በከባድ ሚዛን አገሮች ዘንድ የተከሰተ ግርታ፣ የዞረበት ፍትጊያ፣ የሽርክናና የክብደት ሽግሽግ

(በቀለ ሹሜ)

1) የአጭበርባሪ ፖለቲካ ታሪክ ከገዢነት ታሪክ ጋር የተያያዘ ረዥም እድሜ አለው፡፡ በቅድመ ኢንዱስትሪ ህብረተሰቦች ዘመን ውስጥ ገዥነት በሰማያዊ መባረክ፣ ትንንቆች በፅድቅና በኩነኔ ተተርጉመዋል፡፡ ከዚያ በኋላም ተቀዳድመው የመጡት የምእራብና የምስራቅ ስርአቶች ሲፋለሙ የኖሩት በሰው ልጆች መብትና ነፃነት ስም ነበር፡፡ የምስራቅ ጎራ ላይመለስ ከፈረሰ በኋላ ምእራባዊያኑ የሽኩቻውን ዶሴ ገና አልዘጉትም፡፡ ለዚህም፣ መቀየርም ማንሰራራትም ያልሆነላቸው ትራፊዎች መኖራችው፣ የቻይናም በዲቃላ ቅንብር መጎልበት፣ ሙሉ የመዋቅር ለውጥ ካደረጉ አገሮች ውስጥም የዱሮውን የሚናፍቁ መከሰታቸው ለዶሴው እንቅስቃሴ መቀጠል ሳይጠቅም አልቀረም፡፡

ያም ሆነ ይህ ሶሻሊት ተብዬ ርዝራዦችንና ናፋቂዎችን የማጠናቀቅ ትግል ከፊት ለፊት ወደ ጀርባ ዞሮ፣ ከፀረ ምእራብ ከፀረ እስራኤል እስላማዊ አሸባሪነት ጋርና ይህንኑ ያራባሉ ከተባሉ አገሮች ጋር ያለው ትንንቅ የፊት ለፊቱን ስፍራ ይዞ ቆይቷል፡፡ ይህኛው ግጥሚያ በበከሉ የተለያዩ ደረጃዎችን አልፎ የኒዮርክ መንታ ህንፃዎችን እምሽክ አድርጎ አፍጋኒስታንን፣ ኢራክንና ሶሪያን ማባሪያ ባጣ ጦርነት በልቶ ትርምሶች፣ የሽብር ስራዎችና የመንግስታት መጨንገፍ የተበራከቱበት ሌላ ምእራፍ ውስጥ ከትቶናል፡፡

የኦባማይቻላልአዲስ ለውጥ አመጣ?

2) የነጆርጅ ቡሽን ፀብ-ጫሪ ፖሊሲ የነቀፈውና ለውጥን ያቀነቀነው (ቃላትን በምክንያት የሚጥልና የሚያነሳ አንደበት ያለው) ባራክ ኦባማ በአሜሪካ የምርጫ ውድድር መድረክ ላይ ብቅ ሲል፣ አገሮችም ከትልቅ እስከትንሽ በሱ ዙሪያ መሰባሰባቸው አለም በሙሉ ትርምስን፣ ጦርነትንና ሽብርን የሚያደርቅ መሪ ይሻ እንደነበር ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር፡፡ ኦባማ የአለም ተስፋ መስሎ ነበር፡፡ የአውሮፓ ሃገሮችም እንደህዝባቸው ሰላም የናፈቃቸው መስለው ነበር፡፡

አለም ብዙ የጠበቀበት ኦባማ ያገር ውስጥ ተቀባይነት እድሜ እንኳ ያረዘመ የተግባር ውጤት አላስገኘም፡፡ ኢራክና አፍጋኒሲታን ውስጥ የአሜሪካና የባልደረቦቿ ጣልቃገብነት የፈጠረውን ዝርክርኮሽ ያላስተካከለ አወጣጡም ሽሽት ቀረሽ ነበር፡፡ ከአፍጋኒስታንና ከኢራቅ የጥፋት ልምድ ተምሮ በ”አረብ መነሳሳት” ወቅት አገሮች ከውጪ ጣልቃ ገብነትና ከትርምስ በራቀ ሁኔታ ፖለቲካዊ ጣጣዎችን እንዲያቃልሉ አስተዋፅኦ ማድረግ አልቻለም፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ (በኔቶ በኩል) ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ውስጥ ከመነከር አልራቀም፡፡

በመሰናበቻው ሰአት ላይ፣ ኩባን በተመለከተ ለግማሽ ምእት አመት የተካሄደው ማእቀብ የተፈገለውን ውጤት አላስገኘም በሚል ግምግማ ያደረገው የፖሊሲ ለውጥም ቢሆን በረፈደ ሰአት የተካሄደ የስም ማቆያ ስራ ነበር፤ ምክንያቱም ይህ አመለካከት በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ አያያዙ ላይ ሲሰራ አናገኘውም፡፡ ከሰሜን ኮርያ ጋር የተደረጉ የ6ዮሽ ድርድሮችና በጉርሻ ሰሜን ኮሪያን የኒኩለር ጦር መሳሪያን ከማጎልበት የማራቅ ሙከራዎች ሁሉ በጠላትነት ማእቀፍ ውስጥ የተካሄዱና ማእቀብን ከማስከተል ያልረቁ ዲፖሎማሲያዊ ጨዋታዎች ነበሩ፡፡

በአሜሪካና በደቡብ ምስራቅ ሸሪኮቿ ለሰሜን ኮርያ የተሰጠውንና (አሁንም የሚስተገባውን) የሰላም ጠንቀኝነትና የጠብ ወዳድነት ስም ገለጥ አድርገን ትክክለኛውን ለመረዳት ስንሞክር የምናገኘው እውነት፣ የሰሜን ኮርያን መንግስታዊ ሰርአት አናውጦ ለማፈራረስ ያልተሞከረ ተንኮል እንደሌለ፣ ከደቡብ ኮሪያ በኩል በሰብአዊ መብት ስም በፊኛ እየተንተለጠለ ወደ ሰሜን ሲለቀቅ የኖረው የቅስቀሳ ወረቀት በቶኖች ሊቆጠር የሚችል ጭነት መሆኑንና የሰሜን ኮሪያ የኒኩለር ባለቤት ለመሆን መፍጨርጨርና የህዝቧ ስነጋ መባባስ የገዢው መንግስት ያልሞት ባይ ተጋዳይነት ውጤት (አሜሪካና ደቡብ ኮርያ በትንኮሳቸው የረዥም ጊዜ እገዛ ያደረጉበት) ነው፡፡

በቀጣናው የኒኩለር ሩጫን ለመግታትና ስጋትን ለማስወገድ መሰረት መሆን የነበረበት በግልፅም በስውርም የሚካሄድ የጠላትነት ስራን የሚያፈርስ ተግባር ነበር፡፡ የኦባማ አሜረካ የድርድር ጥረቶች ከዚህ እይታ ውጪ ነበሩ፡፡ በእስያ ፓስፊክ የነበረው አጠቃላይ ግንኙት ራሱ ከቻይናና ከሰሜን ኮርያ ጋር ቀሪዎቹን አገሮች አቃርኖ በአሜሪካ አጫፋሪነት ስር በማቆየት ብሌን የሚመራ ነበር፡፡

በ‹ኮሚንስት› ቀፎዋ ውስጥ ካፒታሊስት ትርፍ አግበስባሽነትን የምትጠበብበት ቻይና በኢንዱስትሪያዊ ኢኮኖሚ፣ በፋይናንስና በወታደራዊ አቅም ልእለ ሃያላዊ ግስጋሴዋ፣ ከዚህም ጋር በርካሽ ዋጋ አማካይነት ገበያ አላሲዝ ያለ የሸቀጥ ንግዷና የአገሮች የውስጥ ጉዳይ ውስጥ የማይገባ የካፒታል ንግዷ አሜሪካንና ሌሎች ምእራባዊ ሃያሎችን ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡ እንደዚያም ሆኖ፣ ንግድሽን ፍትሃዊ አድርጊ ከሚል ፍትጊያና ከተለመደው በሰብአዊ መብትና በቲቤት ጉዳይ ከመጎነታተል በቀር፣ በጥቅሉ ከቻይና ጋር ያለው ግንኙነት ሰላማዊ ነው ሊባል የሚችል ነው፡፡ በዋርሶ ጎራና በሶቮየት መፍረስ ከተፎካካሪ ልእለ ሃያልነት ከወረደችውና መንግስታዊ የሃብት ይዞታን ከማዘረፍ ባልተናነሰ መልክ ወደግል ካፒታሊስት ስርአት ካዞረቺው ሩሲያ ጋር ያለው ግንኙነት ግን (በንግድና በኢንቨስትመንት መገናኘት ቢኖርም) ዛሬም ድረስ፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ወዳጅ መስሎ እያዋዙም ሆነ አጉርጦ ከመሸራራፍና ጎረቤት ከማሳጣት ሊወጣ አልቻለም፡፡

የኦባማ አስተዳደር ይህንኑ ትንንቅ ያባባሰ ነበር፡፡ ጆርጂያና ዩክሬይን ላይ የደረሰው የካርታ መሸረፍን ያስከተለ ቀውስ ሩሲያን ያለ ሸሪክ ራቁት የማስቀረት የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ትንኮሳ ውጤት ነበር፡፡ የአሜሪካንና የአውሮፓን ቆስቋሽነት (ጎረቤት አስከጂነትና ነገር አራጋቢነት) ጋርዶ ሩሲያን ለአካባቢው አገር የወረራ ስጋት አድርጎ ማጠልሸት፣ የሩሲያ ደጅ ላይ ፀረ-ሚሳየል ሚሳየል መትከል፣ ሩሲያን በማእቀብ መሰነግና ቡድን ስምንትነትን ወደ ቡድን ሰባትነት ማውረድ የኦባማ የ”ይቻላል” ዘመን ድሎች ነበሩ፡፡

Image - Uncle Sam and Russian Bear, cartoon

ትረምፕ፣ አሜሪካ፣ የእሲያና የአውሮፓ ቀጣናዎች

3) የሩሲያው ፑቲን በአሜሪካና በፈረንሳይ የቅርብ ጊዜ ምርጫ ውስጥ ወደ ቀኞቹ ተወዳዳሪዎች ማጋደል፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ ዘመድን ከመፈለግ ይልቅ ከሩሲያና ከአሜሪካ-አውሮፓ ሻካራ ግንኙነት አኳያ፣ የሚበጅ እጩ በማማረጥ ፍላጎት የተመራ ነበር፡፡ እንደሚባለው ሩሲያ የምርጫ ውጤት ለማስቀየር እስከ መሞከር እጇን ሰዳ ከነበረም፣ ድርጊቱ የሩሲያ ንቁ ነገረኛት ያመጣው ሳይሆን የአሜሪካ-አውሮፓ ህብረት አላርፍ ባይነት ያስከተለው ነበር፡፡ በሆላንድና በፈረንሳይ ምርጫዎች ጊዜ የዋይልደርስና የሌፒን ፀረ-አውሮፓ (የአውሮፓን መፍረስ የሚያስከትል) አቋም፣ በአሜሪካም እንዲሁ የሂላሪ ክሊንተንን የተለመደ ፀረ-ሩሲያ መስመር የተቃወመውና ከሩሲያ ጋር ወዳጅነትን የፈለገው የትረምፕ መስመር፣ ከምእራባዊ ጉንተላና ከማእቀብ ስነጋ መገላገል ለምትሻው ሩሲያ የማይታለፉ ውድ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡

ከዚህ አኳያ ሩሲያ ምርጫዎቹ ላይ ተፅእኖ ለማሳረፍ ሞክራ ቢሆን እንኳ አጀብ የሚያሰኝ ነገር የለውም፡፡ የ“ሳይበር” ጥቃትን ከወራራ ጋር የማስተካከል ጩኸት የጠብ ፕሮፓጋንዳ ካልሆነ በቀር እራሷ አሜሪካም ሆነች ትልቁም ትንሹ አገር__ እንደየአቅሚቲ ከስለላ ጋር አላልሶ የሚሰራበትና እየተሳሳቀ የሚጠቃቃበት በትር ነው፡፡ በሶቪየት ህብረት መፈራረስ ውስጥ ከዚህም የዘለለ የአሜሪካ ጣልቃገብነት ታሪክ ተከናውኗል፤ ዛሬም ኮምፒተርን፣ የቤትና የኪስ ስልክን፣ ቴሌቪዥንን ሁሉ የስለላ መሳሪያ አድርጎ በመጠቀም ፊት የምትመራው አሜሪካ ነች፡፡

ዋናው ጥያቄም ኮምፒተራዊ መዘራረፉ ሳይሆን ከጎራዎችና ከሶቪየት መፍረስ ወዲህ ሩሲያን እንደወዳጅ መቁጠር ለአሜሪካና ላውሮፓ ስለምን ችግር ሆኖ እንደቆየ ነው፡፡ ሩሲያ በሰብአዊ መብትና በዴሞክራሲ ጉድለት ከነሳውዲ ብሳ ወይስ ሩሲያን ዳግም በልእለሃያልነት እንዳታንሰራራ አድርጎ የማጠናቀቅ ግብ ለአሜሪካም ለጀርመን-አውሮፓም ልእለሃያላዊ ጥቅም ሆኖ? እስከ ኦባማ ዘመን ድረስ የመጨረሻው ምክንያት የእንቆቅልሹ መፍቻ ይመስል ነበር፡፡ የዶናልድ ትራምፕ በአለም ፖለቲካ ላይ ብቅማለት ግን ይህን መላምት በከፊል አናግቶታል፡፡

