የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት አይጣላም!

(ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ)

ስለ ሀገርና ህዝብ ፍቅር የሚናገር ማንም ቢሆን የኋላ ታሪክን ጠንቅቆ ከማወቅ፤ ያሁኑን አጠቃላይ ሁኔታ ከማገናዘብና መጪውን ጊዜ በትክክል ከመተንበይ ቢነሳ የሚሻል የሆናል ስል አሰብኩ፡፡ በርግጥ ትክክል የሚባለው አስተሳሰብ አንፃራዊና ከማህበረሰብ እድገት ጋር ተለዋዋጭ ሁኔታን የሚከተል ቢሆን አይገርምም፡፡ በዚሁ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ተጨባጩን ሁኔታ ያገናዘበ አተያይን መከተል የተሻለ ይመስለኛል፡፡

ከዚህ ባሻገር በአንድ አስከፊ ወቅት በተፈጠረ ሰንካላ አስተሳሰብና ድርጊት ላይ ብቻ በመመርኮዝ ሀገርና ህዝብን መፈረጅ እንዲሁም ጠባሳው እንዳይሽር ማድረግ አጠቃላዩን ዘመን ማጨለም ይሆናል፡፡ ምናልባትም ከዚያ አስከፊ ገፅታ በኋላ ህዝብም ሆነ ሀገር የሰራው አኩሪ ታሪክ ይኖር ይሆናልና ከመወሰን ቀድሞ እንዚያን ሁኔታዎች መመርመር አስፈላጊ ይሆናል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ አብዛኞቹ ፀሀፍት በተለይ ዛሬ ዛሬ እየተግባቡበት እንደመጡት የዴሞክራሲን ፅንሰ ሀሳብ በተግባር ለዓለም ከማስተማር ባለፈ ከመሰል ህዝቦች ጋር በጋራና በአንድነት፤ በመፈቃቀድና በመከባበር እንዴት ይኖር እንደነበረ ሲታሰብ ሀገርንም ሆነ ህዝብን የመገንባት ታሪካዊ እሴት ያዳበረ ህዝብ እንደሆነ ምርምሮቻችንና ጽሑፎቻችን አስረጅ ናቸው፡፡ ስለ አብሮ መኖርና አንድነት እንዲሁም ስለ ኢትዮጵያዊነት ስናገር፤ አንዳንዶቹ መንፈስ አንዳንዶችም የክፋት ካባ አድርገው እንደሚስሉት እንዳይደለ ከወዲሁ አንባቢ ቢረዳኝ እሻለሁ፡፡

እኔ የማወራው ህዝቦች ያለመነቃቀፍና ያለመደነቃቀፍ አንገታቸውን እኩል ቀና አድርገው ስለሚኖሩባት፤ ሁላቸውም አቅማቸው በፈቀደ መጠን ባደረጉት ጥረትና በላባቸው ውጤት ተጠቃሚ ስለሚሆኑባት፤ ፍትሀዊ የተፈጥሮ ሀብት ክፍፍልን ያስተናገደችና መሰረታዊ የህገመንግስትና የፌዴራል ስርዓቱን መርሆዎች ለዜጎቿ ማክበር ስለምትችለዋ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህቺ ሀገር ደግሞ በሁላችን ፈቃድና መተማመን የምትገነባ እየተገነባችም የምታብብ ሀገር ናት፡፡ ነሸጥ ያረገው በአንድ ጀንበር ተነስቶ የሳላት ወይም የሚስላት ንግርትም አይደለችም፡፡ በህዝቦች እውነታ፤ ፍትሀዊና፤ እኩል አብሮ የመኖርና የማደግ ተግባር ውስጥ የምትከሰት እንጂ፡፡

የኦሮሞ  ብሔርተኝነት ከመሰረቱ ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊነት ደግሞ የራስ መብትና ጥቅምን ከሌሎች መብትና ጥቅም ሁሉ እኩል ለማስጠበቅ የሚታገል ነው፡፡ ራስን አጓጉል ወዶ ሌላውን የሚያሳንስ አይደለም፡፡ ለራስ ሲሞላ ለሌላው እንዲጎድል መሻት አይደለም፡፡ የሌላንም እድል ቀምቶ የራስ ማድረግ አይደለም፡፡ ባለኝና በፈጠርኩት እድል ልክ እንድኖር ማንንም ማስፈቀድ የለብኝም፤ መብቶቼ በእጆቼና በህገመንግስቱ ጥላ ስር ናቸው ባይ እንጂ!

ነገሩ እንዲህ ሆኖ ሳለ ከዚህ ባሻገር ደግሞ የኦሮሞ ብሔርተኝነት በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በመሸሸግ ሳይሆን ጎልቶና ጎልብቶ ኢትዮጵያዊነትን የሚያዳብር ስለመሆኑ የሚከራከሩ ሁለት ፅንፍ አስተሳሰቦች አግራሞት ይፈጥሩብኛል፡፡ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ባለ ዛሮች ከሰሞኑ ከተዳፈኑበት ወጥተዋል፡፡ ይህ ምንም ጥያቄ የሌለው የማያከራክርም የባላባቶቹን የመሳፍንቱ የአንድ ድንበር፤ ባንዲራና ቋንቋ አቀንቃኞች መንፈስ መሆኑ ነው እንግዲህ፡፡

ሌላኛው ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን ካለፈው ጠባሳ ያለመሻርና መሸሽ አድርገው የሚስሉቱም ስሙን እትጥሩብን ባዮች ናቸው፡፡ ሁለቱም ለኦሮሞም ሆነ ለሌሎች ወንድም ህዝቦች አይጠቅሟቸውም፡፡ አንደኛው ሞቶ ከተቀበረ ሁለት አስርት ያሳለፈ፤ ሌላኛውም ቢሆን ጠባሳውን ለማከክ ካልሆነ በስተቀር ትውልድ ያለፈውና ህዝባችን በዚህ ድርጊትና ጠባሳ ላይ ሌላ የሰላምና የመፈቃቀድ ሀውልት ያቆመበት ከመሆኑ አንፃር  ጠቃሚ ሊሆን አይችልም፡፡

የኦሮሞ ህዝብ ፈረሶቹን፤ ጋሻና ጦሩን፤ የድል አድራጊነት ወኔውን ባንድ ላይ አድርጎ አድዋ ሲዘምት ጣሊያንን ድባቅ በመምታት የዚህ ሀገር በቀል ህዝቦች ምድር እንዳትደፈር ብቻ ሳይሆን ስርዓቱ እየፈጠረ በነበረው ጠባሳ ላይ የአብሮነት የመፈቃቀድና የእውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አብሮነት ሀውልት እየገነባ ነበር፡፡ 5 ዓመት በዱር በገደሉ ከጣሊያን ጋር ሲተናነቅም የኮበለሉት የስርዓቱ ቁንጮ ቂቤ ቀብተውት እንዳልሆነ አጥቶ ሳይሆን ህዝቦች በጋራና በእውነተኛ አንድነት መኖር ከቻሉ የማትደፈር ሀገር ሊኖረን እንደሚችልና ይህንንም በራሱ መስዋእትነት መገንባት እንደሚቻል በተጨባጭ ማሳየቱ ነበር፡፡

እልፍ ሲልም ከታላቁ የኩሽ ነገድ የተገኙ ህዝቦች ለግሪካውያን በተጣመመ ምእራባዊ አስተሳሰብ የተሰጠውን የዓለም ስልጣኔ መንበር ቀድሞ እንደተቀመጠበት የሚያረጋግጠው ታሪክ የኦሮሞ ህዝብ ከዚህ ሀገር ባሻገርም ለአፍሪካም ሆነ ለዓለም ስልጣኔ ያበረከታቸው ሰልጡን ባህላዊ እሴቶች ባለቤት እንደሆነ፤ ከዚህ መለስ ደግሞ በሀገር ውስጥ ያልተዘመረለት ህዝብ ሆኖ እንዲቆይ የተገደደበትን ሁኔታ ወደትክክለኛው ሚዛን በመመለስ የመፈቃቀድ ኑሮን የሰበከ ህዝብ ስለመሆኑ  አስታዋሻችን ነው፡፡

ይህ ታሪክ ታሪካችን ነው፡፡ ይህ ሀቅ ሀቃችን ነው፡፡ ይህንን መካድ ሲጀመር ብቻ ነው የሌለና ከተቀበረ ዘመናት የቆጠረ መንፈስም ሆነ በክፋት ካባ የተሳለ ጠባሳን አመርቃዥ አስተሳሰብ ሆኖ የሚከሰተው፡፡

ስለዚህ የኦሮሞ  ብሔርተኘነት በምንም መሰረታዊ ነጥብ ከኢትዮጵያዊነት አይጣላም፡፡ አንድ የፌስቡክ ገፅ ፀሀፊ እንዳለው የዚህ ህዝብ ጥያቄ በኢትዮጵያዊ ማንነት ትርክት ላይ እንግባባ ነው፡፡ የሌለና ሊኖር በማይችል ትርክት ሳይሆን ከህዝብ የአኗናርና የልባዊ ፍላጎት ታሪካዊ ዳራ በመነሳት የዛሬይቱን የጋራ ሀገር እንስራ ነው፡፡ ተሰርታ ያለቀች ህንፃ አድርገው የሚያስቧትም ሆነ ፍርስርሷ ብቻ ሲወጣ ነው መልሴ የሚሉቱ ቦታ አላቸው ብዬ ማሰብ ይከብደኛል፡፡ ይልቅስ በዚህ ሀገር ሁሉም ህዝቦች ታላቅ፤ ሁሉም ህዝቦች ተጠቃሚ፤ ሁሉም ህዝቦች ፍትሀዊ የሀብት ባለቤትና የስርዓቱ አባቶች መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

በተፈጥሮ ያገኙትም ሆነ ዘመን ያመጣው መብት የትኛውንም ህዝብ ሊነፈግ አይገባም፡፡ ሰጪም ነሺም ማንም ሊሆንም አይችልም፡፡ ያለፈ፤ አሁን ያለንናና ነገ የሚኖረንን ህብር መተንበይ የሚችል አእምሮ የኦሮሞን ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ከኢትዮጵያዊነት አያጣላም፡፡ ከዚህ የሚገኝ ትርፍ ብተናና መተላለቅ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የኦሮሞን የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ልሂቃንም ሆነ ምልዓተ ህዝቡን በሞተ መንፈስ ማጥመቅ የሚታትሩ፤ የኢትዮጵያዊነትን ማንነትን እነእንቶኔ ከፈጠሩት ጠባሳ በማዋደድ አንዳልሻረ አሊያም ሊሽር እንደማይችል የሚያደርጉቱ የማን ጠበቆች እንደሆኑ ገሀድ እየወጣ መጥቷልና በኛ አይነገድ እላለሁ፡፡

**********

Guest Author

more recommended stories