(ኢዛና  ዘኢትዮጵያ)

አሁን በአገራችን ፖለቲካ እየታየ ያለውን አደገኛ አዝማሚያ ለማስተካከል የአዝማሚያው መገለጫና መሠረታዊ ባህሪያት በትክክል መረዳት የመጀመሪያው እርምጃ ነው፡፡ የችግሩ ገጽታዎች በርካታና ውስብስብ ከመሆናቸው የተነሳ ይህች ፁሁፍ የአዝማሚያው የተሟላ ስዕል ለመስጠት ወይም ለመተንተን አታልምም፡፡ ይልቁንም የአዝማሚያው ዋነኛ መገለጫ የሆነውን የህዝብኝነት (populism) ፤ ህዝበኝነት የሚገለጥባቸውን የሃይል አመክንዮ (blood and iron) እና ማላከክ (scapegoating) ለመግለጽ ተሞክራለች።

በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ የፕራሻ ቻንስለር የነበረው ቢስማርክ ወደ 39 የሚጠጉ ራሳቸውን እንደ ነፃ መንግስታት የሚቆጥሩ ጀርመንኛ ተናጋሪ ግዛቶችን ወደ አንድ በማምጣት የተባበረች ጀርመን ለመፍጠር ማለም ጀመረ፡፡ ቢስማርክ የተባበረች ጀርመን ግንባታ ህልም እውን ለማድረግ በ1864 ከዴንማርክ ጋር በ1866 ደግሞ ከኦስትሪያ ጋር ጦርነቶችን አካሂዶ አሸናፊ ሆኖ በመውጣቱ የልብ ልብ እየሰጠው መጣ። ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ባሻገርም በቴክኖሎጂና በኢንዳስትሪ ፈጣን ዕድገት ማስመዝገብ ጀመረ።  እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1860ዎቹ ገደማ ከፈረንሳይ ጋር የሚወዳደር የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ መድረሱ በወታደራዊ ሃይልም በአውሮፓ በሶስተኛ ደረጃ የሚሰለፍ አድርጐ በመገንባቱ ይበልጥ የልብ ልብ ተሰምቶት ነበር፡፡ ይህ ሆኖም የየአከባቢው ትናንሽ  ጀርመንኛ ተናጋሪ መንግስታት በቢስማርክ አስተዳደር ስር ገብተው አንድ ጀርመን ለመመስረት ፍቃደኛ አልነበሩም፡፡

ቢስማርክ በኢኮኖሚና ወታደራዊ ሃይሉ ሊያማልላቸው ያልቻለ መንግስታት ወደ አንድ ለማምጣት አህጉራዊ ነውጥን በመፍጠርና የተናጠል ህልውናቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ስጋትና ፍርሃት በመፍጠር ወደ አንድ ግንባር ለማምጣት ወጠነ። ነጻ መንግስታቱ ወደ አንድና የተባበረች ጀርመን ለማምጣት የሚከተሉት ስተራተጂዎችን ነደፈ። እነሱም የራሱን ግዙፍ ተክለ ሰወነት (charisma) መጠቀም፣ የደምና ወታደረዊ ጉልበት መርህ (blood and Iron) መከተልና የጋራ ፍላጎት “Cause” መፍጠር ናቸው። የጋራ ፍላጎት ለመፍጠር ከተጠቀመባቸው ዘዴዎች ዋነኛው ደግሞ ፈረንሳይን እንደ ወራሪ ተደርጋ እንድትታይ ማድረግ። በቢስማርክ ስሌት ለወጠነው ዕቅድ የሚስማማ ስልት ከፈረንሳይ ጋር ጦርነት መግጠም ሆኖ አገኘው፡፡ ቢስማርክ ይህንን ውሳኔ ላይ ሲደርስ እራሱንና ጀነራሎቹ ከፈረንሳይ ጋር ጦርነት ገጥመው ማሸነፍ እንደሚችሉ ልበ ሙሉእነት ተሰምቷቸው ነበር፡፡ በ1970 ጦርነቱ ተካሄደ ቢስማርክም እንዳሰበው ተሳካለት።