4) የቅዠትና የእውነት አፈለቃቀቁን ሁኔታ ለማየት እንዲያስችለን በቅድሚያ አስገራሚውን የትረምፕ ነገረስራና በፍንግጥግጦሽ የተሞሉ አቋሞቹን በመጠኑ እንዳስስ፡፡ ትረምፕ፣ ፕሬዘዳንት ከሆነ በኋላ የአሜሪካ ወግ አጥባቂዎች ማህበር ሰዎችን የካቲት 17፣ 2009 ባናገረበት ጊዜ “ሃሳዊ ዜና/ ሀሳዊ ሚዳያ የህዝብ ጠላት ነው፡፡ እንዋጋዋለን!… ወግ አጥባቂዎች ዛሬ ፕሬዘደንታችሁን አገኛችሁ… አሜሪካን ታላቅና ገናና እናደረጋለን! ለናንተ እየታገልኩ ነው! ለህዝበ አሜሪካ እየታገልኩ ነው! የኔ መመረጥ ለወግ አጥባቂ እሴቶች ድል ነው! የኔ ማሸነፍ ለአገር ወዳድነትና ለአሜሪካ ባንዲራ ድል ነው! እኛ ንቅናቄ (ሙቭመንት) ነን! አሁን የኛ ዘመን ነው! መጥፎዎቹን እያበጠርን፣ ወንጀልንና እፅን እያፀዳን አሜሪካንን ትልቅ እናደርጋታለን! የባዶ ቃላት ዘመን አከተመ! አሜሪካ ትቅደም!! … ቅድሚያ ለአሜሪካውያን!!…” ብሎ ነበር፡፡

በዚህ ንግግሩ ውስጥ “አሜሪካን ቅጠሩ! አሜሪካን ግዙ!” የሚል የትራምፕ ብሄርተኛነት ተፈልቅቆ እናገኘዋለን፡፡ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር የገባውን ቅራኔ ለህዝብ ጠላት ከመሆን ጋር ያዛመደበትን፣ አሜሪካንና ባንዲራዋን መውደድን ከወግ- አጥባቂነት ጋር አንድ ያደረገበትን አደገኛ የቀኝ ህዝብኛ ቅስቃሳውን እናገኛለን፡፡ “ወግ-አጥባቂ እሴቶች” ሲል በውስጠ-ታዋቂ ክርስቲያናዊ ወግ-አጥባቂ ስነምግባርና ባህል ማለቱ ነው፡፡ “መጥፎዎቹ”ን፣“እፅና ወንጀል” እያለ ሲናገርም ከማስወረድ ባለፈ በሶዶማዊነትና በሁለት አይነት ወሲብ ውስጥ መኖርን ካንድ ፆታ ወደ ሌላ ፆታ መቀየርን ጨምሮ በውስጠ-ታዋቂ መናገሩ ነው፡፡ የኛ ዘመን ከኔ ፕሬዘዳንትነት ጋር መጣ ብሎ ሲልም የዚህ አይነቱ ነውረኛ ባህል አይፈነጭብንም (አይውጠንም) ማለቱም ነው፡፡

ይህ ንግግሩ በክርስቲያናዊ ወግ አጥባቂ ጨዋነትና ባህል ውስጥ የሚኖር ሰው አድርገን እንድናስበው ይጫነናል፡፡ ከአሜሪካ ድንበር ያለፈ ልዩ ልዩ ሃብት ያለው ቱጃሩ ትረምፕ ግን ከሊቢራልነት ጋር አንድ እስከመምሰል የደረሰው ላሻቃ ባህል ከደራበት የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ጋር የቅርብ ትውውቅ የነበረው ለፕሬዘዳንት ውድድር ራሱን ባጨበት ሰአትም ገቢው ለበጎ ስራ ከመሆኑ በቀር ርባና በሌለው እንትንሽ እንትህ እየተባባሉ ካፍ እስከ ፊንጢጣ ድረስ ሰቅጣጭ ግን የቀልድ ወሲባዊ ብሽሽቅ በሚካሄድበት ሮስት (roast) የሚባል ትርኢት ላይ ራሱንና ውስን የቤተሰብ አባላቱን አስጥዶ በስድ አፍ “እንዲያንጨረጨሩ” (ሮስት እንዲደረጉ) የፈቀደ ሰው ነው፡፡

በንግድ ስራውም፣ በክፉ ቀን ቤት በርካሽ ገዝቶ በውድ ጊዜ የመሸጥ፣ የአሜሪካን የግብር ህግ ማምለጫ ቀዳዳዎችን አጥንቶ በተደጋጋሚ መሹለክ የቻለ መራራ ጮሌነት ያለበትና በዚህም የሚኮራ ሰው ነው፡፡ እንዲህ ያለው ጮካነት ደግሞ “ስራ ከፋች በሚያነቃቃና በሚስብ ደረጃ ግብር ቀንሼ በአሜሪካ ውሰጥ ስራ አስፋፋለሁ” ብሎ ከሲታ የነበረ ድጋፍን ከማጎልበት ባለፈ፣ በስውር ኤሌክትሮናዊ ዘዴ የተቀናቃኝ ገመና እንዲሰጣ ለማስደረግም ሆነ የድምፅ ውጤትን ለማስበረዝ ከመድፈር የማይመለስ ነው፡፡

5) የትረምፕ አፍአዊ የወግ አጥባቂ እሴቶች ከተግባራዊ እሴቶቹ ጋር እንደሚፋለሱብን ሁሉ የፖለቲካ አኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ አቋሞቹም እርስ በርስ ይጋጩብናል፡፡ የአሜሪካን ጥቅም አስቀድማለሁ የሚል አቋሙ ከአሜሪካ የ300__ ሚሊዮን ገደማ ህዝብ ቁጥር ውስጥ 20 ሚሊዮን ገደማ ዜጎችን የጨለፈ የሚባልለትን የጤና ዋስትና እንኳን መቀበል ያቃረው ነው፡፡ (በዚህ በኩል ካንዴም ሁለቴ ያቀረበውን መሻሪያ ሊቀበሉት ያልቻሉት ሪፐብሊካን ተወካዮች አይበልጡትም፡፡ “ኦባማ ኬር” የሚል የሽርደዳ ስም ላወጡለትና እጅግ በጥቂቱ የከበርቴዎችን ገቢ በነካው የጤና ዋስትና ምን ያህል እንደሚበግኑ ቀድሞ አሳይተዋል፡፡

ዛሬ የትረምፕን መሻሪያ ለመቀበል የተቸገሩትም ባራክ ኦባማ የተከለባቸው “ጠንቅ” መነካቱ በሁለት ምክርቤት ያላቸውን የበላይነት ድራሽ እንደሚያጠፋ ስለገባቸውነው፡፡) ብክለትና ሙቀት ቅነሳ የአሜሪካውያን ጥቅም ያልሆነ ያህል ከፓሪስ የያር ንብረት ስምምነት ማፈንገጥም ሌላው ከአሜሪካውያን ጥቅም ጋር የተጋጨበት አቋም ነው፡፡ ካመት አመት ሰደድ እሳት የሚለመጥጣት ካሊፎርኒያ ብቻዋን የፓሪሱን ስምምነት አከብራለሁ ማለቷ የፖለቲካ ክስረቱ መታሰቢያ ነው፡፡ አሜሪካን ገናናና ተወዳዳሪ የለሽ እናደርጋታለን ባይነቱም “የአሜሪካ እንጂ የአለም ፕሬዘዳንት አደለሁም” ከማለቱና የንግድና የወታደራዊ ሽርክናዎችን ከመሸሽ ፍላጎቶቹ ጋር አይግባቡልንም፡፡

