የኢህአዴግ አመራር “የበላይነት” የሚባል የለም ብሎ ደምድሟል – ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል [+Video]

ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የትግራይ የበላይነት የሚባለው ስሞታ <<ምክንያቱ ፖለቲካዊ [ስለሆነ] ምላሹም ፖለቲካዊ ነው፡፡ ላልገባው በማብራራትሆን ብሎ የሚለውን ደግሞ በመግጠም መስተካከል ያለበት ነው፡፡… እንደ ኢህአዴግ “የበላይነት” የሚባል ነገር የለም ተብሎ ተደምድሟል፣ አለ ብሎ ሲያነሳ የነበረም ሳይቀር ማለት ነው፡፡ አንዳንዱ ሆን ብሎ ፖለቲካዊ አጀንዳ ስላለው አንዳንዱ የራሱን ድከመት ለመሸፈን አሻግሮ Divert ለማድረግ (externalization) ተብሎ የመጣ ጉዳይ ነው በሚል በግልፅ ነው የተደመደመው>> ብለዋል።

የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ሚኒስትር እና የህወሓት ም/ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ይህን አስተያየት የሰጡት ባለፈው ቅዳሜ በተለይ ከሆርን አፌርስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነው፡፡ ኢንተርኔት ተዘግቶ የነበረ በመሆኑ ቃለ-ምልልሱን ያትምነው ትላንት እና ዛሬ ነው።

ትላንት በሆርን እፌይርስ እንግሊዝኛ እና በሆርን እፌይርስ YouTube አካውንት ላይ ባወጣነው የቃለ-መጠይቁ ክፍል አንድ ላይ፤ የቴሌኮም አገልግሎት በመንግስት ሞኖፖል ስር  መሆን፣ የኢንተርኔት  መዘጋት፣ የገጠር ቴሌኮም ሽፋን እንዲሁም በመንግስት ስራ ላይ ሆነው ዶክትሬት ትምህርታቸውን ስለማጠናቀቃቸው ከሆርን አፌይርስ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በጥልቅ ተሃድሶ  ውይይቶች ላይ ስለቀረበው የትግራይ የበላይነት አጀንዳ ላቀረብነው ጥያቄ ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሰጡትን ማብራርያ እና ስለሶሻል ሚድያ የሰጡትን አስተያየት ደግሞ ዛሬ በሆርን እፌይርስ YouTube አካውንት ላይ ባወጣነው የቃለ-መጠይቁ ክፍል ሁለት ላይ ተካትቷል።

ከዚያ መካከል፤ በጥልቅ ተሃድሶና ‹‹የትግራይ በላይነት›› ስሞታ ጋር በተያያዘ የሰጡትን መልሶች ጭማቂ በጽሑፍ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

(ይህ ጭማቂ እንጂ እንደወረደ የተፃፈ አይደለም)

ሆርን አፌይርስ፡- ባለፈው ነሐሴ በሰጡት ፕሬስ ኮንፍረንስ ላይ “የብሔር የበላይነት” ስለሚባለው ስሞታ ሲያብራሩ፤  ስሞታው አንዳንዴ ከፈጠራ አሉባልታ አንዳንዴ ደግሞ ከperception የሚመነጭ መሆኑን ገልጸው ነበር። ያንን ለማረቅ የሚሰሩ ስራዎች እንደሚኖሩም ጠቁመው ነበር። አሁን በምልሰት ስናየው “የትግራይ የበላይነት” የሚለውን ስሞታ ለማረቅ የተያዘው ስትራቴጂ የትግራይ የልማት ፕሮጀክቶችን ማጠፍ ነው ወይ የሚል ጥርጣሬ ፈጥሯል። ለምሳሌ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካ፣ የመቐለ-ሽረ ባቡር መስመር፣ የወልዲያ-መቐለ ባቡር መስመር፣ በኢፈርት ታቅደው የነበሩ የኬሚካልና የብረታብረት ፕሮጀክቶች የባንክ ብድር ማጣት፣ ወዘተ። አንድ በአንድ እየዘረዘሩ መልስ ላይሰጡባቸው ይችላሉ። ዋናው ነጥብ ግን የትግራይ የበላይነት የሚለውን ስሞታ ለማስታመም ሲባል የትግራይን ፕሮጀክቶች ማጠፍ እንደአቅጣጫ ተይዟል ወይ?

ዶ/ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፡- ወደዚያ ከመሄደህ በፊት “የትግራይ የበላይነት” የሚለው “ለምን?” የሚለው ነው መመለስ ያለበት፡፡ ምክንያቱን አውቀህ ነው ለዚያ መፍትሄ የምትሰጠው፡፡ ለጨጓራ በሽታ የኩላሊት መድሀኒት ሌላ በሽታ ያመጣል እንጂ ሊፈታ አይችልም፡፡ ትክክለኛውን ምንጩ ለይትህ በምንጩ ትሰራለህ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ “የበላይነት“ የሚባለው ከፕሮጀክቶች ጋር የተያያዘ ነው ወይ? ከሚገባው በላይ የተሰራ ስራ አለ ወይ ነው? ምክንያቱ እሱ ከሆነ ከሚገባው በላይ ፕሮጀክት በመንግስት የተሰራ ስራ ካለ “አዎ ይሄ ተገቢ አይደለም“ ብለህ ታስተካክለዋለህ ወደ መቀነስ ትሄዳለህ፡፡ ምንጩ እሱ ካለሆነ እሱ አይደለም መፍትሄ ማለት ነው፡፡ ወደ ፕሮጀክት አትሄድም፡፡ ወደ ዋናው ምንጩ ነው የምትሄደው፡፡

/የትግራይ የበላይነት/ የሚባለው አንዳንዱ ፐርሰፕሽን /የተዛባ አመለካከት/ ነው አንዳንዱ ደግሞ ፈጠራ ነው፤ የሌለን ነገር እንዳለ አድርጎ የማቅረብ ፈጠራ ነው፡፡ ለምን? ለሚለው ምክንያት አለው፡፡ /በኢህአዴግ/ አንዱ በደንብ የገምገምነው እሱን ነው ፤“የትግራይ የበላይነት“ የሚባል የለም ነው፡፡ የለም፡፡ ለምን? ሄደን ሄደን ስርእቱን እንየው ነው፡፡ ስርአቱ “የበላይነት“ እንዲኖር ይፈቅዳል ወይ? የምንፈቅድ አለን ወይ? የትግራይ ብቻ ሳይሆን የሌሎችም፡፡ ይሄ ስርአት ካልፈረሰ በስተቀር ሊኖር አይችልም፡፡ ይሄ ስርአት የትግራይንም የሌላንም የበላይነት አያስተናግድም፡፡

ከፌዴራል ጀምረህ የስርአቱን አወቃቀር ነው የምታየው፡፡ የበላይነት ዝም ብሎ ሊመጣ አይችልም እኮ ዝም ብሎ ሀሳብ ሊሆን አይችልም ፤ አወቃቀሩ የሚፈቅድ ከሆነ ነው ፣ ካልሆነ ያው ስሜት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ /አወቃቀሩ ካልፈቀደ/ “የበላይነት“ የሚፈልግም ካለ ስሜት ብቻ ፤ “የበላይነት አለ“ የሚልም የራሱ ግምት ብቻ ሆኖ ይቀራል፡፡ በተግባር ይህን የሚፈቅድ ስርአት የለንም፡፡ በህዝብ ተወካዮችም በፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በህዝብ ብዛት መጠን ነው የተወከለው፡፡ እንደ ብሄር እኩል ነን፡፡ ውክልና ግን በህዝብ ብዛት ነው የተኬደው፡፡ ስለዚህ አንዱን የበለጠ የሚጠቅም ነገር ይዘህ በድምፅ ሊያልፍ አይችልም ማለት ነው፡፡ በፖለቲካ ሃላፊነትም እኩልነት ነው የሚታየው፡፡ በኢህአዴግ ምክር ቤትም ሆነ ስራ አስፈፃሚ ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች እኩል ነው ውክልና ያላቸው፡፡ ለምሳሌ አንጋፋው ህወሓት ነው በሚል የተለየ ተጨማሪ ቁጥር አይሰጠውም፡፡ ብዙ ውሳኔ በሚወሰንበት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ከ36ቱ ከሁላችንም እኩል ዘጠኝ ነው የተወከለው፡፡ አብዛኛው ያልተስማማበት ስለማያልፍ ማንም ድርጅት ዘጠኝ ሰው ይዞ የበላይነት ሊያመጣ አይችልም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንኳን የፈለገውን ሁሉ ሊወስን አይችልም፡፡ /በህግ/ የተሰጠው ሃላፊነት አለ የተወሰነውን በራሱ ያስፈፅማል ሌላው ወይ በፓርቲ ወይ ከላይ ሆኖ በሚመራው መንግስት (ካቢኔ) የሚታይ ነው የሚሆነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆኑ ወይም የድርጅት ሊቀመንበር በመሆን እንዲወሰን ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል ውሳኔ ግን ሄዶ ሄዶ የጋራ ነው፡፡ ለምሳሌ በካቢኔ አሁን 30 ነን፡፡ ድሮም ዛሬም ህወሓት ሶስት ሚኒስትር ብቻ እኮ ነው ያለው፤ ሶስት ይዘህ ደግሞ እንዴት ነው የተለየ ልታስወስን የምትችለው?  ስለዚህ “የትግራይ የበላይነት“ ይቅርና አሁን መለስ እያለም አለ ሊባል አይችልም፡፡ ከህወሓት የመጣ ነው በሚል ብቻ “የበላይነት“ ልትል አትችልም፤ አብዛኛው ካልተቀበለው ጠቅላይ ሚኒስትር ስለሆነ ብቻ ሊወስን አይችልም፣ ይሄ ደግሞ ይታወቃል ታሪኮች አሉ፡፡

አንድ ሚኒስትርም ብቻውን ሊወስን አይችልም፡፡ ለምሳሌ እዚህ ቴሌኮም ስለምመራ ለብቻዬ ልወስን አልችልም፣ በጋራ ወስነን ነው ወደ ስራ የምንሄደው፡፡ ቴሌኮሙም መብራቱም ሌላውም ተደራሽነት በእኩልነት የህዝብ ብዛቱ የክልሉ ስፋት ወዘተ እየታየ በቀመር ነው፡፡ የገጠር ቴሌኮም ካልክ በሀገሪቱ ሁሉ ያለ ቀበሌ ወረዳ ማለት ነው፡፡ የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ፓርላማ ነው ያወጣው፡፡ ወደ ክልሎችም ስትሄድ ሁሉም ድርጅት የራሱን ነው የሚያስተዳድረው፡፡ ህወሓት ኦሮሚያን ወይም አማራ ክልልን ሊያስተዳድር አይችልም፡፡ ስርአቱ አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ በክልል የበላይነት የሚባለው የሌለ አምጥቶ የመለጠፍ ፈጠራ ነው፡፡ ስርእቱ በዚህ መሰረት አልተገነባም አይሰራም፡፡

ሌላው መሰረተ ልማት ነው፡፡ ፕሮጀክትም ከበጀት ነው፡፡ በጀት በቀመር ነው የሚሰራው፣ በህዝብ ብዛት ያለው አብላጫውን ይወስዳል፡፡ በዚያ መሰረት ትግራይ 5ኛ ላይ የምትገኘው፡፡ ክልሉ ያንን በብዛቱ መጠን ያገኛትን ይዞ ነው ስራ የሚሰራው፡፡ ፌዴራል የሚሰራቸው ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ የፌዴራል መንግስቱ በሁሉም ክልሎች አመጣጥኖ ነው የሚሰራው፡፡ ሄዶ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወሰነው፡፡ ለትግራይ የተለየ ነገር ይዞ ተኪዶ በየት በኩል ነው የሚፀድቀው? ሌላው ምን ይሰራል? የራሱን ጥቅም አሳልፎ አንዱ ብሄር ይጠቀም ብሎ የሚወስን ሰው ሊኖር አይችልም፡፡ እንደዚህ አይነት ጭፍን ህዝብ አይደለም፡፡ ሁሉም የየራሱን ፍላጎት ግን በእኩልነት እንዲሟላለት የሚፈልግ ነው፡፡ መቼም መሰረተ ልማት ደግሞ ሰርቀህ ልትሰራው አትችልም፡፡

ሆርን አፌይርስ፡- ግን እኮ አሁን ያለው ጥርጣሬ ምንድነው “የትግራይ የበላይነት እያሉ ሲያሳቅቋችሁ ከጭቅጭቁ በማለት፣ በይሉኝታ በመያዝ አንዳንድ ነገሮችን፣ fair የሆነውን ነገር ራሱ፣ እየተዋችሁ ነው” የሚል ነው።

