሚኖሩበት ማህበረሰብ ዘርፈ ብዙ እውነታ በሚኖሩበት ዘመን፣ በዛ ምክንያት ባገኙት ህብረተሠባዊ ንቃተ ህሊና የሚፈጥሩት ሐሳብ፣ በዚህ ንቃተ ህሊና አማካኝነት የሚያነሱት አጀንዳ፣ ተጠያቂው አካል ወይም የፖለቲካ ስልጣኑን የተቆጣጠረው ሃይል በሚሰጣቸው መልስ እንዲሁም ከፖለቲካ ሃይሉ የሚሰጠው መልስ አሉታዊ በሚሆንበት ጊዜ ትግሉን ወደስኬት ለማራመድ ሊኖር ስለሚገባ ፅናት፣ ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት እዚህ ጋር ልንዘነጋ አይገባም፡፡

ዞሮ ዞሮ ይሄ እውነታ ይህ ወጣት ትውልድ በሚኖርበት ዘመን እና በሚኖርበት ሀገራዊ ማህበረሰብ  የዕድገት ደረጃ ይለያይ እንጂ በዋነኝነት ሊያራምደው የሚችለው እና ሲያራምድ የኖረው አጀንዳ በሚኖርበት ማህበረሰብ ሊኖረው ስለሚገባ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና ተጠቃሚነት ብቻ ነው፡፡ 

ይህም የተጠቃሚነት ጥያቄ በዋነኝነት በትኩሱ ሃይል ይነሳ እንጂ በወቅቱ ተገቢው ምላሽ ካልተሰጠው ቀስ በቀስ የዚህ ትኩስ ሃይል ምንጭ እና ለመፈጠሩ ምክንያት ወደሆነው መላው ህብረተሠብ በመዛመት ሀገራዊ የጥያቄ መልክ መያዙ የዚህ ሃይል ቀጣይ ስኬት እና ወደተሟላ የለውጥ ሃይል የሚቀይረው መላውን ህብረተሠብ አስተሳሳሪ ነባራዊ ሂደት ነው፡፡ 

ይህ እውነታ በተለይ ሗላ ቀር ሆነው ከፊውዳል ማህበረሠባዊ መዋቅር ወደተሟላ የካፒታሊስት ማህበረሰብ ለመለወጥ በዲሞክራሲያዊ አብዮት በማይመሩ በሃገርኛ ቅፅል ስም ጆተኒ (በሳንቲም የሚሰራ በሃገራችን በስፋት ያለ መጫወቻ) ብለን መሰየም በምንችላቸው መንግስታት ባሉ የስልጣን ባለቤቶች ˝ጥርስ ላይ ተሰክቶ አልዋጥ በማለት ጉሮሮን እንደደፈነ ስጋ˝ መተንፈሻ የሚደፍኑና ባፋጣኝ መፍትሄ ካላገኙ የሚገሉ ወይም በሌላ አማርኛ ያለውን ስርዓት ለማፍረስ የሚችሉ ሃይሎች ናቸው፡፡ 

በነዚህ ፍትህ ፈላጊ ትኩስ ሃይሎች ላይ ሊኖረው የሚችለው ደካማ ጎን በተገቢው መንገድ የሚመራቸው በማጣት ሌላ የተለየ አጀንዳ (በግልፅ የተቀመጠም ሆነ የተደበቀ) ባላቸው ጥቂት ሆነው ባልተደራጁም ሆነ በተደራጁ ውሱን ቡድኖች እንዲሁም ሌላ የተለየ ፀረ ህዝብ አጀንዳ ባላቸው ሃይሎች ከእውነተኛ ትግላችው ቀድመው ወዳላሰቡት ወይም በቅጡ ወዳልተረዱት እና ወደአልተዘጋጁበት የትግል አቅጣጫ መጠለፍ መቻሉ ነው፡፡ ይህም በሚሆንበት ጊዜ ይሄ የለውጥ ሃይል ታግሎ መጣል ካለበት ጠላቱ ላይ ትኩረቱን ተነጥቆ አዙሪቱ ወደማያልቅ ትግል እና መስዋዕትነት እንዲገባ ይሆናል፡፡ 