ለእስራኤል ጭልጥ ያለ ወገናዊነቱና ከተወሰኑ እስላማዊ አገሮች ተጓዥ ወደ አሜሪካ እንዳይገባ የማገድ ፍላጎቱ ፀረ-አሜሪካ ፅንፈኛነትንና አሸባሪነትን የሚያነቃቃ ነው፡፡ የአሸባሪነት ዋና መፍለቂያ ያልሆነችውን ኢራንን በዋነኛ የሽብር አደጋነት ኮንኖ ከነሳውዲ ጋር በፀረ-ሸብር አላማ መተቃቀፍ አቅጣጫን የመሳት ያህል ነው፡፡ የባህረ-ሰላጤው ጥል ሲከሰት ከነሳወዲ ጎን ሆኖ ካታርን በሽብር እገዛ ተጣድፎ መንቀፉም በሁለት አቅጣጫ (ከሳውዲም ከካታርም ከሌሎቹም ጎረቤታሞች መሳፍንታት አካባቢ ተሸፋፍኖ የሚሾልከውን ረጂነት መጋረድም ነበር፡፡

ቶሎ መታረሙ በጀ እንጂ የዚህ አይነቱ ችኩል ውገና በቴህራን የአያቶላ ሆሚኒ ቤተ-መቃብር ላይ እንደተፈፀመው ጥቃት የሁለት ወገን መጣቃቃት እንዲከፈት መንገድ መፍቀድ በሆነ ነበር፡፡ እንዲህ ላለ ውስብስቦሽ የበሰለ ሁኔታ ባለበት አለም ውስጥ ሆኖ ብዙ ቦታዎች ውስጥ (አፍጋኒስታንና ሶማሊያ ውስጥ ሳይቀር) በፀረ-አሸባሪነት ውጊያ ውስጥ መግባት የማባባስም ሚና ሊኖረው መቻሉ፣ በዚህ ላይ ደግሞ ሰሜን ኮርያ ላይ ማቅራራት መታከሉ፣ ለወታደራዊ በጀት ከበፊቱ እጅግ ከፍተኛ የ54 ቢሊየን ዶላር ጭማሪ ማቀዱ፣ ከሜክሲኮ ጋር የሚጋራውን ወሰን ካላጠርኩ ባይነቱ፣ የአለም ፕሬዘዳንት ከመሆን ተቆጥቦ የአሜረካንን ያረጀ መሰረተልማት በአንድ ሺቢሊዮን ዶላር ለማደስ ማሰቡ፣ ታክስ ቀንሼ ለአሜሪካውያን ስራ አስፋፋለሁ ባይነቱ በገንዘብ ወጪና በገቢ ግንኙነት ሁሉ ይጋጫሉ፡፡

6) እንዲህ ያለው መወነጋገር በሞላ የመደናበር ውጤት ይሆን? በነቀፋና በጥርጠራ ግፊት ውስጥ ግለሰቡ የሚዳፋ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከሩሲያ ጋር የመቀራረብ ፍላጎትን አለመጣሉ፣ የሰሜን አትላንቲክንና የእሰያ ፓስፊክ የንግድ ሽርክናዎችን ከመሸሽም በላይ ኔቶና አውሮፓ ህብረት ቢፈርሱ የማይከፋው የመሆኑ ነገር የሚገናኙበት የጋራ ያስተሳብ ውል ይኖራቸው ይሆን? ነገሮችን እየደረደርን ዝምድና ለማግኘት ስንጥር የተለያዩ መላምቶች እንደሚሞግቱንና መላምት ማንሳትና መጣል እንደሚገጥመን እውቅ ነው፡፡ በበኩሌ የትረምፕን አቋሞች አገናዝቤ ለመረዳት ያደረኩት ሙከራ የሰጠኝ ስእል የሚከተለው ነው፡፡

የጥሬ እቃና የሰውሃይል ዋጋ ቅናሽን እያየ የመረታ ስፍራውን የመቀየር ዝንባሌ ያለው ኮርፓሮት ካፒታሊዝም በዋና ቤቶች ወስጥ እያስከተለ ባለው የስራዎች መሳሳት ውስጥ ትረምፕ ቆሞ፣ ገናናነቷ ያረጀባትንና በግዙፍ እዳ ተጠምዳም ሳለች የአለም መሪነኝ እያለች በተለያዩ መድረኮች ውሰጥ በከፍተኛ መዋጮ አውጪነት የምትንገዳገድ አገሩን ይመለከታል፡፡

እስካሁን የአሜረካ ልእለሃያለዊ ከለላ ያልተለያቸውንና የተፈበረኩ ውጤቶችን በመላክ ረገድ የተሻለ ጥንካሬን አሁንም ያጠበቁትን የጀርመንንና የጃፓንን ጮካነት በጮካ አእምሮው ከአሜሪካ ጋር ያስተያያል፡፡ የቤት፣ ያገልግሎትና የነዳጅ “አሮጌ” ከበርቴነትን ወደ መወከል ያደላው እይታውና ጮሌ ነጋዴነቱ የሚያስችለውን ያህልም ለአሜሪካ መፍትሄ ያሰላላታል፡፡ ብክለት የሚቀንስ ፖሊሲና ከዚሁ ጋር የሚጣጣም አዲስ ጥበብና አዲስ ኢንዱስትሪያዊነት ላይ የተመሰረተ ኑሮና ሃብት፣ ያሮጌ ከበርቴነት ህልውናው ከሚፈቅድለት እይታ ውጪ ነው፡፡

እና በአሮጌ የሃይል ምንጭ ውስጥ በድንጋይ ከሰልና በዘይት ላይ የተመሰረተ ስራን ማጎልበት፤ ባሮጌው የጦር መሳሪያ እሽቅድምድም አሜሪካን ማስፈንጠርና ተወዳዳሪ የለሽ መሳሪያ ሻጭ ማድረግ፤ የኮርፖሬት ቀረጥ ቀንሶና በገቢ እቃዎች ላይ ቀረጥ ጨምሮ ሌላ ቦታ እያመረትኩ ለአሜሪካ ሰፊ ገበያ እሸጣለሁ ከማለት ይልቅ የመረታ ስራንወደ አሜሪካ ውስጥ ማምጣት እንዲጨምር ማድረግ፤ ከወዲሁም ግዙፍ እቅዱ የሚገጥመውን የበጀት እጥረት ለመሸፈን፣ በባህረ ሰላጤው ወዳጅ አገሮች ውስጥ ያለውን ቁልል የነዳጅ ገንዘብ በጦር መሳሪያ ችብቸባና በኢንቨስትመንት መንገድ ወደ አሜሪካ መሳብ፡፡

በተረፈ፣አሜሪካ ከሌላው የላቀ ወጪ የምታደርግባቸውን መዋጮዎችና እርዳታዎች መቀነስና ማቋረጥ፤ የአሜሪካን ወታደራዊ ከለላ ፈላጊዎች ክፍያ እንዲፈፅሙ ማድረግ፤ አሜሪካን እንደልብ የማያፈናፍን ወይም አሜሪካ ባግባቡ ብልጥ ያልሆነችበት ብሎ ያሰበውን ሽርክና ባዲስ ስምምነትና መስፈርት ማስተካከል፣ አለዚያም ጥሎ በመውጣት ከየግል አገራት ጋር መደራደር፡፡ ትረምፕ፣ ኔቶን ጊዜው ያለፈበት ለማለት የደፈረውና የቀኝ አክራሪዎች በአውሮፓ አገሮች ስልጣን ላይ እየወጡ አውሮፓ ህብረትን ቢንዱት ጭንቁ ያልሆነው ከዚህ አኳያ ነው፡፡

ይህ የትረምፕ አቋም ሩሲያ ካላት ከምእራባዊ ጉንተላና አፈና የመላቀቅ ፍላጎት ጋር መግጠሙ፣ ሩሲያም ለትረምፕ ከጮሌዎቹ ጃፓን፣ ቻይናና ጀርመን የተሻለች የንግድና የኢንቨስትመንት ስፍራ ተደርጋ መታየቷ የጋራ መገናኛቸው ነው፡፡ ዋነኛውን የአለማችንን ችግር ፅንፈኛነትንና አሸባሪነትን ከሚታገሉ ጋር ሁሉ ተባብሮ መስራትን ትረምፕ ከፍ አድርጎ ያሰተጋባውም ከተለመደው ሩሲያን የተመለከተ የአሜሪካ ፖሊሲ ሲያፈነግጥ ቅዋሜን ለመመከት እንዲችል ነበር፡፡ ተቀባይነት ግን በቀላል የሚገኝ አልነበረም፡፡ ያም ሆኖ በአለም መድረክ ላይ የትራምፕ ብቅ ማለት ብዙ ነገር አነቃንቋል፡፡

7) ትረምፕ ብዙ ነገር ነው፡፡ የአሜሪካ ባንዲራን አጣፍቶ ከለበሰ አገር ወዳድ ቱጃር ያልዘለለ ፖለቲከኛነቱን፣ የነጋዴ ጮካነቱን፣ ያጋጣሚ ጥቅመኝነቱን፣ ጉረኝነቱን፣ ግብታዊ አስተያየት ለመስጠት ችኩልነቱን፣ “በጣም ጥሩ፣ መጥፎ፣ ድንቅ፣ ግሩም…” በሚሉ ድፍን ስሜታዊ ቃላት ተናጋሪነቱን ይዞ ነጩ ቤተመንግስት የገባ ሰው ነው፡፡ በግንቦት 2009 ውስጥ በመጀመሪያው የውጪ ጉብኝነት ሳውዲ አረቢያ ሪያድ ምድር ላይ ቆሞ ስለ ኢራን ህዝብ መብት መነፈግ “የተቆረቆረ”ና ግንቦት 13 በተካሄደ በርካታ ሙሰሊም አገሮች በተገኙበት ስብሰባ ላይ የመካከለኛው ምስራቅ በጥባጭና ዋና የሽብር ሃይል አድርጎ ኢራንን ለነሳውዲ የሰዋ ሰው ነው፡፡

በዚያው ወደ እስራኤል ወረድ ብሎም ከበፊቱ እጅግ በተበላሸ ባዶ የፖለቲካ ሜዳ ላይ ሆኖ የእስራኤልና የፍልስጤም ችግር የሚፈታበት ጊዜ መጣ ለማለት ያላፈረ ሰው ነው፡፡ ምንም ይሁን ምን ግን፣ በእዳና በጉድለት የተዋጠችው አሜሪካ አለም ላይ መንጠራራቷን አርግባ ቤቷን እንድትታስተካክል የነገራት የመጀመሪያ ፕሬዝዳንቷ ትረምፕ ነው፡፡ በኮርፖሬት ቀረጥ ቅነሳና በገቢ እቃ ላይ ታሪፍ በመጨመር ያገር ውስጥ ስራ ከፈታንና መስፋፋትን የማሳደግም ዘዴ ብዙም የማያራምድ (ሌላውም እኩያ አገር እንደዚያ ቢያደርግ የማያወለዳ ሁኔታ የሚፈጥር) ቢሆንም፣ ቢያንስ በኮርፖሬት ኩባንያዎች ድንበር የለሽነት (አገረ ብዙነት)ና በአገሮች ብሄራዊነት መካከል ያለውን ቅራኔ “ለመፍታት” የበኩሉን ሞክሯል፡፡

8) “ኔቶ” ጊዜው ያለፈበት ወታደራዊ ቃልኪዳን የመሆኑ ነገር ትረምፕ ዛሬ ስላለው አዲስ የማይሆን፣ የአሜሪካ ሪፐብሊካንና ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሰዎችና የአውሮፓ ህብረት ስለተንጫጩ ውሸት የማይሆን እውነት ነው፡፡ በትረምፕ የምርጫ አሸናፊነት ውስጥ የሩሲያ ሩቅ እጅ ኖረም አልኖረ፣ የእሱ ስልጣን ላይ መውጣት ከሁለት አገሮች ልእለሃልነት ዘመን ጋር ተያይዞ የመጣውን ከሩሲያ ጋር በመፋተግ ላይ የተሰካውን የአሜሪካ-አውሮፓ ፖሊሲ እንቅጥቅጡ እንዲወጣ አድርጓል፡፡

እንቅጥቃጤውም የሚያስገርሙ እውነታዎችን ገላልጧል፡፡ ከግለሰቡ ትረምፕ ይልቅ የባሰ መምታታትና መደናበር የት የት እንዳለ አሳይቷል፡፡ ‹ፕሬዘዳንትነቴ ለአሜሪካ እንጂ ለአለም አይደለም› ማለትን ከመደጋገም ጋር፣ ትረምፕ ከአውሮፓና ከሩሲያ ፍትጊያ፣ እንዲሁም ከእሲያ ፓስፊክ ሽርክና ላይ ፊቱን መለስ ባደረገ ጊዜ እነጀርመንና እነጃፓን ስለምን ተዝረጥርጠው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ሮጡ? አሜሪካ በመዋጮም ሆነ በሌላ መልክ የተሸከመችው አለማቀፋዊና አካባቢያዊ ሸክም ወደ እነሱ እንዳይዞር? ፖሊሲያቸውን ቢያለሰልሱ ከሩሲያም ጋር ሆነ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ያላቸው ግንኙነት ወደ ወዳጅነት ሊዞር የሚችል ሆኖ ሳለ፣ ስለ ሰሜን ኮሪያ የአለም ሰላም ስጋትነትና ስለሩሲያ የወረራ ሃይልነት ስለምን መለፍለፍ አስፈለጋቸው? የአሜሪካ ከለላ ሳይሸሻቸው ያደጉበት ግንኙነት ሳይቀየር መቀጠሉን ብልጠቴ ብለውት ወይስ የአሜሪካንን ከለላ ለግማሽ ምእት አመታት የመላመዳቸው ብርታት “ከእንግዲህስ…” የሚል ነገር ሲመጣ ድንግርግሮሽ ውስጥ ከተታቸው? በመልመጥመጣቸው ውስጥ ሁለቱም ምክንያቶች ያሉ ይመስላሉ፡፡

9) የአውሮፓና የሩሲያን ግንኙነት በተመለከተ ሌላም ስውር ምክንያት ሳይኖር አይቀርም፡፡ አውሮፓን የመሰልቀጥ ሙከራ ታሪክ ያላቸው ፈረንሳይና ጀርመን የዛሬዋ አውሮፓ አውራዎች ናቸው፡፡ የዛሬዋ የአውሮፓ ህብረትም የጀርመን- ፈረንሳይ አውሮፓ ተብላ ልትገለፅ ትችላለች፡፡ ጀርመን፣ ፈረንሳይና አውሮፓ ከሩሲያ ጋር በንግድ የተሳሰሩ ሆነው ሳለና በነሱና በሩሲያ መሃል የቀድሞው አይነት የስርአት ልዩነት የሌለ ሆኖ የትንኮሳ አነሳሽነቱን በእጃቸው አድርገው ከሩሲያ ጋር መጋፋትን ለምን ብለው ቀጠሉበት? መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ነው፡፡

