የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ልዩ ጥቅምን አስመልክቶ የተዘጋጀ የጥናት ሰነድ

[የፌዴራልና የኦሮሚያ መንግስት ቃልአቀባዮች ይህንን ሰነድ በድፍኑ አናውቀውም በማለት ለማረጋገጥ ያልፈቀዱ ቢሆንም፤ በሰነዱ ላይ ካለው የአንባቢያን ፍላጎት አንጻር አትመነዋል።]

መጋቢት 2009 ዓ.ም. ፊንፊኔ/አዲስ አበባ

1/ መግቢያ

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ መንግስት አገሪቱ ፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓትን እንደምትከተል በመደንገጉ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ዲሞክራሲያዊ የፌደራል ስርዓት ለመገንባት የተደረጉት ጥረቶች አንድነትን በልዩነት ውስጥ ለመገንባት የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ካደረጓቸው ጥረቶችና ርብርቦሽ ጋር ተጣምሮ መታየት የሚገባው ታላቅ ታሪካዊ ጉዳይ ነው፡፡

ከሀይልና ጭቆና ውጪ ዲሞክራሲንም ሆነ ፌደራላዊ አስተዳደር ሥርዓትን በታሪኳ አይታ የማታውቅ ሀገር በሰላም፣ በዲሞክራሲ የጋራን ጉዳይ በትብብር፣ የግልን ጉዳይ በራስ ሙሉ በሙሉ የማስተዳደር መብትን የሚያጎናፅፍ፣ ለግልና ለቡድን መብቶች እውቅናና ጥበቃን የሚሰጥ ሕገመንግስት ቀርፃ ዴሞክራሲያዊ የፌደራል ሥርዓት በመገንባት በልማት ጎዳና መጓዝ ከጀመረች ሁለት አስርት ዓመታት መቆጠር ችለዋል፡፡

የዲሞክራሲ ባህልና ሥርዓት ግንባታ ሂደት እንጂ የአንድ ጀንበር ክንውን ባለመሆኑ በየጊዜው እየዳበረ የሚሄድ እንጂ ከማማው ጫፍ ደርሰናል፤ተደመደመ የሚባል አይደለም፤ በተለይም ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች በህገ መንግስት የሰፈረ መብታቸውን በዝርዝር ህግ ወደመሬት ለማውረድ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እየጎለበተ መምጣቱ የሚጠበቅ ነው፡፡

በመሆኑም በ1987 ዓ.ም በወጣው የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄራሰቦችና ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ዕውቅና ከመስጠቱም በላይ ጥበቃ አድርጓል፡፡ እነዚህ መብቶች እውቅናና ጥበቃ ከተደረገላቸው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄራሰቦችና ሕዝቦች መካከል የኦሮሞ ብሔር አንዱ ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔር የሚኖርበት ክልል በህገ መንግስቱ አንቀፅ 47(1)(4) የኦሮሚያ ክልል ተብሎ ከኢፌዲሪ ክልላዊ መንግስታት አባላት አንዱ ነው፡፡

በመሆኑም አንደኛ በታሪክም ፊንፊኔ/አዲስ አበባ የኦሮሞ መሬት አካል/እምብርት እና በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ፣ ሁለተኛ የፊንፊኔ/ አዲስ አበባ ነባሪ ነዋሪ ኦሮሞዎች የተመሰረተች ከተማ በመሆኗ እና ሶስተኛ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ ከተማ በመሆኗ ምክንያት የኦሮሞ ህዝብ እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከፊንፊኔ ላይ ያለው መብት መጠበቅ አስፋላጊ በመሆኑ በሕገ-መንግስቱ አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 “የኦሮሚያ ክልል፡ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፣ ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል” ይላል፡፡

 ይሁን እንጂ በሕገ መንግስቱ ሰፍሮ የሚገኘው የኦሮሚያ ክልል መብት ዝርዝር ሕግ እንዲወጣለት በተለያዩ ጊዜያት ጥረቶች ቢደረጉም እስከ አሁን ሳይወጣ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም አሁን ከደረስንበት ተጨባጭ ነባራዊ ሁኔታ እና የዕድገት ደረጃ ኦሮሚያ ከፊንፊኔ/አዲስ አበባ ልታገኝ የሚገባውን ልዩ ጥቅም በተመለከተ መብት በሕግ መመለስ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የግድ ሆኖ በመገኘቱ ይህ ህግ እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ስለዚህ የሕገ መንግስት ድንጋጌ በስራ ላይ ለማዋል ለሚዘጋጀው አዋጅ የአፈፃፀም ሂደቱ በጠንካራ መሰረት ላይ መቆም እንዲችል “የልዩ ጥቅምን” ሥረ-ነገር ከፊንፊኔ ታሪካዊ ዳራ በመነሳት በኦሮሞ ተወላጆችና በፊንፊኔ መካከል ካለው ሕያው ቁርኝት ጋር በማስተሳሰር፣ ልዩ ጥቅምን በሚመለከት በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ተደንግገው የነበሩትን በመተንተን እና ከተለያዩ የዓለም አገራት ተሞክሮዎች ጋር በማነፃፀር ዝርዝር የህግ ማዕቀፍ ለማዘጋጀት መነሻ እንዲሆን ይህ የጥናት ሰነድ ተዘጋጅቷል፡፡

 2/ የጥናት ሰነዱ ዓላማ

 2.1. የኦሮሞ ብሄር የሰፈረበት መልክአ ምድር አንድ አካልና እምብርት የሆነችው ፊንፊኔ ታሪካዊ አመሰራረት፣ ነባር ነዋሪዋንና የስሟ ወደ አዲስ አበባ እና የሌሎች ቦታዎች ስያሜዎች መቀየርና መዛባት ፖለቲካዊ ምክንያቶችና ይህም በሚኒሊክ የተስፋፊ ሥርዓት የደረሰውን ጭቆናና የተፈፀመውን ግፍ ለማስገንዘብ፣

 2.2. የኦሮሞ ህዝብና የኦሮሚያ ክልል ከፊንፊኔ/አዲስ አበባ ሊጠበቅለት የሚገባውን ልዩ ጥቅም ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ኢትዮጵያ ካፀደቃቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች፣ በፌዴራልና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በወጡ ህጎችና ከትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ አንፃር እንዴት መታየትና ልዩ ጥቅሞቹን ለመወሰን መነሻዎችን ለማቅረብ፣

 2.3. የፌዴራል ሥርዓት የሚከተሉ የተለያዩ ሀገራት በፌዴራል መቀመጫ ውስጥ የሚኖሩትን ነባር የአናሳ ብሔረሰብን (indigenous people) መብትና ጥቅም ያስከበሩበት/ያስጠበቁበት አግባብ ተሞክሮ ለመዳሰስ እና

 2.4. የኦሮሚያ ክልል ከፊንፊኔ/አዲስ አበባ ሊጠበቅለት የሚገባውን ልዩ ጥቅም ለመደንገግ የሚወጣው አዋጅ ሊያካትታቸው የሚገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮችን ለማመላከት ነው፡፡

3/ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም መነሻዎች

 3.1/ የፊንፊኔ መልከዓምድራዊና ታሪካዊ ዳራ

 የአገራችን ተጨባጭ የታሪክ ማስረጃዎች እንደሚያረጋግጡት የኦሮሞ ክልል(ኦሮሚያ) አንድ አካል እና እምብርት የሆነችው ፊንፊኔ መጠሪያ ስሟን ያገኘችው በከተማዋ ማዕከላዊ ሥፍራ ከምድሯ ማህፀን የሚያፈልቀውን የተፈጥሮ ፍል ውሀ ምንጭን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ በወቅቱ ፊንፊኔ ተብሎ የሚታወቀው አካባቢና ዙሪያው ከኦሮሞ ጎሳዎች አንዱ የሆነው የቱለማ ጎሣ ከሶስቱ ዐቢይ ጎሳዎች (“Balbala”) አንዱ የሆነው የዳጪ ንዑሳን ጎሳዎች የሆኑት የጉለሌ፣ የኤካ፣ የገላን እና የአቢቹ ጉሳዎች ይኖሩበት እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል፡፡

እነዚህ ጎሳዎች በ12 መንደሮች በመከፋፈልና በየራሳቸው የጎሳ መሪዎች ይተዳደሩ እንደነበር በወቅቱ የነበሩትን የጎሳ መሪዎች ስም በመዘርዘር ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህ የአካባቢ ጎሳ መሪዎች መካከል እነ ቱፋ ሙና፣ ዱላ ሃራ፣ ጂማ ጃተኒ፣ ጉቶ ወሰርቢ፣ ጂማ ጢቂሴ፣ አቤቤ ቱፋ፣ ዋሪ ጎሎሌ፣ ቱፋ አረዶ እና ሞጆ ቦንሳራ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተለይም ፊንፊኔ የጉለሌ ኦሮሞ ጎሳዎች የሚበዙበት እንደነበረች በ1868 አካባቢ በካቶሊክ ሚሲዮኖች የተፃፉ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

 በሌላ በኩል አፄ ሚኒሊክ ቤተ መንግስታቸውን በእንጦጦ ላይ ከማድረጋቸው በፊት በመስከረም 1868 ዓ.ም በፊንፊኔ አካባቢ ካቶሊክ ሚሲዮኖች “የፊንፊኔ ሚሲዮን” በሚል መጠሪያ ቤተክርስቲያንና የዕምነት ማስፋፊያ ጣቢያዎች ከፍተው ሲንቀሳቀሱ እንደነበርና በዚህም ፊንፊኔ በመልማትዋ ምንሊክ መቀመጫውን ወደ አከባቢው እንዲያዛውር በዋነኝነት እንደገፋፋቸው በወቅቱ የነበረ ሉዊፊ ላሴሬ የተባለው ሚሲዮን ፅፏል፡፡

ሌላው ምክንያት አፄ ሚኒሊክ አያታቸው “…አንቺ ምድር ዛሬ “…ች” ሞልተውብሻል፤ ነገር ግን ወደፊት የልጄ ልጅ ቤት ሰርቶብሽ ከተማ ትሆኛለሽ” በማለት ለባለቤታቸው ለእቴጌ ጣይቱ እንደነገራቸውና እቴጌም ባላቤታቸው ደቡብን ለመውረር በመጡበት ጊዜ ከባላቤታቸው ጋር ለጤናቸው ጉዳይ ወደፍል ውሃ ሄደው በነበረበት ወቅት ከነበሩበት ድንኳን ውጭ በመንዝ አካባቢ አይተው የማያውቁትን አበባ አይተው በመደነቅ አዲስ አበባ በማለታቸው ከ1887 ጀምሮ ፊንፊኔ – አዲስ አበባ መባል ጀመረች፡፡ የኦሮሞን ባህልና ቋንቋ ብቻ ሳይሆን የአከባቢዎችም ነባር ስያሜዎች ለውጥ/መቀየር አንድ ተብሎ ተጀመረ፡፡

 በሚኒሊክ የጦር አበጋዞች በመላ ኦሮሞ አካባቢና የደቡብ አካባቢዎች ላይ አጠቃላይ ወረራ እስከታወጀበት እ.ኤ.አ 1870 በነበረው ጊዜ እርሻና ከብት እርባታን የኑሯቸው ዋነኛ መሰረት በማድረግ በፊንፊኔና አካባቢዋ ይኖሩ የነበሩት የኦሮሞ ተወላጆች እንደተቀረው የኦሮሞ ሕዝብ ሁሉ በገዳ ሥርዓት ይተዳደሩ የነበረ ከመሆኑ በተጨማሪ ፊንፊኔ በኦሮሞ ክልል እምብርት ሥፍራ ላይ የምትገኝ መሆኗም የንግድና የአምልኮ ማዕከልም መሆን አስችሏታል፡፡ በገዳ ስርዓት ኦዳ ነቤ ሥነ-ሥርዓት በድምቀት ከሚከናወንባቸው የኦሮሞ መሬት ክፍሎች አንዷም ነበረች፡፡

ምንም እንኳን የፊንፊኔ ኦሮሞዎች በባህላቸው መሰረት ከራሳቸው፣ ከተፈጥሮና ከአካባቢያቸው ጋር ተስማምተው በዚህ ማዕከላዊ በሆነ ስፍራ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በሰላም መኖራቸው የሚያጠያይቅ ባይሆንም በፊንፊኔና በዙሪያዋ በነበሩ የኦሮሞ ማህበረሰቦች ላይ ከሰሜኑ አጎራባች ደጋማ ክፍል በሚነሱ ማህበረሰብ ተወላጆች ወረራና ዝርፊያ ይካሄድ የነበረው ሚኒሊክ የሸዋ ንጉስ ከመሆናቸውም አስቀድሞ እንደነበር በወቅቱ በስፍራው የነበረው የእንግሊዙ የዲፕሎማቲክ ልዑክ ሻለቃ W.C.Harris [የኢትዮጵያ ደጋማ ክፍሎች The Highlands of Ethiopia, (1884)] በሚል ባሳተመው የጉዞ ማስታወሻ መፅሀፉ ሰፍሮ ይገኛል፡፡

 በሂደት ወደ አጠቃላይ ወረራ የተቀየረውና በሚኒሊክ ወራሪ ጦር ድል አድራጊነት የተጠናቀቀው ዘመቻ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአካባቢውን የኦሮሞ ተወላጆች ለሞት፣ ለአካል መጉደልና ስደት ዳረገ፡፡ ከሞትና ስደት የተረፉት የመላ ኦሮሚያና የደቡብ ሕዝቦችም ነፃነታቸው ተገፎ በባርነት ቀንበር ስር ወደቁ፡፡ መሬታቸውን ተቀሙ፡፡ ሃብት ንብረታቸው በወራሪው ተዘረፈ፡፡ ግፍና በደሉ በዚህም አልበቃ ብሎ ፊንፊኔ ከወራሪው ጦር መቀመጫነት ወራሪውን ጦር ተከትለው የመጡ ነዋሪዎች መስፈሪያ ከተማ ሆነች፡፡

 የፊንፊኔ ነባር ነዋሪዎች ከርስታቸው ተነቅለው ለወራሪው ሹሞች ተሰጡ፡፡ ለዚህ አስከፊ ተግባር ህጋዊ መሰረትና ድጋፍ ለመስጠት ሲባል በ1907 እ.ኤ.አ የመሬት አዋጅ (Land Charter) ተከትሎ በወጣው ማስታወቂያ የፊንፊኔ ነባር ኦሮሞዎች ካርታ ያልወሰደ በመሬቱ ከመቀመጥ በስተቀር መሬቱ ያንተ አይደለም ተባለ፡፡ የፊንፊኔ ነባር የኦሮሞ ተወላጆች በገዛ መሬታቸው ጪሰኛ ሆኑ፤ በእምነትና ባህላቸው መሰረት አምልኮአቸውን እንዳይፈፅሙ ታግደው የወራሪውን እምነት የመቀበል የመከራ ቀንበር በግዳጅ በላያቸው ላይ ተጫነ፣ ከዚህም አልፎ የጉለሌና የኤካ ጉሳዎች ሊመናመኑ ችለዋል፡፡

 በወራሪው ጨቋኝ ገዢ የፊንፊኔ ነባር የኦሮሞ ተወላጆች ላይ የወደቀው ግፍና መከራ በግድያ፣ በምርኮ፣ ከርስት መነቀልና በጭሰኝነት ጉልት ሥርዓት በማደር ብቻ ያበቃ አልነበረም፡፡ በኦሮሞ ተወላጅ ላይ እንደተጫነው የወራሪው ባህል ሁሉ በኦሮሞ ባህልና የቋንቋ ስያሜ ይታወቁ የነበሩ የፊንፊኔና ዙሪያዋ አካባቢዎች የከተሞችና የቦታ ጥንታዊ መጠሪያዎች እንዲቀየር ተደረገ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ፊንፊኔ የሚለው የጥንት መጠሪያዋ በሃይል ተቀይሮ “አዲስ አበባ” በሚል ስያሜ ተተካ፡፡

. የጥንት/ቀድሞ መጠሪያ በሳባ መጠሪያ አዲስ መጠሪያ
Agamsa አገምሳ መርካቶ
Doobbii ዶቢ ቀጨኔ
Hurufa Boombii ሁሩፈ ቦምቢ ጃንሜዳ
Dildila ድልድለ እንጦጦ
Eekkaa ኤካ የካ
Birbirsa Gooroo ቢርቢርሰ ጎሮ ፒያሳ
Caffee Araaraa ጨፌ አራራ አራት ኪሎ
Malkaa Daabus መልካ ዳቡስ ቸርቺል ጉዳና
Caffee Tumaa ጨፌ ቱማ ስድስት ኪሎ
Caffee Aannanii ጨፌ ኣነኒ ሜክሲኮ
Qarsaa ቀርሳ ካዛንቺስ
Baddaa Ejersaa በዳ ኤጀርሳ ራስ ካሳ ሰፈር
Mujjaa ሙጃ ሽሮ ሜዳ
Garbii ገርቢ ሰንጋ ተራ
Golboo ጎልቦ ቄራ ቂርቆስ
Calcalii ጨልጨሊ ሳር ቤት
Roobii ሮቢ ነፋስ ስልክ
Burqaa Finfinnee ቡርቃ ፊንፊኔ ፍልውሀ
Tulluu Heexoo ቱሉ ሔጦ ትልቁ ቤተመንግስት
Lupha Kormaa ሉጳ ኮርማ ራስ ብሩ ሰፈር
Baaroo Kormaa ባሮ ኮርማ ራስ ተሰማ ሰፈር
Hrbuu Irrechaa ሐርቡ እሬቻ ራስ ሀይሉ ሰፈር
Karra Qirixi ከራ ቂሪጢ ሰሜን በር
Adami አዳሚ ሰሜን ማዘጋጃ
Babo ባቦ አዲሱ ቄራ
Burqa Qoricha ቡርቃ ቆርቻ የካ ሚካኤል

የነፍጠኛው ድርጊት የኦሮሞ ጥንታዊ ስሞችን መቀየር ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ ጥንታዊ ስያሜዎችን በማዛባትም ጭምር ግፍ የተሰራ መሆኑ ለምሳሌ፡- ሀቃቂ ወደ አቃቂ፣ ቀሊቲ ወደ ቃሊት፣ ቀበነ ወደ ቀበና፣ ኤካ ወደ የካ…ወዘተ አዛብቶ እንዲጠሩም የተደረጉ እስከ ዛሬም ምስክሮች ናቸው፡፡

 በሚኒሊክ እግር የአገዛዙን ሥርዓተ-መንበር የተቀበሉት አፄ ኃ/ሥላሴም ነባሩን የኦሮሞ ተወላጅ ከመሬቱ የማፈናቀል እና ማንነቱን የመፋቅና የመደምሰሱን እርምጃ ከአፄ ሚኒሊክ ባልተናነሰ ይልቁንም በረቀቀና በመጠቀ የትምህርትና ባህል ፖሊሲ በመቅረፅ አጠናክረው ገፉበት፡፡ የኦሮሞን ህዝብ ከሀገሪቱ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት ውስጥ በማግለልና በመግፋት ባህል እና ቋንቋው እንዲጠፋ የተጠናከረ ዘመቻ አካሄዱበት፡፡ ነባሩ የኦሮሞ ተወላጅ ራሱ በመሰረታት ከተማ ከገዛ መሬት ከመፈናቀል አልፎ በቋንቋው እንዳይማር እንዳይገለገል በተቃራኒው ባይተዋር ተደርጎ በባህል በቋንቋው እንዲሸማቀቅ ተደረገ፡፡

 ኦሮሞ ራሱ በመሰረታት ፊንፊኔ በ1960 ዓ.ም ማብቂያ አካባቢ የመሬት ይዞታ መረጃ እንደሚያመላክተው የመሬት ይዞታ ክፍፍሉ ከመሬቱ 50 በመቶ ያህሉ በመኳንንትና መሳፍንቱ እጅ የነበረ ሲሆን፣ 33 በመቶ የሚሆነው ደግሞ የእምነት ተቋማት ሥር ወድቆ እንደነበር ተጨባጭ የጽሁፍ መረጃዎች ያረጋገጡት እውነታ ሲሆን ነባሩ የኦሮሞ ተወላጅ ግን ከይዞታው እየተነቀለ ወደ አልለማውና በወባ ነዲድ በተወረረው ወደከተማዋ ጥግ በመግፋት በከተማው መሃል የኦሮሞ ተወላጅ ቁጥር አናሳ እንዲሆን ተደረገ፡፡

 እግር በግር የተተኩት የአፄ ሥርዓቶች በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የጫኑትን የመከራ ቀንበር የኦሮሞ ሕዝብ ያለተቃውሞ አሜን ብሎ የተቀበላቸው አልነበሩም፡፡ እንደሁሉም የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦች ወቅትና ጊዜው በፈቀደውና በተለያየ መንገድ ጭቆናውን እምቢ/አልቀበልም በማለት አምጿል፡፡ የመጫና ቱለማ የመረዳጃ ማህበር የዚሁ የሰላማዊ አመፅ መገለጫ ነው፡፡ የባሌ ኦሮሞ ገበሬዎች አመፅም እንዲሁ፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ የመብት ጥያቄዎች እና አመፆች የኦሮሞን ሕዝብ ወደድል ባይመሩትም ለ1966ቱ ዓ.ም ሕዝባዊ ንቅናቄ እርሾ ለመሆናቸው በወቅቱ ይስተጋቡ የነበሩት የመሬት ላራሹ፣ የብሔርና የዲሞክራሲ መብት ጥያቄዎች ማስረጃ ተደርገው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡

 የአፄውን መንግስት በሀይል ገልብጦ ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት የገዛው ወታደራዊ መንግስት ለእነዚህ ሕዝባዊ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት የሚያስችል ባህሪም ሆነ መሰረት ያልነበረው የአፄዎቹ ተቀጥላ ከመሆን ያለፈ አልነበረም፡፡ በመሆኑም የብሔር ብሔረሰብና ሕዝቦች ጥያቄን ፈታሁ በሚል በሀይል የተጫነን አንድነት በህዝቦች ላይ አጠናክሮ በመጫን የኦሮሚያን ሀብትና የኦሮሞ ወጣቶችን የስልጣን ዘመኑ ተጀምሮ እስከጨረሰ ላኬሄዳቸው ጦርነቶች መስዋዕት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም መላ ሀገሪቷ በጦርነት እሳት ከጫፍ እስከጫፍ ከመንደዷ በተጨማሪ ሕዝቦቿም የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ሆነው በአስከፊ የድህነት አረንቋ ውስጥ እንዲማቅቁ ያደረጋቸው መሆኑ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ነው፡፡

ደርግ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ አትሞ ያለፈው ጥቁር የታሪክ ጠባሳ በአንድ በኩል የኢትዮጵያ ጭቁን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲ እና ለብሄር መብት መረጋገጥ የሚየደርጉት ትግል በየማዕዘኑ ተፋፍሞ እንዲቀጣጠል ያደረገ ሲሆን ይህም እስካልተረጋገጠ ድረስ ሀገሪቷ ከጦርነት ወደ ጦርነት ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ እንጂ የሰላምም ሆነ የልማትን ጭላንጭል የማየት እድል እንደማይኖራት ሁሉም የዲሞክራሲ ሀይሎች በገሀድ የተረዱበት ዘመን ነበር፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በአጠቃላይ የፊንፊኔ ነባር ተወላጆች የቱለማ ጎሳዎች እና ሌሎች ነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆች በፊንፊኔ ላይ ያላቸውን “የልዩ ጥቅም” ሥረ-ነገር ከዚህ የታሪክና የህግ መብት የሚመነጭ መሆኑን መረዳት አስፈላጊ የሚሆነውም በዚህ የተነሳ ነው፡፡

 3.2/ ከዴሞክራሲያዊ የፌደራል ሥርዓት ግንባታ አንፃር የአጀንዳው ወሳኝነት

 የደርግ አምባገነን ሥርዓት በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሀይሎች ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተገርስሶ ወደማይመለስበት ጉድጓድ ሲወረወር የአፈናና የጭቆና 8   ዘመን አብቅቶ የነፃነት ጎህ ሲቀድ ሰፊው የኦሮሞ ህዝብም ልክ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ጭቁን ህዝቦችና የዴሞክራሲ ሀይሎች ሀገሪቱ ለዘመናት የተጓዘችበትን አቅጣጫ በመቀየር በሀይል የሚጫን አንድነት ሳይሆን በመፈቃቀድ በመተባበር የምትመሰረት አዲሲቷን ኢትዮጵያ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ማነፅ እንደዲቻል በጋራ ባካሄደው ዘርፈ- ብዙ እንቅስቃሴ የዲሞክራሲ የእኩልነት መብቶችና የሁሉም ሕዝቦች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት መርሆዎች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ መብት ምሰሶዎች የሚሆኑበት የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ በር የሚከፈትበትን ጎዳና የኢትዮጵያ የሽግግር ወቅት ቻርተርን በማፅደቅ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡

 ሐምሌ 15 ቀን 1983 ዓ.ም በነጋሪት ጋዜጣ ፀድቆ የወጣው የሽግግር መንግስት ቻርተር የዲሞክራሲ መብቶች በሚል ርዕስ በክፍል አንድ አንቀፅ ሁለት ስር የብሔሮች የብሔረሰቦችና የሕዝቦችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብትን የሚያረጋግጥ ድንጋጌ ማካተቱ የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ትግል ከሌሎች የኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝቦችና የዲሞክራሲ ሀይሎች ጋር ያደረጉት የዘመናት ትግልና መስዋዕትነት ያስገኘው ቀዳሚ የድል ፍሬ ተደርጎም ሊቆጠር ይችላል፡፡

 የኦሮሞ ህዝብ የኢትዮጵያ የሰላማዊ ሽግግር ጉባኤ አካል በመሆን በቻርተሩ ላይ በክፍል አንድ በአንቀጽ 1 እና 2 ስር የሰፈሩትን ዲሞክራሲያዊ መብቶች በተለይ እንዲካተቱ የታገለበት ዋነኛ ምክንያት የኦሮሞ ሕዝብ የፈቃድ እንጂ ዳግም የሀይል አንድነት እንዳይጫንበት ያሳለፋቸው የመቶ ዓመት የጭቆናና የመገፋት ስርዓት እንዳይመለስ እንዲሁም እንደግለሰብ ሁሉ ለቡድን መብቶችም እውቅናና ጥበቃ መስጠት እንዲቻል በማሰብ ነው፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሁሉ የራሱን ማንነት የመጠበቅና የማስክበር ባህሉንና ታሪኩን የማበልፀግ እንዲሁም በቋንቋው የመጠቀምና ቋንቋውን የማበልፀግ መብቱን እንዲያረጋግጥ በማስቻል በመፈቃቀድና በእኩልነት የተመሰረተች አዲሲቷን ኢትዮጵያ ከመፍጠር ውጭ ሌላ መንገድ እንደሌለ ከታሪክ መማር በመቻሉ ነው፡፡

 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገመንግስትና የፌዴራል ስርዓቱ አጠቃላይ ዓላማ በሀገራችን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ ዋስትና ያለው ዲሞክራሲን ለማስፈን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገትን ለማፋጠን የሚያስችል አንድ የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ መገንባት ነው፡፡ በዚህም መሰረት ሕገመንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ሆኖ በተለያዩ ድንጋጌዎቹ ውስጥ የሀገራችንን የፖለቲካ ስርዓት፣ የስልጣን ባለቤትነት፣ የመንግስት አካላትን አወቃቀር 9   የስልጣን ክፍፍልና የመንግስት አሰራርን እንዲሁም የዜጎችን መብቶች፣ ነፃነቶች በመንግስትና በዜጎች መካከል ያለውን ግንኙነት በግልፅ ደንግጓል፡፡ ሕገ-መንግስቱን መሰረት አድርገው የሚወጡ ዝርዝር ሕጎችም ከሕገ-መንግስቱ ጋር መቃረን እንደሌለባቸውና የሚቃረኑም ሆነው ከተገኙ ተፈፃሚነት እንደማይኖራቸው በግልጽ የተመለከተ ጉዳይ ነው፡፡

 ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ዲሞክራሲያዊ የፌደራል ሥርዓት ለመገንባት የተደረጉት ጥረቶች አንድነትን በልዩነት ውስጥ ለመገንባት የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ካደረጓቸው ጥረቶችና ርብርቦሽ ጋር ተጣምሮ መታየት የሚገባው ታላቅ ታሪካዊ ጉዳይ ነው የሚባልበት መሰረታዊ ምክንያት ከዚህ የሚመነጭ ነው፡፡

በከተማዋ ውስጥ የሚገኘው ነባሩ የኦሮሞ ህዝብ እነዚህ መብቶች ማለትም በቋንቋው የመጠቀምና የመማር፣ ባህሉን የመንከባከብና የማሳደግ መብትና እድል ተነፍጎ የሚገኝ በመሆኑ መብቱን ለማስከበር ተጨባጭ እርምጃዎች መውሰድ እንደሚገባቸው አንዱ ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም በፊንፊኔ/ አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖረው ነባር የኦሮሞ ተወላጅና ነዋሪ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 39 ንዑስ አንቀፅ (1) እና (2) መሠረት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ በቋንቋው የመናገር፣ የመፃፍ፣ ቋንቋውን የማሳደግና የማስፋፋት እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት ያለው በመሆኑ ሊከበርለት ይገባል፡፡

 ከዚህም በተጨማሪም ፌዴራላዊ የአስተዳደር ሥርዓታችን እየዳበረ መምጣቱ የሕገመንግስቱን አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስፈልገው ዝርዝር ሕግ ሊያካትታቸው የሚገቡ መሰረታዊ ጉዳዮችን አንጥረን እንድናወጣ ሰፊ እድልም ሰጥቶናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሁለት አስርት አመታት ጉዟችን በትክክለኛ ጎዳና ላይ እንደነበር የሚያረጋግጥን እውነታ የልዩ ጥቅም ማስጠበቂያ ዝርዝር ሕጉም ሳይወጣ እንኳ የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ 7/1984 አንቀፅ 15(1) (ሀ) መሰረት በፀደቀው የመጀመሪያው የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድር ሕገ መንግስት በአዋጅ ቁጥር 2/1985 አንቀፅ 58 መሰረት ፊንፊኔ የክልሉ ዋና ከተማ ሆኖ በመወሰኑ እና ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የክልሉ ዋና ከተማ በመሆኑ የክልሉ መንግስት በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ውስጥ ተስፋ ሰጪ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡

 የኦሮሚያ ክልል የመንግስት መ/ቤት፣ የኦሮሞ ባህል ማዕከል እና የአፋን ኦሮሞ ት/ቤቶች የሚገነቡበትን ቦታ ከሊዝ ነፃ በማግኘት ግንባታዎች ተጀምሯል፡፡ እነዚህን የግንባታ ቦታዎች ከማግኘት ባሻገር አብሮ ለመልማትና ደህንነትን ለማስጠበቅ በትብብር ክልላችንና መስተዳድሩ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ ገላጭ ሲሆን ከሽግግሩ መንግስት ምስረታ አንስቶ በአመዛኙ የመስተዳድሩ ከንቲባ በመሆን ያገለገሉ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የኦሮሞ ተወላጅ መሆናቸው ሕገመንግስታዊ ድጋፍ ያለውና የዚሁ መልካም ግንኙነት መገለጫ ነፀብራቅ ነው፡፡

 በሌላም በኩል ተቋማዊና ሥርዓታዊ ገፅታ ያላቸው ባይሆኑም እንኳ የህገመንግስቱን መንፈስ ሊጎዱ የሚችሉ አንዳንድ ተግባራት መከናወናቸውን ማስተዋል ከባድ አይደለም፡፡ በተለይም የፌደራላዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ባህል ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ውስጥ ለሚገኝ ህብረተሰብ ወደመቃብር የወረዱትን የአፄዎቹና ወታደራዊው መንግስት የጉዞና የሀገር ግንባታ አሻራ የሚያስታውሱ በዚሁ በእኛ ዘመን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት (መሪ ሎቄን በሲኤምሲና በሰንሻይን መተካት፣ ካራን በሀያት፣ ፉሪን በጀርመን አደባባይ፣ በሻሌን በሰሚት ወዘተ በመሰሉ የባእድ ስሞች እንዲተኩ የማድረግ ተግባራት)እዚህም እዚያም ብቅ ሲሉ ማየት መራር እውነታ በመሆኑ ፈጣን እርማትን የሚሹ የአደባባይ እውነታ መሆናቸውን መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

 በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ከመጣው የልማት እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ በግብርና ይተዳደሩ የነበሩ የኦሮሞ ተወላጆች የልማት ተነሺዎችን በተመለከተ መስተዳድሩ የሚከተለው የካሳ ስርዓትና የምትክ ቦታ መስጠት ተግባራት መኖራቸው የሚካድ ባይሆንም አጠቃላይ ሂደት በልማት ተነሺዎች ላይ የሚያሳድረው ትውልድ ተሻጋሪ ጉዳቱን                                                                        ለመቀነስ ሊወሰዱ ከሚገባቸው እርምጃዎች አንፃር ሰፊ ክፍተቶች ያሉበት ነው፡፡ ነባር ተወላጆችን አስመልክቶ በአህጉርና በአለምአቀፍ ደረጃ የወጡ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችም [1. Art. 20 of the  African Charter of Human and Peoples Rights of 1981, 2. International Human Rights, Indeginous rights, rights to self Determination] ጋር ይጋጫል፡፡

በተለይም ይህ ሂደት ከመቶ አመታት በፊት በተካሄደ የግፍ ወረራ ከነባር ነዋሪነት ወደ አናሳ ብሔርነት እየተቀየረ ለመጣው የፊንፊኔ ነባር ተወላጅ የህልውና ጉዳይም በመሆኑ መስተዳድሩ የሚከተለው የካሳ ስርዓትና የምትክ ቦታ አሰጣጥ ተግባራትን በተጨማሪ ደጋፊ የማስተካከያ እርምጃዎች የሕግ ማዕቀፍ ማበጀትን የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡

 ለዚህ ማሳያነት ከማዕከላዊ ስታቲስቲክ ባለስልጣን በተገኘው መረጃ መሰረት በ1999 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ከአዲስ አበባ ከተማ 2,739,551 ነዋሪዎች ውስጥ አማራ 1,288,895(47%)፣ ኦሮሞ 534,547(19.5%)፣ ጉራጌ 447,777(16.3%)፣ ትግሬ 169,082(6.2%) እና ሌሎች 299,150(10.1%) ሲሆን የኦሮሞ ተወላጅ በተወለደበት መሬቱ ላይ አናሳ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው፡፡

 ስለሆነም የኦሮሞ ህዝብ በፊንፊኔ ላይ ያለውን የታሪክና የህግ መብት የሚያረጋግጥለት ‹‹የልዩ ጥቅም›› ሥረ-ነገር በአንድ ፊት ከታሪክ መሰረት የሚነሳ የመሆኑን ያህል ሁለተኛው የመብት መነሾ የአዲስ አበባ መስተዳድር የኦሮሞ መሬት አንድ አካልና እምብርት መሆኗ እንዲሁም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ ከተማም በመሆኗ ጭምር የሚመነጭ መሆኑን መረዳት ተገቢ ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባን ነዋሪ ውሀ ሲያጠጣ የኖረው የገፈርሳ እና የለገዳዲ ውሀ በደጁ የሚያልፈው የኦሮሞ አርሶአደር ከውሀው እንዲጠቀም ለማድረግ በቂ ጥረቶች አለመደረጋቸው እና ከተማዋ ነባር የኦሮሞ አርሶ አደሮችን እያፈነቀለች ከጊዜ ወደ ጊዜ መስፋትዋ መሬት ላይ ያለው ገሃድ ሀቅ በመሆኑ ሁሌም ሀብትን ምክንያት አድርጎ ማቅረብ የሚቻል አይደለም፡፡ በፊንፊኔ/አዲስ አበባ የሚቋቋሙት ኢንዱስትሪዎች ወደ አጎራባች የኦሮሚያ አካባቢዎች የሚለቀቀውን የተበከለ ፍሳሽ ለማከም በምትኩም የተጠቃሚነትን ያህል የፊንፊኔ ባለቤትና የኦሮሞ ተወላጅ በአዲስ አበባ የመንግስት መ/ ቤቶች አገልግሎትን በቋንቋው እንዲያገኝ ለማድረግ በጥቂት አጋዥ እርምጃ ቢደገፍ መልካም ይሆን ነበር፡፡

 በመሆኑም ፌደራላዊ የአስተዳደር ስርዓታችን በየጊዜው እየዳበረና ስር እየሰደደ መምጣቱን እና ህገመንግስቱን አሟልቶ ወደመሬት ለማውረድ እየተደረገ ያለው ጥረት ጠንካራ መሆኑን እንዲሁም የሁለት አስርት አመታት ጉዟችን በትክክለኛ ጎዳና ላይ እንደነበርና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበቱን የሚያረጋግጥ በመሆኑ እና የፌደራላዊ ስርዓት ግንባታ ሂደታችን የሚያሳየው የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ህገመንግስታዊ ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅለት ዝርዝር ህግ በማውጣት ሊጠበቅለት የሚገባ መሆኑን ብቻ ሳይሆን ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት ማረም የሕገ መንግስታችን ዓለማም መሆኑን ያሳያል፡፡

 በአጠቃላይ በጊዜ ሂደት የፊንፊኔ/አዲስ አበባ አስተዳደርንና የኦሮሚያ ክልልን እያስተሳሰሩ የመጡት መጠነ ሰፊ ጉዳዮች የፊንፊኔ/አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል የተለያየ አቅርቦት ስለሚያገኝ የሁለቱን ጥቅም ሚዛን ለመጠበቅ ሲባልና የህገ-መንግስቱን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም እንዲጠበቅለት ማድረግ የግድ ይላል፡፡ በመሆኑም ከላይ በተዘረዘሩት ጉዳዮች መነሻ በማድረግ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም የሚደነግገውን ዝርዝር ህግ ማውጣት በእጅጉ አስፈላጊ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

3.3/ ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶች አንፃር

 በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀፅ 9(4) ላይ ተደንግጎ የሚገኘው ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ህግ አካል ናቸው በሚል ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መካከል የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ(UDHR)፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን(ICCPR)፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን(ICESCR)፣ ሁሉም ዓይነት የዘር ልዩነት ለማስወገድ የተፈረመ ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን(CERD)፣ የተባበሩት መንግስታት የጥንት ነባር ህዝቦች መብቶች ድንጋጌ(UNDRIP)፣ የአፍሪካ ሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር(ACHPR)፣ የሕፃናት መብቶች ስምምነት(CRC) እና የአፍሪካ ሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር(ACRWC) አኳያ የኦሮሞ ብሔር መብት በአጠቃላይ እንዲሁም ነባር የቱለማ ኦሮሞና ነዋሪዎች መብት በተለይ በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ሊኖር የሚገባውን መብቶች በአጭሩ መመልከት አስፈላጊ ይሆናል፡፡

 3.3.1 የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ (UDHR)

እ.ኤ.አ በ1948 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ የሰብዓዊ መብቶች ሁሉ አቀፍ መግለጫ(UDHR) መታወጁ እና አገራችን ኢትዮጵያ ይህን መግለጫ መፈረሟ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መግለጫ አንቀፅ 2 ላይ በዘር፣ በቀለም፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አስተያየት፣ በሕብረተሰብ ምንጭ ፣ በሃብት፣ በትውልድ፣ ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ እያንደንዱ ሰው በዚህ መግለጫ ውስጥ የተጠቀሱትን መብቶችና ነፃነቶች የመጠቀም መብት አለው፣ በአንቀፅ 17 ንዑስ አንቀፅ 1 ማንም ሰው ብቻውንም ሆነ ከሌሎች ጋር በመተባበር የንብረት ባለቤት የመሆን መብት አለው፣ እንዲሁም በአንቀፅ 25 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት ማንም ሰው ለራሱና ለቤተሰቡ ጤንነትና ደህንነት በቂ በሚሆን የኑሮ ደረጃ የመኖር መብት አለው በሚል ተደንግጎ ይገኛል፡፡

 በመሆኑም ነባሩ የቱለማ ኦሮሞ (indigenous Tulama Oromo) እና ሌሎች የኦሮሞ ተወላጆች በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ በቋንቋው የመጠቀምና የመማር፣ ባህሉንና ታሪኩን የማወቅ፣ የማሳደግና የመንከባከብ፣ ከቅድመ አያቶቹ ካገኘው የገዛ መሬቱ ያለ በቂ ምክንያት ያለመፈናቀል እና የንብረት ባለቤት የመሆን መብት እንዲሁም ለኑሮው አስፈላጊ የሆኑትን አገልግሎቶችን የማግኘት መብት እንዳለው እንገነዘባለን፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ነባሩ የኦሮሞ ተወላጅ እነዚህን መብቶች በራሱ በቅድመ አያቶቹ መሬት አዲስ አበባ ላይ ተነፍጎ ይገኛል፡፡

 3.3.2 የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን (ICCPR)

 እ.ኤ.አ በ1966 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን (ICCPR) በአባል አገሮች እንዲፈርሙ እንዲያፀድቁትና እንዲቀበሉት በተወሰነው መሰረት ኢትዮጵያም የዚህ ቃል ኪዳን ፈራሚ ናት፡፡ በቃል ኪዳኑ አንቀፅ 1 ንዑስ አንቀፅ 1ና 2 “ሁሉም ህዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት አላቸው፡፡ በዚሁ መብታቸው መሰረትም የፖለቲካ ሕልውናቸውን ይወስናሉ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ዕድገታቸውን በነፃነት ያራምዳሉ፣ በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን አንድ ህዝብ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑት ጥቅሞች ሊነፈግ አይገባቸውም፡፡”

በአንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 1 መሰረት “እያንዳንዱ ቃል ኪዳኑን የተቀበለ አገር በግዛቱ አገር ለሚኖርና በሥሩ ለሚተዳደር ማንኛውም ግለሰብ በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም ሌላ አመለካከት፣ በብሔራዊም ሆነ ማህበራዊ አመጣጡ፣ በሃብት፣ በውልደት፣ ወይም በሌላ መለኪያ ምንም ልዩነት ሳይደረግ በዚህ ሕግ እውቅና ያገኙትን መብቶች ሊያስከብርለትና ሊያረጋግጥለት ተስማምተዋል፡፡

እንዲሁም በአንቀፅ 27 በጎሳ፣ በሃይማኖት ወይም በቋንቋ ላይ ለተመሰረቱ ቁጥራቸው አነስተኛ ለሆኑ ማህበረሰቦች ባሉበት አገር ውስጥ የእነዚህ አባል የሆነ ሰው ከሌሎች የማህበረሰቡ አባላት ጋር በባህሉ እንዳይጠቀም፣ በሃይማኖቱ እንዳያምን ወይም አምልኮውን እንዳይፈፅም፣ ቋንቋውን እንዳይጠቀምበት መብቱ ሊገፈፍ አይቻልም፡፡”ይላል፡፡ በመሆኑም በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ነባሪ ነዋሪ የሆነው የቱለማ ኦሮሞ ራሱን በራሱ የማስተዳደር፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ህልውናቸውን የመወሰን፣ ለኑሮአቸው አስፈላጊ የሆኑ አገልግሎቶችን የማግኘት እና በቋንቋቸው የመጠቀም መብት ሊከበርላቸው እንደሚገባ እንረዳለን፡፡

 3.3.3 የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን (ICESCR)

 እ.ኤ.አ በ1966 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህል መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን(ICESCR) በአባል አገሮች እንዲፈርሙ እንዲያፀድቁትና እንዲቀበሉት በተወሰነው መሰረት ኢትዮጵያም የዚህ ቃል ኪዳን ፈራሚ ናት፡፡ በዚሁ መሰረት በቃል ኪዳኑ አንቀፅ 1 ንዑስ አንቀፅ 1 ሁሉም ህዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት አላቸው፡፡

በዚሁ መብታቸው ተጠቅመው የፖለቲካ አቋማቸውን በነጻነት ይወስናሉ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ዕድገታቸውንም በነፃነት ያካሄዳሉ፣ በንዑስ አንቀፅ 2 በማናቸውም ሁኔታ ቢሆን አንድ ህዝብ ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑትን የራሱን ጥቅሞች አይነፈግም፡፡ በአንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 2 የዚህ ቃል ኪዳን ተዋዋይ አገሮች በዘር፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አስተሳሰብ፣ በብሔር ወይም በማህበራዊ ምንጭ፣ በሃብት፣ በትውልድ ወይም በሌላ አቋም ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግ በዚህ ቃል ኪዳን የተደነገጉ መብቶችን ለማስከበር ተስማምተዋል፡፡

 3.3.4 ሁሉም ዓይነት የዘር ልዩነቶች ለማስወገድ የተደረገ ዓለም አቀፍ ስምምነት (CERD)

እ.ኤ.አ በ1965 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ሁሉም ዓይነት የዘር ልዩነቶች ለማስወገድ የተደረገ ዓለም አቀፍ ስምምነት የፀደቀ ሲሆን ኢትዮጵያም የዚህ ስምምነት ፈራሚ ናት፡፡ በዚሁ መሰረት በስምምነቱ አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ እንደተቀመጠው ስምምነቱን የተቀበሉ አገሮች በየግዛታቸው ውስጥ የሚኖሩ ጎሳዎች እና ግለሰቦች ሰብዓዊ መብቶቻቸውና መሰረታዊ ነፃነታቸው በተሟላ መንገድና በእኩልነት እንዲጠቀሙ የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች ጥቅሞቻቸውና እድገታቸው የሚያረጋግጡ የተለዩና ተጨባጭ እርምጃዎች መውሰድ አለባቸው፡፡ እነዚህ እርምጃዎች ለተለያዩ ጎሳዎች እኩል ያልሆኑ እና የተለያዩ መብቶች የሚያጎናፅፉ መሆን የለባቸውም ይላል፡፡

 በመሆኑም በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆችን የማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊ እና ሌሎች ጥቅሞቻቸውና እድገታቸው ለማረጋገጥ እንዲቻል የከተማው አስተዳደር ተጨባጭ እርምጃዎችን(የፖሊሲ፣ ስትራቴጂ፣ ህጎችና እቅዶች… ወዘተ) መውሰድ እንደሚገባ እንረዳለን፡፡

 3.3.5 የተባበሩት መንግስታት የጥንት ነዋሪ ህዝቦች መብቶች ድንጋጌ (UNDRIP)  

 እ.ኤ.አ መስከረም 13 ቀን 2007 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባዔ 107ኛ መደበኛ ስብሰባው የተባበሩት መንግስታት የጥንት ነዋሪ ህዝቦች መብቶች ድንጋጌ (the United Nations Declaration on the Rights of Indigenous Peoples -UNDRIP) ያጸደቀ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሲሆን አብዛኞቹ ሀገራት ይህን ድንጋጌ የሀገራቸው የህግ አካል በማድረግ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡

 የጥንት ነዋሪዎችን በተመለከተ በድንጋጌው ውስጥ ዕውቅና ዋና ዋና መብቶችና ጥበቃዎች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት(self determination) ሲሆን በዚህ መብት ውስጥ የጥንት ነዋሪዎች የራሳቸውን ጥቅም የሚነኩ ጉዳዮች ላይ የመሳተፍ፤ መንግስት ወይም የሚመለከተው አካል የሚወስናቸው ህጋዊ ወይም አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጥቅማቸውን የሚነካ ከሆነ የመማከር መብት አላቸው፡፡ ሁለተኛው የጥንት ነዋሪዎች የሚኖሩበት መሬት፤ ሀብት እና ድንበራቸው የመጠበቅ መብት ያላቸው ሲሆን በዚሁ አግባብ የጥንት ነዋሪዎች ያላቸው መሬት፤ ሀብት እና ድንበር ማንነታቸውን ለመጠበቅ እና ለማቆየት ወሳኝ ሀብቶች በመሆናቸው እነዚህ ሀብቶች በማንኛውም አካል እንዳይደፈሩባቸው የማስደረግ፤ ለሀብቶቹ በህግ ዕውቅና እንዲያገኙ ማድረግ መብቶች አላቸው፡፡

በሶስተኛነት የጥንት ነዋሪዎች ባህላቸውን፤ ኢኮኖሚያቸውን እና ማህበራዊ ህይወታቸውን የማሳደግ፤ ለቀጣዩ ትውልድ የማስተላለፍ እና ሌሎች ተያያዥ መብቶች ያላቸው ሲሆን መንግስት ወይም የሚመከለተው አካል በአንድ በኩል የጥንት ነዋሪዎች ማህበራዊ፤ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወታቸውን እንዲበለጽግ የማድረግ ሃላፊነት ያለበት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ወይም የሚመለከተው አካል የጥንት ነዋሪዎችን ማህበራዊ፤ ባህላዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ከመጉዳት መቆጠብ ያለበት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

 ስለሆነም በፊንፊኔ የሚኖሩ የጥንት ኦሮሞ ነባር ነዋሪዎች መብቶች የሆኑት የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶች፤ መሬት፤ ሀብት እና ድንበራቸው የማስጠበቅ መብቶች እና ባህላዊ፤ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወታቸውን የማበልፀግ እና የማስፋፋት መብታቸውን የፌዴራል መንግስት እና የከተማው አስተዳደር ይህንን መብት ለማስጠበቅ የተለያዩ ርምጃዎችን በመውሰድ በዓለም አቀፍ ደረጃ የወጣውን የጥንት ነባር ነዋሪዎች ድንጋጌ ወደ ተግባር በመለወጥ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ማስጠበቅ ይገባል፡፡

 3.3.6 የአፍሪካ ሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተር (ACHPR)

 በአፍሪካ አንድነት ድርጅት 18ኛው የአገርና የመንግስት መሪዎች ጠቅላላ ስብሰባ እ.ኤ.አ ጁን ወር 1981 በናይሮቢ ኬኒያ የፀደቀውን ቻርተር አገራችን ኢትዮጵያ ፊርማ የተቀበለች በመሆኑ በቻርተሩ አንቀፅ 1 መሰረት በቻርተሩ ውስጥ የተደነገጉትን መብቶች፣ ግዴታዎችና ነፃነቶች አውቀው በመቀበል ለተግባራዊነታቸው ሕግ ለማውጣትና ሌሎች እርምጃዎችን ለመውሰድ ግዴታ ገብተዋል፡፡ በአንቀፅ 2 ማንም ሰው በዘር፣ በጎሳ፣ በቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አስተሳሰብ፣ በብሔርና ማህበራዊ ምንጭ፣ በሃብት፣ በመወለድ ወይም በሌላ ሁኔታ ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይደረግበት በዚህ ቻርተር ዕውቅናና ዋስትና ያገኙት መብቶችና ነፃነቶች ተጠቃሚ ይሆናል፡፡

 በተጨማሪም በአንቀፅ 13 ንዑስ አንቀፅ (3) መሰረት ማንኛውም ሰው በሕዝብ ንብረትና በሕዝብ በሚሰጥ አገልግሎት በሕግ ፊት ከሁሉም ሰዎች ጋር እኩል የመጠቀም መብት አለው፡፡ በአንቀፅ 14 የንብረት ባለቤት የመሆን መብት የሕግ ዋስትና አለው፡፡ በአንቀፅ 19 ሁሉም ሕዝቦች እኩል ናቸው፤ እኩል የመከበርና በእኩልነት የመታየት መብት አላቸው፡፡

 በአንቀፅ 22 ንዑስ አንቀፅ (1) ሁሉም ሕዝቦች የኢኮኖሚ፣ የሶሻልና የባህል ልማታቸውን፣ ማንነታቸውንና የሰው ልጅ የጋራ ቅርስ ተጠቃሚነታቸውን በሚያረጋግጥ ሁኔታ እንዲካሄድ የማድረግ መብት አላቸው፡፡ እንዲሁም በአንቀፅ 24 ሁሉም ሕዝቦች ለልማታቸው ተስማሚ የሆነ አካባቢ የማግኘት መብት አለቸው በሚል አስቀምጧል፡፡ ስለሆነም በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ነባሪ ነዋሪ የሆነው የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ከላይ የተዘረዘሩት መብቶች ሊከበርላቸው እንደሚገባ እንረዳለን፡፡

  3.3.7 የአፍሪካ ሕፃናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር (ACRWC)

 በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ውሳኔ እ.ኤ.አ ከኖቭምበር 29 ቀን 1999 ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል የተወሰነውን ቻርተር አገራችን ፈራሚ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በዚህ ቻርተር አንቀፅ 3 ማንኛውም ሕፃን የወላጁ ወይም የአሳዳሪው ወይም የራሱ የዘር፣ የጎሳ፣ የቀለም፣ የፆታ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ፣ ወይም ሌላ አመለካከት፣ የዜግነት፣ የማህበራዊ አመጣጥ፣ የሀብት፣ የውልደት፣ ወይም በሌላ ዓይነት የመጣ ልዩነት ሳይደረግበት በዚህ ቻርተር ዕውቅና በተሰጣቸውና በተረጋገጡ መብቶችና ነፃነቶች የመጠቀም መብት አለው፡፡

እንዲሁም በአንቀፅ 7 ሕፃን በማንኛውም ጉዳይ ላይ ሃሳብ በነፃ የመግለፅ እና አስተያየቱን የማሰራጨት መብት ይኖረዋል በሚል ያስቀምጣል፡፡ ስለሆነም በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ነባሪ ነዋሪ የሆነው የቱለማ ኦሮሞ ልጆች በአፋን ኦሮሞ የመማር እና ሃሳባቸውን በትምህርት ቤትም ጭምር በቋንቋቸው የመግለፅና የመፃፍ መብታቸው ሊከበርላቸው ይገባል ማለት ነው፡፡

 ሲጠቃለል ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ህጎች አካል በመሆናቸው በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ነባሪ ነዋሪ የሆነው የቱለማ ኦሮሞዎችና ነዋሪ ኦሮሞዎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ህልናዊ መብቶቻቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባና እነዚህን መብቶች ተነፍጎት የቆየውና የሚገኘው የኦሮሞ ነዋሪዎችን መብት ማስከበር አገራችን ግዴታ ያለባት መሆኑን ከላይ በዝርዝር ከተመለከትናቸው ስምምነቶች መረዳት ይቻላል፡፡

3.4/ በፌዴራል እና ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የወጡ ሕጎች አንፃር

በዚህ ርዕስ ስር ፊንፊኔ/አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል አንድ አካልና እምብርት በመሆኗ ምክንያት በፌዴራል እና በክልላዊ መንግስት ደረጃ የወጡ ህጎች የኦሮሞ ህዝብና የፊንፊኔ/ አዲስ አበባ ታሪካዊ ትስስርና ኦሮሚያ ከፊንፊን/አዲስ አበባ ሊጠበቅለት የሚገባ ልዩ ጥቅም በሚመለከት በተለያዩ ጊዜያት የወጡትን ሕጎች በዝርዝር እንመለከታለን፡፡

 3.4.1 በፌዴራል ደረጃ ከወጡ ሕጎች አኳያ

 ሀ. የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 7/1984፣

የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት የተወካዮች ምክር ቤት በሽግግር ወቅት ቻርተር አንቀፅ 2(ለ)፣ 9(መ) እና 13 መሠረት ጥር 5 ቀን 1984 ዓ.ም. የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 7/1984 ማፅደቁ ይታወሳል፡፡

 በዚሁ አዋጅ አንቀፅ 3(1) መሠረት ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ማቋቋም የሚችሉ ብሔር፣ ብሔረሰብና ህዝብ ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ አንዱ የኦሮሞ ብሔር መሆኑና የክልሉ ስያሜውም “ክልል 4” ተብሎ የተሰየመ ሲሆን በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (4) መሠረት በክልል 13(ሐረሪ ብሔረሰብ ወይም የሐረር ከተማ) እና በክልል 14(አዲስ አበባ) የኦሮሞ ልዩ ብሔራዊ ጥቅምና የፖለቲካ መብት የተጠበቀ ይሆናል፣ ሰርዝ የተጨመረ፡፡

 የነዚህ መስተዳድሮች ተጠሪነት ለማዕከላዊ የሽግግር መንግስት ሆኖ የመስተዳድሮቹ ግንኙነት በልዩ ሕግ በዝርዝር ይወሰናል በሚል አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ የኦሮሞ ብሔር ወይም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ ያለው ልዩ መብት እንዲጠበቅ በሽግግሩ ዘመን በአዋጅ ቁጥር 7/1984 ህጋዊ ጥበቃ ያገኘ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

 ለ. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት፣ 

 በሕገ መንግስት ጉባዔ የውይይት ቃለ ጉባዔ ገፅ 106 እስከ 108 መረዳት እንደሚቻለው ለኢፌዲሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 49 ንዑስ አንቀጽ 5 መደንገግ ወይም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ከአዲስ አበባ ሊጠበቅለት የሚገባው ተብለው በጉባዔው አባላት የተነሱት፡- አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል የሚገኝ በመሆኑ፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የምትገኝ በመሆኗ፣ የከተማው መስፋት አርሶ አደሮችን የሚነካ በመሆኑ፣ ከተማዋ ያለችበት መሬት የኦሮሚያ በመሆኑ፣ አዲስ አበባ የኦሮሚያ እምብርት በመሆኗ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ ከተማ በመሆኗ እና ይህን ሕዝብም የሚያምነበት በመሆኑ አንቀፁ እንዳለ እንዲፀድቅ በተጠየቀው መሰረት ለድምፅ ቀርቦ በ507 ድጋፍ እና በ6 ድምጸ ተአቅቦ አንቀፅ 49 ሊፀድቅ መቻሉን እንደገነዘባለን፡፡

በዚሁ መሠረት በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 ንዑስ አንቀፅ (5) ፡ “የኦሮሚያ ክልል ፡ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮች በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል፡፡ ዝርዝሩ በህግ ይወሰናል” ይላል፡፡

 ይህ ድንጋጌ ከአዋጅ 7/1984 ድንጋጌ በተለየ መልኩ የኦሮሞ ልዩ ብሔራዊ ጥቅምና የፖለቲካ መብት በሚል ሰፋ ተብሎ የተቀመጠውን ወደ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምና የመሳሰሉትን እንዲሁም አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጠበብ በማድረግ የተቀመጠ ቢሆንም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም በሕገ መንግስቱ የተደነገገ መብት ነው፡፡

 . የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 9 ቀን 1989 ዓ.ም ባፀደቀው የመጀመሪያውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 አንቀፅ 33 ላይ በአዲስ አበባ ስለኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ልዩ ጥቅም በግልፅ ደንግጓል፡፡ በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) ላይ በዚህ ቻርተር አንቀፅ 2(1) የሚከለለው የአዲስ አበባ ወሰን በከተማው መስተዳደርና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በጋራ ተለይቶ የወሰን ምልክት ይደረግበታል፣

በንዑስ አንቀፅ (2) የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት መቀመጫውን በአዲስ አበባ የማድረግ መብት ይኖረዋል፣ በንዑስ አንቀፅ (3) የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ለአዲስ አበባ ህዝብ የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች በመስተዳድሩ አዋሳኝ ለሚኖረው የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ሊዳረሱ የሚችሉ ሲሆን ነዋሪዎቹ በተመሳሳይ ሁኔታ የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል እና

በንዑስ አንቀፅ (4) የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ለአዲስ አበባ ህዝብ ከሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ጋር በተያያዙ የልማት ሥራዎችን በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ጋር በመመካከርና በመስማማት ይሆናል በሚል ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡

 በጥቅሉ ሲታይ በአዋጁ የኦሮሚያ ልዩ መብቶች ተብለው የተዘረዘሩት አራት ጉዳዮች መሆናቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ አንደኛው የከተማው ወሰን በኦሮሚያ ክልል ስምምነት ብቻ የሚካለል መሆኑ፣ ሁለተኛው ክልሉ መቀመጫውን አዲስ አበባ የማድረግ መብት፣ ሶስተኛ ከክልሉ ለከተማው ህዝብ የሚገኙ አገልግሎቶች የክልሉ ነዋሪዎች የመጠቀም መብት እና አራተኛው ከተማው ማንኛውንም የክልሉን ህዝቦች የሚነኩ የልማት ሥራዎች በክልሉ ሊሰራ የሚችለው በቅድሚያ ከክልሉ ጋር በመመካከርና ክልሉ ሲስማማ ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

 . የተሻሻለው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 311/1995

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥር 8 ቀን 1995 ዓ.ም ባፀደቀው ሁለኛው የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 311/1995 አንቀፅ 62 መሠረት የከተማው አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ግንኙነት በሚል አስቀምጧል፡፡ በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (1) ላይ የከተማው አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር ፍሬያማ ትብብርን መሰረት ያደረገ ግንኙነት ይኖረዋል፡፡

በንዑስ አንቀፅ (2) በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 49 (5) መሠረት የኦሮሚያ ክልል ጥቅም የተጠበቀ ነው፡፡ ዝርዝሩ በከተማው አስተዳደርና በክልሉ መንግስት መካከል በሚደረግ ስምምነት ወይም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወጣ ህግ ይወሰናል በሚል ተቀምጧል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም በአዋጁ አንቀፅ 5 ስለ ወሰን ሲደነግግ አሁን ያለው የከተማው ክልል እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የከተማው አስተዳደር ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚያደርገው ስምምነት ወይም በፌዴራል መንግስት ይወሰናል፣ የወሰን ምልክትም ይደረግበታል በሚል አስቀምጧል፡፡

 ከዚህ አንቀፅ ድንጋጌ መረዳት እንደሚቻለው በሕገ መንግስቱ “ልዩ” ጥቅም የሚለውን ያላካተተ፣ ጥቅሙንም ከሕገ መንግስቱ በተቃራኒ በከተማውና በክልሉ ስምምነት እንደሚፈፀም አድርጎ አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪም ወሰንን በተመለከተ ከአዋጅ 87/1989 በተቃራኒ የሁለቱ ስምምነት ሳያስፈልግ በፌዴራል መንግስት ሊወሰን እንደሚችል ደንግጓል፡፡ ይህ አዋጅ ሲመዘን የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ከመጀመሪያው ቻርተር መብቶቹን ከማሳነስ አልፎ የከተማው ወሰን ያለ ክልሉ ስምምነት በፌደራል መንግስት ሊወሰን እንደሚችል የደነገገ ቻርተር ነው፡፡

 . የተሻሻለው አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995

 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሐምሌ 17 ቀን 1995 ዓ.ም ባፀደቀው ሶስተኛው የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 አንቀፅ 62 በከተማው አስተዳደርና የኦሮሚያ ክልል ግንኙነት እና በአንቀፅ 5 ስለወሰን በአዋጅ 311/1995 በተመሳሳይ/ባልተለየ መልኩ ደንግጓል፡፡

 3.4.2 በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከወጡ ሕጎች አንፃር 

 . የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድር ሕገ መንግስት (1984) 

 የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድር ሕገ መንግስት አዋጅ ቁጥር 2/1985 ሰኔ 14 ቀን 1984 ዓ.ም በተካሄደው ሕዝባዊ ምርጫ ተከትሎ ከነሐሴ 9 እስከ 14 ቀን 1984 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መኮንን አደራሽ በተካሄደው አዲስ በተቋቋመው የኦሮሚያ ምክር ቤት የፀደቀ ሕገ መንግስት ነው፡፡ ይህ ህገ መንግስት በታሪካዊነቱ የመጀመሪያ የኦሮሚያ የህጎች ሁሉ የበላይ እና ቁንጮ ህግ ነው፡፡

ምክንየቱም ኦሮሞ በአንድ ጨፌ ስር መተዳደር ሲጀምር የወጣ ህግ መሆኑ፣ በዚሁ ሕገ መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ ኦሮሞ በአንድ አባ ቦኩ/ፕሬዚዳንት/ በጨፌ/ምክር ቤቱ የተመረጠበት መሆኑ፣ በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 55 የክልሉ መጠሪያ ስሙ ኦሮሚያ መሆኑ፣ በአንቀፅ 57 የክልሉ የሥራ ቋንቋ አፋን ኦሮሞ መሆኑና የሚፃፈውም በላቲን ፊደል መሆኑን እና በአንቀፅ 58 የክልሉ ዋና ከተማ ፊንፊኔ መሆኑን የተወሰነበት በመሆኑ ነው፡፡

 . የኦሮሚያ ሕገ መንግስት (1987) 

 ሁለተኛው የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግስት አዋጅ ቁጥር 1/1987 የሽግግሩ ወቅት ተጠናቆ ሕዝባዊ መንግስት በምርጫ መቋቋምን ተከትሎ ሰኔ 15 ቀን 1987 ዓ.ም በመስራች ጉባዔ የፀደቀ ሕገ መንግስት ነው፡፡ በዚህ ህገ መንግስት አንቀፅ 6 መሰረት የኦሮሚያ ክልል ርእሰ ከተማ ፊንፊኔ መሆኑን እንደ መጀመሪያው ሕገ መንግስት ለሁለተኛ ጊዜ ተደንግጎ እናገኛለን፡፡

 . የተሻሻለው የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግስት (1994) 

 ሶስተኛው የተሻሻለው ኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግስት አዋጅ ቁጥር 46/1994 የ1993 ዓ/ም የተካሄደውን ተሃድሶ ተከትሎ ጥቅምት 17 ቀን 1994 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በተካሄደው የጨፌ አስቸኳይ ጉባዔ የፀደቀ ሕገ መንግስት ነው፡፡ በዚህ ህገ መንግስት አንቀፅ 6 መሰረት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርእሰ ከተማ አዳማ መሆኑን ይደነግጋል፡፡ ምክንያቱም ቀደም ሲል ከሐምሌ 3-5 ቀን 1992 ዓ.ም በዝዋይ ከተማ በተካሄደው 9ኛው የጨፌ ኦሮሚያ መደበኛ ጉባዔ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ለመወሰን የወጣ አዋጅ ቁጥር 35/1992 ዓ.ም አንቀፅ 3 ንዑስ አንቀፅ (1) መሰረት ከሐምሌ 5 ቀን 1992 ዓ.ም ጀምሮ አዳማ ከተማ የኦሮሚያ ዋና ከተማ በመሆን ተቋቁሟል በሚል በመታወጁ ነበር፡፡

 ይሁን እንጂ ከአዋጁ መታወጅ ማግስት ጀምሮ በተካሄደው የህዝብ ተቃውሞና በተለይም የ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ጠቅላላ ምርጫ ውጤት ተከትሎ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቀመጫውን ወደ ፊንፊኔ ከተመለሰ በኋላ ጳጉሜ 1 ቀን 1997 ዓ.ም በተካሄደው የጨፌ ኦሮሚያ ጉባዔ በ1994 ዓ.ም የተሻሻለውን የኦሮሚያ ክልል ሕገ መንግስት አዋጅ 46/1994ን ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 94/1997 አንቀፅ 2 ንዑስ አንቀፅ (3) መሰረት የኦሮሚያ ዋና ከተማ ፊንፊኔ እንዲሆን በመወሰን የሕገ መንግስቱ ግንጋጌ እንዲሻሻል ተደርጓል፡፡

 . የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 115/2000 

 የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስተደደር ምክር ቤት(ካቢኔ) ነሐሴ 8 ቀን 2000 ዓ.ም በደንብ ቁጥር 115/2000 የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን መስተዳድር ፅ/ቤት ማቋቋሙ ይታወሳል፡፡ በዚህ ደንብ አንቀፅ 9 ንዑስ አንቀፅ (2) መሰረት ከፊንፊኔ ከተማ አስተዳደር ጋር በቅንጅት መስራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ጥናት በማካሄድ የመፍትሔ ሀሳብ ለሚመለከተው አካል ያቀርባል፣ ሲጸድቅም ሥራ ላይ እንዲውል ያደርጋል፣ እንዲሁም በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (6) የፊንፊኔ ከተማ እና አሮሚያ ድንበር ተለይቶ እንዲታወቅ ከሚመለከተው አካል ጋር ይሰራል የሚሉ ስልጣንና ተግባራት ለልዩ ዞን መስተዳድር ፅ/ቤት የተሰጡት ናቸው፡፡

 በመሆኑም ልዩ ዞኑ ከፊንፊኔ/አዲስ አበባ/ ጋር አዋሳኝ ከተሞችን በመወከል ከፊንፊኔ/ አዲስ አበባ/ ጋር የመስራት፣ የመመካከርና በትብብር በመስራት የዞኑን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ ይጠበቅበት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ግልፅ ባልሆኑ ምክንያቶች ደንቡ ሳይሻሻል ከተሞችን ከልዩ ዞኑ እንዲወጡ ስለተደረገ በከፊል እንዲፈርስ በመደረጉ አሁን ባለው ሁኔታ    የተቋቋመበትን ስትራቴጂካዊ ተልዕኮውን ሊወጣ የሚችልበት ቁመና ላይ አይገኝም፡፡

 3.4.3 ከትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ አንፃር 

 የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት በ1986 ዓ.ም አዲስ የትምህርትና የስልጠና ፖሊሲ አውጥቶ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ወዲስ 23 ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በመሆኑም በፖሊሲው በተቀመጠው አቅጣጫ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን በዜጎች ቋንቋ ማስተማር ነው፡፡

ይህንን በሚመለከት በገፅ 12፣ አንቀፅ 3.5.1 እና 3.5.2፡

 “በአፍ መፍቻ ቋንቋ መማር ትምህርታዊ(ፔዳጎጂ) ጠቀሜታ ስለአለውና ብሔር/ብሔረሰቦች በራሳቸውን ቋንቋ የመጠቀም መብታቸውን ስለሚያረጋግጥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትና ተመጣጣኝ ስልጠና በብሐየር/ብሄረሶቦች በራሳቸው ቋንቋ ይሰጣል፡፡ይላል፡፡ 

 ይህን በይበልጥ ግልፅ ለማድረግ የትምህርት ሚኒስቴር የካቲት 1994 ዓ.ም ባሳተመው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲና አተገባባሩ በሚል ሰነድ ገፅ 34 ባፍ ቋንቋ መማር ያለውን ጠቀሜታ እንዲህ ገልጾታል፡፡

  1. ቋንቋ አንድ ህዝብ የሚማርበት ብቻ ሳይሆን የሚታወቅባትም ምልክት ጭምር ነው፣ በቋንቋው ማንነቱ ይታወቃል፡፡
  2. በራስ ቋንቋ በመማር ትምህርቱን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ ቋንቋ ካለመቻል የሚመነጭ ችግር አይገጥምም፡፡
  3. ቋንቋውን በስራ ላይ በማዋል ከመረሳት ብሎም ከሞት ያድነዋል፡፡
  4. በራሳቸው ቋንቋ በመማራቸው ብሎም በእሱ በመታወቃቸው ከፍተኛ የክብር ህልና እርካታ ይሰማቸዋል፡፡ በራሳቸው የሚተማመኑና በማንነታቸው የሚኮሩ ዜጎች ይሆናሉ፡፡ በራስ መተማመን ደግሞ በትምህርት ከሚገኘው ችሎታ ጋር እየተዳመረ የዘለቄታው አስተማማኝ የሆነ ሥራ ለመስራት ያስችላል፡፡ በሚል ዘርዝሯል፡፡

 ከዚሁም በመነሳት በራስ ቋንቋ መማር ከፍ ሲል እንደተጠቀሰው መብት በመሆኑ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ20 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች የአንደኛ ትምህርት ይሰጣል፡፡ ለምሳሌ፡- በሐራሪ ክልላዊ መንግስት በአደሪኛ/ሐረሪ ቋንቋ/፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሶማልኛና አማሪኛ፣ በድሬደዋ ከተማ አስተዳደር በአማሪኛ፣ አፋን ኦሮሞና ሶማሊኛ ቋንቋዎች በማስተማሪያነት ያገለግለሉ፡፡

 በመሆኑም የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት(UNESCO) እያንዳንዱ ሰው አፍ በፈታበት ቋንቋው ቢማር ተገቢ መሆኑን ሰፊ እንቅስቃሴ የሚደረግበትን ሳይንሳዊ ሀቅ እና የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ አቅጣጫን እንዲሁም በተግባር በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ተግባራዊ የሆነውን ወደ ጎን በመተው በፊንፊኔ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አፋን ኦሮሞ የሆኑት ህፃናት ዛሬም እንደትላንቱ መብታቸው ተነፍጎ በአማርኛ መማር የግድ ሆኖባቸው ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ይህ የህዝቦችን ዲሞክረሲያዊ መብት ከማስከበር አኳያ ሲታይ ኢ-ዲሞክራሲያዊ በመሆኑ በአፋጣኝ ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡

 በአጠቃላይ አገራችን ካፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች፣ በፌደራልና በኦሮሚያ የወጡ ሕጎች ስንነሳ በፊንፊኔ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ሰብዓዊ መብቶችና ነፃነቶች ሊከበርላቸው እንደሚገባ እንገነዘባለን፡፡ በተጨማሪም ከታሪካዊና መልከዓምድራዊ ምክንያቶች ፊንፊኔ የኦሮሞ መሬት አንድ አካልና እምብርት በመሆኗ የኦሮሚያ ክልል እና የኦሮሞ ህዝብ በፊንፊኔ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ሊጠበቅ እንደሚገባ ለማመላከት ተችሏል፡፡

 ስለሆነም ከላይ የተዘረዘሩት በፌደራል ደረጃ የወጡት ህጎች ስለ ኦሮሞ ብሔር ወይም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ከተማ ላይ ያለው ጥቅምን በሚመለከት የተገለፁት ድንጋጌዎችን ስንመለከት፡- የኦሮሞ ብሔራዊ ጥቅምና የፖለቲካ ልዩ መብቶች፣ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምንና የመሳሰሉትን ጉዳዮች በተመለከተ እንዲሁም አስተዳደራዊ ጉዳዮች፣ የከተማው ወሰን በኦሮሚያ ክልል ስምምነት ብቻ የሚካለል መሆኑ፣ ክልሉ መቀመጫውን አዲስ አበባ የማድረግ መብት፣ ከክልሉ ለከተማው ህዝብ የሚገኙ አገልግሎቶች የክልሉ ነዋሪዎች የመጠቀም መብት፣ ከተማው ማንኛውም የልማት ሥራዎች በክልሉ ሊሰራ የሚችለው በቅድሚያ ከክልሉ ጋር በመመካከርና ክልሉ ሲስማማ መሆኑን ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡

3.5/ የፌደራል ሥርዓትና የልዩ ጥቅም ትግበራ የሀገራት ተሞክሮ 

 የትናንቶቹ ሀያላን ሀገራት በሀይልና በጦር ማንነትን ፍቀው ሰብዓዊነትን ድጠው ሀገር የገነቡበትና የመሰረቱበት አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ በማመን ያለፈውን ለማረም የነባር ተወላጆችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሕይወትን የተሻለ መብት ማረጋገጫ የህግ ማዕቀፍ ቀርፀው ለተግባራዊነቱ ደፋቀና በሚሉበት የዛሬዋ ዓለማችን በእኛ ደረጃ የዲሞክራሲና የፌደራል ስርዓት ባህል ግንባታ ጀማሪ ሀገር በፍፁም ሊጓዝበት የማይገባ ጎዳና መሆኑን ማብራሪያ አያስፈልገውም፡፡

ይህምበተመሳሳይ የታሪክ አጋጣሚ የተፈጠሩ ተመሳሳይ ክፍተቶችን ለመቅረፍ በተለየና አትኩሮትን በተላበሰ ጥልቅ መንፈስ የነባር ተወላጅ መብቶችን እና መሰል የፌደራል ስርዓት ትብብሮችን እና ግንኙነቶችን ከሀገራቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም የተገበሩትንና የዳበረ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የገነቡትን የዓለማችንን ሀገራት በህገመንግስት የሰፈረ የልዩ ጥቅም መግለጫና የጋራ አስተዳደር አሰራርን በዝርዝር የህግ ማዕቀፋቸው ምላሽ የሰጡበትን አሰራር እንድናይ ያስገድደናል፡፡ ለተሞክሮም የካናዳ፣ የስዊዘርላንድ፣ የቤልጂየም እንዲሁም የአሜሪካን የነባር ተወላጆች መብት የህግ ማዕቀፍ በአጭሩ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

 3.5.1 የካናዳ ተሞክሮ 

 . የቀደምት ህዝቦች የሀብት ተጠቃሚነት በካናዳ 

 በሰሜናዊ ካናዳ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ለውጥ በታየባቸው በ1950ዎቹ አካባቢ የቀደምት ህዝቦች የሀብት ተጠቃሚነት ብዙም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ አልነበረም፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው መንግስትና የቢዝነስ ካምፓኒዎች የኢንቬስትመንት ስራዎቻቸውን እስካከናወኑ ድረስ የቀደምት ህዝቦች በራሳቸው ጥረት በቅጥርና በሰብ-ኮንትራክተርነት ተጠቃሚ ይሆናሉ የሚል ሃሳብ ሰፍኖ ስለቆየ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ እንደታሰበው መቀጠል አልቻለም፡፡

ይባስ ብሎ የልማት እንቅስቃሴዎች ቀደምት ህዝቦችን ከሚተዳደሩበት ስራና ከመሬታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት መሆኑ ነው የተረጋገጠው፡፡ በመሆኑም የሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ በተፈጠረው የኢኮኖሚ መነቃቃትና እሱን ተከትሎ በመጣው ማህበራዊ ቀውስ ለቀደምት ህዝቦች መብት ትግል መጠናከር ምክንያት ሆነዋል፡፡

 ‹‹በታሪካዊ መሬታችን ላይ በሚደረግ እንቅስቃሴ ከሚመነጭ ሀብት ማህበረሰባችንን ለማልማት በሚያስችል መልኩ ተጋሪ መሆን አለብን›› የሚለው የቀደምት ህዝቦች ክርክር በካናዳ መንግስት ተቀባይነት እያገኘ በመምጣቱ 1960ዎቹና 1970ዎቹ በተሻለ መልኩ አሁን ላይ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ቀደምት ህዝቦችን የሀብት ተጋሪ ለማድረግ የተከናወኑት ተግባራት በዋናነት ሶስት ይዘቶች አሉት፡፡ 

 * የቀደምት ህዝቦችን መሬት የሚያለማ የትኛውም ካምፓኒ ለባለቤቶቹ ክፍያ እንዲፈፅም ይደረጋል

* የቀደምት ህዝቦችን ተጠቃሚ ለማድረግ የስልጠናና የስራ እድል ይመቻቻል

* ቀደምት ህዝቦች ከትልልቅ ካምፓኒዎች ጋር በሰብ-ኮንትራትነት እንዲሰሩ ይደረጋል

በነዚህ መንገዶች የሚገኝ ገንዘብን የካናዳ ቀደምት ህዝቦች በተለያየ መንገድ ጥቅም ላይ ሲያውሉት ይታያል፡፡ ለምሳሌ በሰሜን ኬቤክ በዚህ መንገድ የሚገኝ ገንዘብ ለግለሰብ ዜጎች ለሚደረጉ ክፍያዎችና ለመሰረተ ልማት ግንባታዎች ይውላል፡፡

 በተጨማሪም እነኚህ የቀደምት ህዝቦችን ጥቅም የማስጠበቂያ መንገዶች ለበርካታ በቀደምት ህዝቦች ባለቤትነት የሚተዳደሩ ካምፓኒዎች መመስረት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ካምፓኒዎቹ ቀስ በቀስ የመዋዕለ ነዋያቸውን የፍሰት አድማስ ከማዕድን ቁፋሮ ወደሌሎች ዘርፎች ማስፋት ችለዋል፡፡

 በአጠቃላይ የካናዳ መንግስት ከቀደምት ህዝቦች ጋር የሚደረግ የሀብት መጋራት ስራዎችን እንዲሰራ በተለያዩ ምክንያቶች ድጋፍ ይሠጣል፡፡ የቀደምት ህዝቦች የሀብት ይገባኛል ጥያቄን በመመለስ የልማት ስራዎችን ማፋጠን መቻሉን መረዳቱ አንዱ ምክንያት ሲሆን የቀደምት ህዝቦች ለመብታቸው መከበር መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውና የሀብት መጋራት ጥያቄዎቻቸውም ከእለት እለት በፍርድ ቤቶች ተቀባይነት ማግኘታቸው ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ የቀደምት ህዝቦች የሀብት ክፍፍል ጥያቄ እያደር የህዝቦቹ የሞራል መብት መሆኑና በተለያዩ የመንግስት አካላት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ የቀደምት ህዝቦች ጥያቄን ለመመለስ መንገድ ከፍቷል፡፡

 . የካናዳ የፌደራል ስርዓትና የኬቤክ ጉዳይ 

 ኩቤክ ካናዳ ካሏት አስራ ሶስት ግዛቶች መካከል አንዷ ነች፡፡ ኩቤክ ያላት ህዝብ የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ህዝብ ከመሆኑ አንፃር ግዛቷ ከማዕከላዊው የካናዳ መንግስት ጋር ያላት ግንኙነት ምን መምሰል አለበት የሚለው ጉዳይ ለዘመናት አጨቃጫቂ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የኩቤክ ጉዳይ በካናዳ ፖለቲካ ውስጥ አነጋጋሪ አጀንዳ መሆን የጀመረው በ1960ዎቹ ነበር፡፡ በወቅቱ ‹‹ፀጥተኛው አብዮት›› (Quite Revolution)በመባል የሚታወቀው ይህ የፈረንሳይኛ ተናጋሪ የፖለቲካ ምሁራን የጀመሩት እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ያተኩር የነበረው ኩቤክ በካናዳ ፌደራላዊ ስርዓት ውስጥ ያላት ሚና ላይ ሲሆን በተለይም እንቅስቃሴው ኩቤክን ልዩ ህገመንግስታዊ መብቶችን በማጎናፀፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በተለይም ኩቤክን ማዘመንና በሌሎች አካላት ሲከናወኑ የነበሩ ተግባራትን የኩቤክ መንግስት በኩቤክ ህዝብ ፍላጎት አማካኝነት ማከናወን የሚችልበትን መንገድ መፍጠር የአብዮቱ አላማ ነበር፡፡

 የኩቤክ የልዩ መብት ጥያቄ በፖለቲካው መስክ ሲብላላ ቆይቶ የኩቤክ ፖለቲከኞች ‹‹ሉዓላዊ ጥገኝነት›› (Soveriegn  Association) የሚል የመፍትሄ ሀሳብ አቀረቡ፡፡ ይህ የፖለቲካ አማራጭ በኋላ ላይ ሲቀነቀን ከነበረው የሙሉ ነፃነት (Secession) አማራጭ ለዘብተኛ የተባለ አማራጭ ቢሆንም በኩቤካውያንም ሆነ በአጠቃላይ ካናዳውያን ዘንድ ብዙም ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የኋላ ኋላ የኩቤክ ክልላዊ መንግስት ኩቤካውያን ህዝበ-ውሳኔ እንዲያደርጉ በወሰነው መሰረት በግንቦት ወር 1980 በተካሄደ የድምጽ አሰጣጥ የሉዓላዊ ጥገኝነት ሀሳብ 60%፣ በ40% በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡

 በ1982 በተያያዥነት በተካሄደ የፌደራል ስርዓት ለውጥ የኬቤካውያን አቋም እንዲቀየር ምክንያት ሆነ፡፡ ለውጡ ኩቤክን እንደአንድ ብሄር ከመቁጠር ይልቅ ካናዳን በግለሰቦች መብት ዙሪያ የተመሰረተች ሀገር እንድትሆን አድርጓታል፡፡ ለውጡ ‹‹ህብረ-ብሄራዊነት›› የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ በካናዳ ከሚኖሩና የፈረንሳይም ሆነ የእንግሊዝ ዝርያ ከሌላቸው ግለሰቦች ጋር አዛምዶ በመተርጎሙ የኩቤካውያንን የሁለት ብሄሮች ትግል ሀሳብ በተለይም ፈረንሳይኛ ተናጋሪ የሆኑት ኩቤካውያን በእንግሊዘኛ ተናጋሪ ካናዳውያን ተውጠናል የሚለውን ክሳቸውን ያዳፈነ ነበር፡፡ ኩቤክ የነበራት የህገ-መንግስት ማሻሻያ ጥያቄን በድምጽ የመሻር መብት (Veto right over constitutional reform) ቀለበሰ፡፡

 ቀጥሎ የመጣው የብራያን ሙልሮኒ መንግስትም በኩቤካውያን የህዝብ ተወካዮች ዘንድ በምክር ቤቱ ከፍተኛ ድጋፍ ስለነበረው የኩቤክን ጉዳይ አጥብቆ ያዘ፡፡ በመቀጠልም Meech Lake Accord የተባለ ያልተሳካ ህግ የማጽደቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ የህግ ማዕቀፍ ሁሉንም የኩቤክ የመብት ጥያቄ የሚመልስ ባይሆንም የኩቤክ መንግስት በ1982 የተቀለበሱትን የኩቤክ ልዩ መብቶች እንደመመለሻ መንገድ የተመለከተ ነበር፡፡ የኩቤክ መንግስት ፍላጎቶችም፡-

* የኩቤክ እንደ ልዩ ማህበረሰብ የመታየት እውቅና፣

* ስደተኞችን በመለየትና በመቀበል ረገድ የተሻለ የመወሰን አቅም (ኩቤካውያን የካናዳ መንግስት ሆን ብሎ እኛን ለማስዋጥ ሌላ ዝርያ ያላቸውን ሰዎች ይቀበላል የሚል ሮሮ ነበራቸው)፣

* ኩቤካውያን ዳኞች በጠቅላይ ፍርድ ቤት በሚመደቡበት ሂደት የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ፣

* የፌደራል መንግስት የገንዘብ አጠቃቀም ስልጣን እንዲወሰንና

* የኩቤክ ህገመንግስት ማሻሻያ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት እንዲመለስ የሚሉት ነበሩ፡፡

 ይህ ማዕቀፍም ሆነ ቀጥሎ የመጣው Charlottetown Accord ለኩቤክ ያልተገባና ለሌሎች ግዛቶች ያልተሰጡ ጥቅሞችን በሚሉና በሌሎች ምክንያቶች ሳይፀድቁ ቀርተዋል፡፡

 በአጠቃለይ መልኩ ሲታይ በተለያየ ጊዜ ኩቤክን ያስተዳደሩ መንግስታት ‹‹በደጋፊ ፌደራላዊ ጽንሰ-ሀሳብ›› (Concept of Subsidary Federalism) ተፅዕኖ ያደረባቸው ነበሩ፡፡ ራሳቸውን እንደዋነኛ/ግንባር ቀደም የመንግስት ስራ ፈፃሚ (ከባህል፣ ትምህርት የተፈጥሮ ሀብትና ማህበራዊ አገልግሎት አስተዳደር አንፃር) የሚቆጥሩና የፌደራል መንግስት ሚና ደግሞ ደጋፊነት ብቻ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

ስለዚህ የፌደራል መንግስት የኩቤካውያንን ጉዳይ ለኩቤካውያን በመተው ለሁሉም ግዛቶች ተመሳሳይ ህግ ከማውጣትና የበጀት አጠቃቀማቸውን ከመወሰን መታቀብ እንዳለበት ያምኑ ነበር፡፡ ነገር ግን የካናዳ መንግስታት ያልተማከለ አስተዳደር የማስፈንና የኩቤክን የራስን በራስ የማስተዳደር መብት አለመቀበል ኩቤካውያን የፌደራል መንግስት የደጋፊነት ሚና ብቻ ይኑረው የሚለውንም ሆነ ኩቤካውያን በማንነታቸው ሊከበሩ/እውቅና ሊሰጣቸው ይገባል የሚሉትን ጉዳዮች መቀበል ተስኗቸው ቆይተዋል፡፡

 የዚህ የካናዳ መንግስታት አቋም ነፀብራቅ የሆነው የ1982 ህገመንግስታዊ ለውጥም ፌደራላዊ ስርዓት በካናዳ የነበረውን ገጽታ በግለሰባዊነት ላይ ባተኮረ አዲስ የፖለቲካ ቅኝት የተካ ነበር፡፡ ለውጡ ካናዳ በሁለት ብሄሮች መፈቃቀድ ላይ የተመሰረተች ሀገር የመሆኗን እውነታ ከህገመንግስታዊ ስርዓትና አስተሳሰብ ውጪ አደረገው፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ግን የካናዳ ህገመንግስት ካናዳ ፌደራላዊ ቅርጿን ይዛ እንድትጓዝ አስችሏል፡፡

 በርግጥ የኩቤክ መንግስታትም ቢሆኑ የ1982ቱን ለውጥ አምርረው የተቃወሙት ለግለሰብ መብቶች ካላቸው ጥላቻ የተነሳ ሳይሆን ለውጡ የተካሄደበትን መንገድና መብቶችን ለማክበር የተመረጠውን መንገድ ባለመቀበል ነበር፡፡ ከ1982ቱ ለውጥ በፊትም ቢሆን ኩቤክ ለግለሰቦች መብት ያላት ቁርጠኝነት በምንም መልኩ የሚያጠያይቅ አልነበረም፡፡

 በዚህም ምክንያት ነበር Charter of Human Rights and Freedom ሲፀድቅ ኩቤካውያን ያልተቃወሙት፡፡ ነገር ግን የመብቶች ትርጓሜም በጠቅላይ ፍርድ ቤት ከሚከናወን ይልቅ በህገመንግስት ተርጓሚ ፍርድ ቤት ቢከናወን የኩቤክ መንግስታት ምርጫ ነበር፡፡ ለምሳሌ የፌደራላዊ ስርዓት አተገባበርና የግለሰብ መብት አጠባበቅ የሚጣጣሙበትም መንገዶች ቢፈጠሩ ኖሮ ምርጫቸው ነበር፡፡ ኩቤክን እንደልዩ ማህበረሰብ/ግዛት መቁጠርና ኩቤክ በ1975 ያጸደቀቻቸውን የኩቤክ Charter of Human Rights and Freedom ከ1982ቱ የፌደራል ለውጥ ቻርተር ይልቅ የማጉላት ምርጫዎች ነበሩ፡፡ የነዚህ እርምጃዎች ቀደም ብሎ አለመወሰድ የኩቤክን ችግር ሲያወሳስበው ቆይቷል፡፡

 ኩቤካውያን በ1995 ካደረጉት ህዝበ-ውሳኔ በኋላ ሁለት ነገሮችን መረዳት ችለናል፡፡  የኩቤካውያን የራሳቸውን የፖለቲካ ማህበረሰብ የመፍጠር ፍላጎት በዋናነት የመነጨው በዘር ሀረግ ላይ ከተመሰረተ ብሔርተኝነት አለመሆኑ አንዱ ነው፡፡ ይልቁንም ኩቤክ ቀስ በቀስ የራሱ ተቋማት ያሉት ህብረተሰብ በራሱ ማህበራዊ አደረጃጀትና ባህል፣ ብሄራዊ ግቦችና የተለያዩ ፖሊሲዎች ያሉት ከክልልነት ይልቅ ወደሀገርነት የተጠጋ ማህበረሰብ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ኩቤክ ከ1960ዎቹ በኋላ በህግ የበላይነትና ፓርላሜንታዊ ስርዓት መገለጫው የሆነ በፖለቲካው ስርዓት ውስጥም ፍትሀዊነትና የሀሳብ ብዙሀነትን ማስፈን በሚያስችል መልኩ ራሱን እንደአንድ ዘመናዊ የፖለቲካ ማህበረሰብ ሲያዋቅር ቆይቷል፡፡

 ሁለተኛው መረዳት የምንችለው ጉዳይ ደግሞ የካናዳ መንግስት የኩቤክን ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ለመመለስ የሄደባቸው መንገዶች አጠያያቂ ቢሆኑም እስካሁን የተወሰደውን ውሳኔ ጨምሮ ላለፉት ሰላሳና አርባ አመታት የኩቤክ መንግስት በክልሉ ህግ የማስፈፀም ሂደቶችን ማክበሩ የሚመሰገኑ ናቸው፡፡ በተለይም በተዋቀረው ፌደራላዊ ስርዓት መሰረት በፌደራል መንግስት ደረጃ ሁለት እኩል የህግ ቁመና ያላቸው ቋንቋዎች (እንግሊዘኛና ፈረንሳይኛ) ጥቅም ላይ በሚውሉበት ሂደት ውስጥ የኩቤካውያን በራሳቸው ግዛት ፈረንሳይኛን እንደቀዳሚ ቋንቋ የመጠቀም መብታቸውን ለማረጋገጥ የተካሄደበት የብልሀት መንገድ (pragmatism)የሁለቱን አካላት ቅራኔ የመፍታት ሁነኛ ምሳሌ ነው፡፡

 3.5.2 የስዊዘርላንድ ተሞክሮ  

 ስዊዘርላንድ ከነበረችበት የርስ በርስ ጦርነት ወጥታ በ1948 እንደ ፌደራላዊ ሀገር ስትመሰረት የፌደራል ስርዓቱ አሀዳዊ ስርዓተ መንግስትን ለመመስረት ፍላጎት የነበራቸውን ፕሮቴስታንት ክርስቲያኖችና የቀድሞ ኮንፌደሬሽኑን ለማስቀጠል የፈለጉ ወግ አጥባቂ ካቶሊኮችን ለማስታረቅ የተወሰደ የመፍትሄ እርምጃ ነበር፡፡ በተጨማሪም የፌደራል ስርዓቱ የአራቱን ብሔራዊ ቋንቋዎችን (ፈረንሳይኛ፣ ጣሊያንኛ፣ ጀርመንኛ ሮማንሽ) የማቻቻል አላማ ነበረው፡፡

 . የህገመንግስት ማሻሻያዎች  

 ፌደራላዊት ስዊዘርላንድ ከተመሰረተች በኋላ እስካሁን ድረስ ህገመንግስቱ ሁለት ጊዜ ብቻ ሙሉ በሙሉ የተከለሰ ሲሆን በተወሰነ መልኩ ግን ከ100 ጊዜ በላይ ተሻሽሏል፡፡ ህገመንግስቱ በ1848 ሲፀድቅ ዋነኛ አላማው ክልሎችን በማጠናከር ከማዕከላዊው መንግስት የተሻለ አቅም እንዲኖራቸው ያለሙ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የተደረጉት የህገመንግስት ማሻሻያዎች በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተደረገው ጦርነት ወቅት የታየው የስዊዘርላንድ ደካማ የጸጥታ ፖሊሲን ለመቅረፍ የማዕከላዊውን መንግስት ስልጣን ያሻሻሉ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ነበር የማሻሻያዎቹ መፈክር ‹‹አንድ ጦር፣ አንድ ኢኮኖሚ፣ አንድ ህግ›› የሚል ነበር፡፡

 በስዊዘርላንድ በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ሲቪል ማህበራት ወቅታዊ ማህበራዊ ጉዳዮችን ላይበማተኮር የህገመንግስት ማሻሻያ ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡ ነገር ግን ከ1948 ጀምሮ ከቀረቡ 142 የማሻሻያ ጥያቄዎች ውስጥ አስራ አንዱ ብቻ ተቀባይነት አግኝተዋል፡፡ ነገር ግን ቀድመው ውድቅ የተደረጉ ጥያቄዎች የኋላ ኋላ በህገመንግስታዊ ለውጦች ላይ በሁለት መልኩ አስተዋጽዖ ነበራቸው፡፡ አንደኛው ውድቅ በተደረጉ ጥያቄዎች ላይ በመመስረት የፌደራል ምክር ቤቱ ሲያወጣቸው በነበሩ የማሻሻያ ማዕቀፎች አማካኝነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መንግስት የተነሱትን ሀሳቦች በኋላ ላይ በህዝበ-ውሳኔ በተደረጉ የህገመንግስታዊ ማሻሻያዎች ውስጥ እንዲካተቱ በማድረጉ ነበር፡፡

 . የባህልና የቋንቋ ጉዳዮች  

 የስዊዘርላንድ ህገመንግስት ለማእከላዊ መንግስቱ የባህል ልዩነትን በተፈቀደለት የህግ ማዕቀፍ ውስጥ የማበረታታት ሀላፊነት ጥሎበታል፡፡ ከቋንቋም አንፃር ማዕከላዊ መንግስቱ በተለየዩ የቋንቋ ተናጋሪዎች መካከል የተሻለ መግባባት እንዲኖር የመስራት ሀላፊነት አለበት፡፡ ነገር ግን ዩንቨርስቲዎችን ጨምሮ የትምህርት ተቋማት የሚጠቀሙበትን ቋንቋን መምረጥ በተመለከተ እያንዳንዱ ክልል የሚወሰንበት ጉዳይ ነው፡፡

 በነዚህ ህገመንግስታዊ መርሆዎች ምክንያት ስዊዘርላንድ አራት ኦፊሴላዊ ቋንቋዎች እኩል የህግ እይታ ያላቸው ሲሆን የትርጓሜ ልዩነት ቢፈጠር እንኳን በእያንዳንዱ ቋንቋ ያለው ትርጉም በህግ ፊት እኩል ነው (If there are different meanings or different interpretations, then each language has to be considered as an originl and authoritative text)

ይሁንና ሶስቱ ማለትም ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛና ጣልያንኛ እኩል ደረጃ ሲኖራቸው ሁሉም ህጎች ግን ወደ አራተኛው ሮማንሽ ቋንቋ አይተረጎሙም፡፡ የሮማንሽ ቋንቋ የተለያዩ ዘዬዎች ስላሉት በአንድ አመት የሚወጡ ህጎች በአንዱ የሮማንሽ ዘዬ የሚተረጎም ሲሆን በቀጣዩ አመት ደግሞ በሌላ ዘዬ ታትሞ የሚዋጣ/የሚወጣ ይሆናል፡፡

 ለዚህም የሚሰጠው ምክንያት ወጪን ለመቀነስ የሚል ነው፡፡ ማንኛውም የፌደራል መንግስት ሰራተኛ ራሱን ለመግለፅ በራሱ ቋንቋ የሚጠቀም ሲሆን እንደፌደራል መንግስት ሰራተኛነቱ ግን ቢያንስ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛና ጣልያንኛ ቋንቋዎችን መረዳት መቻል ይኖርበታል፡፡ ይህንኑ የሚያንፀባርቅ አንድ የተለመደ የጣልያንኛ ቋንቋ ተናጋሪ የፓርላማ አባላት አባባል አለ፡

 ለቋንቋህ ውበት የምትጨነቅ ከሆነ በጣልያንኛ ተናገር፤ የፓርላማ አባላት እንዲሰሙህ ከፈለክ በፈረንሳይኛ ተናገር፤ የሚሰሙህ ሰዎች እንዲረዱህ የምትፈልግ ከሆነ ግን በጀርመንኛ ተናገር፡፡

 በብሔራዊ ካውንስል (የታችኛው ምክር ቤት) ውይይት በሚደረግበት ወቅት በሌሎችም ቋንቋዎች የትርጉም አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ክልሎች ኦፌሴላዊ ቋንቋ የመምረጥ ሙሉ ነፃነት አላቸው፡፡ ሁለት ቋንቋዎች በስፋት የሚነገርባቸው ክልሎች ሁለት ኦፌሴላዊ ቋንቋዎች ሲኖሯቸው ሶስት ቋንቋዎች ማለትም ጀርመንኛ፣ ጣልያንኛና ሮማንሽ ኦፊሴላዊ ቋንቋዎች የሆኑበት ግሪሰን የሚባል ክልል ይገኛል፡፡

 . የክልሎች ስልጣን  

 ክልሎች ራሳቸውን በፈለጉት መንግስታዊ መዋቅር ማደራጀት፣ እንዲሁም በራሳቸው ከባቢያዊ የራስ ገዝነት (local autonomy) አረዳድና የፍትህ ስርዓት መመራት መቻላቸውን ታሪካዊ የዲሞክራሲያዊ አስተዳደር ስርዓታቸውን እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል፡፡

 ህገመንግስታዊና ህጋዊ ስርዓቶቻቸውም የሀይማኖቶቻቸው፣ የቋንቋቸው፣ የአለምአቀፍ ጉርብትና መገለጫዎቻቸው ከመሆንም ባሻገር የገጠር አኗኗር ዘዬያቸው፣ የመሳፍንትነት ትሩፋቶቻቸው አልያም የንግድ ልምዳቸው መገለጫዎቻቸውም ጭምር ናቸው፡፡ ክልሎቹ የነበራቸው የራሳቸውን ዲሞክራሲያዊ እሴት የመገንባት መብታቸው የተረጋገጠ ሲሆን ብዙዎቹ የስዊዘርላንድ ዲሞክራሲያዊ እሴቶችም የመነጩት ከክልሎች ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል የሴቶችን የመምረጥ መብት በቅድሚያ ያረጋገጡት የፈረንሳይኛ ተናጋሪ ክልሎች ሲሆኑ በመቀጠልም ሌሎች ክልሎችና የማእከላዊ መንግስቱ ይህንኑ ፈለግ ተከትለዋል፡፡

 3.5.3 የቤልጂየም ፌደራላዊ ስርዓት የመንግስት ተሞክሮ  

 . የቤልጂየም የስልጣንና ሀብት ክፍፍል፣ ቋንቋ አጠቃቀምና የዋና ከተማ አስተዳደር

ቤልጂየም በአለማችን ከሚገኙ የፌደራላዊ መንግስት ስርዓትን ከሚከተሉ ሀገሮች አንዷ ስትሆን ህገመንግስታዊ የንጉሳዊ ስርዓትን ከፓርላሜንታዊ የመንግስት ስርዓት ጋር አጣምራ ትጠቀማለች፡፡ ከአጠቃላይ 11,190,845 ህዝብ የፍለሚሽ ክልል 6,437,680 ዋሎንያ 3,585,214 እና የብራሰልስ አስተዳደራዊ ክልል ደግሞ 1,167,951 ህዝብ ይኖርባቸዋል፡፡

 የሀገሪቷ ህገመንግስት ቀደምት ከሚባሉት ህገመንግስቶች አንዱ በመሆን በ1831 እ.ኤ.አ የፀደቀ ቢሆንም ሀገሪቷን የፌደራላዊ ስርዓት ቅርፅ የሰጣት ግን በ1970 እ.ኤ.አ የተደረገው መዋቅራዊ ህገመንግስታዊ፣ የፖቲካዊ ስርዓት ለውጥ እ.ኤ.አ በ1993 በፓርላማው ከፀደቀ በኋላ ነበር፡፡ ቤልጂየም ወደ ፌደራላዊ ስርዓት እንድትለወጥ እንደ ዋና ምክንያት የነበረው በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ እና በደች ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ክፍሎት መካከል በዋና ከተማዋ ብራሰልስ ተከስቶ የነበረው ግጭት ነበረ፡፡

 በአሁኑ ጊዜ የቤልጂየም የፌደራል ስርዓት 3 አስተዳደራዊ መዋቅሮች ያለው ሲሆን እነዚህም የፌደራል መንግስት፣ የማህበረሰብ እና ክልላዊ አስተዳደር የተከፈሉ ናቸው፡፡ የማህበረሰብ አስተዳደር ክፍሎቹ የፍለሚሽ፣ የፈረንሳይ እና የጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያካተቱ ናቸው፡፡ ሶስቱ የአስተዳደር ክልሎች ደግሞ ፍለሚሽ፣ ዋሎን እና የብራሰልስ ከተማ ክልል ናቸው፡፡ ሶስቱም የአስተዳደር ክልሎች የራሳቸው የክልል ምክር ቤት ሲኖራቸው በፌደራል መንግስት ውስጥም በህግ አውጪው እና አስፈፃሚው ክፍል በተለየ ቀመር የተሰራ ውክልና አላቸው፡፡

ለምሳሌ፡- በፌደራሉ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አጠቃላይ የሚኒስትሮች ብዛት ከአስራ አምስት የማይበልጥ ሲሆን የደች እና የፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ተወካይ ሚኒስትሮች ቁጥር እኩል መሆን ይኖርበታል፡፡ የፌደራሉ መንግስት ወሳኝ የሚባሉ የውጭ ጉዳይ፣ መከላከያ፣ ፍትህ፣ ገንዘብ እና ማህበራዊ ደህንነት ጉዳዮች ላይ ህገመንግስታዊ ስልጣን ሲኖረው በሌሎች ፌደሬሽኖች ባልተለመደ ሁኔታ ሶስቱ የማህበረሰብ እና ክልላዊ አስተዳደሮችን የራሳቸውን የውጭ ግንኙነት እንዲያደርጉ ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡

 በደች ፈረንሳይ እና ጀርመን ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ አስተዳደሮች ሙሉ በሙሉ በክልሎቹ የስልጣን ቁጥጥር ስር ሲሆኑ የዋና ከተማዋ ብራሰልስ ክልል አስተዳደር ግን የራሱ የሆነ በሕግ የተቀመጠ ልዩ ተቋማዊ የአስተዳደር ስርዓት አለው፡፡ ከሶስቱ ክልላዊ አስተዳደሮች መሀል በህዝብ ብዛት እና የቆዳ ስፋት ትልልቆቹ ፍላንደርስ እና ዋሎንያ እያንዳንዳቸው አምስት አምስት አካባቢያዊ የአስተዳደር መዋቅሮች ሲኖሯቸው ብራሰልስ አስተዳደር ደግሞ ወደ አስራ ዘጠኝ የከተማ አስተዳደር ክፍሎች የተከፈለ ነው፡፡ የቤልጂየም ዋና ከተማ ብራሰልስ በደች ቋንቋ ተናጋሪ የፍለሚሽ ክልል ማለትም ፍላንደርስ ተከባ የምትገኝ ከተማ ስትሆን የከተማዋ የስራ ቋንቋ ግን ፈረንሳይኛ እና ደች እንዲሆን በህግ ተደንግጓል፡፡

 . የብራሰልስ አስተዳደር እና የቋንቋ አጠቃቀም ስርዓት  

 ከአስራ አንድ ሚሊየን በላይ ከሚሆነው አጠቃላይ የቤልጂየም ህዝብ ወደ 59% የሚሆነው የፊለሚሽ ማህበረሰብ አካል እና የደች ቋንቋ ተናጋሪ ሲሆን 40% የሚሆነው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ እንዲሁም 1% የጀርመንኛ ቋንቋ ተናጋሪ ነው፡፡ በደች ቋንቋ እና ፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪ ቤልጂየማውያን በታሪክ ሂደት የተፈጠረውን የቋንቋ፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ደረጃ ልዩነት በዘመናት ሂደት በዋና ከተማው የፖለቲካ እና ባህላዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ገጽታ ላይ የራሱን አሉታዊ አሻራ አስቀምጧል፡፡

በመሆኑም እ.ኤ.አ ከ1830 ጀምሮ እስከ 20ኛው ክ/ዘመን ድረስ ባለው የታሪክ ሂደት የብራሰልስ ከተማ ከብዙሀን የደች ቋንቋ ተናጋሪ ህዝብ መቀመጫ ከተማነት ወደ ፈረንሳይኛ የተጫነው የሁለት ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች ከተማነት ተለውጣለች፡፡ ይህ ለውጥም ፈረንሳይኛ ዋናው የአስተዳደር፣ ፖለቲካእና ትምህርት ቋንቋ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን በተቃራኒው የደች ቋንቋ የዝቅተኛ ማህበራዊ ደረጃ እና ክብር መገለጫ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በተጨማሪም የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ቤልጄማውያን በብዛት ወደ ከተማ መፍለስ እና የከተማዋ ድንበር እጅግ እየሰፋ መሄድ የብራሰልስን ከተማ ከደች ወደ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከተማነት ሽግግር አፋጥኖት አልፏል፡፡

 በጊዜ ሂደትም የደች ቋንቋ ተናጋሪዎች ከፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪዎች እኩል በመንግስታዊ ተቋማት ለመገልገል በሚያደርጉት ጥረት ፈረንሳይኛን በመማራቸው የከተማዋ የሁለት ቋንቋ ተናጋሪዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም በፍጥነት እያደገ ከመጣው የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰብ ጋር ሊስተካከል ባለመቻሉ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የፈረንሳይኛ ቋንቋን ብቻ የሚናገሩ ተናጋሪዎች ቁጥር በእጅጉ ሊበልጥ ችሏል፡፡

 በጂኦግራፊያዊ አቀማመጧ ሙሉበሙሉ የደች ቋንቋ ተናጋሪዎች ክልል ውስጥ የምትገኘው ብራሰልስ በጊዜ ሂደት ብዙ ፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚኖሩባት ከተማ መሆኗ ብዙ የቤልጂየም ደች ፖለቲከኞች የባህላዊ አሉታዊ ተፅዕኖ መገለጫ እንደሆነ ስለሚያምኑ የደች ቋንቋ ተናጋሪ የከተማዋ ክፍል ለብቻው እንዲካለል እስከመጠየቅ ደርሰው ነበር፡፡ ብራሰልስ በአሁኑ ሰዓት የቤልጂየም ብቻ ሳይሆን የአውሮፓ ዋና ከተማ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የቋንቋ አጠቃቀሟ እየተለወጠ ይገኛል፡፡