በወቅቱ ፈረንሳይን ይገዛ የነበረው ናፖሊዮን ሶስተኛው በፕራሻ የሽቅብ ዕድገት ምክንያት ስጋት ውስጥ የገባበት ወቅት ስለነበረ ቢስማርክ የፈረንሳይን ስጋት በማባባስ ወደ ጦርነት እንዲገባ  ለመተንኮስ  ቀላል ሰራ ሆነለት፡፡ፈረንሳይን በማበሳጨት ወደ ጦርነት ለመገፋፋት ጥሩ መሳሪያ አድርጐ የወሰደው ደግሞ የጀርመንን ንግስና ከሆሀንዞለርን አስነስቶ በስፓንሽ ንግስና ዘውድ የማስቀመጥ ሃሳብ ለፈረንሳይ ፕሮፖዛል አቀረበ፡፡ ቢስማርክ እንደገመተው ፈረንሳይ በመከበብ ስሜት ውስጥ ከተታት፤ በፈረንሳይ ዕይታ የጀርመንን ንግስና በስፓንሽ ንግስና ማስቀመጥ ማለት ለብዙ ዘመናት ተጠብቆ የቆየውን የአውሮፓ ሃይል ሚዛን እና የፈረንሳይን አገዛዝ ማዛባትና መለወጥ ማለት ነበር፡፡ ይህ ዕውን ከሆነ የፈረንሳይን ክብርና ፍላጎት አፈር ድሜ እንደመክተት ተቆጠረ፡፡

ስለሆነም ቢስማርክ ባቀረበው ፕሮፖዛል ላይ ማስተባበያ እንዲሰጥ ናፓሊዮን ቢጠይቅም የቢስማርክ መልስ እምቢታ ሆነ፡፡ የጦርነት ውጥረት እያየለ ሲሄድ ቢስማርክ ያኔ ኢሞስ ተሌግራም ተብሎ የሚታወቅ ፕረስ በመጠቀም ሁኔታውን እንዲጋጋልና ናፓሊዮን ጦርነት እንዲያውጅ ገፋፋው፡፡ ቢስማርክ ባቀደለት መንገድ ተከትሎ ናፓሊዮን ሶስተኛው ጦርነት አወጀ። ቢስማርክ በዋናነት የፕራሻ ጦር በመጠቀም እንዲሁም ከተመረጡ ብሄራዊ ነገስታት (Principalities) በተወጣጣ ሰራዊት ድጋፍ በመታገዝ በጦርነቱ አሸናፊ ሆኖ ወጣ፡፡ ድሉም የተባበረች ጀርመን ለመፍጠር ተጠቀመበት፡፡

ቢስማርክ የተጋነነ ፍርሃትንና ህልውናን የማጣት ስጋት በዝብዞ የውጭ ጠላት በመሳልና ሃላፊነት የጐደለውን ምላሽ እንዲሰጥ በማስገደድ በብሄራዊ ነገስታት ውስጥ ይታይ የነበረውን ማንቀላፋት እና ስታትስኮ የሰበረ ለውጥ ለማምጣት ተጠቅሞበታል፡፡ ሰዎችን በማጣትና ውድቀት ፍርሃት ውስጥ በመክተት ወደ ኢ-ምክንያታዊ እርምጃ እንዲገቡ በማድረግ ኢምፓየርን የመገንባት እና ቅቡልነትን (Legitimacy) የመፍጠር ስትራቴጂ ተከትሎ ግቡን አሳክቷል፡፡ በወቅቱ ከነበረው የዛ አከባቢ ሁኔታና የጀርመናውያን የውስጥ ሁኔታ የቢስማርክን ስትራተጂዎች  ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏል።– የፍራኮያ ጦርነትከሃምሌ 19,1870 እስከ ግንቦት 10,1871 ተካሂዷል፡፡

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የታየው ክስተት በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአገራችን አሁን እየታየ ካለው ሁኔታጋር በባህሪዩ የማይመሳሰል ቢሆንም፤ በሃገራችን ችግሩን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉት እንቅስቃሴዎችን ልብ በሎ ለተመለከተ ግን ቢስማርካዊ ናቸው ወይም ቢስማርክ መሳይ መሪ ፍለጋ ላይ እነደሆንን ያመለክታሉ። ይኸውም የሃሳብ ጥራትና መስመርን ሳይሆን ጉልበትን፤ የቡድን ወይም ድርጅታዊ አመራር ሳይሆን፤ ግለሰባዊ ተክለ ሰውነትን፣ የውስጥ ችግርን በሰከነና አሳታፊ በሆነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ወደ ውጭ የማላከክ ስትራተጂዎች   አዝማሚያዎች ቁልጭ ብለው መታየት ጀምሯል።

ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በአገራችን አንዳንድ ቦታዎች በተለይም ቀደም ሲል በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች አሁን ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው አመፅና ግጭት መሰረታዊ ምክንያቱ የመልካም አስተዳደር እጦትና ኢኮኖሚያዊ ችግር ቢሆንም በሂደት ወደ ተሳሳተ አቅጣጫና ቅርፅ ሲቀየር ታይቷል፡፡ በጎንደርም ሆነ በኦሮሚያ የታየው ሃይል የተቀላቀለበት አመፅ የተሳሳተ አቅጣጫ ስለመያዙ ዋነኛ ምስክር ሃይል መጠቀሙ ብቻ ሳይሆን ሃይልን ለማሰባሠብ ስራ ላይ የዋሉትን መፈክሮች ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡  በጣም ብዙ መፈክሮች ጥቅም ላይ የዋሉ ቢሆንም በዋናነት፡-

1. ወያነ ከስልጣን ይውረድ (የወያነ አገዛዝ ይቁም)
2. ኦሮሞ የኛ ነው፤ አማራ የኛ ነው የሚሉት ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም. በነበሩት ጊዚያት እነዚህን መፈክሮች በመቀየስና በማሰራጨት ጃዋር መሐመድ በኦሮሚያ እና ግንቦት 7 በአማራ ከውስጥ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት የመሩት ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ በቀጠለው አመፅ ላይ ግን የጁውሃር መሐመድ መሃንዲስነት ሚና ያከተመ መስሎ እንዲታይ ያደረገና መሪውን በውል ለመለየት አስቸጋሪ ሆኖ የወጣ ቢሆንም በይዘት ለውጥ አልታየበትም፡፡

በአሁኑ ወቅት እየታየ ካለው አገራዊ ሁኔታ በመነሳት አብዛኛው ሰው በቀላሉ አራት ሃቆችን መገንዘብ ይችላል፡፡

1. ህዝብ በመልካም አስተዳደር እጦት ችግር ውስጥ በመግባቱ ምክንያት የተፈጠረ ቁጣ (resentment) እና ጠንካራ የማደግ ፍላጎቱ መጓተቱ የፈጠረው መከፋት (Anxiety) መኖሩ፣

2. በቁጥር አንድ የተጠቀሠው ሃቅ አገላለፁ ቢለያይ እንደሆነ ነው እንጂ ብሄራዊ ማንነት ሳይገድበው በሁሉም የአገሪቷ አገር ህዝቦች ያለ ጥያቄ መሆኑ፣

3. መሰረታዊ የህዝቦች ጥያቄዎች በመረዳት ወጥነት ባለው አቋምና ዲሰፕሊን መፍትሄ ይሳጣል ተብሎ ይጠበቅ የነበረውን ኢህአዴግ እና አባል ድርጅቶቹ በድርጅቱ ታሪክ ከሚታወቀው መስመርና ዕውነታ በወጣ መንገድ በመሄድና ህዝብኝነትንና ኢ-ዲሞክራሲያዊ ፉክክር በሚያጠናክር አኳኃን ለመመለስ እያደረገ ያለው ሙከራ ችግሩን እያባባሠው መሆኑ፣

4. በስርአቱ ውስጥ የተለየ ጥቅም ያላቸው ሃይሎች እና ፓትሮኔጅ ኔትዎርኮች እንዲሁም ከዚህ በፊት በተለያየ ጎራ የተሠለፉትን ሃይሎች ሁኔታውን በማባባስና የየራሳቸውን ፈረስ በመጋለብ በአገሪቱ እየተገነባ ያለውን መልካም ስርአት ገፅታ ለመደርመስና በ19ኛው ክፍለ ዘመን በአውሮፓ የታየው ኢምፓየር የመገንባት ጦርነትና አጋጣሚውን በመጠቀም ቅቡልነትን (legitimacy) ለመፍጠር የሚደረግ ውድድር በአገራችን እንዲገለጥ እና በከፍተኛ ፍጥነት እየተራመዱ መሆኑ ነው፡፡

ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ሶስት ያሉትን ሀቆች በተመለከተ በሌላ ፅሁፍ የሚታዮ ሆነው ለአሁኑ በተራ ቁጥር አራት የተጠቀሠውን ክስተት ባህሪና አደጋውን በተመለከተ መግለፅ አስፈላጊ ነው፡፡

ቀደም ብሎ እንደተገለፀው ቀደም ብሎ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የተከሠተው አሁን ደግሞ በኦሮሚያ እየተካሄደ ያለው አመፅ መሰረቱ ህዝባዊና ትክክለኛ ጥያቄ የነበረ ቢሆንም ከህዝቡ የተለየ ፍላጎት ባለው ሃይል ተቀምቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኦሮሞ ህዝብ ከትግራይ ህዝቦች ወይም አማራ፣ ሶማልያ እና ሌሎች ክልልሎች ህዝብ የተለየ ጥያቄ የለውም፡፡  የሁሉም ህዝቦች ጥያቄ ፍትሃዊ ዕድገት ከማስቀጠልና መልካም አስተዳደር ከማግኘት ጋር የተያያዘ ነው፡፡  በየክልሉ ያሉ ህዝቦች የተለየ በራሳቸው ሁኔታ የተቃኘ ጥያቄ ቢኖራቸውም እንኳ በራሳቸው መንገድ ህግን ተከትለው መፍታት የሚችሉት ጉዳይ ነው፡፡