ከዚህ ጋር ደግሞ፣ ትረምፕ እንደፈለጉት አለሁላችሁ አልል ሲል ጀርመንም ፈረንሳይም ጉብኝትን የጨመረ ዲፕማሲያዊ መለሳለስ ለሩሲያ ማሳየታቸው መገናዘብ አለበት፡፡ “ማባበላቸው” አሜሪካ ዘወር ካለች ሩሲያ ትወረናለች ከሚል ፍርሃት የመጣ ነው? የማይመስል ነው፡፡ የሆኑ ነገሮች አሟይና የአውሮፓ ህብረት አባል ሁኚ ቢሏት ሩሲያ እሺ እንደምትል ያቁታል፡፡ የ“ስጋቱ”ና የትንንቁ ምክንያት በሌላ አቅጣጫ ነው የሚገኘው፡፡

የአሜሪካና የአውሮፓ ከሩሲያ ጋር የኖረ ንቁሪያ እንዳለ ቀጥሎ ሩሲያ እየተሸራረፈችና እየተዳከመች እንድትሄድ ከማድረግ ጋር እነሱ ደርጅተው በአውሮፓ ምድር ከምእራብ እስከ ምስራቅ አውሮፓ ተፎካካሪ ሳይኖራቸው፣ ራሷን ከለላ ሰጪያቸውን አሜሪካን በሃያልነት ልቆ መውጣት አንዱ አቅጣጫ ነው፡፡ ሌላው አቅጣጫ ባጠቃላይ ምእራባውያንን የሚመለከት ነው፡፡ አሜሪካኖች ሶቪየት ህብረት ከፈረሰችና ከተዳከመች ወዲህ ወዳጅም መስለው ቢሆን ሩሲያን ከመገዝገዝ ተግባር ያልራቁት የሩሲያ ማንሰራራት ከሌላው ይበልጥ አስፈሪ ስለነበር ወይም ከአውሮፓ ጋር ሩሲያ ገጥማ ልእለሃያልነታቸውን የሚያኮስስ ግዙፍ ሃይል እንዳይፈጠር ፈርተው ይሆናል የሚል መላምት ለማስቀመጥ የሚያስችል አውነታ አይገኝም፡፡

ከሩሲያ ይበልጥ የሚያሰጋቸው የቻይናና የጀርመን ግስጋሴ ነው፡፡ የጀርመን-አውሮፓ ግስጋሴም የግድ የሩሲያን ጓደኝነት ሳይሻ እየታየ የነበረ ነው፡፡ የቻይና ልእለሃያላዊ እድገት የቅርብ እንደመሆኑም እነደቡብ ኮሪያንና ጃፓንን ከቻይና የተሰሚነት ቀለበት የማራቅ ስሌት ከሰሜን ኮሪያ ጋር ለነበረው የረዥም ጊዜ ፍትጊያ ማብራሪያ አይሆንም፡፡ ዛሬ ከሩሲያ ጋር የቆየውን የመጠማመድ ግንኙነት ወደ በጎ ግንኙነት ለመቀየር በፈለገው ትረምፕ ላይ የአሜሪካ ሪፐብሊካንም ሆኑ የዴሞክራቲከ ፓርቲ ፖለቲከኞች እንዲሁም ጋዜጠኞች መንጫጫታቸው ለአሜሪካ ልእለሃያላዊ ጥቅም ከመቆርቆር ነው ተብሎ ቢታሰብ ምኞታዊነት ይሆናል፡፡

የትረምፕ የፖሊሲ ለውጥ ትልቅ የተከበረ ሃውልት የመስበር ያህል አስገርሟል፡፡ ሩሲያ በሆነ ገመና አስገድዳ እጁን ጠምዝዛዋለች ብሎ እስከመጠርጠር ድረስ ግምት ነጉዷል፡፡ ይህ ግምት እውነት ሆኖ የትረምፕ የስልጣን እድሜ ቢያጥር የሚናፍቅ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ ድረስ ጥቂት አይደለም፡፡ ሌሎች ተደራቢ ምክንያቶች ቢኖሩም የሩሲያንና የአሜሪካን ግንኙነት ወዳጃዊ ማድረግን ከጥፋት ያስቆጠረው (በነዩክሬን ቀውስ ውስጥ የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረትን የቆስቋሽነት ጥፋት ከማስተዋል ያገደው) ለረዥም ዘመን ፖለቲካውን፣ መገናኛ ብዙሃኑን፣ የፊልም ኢንዱስትሪውን ባጠቃላይ ህሊናን ሲያሟሽ የኖረው የሁለት ልእለሃያላን ተቃርኖ ቆሌ ዛሬም እየገዛ መሆኑ ነው፡፡ ትረምፕ መጥቶ ያንገጫገጨው ይህንን ልብስና ጫማ የማድረግ ያህል የተለመደን ቆሌ ነው፡፡

ሽግሽግና አደጋዎች

10) ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ እጇን አስገብታለች አላስገባችም? ትረምፕ ከዚህ ጣጣ ጋር ንክኪ አለው የለውም? በነዚህ ጥያቄዎች ላይ የተሰጡ ወደ አወንታ ያደሉ የ”ትንታኔ” ፍትፈታዎች የሩሲያ ጉዳይ (በውስጠ ታዋቂ የትረምፕም) በምርመራ የመያዙ ነገር ሁሉ እውነቱን ከማወቅ ባለፈ ትረምፕ በውክቢያ ተገፍቶና ከሩሲያ ጋር የሚያጣብቅ ስውር ነገር እንደሌለው በማረጋገጥ ፍላጎት ተጠምዶ፣ ሩሲያን ወደ መራቅና ወደ ተለመደው የተቃርኖ ፖለቲካ እንዲገባ የማድረግም ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ የፖለቲካ ወግ ሲጣስ ከቃላት ንዝነዛም ያለፈ በተግባራዊ “ማሳመኛ” ወደ ወጉ የማስገባት ስውር ሴራም አይሞከርም ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡

የሶሪያው በሽር የፀረ-ሽብር ትግል አጋር ተደርጎ የመታየትን ታምር በዶናልድ ትረምፕ ባገኘበት ሰአት ምን ቢደድብ ነው የኬሚካል የጦር መሳሪያ የተጠቀመው? ከዚህ ጥያቄ ጋር “የኬሚካል ጥቃት አልፈፀምኩም ይመርመርልኝ” እያለ ሲወተውት ለመመርመር የሚፈጥን መታጣቱን አሜሪካም ከሰላዮቼ መረጃ አለኝ ከማለት በቀር ማስረጃ አለማቅረቧን አያይዘን ቢያንስ ሽፍንፍኑ ተገፎ እውነት ወለል እስኪል ድረስ፣ ትረምፕ ግብታዊ እርምጃ እንዲወስድ ስውር ስራ (በውስጥም እጅም ሆነ በምርጥ ወዳጅ በኩል) ተካሂዶ ቢሆንስ የሚል ጥርጥሬ ቢያድርብን ጥፋት አይሆንም፡፡ የትረምፕ ፈጣን የሚሳየል ጥቃት (በኋላም በሰኔ ውስጥ የጦር አይሮፕላንና “ድሮን” መትቶ መጣል) በስሜታዊነት ብቻ የተከተለ ሳይሆን አጋጣሚውን በቅዋሜ ማቅለያነት የመጠቀም ብልጠትም ነበር፡፡

ከሰሜን ኮሪያ ላይ ጎራዴ መምዘዙና ከነደቡብ ኮሪያ ጋር የጦር ልምምድ መክፈቱ፣ የኔቶን አስፈላጊነት ”ማመኑ”ና ከሩሲያ በኩል የሚመጣ ጥቃትን በኔቶ በኩል ስለመመከት ለአውሮፐውያኑ (በግንቦት አጋማሹ የኔቶ ስብሰባ ላይ) መናገሩ ሁሉ ካቋም ወደ አቋም የመዋዠቅ ጉዳይ ከመሆን ይልቅ በቅዋሜ ግፊት ምክንያት የተደረገ “ለውጥ” ነበር፡፡ ምንዛሪዋን በማቅለል ዘዴ የነጠቃ ንግድ ታካሂዳለች ሲል ያወገዛትን ቻይናን በድንቅ ወዳጅነት ማሞጋገሱም ማሳሳቂያ ብልጠት ነበር፡፡

11) ትረምፕ ወዲያም አለ ወዲህ፣ ምእራብያኑ እንደ ወግ ለያዙት የፖለቲካ መስመር ገና አልገበረም፡፡ ግለሰቡ፣ በአለም አቀፍ የፖለቲካ መድረክ ውስጥ ያለው ሁነኛ ፍላጎትም አሸባሪነትን በውጊያ ከመጠራረግና የአሜሪካን ጥቅም በነጋዴ ትርፍና ኪሳራ ከመለካት (አሜሪካ ለጊዜው ሰብሰብ ብላ የጦር መሳሪያ ችብቸባዋንና በወታደራዊ ልቀት ተወዳዳሪ የለሽ የመሆን ምርምርና ፍልሰፋዋን እንድታጦፍ ከማድረግ) የዘለለ አይደለም፡፡ እናም፣ ድብስብሶሽ እንዲቀደድና ጀርመን የምትመራው አውሮፓ አሜሪካን መንተራስ አቁማ በራሷ እንድትቆም፣ ቻይናም የልእለ-ሃየልነቱን አክሊል ከአሜሪካ እንድትረከብ ረድቷል፡፡ ሁለቱም ወደፊት የመጡበት ስነስርአት የተካሄደውም በ2009 የግንቦት 24ቱ የቡድን 7 ስብሰባ ላይ ከፓሪሱ ያየር ንብረት (የሙቀት ቅነሳ) ስምምነት አሜሪካ ባፈነገጠች ማግስት፣ ቻይና ለፓሪሱ ስምምነት መፅናት ከአውሮፓ ህብረት ጋር አብሬ እቆማለሁ ስትል፣ ጀርመንም ከእንግዲህ ወደማንም ማንጋጠጥ እንደማያስፈልግ በተናገረች ጊዜ ነበር፡፡

ከዚያም በኋላ የቡድን 20 ስብሰባን በማስመልከት አንጌላ መርክል አፍሪካውያንን በልማት ትግላቸው ሳንረዳ ስደትና ሽብርን ማሸነፍ አንችልም ስትል መናገሯ የመሪነት ሚናን የሚያንፀባርቅ ነው፡፡ በስተኋላም እሷና የቻይናው ፕሬዘዳንት ተገናኝተው ወደኋላ የቀሩ ሃገሮችን በመርዳት ረገድ ለመተባበር መግባባታቸው ለአዲስ መሪነት መፈላለግንና መገማመትን የሚጠቁም ነው፡፡ ከእንግዲህ በኋላ የትረምፕ የስልጣን እድሜ አጥሮ አሜሪካ ወደ ነባሩ አለሁ ባይነቷ መስመር ብትመለስ እንኳ በአሜሪካና በአውሮፓ ላይ ብቻ ከመንጠላጠል የዘለለ አለማቀፋዊ የገበያ መቀነት እየፈጠረች ያለችውን ቻይናን መጋረድ ይከብዳታል፡፡

12) አሜሪካ፣ ከትረምፕ ጮካነት ጋር አፈግግጋ ብትቆይስ በሃይማታዊ ፅንፍና አሸባሪነት መጠመዷን፣ የእዳ ውዝፏን፣ የበጀት ጉድለቷን አቃላና ይበልጥ በሃይል ጎልብታ እንደገና ወደ አለም መሪነቷ መመለስ ትችል ይሆን? በአሜሪካ ማፈግፈግስ አለም ጣጣው ይቀልለታል? አይመስልም፡፡ ይህንን ለማለት የሚያስደፍሩ አሳሳቢ ነገሮች አሉ፡፡ በትራምፕ__ አይነቱ የነጋዴ ጮካነት ውስጥ በችኩልነትም ሆነ በአጋጣሚ ተገለባባጭነት ያልታሰበ ጦርነት የመክፈት ዘራፍ ባይነትም አለ፡፡ አጠቃላዩ አለምም እንዲሁመጠማመድን፣ ግጭትን፣ ሽብርንና ውድመትን ከሚያብሱ ስሌቶችና ቅራኔዎች ውስጥ መደናበሩ ገና እንዳለ ነው፡፡

ኢራንን ጠላት አድርጎ ለሳውዲ የ10 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ሊሸጥና የ380 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት (ስራ ከፋች ንዋይ) ሊስብ፣ ከሳውዲ ጋር ጠብ ውስጥ ለገባችው ካታርም እንዲሁ የ12 ቢሊዮን ዶላር ጦር መሳሪያ ሊሸጥ የዘየደው የትረምፕ ጮካነት የፖለቲካ ጅልነትንና አጥፊነትንም ያዘለ ነው፡፡ አሜሪካ ጠንካራ የሚባል የጦር ሰፈር ካታር ውስጥ ያላት እንደመሆኑ፣ ቱርክም እዚያው ያላትን የጦር ሰፈር በሺዎች በሚቆጠር ተጨማሪ ሰራዊት ለማጠናከር እንደመፍጠኗ፣ ሁለቱም ፀበኞች የአሜሪካን ጉያ የተጠጉ እንደመሆናቸው እነ ሳውዲ በካታር ላይ ቀጥተኛ ጦርነት የመክፈታቸው ነገር ይሆናል ተብሎ የማይታሰብ ነው፡፡ ካታርን በንግድ ማእቀብ፣ ያየርና የየብስ መተላለፊያ በመንፈግ የማፈኑ አድማም ለካታር በወገኑ አገሮች በኩል መላ ማግኘቱ አይቀርም፤ እያገኘም ነው፡፡ ነገር ግን ሳውዲ አረቢያም ሆነች ካታር ፅንፈኛነትንና አሸባሪነትን በዘዋራ እጅ በመደገፍ መታማታቸው የቆየ እንደመሆኑና የጠብ ጎራውን በነሳውዲ በኩል እስራኤል፣ በነካታር በኩል ኢራን ባጋጣሚ-ወለድ ወዳጅነት የተደረቡ እንደመሆናቸው ከሁለት አቅጣጫ በሽብር ዘዴ መቆራቆስ ሊከፈት ይችላል፡፡

የእስራኤል ለነሳውዲ መደረብ ጥቂት ጊዜ ለማደናገር ቢጠቅማትም፣ ፍልስጥኤሞች ላይ የምታራምደው ምንም አይነት ነገር የማይደብቀው ፍትህ አልባነትና የአሜሪካ-ትረምፕ አይን የሌለው ደጋፊነት፣ ሽብርን ለመመንጠር እየተባለ የሚካሄደው ወታደራዊ ጣልቃገብነት፣ ከተቃወሱ እስላማዊ አገሮች ስደተኛን ለማስገባት አለመፍቀድና የገባንም የመመለስ ተግባር አንድ ላይ በፀረ እስላምነት እየተተረጎሙ ለጅሃዳዊ በቀል መቀስቀሻነት መዋላቸውና ሽብር መባዛት መቀጠሉ የማይቀር ነው፡፡ እነዚህ የተጠቀሱት መነሳሻዎች እስካሉ ድረስም የካታርና የሳውዲ ፀብ ምንም ያህል ለሽብርተኞች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍን የመሸምቀቅ ተፅእኖ ቢኖረውም፣ አሜሪካ የቱንም ያህል ከሁለቱም አገሮች ጋር “ፍቅሯን” ብታሞቅና የሽብርን የንዋይ ምንጭ የማድረቅ (ደጓሚ የተባሉን የማስለቀም) ውል ብታደርግም፣ ፀረ-አሜሪካና ፀረ-እስራኤል አሸባሪነት የአክራሪ አረብ መሳፍንትን ስውር ድጎማ ማግኘቱ አይቀርም፡፡ ፀረ-አሜሪካ/ ፀረ-ምእራብ እስላማዊ ፖለቲከኛነትም ከኢራንና ከሳውዲም ሆነ ከሳውዲና ከካታር ቅራኔዎች ልቆ መውጣቱና መበጥበጡ ይጠበቃል፡፡ ፅንፈኝነትና ሽብር ከደሃ አገሮች እርዳታ መቀነስ ጋር ተገናኝቶ የሚያባብሰው ቀውስ ደግሞ ራሱን የቻለ ታሪክ ነው፡፡

ደቡብ ኮሪያና ጃፓንም ሰሜን ኮሪያን የሚያለዝብና በር የሚያስከፍት ሰላማዊ ወዳጃዊ መንገድ ካልፈለጉና በኩነና፣ በጦር ልምምድና በጦርነት ጉሰማ ከአሜሪካው ትረምፕ ጋር ካበዱ፣ ቻይናም እብደቱን አቅጣጫ የማስለወጥ ሚናዋን ካልተወጣች አካባቢው ወደ ዘግናኝ የእልቂት ቀጣናነት የመቀየሩ አደጋ አፍንጫ ስር ነው፡፡ ይህንን ስጋት የምናወራው በልምጭ ሽውታ ድምፅ እየተመራ መስራት የሚጠበቅበትን ወደሚሰራ የሰርከስ እንስሳ ህዝባቸውን የቀየሩትንና ከአሜሪካና ከደቡብ ኮርያ ጋር ቅራኔያቸው ስለገረረ ብቻ የደቡብ ኮሪያን የፍቅር ፊልሞችን እንኳ ይዞ ወይም ሲከታተል የተገኘን በሞት እንቀጣለን እስከማለት ድረስ ግፈኝነት መዝምዞ የጨረሳቸውን የሰሜን ኮሪያ ገዢዎችንም አስበን ነው፡፡

ልክ እንደዚያው ከሶቪየት ህብረት መፈራረስ የተረፈችው (አሁንም ግን አህጉር አከል ስፋት ያላት) ሩሲያ ከየትም በኩል የሚመጣ ትንኮሳን በብልሃት እያሳለፈች ከምንም በላይ በቤቷ የውስጥ ችግሮች ላይ ማትኮርና የሸሹ ጎረቤቶቿን መልሶ የሚማርክ ተመንዳጊ ለውጥ ላይ መስራት ሲገባት፣ ጭራሽ ጥርስ የሚያስገባኝ ምን ጥፋት ልስራ ብሎ ጣጣ ከማነፍነፍ የማይተናነስ ስራ እየሰራች መሆኗና የሶሪያውያን መከራ አዛቋኝነቷ በአሜሪካ የምርጫ ሂደት ውስጥ እጅሽን አስገብተሻል ከሚል ነገር ፍለጋ ጋር ተላኩሶ ከመካከለኛው ምስራቅ የዘለለ ጦርነት እንዳያመጣም እያሳሰበ ነው፡፡

13) እነዚህ ሁሉ የተጠላለፉ የአለማችን ችግሮች የሚመሩን ወደ አንድ መልእክት ነው፡፡ ብዙ ነገሮች የዞሩበትና ትክክለኛ መፍትሄዎች የጠፉት የዛሬው አለም ከሁሉም ነገር በበለጠ ፅንፈኝነትን፣ ሽብርንና ጦርነትን፣ እንዲሁም ያየር ንብረት መረበሽን የሚቀንስ የስልጣኔ መሪነትን ይሻል፡፡ መፍትሄዎቹም ስውር አደሉም፡፡

ቀውስ የሚጎትትና የሚያባብስ ጣልቃ ገብነትን መቃወምና መከላከል፣ድህነትን ከአለም ለመጠራረግ መስራት፣ በዚህም ውስጥ አረንጓዴ የኢኮኖሚ ልማት ፖሊሲን የሁሉም ማድረግ፣ የአረንጓዴ ልማት ጥበቦችን (ቴክኖሎጂዎችን) ምርምሮችና ፍልሰፋዎች ማትባትና በሰፊው እንዲዛመቱ ማገዝ ሁለት ድርብ ድልን ያስገኛሉ፡- 1ኛ) የምድሪቱን ስነምህዳራዊ ሚዛንና የሰው ልጅን ህልውና በብክለትና በግለት ከመናጋት ያተርፋሉ፡፡ 2ኛ) ለውጡ፣ በበካይ ነዳጅ ላይ የተመሰረተን ቱጃርነት የትናንት ጉዳይ የሚያደርግ እንደመሆኑ ከዚሁ ጋር ስልጣኔ እንደ መዛመቱ ፅንፈኝነትና አሸባሪነት የማህበራዊ ቀርነትና የነዳጅ ንዋይ እትብታቸው ይበጠስባቸዋል፡፡

በዚህ ጎዳና ውሰጥ አለም የመፍሰሱ ነገር ግን ገና ብዙ ብዙ መዳፋት፣ መጋጋጥና መተላለቅ ያለበት ይመስላል፡፡ እንደማንኛውም አገር ኢትዮጵያም በዚህ ፈተና ውስጥ አለችበት፡፡ ፈተናውን ተረድቶና ቤትንና ዙሪያ ደጅን አስተውሎ ደግ ደጉን ማምለጫና መጠማዘዣ እየመረጡ መራመድ ግን የማይቻል ነገር አይደለም፡፡

*******

Guest Author