ዶ/ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፡-  ገባኝ።፡ግን መነሻው እሱ ስላልሆነ ነው እኮ ያልኩህ፣ በዚያም እኛ ወደ ኋላ የምንልበት ምክንያት የለም፡፡ ምክንያቱ እሱ ስላልሆነ ያልኩህ ለዛ ነው፡፡ ስርአቱ አይፈቅድም፣ ስለዚህ ለምን ወደ ኋላ ትላለህ፡፡ የበላይነት የሚባል የለም ነው እያልን ያለነው፡፡ ፕሮጀክት ተጨማሪ ብትወስድ ኖሮ ትክክል ነው፣ ግን የለም፣ በየት አድርገህ፡፡ ስለዚህ ወደኋላ ልትል አትችልም፡፡ ማካካሻ ሊሆን አይችልም ይሄኛው፡፡

“የትግራይ የበላይነት አለ” የሚባለው መሰረቱ ሌላ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ነው፡፡ አንዱ ምክንያት ወደ ኋላ ታሪክ ተኪዶ ያለፈውን ስርአት በማፍረስ ላይ ህወሓት የተለየ ሚና ነበረው ከሚል ነው፡፡ ሁሉም የየራሱን ሚና የተጫወተ ቢሆንም ህወሓት በሂደቱም በመስዋእትነቱም ጎላ ያለ ሚና እንደነበረው ይታወቃል፡፡ ስለዚህ ከዚያ ተነስቶ ቅሬታ ያለው ወገን አለ፡፡ የቆየ ቅሬታ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ተደጋግመው የሚነሱት የመከላከያ የደህንነት ተቋማትም የሆኑትም ታሪኩ ከኋላ የተነሳ ነው፣ ከትግል የመጣና የገባ ሀይል አለ እዚያ፡፡ ያ እስካለ ድረስ ህዝብ እስካገለገለና ውጤታማ እስከሆነ ድረስ ሁሉንም ያገለግላል የአንድ ወገን ስራ አይደለም የሚሰራው፣ በሂደት ለማመጣጠንም የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ በሚመስሉ ነገሮች ላይ (በፐርሰፕሽን ችግር) ተመስርቶ የሚነሱትንም የስርአቱን አወቃቀርና አሰራር በማስረዳት ነው የሚፈታው፡፡

ሌላው ምክንያት ስርአቱን ለመቃወምና ለማፈረስ የሚፈልግ የፖለቲካ አጀንዳው ስለሚያደርገው ነው፡፡ በፊት (ትግራይ) ያልተሰራ ተሰራ እየተባለ አልነበረ እንዴ የሚወራው? የሚመስል ነገር ስታመጣ ደግሞ ስርአቱን ለማፈረስ ህዝቡን የበለጠ ለማንቀሳቀስ ስለሚመች ትጠቀምበታለህ ፤ ከወደቀ ደግሞ ሌላ አጀንዳ ትፈልጋለህ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ምክንያቱ ፖለቲካዊና ስርአቱን ለማፍረስ ለመጠቀም ወደ ዘር ቅስቀሳ የሄደ ነው ማለት ነው፡፡

ስለዚህ ምክንያቱ ፖለቲካዊ ከሆነ ምላሹም ፖለቲካዊ ነው፡፡ ላልገባው በማብራራት ሆን ብሎ የሚለውን ደግሞ በመግጠም መስተካከል ያለበት ነው፡፡ የሚነሱት በፕሮጀክት ላይ የሚነሱ አይደሉም፣ ወደ ፕሮጀክት አይሄድም፡፡

ሌሎቹ (ሳይሰሩ የዘገዩት) ፕሮጀክቶች ጉዳይ ከዚህ ጋር ምንም ግንኙነት የላቸውም፣ የየራሳቸው ምክንያቶች አላቸው፡፡ የባቡሩ ጉዳይም ተደጋግሞ ሲነሳ ሰምቸዋለሁ፡፡ አይሰራም አይደለም፡፡ ይሄ ከመቐለ ወደ ሽረ የሚሄደው በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን እቅድ ላይ ሊታይ ይችላል – ጥናት (ይደረግበታል) ብለን ነው የያዝነው፣ አሁንም ጥናት ነው፡፡ ስለመስራት አሁን ልናወራም እኮ አንችልም፡፡ እቅድ የያዝነው ለጥናት ነው፣ ክጥናት በኋላ ነው መስራት የሚመጣው፡፡ ስለዚህ አልተቀየረም፡፡ የተቀየረ ነገርም አሁን የለም፡፡ ገንዘቡ “ውድ ነው” “አነስተኛ ነው”… በኋላ ነው የሚታየው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ወደ ኋላ የተመለሰም ነገር የለም አሁንም ይቀጥላል፡፡

