ስኬታማው የኢትዮጵያ ፕብሊክ ዲፕሎማሲ እና እያደገ የመጣው ተሰሚነት

(ስንታየሁ ግርማ)

አዲሱ ዲፕሎማሲ ከሴፕተምበር 9/11 በኋላ በስፋት ተቀባይነት እያገኘ እንደመጣ አንዳንድ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ ለአዲሱ ዲፕሎማሲ መጠናከር ዋነኛ ምክንያቶች ተብለው የሚጠሩት ግሎባላይዜሽን (ሉላዊነት) እየተስፋፋ መምጣቱ እና ዓለም በኢንፎርሜሽን ኔትወርክ በጥብቅ መቆራኘት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡

አዲሱ ዲፕሎማሲ ከመንግስት ለመንግስት ብቻ ያተኮር የነበረው “አሮጌውን ዲፕሎማሲ” በህዝብ ዲፕሎማሲ እንደተካው የሚያምኑ ብዙ ናቸው፡፡ አሁን ባለንበት ዘመን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዓላማዎችንና ግቦችን ለማሳካት መንግስትን ብቻ ማሣመን በቂ አይደለም፡፡ የህዝብ አስተያየትን መቅርዝ ህዝብን ማሳመን እና ሰጥቶ መቀበል የአዲሱን ዲፕሎማሲ ዋነኛ ማጠንጠኛ ነው፡፡

በሉላዊነት ዘመን በተለያዩ የዓለም ክፍል ያሉ ሠዎች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በተለይም በኢንተርኔት በጥብቅ የተሣሠሩ በመሆኑ ከዜጎች መረጃ በመደበቅ የውጭ ጉዳይ ፖሊስን ዓላማን እና ግብ ማሳካት ከማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ያገባናል የሚሉትም እየበዙ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት በሌላ ሀገር የሚኖሩ ሠዎችን አስተሳሰብ እና አስተያየት መቅረዝን እና በጋራ መግባባት ላይ መድረስ ትኩረት እየተሰጠው ነው፡፡

የኢትዮጵያን የፕብሊክ ዲፕሎማሲ ስኬታማነትን ካሳዩት መካከል የሰላም አስከባሪ ሀይላችን በተሰማራባቸው በአፍሪካ ሀገሮች ያሣየው የሥነ ምግባር ብቃት፣ ለልማት እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ ይገኝበታል፡፡ ይህንን ደግሞ ዓለም የመሠከረው ነው፡፡

አልጀዚራ “the secret to Ethiopian’s Counter terrorism Success’’ ጁላይ 30/2015 በሚል ርዕሰ አንቀጽ ባወጣው ዘገባ መሠረት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦባማ አሜሪካ ከኢትዮጵያ የፀረ ሽብር ስትራቴጅዎች መማር እንደምትፈልግ ገልፀዋል፡፡ አልጀዚራ በመጣጥፉ ኢትዮጵያ በፀረ ሽብርተኝነት ላይ የተሳካላት ዋነኛው ምክንያት በፖለቲካ ነው ይላል፡፡ በኢትዮጵያ እምነት ወታደራዊ እና የወንጀል ፍትህ በፖለቲካ ሊመሩ ይገባል የሚል እምነት ይዛ በመተግበር ውጤታማ ሆናለች ይላል፡፡

የፖለቲካ ስራው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር መወያት እና እነርሱ እራሳቸውን በፈቃደኝነት አደራጅተው ሽብርተኝነትን እንዲዋጉ ማስቻል ነው፤ ወታደሩ የፖለቲካውን እና የሲቪል ስራውን ከመርዳት ያለፈ ሚና የለውም፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ስታደርግ የአካባቢውን በዓል በማክበርና ግምት ውስጥ በማስገባት ነው ይላል አልጀዚራ፡፡ ከተለመደው ግዛትን ይዞ ከመቆየት ይልቅ ኢትዮጵያ የአካባቢውን ህብረተሰብ በማወያየት እና ሀሳባቸውን በማክበር፣ በማሠልጠን፣ በማስታጠቅ እና የአካባቢ አስተዳደር እንዲቋቋሙ በመርዳት ራሳቸውን ከሽብርተኝነት እንዲከላከሉ በማድረግ በኩል ውጤታማ ሆናለች ይላል፡፡

የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ሀይል በተሠማራባቸው ሀገሮች በልማት ጭምር መሣተፍ የኢትዮጵያን ገፅታ በመገንባት በኩል የራሱን ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ እንዴት Hard Power (ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሃይልን) ወደ ተሰሚነት (Soft Power) መቀየር እንደሚቻል ያሣየች ሀገር ናት፡፡ ተሰሚነት የፕብሊክ ዲፕሎማሲ አንዱ መሣሪያ ነው፡፡

ሁለተኛው የኢትዮጵያ ተቀባይነት ያለው እና ብዙ ዲፕሎማሲ እና ተሰሚነቷን ያሣደገላት ጉዳይ የስደተኝነት አያያዟ ነው፡፡

ዛሬ ድፍን አውሮፓ እና አሜሪካን በተጠናወታቸው የዘረኝነት ሱስ በእነርሱ ምክንያት ከሶሪያ፣ ከሊቢያ ወዘተ… እየተሰደዱ ያሉ ዜጎችን እንዴት እንደሚቀበሏቸው ዓለም እየታዘበ ነው፡፡ ምዕራቡ ዓለም የነጮች ብቻ መሆን አለበት ከሚል እሳቤያቸው በመነሳት በእነርሱ ምክንያት ሀገራቸውን እና ሀብታቸውን ጥለው የሚሠደዱ ዜጎችን የምርጫ ዓላማ በማድረግ ፅንፈኛ ፣ዘረኞች በየሀገሮቹ ሥልጣን በመቆናጠጥ ስደተኖችን ቁምስቅላቸውን እያሳዩ ነው፡፡

ዘ ክርስቲያን ሳይንስ ሞኒተር ፀሐፊ ጀምስ ጀፈሪ አፕሪል 17, 2017 “Instead of wall an open door, Why Ethiopia welcomes an enemy’s refugees” በሚል ርዕስ አንቀጽ ባወጣ መጣጥፍ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ኤርትራን ጨምሮ በመቶ ሺህ በላይ ስደተኞችን ተቀብላ በአግባቡ እያስተናገደች መሆኑን ዘግቧል፡፡ ዮርዳኖስ የተባለች የኤርትራ ዜጋ የኢትዮጵያን ወታደሮች “እንደ ወንድሞቿ” እንደምታያቸው ምስክርነቷን ሠጥታለች፡፡ ኢትዮጵያ ህዝብን እና መንግስታትን ለይታ እንደምታይ ዘክርስቲያን ሞኒተር ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ ስደተኞችን በአግባቡ ማስተናገዷ እና በሯን ክፍት በማድረግ (Open door policy)መከተሏ ስትራቴጅካዊ ጠቀሜታዎ እንዳሏት ጀነፈር ሬጋን የተባሉ በአርካዲያ ዩኒቨርስቲ (ፔንሳይልቫንያ) ስለ ኤርትራ ስደተኞች በኢትዮጵያ ያጠኑ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ጥናቱ ተባባሪ ፕሮፌሰር ይገልፃሉ፡፡ “ኢትዮጵያ ስደተኞችን በአግባቡ ማስተናገዷ ለቀጣይ ግንኙነት ምቹ መንገድ ይከፍታል” ብላ ታምናለች ይላሉ ፕሮፌሰሩ፣ ዘ ክርስቲያን ሞኒተር አክሎም ኢትዮጵያ በምታስገነባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች 30 ሺህ የሌላ ሀገር ዜጎቿን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዷን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የኤርትራ እና የሌሎች ሀገር ዜጎችን የትምህርት እድል ማመቻቸቷ ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማሻሻል ወሳኝ የፕብሊክ ዲፕሎማሲ ዘዴ መሣሪያ ነው፡፡

3ተኛው የኢትዮጵያን ፕብሊክ ዲፕሎማሲ ውጤታማነት ማሣያ ደግሞ ታላቁ ሩጫ ነው፡፡ ታላቁ ሩጫ በአፍሪካ በአስደሣችነቱ እና በአሳዛኝነቱ ሣይቀር የመጀመሪያው መሆኑን እነጋርዲያን ሣይቀር ምስክርነት የሰጡበት ነው፡፡ በታላቁ ሩጫ የሚሳተፍ የውጭ ሀገር ዜጎችም በተደጋጋሚ ስለኢትዮጵያ ህዝብ እንግዳ ተቀባይነት እና ስለ አኩሪ ባህሏ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ታላቁ ሩጫ ከኢትዮጵያ አልፎ ወደ ጎረቤት ሀገር ደቡብ ሱዳን ኤክስፖርት መደረጉ ይታወቃል፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ የፕብሊክ ዲፕሎማሲው እና የተሰሚነት ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እና እያደገ የመጣ ቢሆንም አሁንም ያለን አቅምንና ያለበትን ደረጃ ብዙ ይቀረዋል፡፡ ይሁንና ተሰሚነቱ በየጊዜው እያደገ የሚሄድ በመሆኑ ሌሎች እምቅ አቅሞቻችንን መለዬት እና በአግባቡ ለውጭ ዓለም የመሸጥ አቅማችንን (Promoting Capacity) እያሳደግን መምጣቱ ይገባናል፡፡

***************** 

* ስንታየሁ ግርማ የፌዴራል ኤችአይቪ/ኤድስ መከ/መቆ/ጽ/ቤት የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ነው፡፡

Guest Author

more recommended stories