የምንዛሬ ተመን ማስተካከያና ያለንበት አዙሪት

መነሻ

ብሔራዊ ባንክ የምንዛሬ ተመኑን በ15 በመቶ አወረደ

ዳራ

የአለም ባንክ ባለፈው አመት ሚያዝያ ላይ ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል ኢትዮጵያ የምንዛሬ ተመኗን ማውረድ (devalue) ይኖርባታል በማለት መክሮ ነበር፡፡

እንደ አለም ባንክ እምነት ብር የነበረው ተመን (19.60) ከእውነተኛ ዋጋው/አቅሙ/ (over-valued) የተጋነነ ነው፡፡ በቀላል አማርኛ አንድ ዶላር ይዞ ለመጣ ሰው 19.60 ብር ብቻ መስጠት ተመጣጣኝ አይደለም ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ተመኑን በ10 በመቶ በማውረድ 22 ብር ወይም በ20 በመቶ በማውረድ 24 ብር መስጠት አስመጪዎች ለአንድ ዶላር የሚያወጡትን ብር ስለሚጨምርባቸው የማያበረታታ (discouraging) ይሆናል፤ ላኪዎች በበኩላቸው ለሚልኩት ተመሳሳይ መጠን ተጨማሪ ብር ስለሚያገኙ ይበረታታሉ ይላል፡፡

ጥናቱ የ10 በመቶ የምንዛሬ ተመን ቅነሳ የውጭ ንግድን (export) ከአምስት በመቶ በላይ ሲያሳድግ የአመታዊ የኢኮኖሚ እድገትን (growth) ከ2 በመቶ በላይ ይጨምራል ብሎ ይተነብያል፡፡

በተጨማሪም ይላል ጥናቱ ወደ ውስጥ ገንዘብ የሚልኩ ኢንቨስተሮች እና ዜጎች ለሚልኩት ዶላር የተሻለ ብር ስለሚያገኙ ተጨማሪ ለመላክና ኢንቨስት ለማድረግ ይበረታታሉ፡፡ ይህም ወደ 11 ቢልየን ዶላር በደረሰው የሚመጡ የውጭ ምርቶች ወጪና ከ 3 ቢልየን ያልዘለለው ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ገቢ መሃከል ያለውን ልዩነት ያጠባል ይላል፡፡

ዶ/ር አለማየሁ ገዳ በግንቦት ወር Ethiopian Business Review በተባለ የሃገር ውስጥ መፅሄት ላይ ባወጡት ፅሁፍ የብሔራዊ ባንክን ተመኑን የመቆጣጠር ፖሊሲ ትክክል ነው ሲሉ የአለም ባንክን ትንበያና ምክር አጣጥለውታል፡፡

Photo - Ethiopian currency, one birr notes
Photo – Ethiopian currency, one birr notes

ያስቀመጧቸው ነጥቦች፡-

1/ ኢትዮጲያ ከምታስመጣቸው ምርቶች 70 በመቶው መሰረታዊ (strategic) ፣ ማለትም እንደ ነዳጅ፣ ዘይት… የመሳሰሉ በመሆናቸው ቢወደዱም ማስገባታችን የማይቀር በመሆኑ ለምንዛሬ ተመን ለውጥ ተጠባቂውን ምላሽ (reaction) የሚያሳዩ አይደሉም፡፡ ሰለዚህም ተመን ማውረዱ የእቃዎችን ዋጋ ከማውረድ ያለፈ ውጤት አይኖረውም፡፡ ይሄም መንግስት በትግል ያወረደውን ግሽበት መልሶ የሚቀሰቅስ ይሆናል፡፡