የወልድያ-መቐለውም ሌላውም በብድር ነው የምንሰራው፡፡ ሌሎችም ፕሮጀክቶችም አሉ የምንፈልገውን ብድር ያላገኘንባቸው፣ ትግራይ በመሆኑ አይደለም፡፡ ከትግራይ ምንም የማያገናኛቸው የኢነርጂ ፕሮጀከቶችም ላይ ብድር ያላገኘንባቸው አሉ፡፡ ስለዚህ ጥረት ነው ማድረግ አለብን ማለት ነው፣ በእቅድ አስቀምጠነዋል፣ እኛም ለመስራት ነው ጥረት እያደረግን ያለነው፡፡ አክችዋሊ የወልድያውም እየተሰራ ነው፣ በመንግስት ገንዘብም ቢሆን፣ የቆመ ነገር የለም፡፡ ግን የፈለግነውን ገንዘብ አላገኘንም ተጨማሪ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ ስለዚህ ይሄ ሀሳብ የመቀየር ነገር ሳይሆን ብድር የማግኘት ጉዳይ ነው፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳለብን ይታወቃል እኮ፡፡ ስለዚህ አገር አቀፍ ችግር ነው እንጂ የታጠፈ ነገር የለም፡፡ /ለበላይነት ክስ/ ማስታገሻ የሚባል ነገርም እንደሌለ ብንገነዘብ..

ሆርን አፌይርስ፡- በዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ በየመስሪያ ቤቱ በተደረጉ የጥልቅ ተሀድሶ ውይይቶች ላይ “የትግራይ የበላይነት አለ ወይ” የሚል አጀንዳ ነበር። በአጀንዳው ላይ በቂ በመረጃና ትንታኔ የተጠናቀረ ሰነድ ባልቀረበበት ሁኔታ  የተደረገ ውይይት ነው። ስለሆነምየውይይቱ ውጤት ለስሞታው legitmacy መስጠት ነው የሚል ግምገማ  አለኝ። ለምሳሌ የዚህ መሰረተ-ቢስ አስተሳሰብ ተግባራዊ መገለጫው ባለፈው ክረምት በትግራዮች ላይ የተፈጸሙትን በማሳያነት ሊቀርብና በዚያውም የሚወገዝበት ሊሆን ይችል ነበር። በተቃራኒው በቀጣይ ወራት ያየነው፤ የትግራይ ተወላጆች  “ባለፈው ክረምት ከኢሕአዴግ እህት ፓርቲዎች አንዱን ተቻችሁ” በሚል ማሸማቀቅ ነበር። በአጠቃላይ ሂደቱ ለጽንፈኞች መንግስታዊ ሽፋን የመስጠት ውጤት ነበረው የሚል ግምገማ አለ። በዚህ ላይ ምን ይላሉ?

ዶ/ደብረፅዮን ገብረሚካኤል፡- የጥልቅ ተሀድሶ ውይይቶች ሁሉም “የበላይነት አለ” እንዲል ተፈልጎ የመጣ አይደለም፡፡ በድርጅቶችም በመንግስትም አጠቃላይ ችግር አለ፣ ህዝብ የሚፈልገውን አገልግሎት እያገኘ አይደለም…ብዙ ቅሬታ አለ፣ የዚህ ቅሬታ ምንጭ በድርጅቱ ውስጥ ያለ አመራር ነው ራሱን ይፈትሽ በሚል ነው፡፡ በጥልቀት የተባለውም ለዚያ ነው እንጂ “የበላይነት” አይደለም ዋናው አጀንዳው፡፡ ግን ይፈተሽ ሲባል ቅድም ፖለቲካዊ ስራ ነው እንዳልኩት በሌለ ብዙ ይነሳ ነበርና ውይይት ያስፈልገዋል ማለት ነው፡፡ እንደዚህ ነው ይሄ ስርአት በሚል ለመወያየት..እንደዚያ ነው የተደረገው በየአካባቢው፡፡ ስለዚህ ውይይቱ የኪራይ ሰብሳቢነት፣ የመልካም አስተዳደር… በአጠቃላይ ጉድፎቻችንን እናራግፍ በሚል የተካሄደ ነው፡፡

በአንድ አጀንዳ ብቻ ልንመዝነው አይገባም፣ መራገፍ ከሚገባቸው አስተሳሰቦች አንዱ ስለሆነ ነው፡፡ እቺን ነጥዬ በሁሉም ደረጃ ውይይቶች እንዴት ነበሩ ብዬ ለማስቀመጥ አልችልም፤ የጎደለ ነገር እንዳለ ግን አውቃለሁ፡፡ እንደ አጠቃላይ የትምክህትና የጠባብነት አመለካከቶች ጋር በተያያዘ መራገፍ ያለባቸው አስተሳሰቦች አካል አድርገን ነው የምንወስደው፡፡ መገለጫዎቹ ብዙ ናቸው ይሄ አንዷ ናት፡፡ ስለዚህ ፍተሻው ላይ የተጓደለ አለ በዚህም ላይ ሊጎድል እንደሚችል መገመት አይከብድም፡፡ ቢሆንም ነገሮች ለውይይት መውጣቱ ሁሉም ያለውን ማውጣቱ ጥሩ ነው፡፡ አመለካከቶች የሚስተካከሉት በውይይት በመሆኑ መድረኩ መፈጠሩ በራሱ ጥሩ ነው፡፡

የመጀመሪያ መድረክ በመሆኑ የተጓደለ ነገር እንዳለ እናውቃለን ማለት ነው፡፡ “የበላይነት” የሚለው የሚደጋገምባቸው አካባቢዎችም ካሉ ይህንን ጨምሮ የተጓደሉ ነገሮች ላይ ተጨማሪ እንስራ ነው ያልነው፡፡ ዋናው ግን በአጠቃላ የተዛቡ እመለካከቶችን ማረም…ህዝብን ከማገልገል አንፃር ሁሉም ህዝብ ወገኔ ነው የሚል አተያይ…ከአተያይ ጀምሮ ብዙ የተበላሹ ነገሮች አሉና እሱ ሲስተካከል ይሄም አብሮ ይስተካከላል ብለን ነው የያዝነው፡፡ በሰቪል ሰርቫንቱ ብቻ ሳይሆን በድርጅቶቹ ውስጥም ራሱ በደንብ እንስራ ብለናል፡፡ ባለፈው ክረምት ከነበረው በጣም ተሻሽሏል፣ በቂ አይደለም ብለናል፡፡

አክችዋሊ እንደ ኢህአዴግ “የበላይነት” የሚባል ነገር የለም ተብሎ ተደምድሟል፣ አለ ብሎ ሲያነሳ የነበረም ሳይቀር ማለት ነው፡፡ ለምን? በውይይት እንፈትሸው ስለተባለ፡፡ እስቲ ይውጣ ከምን ተነስተን ነው አለ የተባለው በሚል ተነስቶ መልስ ተሰጥቶበታል፡፡ ስለዚህ እንደ ኢህአዴግ ይሄ አንዳንዱ ሆን ብሎ ፖለቲካዊ አጀንዳ ስላለው አንዳንዱ የራሱን ድከመት ለመሸፈን አሻግሮ Divert ለማድረግ (externalization) ተብሎ የመጣ ጉዳይ ነው በሚል በግልፅ ነው የተደመደመው፡፡

በከፍተኛ ደረጃ እንዲህ ቢሆንም ታች በሁሉም ቦታ እንደዛ እንዳልተደመደመ እናውቃለን፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክት ቀነሳ ሳይሆን ቀጣይ ስራ መስራት አለብን እንጂ በፕሮጀክት የሚገለፅ ቅነሳ በምንም አይነት አይታሰብም፤ እሱ ስላልሆነ መፍትሄው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሆነ ችግር ሲኖር ከዚያ ጋር የሚገናኝ አድርገንም መውሰድ የለብንም ስህተት ነው እላለሁ፡፡

********

Fetsum Berhane is an Ethiopian resident, economist researcher and a blogger on HornAffairs.

more recommended stories