ከዚህ ድክመት ውጪ በማንኛውም ቦታ እና ማህበረሠባዊ መዋቅር ውስጥ የሚገኝ ትኩስ ሃይል ያሰበውን አላማ በአግባቡና በጥብቅ ዲሲፕሊን መዋቅራዊ በሆነ መልኩ አብዮቱ ማድረግ ከቻለ አላማውን ከማሳካት የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑ እና ማሳካቱ ከሁሉም የህብረተሠብ ክፍሎች የተለየ ያደርገዋል፡፡

ዛሬም ከተፈጥሮዋዊ ባህሪያት እና ከመገለጫዎቹ ባልተለየ መልኩ እንደማንኛውም የህብረተሠብ ዕድገት ለውጥ ውስጥ እንደሚገኝ እና ወቅታዊ ፍላጎቱ እንዳልተሟላለት ሃይል ሀገራችን ወጣት ከፍተኛ አብዮት ውስጥ ከገባ ጥቂት የማይባል ጊዜ አሳልፈናል፡፡ 

ሀገራችንን የሚመራው ኢህአዴግ  በዚህች ሃገር ስልጣን ከተረከበ ጊዜ አንስቶ ከነእንከኑ ቀላል የማይባሉ ሀገራዊ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡ እነዚህ ስኬቶች በዜጎቻችን የእለት ተለት ኑሮ ላይ ካሳደሩት በጎ ተፅዕኖ ባሻገር በከፍተኛ ደረጃ ለአዳዲስ ህዝባዊ ፍላጎቶች እና በለውጡ ልክ የተወሳሰቡ ሁኔታዎችን እየፈጠረ መጥቷል፡፡ 

እንደሚታወቀው ኢህአዴግ በሚመራበት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ የሰነቀው አላማ እና ለማሳካት የሚፈልገው ነገር የሀገራችን ህዝብ ወደተሟላ ካፒታሊስታዊ ማህበረሰብ እስከሚቀየር ድረስ የሁሉንም የህብረተሰብ መደቦች ፍላጎትን በፍትሃዊነት በሚያሟላ መልኩ ቅርፅ እያሲያዙ እና እየመሩ መሄድ እና የሁሉም መድቦች እድገት ተመጣጣኝ ሆኖ አላማው በሚሳካበት ወቅት የተፈጠረው ሁኔታ ለሚፈልገው አስተሳሰብ ቦታውን መልቀቅ ነው፡፡ 

ይህም ሀገራችን ከነበረችበት የፊውዳላዊ ስርዓት እና ቅጥ አምባሩ ከጠፋው የደርግ ስርዓት በተራማጁ ሙሁር አማካኝነት ህብረተሠቡን ወደተሟላ ለውጥ የመውስድ የባላአደራነት ሸክም ነው፡፡ 

በዚህም ሪዕዮቱ የኢትዮጲያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክሪያሲያዊ ግንባር ወደተሟላ ካፒታሊስታዊ ህብረተሠብ ለሚደረገው የህዝባችን ጉዞ ከነጉድለቶቹ መልካም መደላድሎችን መፍጠር ችሏል፡፡ 

መፍጠር እንደነበረበት ፈጥሯል ወይ የሚለው ጥያቄ ግን በአግባቡ መመለስ አለበት፡፡

እንደሃገራችን አይነት መሰረቴ ህዝብ ነው ብሎ ህዝብ የሚመራና መርሁ ዲሞክሪያሲያዊ አብዮት የሆነ ፓርቲ እየፈጠራቸው በሚሄዱት የህብረተሠባዊ ለውጥ መደላድሎች የተለዩ እድሎች እና አደጋዎች ይዘው እንደሚመጡ ማወቅና መዘጋጀት አለበት፡፡ 

ወደተሻለ ሂደት እየቀየርኩት ያለ ማህበረሠብ ወደሰፉ ፍላጎቶችና ወደተወሳሰቡ ማህበረሰባዊ ኡደቶች ስለሚገባ በዛ ደረጃ የአመራር ክህሎቴና ምላሽ አሰጣጤ በተፈጠረው ህዝባዊ ፍላጎት እና መወሳሰብ ልክ እዘጋጃለሁ ብሎ መትጋት አለበት፡፡ ልፋቱ የትኛውንም ያህል ቢሆን! የዚህንም አካሄድ እለት በእለት መገምገምና የፖለቲካ ወትሮ ዝግጁነት መረጋገጡን መከታተል እና መገምገም ያስፈልጋል፡፡ 

ታዲያ ኢህአዴግ ከዚህ እውነታ አንፃር እንዴት ይታያል?

ኢህአዴግ በታሪኩ ለህዝባችን እየፈታቸው ከመጣቸው ጉዳዮች እና ቀጥሎ እየተወሳሰቡ ለሚመጡ ቀጣይ ጥያቄዎች በሚጠበቀው መልኩ እየተዘጋጀ እና አቅሙን ጊዜው በሚሻው መልኩ ዕያጎለበተ መጥቷል ወይ የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይኖርብናል፡፡

ምላሹም የህዝቡን ጥያቄ በተነሳበት አግባብ እና በሚፈለገው ፍጥነት በተወሳሰበበት መልኩ ተደራጅቶ እና ተዘጋጅቶ አልጠበቀም ነው፡፡

ልክ እንደዛፍ ላይ ዕንቅልፍ ልትወድቅ ስትል የሚነቃበት እንጂ አብዮቱን ያለመንገራገጭ ለመምራት ፖለቲካዊ ወትሮ ዝግጁነቱን በሚጠበቅበት መጠን በብቃት እያሟላ የመጣ አይደልም የሚል እምነት አለኝ፡፡

ለዚህም እውነታ ህልቆ መሳፍርት ምክንያቶችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ 

በዋነኝነት ግን ሪዕዮተ አለሙን በሞግዚትነት እየመራ ለተሟላ ስኬት ያደርሰዋል ተብሎ የታጨው ተራማጅ ምሁር ተራማጅ ሙህርነቱ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በየደረጃው ወደተሟላ መሪነት ማብቃት ነበር፡፡  

ለህዝቡ ካለው ተቆርቋሪነት እና የራሱንም ግላዊ ፍላጎት የህዝቡ ጥያቄ በሚሳካበት ወቅት ይሳካል ብሎ እንጂ ለኔ ብሎ የሚያደርገው ትግል አይኖርም ተብሎ በተራማጅነት ተመልምሎ ህዝቡን እንዲመራ የተደረገው ተራማጅ ተብዬ በሙሉ ባይሆንም ከላይ እስከታች ባብዛኛው ራሱን ወደገዢ መደብነት በመቀየር ከህዝብ አገልጋይነት ወደንዑስ የገዥ መደብነት ራሱን ወደመቀየር ተሸጋገረ፡፡ 

ኢህአዴግም የዚህን አዝማሚያ በእንጭጩ ከመቅጨት ይልቅ ሁኔታው የከፋ ተፅዕኖ ማሳደር እና የፀረ ህዝብ ተግባሩን በፓርቲው መዋቅር ሆኖ እስኪተገብር ድረስ የፓርቲውን የመደብ መሠረት ከመርሳት፣ ህዝባዊ ተቆርቋሪነትን በማጥፋት፣ በሌብነት ተግባራት በስፋት በመሳተፍ፣ በስንፍና በዳተኝነት ይኸው እስከአሁን የሆነው ከህዝባዊነት ያፈነገጠው ሁኔታ ሊሆን ችሏል፡፡ 

በዚህም ምክንያት ዛሬ እምነት የጣለበትን ሠፊውን ህዝብ በአግባቡ መምራት ተስኖት ወደቀውስ ውስጥ እንዲገባ ሆኗል፡፡

የታገሰውም ሆነ መታገስ የበቃው፤ ዝምታን የመረጠውም ሆነ በመናገር የሚመጣውን መከራ ለመቀበል የፈቀደውን ትኩስ ሃይል ከሞላ ጎደል ኢህአዴግ በፈጠራቸው መልካም እድሎች እና ነባራዊ የአለም ሁኔታዎች ጥያቄውና ፍላጎቱ የሰፋ ሆኖ በጥያቄዎቹ ልክ ምላሽ ባለማግኘቱ የተነሳ  ትውልድ ነው፡፡ 

ለፍትህ ከመሆኑ በስተቀር ከዚህ ቀደም ከተነሱት የጊዜው ወጣቶች ጭብጡ ፍፁም ይለያያል፡፡ የዛሬ አስር አመት የነበረ ወጣት እና ዛሬ ያለ ወጣት በምንም ተዓምር የሚፈልጉት ነገር አንድ ሊሆን አይችልም፡፡ በርግጥ የሁሉንም አዲስ ትውልድ ጥያቄ ፍትሃዊነት መሆኑ ያመሳስላቸዋል፡፡ ምንም እንኳ የአጀንዳው ጥልቅ ይዘት መለያየቱ ቢያስተማምነንም፡፡

የወጣቱ ጥያቄ እና የምንጠብቀው የኢህአዴግ መልስ!

የዚህ ዘመን ወጣት በዋነኝነት ይዞት የተነሳው ጥያቄ ወቅቱ በሚጠይቀው መልኩ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ነው፡፡  ከሞላ ጎደል የበላተኛ ተመልካች እንድሆን ተደርጌያለሁ የሚል ተጠቃሚ ካለመሆን የመነጨ ቁጭት ነው፡፡ ዘርፈ ብዙ ነው በሚባለው  የሃገሪቱ እድገት ውስጥ የሚገባውን አስተዋፅዖ እንዲያበረክት ዕድል እንዲመቻችለት እና ተጠቃሚነቱም በዛው ልክ እንዲሰፋ ካለው ፍላጎት ነው የአመፁ መነሻ፡፡ ልብ እንበል ሁኔታዎች ተባብሰው ወደአመፅነት እስኪቀየሩ በዝምታ የተመለከተ አካል አለ፡፡

ከ2006 መባቻ ጀምሮ እዚህም እዛም በሚነሱ አመፆች የትኩስ ሃይሉ ጥያቄዎች መታየት ቢጀምሩም ኢህአዴግ ይህንን አዝማሚያ በቶሎ ተረድቶ በከፍተኛ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ችግሮችን ለመፍታት  መንቀሳቀስ አልቻለም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ችግሮቹ እየሰፉና በአጭሩ በፖለቲካዊ ውሳኔ ሊፈቱ የሚችሉ ነገሮች መልካቸውን እየቀየሩና አጀንዳቸው እየሰፋ እንዲሄድ ሆንዋል፡፡ 

በፓርቲው ቁርጠኝነት ማጣት ወጣቱ ሃይል ለፍትሃዊ ተጠቃሚነት ያነሳው ጥያቄ በቶሎ ምላሽ ባለማግኘቱ በውስጥም በውጭም የሚኖሩ የስርዓቱ ጠላቶች ይህንን ሃይል እንዲቀራመቱት እና በተወሰነ መልኩም የአጀንዳቸው አራማጅ ሲያደርጉት ተስተውሏል፡፡ ህዝብ ለሚያነሳው ጥያቄ ወቅታዊ እና ተገቢውን ምላሽ አለመስጠት ምን እንደሚያስከትል ሀገራችን አሁን ያለችበት ሁኔታ አስረጂ ነው፡፡

ህዝቡ ባጠቃላይ በዋነኝነት ወጣቱ በመልካም አስተዳደር እየተሰቃየ እና በተራማጅ ምሁርነቱ ህዝቡን መርቶ ለተሟላ የማህበረሰብ እድገት ያደርሳል የተባለው አብዛኛው በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት አመራር ኑሮው እየተደላደለ እና በሃብት ላይ ሀብት እየጨመረ ሲሄድ ፓርቲው እና መንግስት ባጠቃላይ በዝምታ ነበር የተመለከተው፡፡ 

ባብዛኛው በመዋቅሩ ውስጥ ያሉ አመራሮች እራሳቸውን ከአገልጋይነት ወደጆተኒነት የቀየሩ ናቸው፡፡ መቼም ጆተኒ የማያውቅ የለም ሳንቲም ካልተጨመረበት በስተቀር ምንም አይነት አገልግሎት አይሰጠም፡፡ 

ይህንን ፀሃይ የሞቀው ተግባር በግልፅ እየታወቀ ይህንን ጆተኒያዊ ባህሪ እያስታመመ እና እንዳላየ እያለፈ ሳይፈታ ዛሬ ላይ ልንደርስ ችለናል፡፡ 

ይህም የሚያሳየን በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ትክክለኛ ተራማጆች እና ለህዝብ እድገት የሚተጉት ታጋዮች በሌብነት ዋነኛ ተዋናይ ሆነው ራሳቸውን ወደገዥ መደብነት በቀየሩት እንዲሁም ወደሞቀበት በሚያጋድሉ ማህል ሰፋሪ አደር ባዮች በስፋት ብልጫ ተወስዶባቸው እንደነበረ ነው፡፡ 

ይህ የሚሆነው ግን አሁን እስካለንበት ጊዜ ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳ አብዮታውያን እና ትክክለኛ የህዝብ ልጆች ለጊዜው ብልጫ ቢወሰድባቸውም ሀገራችን አሁን የደረሰችበት የቀውስ ደረጃ እና የህዝቡ በተለይ የወጣቱ ሃይል ግፊት ትልቅ ጉልበት ይዞላቸው ይመጣል፡፡ 

እንደሀገር ወይ መጥረግ ወይ መጠረግ ላይ በሚደረስበት ጊዜ የዘቀጠው ጥገኛ ሃይል የተለያዩ ማስቀየሻ አጀንዳዎችን እየፈጠረ ለመንቀሳቀስ ቢሞክርም የህዝቡን እና የወጣቱ ሃይል ግፊት ባግባቡ የሚጠቀምበት ከጥገኝነት የፀዳው ተራማጁ ሃይል ነው፡፡ የሚቆረጠውን ቆርጦ ፖለቲካዊ ትግሉን በድል ከተወጣም በሗላ ይህንን ሃይል ባግባቡ በማደራጀት እና ማበርከት ያለበትን እንዲያበረክት እድሉን ካመቻቸ መሠረቱ የሰፋ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገብ ይችላል፡፡ 

ስለዚህ በኢህአዴግ ቤት ያለው ፖለቲካዊ ትግል በተራማጅ እና በህዝብ ተቆርቋሪዎች በአሸናፊነት በሚጠናቀቅበት ጊዜ የኢትዮጲያ ህዝብም  ሆነ ወጣቱ የሚከተሉት አፋጣኝ እርምጃዎች እንዲከናወኑ ይፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡

1) ኢህአዴግን በመሰረቱት በአራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ከትንሽ እስከትልቅ ሌቦችን ለፍትህ በማቅረብ የማያወላውል እርምጃ መውሰድ መጀመሩን ለህብረተሰቡ ማሳየት።

2) ከቀበሌ አመራር ጀምሮ እስከላይኛው የመንግስት መዋቅር ድረስ ባሉ ጆተኒ አመራሮች ህገ ወጥ በሆኑ መንገዶች የተከማቹ ንብረቶች በስፋት ህዝቡን በማሳተፍ እንዲጋለጡ በማድረግ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም በተለይ ለወጣቱ ሲባል ህጉን በተከተለ መልኩ መውረስ፡፡ ለዚህ ደግሞ የህዝቡ ተሳትፎ የማይተካ ነው፡፡ እያንዳንዷ ሌብነት ከህዝቡ የተሰወረ አይደለም፡፡ 

ይህም ሁለት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ አንደኛው ያላግባብ የተከማቸ ንብረት የፈጀውን ጊዜ ቢፈጅ መጋለጡ እንደማይቀር ያሳያል፡፡ በዚህም ያጠፋውን ከመቅጣት ባሻገር ለመጪውም እንዳይሞክራት መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መንግስት ከሚመድበው በጀት በተጨማሪ ለወጣቱ  የስራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ ካፒታል ማስገኘት መቻሉ ነው፡፡

3) ወጣቱን በየዘርፉ በማደራጀት እና ወደማያቋርጥ ንቅናቄ ውስጥ በማስገባት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ብቻ ሳይሆን ይህ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነን ሃይል በእውቀትም ሆነ በክህሎት የሚበቃበትን እድል መፍጠር እና እገዛ ማድረግ፡፡

4) ችግሮች አሁን ባሉበት ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ህዝቡ ራሱ ከቀበሌ ጀምሮ ለመብቱ የሚታገልበትን ዲሞክራሲያዊ አሰራር መዘርጋት እና ተሳትፎውን ማረጋገጥ፡፡ አሁን ያሉንን የህዝብ ምክር ቤቶችን ባግባቡ በመፈተሽ እንደገና የሚደራጁበትን ሁኔታ አመቻችቶ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች መወከላቸውን ማረጋገጥ፡፡

5) ኢህአዴግ ፖለቲካዊ ወትሮ ዝግጁነቱን ሊፈትሽ እና ሊያስተካክል ይገባል፡፡ በህዝባችን ላይ የሚፈፀሙ በደሎች ሠላም አሳጥተው ሀገራችንን ምስቅልቅል ውስጥ እስኪከት በዝምታ መመልከት የለበትም፡፡ ፖለቲካዊ ወትሮ ዝግጁነት ቢኖር ችግሮች በተከሰቱበት ቅፅበት እርምጃ በመውሰድ ችግሮች እንዳይሰፉና በደሎች እንዳይሰፉ ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ፓርቲው ይህንን ወትሮ ዝግጁነት የሚያጎለብትበትና የሚፈፅምበትን አሰራር በማጥናት ባፋጣኝ ወደትግበራ መግባት ይኖርበታል፡፡

ባጠቃላይ ኢህአዴግ ይህንንና ወገናዊነቱ ለሠፊው ህዝብ የሆነ ሌሎች እዚህ ጋር ያልተጠቀሱ እጅግ ብዙ ተግባራትን መተግበር ከቻለ እስከዛሬ ካሳካው በላይ ህዝቡን በማነቃነቅ ያለጥርጥር የህብረተሰባችንን እድገት እና ሀገራዊ የመዋቅር ለውጡን ለማሳካት ከአቀደው ጊዜ በታች ለማሳካት የሚያስችለው ጉልበት ይሰንቃል፡፡ ለማንኛውም ፓርቲው የጀመረው ስብሰባ በህዝብ ሀይሎች አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ እመኛለሁ፡፡ 

ሞት ለጆተኒያዊ እሳቤና ተግባር!  ድል ለሰፊው ህዝብ!

************* 

* የዚህን ጽሑፍ ጸሐፊ ሀፍቶም ገ/እግዚያብሄር በኢሜይል አድራሻ [email protected] ማግኘት ይቻላል።

Guest Author

more recommended stories