የኔ እይታ

እዚህ ጋር በዶ/ር አለማየሁ ትንተና ከሞላ ጎደል እስማማለሁ፡፡ በኢኮኖሚክስ የአንድ ነገር ውጤት በአጭር ግዜ እና በረጅም ግዜ ተከፍሎ ይታያል፡፡ አጭርና ረጅም የጊዜ ተመን ባይቀመጥላቸውም 1-3 አመታት ያሉት አጭር የሚባሉበት ልምድ ይታያል፡፡ ላኪዎችን የሚያበረታታ የተመን ማውረድ ውጤት ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ላይ በፍጥነት ሊታይ ቢችልም በኢንቨስትመንት ላይ ግን በዋጋ አዋጪነት ተስበው ፋብሪካዎች እስኪመጡና ማምረት እስኪጀምሩ በትንሹ ከ6 ወር እስከ አመት መፍጀቱ አይቀርም፡፡ (መንግስት ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከፍቶ ተዘጋጅቶ እየጠበቀ መሆኑ የማፍጠን ውጤት ይኖረዋል፡፡

ስለዚህም በአጭር ግዜ ውጤት የዶ/ር አለማየሁ ትንበያ ትክክል ሲሆን በረጅም ግዜ ውጤት ደግሞ የአለም ባንክ ጥናት ትንበያ ስሜት ይሰጣል፡፡ የብሔራዊ ባንክ ስራም ከተመን ማውረዱ የሚገኘውን ጥቅም ከጉዳቱ (ግምትን የጨመረ) ዝርዝር ሂሳብ ሰርቶ አዋጭውን መምረጥ ነው፡፡ የመረጃ እጥረት ባይኖር ይሄንን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትም ሊሰሩት ይችላሉ፡፡ ዶ/ር አለማየሁም ካላቸው ልምድና መረጃ ድምዳሜያቸው በቲዎሪ ብቻ ተመስርቶ እንዳልተሰራ አውቃለሁና ቀላል ቦታ የምሰጠው አይደለም፡፡

2/ ዶ/ር አለማየሁ “በራሴና በቀድሞ ተማሪዬ ጥናት እንዲሁም ባለፈው የተመን ለውጥ” የተረጋገጠ ያሉት የተመን ለውጡ በግሽበት ላይ የሚኖረው ውጤትን ነው፡፡

የ20 በመቶ የተመን ማውረድ ግሽበትን በ40 በመቶ ይጨምራል፡፡ የኢትዮጵያ ነጋዴ ጭማሪውን ወደ ሸማቹ የማስተላለፍ አቅሙ ከፍተኛ እንደመሆኑ ግሽበቱ ሸማቹን በተለይም ድሃውን የሚጎዳ ይሆናል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም  ከውጭ የሚመጡ የምርት ግብአቶች ዋጋ መናር የተመን ማስተካከያው ሊያሳካ ካሰበው አላማ በተቃራኒ አምራቾችን የማዳከም ውጤት ሊኖረው ይችላል፡፡

የኔ እይታ

በዋነኝነት ይሄ ትንበያ ባለፉት አስር አመታት ካስተዋልነው እውነታ የሚጣጣም በመሆኑ፤ እንዲሁም ዶ/ር አለማየሁ የቀድሞ ተማሪዬ ያሉት የኔን የቀድሞ መምህር እንደመሆኑ የአካዳሚ አያትና አባቴ የሰሩትን ጥናት ክብደት ልሰጠው ግድ ይለኛል፡፡

የግሽበት ውጤቱ ይህን ያህል የሚሆን ከሆነ፤ መንግስት ያለው የጣልቃ መግባት ተሞክሮ ወጭው ብዙ ውጤቱ የማያመረቃ ከመሆኑ አንፃር አሳሳቢና ብሔራዊ ባንክ ውሳኔውን ሲወስን ይህንን እንዴት እንዳየው እንድንጠይቅ የሚያደርግ ነው፡፡ የጥቁር ገበያ ንግድን ለመግታት እና ተመኑን ለማስተካከል አማራጭ የለንም በሚል የተውሰደ እርምጃ ከሆነም የብሔራዊ ባንኩ ኢኮኖሚስቶች ሊያስረዱን ይገባል፡፡ ለዚህ የሚኖረው መልስ የተመን ማስተካከያ መጠኑንም (15%) አወሳሰን የሚጨምር መሆን ይኖርበታል፡፡

3/ የተመን ማስተካከያው በአለም ባንክ የታሰበውን ያህልም የውጭ ንግድን ላያበረታታ ይችላል ይላል የዶ/ር አለማየሁ ትንተና፡፡ በተሰሩ ጥናቶች እንደታየው የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ መሰረታዊ ማነቆ ዋጋ (በተመን ለውጥ የሚፈታ) ሳይሆን ለማምረትና ለማቅረብ ያሉ ችግሮች ናቸው፡፡ የመሬት አቅርቦት፣ የጉምሩክ ስርአት፣ የግብር ህጎች መጠንና አወሳሰን እንዲሁም ሙስና ናቸው፡፡

በተለይ የ70 በመቶው ላኪዎች ችግር የመሬት አቅርቦት ነው፡፡ የመሰረተ ልማት ችግሮች፣ የፋይናንስ እጥረት እና የአፈፃፀም ድክመት ሌሎቹ ተጨማሪ ማነቆዎች ናቸው፡፡ ይሄም የውጭ ንግድ ላይ ያለው ማነቆ ከፋይናንስ ይልቅ መዋቅራዊነቱ ያመዝናል፡፡ ስለዚህም ከተመን ለውጥ ይልቅ እዚህ ላይ ማትኮር ከፍተኛ ለውጥ ያስገኛል፡፡

ማጠቃለያ

ከአለም ባንክ ጥናት (ምክር) እና ከዶ/ር አለማየሁ ትችት አምስት ወራት በኋላ ብሔራዊ ባንክ አያስፈልገኝም ያለውን የተመን ማስተካከያ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ለሃሳብ ለውጡ ምክንያት የሆኑ አስገዳጅ ሁኔታዎች (ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ለመፈፀም የሚያስፈልግ የውጭ ምንዛሬ እጥረትን የመሳሰሉ) እንደሚኖሩ መገመት ይቻላል፡፡ የውጭ ንግድ ገቢ ከእቅዱ በ75% መቀነሱም ሌላው ምክንያት እንደሆነ ይታየኛል፡፡

ሆኖም በተጠቀሰወ ፅኁፍ በተለይ በሶስተኛነት የተነሳው ነጥብ (ከመሰረተ ልማት ውጭ ያሉት) ተደጋግሞ የተነገረና በመሻሻል ፈንታ እየባሰበት የሄደ ነው፡፡ ቢ.ፒ.አር የኮርያው የእንግሊዙ…እየተባሉ የተሞከሩ የአሰራር ማሻሻያዎች ያላቀላጠፉት ቢሮክራሲ፣ በአዲሱ የግብር ግመታ እንደታየው ለነጋዴው ተገማችነትና ግልፅነት የሌለው እና ለሙስና የተጋለጠ የግብር ስርአት፣ እነዲሁም የመሬትና መሰል ችግሮች ለአመታት አጀንዳ ቢሆኑም ትልቅ መሻሻል ሊታይባቸው አልቻለም፡፡

ለዚህም ይመስላል ጉድለቱን ለማስተካከል ለመንግስት የቀለለው ብቸኛ አማራጭ (instrument) የተመን ማስተካከያ ማድረግ ሆኖ የቀረው፡፡

እነዚህ መሰረታዊ ችግሮች መቀረፍ እስካልጀመሩ ድረስ ጉድለቱ እየሰፋና ከጥቁር ገበያ ጋር የሚኖረው የተመን ልዩነት እየሰፋ መሄዱ ስለማይቀር በየቅርብ አመቱ የተመን ማስተካከያ ማድረግ የግድ እየሆነ አዙሪት ውስጥ የሚያስገባን ነው የሚሆነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለሚድያ መረጃ የመስጠትና የማስረዳት ሃላፊነት የብሔራዊ ባንኩና ባለሙያዎቹ ነው፡፡

…………………….

Fetsum Berhane is an Ethiopian resident, economist researcher and a blogger on HornAffairs.

more recommended stories