ስለኦሮሞና ኦሮሞነት ማንሳት እንደወንጀል መታየት የለበትም – ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ

(አዲሱ አረጋ ቂጤሳ)

27ኛዉ የኦህዴድ ምስረታ በዓል በአዳማ ከተማ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በፓናል ዉይይት ተከብሯል፡፡ በፓናል ዉይይቱ ወቅት በተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕረዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ምላሽና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡

በፓናሉ ማጠቃለያ ፕረዝዳንቱ የደረጉትን ንግግር የተወሰነ ክፍል ዋና መልዕክት ተርጉሜ አቅርቤላችኋለሁ፡፡ መልካም ንባብ! 

———–

“በዚህ ሥራ ውስጥ እስካለን ድረስ የህዝብ ተልዕኮ እስካለን ማየት ያለብንን ነገር ያለምንም መሰልቸት ቢያመንም ደጋግመን መነጋገር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ጥያቄ የጠየቃችሁ ሰዎች ባነሳችሁት ጥያቁ ላይ ልዩነት የለኝም፡፡ 27 አመታት ቆይታችን፤ በዚህ 27 ዓመታት ውስጥ መድረስ የነበረባችሁ ቦታ ደርሳችኋል ወይ ብላችሁ የጠየቃችሁ በሀገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የሚፈጠሩ ለውጦችን ይህ ድርጅት እያየ በመሄድ ላይ ነው ወይ ብላችሁ በጠየቃችሁት ላይ በነዚህ 27 ዓመታት ደጋግመን እየተነጋገርን ያለነው ይህ ድርጅት ብዙ ለውጦችን አምጥቷል፡፡ ይህ አይካድም፤ አይደበቅም ተጨባጭ በመሆኑ፡፡ እንደ ዕውነት በትኩረት ካየን ደግሞ 27 ዓመታት ብዙ ጊዜ ነው፡ መንግስት ሆኖ ሀገር በማስተዳደር 27 ዓመት አይደለም በ7 ዓመት ፣ በ7 ወር ብዙ ነገር ስለሚሰራ ነው፡፡”

———–

“27 ዓታት ወደኋላ ተመልሰን ዛሬ የደረስንበትን ደረጃ ስናይ በእውነት ከወሰድነው ጊዜ ጋር ስናነፃፅር መስራት ያለብንን ሥራ በእውነት ሰርተናል ወይ ብለን ብናይ፣ አልሰራንም፡፡መስራት ያለብንን ሥራ ሰርተን ብንገኝ ኖሮ ህዝቡ ለምን ያኮርፋል? ለምን ይነሳብናል? ለምን ይቆጣል ማመስገን ሲገባው? ስላልሰራን ነው ይህ አያጠያይቅም፡፡ የቤት ሥራችንን ስላልሰራን ነው፡፡ 27 ዓመት ብዙ ጊዜ ነው፡፡ እያየን እዚህ ውስጥ ነው የተወለድነው፣ ልጅነትና የወጣትነት ጊዜያችንን ጨርሰን እያየን አረጀን፡፡ ብዙ ጊዜ ነው እርግጥ ነው የሰራናቸውን ሥራዎች እንደብቅ ማለት አይደለም፣ ለራሳችን እማኝ ከመሆን ይልቅ ህዝቡ እማኝ ይሁንልን፡፡ እኛ የምንሰራው ሥራ ለህዝብ ነው፡፡ እማኛችን ህዝብ ነው፡፡ ይህ ህዝብ ደግሞ እንኳን ብዙ ሥራ ሰርተን ይቅርና በሰራነው ጥቂት ሥራ እማኝ ሊሆነን ችግር የለበትም፡፡

እኛ እንደ አንድ ፖለቲካ ድርጅት 4 ሚሊየን አባላት እንዳሉት ድርጅት እንደ 40፣ 50 ሚሊየን ህዝብ እና ሰፊ ክልል እንደሚያስተዳድር ድርጅት ራሳችንን ስናይ ከትላንቱ ጋር አፈፃፀማችንን ነው ማየት ያለብን፡ ዛሬ ላይ ሆነን ከደርግ፣ ከኃ/ስላሴ ሥርዓት ጋር ራችንን ማወዳደር አለብን ወይ; በዚህ ራሳችንን የምንገመግም ከሆነ ግምገማው ትክክል አይደለም፡፡ ደርግ 17 ዓመት ነው ያስተዳደረው እኛ 27 ዓመት ነው ያስተዳደርነው፡፡ ከዚህ ጋር በምንም መመዘኛ ልናወዳድር አይገባም፡፡ ጊዜዉም የተለያየ ነው፡፡ ብዙ ነገር ተቀይሯል፡፡”

———– 

Photo - Oromia President Lemma Megersa
Photo – Oromia President Lemma Megersa

“ዛሬ ከ27 ዓመት በኃላ በምንም መመዘኛ ደርግ ይህን አድርጓል ኃ/ስላሴ ይህን አድርጓል እኛ ይሄን አድርገንልሃል ብለን የምንነግድበት ሸቀጥ በእጃችን የለም፡፡ እንደ ፖለቲካ ድርጅት ህዝብ እንደሚያስተዳድር ድርጅት፤ ራሳችንን የምናይ ከሆነ እንደ ምሣሌ የሚታዩ ሀገሮች በ30 ዓመት ጊዜ ውስጥ ለምሳሌ የኤዥያ አገሮችን ብንወስድ ