ግንቦት ሰባት – የነአምን ዘለቀና ኢሳያስ አፈወርቂ ስውር ሴራ ሰለባ

(አለባቸው ተሰማ)

እኔ በኢትዮጵያ አንድነት ሀይሎች ስር ሆኜ ኢህአዴግን ከስሩ ለመመንገል ወስኜ መታገል ከጀመርኩ ቀላል የማይባሉ ጊዜያት አሳልፍያለሁ። በከፍተኛ ወኔ’ና የሀገር ፍቅር መንፈስ ነበር የአንድነት ሀይሎችን የተቀላቀልኩት።

ለሀገሬ አንድነት መታገሌ አሁንም የምኮራበት ውሳኔየ ነው። ምናልባት አሁን ካለሁበት የትግል መስመር ብወጣ እንኳን በህይወት ከኖርኩ ለሀገሬ አንድነት ከመታገል እንደማላቆም ሙሉ ልቤ ያውቀዋል።

በትግል ውሰጥ ሁሉም ዓይነት ፈተናዎች ያጋጥማሉ። ከፈተናዎች ሁሉ የከበደኝ ነገር ግን በአንድነት ስም እንታገላለን ብለው ሀገራችንን የሚያፈርሱ፤ የኢህአዴግ ተላላኪዎች ሆነው የሚሰሩ ከዚያም አልፈው ሰብአዊ ማንነታቸውን ክደው ለሌሎች በባርነት እያገለገሉ የኢትዮጵያን ህዝብ የዴሞክራሲና የእኩልነት ተስፋን የሚያቀጭጩ ሰዎችን እያየሁ መብሰለሰኬና መቃጠሌ ነው።

ከመጠን በላይ የሚያመኝ ግን እነዚህ ሰዎች ተራ የአንድነት ሀይሎች አባላት ወይም ደጋፊዎች ሳይሆኑ ትግሉን እንመራለን የሚሉ ሰዎች በራሳቸው ትግሉን ለማጥፋት ሲጥሩ ሳይ እነዚህ ሰዎች እያሉ እኔ ለሀገሬ አንድነት መታገሌ ፋይዳቢስነቱ ይጎላብኛል።

ይሄን ነገር ለረጅም ጊዜያት በውስጤ አምቄ የትግል ጉዟችንን ላለመጉዳት እያልኩ ብዙ ነገሮችን ሳላጋልጥ ቆይቻለሁ። አሁን ግን በቃኝ! ሳይደፈርስ አይጠራም! እዚሁ እኔ ያለሁበትን ቤት አንድነት እያፈረሱና ፋይዳቢስ እያደረጉት እያየሁ ኣንዳች ነገር ካላደረግኩ ምኑ ነው የአንድነት ታጋይ የሚያስብለኝ?!

ከዛሬ ጀምሬ የእነዚህ እባቦችን ሙሉ አረመኔያዊ ተንኮሎቻቸውና ተግባሮቻቸውን የሚያጋልጡ ሚስጢሮችን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲያውቁት ለማድረግ ሙሉ መረጃዎችን በተከታታይ እንደምፅፍ ቃል እገባላችኋለሁ። በዚህ ፅሁፍ የምገልፅላችሁ ግን በዋናነት የአቶ ነአምን ዘለቀን ተግባራት የሚመለከት ነው።

ጉዳዩ ወዲህ ነው።

የኤርትራ መንግስት በጥር 21/2013 በሀገሩ ውስጥ አብዛኞቹ ሙስሊም የሆኑ ከፍተኛ ወታደራዊና ሲቪል አመራሮች የተሳተፉበትና ከመፍረስ አፋፍ ላይ ያደረሰው የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ አጋጠመው። ሙከራው ለምን ከሸፈ፣ በማን እና ለምን የሚሉ ጥያቄዎችን ለጊዜው ልተወውና ክስተቱ የፈጠረው አንድ መሰረታዊ ለውጥ ግን ተፈጥሯል፡፡

በሙከራው ተነቃቅተው በተለይ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ ኤርትራውያን ዳያስፖራ ወጣቶች የሚያደርጉት ተቃውሞ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነትና ጥንካሬ ወደ አዲስ ምእራፍ ተሸጋገረ። በኤርትራ መንግስት ላይ ተጨማሪ ማእቀብ እንዲጣልና የሰው ዘር በማጥፋት ወንጀል እስኪከሰስ ድረስ ጫና መፍጠር ቻሉ።

ይሄን ልብ ያለው የኤርትራ መንግስት ከተፅዕኖው ለመውጣት ከዘረጋቸው ብዙ ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ’ና ዋናው፡ የኢትዮዽያ አንድነት ሀይሎችን ከራሱ መዋቅሮች ጋር በማስተሳሰር በመሳርያነት መጠቀም እንዳለበት መወሰኑ ነው። መጀመርያ አቶ የማነ ገብረአብ ለአርበኞች ግንቦት 7 “እኛ’ና እናንተ አብረን እንስራ” የሚሉ ውትወታዎች ሲያደርግ በአርበኞች ግንቦት 7 ውስጥ ብዙ ክርክሮች ተደርገዋል። መጨረሻ ላይ ግን ድርጅቱ በከፍተኛ ደስታ ነበር የተቀበለው፤ ቢያንስ ኢህአዴግን ለማዳከም የሚያግዘን ብቸኛ አማራጭ ነው ብሎ ነበር የገባበት።

ይበልጥ እየተቀራረቡ ሲሄዱ ግን በተግባር የሚታየው ሌላ ነው። የኤርትራ መንግስት የያዘው ድብቅ ስትራቴጂ ገና ከመነሻው አንድነት ሀይሎችን ተጠቅሞ ተፅዕኖዎቹን ለመከላከል እንጂ የጋራ ትብብርን ፈልጎ ስላልነበረ። የስትራቴጂው ዋነኛ ይዘት እንደሚከተለው ነው።

ፕረዝዳንት ኢሳያስ አጀንዳ እየመረጠ ይቀርፃል፤ በእነ የማነ ገብረአብ አማካኝነት ለበሰሜን አሜሪካ’ና በአውሮፓ የህግደፍ አመራሮች ለሆኑት ለእነ ሶፍያ ተስፋማርያም ትእዛዝ ያስተላልፋል፤ በሶፍያ ተስፋማርያም ስርም እነ ጌዴዎን አባይ አስመሮም፣ አማኒኤል በእደማርያም፣ ዳዊት ሀይሌ፣ ሀድነት ቀለታ እና ሌሎች የህግደፍ የዳያስፖራ መዋቅሩ ቀንደኛ አንቀሳቃሾች ትእዛዙን ከየማነ ገብረአብ ይቀበላሉ፤ እነዚህ በበኩላቸው ከነአምንና በነአምን ስር ካሉ ሰዎች ጋር ይነጋገራሉ።

የተነጋገሩበት ጉዳይ ውጤት አንድም ሳይቀር በቀጥታ ለኢሳያስ ይላካል፤ ኢሳያስ ውሳኔ ይሰጥበትና በውሳኔው መሰረት እነ ነአምን እና እነ ሶፍያ ተስፋማርያም ይተገብሩታል። በዚህ ስትራቴጂ ማእቀፍ ውስጥ የሚገኙ ህሊናቸውንና ሆዳቸውን ሸጠው እራሳቸውን ለባርነት ያዘጋጁ የሀገሬ ሰዎች ናቸው እንግዲህ ሻዕብያ የውሸት ስም እያለበሰ ሀገር ወዳድ ኢትዮዽያንን ወደ አፍራሽ ጥቅሙ የሚቀይርበት ታክቲክ የነደፈው። በአርበኞች ግንቦት 7 ውስጥ የአቶ ነአምን ዘለቀን ዲፓርትመንት ከኤርትራ መንግስት አቅሞች ጋር ተሳስሮ መስራት መልካም ነገር ነው፤ ፍፁም የኤርትራ መንግስት አስፈፃሚና ተገዢ መሆን ግን በታሪካችን የሌለ ለትውልድ የሚሸጋገር አደገኛ ስህተት ነው።

ይሄን አሳፋሪ ስራ የሚያውቁት በነአምን ዘለቀ ስር ያሉት አባላት እንደ እነ መሳይ ከበደ፣ ጌታቸው በጋሻው፣ ሉሊት መስፍን፣ ብሪታዊት ግርማዬ እና አበበ ገላው ያሉት የተወሰኑቱ ናቸው። ሌሎቹ ግን ይሄን አያውቁም። እንደነ እንግዱ ወልዴ፣ ዳኛቸው ተሾመ፣ ሙሉጌታ ውዱ፣ ሻ/ቃ ዳዊት ጊዮርጊስ፣ ሻውል በትሩ፣ ዘላለም ከበደ፣ ዶ.ር ዳዊት ሀይሌ፣ እና ሌሎች በአርበኞች ግንቦት 7 ላይ ተስፋ አለን የሚሉ የድሮ ሰዎች ይሄን ሀቅ አያውቁም፤ ሻዕብያን በጥሩ ሁኔታ እንደሚደግፋቸው እንጂ መጠቀሚያ እንዳደረጋቸው አያውቁም።

ይሄን የሚያረጋግጥ በቅርቡ የተከሰተ አንድ እውነታ ልንገራችሁ።

በቅርቡ “ነፃነት ቡልቶ” በሚል ስም ስለ ኢህአዴግ መንግስት ባለስልጣናት መከፋፈል፣ ስለ ኢህአዴግ መዳከም፣ ወዘተ የሚገልፅ ፅሁፍ በኤርትራ መንግስትና በአርበኞች ግንቦት 7 ቁጥጥር ስር ባሉ የዳያስፖራ ሚድያዎች ተለቆ ነበር። ይህ ፅሁፍ ተራ ፅሁፍ አይደለም።

ኢህአዴግ በፅሁፉ ላይ በተገለፀው ደረጃ ቢከፋፈልና የኢትዮዽያ አንድነት ሀይሎች ቢጠናከሩ እሰዬው! የሚያሰኝ ነበር። ሆኖም ግን በትክክል የኢህአዴግን መከፋፈል እንደ እድል ለመጠቀምና የአንድነት ሀይሎች እንዲጠናከር የተዘጋጀ ፅሁፍ ሳይሆን እነ ነአምን ዘለቀ ለፕሬዚደንት ኢሳያስ በባርያነት እያገለገሉ መሆናቸውን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ፅሁፍ ነው።

“ነፃነት ቡልቶ” ነኝ ያለው ሰውዬ እውነት ነፃነት ቡልቶ ሳይሆን አቶ ነአምን ዘለቀ ነው። ባጭሩ ፅሁፉን የፃፈው አቶ ነአምን ዘለቀ ነው – ነፃነት ቡልቶ የሚባል ሰው አይደለም። “ነፃነት ቡልቶ” የሚባል ኮድ የተሰጠውም ነአምን እራሱ መርጦት ሳይሆን ሶፍያ ተስፋማርያም ነበር በአጭር ትእዛዝ “ይሄን ተጠቀም” ያለችው። እሱ ራሱ እንኳን የመደበቅያ ስሙን መምረጥ አይችልም።

ነፃነት ቡልቶም የሚለው ስያሜ የተሰጠበት ምክንያትም አንድም እነ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ ጉዳዩን አያውቁምና ጥያቄ እንዳያነሱ ወይም በመሀከላቸው ቅራኔ እንዳይነሳ ተብሎ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ግን “ከአማራም ከኦሮሞም ቃላት ያጣመረ ስም ያለው አንድ ኢትዮዽያዊ ፅፎታል” ተብሎ የአማራንና የኦሮሞን ወጣቶች ቀልብ ለመግዛት ነው የተፈለገው። አቶ ነአምን ዘለቀ ኢትዮዽያዊና ህዝባዊ ጥያቄዎችን ይዞ ህዝብን አንድ ለማድረግ አስቦ ቢፅፈው እሰየው፤ ጀግና በኢህአዴግ ላይ አንድ አእምሯዊ ውድቀት አስመዝግቧል ማለት እችል ነበር።

ነገሩ ግን ወዲህ ነው።

ነአምን ዘለቀ ፅሁፉን እንዲያዘጋጅ የኢሳያስ አፈወርቂ መተንፈሻ ጉሮሮ /ቱቦ/ የሆነው የማነ ገብረአብ ነበር ትእዛዝ የሰጠው። አቶ የማነ ገብረአብ “ወያኔ እርስ-በርስ እየተባላ ነው፤ በፓርቲውም ሆነ በመከላከያ ውስጥ ያሉት የህወሀት ባለስልጣናት በሙሉ እርስበርስ እየተናቆሩ መሆናቸውን የሚያሳይ አንድ ፅሁፍ ያዘጋጅና ለዚህም የኛን ማቴርያሎች መጠቀም ይችላል” ብሎ ለሶፍያ ተስፋማርያም ይነግራታል።

ሶፍያና የማነ በሚዘጋጀው ፅሁፍ ርእስ ላይ ተወያዩና ርዕሱን “The Crisis of Leadership inside TPLF” የሚል ስያሜ ነበር የሰጠችው። አቶ የማነ ግን “Loss of legitimacy of TPLF Minority Regime” የሚል ሀረግ መጨመር አለበት ብሎ በነገራት መሰረት “the Crisis of leadership and Legitimacy inside Ethiopia’s TPLF minority Regime” የሚል ርእስ እንዲሆን ተስማሙ።

በዚሁ መሰረት ሶፍያ ተስፋ ማርያም የፅሁፉ ርእስን ለነአምን ዘለቀ በነገረችው በሁለተኛው ሳምንት ነአምን ዘለቀ ፅሁፉን አዘጋጅቶ ለሪቪው ሰጣት። ኢሳያስ አፈወርቂ አይቶት ካፀደቀው በኋላ አቶ የማነም ለሁሉም የኤርትራና የአርበኞች ግንቦት 7 ጋዜጦች እንዲበተን ባስተላለፈው ትእዛዝ መሰረት ፅሁፉ ተበተነ። ከሚገርማችሁ ፅሁፉ ቀድሞ የተሰጠውና የለቀቀው ሚድያ “tesfa news” የሚባል የኤርትራ ድረገፅ ነው። ይሄውም እነ የማነ ገብረአብ ፅሁፉን ኤዲት አድርገው ሲጨርሱ ገና ለነአምን እንኳን ሳይሰጡ ነበር ለራሳቸው ሚድያዎች ያሰራጩት።

ልብ በሉ፡ ነአምን ዘለቀ ፅሁፍ እንዲያዘጋጅ ያዘዘው የማነ ገብረአብ ነው፤ “ነፃነት ቡልቶ” የሚል የኮድ ስም እንዲጠቀም ያዘዘችው ሶፍያ ተስፋማርያም ናት፤ የፅሁፉን ርዕስ የመረጡት የማነ እና ሶፍያ ናቸው፤ ፅሁፉን ኤዲት ያደረጉትም እነሱ ናቸው፤ ፅሁፉም የተለቀቀው በኤርትራ እና በአርበኞች ግንቦት 7 በሁሉም የፅሁፍ ሚድያዎች ነበር።

አርበኞች ግንቦት 7 ፅሁፍ ሊያወጣ ከሆነ በራሱ እምነትና ውሳኔ ሳይሆን እነ ኢሳያስ አፈወርቂ’ና አቶ የማነ ገብረአብ ሲፈልጉ ብቻ ነው። በአጭሩ የነአምንና የግንቦት 7 አባላት የውጪ እንቅስቃሴዎችን የሚመራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስና ኢሳያስ አፈወርቂ ብቻ መሆኑን ላረጋግጥ እወዳለሁ።

እነ አቶ የማነ ገብረአብ እና እነ ሶፍያ ተስፋማርያም ነአምንን በዚህ መልኩ በመቆጣጠር በፈለጉት መንገድ ትእዛዝ አስተላልፈው ሲያስፈፅሙ የድርጅቱ ሊቀ-መንበር ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የሚያውቁት ነገር የለም። ፕሮፌሰር ብርሀኑ ነጋ የኢሳትም ሆነ የነአምን ዘለቀ የውጪ እንቅስቃሴዎችን ማየት፣ መገምገምና መከታተል ብሎም የእንቅስቃሴዎቻቸው ሪፖርት ሊደርሳቸው ይገባል። ሆኖም ይሄ ፅሁፍ ሲዘጋጅ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው የኢሳያስ ትእዛዞች በቀጥታ በየማነ’ና በሶፍያ በኩል ለነአምን እየተላለፉ ፕሮፌሰሩ ምንም እውቅና ሳይሰጧቸው ናቸው የሚተገበሩት።

እኔ አንዳንዴ አቶ ነአምን ይሄን ሁሉ ተቀብሎ በአንድነት ሀይሎች ስር ነኝ ብሎ ሲንቀሳቀስ ኢትዮጵያዊ ነው ወይስ ኤርትራዊ? የሚል ጥያቄ ነው የሚመላለስብኝ። ይሄ በአጠቃላይ የአንድነት ሀይሎች ላይ የተደቀነ አደጋ ነው። የኢትዮጵያ አንድነት ሀይሎች እንዴት የሻዕብያ መንግስት ቁጭ ብድግ ሊያሰራን ይችላል! እንዴት በራሱ ሳምባ እንተነፍሳለን! የራሳችን ህልውና እና አቋም ሊኖረን አይችልም!?

እኔ እስከማውቀው ድረስ የአርበኞች ግንቦት 7 አላማ አንድ’ና አንድ ነው፡ ኢህአዴግን ታግሎ በመጣል ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በመትከል አንድነቷን ማረጋገጥ ነው። እነ አቶ ኢሳያስና አቶ የማነ ይሄን አይቀበሉም ማለት ነው?

የኤርትራ መንግስት እስከ አሁን ነአምን ዘለቀን ብቻ ሳይሆን ተስፋዬ ገብረአብንና መሰሎቹን በመጠቀም ኢትዮዽያ ውስጥ ምን ለመፍጠር ሲጥር እንደቆየ ሁላችን የምናውቀው ሀቅ ነው። ተስፋዬ ገብረአብ በኢህአዴግ ላይ አነጣጥሮ ቢታገል ኖሮ እኔ ኤርትራዊነቱም ትዝ አይለኝም ነበር! ነገር ግን ይህ ሰውዬ ሀገሬን ለመበተል ሲታትር የኖረ ሰው መሆኑ እኔ ሳልሆን ስራዎቹ በራሳቸው ግልፅ ምስክሮች ናቸው።

ከዚህ በፊት ወጣት አለማየሁ መሰለ እና ወልደሚኪኤል መሸሻ የተባሉ ሁለት ኢትዮዽያዊነታቸው አላስችል ያላቸው ሁለት ጀግኖች ወንድሞቼ ይሄን ሰውዬ ተከታትለው በሚገባ ማጋለጣቸውን ታስታውሱት ይሆናል። እንግዲህ ከተራ መታወቂያ ወረቀት ጀምሮ እስከ መኖርያና መተዳደርያ ወጪዎች የሚሸፍንለት የኤርትራ መንግስት ነው፤ በሚፅፋቸው ፅሁፎች በሙሉ ኤዲተሮቹ የማነ እና ኢሳያስ ናቸው፤ ፅሁፎቹ ስለምን እንደሚሰብኩ እናውቃለን።

ይሄን የሚያደርጉ የኤርትራ መሪዎች ናቸው አቶ ነአምን ዘለቀን መጮህ በማይችልበት የህልም ሲቃይ ውስጥ በማሰር ሌላው ንፁህና ምንም የማያውቀው ገንዘቡን እያዋጣ፣ እውቀቱን እየሰጠ ለሀገሩ የሚቃጠል ኢትዮዽያዊውን ወደ አፍራሽ ጥቅሙ ለማዋል የሚሰራው። በነገራችን ላይ ተስፋዬ ገብረአብን የሚመለከቱ ሰምታችሁዋቸው የማታውቁ ጉዶችን በቅርቡ እንደምለቅ ልገልፅላችሁ እወዳለው።

የአቶ ነአምን ዘለቀ ቅሌትና ውርዴት ይሄ ብቻ አይደለም። በቅርቡ በተከበረው የኤርትራ 26ኛው የነፃነት በዓል ላይ ኢሳያስ አፈወርቂ’ና ሌሎች የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቁጭ ብለው በሚመለከቱበት አስመራ ስታድዮም ውስጥ የሀገራችንን ሰንደቅ ዓላማ ረግጠው ሲጨፍሩና ሲጨበጨብላቸው፤ ባለስልጣናቱም ፊታቸው በርቶ እየሳቁና እየተሳለቁ ነበር የዋሉት።

የኤርትራ መሪዎች ባንዲራችንን የረገጡት ዛሬ ብቻ አይደለም! ትግረኛቸውን ስለማንሰማው እንጂ ምን ጊዜም ኤሪ-ቲቪን ብትመለከቱ‘ኮ ድራማም ሲሰሩ፣ ፊልምም ሲሰሩ፣ ንግግርም ሲያደርጉ፣ ወዘተ ሁልጊዜ ሻዕብያ ባንዲራችንን እንደረገጠና እንዳቃጠለ ነው። ቋንቋውን በደንብ መስማት ብንችል ኖሮ በአይናችን ከምናየው የባንዲራችን መረገጥና መዋረድ የማይተናነስ ስሜት ቆስቋሽ ዘለፋዎች እንደሚኖሩበት ምንም ጥርጥር የለብኝም።

በጣም የገረመኝና ያስደነገጠኝ ጉዳይ ግን አቶ ነአምን ዘለቀ በዚህ ባንዲራችን በተረገጠበትና ሀገራችን በተዋረደችበት በዓል ላይ ለመገኘት ያላደረገው ጥረት አልነበረም! ይባስ ብሎ “በሀገር ውስጥ እንኳን ባይሳካልኝ አሜሪካ ውስጥ በምታዘጋጁት በዓል ላይ መገኘት አለብኝ ብሎ” ለሶፍያ ተስፋ ማርያም ብዙ ጊዜ ጨቅጭቋታል። ሶፍያም ጉዳዩን አንስታ ከየማነ ገብረአብ ጋር ተነጋገረችና የማነ ገብረአብ “ነአምን ሌላ ስራ ተሰጥቶት እየሰራ ስለሆነ በበዓሉ ሊገኝ አይችልም!” የሚል መልስ ሰጣት። ቀጥሎም የማነ “ከኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ውይይት ታደርጋለህ” የሚል ትእዛዝ ለነአምን አስተላለፈለት።

ሶፍያ ተስፋማርያም ይሄን ስታውቅ ለነአምን “እንደውም በVIP ቲኬት ነው የምትጋበዘው፤ ሁሉም ነገር ተዘጋጅቶልሀል! ና’ና ተሳተፍ” አለችው። እንግዲህ ነአምን ሌላ ስራ መሰጠቱንና አምኖበት እየሰራ መሆኑን የሚያውቅ ቢሆን በዚሁ ሰዓት “ሊያመልጠኝ አይገባም! በዓሉን ልቀላቀል” ብሎ ለሶፍያም ሆነ ለሌሎቹ ባልወተወታቸው ነበር።

ልብ በሉ! ሁለቱም ሆን ብለው አቶ ነአምንን ከመጤፍ ሳይቆጥሩ እንደ አሻንጉሊት ሲጫወቱበት የማነ ገብረአብ በበዓሉ ወቅት መርጦ “ከኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ጋር ውይይት ታደርጋለህ” የሚል ትእዛዝ አስተላለፈለት፤ ሶፍያ በበኩልዋ “በVIP ቲኬት ነው የምንጠራህ” ብላ ተሳለቀችበት። ትክክለኛው የአርበኞች ግንቦት7 አቋም’ኮ “ኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ለአንድነት ቅርብ አይደሉም፤ ከኛ ይልቅ ከኦነግ ጋር ይገናኛሉ፤ በመሆኑም ቅድምያ መስጠት ያለብን በአንድነት ለሚያምኑ ሌሎች ድርጅቶች ነው” የሚል ነው። ሆኖም የማነ ገብረአብ ስለፈለገ ብቻ “ታደርገዋለህ!” ተብሎ ለነአምን ዘለቀ ትእዛዝ ተላለፈለት።

ይሄ ለኔ አሳፋሪ ውርዴት ነው! ቀድሞውንም ይሄን ለማጋለጥ የተነሳሁት ኢትዮዽያዊነቴ የማይፈቅድልኝ የሰው ባርያነት ሊዋጥልኝ ስለማይችል ነው! አፄ ሀይለስላሴ እንኳን በዛ በጣልያኑ ጨካኝ አረመኔ ወረራ ሲያጋጥመን እንግሊዝ ሀገር ሲሄዱ ከነሙሉ ኩራታቸውና ሀገራዊ ክብራቸው ጋር ነው! ኢትዮዽያዊ ተሸንፎም ቢሆን ክብሩን በሚያዋርድና ማንነቱን በሚያራክስ መልኩ መኖርን ፍፁም አይቀበልም!

እቺ ሀገር’ኮ እነ ዘራይ ደረስ እና አብዲሳ አጋን የመሰሉ በጠላት መንጋጋ ውስጥ ሆነውም “ባንዴራችንን አናስነካም!” ብለው ህይወታቸውን የሰውባትና ባንዲራዋንም በመላው አውሮፓ ሳይቀር ያውለበለቡላት ምድር ነች! እቺ ሀገር በዚህ በማይረባ ልክስክስና ውርደተኛ ልትወከልና ስሟ ሊጠራ አይገባም የሚል ስሜቴ ገንፍሎ መቋቋም ባለመቻሌ ነው መፃፌ።

የቀደሙት አባቶቻችን በሀገራችን ስም ምለውና ቃል ኪዳን ገብተው የሻብያ የቅኝ አገዛዝ ጌቶችን /Colonial master/ን አዋርዷል፤ አቶ ነአምን ዘለቀ ግን የኢትዮዽያን ስም አንስቶ በተራ ማፍያ ቡድን ሲዋረድ በዚህ ምድር ከዚህ በላይ ምን ዝቅጠት አለ!

********************* 

ማስታወሻ (ከአዘጋጁ)፡- በዚህ ፅሁፍ ውስጥ “ወያኔ” የሚሉ ቃላትን “ኢህአዴግ” በሚል ቃል የተካን መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

Guest Author

more recommended stories