አመራሮች ሆይ በልብም በግብርም አንድ ሁኑልን

(ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ)

በዚህ መድረክ አንዳንድ ትችቶችን ማቅረብ ከጀመርኩ ውዬ አደርኩ፡፡ ተነካን ብለው ከሚያነካኩ ሰውሮ ውሎ ያሳድርህ በሉኝ እንጂ እኔማ ባለኝ መረጃ አቅም ህዝብ ህገ መንግስቱ በፈቀደለት የአብሮ መኖርና ከልማቱ የመጠቀም ሉዓላዊ መብቱ እንዳይሸራረፍ የሚጠቁሙ ሀሳቦችን ከማቀበል አልቦዝንም፡፡

መቼም ያለውን የሰጠ ንፉግ አይደለምና ሁሉም በየመስኩ ለህዝብና ለሀገር ሉዓላዊነት መስዋእትነት የመክፈልን አደራ ፈቅዶና ወዶ ቢቀበል ማለፊያ ይመስለኛል፡፡

ይህ ሲሆን ደግሞ ባለፉት ስርዓቶች ጉዳት ደረሰበት፤ ተጨቆነ፤ ተገፋ የምንልለት ህዝባችንን በትግሉ ያገኛቸውን መብቶቹን ሳያዛባ የአብሮ መኖር መርሆችን ሳይጥስ ተጠቃሚነቱን እንዲያጎለብት ልናደርገው እንችላለን፡፡

በታሰበለት ጊዜም ጠንካራ ኢኮኖሚ ያለውና የዳበረ ፖለቲካዊ አስተሳሳብ የተጎናጸፈ ህዝብ ልንፈጥር እንችላለን፡፡ ህብረ ብሔራዊነቱን ለበለጠ አብሮነትና ብልጽግና ለማዋል ንቃተ ህሊናው የበቃ ህዝብም ሊኖረን ይችላል፡፡

ታዲያ ይህ የሚሆነው በተያያዝነው የህዝብ ተጠቃሚነት መርህ ማንም ሳይጎዳና የማንም መብት ሳይነካ መፈጸም ስንችል ነውና ትእግስት፤ አርቆ ማሰብና አስተዋይነት የተሞላበት ጉዞን በደንብ የራስ ማድረግን ይጠይቃል፡፡ከሁሉም በፊት የራስ ጥቅምን ያለማስቀደም፤ ለብልጣ ብልጥ ጥገኞች ሴራ ያለመንበርክክ፤ በግል ጥቅምና ህዝባዊነት መካካል ያለን ትልቅ ገደል ማጤንን ይጠይቃል፡፡

የሆነስ ሆነና እኛ ራስን በራስ የማስተዳዳር ህገመንግስታዊ ፈቃዱን የምንተገብር አመራሮችስ ምን ያህል እንተዋወቅ ይሆን?? ምን ያህላችንስ የምንመራውን ህዝብ ለእድገትና ለብልጽግናው የሚያስፈልገውን መስዋእትነት ለመክፈል ተዘጋጅተን ይሆን??

ስንታችንስ የተጀመረው የህዝብን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ክልላዊ አብዮት ግቡን ይመታ አይመታ ስንል ልክ እንደ ነፃ ትግል ሜዳ ተመልካች ልባችን ተንጠልጥሎ አለ? ስንታችንስ እንሆን ስናውቅ በድፍረት ሳናውቅም በስህተት ከምንቃርማት የህዝብ መቀነት ፍራንክ ላይ ሀሳባችንና ዓይናችን ተተክሎ የቀረ?

ስንቶቻችን እንሆን እነ እንቶኔ በፈጠሩት የእዝ ሰንሰለት ተተብትበን የገዛ ተፈጥሮአችን የቸረችንን ሀብት ወደ ምጣኔ ኃብት መቀየር የማንችል ደካሞች አድርገን ራሳችንን የቆጠርን? ስንቶቻችንስ እንሆን መንግስት ለስራ ፈጠራ የሚሰጣቸውን አቅጣጫዎች በፈንድ የመደገፍ አልፋና ኦሜጋ አድርገን በመቁጠር ተስፋ ቆርጠን መቆዘም አሊያም ማሳበብ የጀመርን?

እንግዲህ የዛሬው ጽሁፍ አመራሩን የሚመለከት ነውና ህዝባዊ ወገንተኝነትና ኢኮኖሚን የመምራት ብቃት ሲያንስ የእናቴ መቀነት አደነቃቀፈኝ ሰበብ ይዘን ህዝብን ከቀደመበት ለመመለስና አብረን ለመጥፋት የምናስብ ራሳችንን እንድናውቅ ብሎም እጃችንን እንድንሰበስብ ሲዘልቅም ከመንገድ ላይ ዞር በማለት እንቅፋት ላለመሆን የመጣርን ምክር ጀባ የምልበት መጣጥፍ ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡

አሁን ማ’ይሙት ሁሉም የኦሮሚያ ወረዳና ከተማ አመራር ባለበት የየራሱን ቀዬ የንግድ፤ የኢንቨስትመንትና ስራ ፈጠራ ያደረገ ስራ በቁርጠኝነት ቢያከናውን እስካሁን የምናስመዘግበው ውጤት ምንኛ ያኮራ ነበር?

በየራስ ቀዬ ያለን ኢንቨስትመንት ስራ ቆጠራ /ኢንቬንቶሪ/ ለማካሄድ በከፍተኛ አመራሩ አዝማችነት የተጀመረው አብዮት በቂ አይደለምን??

ጥገኛ ባለሀብቱን አንድም በምክር አንድም በህግ ወደ መስመር በማስገባት ስግብግብ እጁን እንዲሰበስብ ለማድረግ የግድ ፕሬዝዳንቱ በየዞኑና በየወረዳው መገኘት ይጠበቅባቸዋል? ይህ ከሆነስ የናንተ አስፈላጊነት እምኑ ላይ ነው ያሰኛል፡፡

በርግጥ ሁሉንም ህገወጦች ህግ ለማስያዝ ህጉን ጠንቅቆ ማወቅና መተግበር ወሳኝ እንደሆነ ሳይዘነጋ ነው ታዲያ፡፡ ህገወጦችን ስርዓት በማስያዝ ወደ ህዝባዊነታችን ለመመለስ የተያዘውን የጥልቅ ተሃድሶ ጉዞ ቆሞ በመመልከት ሳይሆን በተግባባንበት አግባብ መፈጸም ብቻ ነው የሚያወጣው፡፡ ካልሆነ ቦታውን ለራሱ ለህዝቡ አስረክቦ ከዳር ቆሞ መመልከት ይሻል ይመስለኛል፡፡

የክልሉ መንግስትም እነዚህን አብዮቱ ይሳካ አይሳካ፤ ወደፊት ይጓዝ ወይስ ልጓም ተበጅቶለት ይደነቃቀፍ እንደሁ እስኪ ቆየት በለን ብናየው በሚል ዓይነት ስሜት ቆመው የቀሩ የታች አመራሮች ይህ መቆሚያ ቦታ ሳይሆን ሚዛን ሳይስቱና ፍጥነትን ሳይቀንሱ ለህዝብ ጥቅም ብቻ የሚሮጡበት መም ነውና ደንቃራ አትሁኑ ቦታ ፈልጉ ቢላቸው የተሻለ ነው፡፡

አሊያማ ልክ በአርሲ ገደብ አሳሳ እንደሆነው ፕሬዝዳንቱ በህገወጥ የተያዘን ባዶና ያልለማ መሬት በህጋዊ መንገድ ቀምተው ለወጣቶች በሰጡ ማግስት የሆነ ልቡ ያበጠ ትምክህተኛ ባለሀብት ተነስቶ ወጣቱን ሲያባርርና መሬቱን መልሶ ሲቆጣጠር የውጊያ ሜዳውን መምራት የሚሳነው አመራር ለኔ በጥቅም አሊያም በፍርሃት ከመልፈስፈስ ውጪ የሚሰጠኝ እንድምታ የለም፡፡

እናም እንተዋወቅ ይሆን ብዬ ድርጅቴንና መንግስቴን እንደጠይቅ አደረገኝ፡፡

ወጣቱን ስራ ፈጣሪ ሁን ስንለው መንግስስት ከዚህም ከዚያም ለቃቅሞ በሚያበድረው ሳንቲም ብቻ ምልዓተ ህዝቡን ጠንካራ ኢኮኖሚ ያለው ማድረግ የምንችል ይመስል በየስብሰባ አዳራሹ ወጣቱን አጉሮ ከፌዴራል ወይም ከክልል ብር ስላልመጣ እንዲህ ሁኑ እንዲያ ስላለ ከተጠያቂነት የሚድን የሚመስለው ስንት ጉደኛ አመራር አለ መሰላችሁ፡፡

ኢኮኖሚን መምራት እውቀት ይጠይቃል፡፡ ይህም እውቀት ህዝቡ ጋር አለ፡፡ የየአካባቢውን ተፈጥሮና የልማት እድል በማጥናት ወጣቱ ከድህነት ጋር ትንቅንቅ እንዲገጥም፤ መንግስት የሚያስገኛቸው እድሎች እንደ አንድ እንጂ እንደ መጨረሻ አማራጭ መወሰድ እንደሌለባቸው ማስተማር፤ ንቃትን ማስታጠቅና ቁጭትን ማስረጽ የሁሉም አመራር ስራ ነው፡፡

ይህቺ ሀገር መራር ድህነትና ኋላቀርነት ያለባት እንደመሆኗ መጠን ሚዛን የሚያስታት እንቅፋት መጠኑ ለሌሎች ሀገራት ቁብ የማይሰጣቸው ምናልባትም ስንደነቃቀፍ ሲመለከቱን መሳቂያ ልንሆናቸው ሁሉ እንችል ይሆናል፡፡

ታዲያ ይህ ቁጭትን የሚፈጥር እንዲሆን ወጣቱ ትንቅንቁን ከማጣት (ድህነት) ጋር አድርጎ በአሸናፊነት እንዲወጣ የማንንም እጅ እንዳይጠብቅ የማድረግ ስራ ጎን ለጎን ካልተሰራ፤ በየአካባቢው ባለ የምጣኔ ሃብት ክምችት በመጠቀም ለማሰማራት በጥልቀት ካልታሰበ ወደላይ በማንጋጠጥ ብቻ የሚፈጠር ሀብትም ሆነ የሚቀረፍ ድህነት አይኖርም፡፡

በርግጥ ፌዴራል መንግስቱም በመስከረም ወር የመጨረሻው ሳምንት የመጀመሪያው ሰኞ ለወጣቶች ቃል የገባው አስር ቢሊዮን ብር የት እንደ ገባ ቢነግረን የተሻለም ነው፡፡ እሱ መልስ እስኪያገኝ ደግሞ የመካከለኛና የታች አመራሮቻችን የጥያቄ ሳይሆን የመፍትሄ አካል መሆን ይገባቸዋል፡፡

የዚህ ጊዜ ምልዓተ ህዝቡ ክቡር ፕሬዝዳንቱ እኛ ወረዳ ወይም ዞን ባለመድረሳቸው ነው ከሌላው ህዝብ እኩል ጥቅማችን ያልተጠበቀው ብሎ ከመማረር ለካ ፕሬዝዳንቱ በየቤታችን አሉና ሲል አብሮህ ወደልማትና እድገት ይተማል፡፡

አለዚያማ ይኸው በአብዛኞቹ ኦሮሚያ ከተሞች እንደምንሰማው የመሬት መስሪያ ቦታ አገኛችሁ ተብለው ከሶስት ወራት በኋላም ምንም እጃቸው ሳይደርስ ላም አለኝ በሰማይ እያሉ እንደሚገኙት የመንግስት ሰራተኞች ሁሉ ህዝብም በናንተ ትከሻ ተሸግሮ የላይኛውን እርከን ሲመለከትና አውቶቡስ ሞልቶ ፊንፊኔን ሲያጨናንቃት መዋል ብቻ ሳይሆን የኋላኋላ ያለችውንም ጥሪት ከእጁ ስትሟጠጥ የሚከተለውን አብረን መገመት እንችላለን፡፡

አመራሮቻችን ሆይ ልባችሁ ብቻ ሳይሆን ግብራችሁም አንድ ይሁንማ!!

********

Guest Author

more recommended stories