ስለ ፊንፊኔ አዲስ አበባ እንቅጩን እንነጋገር

(ቶለዋቅ ዋሪ)

እውነት እውነቱን መነጋገር ተገቢና አስፈላጊ ነው ፊንፊኔ አዲስ አበባ የፌዴራል መንግስት መቀመጫና ዋና ከተማ፤የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መቀመጫና ዋና ከተማ፤ የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫና የበርካታ ዲፕሎማቶች መኖሪያ ቦታ ናት፡፡

እንዲሁም ፊንፊኔ አዲስ አበባ በርካታ የአገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ ምክንያቶች በፊት ከነበሩበት አካባቢ መጥተውባት የሚኖሩባት እጅግ በጣም ሰፊ ዋና ከተማችን ናት፤ ስለ ፊንፊኔ አዲስ አበባ ተጨባጭ እውነታዎች ከዚህም በላይ ብዙ ነገሮችን መዘርዘር ይቻላል፡፡

ፊንፊኔ በውስጧ ሌባውን፤ አጭበርባሪውን፤አጨናባሪውን፤ ቀምቶ አዳሪውን፤አወናባጁን፤አስመሳዩን በውስጧ የያዘችውን ያህል ቅን አሳቢዎችን፤ ለፍቶ አዳሪዎችን፤አርቆ አሳቢዎችን እንዲሁም ለአገራችን በቅንነት ከተንቀሳቀሱ ብዙ ነገር በመስራት ላይ ያሉና መስራት የሚችሉ በርካታ ምሁራንን ሰብሰብና እቅፍ አድርጋ በውስጧ የያዘች መዲናችን ናት ፊንፊኔ አዲስ አበባ፡፡

ከመሬት ሃብት ጋር ተያይዞ በፊንፊኔ አዲስ አበባ ዙሪያ ቀደም ሲል በባርካታ ሞጭላፋዎች በርካታ ወንጀሎች ተፈፅመዋል ኣሳቃቂ ወንጀሎች ነበሩ በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ለዘመናት የኖሩ የኦሮሞ አርሶ አደሮች በልማት ስም እየተገፉ ከመሬታቸው እንዲፈናቀሉ ተደረገ፤ለስም የተሰጠው ውስን ካሳ ሲሟጠጥ አርሶ አደሩ በአዲስ አበባ የተለያዩ ግለሰቦች መኖሪያ ቤትና ማህበራት ዘበኛ ሲሆን ወንዶች ልጆቹም መማር ሲገባቸው በተመሳሳይ ጥቃቅን ስራዎች ላይ ለመሰማራት ተገደዱ ሌሎቹም ተሰደዱ፤የአርሶ አደሩ ሴት ልጆች ደግሞ የአዲስ አበባ ቡና ቤቶች አገልጋይና ለአረብ አገራት ዜጎች ገረድ ሆነው ቀሩ፤በጣም ያሳዝናል ጉዳዩን በቅርበት ላየውም ያንገፈግፋል፡፡

በኦህዴድ/ኢህአዴግ መስመር የሚመራው የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ስለፊንፊኔ ይህን ሁሉ እውነታ ያውቃል፤ በአግባቡም ይረዳል በዚህ ምክንያት በፊንፊኔ ያሉ መልካም ነገሮች በአብሮነት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እኩይ ድርጊቶች ዳግሞ ሙሉ በሙሉ እንዲወገዱ ፅኑ ፍላጎትና አቋም አለው፡፡

ነባር ወንጀሎችን በአስተማማኝ ሁኔታ መከላከል እንዲቻል ደግሞ የፊንፊኔ አዲስ አበባና የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ዳር ድንበር በሁሉም አቅጣጫ ያለ ምንም ማድበስበስ ተለይቶ መታወቅ አለበት፤ ይህ ሲሆን በአካባቢው ያለውን የኦሮሞ አርሶ አደር በጥቂት ገንዘብ በማማለል መሬቱን ሸንሽኖ ለግለሰቦች እንዲሸጥ ውስጥ ለውስጥ የሚደረገውን እኩይ ድርጊት ማስቀረት ይቻላል አርሶ አደሩም ከህገ ወጥ የመሬት ሃብት ችርቻሮ ወጥቶ በአንድ ሃሳብ በምርትና ምርታማት ስራ ላይ በመሰማራት ለአዲስ አበባ በሚያቀርበው ምርት ከኢኮኖሚው ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