በመሆኑም 63% ከከተማዋ ነዋሪዎች ፈረንሳይኛ 20% ደች እና 2.5% እንግሊዘኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ሲሆን 29.7% የሚሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች የእንግሊዘኛ ቋንቋን መናገር ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ደች እና ፈረንሳይኛ ቋንቋ በእኩል የስራ ቋንቋ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ ከአጠቃላዩ ቤልጂየም 59% ፍለሚሾች ፈረንሳይኛ ቋንቋ መናገር ሲችሉ 19% ዋሎናውያን ብቻ የደች ቋንቋ መናገር ይችላሉ፡፡

 . ብራሰልስ ዋና ከተማ /Brussels-capital region/  

 ብራሰልስ የሚባለው የአስተዳደር ክፍል ሁለት ነገሮችን የሚወክል ሲሆን በቤልጂየም ህገመንግስት አንቀጽ 194 በተቀመጠው መሰረት መካከለኛው የብራሰልስ ክልል እንደ ቤልጂየም ዋና ከተማነት እንዲያገለግል ሲካለል የተቀረው ዙሪያ የከተማ አካባቢ እንደ ፍላንደርስ እና ዋሎንያ ሁሉ የራሱ ክልላዊ አስተዳደር መንግስት ሆኖ እ.ኤ.አ በ1989 እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡

የመካከለኛው ብራሰልስ ከተማ የፌደራል መንግስቱ ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈፃሚ እና ህግ ተርጓሚ ተቋማት፣ መቀመጫ ብቻ ሳይሆን የሁለቱ ክልላዊ መንግስታት ማለትም ዋሎንያ እና ፍላንደርስ መንግስታት መቀመጫም ነው፡፡ በተጨማሪም የፈረንሳይ እና ፍለሚሽ ማህበረሰብ አስተዳደር ተቋማት መቀመጫም በመሆን ያገለግላል፡፡ በሌላ በኩልም እ.ኤ.አ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ይህ የከተማዋ ክፍል የአውሮፓ ሕብረት ተቋማት መቀመጫ እና ዋና ከተማም በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡

 የብራሰልስ ከተማ ከ19ኙ የብራሰልስ ክልል አስተዳደር ከተማ አካባቢዎች አንዷ ስትሆን የህዝብ ብዛትዋ ከ170 ሺህ በላይ ሆኖ 32.6 ስኩዬር ኪ.ሜ ስፋት አላት፡፡ በአስተዳደር ረገድም ከተማዋ ከብራሰልስ ክልል መንግስት ምክር ቤት በሚመረጥ ከንቲባ ትተዳደራለች፡፡ ዋና ከተማዋን ጨምሮ ለ19ኙም የብራሰልስ ክልላዊ መንግስት የከተማ አስተዳደሮች ፈረንሳይኛ እና ደች ቋንቋዎች የስራ ቋንቋ በመሆን ያገለግላሉ፡፡ በመሆኑም በከተማዋ የሚገኙ የመንገድ ስሞች፣ የመንገድ ምልክቶች፣ ማስታወቂያዎች በሁለቱም ቋንቋዎች ተፅፈው ይገኛሉ፡፡

 የብራሰልስ ክልል ከተማ አስተዳደር እንደ ዋሎንያ እና ፍላንደርስ ክልላዊ መንግስታት ሁሉ በፌደራል ስርዓቱ የታቀፈ 3ኛው ክልላዊ አስተዳደር ሆኖ በህገ መንግስቱ የተዋቀረ ሲሆን የብራሰልስ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ክልል የሚገኘው በፍላንደርስ ክልል ውስጥ ነው፡፡

 ይህ ክልል 1.8 ሚሊየን በላይ ህዝብ የያዘ ክልል ሲሆን 162 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ስፋት አለው፡፡ በአስተዳደር ረገድም 89 አባላት ያሉት ፓርላማ ሲኖረው በሕግ በተደነገገው መሰረት ከ89 የፓርላማ አባላት ውስጥ 72 ፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ እና 17 የደች ቋንቋ ተናጋሪ የምክር ቤት አባላት ይኖሩታል፡፡ በተጨማሪም 8 አባላት ያሉት ክልላዊ የሥራ አስፈፃሚ ካቢኔ ሲኖረው ሁለት ከፈረንሳይ ሁለት ከደች ቋንቋ ተናጋሪዎች ሚኒስትሮች እና ሁለት ፈረንሳይኛ ሁለት ደች ቋንቋ ተናጋሪ ፀሀፊዎች እንዲሆኑ በህግ ተደንጓል በተያያዘም በህግ ባይወሰንም ከልምድ በተደጋጋሚ እንደሚሆነው እስከ ዛሬ ባለው አሰራር የካቢኔው ሰብሳቢ ሚኒስቴር ፕሬዝዳንቶች የሁለቱም ቋንቋ ተናጋሪዎች ሲሆኑ ይታያል፡፡ በተጨማሪም ከ72 የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪ የብራሰልስ ክልል ፓርላማ ተወካዮች ውስጥ 19 ያህሉ የፌደራሉ የፈረንሳይ ማህበረሰብ ፓርላማ አባላት በመሆን ይሰራሉ፡፡

 . በብራሰልስ ዋና ከተማና በብራሰልስ ክልላዊ መንግስት መካከል ያሉ ግንኙነቶች  

  1. አስተዳድራዊ መዋቅሮች

 የብራሰልስ ዋና ከተማ በፍላንደርስ ክልል ውስጥ በሚገኘው የብራሰልስ ክልላዊ አስተዳደር መሀል እንደመገኘቷ የሁለቱም ክልላዊ መንግስታት መቀመጫ በመሆን ታገለግላለች፡፡ የከተማዋን አስተዳደር ፖለቲካዊ ሚዛን በማስጠበቅ ከንቲባውን የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት እንዲመርጠው ቢደረግም የመጨረሻው ሹመት የሚፀድቀው ግን የብራሰልስ ክልላዊ መንግስት እንዲሆን ተደርጓል፡፡ እ.ኤ.አ ከ1830 ጀምሮ ከተማዋ በ18 ከንቲባዎች የተዳደረች ሲሆን ከንቲባዎች የስልጣን ዘመን ስድስት ዓመት ነው፡፡

 በሌላ በኩል በብራሰልስ ከተማ ክልል የተቋቋመው የጋራ ማህበረሰብ ኮሚሽን ደግሞ የፍላሚሽ እና ዋሎንያ የጋራ ማህበረሰባዊ ጉዳዮችን የሚመለከት ተቋም እንዲሆን የተቋቋመ ምክር ቤት ሲሆን በተለይ የሁለቱን ማህበረሰብ የሚመለከቱ የፖሊሲ ጉዳዮችን እንዲከታተል ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ በተጨማሪም የቤልጂየም ህገመንግስታዊ ፍርድ ቤት በሶስቱ ማህበረሰቦች መካከል የሚነሱ ጉዳዮችንና እንዲመለከት እና የቋንቋ አለመግባባቶችን እንዲፈታ ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡

 በፌደራሉ መንግስት የተቋቋመው የብራሰልስ ከተማ ክልል እና የብራሰልስ ከተማ ትብብር ኮሚቴ አራት የፌደራሉ መንግስት ሚኒስትሮችን እና አራት የብራሰልስ ከተማ ሚኒስትሮችን የያዘ ሆኖ በሶስቱ ማህበረሰብ መንግስታት መካከል የሚነሱ የከተማ ፕላን፣ ትራንስፖርት እና ህዝባዊ አገልግሎቶችን የሚመለከቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት እንዲያደራድር ስልጣን የተሰጠው አካል ነው፡፡ እንደምሳሌ በብራሰልስ ከተማ ደቡባዊ ጫፍ ክፍል የተገነባው ቻርሌሮይ አየር ማረፊያ የብራሰልስ ከተማ ክልል ነዋሪ በሆኑት ዋሎናውያን ላይ የድምጽ ሁከት ፈጥሯል በሚል የዋሎን ማህበረሰብ መንግስት ያቀረበውን ክስን በማደራደር ተፈቷል፡፡

  1. ቋንቋ፣ ትምህርት እና ባህል

 የትምህርት ቋንቋ አጠቃቀም በማህበረሰብ አስተዳደር ተቋማት የሚወሰን ሲሆን በደች ቋንቋ ተናጋሪ ክልሎች በሆኑት ፍላንደርስ እና ብራሰልስ ክልላዊ የመንግስት ት/ቤቶች በደች ቋንቋ ሲሰጥ በፈረንሳይ ማህበረሰብ መኖሪያ ዋሎንያ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ይሰጣል፡፡ እንዲሁም በጀርመን ቋንቋ ተናጋሪ ክልል በጀርመንኛ ቋንቋ ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል የፈረንሳይኛና ደች ቋንቋ ተናጋሪዎች በጋራ በሚኖሩባት ዋና ከተማ ብራሰልስ ደግሞ ትምህርት በደች እና ፈረንሳይ ቋንቋዎች እንዲሰጥ በህግ ተወስኗል፡፡

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የፍላንደርስ ክልል ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በዋና ከተማዋ የሚገኙ ወላጆች የፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑትን ጨምሮ የሥራ እድልን በክልሉ ለማመቻቸት ሲሉ ልጆቻቸውን ወደ ደች ት/ቤቶች መላክ ጀምረዋል፡፡ ይኽም በዋና ከተማዋ የደች ቋንቋ ተናጋሪዎችን ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱም በተጨማሪ በሁለቱ ማህበረሰቦች መካከል ያለውን የፖለቲካ ውጥረት እየቀነሰው ይገኛል፡፡ በውጤቱም ለብዙ ዘመናት የመገለል እና በቂ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ባህላዊ ውክልና አጥተው እስከ መገንጠል ይደርስ የነበረው የደች ቋንቋ ተናጋሪ ቤልጂየማውያን የፖለቲካ ጥያቄ ሊቀየር ችሏል፡፡

 በዋና ከተማዋ ብራሰልስ ፍላሚሾች ምንም እንኳን በቁጥር ከዋሎኖች በእጅጉ ያነሱ ቢሆንም የፍላሚሾችን ቋንቋ እና ባህል ለመጠበቅ ሲባል የደች ቋንቋ ከፈረንሳይኛ ቋንቋ እኩል በከተማዋ እና በብራሰልስ ክልል ከተሞች ሁሉ በሚገኙ የአስተዳደር ቢሮዎች የሚሰሩ አስተዳዳሪዎች ቢቻል ሁለቱንም ቋንቋ እንዲችሉ ካልሆነ ግን ዋናው ኃላፊ ፈረንሳይኛ ቋንቋ ብቻ ተናጋሪ ከሆነ ምክትሉ የግድ የደች ቋንቋ ተናጋሪ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ሲባል የሲቪል ሰርቫንቶች ቅጥር ኮታ ላይ የተቀመጠ ሲሆን 30% ፍላሚሽ እና 70% ፍራንኮፎን ቀመር ወጥቶታል፡፡

  1. የሀብት ክፍፍል  

 ከአጠቃላዩ የቤልጂየም በጀት የፌደራሉ መንግስት ወደ 50% ያህሉን የሚቆጣጠረው ሲሆን ከአጠቃላዩ የመንግስት ወጪ 38% የሚሆነው በክልሎች ነው፡፡ ክልሎች ግብር የመጣል፣ መጨመር እና መቀነስ ስልጣን ያላቸው ሲሆን የቤልጂየም ፌደራል ስርዓት በሚፈቅደው መሰረት ለክልሎቹ በተሰጡ የኢኮኖሚ እና ፋይናንስ ጉዳዮች ላይ ክልሎች ከአውሮፓ ህብረትና ለሌሎች ሀገራት ትብብርና ስምምነት ማድረግ ይችላሉ፡፡

 3.5.4 የአሜሪካ የፌደራል ሥርዓት የነባር ሕዝቦች ጥበቃ ተሞክሮ  

 በዳበረ የዲሞክራሲያዊ ፌደራል ሥርዓቷ የምትታወቀው አሜሪካ ፌደራል ሥርዓቱን ያዋቀሩት ክልሎች በጋራና በትብብር በሚያከናውኗቸው ጉዳዮችን የሚያስፈፅሙበት በጣም ዝርዝር የህግ ድንጋጌ ያላቸውና በየጊዜውም እየተሻሻለ የሚሄድ ሲሆን የቀድሞ የግዛቲቱ ነባር ነዋሪዎች መብትን የሚጠብቁና እውቅና የሚሰጡ ድንጋጌዎች አሏቸው፡፡

 ለምሳሌ በአሜሪካ አሪዞና ስቴት፣ ሎስ አንጀለስ ስቴት ወይም ኮሎራዶ ስቴትስ ከካሊፎርኒያ ስቴት ለውሀና ኤሌክትሪክ ሀይል ክፍያ የሚቀበሉበት ሕጋዊ ሥርዓት ዘርግተዋል፡፡ በአሜሪካ የአላስካ ነባር ነዋሪዎች መብት የሚጠበቅበት ACT of 1971 ዓ.ም በፌደራል ሥርዓታቸው ውስጥ ተካቶ ወደተግባር የተሸጋገረ ሲሆን በዚህም ነባር የግዛቲቱ ነዋሪዎች ከቋንቋ አጠቃቀም፣ ከይዞታ ባለቤትነት አንስቶ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን፣ የትምህርት፣ የህክምና የባህላዊ እውቀት ጥበቃን የሚያረጋግጡ መብቶች ማጎናፀፍ ያስቻለ ድንጋጌዎች ተካተዋል፡፡

በኔቫዳ ግዛት የዩካን ተራራ ላይ ለሚፈሰው የኑክሌር ዝቃጭ የኔቫዳ ነዋሪዎች መብት የሚጠበቅበት ዝርዝር ድንጋጌዎች ያለው ACT of 1982 ወጥቶ ሰውን፣ መሬትን አካባቢና አየርን መጠበቅና ከጉዳት መከላከል የተቻለበት ሁኔታ መኖሩ ይስተዋላል፡፡ ምንም እንኳን በአሜሪካ የፌደራል ህገመንግስት የስራ ቋንቋ አስመልክቶ የሰፈረ ድንጋጌ ባይኖርም እያንዳንዱ ስቴት ያለውን ታሪካዊና ወቅታዊ የነዋሪ ሥብጥር መሰረት በማድረግ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግስታዊ አገልግሎቶችን ዜጋው በመረጠው ቋንቋ በአስተርጓሚ የሚያገኝበትን አሰራር ዘርግተው ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

 3.5.5. የሀገራት ተሞክሮ ማጠቃለያ  

 በመነሻ ሰነዳችን ላይ በተሞክሮነት የዳሰስናቸውን ሀገራት በረጅሙ የሀገር ምስረታና ግንባታ ሂደት የገጠሙዋቸውን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ አስጨናቂ ጉዳዮች በየደረጃው መፍታት ያስቻላቸውን የአመፅ መንገድ ሳይሆን ሰላማዊና የገነቡትን ዲሞክራሲያዊና ፌደራላዊ የአስተዳደር ሥርዓትን መሰረት በማድረግ ልዩነታቸውን እያጣጣሙ የጋራ ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጡ በተጨማሪም የህዝቦቻቸውን ግላዊ መለያ እያስጠበቁና እያስከበሩ ወዲያውም ግን ሰፋ ያለውን የጋራ ቤታቸውን እንደ አንድ ቤተሰብ ለመገንባት የሥልጣን ክፍፍልን፣ የሀብት ክፍፍልን የቋንቋና ባህል ግንባታን፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦትና የአካባቢ ጥበቃ አሰራሮችን በጠንካራ ዝርዝር ህግ እውቅናና ጥበቃ ሰጥተው በመጓዝ ረገድ ረጅም ርቀት መጓዝ እንደቻሉ መገንዘብ ተችሏል፡፡

 በመሆኑም የኦሮሚያ ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የምናረጋግጥበት ዝርዝር ህግ እነዚህን ተሞክሮዎች መሰረት በማድረግ በሌላም በኩል በመሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ የፌዴራላዊና ዲሞራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሁኔታ በማገናዘብ አጠቃላይ የአዲስ አበባ ታሪካዊ ደራና የኦሮሞ ህዝብ ታሪካዊ ትስስር፣ በአዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሞ ነባር ነዋሪዎች መብት፣ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ባህል፣ ታሪካዊ ቦታዎች እውቅና የሚያገኙበትን ሁኔታ፣ ከአዲስ አበባ ወደ ኦሮሚያ ስለሚፈሱ ቆሻሻዎችና ደረቅ ቆሻሻ ስለማከም…ወዘተ በሰከነና ሚዛናዊነት በተላበሰ አካሄድ ወደ ተግባራዊነት ማሸጋገር የዘላቂ ሰላም ዋስትናም የሀገራዊ ህልውናም ማረጋገጫ በመሆኑ ፈጣን እርምጃዎች መካሄድ ይኖርባቸዋል፡፡

4/ አዋጁ ሊያካትታቸው የሚገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች  

 ከላይ በዝርዝር ከያናቸው ከፊንፊኔ መልከምድራዊ አቀማመጥና ታሪካዊ ዳራ፣ በፌዴራልና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ህጎችና የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ፣ ከዓለም አቀፍና አህጉራዊ ስምምነቶች እና ከተለያዩ ሀገራት ተሞክሮ በመነሳት የኦሮሚያ ክልል ከፊንፊኔ/አዲስ አበባ ሊከበርለት የሚገቡ ልዩ ጥቅሞች እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

4.1/ አስተዳደራዊ መብቶች፤  

  1. በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ውስጥ የጥንት ነባሪ ነዋሪ የሆነው ኦሮሞ ተወላጆች የራሱን እድል በራስ የመወሰን መብት እንዲኖረው የኦሮሞ ተወላጆች ብቻ የሚወዳደሩበት የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ጉባዔ እንዲቋቋም በማድረግ በከተማው ውስጥ የኦሮሞ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ እንዲጠበቅ፣ እንክብካቤ እንዲያገኝ እንዲሁም ነባሪ የቦታ ስያሜዎች ተመልሰው እንዲያንሰራሩ በሕግ ማዕቀፎች እንዲጠበቅ የማድረግ ኃላፊነት እንዲኖረው ማድረግና የኦሮሞ ተወላጆች ነባር የከተማዋ ነዋሪ መሆናቸውን እውቅና መስጠት፣
  2. የኦሮሞ ተወላጆች የፊንፊኔ ነባር ሕዝብ በመሆኑ የብሔሩ አባላት የሚወዳደሩበት 30% መቀመጫ በከተማው በየደረጃው ባሉት የአስተዳደር ምክር ቤቶች እና የሥራ  አስፈፃሚው ውስጥ የኦሮሞ ተወላጅ ውክልና እንዲኖር ማድረግ፣ በከተማው  መንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሲቭል ሰርቫንት የኦሮሞ  ተወላጆች ኮታ እንዲጠበቅ ማድረግ እንዲሁም የከተማው ካንቲባ አመራረጥ  በኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ጉባዔ አቅራቢነት በከተማው ምክር ቤት እንዲፀድቅ  ማድረግ፣
  3. ኦሮሚያ ከልላዊ መንግስትና የከተማ አስተዳደሩ የጋራ ምክር ቤት በማቋቋም የአዋጁን ተግባራዊነት እንዲያስፈፅሙ እንዲደረግ፣
  4. በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አማርኛ እና አፋን ኦሮሞ እኩል የስራ ቋንቋ በመሆን እንዲያገለግሉ ማድረግና በከተማው የሚገኙ የመንገድ ስሞች፣ የመንገድ ምልክቶች፣ ማስታወቂያዎች በሁለቱም ቋንቋ እንዲፃፉ ማድርግ፣
  5. ፊንፊኔ/አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዋና መቀመጫ የማድረግ መብት እንዳለው ዕውቅና የሚሰጥ ህግ እንዲደነገግ ማድረግና የተዛባ የታሪክ ግንኙነት ለማረም ፊንፊኔ ተጠሪነቷ በጣመራነት ለፌዴራል መንግስትና ለክልላዊ መንግስት እንዲሆን ማድረግ፣
  6. የፊንፊኔ/አዲስ አበባ መስፋፋት በዙሪያዋ ያለውን ነባር ህዝብ ህልውና እና የኦሮሞ ህዝብ ብሔራዊ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በክልሉና በከተማ አስተዳደሩ መካከል ያለው ወሰን ግን የአከላለል ለውጥ ሊኖረው ስለማይችል ከተማዋ በምንም ዓይነት ሁኔታ መስፋፋት የማይቻል መሆኑና ወሰኑም በከተማው መስተዳድርና በክልሉ መንግስት በጋራ ስምምነት ብቻ ተለይቶ የወሰን ምልክት እንደሚደረግበት በህግ ሊደነገግ ይገባል፣
  7. የከተማ አስተዳደሩ የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች፣ ሕጎችና ዕቅዶች የጥንት ነባሪ የኦሮሞ ተወላጆችን ጥቅሞችና ፍላጎቶች ግምት ውስጥ ያስገባና መብቶቻቸውን የሚያስከብር መሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ እንዳለበት መደንገግና የአሮሚያ ክልላዊ መንግስትም አስተያየት ከመስጠት አልፎ መብት እንዲኖረው ማድረግና እንዲሁም ከተማውንና ክልሉን በሚያስታሳስሩ ጉዳዮች ላይ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችና ህጎችን የማመንጨት ስልጣን እንዲኖረው ማድረግ፣

 1) ፊንፊኔ/አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ዋና ከተማ በመሆኗ በኦሮሚያ  የመንግስታዊና ህዝባዊ ድርጅቶች መስሪያ ቤቶች ውስጥ ወይም ጉዳዮች ላይ  የሚፈፀሙ ወንጀሎች እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወንጀል ሰርተው ወደ  ፊንፊኔ/አዲስ አበባ በመምጣት የሚደበቁትን ተጠሪጣሪ ወንጀለኞች የክልሉ  ፖሊስ፣ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤቶች ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመመመርመር፣  የመያዝና የመቅጣት መብት እንዲሆን ማድረግና በፊንፊኔ/አዲስ አበባ የተፈፀሙ  ከክልሉ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች ከፌዴራልና ከከተማ አስተዳደሩ የፍትህና የፀጥታ  አካሎች በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል፡፡

4.2/ የማህበራዊ አገልግሎቶች መብቶች፤

  1. የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ ፊንፊኔ/አዲስ አበባ በመሆኗ ለተለያዩ መንግሥታዊ፣ ሕዝባዊና የልማት ማህበሮች ቢሮዎች፣ ክልሉ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እሴቶቹን ለስብሰባ አደራሾች፣ የኮሚኒቲ ማዕከላትና ለሌሎች ሕዝባዊ አገልግሎቶች የሚውሉ ህንፃዎችና ፋሲሊቲዎች የሚገነባበት በቂ መሬት ከከተማ አስተዳደር ከሊዝ ነፃ እንዲያገኝ የሚያስችል እንዲሆን ማድረግ፣
  2. የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሠራተኞች እና የከተማው ነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆች በማህበር ተደራጅተው የቤት መሥሪያ መሬት (ቦታ) ከሊዝ ነፃ የማግኘት፣
  3. ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የኦሮሞ ተወላጆች የመኖሪያ ቤት በከተማ አስተዳደሩ ከሚገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች በ15% የማግኘት ወይም የመከራየት መብት እንዲኖር ማድረግ፣
  4. የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስታና የከተማው ነዋሪ የኦሮሞ ተወላጆች አደባባዮች፣ ማዕከላት፣ አዳራሾች፣ ስታዲየሞች፣ ሜዳዎች..ወዘተ አገልግሎት ሲፈልጉ ማግኘት እንደሚችሉ
  5. በከተማው አስተዳደር ውስጥ ነዋሪ ለሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በአፋን ኦሮሞ የሚያስተምሩ ት/ቤቶች በመስተዳድሩ ወጪ ትምህርት እንዲሰጥ ያደርጋል፡፡
  6. የከተማ አስተዳደሩ ከከተማው ዳሪ ላይ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የጤና አገልግሎት በቅርብ እንዲያገኙ የጤና ተቋማትን እንዲያስፋፋ የማድረግ፣
  7. የክልሉ ቢሮዎችና ሠራተኞች የሚጠቀሙባቸው የመኖሪያ ቤቶች የሚሆን የመብራት፣ ውኃ፣ ስልክና ወዘተ አገልግሎት የሚያገኙ መሆኑ፣
  8. በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ዙሪያ ለሚኖረው ሕብረተሰብ ልዩ ልዩ የማህበራዊ አገልግሎቶች እንደ መንገድ፣ ትራንስፖርት፣ መብራት፣ ውኃ፣ ስልክና የመሳሰሉትን በማቅረብ የፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ዞን ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣
  9. የከተማ መስተዳድር ለከተማው ህዝብ የሚያቀርባቸው አገልግሎቶች በመስተዳድሩ አዋሳኝ ለሚኖረው የኦሮሚያ ክልል ሕዝብ ሊዳረሱ የሚችሉ ሲሆን ነዋሪዎቹ በተመሳሳይ ሁኔታ የአገልግሎቶቹ ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዲኖራቸው ማድረግ፣
  10. ከከተማ ጋር ተያይዞ ለሚደርሰው የሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች በክልሉ ከተሞች ላይ እንዳይደርስ የመጠበቅና ከጉዳት የመከላከል ሃላፊነት እንዳለበት ማድረግ፣
  11. የከተማው አስተዳድር ለከተማው ህዝብ ከሚያቀርባቸው አገልግሎቶች ጋር በተያያዙ የልማት ሥራዎችን በክልሉ መንግስት ጋር በመመካከርና በመስማማት ሊፈፅም እንደሚችል…ወዘተ መብቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

4.3/ ባህላዊና ታሪካዊ መብቶች፤

  1. የአዲስ አበባ ከተማ ስያሜን በሚመለከት የኦሮሞ ህዝብ በአዲስ አበባ ላይ ካለው ፍላጐትና ከሚያቀርበው ጥያቄ በመነሳት ስንመለከት በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ያለው  ትርጉም ከፍተኛ በመሆኑ እና ካለፈው ታሪክ ጋር አያይዘን ስንመለከት የአዲስ አበባ  ከተማ የመጀመሪያ ስሟ ፊንፊኔ በመሆኗ ከተማው በኦሮሞዎች የተመሰረተችና  ጥንት ነባር ኦሮሞዎች የሚኖሩበትና የኦሮሞ መሬት አካል በመሆኗ የተዛበውን  ታሪክ ማስተካከል የህገ መንግስታችን ዓላማም በመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ  ኦፊሴላዊ መጠሪያ አዲስ አበባ መሆኑ ቀርቶ ወደ ነባር ጥንታዊ ስሙ ፊንፊኔ  እንዲመለስ ወይም በጣምራነት በ”ፊንፊኔ/አዲስ አበባ” ስም እንዲታወቅ በሕግ  እንዲደነገግ ማድረግ፣
  2. በከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች መጠሪያ/ስያሜዎች በጥንት ስሞቻቸው እንዲጠሩና ተዛብተው እየተጠሩ ያሉት ስሞች እንዲስተካከል ማድረግ፣ 3. የኦሮሞ ሕዝብ ብሔራዊ ማንነት የሚያንፀባርቅ አሻራ በከተማው ውስጥ በቋሚነት እንዲኖር ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር የተያያዙ ታሪካዊ ክስተቶች ወይም በኦሮሞ  ብሄራዊ ጀግኖች ስም መታሰቢያዎች እንዲኖሩ የመንግስት ተቋማት ህንፃዎች፣  አደባባዮች፣ ጎዳናዎች፣ አይሮፕላን ማረፊያ እና የመሳሰሉት በስማቸው እንዲሰየሙ  ማድረግ፣
  3. በመንግስት ወጪ በተቋቋሙ የሬድዮና የቴሌቪዥን ማሰራጫ ጣቢያዎች ከከተማው የሚተላለፉ ፕሮግራሞች የኦሮሞ ህዝብ ብሔራዊ ማንነት ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ የሚያስገድድ፣
  4. በፊንፊኔ/አዲስ አበባ የሚኖረው የዛሬውና መጪው ትውልድ የፊንፊኔን ታሪክ በተዛበ መልኩ ሳይሆን ኦሮሞዎች ይኖሩበት የነበረች ጥንታዊ መሬታቸው እንደነበረችና በወረራና በኃይል ተገፍተው ወደ ዳር በመገፋታቸው ቁጥራቸው እየተመናመነ መሄዱንና ወደ አናሳነት መቀየራቸውን ህዝቡ እንዲያውቅና እውቅና እንዲሰጥ ማድረግ፣
  5. በመስተዳድሩ ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች የታሪክ ማስተማሪያ መፃሕፍት ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ የፊንፊኔ/አዲስ አበባ የጥንት ነባር ሕዝብ አዲሱ ትውልድ እንዲገነዘብ ማድረግ፣
  6. በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጆች የማንነቱ ዋና መገለጫ የሆኑት ታሪኩን፣ እምነቱን፣ ቋንቋውን፣ ባህላዊ እሴቶቹን የመጠበቅ፣ የማሳደግና ስራ ላይ የማዋል መብቱ ሊከበርለት ይገባል፣ በዚህም በከተማው ውስጥ የሚገኙ ፓርኮች፣ የባህል ማዕከላት የሲኒማና ትያትር ቤቶች፣ ሙዚያሞች የኦሮሞ ባህላዊ እሴቶች፣ ቋንቋ፣ ታሪክና ወግ ጠፍተውና ደብዝዘው የሚገኙ ስለሆነ መልሰው ሊያንሰራሩበት የሚችሉ ስልቶችን በመቀየስ የድጋፍ እርጃዎችን መውሰድን የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

4.4/ ኢኮኖሚያዊ መብቶች፤

  1. መሬት የሀብት ማፍረያ ብቻ ሳይሀን ለነባር ህዝቦች የማንነት መገላጫ፣ ለባህል መቀጠልና በራስ ጉዳይ ላይ በራስ ለመወሰን ወሳኝ መሳሪያ ናት፡፡ መሬትና የተፈጥሮ  ሀብቷ በሌሉበት የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ራሱን ሊያኖር ስለማይችል የሰው  ልጅ ህልውናው ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለሆነም በከተማው የሚኖረው ነባር  የኦሮሞ ተወላጅ በመሬቱ ዋስትና ሊያገኝ ይገባል፣ መሬቱንም ያለ ህጋዊ አሰራር  ሊያጣ አይገባም፡፡ ስለሆነም ለልማት ተነሺ መሆኑ ሲረጋገጥ በቂ ቅድመ ዝግጅት  እነዲያደርጉ ማሳወቅ፣ በካሳ ግመታ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግና የወቅቱን የገበያ  ዋጋ ያገናዘበ የካሳ ክፍያና ምትክ ቦታ እንዲያገኙ ማድረግ፣
  2. በልማት ምክንያት የሚፈናቀሉ አርሶ አደሮች የተከፈላቸውን ካሳ በዘላቂነት መጠቀም እንዲችሉ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ ስራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ፣ ራሱን ያቻለ ይህን ስራ የሚሰራ ተቋም በማቋቋም መደገፍና መከታተል፣
  3. ቀደም ሲል በልማት ምክንያት ከይዞታቸው ተነስተው ለተለያዩ ማብበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው ተገቢውን መረጃ በማሰባሰብና በማደራጀት እንዲቋቋሙ ማድረግ፣
  4. መስተዳድሩ ከክልሉ ከተፈጥሮ ሀብትና ከአገልግሎቶች አቅርቦት ጋር የተያያዙ ከሚያገኘው ገቢ ውስጥ የተወሰነ % ለክልላዊ መንግስት እንዲከፍል ማድረግ ወይም ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ለኢንዱስትርና ለፋብሪካዎች የሚውሉ ጥሬ እቃዎች፣ ለመጠጥ ውሃና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች የከተማ መስተዳድሩ የሚያገኘው ከክልሉ በመሆኑ ክልሉ ግብር እንዲያስከፍል ማድረግ፣
  5. በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚመረቱ የአርሶ አደር ወይም ማህበራት ምርቶች ፊንፊኔ/ አዲስ አበባ ውስጥ ገበያ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣
  6. የከተማ ነዋሪ የሆነው የኦሮሞ ተወላጆች በንግድና በሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የስራ መስኮች ውስጥ ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እንዲያድግ የድጋፍ ርምጃዎችን (Affirmative actions) በመውሰድ ነባሩን የኦሮሞ ህዝብ በከተማው ከሚኖረው አብዛኛው ማህበረሰብ ጋር ፍትሃዊ የሐብት ክፍፍል እንዲኖር ሁኔታዎች የማመቻቸት ስራዎችን የመሳሰሉትን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

4.5/ የአካባቢ ደህንነት መብቶች፤

  1. ከከተማው አስተዳደር የሚወጡ ደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻዎች ወደ ክልሉ እንዳይለቀቁ ማድረግ፣ ተለቆ ከተገኘ በሰው፣ በእንስሳትና በተፈጥሮ አከባቢ ላይ የሚደርሰውን ጉዳትና ብክለት መተበቅና መከላከል፣ መስተዳድሩ ወደ ክልሉ በተጣሉ ወይም በፈሰሱ ቆሻሻዎች ምክንያት በሰው፣ በእንስሳት፣ በመሬት፣ በአከባቢና በአየር ብክለት ላይ ለደረሰው ጉዳት በቂ ካሳ እንዲከፍሉ ማድረግ፣
  2. መስተዳድሩ ከከተማው የሚያወጣቸው ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎችን የማከም ወይም እንደገና የመጠቀም መርሃ ግብር እንዲቀይስና ይህንንም ደረጃ በደረጃ ተግባራዊ እንዲያደረግ የሚያስገድድ እና ቆሻሻ የሚያፀዱ ክሊኒኮችን በራሱ ወጪ እንዲያቋቁም ማድረግ፣
  3. የቆሻሻ መጣል ተግባር ከመስተዳድሩ ክልል ውጭ ሊፈፀም የሚችለው ክልሉና መስተዳድሩ በስምምነት ባዛጋጁት መደበኛ ቦታዎ በቻ እንዲሆን የሚያስገድድ እና
  4. በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ዙሪያ ለሚገኙት ቀበሌዎች ወንዞችና የተፈጥሮ ሀብቶች አስፈላጊውን እንክብካቤ የማድረግ ግዴታ የሚጥልበት የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

 ስለሆነም የኦሮሚያ ክልል ከፊንፊኔ/አዲስ አበባ ልጠበቅለት የሚገባውን ልዩ መብት አዋጅ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ዋና ዋና ጉዳዮች አካቶ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡

5/ ማጠቃለያ

 የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህገ-መንግስት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በህግ የበላይነትና በራሳቸው ፈቃድና ፍላጎት የተመሰረተ የጋራ ጥቅማቸውን መብታቸውንና ነፃነታቸውን በጋራና በደጋፊነት ለማሳደግና አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ለመገንባት ያስችላቸው ዘንድ ያፀደቁት የቃል ኪዳን ሰነድ ነው፡፡ ይህ ህገመንግስት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ ሥልጣን መገለጫና ማረጋገጫ በመሆኑ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ ነው፡፡ የህገመንግስቱ የበላይነት የሚከበረውም ሕገመንግስቱን በማክበርና በማስከበር እና ለሕጉ ተገዢ በመሆን ጭምር መሆኑን በህገመንግስቱ አንቀጽ 9 ሥር ተደንግጓል፡፡

 በመሆኑም በህገመንግስቱ ዋስትና ያገኙ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መብትና ነፃነትን በስራ ላይ እንዲውሉ ዝርዝር የህግ ማዕቀፍ እንዲወጣላቸው ከተደነገጉ መብቶች መሀል አንዱ የኦሮሚያ ክልል በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም ነው፡፡ ይህን ልዩ ጥቅም በዝርዝር ህግ ወደመሬት ከማውረድ ጋር ተያይዞ አድማሳችንን ለማስፋት ያየናቸው የፊንፊኔ ታሪካዊ ዳራ፣ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደታችን፣ የተለያዩ አገራት ተሞክሮዎችና ልምዶች እንዲሁም በዚህ ሰነድ ላይ በጥልቀት የተዳሰሱት ዓለም አቀፋዊና የአገራችን የሕግ መሰረቶች የኦሮሞ ብሄርና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በፊንፊኔ/አዲስ አበባ ላይ ያለውን ልዩ ጥቅም የሚከበርበት ዝርዝር ህግ መውጣት እንዳለበት የሚያስገነዝቡንና የሚያረጋግጡልን ሲሆን ይህንን የህገመንግስቱን ድንጋጌ ማክበር እና ማስከበር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፈቅደውና ተስማምተው የሰጡትን ልዩ መብት ከማስከበር እና አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበረሰብ ከመፍጠር አኳያ የሚኖረው ፋይዳና የሚሰጠው ትርጉም ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል፡፡

*************

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories