በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት 34ቱ ሀላፊዎችና ባለሀብቶች

(በታሪክ አዱኛ – ፋና)

መንግስት በሙስና ወንጀል ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው 34 የተለያዩ ተቋማት የስራ ሀላፊዎች፣ ባለሀብቶችና ደላሎች ሐሙስ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ተጠርጣሪዎቹ ባዘሬው እለት በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ የወንጀል ችሎት ቀርበው የተጠረጠሩበት መነሻ በፖሊስ ተገልፆላቸዋል።

በተለያዩ 14 የክስ መዝገቦች ተከፋፍለው የቀረቡት ከኢትዮጵያና ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን፣ ከስኳር ኮርፖሬሽን እና ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ 34 ተጠርጣሪዎች ናቸው።

ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን

ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ /የቀድሞ የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ/

ኢንጂነር አህመዲን ቡሴር

ኢንጂነር ዋስይሁን ሽፈራው

ሚስተር ሚናሽ ሌቪ (የትድሃር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት እና ስራ አስኪያጅ)

ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን ተጠርጥረው የቀረቡት፥ በአዲስ አበባ ከተማ ከማዕድን ሚኒስቴር እስከ ውሃ ሃብት ድረስ ያለውን መንገድ ሲያሰሩ ያልተገባ ውል መዋዋላቸውን ፖሊስ ለችሎቱ ገልጿል።

ተጠርጣሪዎቹ በዚህ ፕሮጀክት ከትድሃር ጋር በመሻረክ 198 ሚሊየን 872 ሺሀ 730 ብር ከ11 ሳንቲም መንግስትን አሳጥተዋል ሲልም ነው ፖሊስ ያቀረበው።

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን

አቶ አብዶ መሐመድ

አቶ በቀለ ንጉሤ

አቶ ገላሶ ቡሬ

አቶ የኔነህ አሰፋ

አቶ አሰፋ ባራኪ

አቶ ገብረአናንያ ፃዲቅ

አቶ በቀለ ባልቻ

ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በተጠርጣሪነት የቀረቡት እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ በከፍተኛ ሀላፊነት ሲሰሩ፥ ኮምቦልቻ፣ ሃረር፣ ጅግጅጋ እና ጋምቤላ ጎሬ በተሰሩ አራት የመንገድ ፕሮጀክቶች ላይ አስፈላጊ የዲዛይን ጥናት ሳይደረግና ምንም ህጋዊ ውል ሳይኖር ሆን ተብሎ ዋጋ እንዲጨመር በማድረግ፣ ከአሰራር ውጪ የኮንትራት ውል አዘግይተዋል ነው ያለው ፖሊስ።

በዚህም ፕሮጀክቶቹ በመዘግየታቸው 646 ሚሊየን 980 ሺህ 626 ብር ከ61 ሳንቲም ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው መቅረባቸውን ፖሊስ ጠቅሷል።

ከስኳር ኮርፖሬሽን

ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ

አቶ አበበ ተስፋዬ /በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የአገዳ ተከላ ምክትል ዳይሬክተር/

አቶ ቢልልኝ ጣሰው /በተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ ጠቅላላ ሂሳብ ያዥ/

ሁለቱ ግለሰቦች በጋራ በመመሳጠር ፖሊስ ስሙ ለጊዜው በመዝገብ ካልጠተጠቀሰው  ኩባንያ ጋር የአርማታ ብረት እና ሲሚንቶ በዓይነት ማስረከብ ሲገባ፥ ሳይረከብና ተቀናሽ ሳይደረግ 31 ሚሊየን 379 ሺህ 985 ብር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተመልክቷል።

ከመተሃራ ስኳር ፋብሪካ

አቶ እንዳልካቸው ግርማ

ወ/ሮ ሰናይት ወርቁ

አቶ አየለው ከበደ

አቶ በለጠ ዘለለው

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አቶ እንዳልካቸው፣ ወ/ሮ ሰናይት እና አቶ አየለው በመተሃራ ስኳር ፋብሪካ የግዢ ቡድን መሪ እና የውጭ ሃገር የእቃ ግዢ ሀላፊዎች ሆነው ሲሰሩ፤ 13 ሚሊየን 104 ሺህ 49 ብር ከ88 ሳንቲም ለአቅራቢዎች ያለአግባብ እንዲከፈል በማድረጋቸው፤ እንዲሁም አቅራቢዎቹ ባላቀረቡበት ሁኔታ ላይ 0 ነጥብ 1 በመቶ ቅጣት ማስቀመጥ ሲገባቸው በዚህም 2 ሚሊየን 743 ሺህ 35 ብር በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

አቶ በለጠ ዘለለው በመተሃራ ስካር ፋብሪካ የፋይናንስ ሀላፊ ሆኖ ሲሰራ ፋብሪካው ለመሳሪያ እድሳት ያልተሰራበትን 1 ሚሊየን 164 ሺህ 465 ብር ክፍያ በመፈፀም ተጠርጥሯል።

ከኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5

አቶ መስፍን መልካሙ/የኦሞ ስኳር ፋብሪካ ቁጥር 5 ምክትል ዋና ዳይሬክተር/

ወይዘሮ ሳሌም ከበደ

ሚስተር ጂ ዮኦን /የቻይናው የጄጄ አይ ኢ ሲ ተቋራጭ ስራ አስኪያጅ/

አቶ ፀጋዬ ገብረአግዚአብሄር

አቶ ፍሬው ብርሃኔ

ተጠርጣሪዎቹ በኦሞ ኩራዝ ቁጥር 5 ሲሰሩ ከተዘረዘሩት ተጠርጣሪዎች ጋር በመመሳጠር በስራ ላይ የሚገኘውን ፕሮጀክት ያለአግባብ ውል በመስጠት 184 ሚሊየን 408 ሺህ ብር ጉዳት በማድረስ ፖሊስ መጠርጠራቸውን ጠቅሷል።

ከተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ

አቶ አበበ ተስፋዬ

አቶ ዳንኤል አበበ

አቶ የማነ ግርማይ

በተንዳሆ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የቤቶች ልማት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል አበበ ከፋብሪካው የአገዳ ቆረጣ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ ተስፋዬ ጋር በመመሳጠር የተለያዩ የክፍያ ሰነዶችን በመሰረዝ እና በመደለዝ ለሶስተኛ ወገን ለአቶ የማነ ግርማይ 20 ሚሊየን ብር ያለአግባብ ክፍያ በመፈፀም እና በዓይነት እና በገንዘብ ሳይመለሰስ በመቅረቱ ተመሳሳይ መጠን ያለው ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

በሌላ መዝገብ

አቶ አበበ ተስፋዬ

አቶ ኤፍሬም ዓለማየሁ እና

አቶ የማነ ግርማይ

አቶ አበበ እና አቶ ኤፍሬም ከአቶ የማነ ግርማይ ጋር በመመሳጠር ለባቱ ኮንስትራክሽን 2 ሺህ ሄክታር መሬት ምንጣሮ 1 ሄክታሩን በ25 ሺህ ተዋውሎ ሳለ ስራውን ከባቱ ኮንስትራክሽ በመንጠቅ ለአቶ የማነ ግርማይ አንዱን ሄክታር በ72 ሺህ 150 ብር የ42 ሚሊየን ብር ልዩነት እያለው ያለምንም ጨረታ እንዲሰጠው በማድረግ በአጠቃላይ ከ216 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል።

አቶ ፈለቀ ታደሰ

አቶ ኤፍሬም ደሳለኝ /የተንዳሆ ስኳር ፋብሪካ የግዢ እና ንብረት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተር/

1 ሺህ ሄክታር መሬት እንዲመነጠር ለባቱ ኮንስትራክሽን በመስጠት ተገቢው ስራ ሳይሰራ 10 ሚሊየን ብር ለባቱ ኮንስትራክሽን እንዲከፈል በማድረግ ተጠርጥረዋል።

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር

አቶ ሙሳ መሐመድ /የሚኒስቴሩ የፕሮጀክት ምክትል ስራ አስኪያጅ/

አቶ መስፍን ወርቅነህ /የሚኒስቴሩ የፕሮጀክት ባለሙያ/

አቶ ዋስይሁን አባተ /የሚኒስቴሩ የህግ ክፍል ዳይሬክተር/

አቶ ታምራት አማረ /የሚኒስቴሩ ባለሙያ /

አቶ ሰም ጎበና /የሚኒስቴሩ ባለሙያ /

አቶ አክሎግ ደምሴ /የሚኒስቴሩ የህግ ባለሙያ/

አቶ ጌታቸው ነገራ /የሚኒስቴሩ ባለሙያ /

የሚኒስቴሩ ባልደረባ ያልሆኑ፡-

ዶ/ር ወርቁ ዓለሙ

አቶ ዮናስ መርአዊ

አቶ ታጠቅ ደባልቄ

ተጠርጣሪዎቹ በሚኒስቴሩ በተለያዩ የስራ ሀላፊነት ላይ ሲሰሩ መንግስት የፋይናንስ ስርዓቱን ለማዘመን 2 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድር በመውሰድ ለቴክኖሎጂው ማስፋፊያ ስራ የበጀተውን ገንዘብ ያለ አግባብ በመጠቀም ቴክኖሎጂውን ከሚሰሩት ዶክተር ወርቁ ዓለሙ፣ አቶ ዮናስ መርዓዊ እና አቶ ታጠቅ ደባልቄ ጋር በመመሳጠር ቴክኖሎጂው በተገቢው መንገድ አቅም ላላቸው ባለሙያዎች መስጠት ሲገባው ዓለም አቀፍ ህጋዊ ጨረታን ሳይከተሉ በማሰራት 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረዋል። ተመሳሳይ የገንዘብ መጠን ያልተሰራበትን እንደተሰራ በማድረግ ክፍያ በመፈፀም ነው የተጠረጠሩት።

በአጠቃላይም 37ቱም ተጠርጣሪዎች ከ1 ነጥብ 15 ቢሊየን ብር በላይ ለተለያዩ የመንግስት ተቋማት የፕሮጀክት ስራ የወጣን ወጪ አጉድለዋል ሲልም ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል።

ተጠርጣሪዎቹ የዋስትና ጥያቄ ይፈቀድላቸው ዘንድ ችሎቱን ጠይቀዋል።

ፖሊስ በበኩሉ ያልጨረስኩት ሰነድ እና ማስረጃ ስላለ ለምርመራ ተጨማሪ 14 ቀን ይሰጠኝ በማለት ጠይቋል።

ተጠርጣሪዎቹ የተለያዩ ሰነዶችን ሊያሸሹ ይችላሉ በማለትም የጠየቁት የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ይሁንልኝ ብሏል።

ችሎቱም የፖሊስን ተጨማሪ የ14 ቀን ቀጠሮ በመፍቀድ ለነሃሴ 3 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ ባላፈም ተጠርጣሪዎች ከጠበቃና ቤተሰብ ጋር እንዳንገናኝ ተከልክለናል በማለት ላቀረቡት አቤቱታ ችሎቱ ፖሊስ ተጠርጣሪዎቹ ከጠበቃና ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ እንዲያደርግ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

*******

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories