ሁላችን ሁላችንን እናውቃለን?

(ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ)

ዓለምን ከመለወጣችን በፊት የአስተሳሰባችንን መንገድ መለወጥ ይገባናል ይላል ሩሴል ብራንድ፡፡ እስራኤላውያን ደግሞ አስደናቂውን የኢኮኖሚ ሽግግር ለማስገኘት ካስቻሉን ጉዳዮች አንዱና ዋነኛው ሁላችንም ሁላችንን ስለምናውቅ ነው ብለው ይመካሉ፡፡ በርግጥም የሲናን በረሃ ለማልማት ተመሳሳይ ቁርጠኝነት የተገኘው፤ ከሁሉም የዓለም ክፍሎች አይሁዳውያንን የማሰባሰብ መርሃ ግብሮች በሚገርም ፍጥነትና ይሁንታ መከናወኑ ሁላቸው ልብና ልቦቻቸው ስለሚተዋወቅ ይሆን? ያሰኛል፡፡

በርግጥ ህዝባዊ አብዮቶች ወደ ንቅናቄ ከመግባታቸው በፊት የህዝብን ልቡና ለመግዛት ቅድሚያ የሚሰጡት ከዚሁ እምነት በመነሳት ይሆናል፡፡ ርእዮቶች ህዝባዊ ይሁንታ ካላገኙና በዜጎች ተሳትፎ ካልተጠናከሩ ህልም ብቻ ሆነው ይቀራሉና፡፡

በተለይም የርእዮቶቹ ዋና አቀንቃኞችና የየአብዮቶቹ መሪዎችም እምነት የሚጣልባቸው ሲሆኑ፤ በሌላ አባባል የህዝብን ልቡና መግዛት ሲችሉ የትግላቸው ፍሬ አስደሳች ስለመሆኑ በአብዛኛው ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት አይሆንም፡፡ ዜጎች መሪዎቻቸውን መሪዎችም ዜጎቻቸውን የሚያውቁ ሲሆን ነገሩ እንደዛ ነው፡፡

ስለዚህ የሁሉም አብዮት መሪዎች ማሰብ ያለባቸው የህዝብን ቀልብ ስለመሳባቸው ብቻ ሳይሆን የህዝብን ልብ መግዛት ስለመቻላቸው፤ በህዝቦቻቸው ስለመታመናቸው ማረጋገጥ ይገባቸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ የገነቡት ስርዓት ድንገት ደራሽ እንዳገኘው ተፈረካክሶ መና ሊቀር ይችላልና፡፡

የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ በመሰረቱ በዓለም ታይቶ የማይታወቅና ለኛና ለኛ በኛ ብቻ እንደተፈበረከ ተደርጎ ሲነገር የነበረው ስህተት እንደሆነ አንዳንድ ጽሁፎች ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱም ዴሞክራሲን ለማስፈን ህዝባዊ ንቅናቄን/አብዮቶችን/ የማቀጣጠል አስተሳሰብ ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተተገበረ በመሆኑና በኋላም የፈረንሳይ ፤የሩሲያ፤ የቻይና፤የኮሪያናና የመሳሰሉት ሀገራት አብዮቶች የህዝባዊ ንቅናቄ ውጤት ከመሆናቸው አንፃር የአስተሳሰቡ መነሻ ግራ ዘመም የፖለቲካ አስተሳሰብ ሆኖ በሂደት ተለዋዋጭና ከሁሉም ጎራ ለህዝብ ጠቃሚ የሆኑ ርዕዮቶችን ቀነጫጭቦ የሚተገብር በመሆኑ ነው፡፡

ምንም ይባል ምንም ዴሞክራሲ፤ ልማትና ሰላም የርዕዮቱ ማጠንጠኛ እንደመሆናቸው መጠን በአብዛኛው የየሀገራቱን ዜጎች ፍላጎት የመኮርኮር አቅም ያለው አብዮትና በአግባቡ ሲመራም ውጤታማ እንደሚሆን በተግባር ታይቷል፡፡

በኛም ሁኔታ ቢሆን አንዳንዶች እንደሚሉት በዓለም ታይቶ የማይታወቅና ለጥፋት የሚዳርገን አብዮት ሳይሆን ይልቁንም በሀገራችንና ህዝባችን የተፈጥሮ ሁኔታ /ብዝሃነታችን/ ሲገመገም የተሻለ ጥቅም ሊያስገኝ የሚችል አብዮት እንደሆነ ይታመናል፡፡

ለዚህ ማሳያ ባለፉት ሁለት አስርታት የተገኘው አንፃራዊ ሰላም፤ የሁሉንም ዜጋ ህይወት የለወጠም ባይሆንየተገኘው ሀገራዊ እድገት፤ በፖለቲካው መስክ ሁሉም ህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ የጋራ ኢኮኖሚሚ መገንባት የሚችሉበትን እቅጣጫ ያሳየ እንደሆነ ምስክሩ መሬት ላይ ያለው እውነታ ነው፡፡ ፈተናው መስመሩ ያሳየው አቅጣጫ በዘዋሪዎቹ /ሁሉም ባይሆኑ በብልጣብልጦቹ/ ሲጠመዘዝ ማየታችን ነው፡፡

ዛሬ ዛሬን ከልማታዊነቱ ይልቅ ኪራይ ሰብሳቢነቱ አይሎ፤ በቁንጮ ዘዋሪዎቻችን መካከል ከመተማመንና ፍትሃዊ የህዝቦች ተጠቃሚነትን ከማስፈን እርስበርስ በጥርጣሬ ዓይን በመተያየት ህገመንግስቱንና ፌዴራላዊውን ስርዓት እንዲጣመም ለማድረግ ግብግቡ ሲጦፍ ከማየት የዘለለ እኛና ሁላችን ስለመተዋወቃችን የሚያስጠይቅ ሁኔታ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡

 እኔ ባለሁበት ኦሮሚያ ክልል ዜጎች እያንዳንዳቸው ህይወታቸው ተለውጦ ማየት ባይችሉም ባላቸው አቅም፤ የተፈጥሮ ሀብትና ጉልበት በአግባቡ ቢጠቀሙ ይህ ሊሆን እንደሚችል ከተረዱ ውለው አድረዋል፡፡ ይህ እንዳይሳካ እንቅፋት የሆነው ደግሞ ከራሱ አብራክና አድባር ወጥተናል የሚሉ ቁንጮዎች የፈጠሩት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡

እለት ተእለት በዚህ ታላቅ ህዝብ ሲምሉ የሚውሉቱ አለን የምንለው ሰፊ መሬትና ተፈጥሮ ሀብት በብልጣብልጦች ብቻ ሲዘረፍ፤ ሀገሬው ከቀዬው እንዲኮበልል ሲገፋና የቋጠሩለትን ስንቅ ከመንገድ ጨርሶ /አጠቃቀሙንም ባለማወቅ ጭምር/ ከርታታና ፈላሽ ሲሆን፤ የመሬት ቅርምቱን ዳር ቆሞ እንዲመለከት ያስገደደው የኢኮኖሚ አቅም አንጀቱን ሲያሳርረው አንድ እርምጃ መውሰድ ቀርቶ ድምጽ ያለማሰማታቸው አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ሌላ ሌላውማ ስንቱ ይነገራል!

የገዛ መሬቱን ለማልማት በሚል ሰበብ ህጉ በሚፈቅደው አግባብ በዝግ የባንክ ሂሳብ ሰባራ ሳንቲም ሳያስገቡ ሞግዚቶቹ ባስተላለፉት ትእዛዝ መሬት እንዲወስዱ ሲደረግ፤ መውሰዳቸው ባልከፋ አየር በዓየር ሽጠው ሚሊዮኖችን በአንድ ጀንበር ሲዝቁ ከዛችው ፍርፋሪ የሚለቅሙቱ የኛ ዘዋሪዎች ነገሩን ጆሮ ዳባ ማለታቸው ትክን ያደርጋል፡፡

ለመሆኑ ከኛስ ወጥተው ይሆን? ልባቸውና ልባችንስ ይተዋወቅ ይሆን? ብሎ ዜጋ ቢጠይቅ ከዚህም ተነስቶ ጥላቻ ቢያድርበት፤ ከጥላቻም ባሻገር እጁን በገዛ ራሱ ላይ እንዲያነሳ ስሜቱ ቢገፋው የሚኮነን አይመስለኝም፡፡ በርግጥ እንደሰው ስሜትን በመግዛት ሀገር እንደሚሰራ ያለማወቅ ህልኒ ንቃት ደሃ መሆኑ አግባብ ባይሆንም፡፡

ታዲያ እኒህ ዘራፊዎች ከዚህም ባሻገር በወሰዱት መሬት ስም ስሙ ኢንቨስትመንት ነውና ብረቱን፤ ቆርቆሮውን፤ ማሽኑን፤ ምናምኑን ሁሉ ከቀረጥ ነፃ ወደሀገር ያስገቡና መርካቶ ወስደው ችብችብ ያደርጉታል፡፡ ይህንን የሚያውቁ ቁንጮዎቻችን አሁንም ዝም፡፡

በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ ከደሀው ገበሬ የተውጣጡና በላባቸው ሊያልፍላቸው የሚታትሩት ነጋዴዎች ደግሞ በነፃ ወደ ሀገር ገብቶ መርካቶ ከሚቸበቸብ ምርት ጋር መወዳደር ያቅታቸውና ከመንገታገት አልፈው በራቸውን የቆለፉ ቤት ይቁጠራቸው፡፡ አቤት ቢሉስ ወዴት? ቱባዎቹማ ከመርካቶው ትርፍ ተካፍለው እንዴት ይተንፍሱት?

የዘመቻው አካላት ብዛታቸው አይነገርም፡፡ መንግስትና ህዝብ የጋራ ችግሮችን ለመቅረፍ ብለው በጨረታ ከሚያቀርቡት የፕሮጀክት ግንባታም በስመ ኮንትራክተር የወረቀት ጋጋታ ይዘው ይሰለፉና ንጹሀኑ ከሚያቀርቡት የገበያ ዋጋ በጣም ያነሰ ዋጋ በማቅረብ እንዲያሸንፉ ሲደረገ አሁንም ባለስልጣኖቻችን ሰነዶቹን አይተው ያጸድቁታል፡፡

ከየት አምጥቶ በዚህ ሰፊ ልዩነት ሊገነባልን ነው ብለቅ መጠየቅ አይፈቅዱም፡፡ ማታ የሚላክላቸውን ጥቂት እሽግ ብር ለመቃረም እየቋመጡ የትውልድን ራእይ ይቸበችቡታል፡፡ እነዚህ ኮንትራክተር ተብዬዎች ወትሮም ዓላማ ዓላቸው፡፡ የግንባታ ማስጀመሪያ ከ20-30 በመቶ ድርሻ ኪሳቸው ይከቱና ደብዛቸው ይጠፋል፡፡ በዚህም ሌላው ሲለወጥ እያየ  የማይለወጥ ባለበት ተጓዥ ማህበረሰብ የመፍጠር ዓላማቸውን ያሳኩታል፡፡

ትልልቅ የውጭ ባለሀብቶች ሲመጡ ገንዘቡን ከየት እንደሚያመጡት ያለመታወቁ ሳያንስ ሼር ይገቡና ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሼራቸውን መሸጥ፤ የውጭ ኢንቨስተሮቹ ብቻቸውን መቀጠል ሲያቅታቸው ንብረቱን ለባንክና ለመንግስት ጥለው እብስ ይላሉ፡፡ ይሄኔ የኔው ከርታታ ዜጋ ሜዳ ላይ ይፈሳል፡፡ ያችኑ ጉልበቱን እየተበዘበዘ የሚያገኛትን ቁራሽ እንዲያጣ ሆን ተብሎ ይደረጋል፡፡ እንግዲህ ይህን ሁሉ ደባ የሚፈጽሙት አካላት በእብዮታዊና ልማታዊ እንዲሁም ፌዴራላዊስርዓት ከለላ ስር ሆነው ነው፡፡

የስርዓቱ አካላት አንድም ድርጊቱ ፈፃሚና አስፈፃሚ በግላጭ ዘመዶቻቸው፤ የጥቅም አካፋዮቻቸውና የድብቅ ዓላማቸው አራማጆች መሆናቸው ገሀድ እየወጣ መጣ፡፡ ልብ ያለውና ሀይ የሚል ቁንጮ በጠፋበት ሀገር ህዝባዊ ስሜት ፈንቅሎ ቢወጣ ምን ይገርማል ጎበዝ?

ለመሆኑ እንዲህ የሆነው በኛና በኛው መሀል መሆኑስ እኛና እኛ እንተዋወቅ ይሆን አያሰኝም? በሌላ በኩል ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ ከራስ የጀመረ አመራር ድንገት ሲገኝ ደግሞ ህዝብ ከዐይን ያትርፍህ፤ ትንሽ እድሜ በሰጠህና የአንጀቴን ትኩት ባበረድክልኝ ሲለው ሰማን ተመለከትን፡፡

የአኮኖሚ አብዮቱ መቀጣጠሉ ሳይሆን ህዝብ እየታዘበ አንጀቱ ሲያር የኖረበት ጉድ ከየጓዳው ሲጎለጎል በማየጡ ብቻ እልታው ምድሪቱን ሞላት፡፡ ትናንት አራምባና ቆቦ የነበረው የአመራሩና የህዝብ ልብ እነሆ መተዋወቅ አብሮም መድመቅጀመረ፡፡ እንግዲህ ያዝልቅልንማ!! በቀጣዩ ፅሁፍ ለመሆኑ ሁላችን የአንድ ሀገር ብዝሀነቶችስ ሁላችንን እናውቅ እንደሆነለማጤን ተዘጋጅቻለሁ፡፡ ቸር እንክረም፡፡

********

Guest Author

more recommended stories