ታዲያ እውነታው ይህ ከሆነ የተለየ ብሄራዊ ጥያቄ እንዳለና በዚች አገር ውስጥ ተበዳይና በዳይ እንዳለ እንዲሁም ችግሩ የውስጥና የራስ ሳይሆን ከውጭና በወያነ በተጫነ አገዛዝ የተፈጠረ አስመስሎ ለማስጮህና አመፅ ለማቀጣቀል ለምን ተፈለገ; የሚለው ጥያቄ ከስነልቦናዊ ባህሪያዊ ምልከታ ተነስቶ መመርመሩ ጠቃሚ ይሆናል፡፡  በዚህ ፁሁፍ አዘጋጅ ዕይታ አንፃር ሁለት ጉዳዮችን ማየት ጠቃሚ ይሆናል፡፡

1. በህዝቡ ውስጥ የተፈጠረውን መከፋት በመፍጠሩና በማባባሱ ሂደት ተዋናኝ የሆኑትን አፍራሽ ሃይሎች ችግሩ እንደ ዕድል ተጠቅመው ከቻሉ የነሱ ልዕልና የምትቀበል ኢትዮጵያ በመፍጠር ለመግዛት ካልቻሉ ደግሞ የኔ የሚሉትን ብሄር ነጥለው ኢምፓየር ለመፍጠር ወይም ደግሞ በአደናጋሪ መፈክር ተጠቅመው ተቀባይነት በመገንባት አሁን ባለው የሃይል ሚዛን ውስጥ የአምበሳውን ድርሻ ለመያዝና ለመደራደር የሚያስችላቸውን ቦታ ለመቆጣጠር እየተጉ ነው፡፡ ይህንን ለማሳካት ቢስማርክ በጀርመን እንዳደረገው ሁሉ የሌለን ጠላት በመፍጠር በውስጣቸው ያለውን መከፋፈል በማስወገድ ወደ አንድ ለማምጣትና የህዝቡን ትክክለኛ ጥያቄ አቅጣጫ በማሳት በነሱ ላይ ሊነሳ የሚችል ጥያቄና ብትር ለማስወገድ መስራት አለባቸው፡፡

በስነልቦና ሳይንስ መነፅር መሰረት በግለሠብ፣ በቡድን ወይም በህብረተሠብ ደረጃ ፍርሃት፣ጭንቀት (Anxiety) ወይም የህልውና (survival) ጥያቄ በሚቀሰቀስበት ወቅት ከጭንቀቱ የሚገላግል ታዳጊ መሪ ወይም መሲህ የመፈለግ፣ በዕውነት አለም የሌለውን አንድነት ለመፍጠር የመጣር፣ የመፋለም ወይም የመሸሽ (fight/flight) እርምጃ መውሠድና ከማትጣመረው ሃይል ጋር የመጣመር ጥረት (unholy pairing) ክስተቶች ማየት የተለመደ ነው (Derek Hendrikz, 1999)፡፡ በአንድ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ህብረተሠብ ውስጥ ይህችግር በሚታይበት ወቅት ሳይንሳዊ መፍትሄው የችግሩ ባህሪ በማጥናት ዋነኛ ምንጭ ለይቶ ማከም ነው፡፡ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ግለሠቦችና ሃይሎች ዋነኛ ትኩረት ግን በተገለቢጦሽ የሚታይ ነው፤ ክስተቱን ለራስ አላማ መጠቀም፡፡ ስጋትና ፍርሃትን ማጫርና ማባባስ በዚህ ሂደት ውስጥ የራስን ጥቅም ማስከበር ዋናው አላማቸው ነው፡፡ አሁን በአገራችን እየታየ ያለው ሃቅም ይህ ነው፡፡

ቀደም ሲል ኢህአዲግ የሚከተለው የአብዮታዊ ዲሞክራሲና ልማታዊ መንግስት ፅንሰሃሳብ ዋነኛ አቀንቃኞች መስለው ይታዩ የነበሩትን ሳይቀር“ሰዎች በትምክህትና ጠባብነት መፈረጅ አንድነታችን ለመከፋፈል የተዘየዱ መሳሪያዎች እንጂ እንዲህ ብሎ የለም” ብለው እስከ መስበክና ከዚህ ቀደሞ በአላማም በፍላጎትም የ180 ዲግሪ አሰላለፍ ላይ የነበሩትን ሃይሎች ሳይቀር ያካተተ አንድነት እስከመስበክ ደርሰዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ራሳቸውን የነፃ አውጪነት ሃላፊነት ካባ በማልበስ “እኛን ካልተከተልክ የነፃነት ትግልህ ይኮላሻል፤ጥቅምህን ለተንበርካኪዎችና ለወያነ አገልጋዮችት ዳርጋለህ፡፡ የእስካሁኑ ችግርህ ምንጮችም ለሌላ ያደሩ የላምህ ልጆችና ወያነ ናቸው፡፡” በሚል የሌለ ጠላት በመሳል የህዝብን ትክክለኛ ጥያቄ እያዛቡ ይገኛሉ፡፡

ይህ ሁኔታ ቢስማርክ የተከፋፈለች ጀርመን ወደ አንድ በማምጣት ኢምፓየሩን በምድረ አውሮፓ ለማስፋት የተጠቀመበት የሀገረ መንግስት ግንባታ (state building) አቅጣጫ ጋር የመመሳሰል ባህሪ ይታይበታል፡፡ በእውነቱ ከሆነ ፈረንሳይ የጀርመን ጠላት አልነበረችም፡፡ በራሷ ተነሳሽነትም ጦርነት አልጫረችም፡፡ሆኖም ቀድማ በተጎናፀፈችው ጥንካሬ ምክንያት የአውሮፓ ልዕለ ሃያል ተደርጋ ትታይ ነበር፡፡ ስለሆነም ቢስማርክ የራሱ የአውሮፓ ኢምፓየር የመገንባት ህልሙ የምታደናቅፍበት መሆኗ አምኗል፡፡  የፈረንሳይን ኢምፓየር አፍርሶ የጀርመን ኢምፓየር የመገንባቱ ጉዳይ ግን ለጀርመን ህዝብ የሚፈይደው ነገር አልነበረም:: ይልቁንስ ተከታትለው በተፈጠሩ የአለም ጦርነቶች የጀርመን ህዝብ ኢላማ ሆኖ እንዲመታ አደረጉት እንጂ፤ ጀርመንን ወደ አንድ የማምጣት ጥያቄን ለመመለስ ቢሆን ብዙ አማራጮች ማየት ይቻል ይሆናል፡፡

ፕሪሻዎች ራሳቸውን በኢኮኖሚ ዕድገት ማራኪ በማድረግ ቀልብን መግዛት (Positive attraction) በመፍጠር እንዲሁም በውይይትና ዲሞክራሲያዊ ድርድር ችግር መፍታት ከአማራጮቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡  ቢስማርክ ግን የውጭ ጠላት በመፍጠር ከፈረንሳይ ጋር ጦርነት ውስጥ በመግባት አንድነቱን ማምጣት መረጠ፡፡ የጀርመን ውህደት ዋነኛ ምክንያት ቢስማርክ በፈረንሳይ ላይ የለኮሰው ጦርነት ነው ብሎ መደምደምበራሱ አጠያያቂ ቢሆንም ቢስማርክ በወቅቱ የመረጠው አቅጣጫ በክፍለ ዘመኑ የነበረ የሠው ልጅ የማህበረሠብና አለማዊ ሁኔታ የሚፈቅደው እሱ ነበር ብሎ መሟገት ግን ይቻል ይሆናል፡፡

እዚ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ አለ፡፡የ19ኛው ክፍለዘመን ስልት በ21ኛው ክፍለዘመን መንፀር ሲታይ ኋላ ቀርና የማይሰራ መሆኑ ነው፡፡  ምክንያቱም በዚህ ዘመን በውሸት መፈክሮች ህዝብን አታሎ የተሳሳተ እርምጃ እንዲወስድ ማስደረግ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡  ሌላውን ደፍቆ ኢምፓየር መገንባት የሚቻልበት ዘመንም አልፏልና፡፡  ቢስማርክ ያንን እርምጃ በሚወስድበት ወቅት የነበረ ሁኔታ እና አሁን በአገራችን ያለው ሁኔታም አይገጣጠምም፡፡ ያኔ ፕሪሺያ በኢንዳስትሪና ቴክኖሎጂ ረገድ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገች በወታደራዊ ሃይል እየፈረጠመች ነበር፡፡

ዘመኑ በወታደራዊ ሃይልና ኢኮኖሚ የፈረጠመ ሌሎችን በመውረር ግዛት የሚያሰፋበት ሁኔታ ይፈቅድ ነበር፡፡ ወዘተ… ይህ ሁሉ በኛ ሁኔታ የለም፡፡ ይህ ሲባል ግን እንቅስቃሴው አሳንሶ ለማየት አይደለም፡፡ ምክንያቱም በተለይም በኛ ሁኔታ የዘረኝነትና የኋላ ቀር መፈክሮችን አንግቦ ትርምስ መፍጠር የሚያስችል ስፊ ማህበራዊ መሠረት አለ፡፡ ብዙ ስራ አጥና 27% ከደህነት ወለል በታች የሚኖር ህዝብ ባለበት አገር ውስጥ ኮርኳሪና ኋላ ቀር መፈክሮች እንደ መፍትሄ አማራጭ የሚያይና የሚከተል ሃይል መፍጠር ቀላል ነው፡፡ በዚህ ላይም በአቋራጭ የመበልፀግ ፖለቲካል ኢኮኖሚው በተለይም በከተሞች የበላይነት ከጨበጠበት ወቅት የምንገኝ በመሆኑ ሊፈጥሩት የሚችሉት አደጋ ከማንኛውም ስጋት በላይ መሆኑ በገሃድ እየታየ ነው፡፡ የብልጣ ብልጦች ህልምና እንቅስቃሴ ዋነኛ ትኩረት በህዝቦች መካከል ያለውን የአብሮነት ባህልና እሴቶች በመሸርሸር ጥርጣሬና ጥላቻን ማስፈንና በተባበረ የህዝቦች ክንድ ሊደርስባቸው የሚችለውን ጥቃት ማምከን ነው፡፡ ለዚህም ሲባል በአሁኑ ወቅት በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ አንዲት ጠንካራ ኢትዮጵያን ለመፍጠር የተጀመረውን ጉዞ በማጨናገፍ የራሳቸው መንገድ የመዘርጋት (path creation and construction process) እንዲሁም በ21ኛው ክ/ዘመን ውስጥ ከጭንቅ የሚገላግል ቢስማርክ ፍለጋ ተጣጥፏል፡፡ ይህ ችግርም ከኢህአዲግ ከራሱ የሚመነጭ ችግር መሆኑ የማይታበል ሃቅ ሆኗል፡፡

2. እላይ እንደተገለፀው አገር በማቅናት የሚጠበቀው ኢህአዲግም ችግር ላይ ወድቋል፡፡  የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መለያው ተሸርሽሯል፡፡  መርህ ተኮር አካሄዱ እየተፈተነና በህዝበኝነት እየተተካ ይገኛል፡፡በውስጡ ምህረት የለሽ ትግል የማካሄድ ባህሪው በመሞዳመድ እና አድርባይነት እየተተካ ይገኛል፡፡ ነገሮች ከፍ ብሎ የማየትና የመተንተን አቅሙ እየተዳከመ በአጫጭር ዕይታዎች እየተተካ ይታያል፡፡ በጋራ አመራር (Collective leadership) የመስጠት ባህሪ በተናጠልና የእኔነት ባህሪያት እየተበረዘ ይገኛል፡፡ችግሮች በሚከሰቱበት ወቅት ከስር መሠረታቸው መርምሮ ቆራጥ እና እውነተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ ያረጋገጠ አፈታት አቅጣጫው በቶሎ ቶሎና የይመስል እርምጃዎች መውሰድ እንዲሁም እንደ ራስ ምታትን የማስታገስ እርምጃዎች መውሰድ እየተተካ ነው፡፡

ይባስ ብሎም በአመራር ላይ የሚገኝ ሃይል ራስ በራሱ በመናናቅና መደማመጥ አለመኖር በውድድርና የራስ ኔትዎርክ በመዘርጋት እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ የመጠመድ ችግር አለበት፡፡ እንዲሁም በአንድ በኩል አሳሳቢ ችግር እንደሌለ የሚክድ  (denial mode) ውስጥ የገባ አድርባይ ሃይል በሌላ በኩል አሳሳቢ ችግር እንዳለ የገባው ነገር ግን መውጫ መንገዱ የጠፋውና የሚጨነቅ የተበታተነ ሃይል ከዚህ በተፃራሪ ደግሞ ሆን ብሎ ኢህአዲግን በመሸርሸር ፍላጎቱን ለመጫን የሚሠራ ሃይል በአንድ ጀልባ ተሳፍረው የሚጓዙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ከሚና አንፃር ሲታይም የችግሩ አሳሳቢነት የሚክድ አድርባይ ሃይሉ ዋነኛው አደጋ ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በሌላ በኩል በህገ መንግስታዊ ስርአቱ ተጠቃሚ ነኝ ብሎ ያመነ ህዝብ ወደፊት እንጂ ወደኋላ መመለስ የማይፈልግ ህዝብ መኖሩ የሰላማችን ቀጣይነት ዋነኛው መሠረት ሆኖ እየታየ ነው፡፡  ስርአቱን ማስቀጠል የሚፈልገው ህዝብ አንድም ባለፉት አመታት በተመዘገቡት ድሎች ተጠቃሚ በመሆኑ ሁለትም በዛው መንገድ ከተቀጠለ ከድህነት የመውጣት ተስፋው በመለምለሙ ነው፡፡  አሁን ህዝቡ እየጠየቀ ያለው መሪ ድርጅት ነው፡፡ የህብረተሠቡ ክፍል የሆነው የተማረው ሃይል አሰላለፍም በኢህአዲግ ውስጥ እየታየ ካለው አሰላለፍ የተለየ አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ስርአቱ እንዲወድቅ የሚፈልግ የተማረ ሃይል ቀላል ቁጥር እንደሌለው ሁሉ ስርአቱ እንዲቀጥል የሚፈልግ ሃይል ቁጥርም የትየለሌ ደርሷል፡፡ ሆኖም የዲሞክራሲና የልማት ሃይሎች በተበታተነና በተናጠል ሁኔታ ላይ ሲገኙ ተፃራሪው ሃይል የተሻለ መሰባሠብ ይታይበታል፡፡