አዲስ አበባ ውስጥ ያለው ደላላና የአየር በአየር የመሬት ነጋዴም አርፎ ይቀመጣል በገንዘብ ኃይላቸው ተመክተው መሬት ለመግዛት የሚጎመዡ አዲስ አበቤዎችም ቁርጣቸውን አውቀው አርፈው ይቀመጣሉ፤ስለዚህ ዳር ድንበሩ የቱጋ እንደሆነ ተለክቶ በአግባቡ ተለይቶ መታወቅ አለበት ይላል የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በፅኑ አቋሙ፡፡

ይህን ግልፅና ፅኑ አቋም የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ለማ መገርሳ በዘንድው የጨፌ ኦሮሚያ 6ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ በክልሉ ሕግ አውጪና ወሳኝ አካል ፊት ቀርበው ይፋ አድርገዋል፤ ውሳኔውም የተሰመረበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ለማ እንዳሉት ዘንድሮ በኦሮሚያ ክልልና ሌሎች ክልሎች መካከል የነበሩ የድንበር ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኙ ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ አመርቂ ውጤት ተገኝቷል፤ የኦሮሚያና የፊንፊኔ የድንበር ጉዳይ ግን ዘላቂ መፍትሄ ሳያገኝ አስከ አሁን እንደ አለ አለ፤ችግሩ ዘላቂና የማያወላዳ መፍትሄ እንዲያገኝ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርና ከኦሮሚያ ክልል የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ሰሞኑን የተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ አስረኛው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተግባራዊ የሚሆንበትን አቅጣጫ በማስቀመጥ አፅድቆታል፤ የከተማዋ ከንቲባ ክቡር አቶ ዲሪባ ኩማ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከአሁን በኋላ አዲስ አበባ ወደ ጎን የምትሰፋበት ዕድል ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል፤ ከእንግዲህ ፊንፊኔ አዲስ አበባ በአዲሱ ማስተር ፕላን መሰረት ማደግ የምትችለው ወደ ላይ ብቻ ነው! የወደ ጎኑ ነገር አበቃለት!

ስለዚህ በሁለቱም ወገኖች በኩል የማይነቃነቅ አቋም የተያዘ መሆኑ ግልፅ ሆኗል፤ከአሁን በኋላ ምክንያት በመደርደር የእናቴ መቀነት አደናቀፈኝ ማለት አይቻልም!ለድንበር ማካለል ስራ የተቋቋመው የጋራ ኮሚቴ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ በመስራት ተልዕኮውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን የኦሮሚያ ክልል ከፊንፊኔ አዲስ አበባ በሚያገኘው ልዩ ጥቅም ላይ ተፅዕኖ የሚያደርስ ከሆነ ሊተገበር የማይችል እንደሆነም በግልፅ አቋም ይፋ ተደርጓል፤ ይህ አቋም ትክክለኛና ሁሉም ቅን ኦሮሞዎች የሚደግፉት መሆኑን በመረዳት አዲሱን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ያለምንም ወለም ዘለም በትክክለኛ አቅጣጫ መተግበር ለጋራ ተጠቃሚነት ምቹ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር ግልፅ ነው

ፊንፊኔ የእኛ ብቻ ናት ለሚሉቱ!

ፊንፊኔ አዲስ አበባ በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ የአንድ የተወሰነ አካል ዋና ከተማ አይደለችም፤ፊንፊኔ አዲስ አበባ አሁን የሁሉም ናት፤ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መቀመጫና ዋና ከተማ መሆኗ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠ ጉዳይ ነው ክልላዊ መንግስቱ በማያዝባት ከተማ መቀመጥ አይችልም ሄዶ የራሱን ዋና ከተማ ይፈልግ ማለትም አይቻልም! አያዋጣም አሁን ባለው ሁኔታ ፊንፊኔ የእኛ ብቻ ናት ሌሎቹ የራሳቸው ጉዳይ ብሎ በጥበት አመለካከት ድርቅ ማለትም የሚያዋጣ አካሄድ አይደለም፡፡

በፊንፊኔ አዲስ አበባ ጉዳይ ሰሞኑን ጠባቡና ትምክህተኛው ኃይል ሲለፍፍ የቆየው ሁሉ ተሰምቷል፤ታወቋል ይህ ኃይል ለጥቅሙ ሲል መስራት ያለበትን ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ግልፅ ነው፤አሁን ያለውና በአዲስ መልክ የተዋቀረው የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ደግሞ ከሚመራው ሰፊ ሕዝብ ጋር በመሆን ለዘላቂ ጥቅሞች መረጋገጥና ለአብሮነት ኑሮ ቀጣይነት የሚሰራውን ሁሉ ያውቀዋል ሙያ በልብ ነው ይላል ያገሬ ሰው።

*********

Guest Author

more recommended stories