የማንነት ተቋማትን በማፍረስ የሚገነባ ሀገራዊ አንድነት አይኖርም

(ኤቢሳ ከጨፌ ዶንሳ)

ሀገራችን ባላት ልዩና ህብረ ብሔራዊ አፈጣጠር ዓለምን ያስደመመ የመቻቻልና የአብሮነት ብህል ባዳበሩ ህዝቦች ተሞልታለች፡፡ በደስታቸው ቀን ብቻ ሳይሆን በሰቆቃ ዘመን ሳይቀር የጎዳቸውን አካል ለይተው በመታገል የርስ በርስ መከባበርና የመፈቃቀድ እሴቶቻቸውን ሳይለቁ ዘመናት የተሻገሩ ህዝቦች መሆናቸውም ጭምር ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡

መቼም ህዝብ በህዝብ ላይ ተነስቶ የማንነት ተቋማትን፤ባህላዊ እሴቶችን፤ የተለዩ ህዝባዊ መስህቦችን የማዳከምና የማጥፋት ሴራ የጎነጎነበት ዘመን ጨርሶ በኢትዮጵያ ታሪክ አይታወቅም፡፡

ይልቁንም ለሁሉም ባህሎችና እምነቶች ያለውን አኩል ክብር ባገኛቸው አጋጣሚዎች ሲገልጽ፤ በወራሪ ጠላት ላይ በጋራ ሲዘምት፤ በትግል ሜዳዎችም ያገኘውን በጋራ ሲመገብና ሲደጋገፍ ኖረ እንጂ መለያየት ታየበት የሚል አንድም ታሪክ ሰምተን 
አናውቅም፡፡ የዛሬውን ፌዴራላዊ አብሮነት፤ መፈቃቀድና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አኗኗር አጥብቆ የሚሻውም ከዚህ መነሻ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ በዚህ ሀገር ያልደረሰበት ጫፍ የለም፡፡ በደረሰበት ሁሉ የሚያገኛቸውን ወንድም ህዝቦች ከራሱ ባህልና እምነት ጋር ከማዋደዱም ባሻገር ማንነቱን ያለምንም መሰሰት የሚያካፍል፤ ከታላቁ ገዳ ስርዓት ክፍሎች ሁሉ ቤት ለእንግዳ በማለት የመቀበል ብቻ ሳይሆን ባለቤትነትን በገዛ ፈቃዱ እንዲጎናፀፍ የሚያደርግ ህዝብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የሌሎች ህዝቦች እምነትና ባህልንም ጭምር ከማክበርም ባሻገር ያለምንም ችግር ተቀብሎና አክብሮ ከራሱም ጋር አዋዶ የሚኖር ህዝብ እንደሆነ በገሀድ ይታወቃል፡፡ በመሰረቱ ይህ ራሱ እራሱን የቻለ የህብረ ብሔራዊነታችን ውበት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡

ታዲያ በአንድ የታሪክ አጋጣሚ ከሀገራቸን አንደኛው ክፍል የተነሳ የገዢ መደብ በሁሉም የሀገሪቱ ህዝቦች ላይ ያደረሰው ሰቆቃ ከፍተኛ ቢሆንም የኦሮሞ ህዝብ እንዲያጣ የተደረገው ማንነቱን ጭምር ነበር፡፡

በፈጣሪ የተለገሰውን ቋንቋ እንዳይናገርበት፤ አደባባይ እንዳይሰማና በዚህ ተፈጥሮው እንዲያፍር፤ ሊቀየር የማይችል ማንነቱን እንዲቀይር ሲገደድ የነበረ ህዝብ ነው፡፡ መራራውን የህዝብ ልጆች ተጋድሎ የፀነሰውም ይህ ጫናና ጭቆና እንደነበረ ይታወቃል፡፤ ቀዳሚው ጥያቄ የማንነት ጥያቄ ነበር፡፡

የዜጎቿን ማንነት የማታከብር ሀገር ለመፍጠር በተደረገ የገዢዎች መሳፍንታዊ አስተሳሰብ በርግጥም እንደዚህ ተገንብታ ረጅም ዘመን መሻገር የምትችል ሀገር እንደማትኖር ያሳየ እውነታችን ነው፡፡ እናም ህዝባችን በተበታተነ መልኩም ሆነ በተለያ ድርጅታዊ ማእከል ከተደራጀ በኋላም ህዝባችን የከፈለው ውድ መስዋእትነት ይህንን ማንነቱን ለማስከበር እንደነበረ ታሪክ ዘግቦታል፡፡

ለዴሞክራሲ ስርዓት መነሻ ሆነውን ታላቁን የገዳ ስርዓትና ተቋማቱን በማፍረስ ህዝብን ያሸማቀቀ ተግባራት በጠንካራ ክንዱ ለማስመለስ የተጋውና የተጋደለው ከማንነት መታፈን በላይ ምንም የሚያም ነገር እንደሌለ ለገዢ መደቦቹ በግልጽ መንገር ብቻ ሳይሆን ዳግም እናዳያንሰራሩ አድርጎ ለመቅበር ያስቻለም ሁኔታ ፈጥሯል፡፡

ሁሉም ህዝቦች የሰላ ጥያቄአቸው የነበረውን የማንነታቸው ጉዳይ ለሀገራዊ ግንባታ ሊውል በሚችልበት አስተማማኝ መሰረት ላይ ባቆሙበት፤ የጋራ ማህተማቸውን በህገመንግስታዊ ማዕቀፍ ባኖሩበት ሁኔታና ፍትሀዊ ተጠቃሚነታቸውን በዴሞክራሲያዊ እኩልነት የማስጠበቅ ተልእኮ አንግበው በፍጥነት መራመድ በጀመሩበት ያለፈው ሁለት አስርት ዓመት ጉዞ ስኬትን የተጎናፀፉትን ያህል ዳግም ላያንሰራራ ተቀበረ ብለን የደመደምነው ማንነትን የመድፈቅ አስተሳሰብ ውስጥ ወስጡን እየዳኸ ከኪራይ ሰብሳቢነት ካባ ጋር ተሞዳምዶ የክልላችን ህዝብ ጥያቄ ዳግም እንዲያነሳ፤ ለማንነቱ በግልጽ እንዲፋለምና ማንነትን ያላከበረ ሀገራዊ አንድነት መገንባት አይቻልም ሲል ድምፅ እንዲያሰማ የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

ዛሬ ፊንፊኔና ዙሪያዋ ባማሩ ህንፃዎችና መንገዶች ተውባ መታየቷ የእድገትም ምልክት ጭምር ነውና እሰየሁ በበረታን የሚል ስሜት እንደሚፈጥር ማንም ክርክር አይገጥምም፡፡ ነገር ግን ይህ እድገትና የግንባታዎቹ ፍጥነት፤ የመሬት ቅርምቱ፤ ነባሩን አርሶ አደር ያለምንም ርህራሄ የማፈናቀሉ ተግባር አንድ ትልቅ ነገር አበላሸና ወዴት ወዴት አሰኘ፡፡

የኦዳ ነቤዋ ምድር ገላን ጨፌ ቱማ ባህላዊ ማእከልነቷ ተገፎ ባጠቃላይ በጋራ መኖሪያ ቤቶችና የፋብሪካ መዓት እየተሞላች የዚህ ታላቅ የማንነታችን ተቋም አካላትና አባላት የሆኑ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ተነቅለው፤ ጥንት ኦሮሞ ከመደወላቡ ተነስቶ በኦዳ ነቤ የገዳ ሙዳ ስርዓቱን አከናውኖ ህግ ለማውጣትና ስርዓት ለመለፈፍ የሚገኛኝባት የገላን ጨፌ ቱማ ደብዝዛ እየጠፋሁ ወይስ እየለማሁ ብላ መጠየቅ ጀምራለች፡፡

ከሰበታ እስከ ለቡ ያለው የሙዳ ፉሪ የባህላዊ እሴት ምድር በዘመቻ መሬቱን በተቀራመቱ ባለሀብቶችና ቱባ ባለስልጣናት የመሬት ንግድ ጡዘት ቆሌ ርቆታል፡፡ የገፈርሳ ማዶው የአባቶቻችን ለም ምድርም እንደዚሁ፡፡ የኤካንና ጋራ ቦሎን ነገርማ ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ ቀበረ እንዲሉ ያለፈ ማንነቱን ተገፎ አለላችሁ፡፡

በዓለማችን ያደጉ ሀገራት ጥንታዊ ማንነታቸውንና ባህላዊ እሴቶቻቸውን በማሳደግ ከራሳቸው አልፈው የዓለም ሀብት ሲያደርጉት ይስተዋላል፡፡ ቲቤታውያን የባህል ህክምናቸውን የአለም የአስትሮ ሳይንስ የስበት ማእከል እንዲሆን ማድረግ በቻሉበት፤ ህንዶች ቤተ እምነቶቻቸውንና ባህላዊ

ታሪኮቻቸውን ዓለሙን እንዲያስገርም ማዳበር በቻሉበት፤ አሜሪካውያን የፈጠሯት ታላለቆች ዓላማን እያዳነቀች የአባቶች ሀገር አሜሪካ ብለው ቁንጮ ባደረጓት ሁኔታ ውስጥ ምነው የኦሮሞ ህዝብ ባህላዊ የማንነት ተቋማት መፍረስ አይገባቸውም ብለን ስንል የሚታመመው በዛሳ?

የሚገርመው ደግሞ እነዚህ በሂደት ከክልላችን ማእከል ፊንፊኔ እንዲጠፉ እየተደረጉ ያሉ የማንነት ተቋማዊ እሴቶች በስመ ኢንቨስትመንትና የባለሀብት ጋጋታ ለመሬት ንግድ፤ አቋራጭ ጥቅም በደላሎችና ዓላማዬ ብለው ይህንን መዳከም በሚሹ ኃይሎች ውስጥ ውስጡን በተደረገ ዘመቻ የተፈጠረ ነው፡፡

አንዳንዶቹማ በጀነራል እንቶኔ ወይም ሚኒስትር ዝምድና ስም መሬት ወስደው መሸጥ፤  የመንግስት ፕሮጀክቶችን ተወዳድረው በአነስተኛ ዋጋ በማሸነፍ የስራ ማስጀመሪያ የተወሰኑ ሚሊዮኖችን ቆንጥረው ፕሮጀክቱን አፉን አስከፍተውት እብስ፡፡

ካሳ ተሰጥቶት የተፈናቀለው አርሶ በሌ ታጥሮና ተቆፍረው የተቀመጠውን ይህን ማንነቱን እያየ እምባ መርጨት፡፡ ይህንን ፈር የሳተ ጉዳይ ማስተካከል የማንስ ኃላፊነት ሊሆን ይችላልና ነው እሪታው ጎበዝ?

አንድ ወዳጄ ጋር ስናወራ በዚሁ ክልላችን በደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ ከተማ ሪፈራል ሆስፒታል ለማስገንባት የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ የክልሉ ጤና ቢሮ ጨረታ ያወጣል፡፡ ጨረታውን ያሸነፈው ኮንትራክተር የእንቶኔ ጄኔራል የአክስት ልጅ ነኝ ብሎ ያስወራና ጨረታውን ከሌሎች ተጫራጮች በ 30 ሚሊዮን ብር አሳንሶ ማስገባት፡፡

እንግዲህ ተመልከቱ ከተጫራቾች 30 ሚሊዮን ብር አሳንሶ አቅርቦ ምን ሊፈጥር እንደሚችል፡፡ እነ ጤና ኃላፊዎቻችንም ጌቶቻቸው እንዳዘዙአቸው ያነሰ ዋጋ ባቀረበ በሚለው ህግ መሰረት ማስረከብ፡፡ ጨዋታው አለቀ፡፡ ግንባታውም አላለቀ፤ የሚጠይቀውም አልተገኘ፡፡ ሰውየው አሁን አሁንማ የአካባቢው ማህበረሰብ ፕሮጀክቱን ለማየት ወደዛ ሲጠጋ ኮማንድ ፖስት አስጠርቶ ያባርር ጀመረ አሉ፡፡

ነገሩ ወትሮውንም በክልሉ የሚሰሩ ፕሮጀክቶችን ሆን ብሎ ማዘግየት፤ ገንዘብ ዘርፎ ጥሎ መሄድ፤ ጥራቱ ያልተጠበቀ ግንባታ በማካሄድ የህዝብ ህልሞቹን ማፈራረስ ነዋ!!! ለዚህ ጉዳይ ሲባል የተደራጀ ኃይል በዴሞክራሲያዊት ሀገር እንዳለ ስትሰሙ ምንኛ ያማል መሰላችሁ፡፡ እነዚህን በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች ስትሔዱ ታገኙአቸዋላችሁ፡፡

ይህን አስተሳሰብ በመያዝ በፊንፊኔ ዙሪያ ሲዘመትም አንድም የአካባቢውን የኢኮኖሚ ስበት በተወሰኑ ቡድኖች እጅ ለዘለቄታው ማኖር፤ ከዚህም የቡድኑ አባላት የሆኑ ኪራይ ሰብሳቢ ባለስልጣናትና ደላሎቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ፤ ጎን ለጎንም የምድሪቱን ህዝባዊ ማንነት መግፈፍ፤ የማንነት ተቋማትን ደብዛቸውን ማጥፋትና ሌላ ቀለም መቀባት፤ ባህላዊ ታሪኮች ተደፍቀው እንዲጠፉ ነው ምስጢሩ፡፡

እነዚህ ሰዎች ይህንን ምስጢር ስታወጣ ሀገራዊ አንድነት፤ ፌዴራላዊ ስርዓት ተገፋ ብለው እሪታ ያሰማሉ፡፡ በመሰረቱ የማንነት ተቋማት በማፍረስ የምትገነባ አንድ ሀገር ፈፅሞ ልትኖር አትችልም፡፡

ትናንት መሳፍንቱ እንዲህ አድርገው የሰሯት ሀገር የመበተን አደጋ የሰላ ጫፍ ላይ የደረሰባት በተመሳሳይ የጅሎች አስተሳሰብ ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ የሚፈልጋት፤ የሚንከባከባትና እንድትኖርለት የሚመኛት ኢትዮጵያ ፍትሀዊ ተጠቃሚነቱን ያከበረችለት፤የኦሮሞ ህዝብን የማንነት መገለጫ ቁሳዊና መንፈሳዊ ማንነት ተቋማት አክብራ የጠበቀች፤ ለዚህም ዘብ የቆመችና በተመሳሳይ ለሁሉም ብሔር ብሐረሰቦችና ህዝቦች ያደረገች እንደሆነ ብቻ ነው!

***********

Guest Author

more recommended stories