አሁን መነሳት ያለበት ዋነኛው ጥያቄ ምን ይደረግ ነው፡፡  በዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ዕይታ አሁን ያለው ሁኔታ ተቀብሎ መቀጠል ብዙ ርቀት አይወስድም፡፡ ይልቁንስ አሳሳቢ የፖለቲካ ችግር እንዳለ መቀበል፤ችግሩም ከስርአቱ የሚመነጭ ሳይሆን ከራሱ ከኢህዲግ አመራር ብልሽት የሚመነጭ መሆኑን ማመን፤ የህዝቡ ፍላጎት በህገመንግስዊ ስርአቱ ፍትሃዊ ዕድገትን የማስቀጠል መሆኑን መረዳት፤ አለማዊ ሁኔታው ለህዝብኝነት እና የሴራ  ፖለቲካ  (political conspiracy) የተመቻቸበት ወቅት ቢሆነም  ቻይናን በመሳሰሉ ሃገራት ያለው ዕድገት ቀጣይነት ያለው እድገትና ለውጥ የብሩህ ተስፋ ፍንጣቂና ዕድል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለህገ መንግስቱ የቆመ ተቋማዊ ስርአት (Constitutional system) መገንባት መሆኑ ታውቆ ያደረ ሃቅ ነው፡፡

ከአሁኑ ሁኔታ ለመውጣት ግን በእጃችን ሁለት አማራጮች አሉ፡፡አንደኛው አሁን እየተኬደበት ያለው በቀውስ አስተዳደር ተጠምዶ እና ፈረንጆች እንደሚሉት በእሳት ላይ የተጣደች እንቁራሪት ስሜት (boiling frog mentality) ውስጥ መኖርና በጥፋት ቁልቁለት ተጉዞ የመበታተን አደጋ እንዲከሠት መፍቀድ ነው፡፡  ታላቁ መሪ መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት የሚያስፈራህ ነገር ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ተጠይቆ የሠጠው መልስ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡

“… ሁል ጊዜ ከእንቅልፌ የሚያባንነኝ ነገር ፍርሃት ነው፡፡ ይህች ከአንድ ሺህ አመታት በፊት ታላቅ የነበረች ሃገር ባለፉት አንድ ሺህ አመታት ወደታች ስታሽቆለቁል ቆይታለች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ የሚራቡባትና የሚሞቱባት ህልውናዋ አደጋ ላይ የወደቀባት ሃገር ነበረች፡፡ የአሁኑ ፍርሃቴ የሃገሪቱ ህልውና አይደለም፤ ይህንን አልፈነው ሄደናል እኔን የሚያስፈራኝ ነገር አንድ ሰው የሆነ ቦታ ላይ በሚሰራው ስህተት ምክንያት አሁን በዚች ሃገር ውስጥ ፍንጩ መታየት የጀመረው የህዳሴ ጭላንጭል ተመልሶ እንዳይደበዝዝ ነው” ብሎ ነበር፡፡

በዚህ ፁሁፍ አቅራቢ አረዳድ መለስ የሠጠው መልስ አንድ ሰው በሚፈጥረው ስህተት ሲባል በዚች አገር እጣ ፋንታ ላይ የአንድ ሠው ሚና አጋኖ ስለመመልከት ወይም ደግሞ በተለመደው የተዋረድ ስልጣን ዕይታ አንድ ባለስልጣን ለመጥቀስ አይመስለኝም፡፡ይልቁንስ ስርአቱን በማስቀጠል ግንባር ቀደም አመራር መስጠት ያለባቸውን ሃይሎች በሙሉ የሚመለከት ነው፡፡ስለሆነም ችግሩን አሁን በሚሄድበት ሁኔታ እንዲቀጥል መፈቀድ የለበትም፡፡ ስለሆነም ሁለተኛው አማራጭ አጠንክሮ መያዝ ያስፈልጋል፡፡

ሁለተኛው አማራጭ የዲሞክራሲ ሃይሎች እንደገና ራሳቸውን በማደራጀት መስመር ማዕከል ያደረገ ምህረት የለሽ ትግል ውስጥ ገብቶ ተጠናክሮ መውጣት ነው፡፡  በዚህ አማራጭ በኢህአዲግ ድርጅቶች ውስጥ ያሉትና ከድርጅቱ ውጭ ያሉትን ዲሞክራት ሃይሎች ከህዝቡ ጋር ባቀናጀ መንገድ መፈፀም ያለበት ነው፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን በመጀመሪያ ደረጃ ከድርጅታዊ እና ብሄራዊ አጥር ወጥቶ አለም አቀፋዊ ሁኔታን ያገናዘበ አገራዊ ዕይታ ላይ ማተኮር ይጠይቃል፡፡ በሃሳብ ፍጭት ላይ የተመሠረተ ሃይልን የማሠባሠብ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሠጠው ይገባል፡፡ከጥቃቅን አጀንዳዎችና በሁለተኛ ደረጃ የሚታዩ ግጭቶችን ወጥቶ ስርአቱን በማስቀጠል አጀንዳ (መስመር) ላይ ያነጣጠረ ከራስ በላይ የህዝብን ዘለቄታዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ የዲሞክራት ሃይሎች ጥምረት (Alliance) ላይ የሚያተኩር እንቅስቃሴ ሲደረግ ነው፡፡  በአሁኑ ወቅት ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ የሃሳብ ፍጭትና የሃሳብን ድንበር የለሽ መንሸራሽርና ውይይት ይጠይቃል፡፡ በዚህ ፁሁፍ አቅራቢ እምነት በአሁኑ ወቅት የመስመርና አቅጣጫ ግልፅነት ችግር ሳይሆን የአሠላለፍ መዛነፍ፣ የጐራ መደበላለቅና እንዲሁም ግለኝነትና አድርባይነት የፈጠረው ዲሞክራሲያዊ ሂወትና የትግል መቀዝቀዝ ነው ዋናው ችግር፡፡  ስለሆነም በድርጅት ውስጥ ያለም ሆነ በህብረተሠቡ ውስጥ ያለ አብዮታዊ ዲሞክራት በዲያሎግ ላይ የተመሠረተ መግባባት ፈጥሮ የመሪነት ሚናው ወደሚጫወትበት ምዕራፍ መሸጋገር አለበት፡፡ ሁሉም ጥረት ስርአቱን በመታደግ እና የተጀመሩትን የለውጥ ጭላንጭሎች በማስፋት ወደማይቀለበስበት ደረጃ ላይ በማድረስ ላይ ማተኮር አለበት፡፡

ይህ ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ፡፡ አንደኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎት አንድ ነው፡፡ ፍትሃዊ ዕድገትና ዲሞክራሲ ይህንን ህልሙ የሚያደናቅፍ ጥገኛ ሃይል ማስወገድና መልካም አስተዳደር ማስፈን፡፡ ስለሆነም ማንኛውም እንቅስቃሴ የህዝቦች ዘላቂ ጥቅም ያማከለና ህዝቡን በሚያሳትፍ አኳኃን መፈፀም ብቻ ነው የሚጠይቀው፡፡  ሁለተኛው ኢህአዲግ አሁንም አሳሳቢ ችግር ላይ ቢወድቅም የፀረ ህዝብ ፍላጎት ያለው ሃይል የበላይነት አልጨበጠም፡፡ ይህ በድርጅቱ ውስጥ የዲሞክራት ኢለመንቶች መኖራቸውን ያንፀባርቃል፡፡ ሶስተኛው በህብረተሰቡ ውስጥ ስርአቱን የሚደግፍ የተበታተነ ዲሞክራት ሃይል አለ፡፡ ሆኖም እነዚህ ሃይሎች መኖራቸው ሳይሆን መቀናጀታቸው ነው ዋስትና የሚሆነው፡፡ በመሆኑም ሃይሎቹን የማቀናጀት ወደ መስመር የማስገባት ጉዳይ ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፡፡ ቅንጅቱ ለማረጋገጥም ቀደም ብሎ እንደተገለፀው አጥር የማይበግረው በህዝባዊ አጀንዳ ላይ አሳታፊ ውይይት ማድረግ ነው፡፡

********

Guest Author

more recommended stories