ከሚኒስትሮች ይልቅ ገንዘብ ላይ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸው ዳይሬክተሮች ናቸው – ጠ/ዓቃቤ ሕግ ጌታቸው አምባዬ

የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች የሚባሉት በሚኒስትርና በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ ብቻ ያሉት አለመሆናቸውን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ አስታወቁ፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ይህንን ያሉት ቅዳሜ ሐምሌ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡

የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ተደርገው የሚወሰዱት ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች የፖለቲካ አቅጣጫ ከመስጠት ባሻገር ብዙ ሚና እንደሌላቸው፣ ይልቁንም በዳይሬክተር ደረጃ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በአጠቃላይ በገንዘብ እንቅስቃሴዎችና በቢሮክራሲያዊ ጉዳዮች ላይ የመወሰን ከፍተኛ ሥልጣን እንዳላቸው በመግለጽ፣ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በሙስና ጠርጥሮ አላሰረም ተብሎ የቀረበውን ትችት አስተባብለዋል፡፡

Photo - Ethiopian Attorney General Getachew Ambaye
Photo – የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ጌታቸው አምባዬ

መንግሥት በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው ግለሰቦች ውስጥ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደሚካተቱ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ይሁንና ዝርዝሩ ይፋ ከተደረገ በኋላ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አልተካተቱም ተብሎ ትችት እየተሰነዘረበት ነው፡፡

ይኸው ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ጌታቸው፣ ‹‹የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ብለን የምናስባቸው በሚኒስትርና በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ ብቻ ያሉትን ከሆነ ስህተት ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ በመንግሥት ኃላፊነት ከፍተኛውን የመወሰን ድርሻ ያለው በዳይሬክተር ደረጃ ያለው ኃይል ነው፡፡ አጠቃላይ የገንዘብ እንቅስቃሴውንና በቢሮክራሲው ላይ የመወሰን ሥልጣን በእነዚህ ጫንቃ ላይ የወደቀ ነው፡፡ ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች የፖለቲካ ተሿሚዎች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በዚህ ጉዳይ የሉበትም ባይባልም እንኳን፣ ዋነኛ ሥራቸው ፖለቲካዊ አቅጣጫ መስጠት ነው፡፡ ነገር ግን በምርመራው የሚገኘው መረጃና ማስረጃ ተሳትፎ እንዳላቸው ካረጋገጠ፣ በእነሱም ላይ ዕርምጃ መወሰዱና መጠየቃቸው አይቀርም፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት በሙስና ወንጀል የተሳተፉት ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ ቃል ከገባ የሰነበተ ከመሆኑ አንፃር ዕርምጃው አልዘገየም ወይ ተብለው የተጠየቁት አቶ ጌታቸው፣ የወንጀል ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚጠየቀው የማስረጃ ሚዛን ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ መሠረታዊ መዘግየት ታይቷል ለማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የፖለቲካ ሹመኞችን ከቦታቸው የማንሳት ያህል የወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደማይቀል በንፅፅር አቅርበዋል፡፡

አቶ ጌታቸው በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉ ግለሰቦች ላይ ዝርዝር መረጃ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም ውሳኔው የተወሰደው መንግሥት በሙስና ተግባር የተሳተፉትን በሕግ ፊት ለማቅረብ ቃል በገባው መሠረት፣ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግና በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዙሪያ ቅንጅት እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የዕርምጃው መነሻም የፌዴራልና የአዲስ አበባ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤቶች ሪፖርቶች፣ የመንግሥት ሠራተኞች ጥቆማ፣ ከኅብረተሰቡ የተሰጠ ጥቆማና መንግሥት በራሱ ያደረጋቸው ጥናቶችና ክትትሎች እንደሆኑ አስገንዝበዋል፡፡

ውሳኔ የተወሰደው በዋነኛነት በአምስት መሥሪያ ቤቶች ላይ ሲሆን እነዚህም የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን፣ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ስኳር ኮርፖሬሽንና የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ናቸው፡፡ ከእነዚህ መሥሪያ ቤቶች ያልተገባ እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ 42 ግለሰቦች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል፡፡ እነዚህም 32 የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎች፣ ሦስት ደላሎችና ጉዳይ አስፈጻሚዎች፣ ሰባት ባለሀብቶች በድምሩ 42 ግለሰቦች ናቸው፡፡

በፌዴራል ደረጃ በርካታ ተገቢ ያልሆኑ የሙስና ተግባራት ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩት ግለሰቦች በተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ውስጥ የተሳተፉ ናቸው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶችም የኮምቦልቻ-ወልዲያ መንገድ ፕሮጀክት፣ የማይፀብሪ-ዲማ መንገድ ፕሮጀክት፣ የጊምቦ-አርባ ምንጭ መንገድ ፕሮጀክት፣ የሐረር-ጅግጅጋ መንገድ ፕሮጀክት፣ የጎሬ-ጋምቤላ መንገድ ፕሮጀክት ናቸው፡፡ በእነዚህ አምስት የመንገድ ፕሮጀክቶች ለመንግሥት ገቢ መደረግ የነበረበት 1.358 ቢሊዮን ብር እንደከሰረም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕጉ ገልጸዋል፡፡

አቶ ጌታቸው ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በፍርድ ቤት መያዣ መሆኑን ጠቁመው፣ በግለሰቦቹ ንብረት ላይ የብርበራና ፍተሻ ትዕዛዝ ከፍርድ ቤት በመውሰድ በተደረገው ብርበራና ፍተሻ በርካታ የአሜሪካን ዶላር፣ የእንግሊዝ ፓውንድ፣ ዩሮና ሌሎች የውጭ ገንዘቦች በብዛት መገኘታቸውን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም የባንክ ደብተሮች፣ የቤትና የይዞታ ማረጋገጫ ሰነዶች፣ የቤትና የጭነት ተሽከርካሪ ሊብሬዎች፣ የአክሲዮን ክፍያ ሰነዶች መገኘታቸውንም አመልክተዋል፡፡

********

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories