“አምና በዚች ወቅት ምን ውስጥ ነበርን? ዛሬስ የት ነን?” ~ ለማ መገርሳ

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ በዚህ ሳምንት በአዳማ ከተማ በተካሄደው የክልሉ 2009 ዓመት አፈፃፀም እና 2010 ዓመት እቅድ የግምገማና የውይይት መድረክ ላይ የተናገሩት ንግግር፡፡ [ክፍል አንድ]

(ከአፋን ኦሮሞ ወደ አማርኛ በHornAffairs የተተረጎመ)

ተሀድሶ ውስጥ ለምን እንደገባን ሁላችንም እናውቃለን፡፡ እራሳችን ባመጣነው ውጤት ነው ወደ ጥልቅ ተሀድሶ የገባነው፡፡ በተሀድሶ ውስጥም በጥልቀት ስናየው እየሰራንበት የነበረው ሁኔታን አኳሀን እና አሰራርን ማስተካከል አስፈላጊ ነው ብለን ባስቀመጥነው መሰረት በሁሉም አቅጣጫ ተጨባጭ ለውጥ አምጥተናል፡፡

በዚህም ትናንት የድንጋይ ናዳ ላያችን ላይ ያዘንብ የነበረውን ህዝብ፣ ቤታችን እና ቢሮአችንን እላያችን ላይ ያቃጥል የነበረው ህዝብ፣ almost ሙሉ በሙሉ ማለት በሚቻል ደረጃ እኛ ላይ ፊቱን አዙሮ የነበረውን ህዝብ፤ ዛሬ መልሰን ልናግዘው ችለናል፡፡ አብላጫውን ህዝብ ከጎናችን ማሳለፍ ችለናል፡፡ ይሄን ስኬት በየትኛውም ዋጋ ልንለካው አንችልም፡፡ ይሀ ስኬት በ20፣ በ30 እና በ50 ፕሮጀክቶች ውጤት የሚገመት አይደለም፡፡

How did it come? ይህ እንዴት መጣ? አምና በዚች ወቅት፣ በዚች ሰዓት፣ በዚች ደቂቃ ምን ውስጥ ነበርን? ዛሬስ የት ነን? ይህንን በአግባቡ መመልከት ይኖርብናል፡፡ ለውጣችን፣ ስራችን፣ ውጤታችን፣ በተጨባጭ ስኬታማ መሆን አለመሆኑን መመልከት ያለብን ይሀን በማነፃፀር ነው መሆን ያለበት፡፡

ግልፁን ለመነጋገር እዚህ ያለነው አመራሮችን ጨምሮ አምና በዚች ሰዓት ‹‹ነገ ምን ይውጠናል? ይህ መንግስት ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም? ድርጅታችን ይፈርሳል ወይስ ይቀጥላል? እውነት ከዚህ ጨለማ መውጣት እንችላለን ወይ?›› እያለ አብዛኛው ሰው – አመራሮቻችን ጭምር – ተስፋ የቆረጠበት ጊዜ ውስጥ ነበር፡፡

Photo - Oromia President Lemma Megersa
Photo – Oromia President Lemma Megersa

ከዛ ጨለማ ለመውጣት ስትራቴጂያችንን ቀይሰን፣ አካሄዳችንን እና አሰራራችንን አስተካክለን እንዲሁም ካለፈው የድርጅታችን የትግል ሂደት የቀሰምነውን እውቀት እና ልምድ አጣምረን፣ አመራሩ ብቻ ሳይሆን በሀገር ደረጃም ጭምር ተስፋ-አስቆራጭ የነበረው ሁኔታ ውስጥ ቆመን፣ ተስፋ-ሳንቆርጥ ታግለን፣ ማንም ያልጨበጠውን እሳት ሳንፈራ ጨብጠን በመስራት፣ የነበረውን ሁኔታ በመቀልበስ ተስፋ-ሰጪ ሁኔታ እና አበረታች ለውጥ አምጥተናል፡፡

ይህንን ሁኔታ ማንም አልቀየረውም፡፡ አንድም ሰው በዚህ ሂደት ውስጥ የተለየ ሀሳብ እና የተለየ ጉልበት ሰጥቶን አግዞን አይደለም ሁኔታውን የቀየርነው፡፡ እሳት ውስጥ ሆነን፣ ጦርነት ውስጥ ሆነን ነው የሚፈለገውን መሰዋዕትነት ለመክፈል በቁርጠኝነት ታግለን ነው ሁኔታውን የቀየርነው፡፡

As a system exist ማድረግ፣ መቀጠል በራሱ ጥያቄ ምልክት ውስጥ በነበረበት ሁኔታ ውስጥ ነው የነበርነው፡፡ ይህ 3 እና 4 ሚሊዬን የምንለው አባላቶቻችን እና በሺዎች የሚቆጠሩ አመራሮቻችን ጭምር ተስፋ ቆርጠው ነበር እኮ! በአካል አጠገብህ ቢኖርም፣ በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ አጠገብህ ቢኖርም psychologically divorce አድርጎ፣ ፍቺ ፈፅሞ ነበር እኮ! ትጥቁን ፈቶ ነበር! አምና በዚህች ወቅት!

ይሀ ትጥቁን ፈቶ የነበረውን ሰራዊት መልሶ በማስታጠቅና ታግሎ በማታገል፣ አሁንም መታገል እንደሚቻል ማሳመኑ ላይ ቀላል ስራ አይደለም የሰራነው፡፡ ትልቅ ስራ ይጠይቅ የነበረውም ይሀ ነው፡፡

ይህ ትልቅ ድል ነው፡፡ በዚህም ትናንት ፊቱን አዙሮብን ጠልቶን የነበረው ህዝባችን፡ ዛሬ ከጎናችን ተሰልፎ በርቱ እያለን ነው፡፡ ምንድነው ሚስጥሩ? ስለሰራን ነው፡፡

ምንድነው የሰራነው? ምንድነው የተለየ የሰራነው ሚስጥሩ? ትናንት እኛ ላይ ይዘንብ የነበረው ህዝብ ዛሬ ከኛ ጎን ለመሰለፉ ምስጢሩ ምንድነው?

አንደኛ፤ የቆምንለት ዓላማን ለቆምንለት ህዝብ boldly ግልፅ ሆነን ስለነገርነው ነው፡፡ Genuinely ለሱ እንደቆምን፣ ልባችን ውስጥ ያለውን ሀቅ በንጽህና ስለነገርነው ነው፡፡ ውሸት ሳይሆን ሌላ የተበረዘ ዓላማ የሌለው እውነታን ለህዝቡ መናገር ሰለቻልን ነው፡፡

ሁለተኛ፤ እውነት ለዚህ ህዝብ እዚህ እና እዛ ሳንል፣ ማነው እና ምነው ሳንል፣ ከልብ መታገል እንዳለብን ተመልሰን ለህዝቡ በይፋ በአደባባይ ቃል ስለገባንለት ነው፡፡ ፊቱን አዙሮብን ወደ ነበረው ህዝብ ፊታችንን አዙረን ስላሳየነው ነው፡፡

እኛ የምንፈልገው ብቻ ሳይሆን፣ ሌላው የሚፈልገው ብቻ ሳይሆን፣ የህዝቡን ፍላጎት መናገር ስለጀመርን ነው፡፡ የህዝቡን ልብ መናገር ስለጀመርን ነው፡፡ This is the secret.

በመናገራችን ብቻ አይደለም ህዝቡ ያመነን፡፡ Action! በተግባርም ስላሳየነው፣ የተናገርነውን ወስነን ተግብረን በስራ በተጨባጭ ለውጥ ማሳየት ስለጀመርን ነው፡፡ አንድ ሁለት ተብሎ ሊቆጠር በሚቻል አኳሃን በተግባር መስራት ስለጀመርን ነው፡፡ ሰርተን መለወጥ እንደሚንችል ህዝቡን ስላሳየነው ነው ባለፈው ዓመት በዚህ ወቅት ከኛ ተቃራኒ ቆሞ ሲፋለመን የነበረው ህዝብ፤ ዛሬ ከኛ ጎን ተሰልፎ ምን ላግዛችሁም ጭምር እያለ ያለው፡፡ ምስጢሩ ይኸው ነው፡፡

እንደኔ እምነት እንደ ድርጅት ለድርጅታችን OPDO ይሀ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡

**********
* የፕ/ት ለማ መገርሳ ንግግር ክፍል ሁለት – ከኛ ጎን ለመሰለፍ ማንም ከማንም የማንነት ሰርተፍኬት እውቅና ሰጪ አያስፈልገውም
* የፕ/ት ለማ መገርሳ ንግግር ክፍል ሶስት – ከ4000 የሚበልጡ አመራሮችን አራግፈናል

Daniel Berhane

more recommended stories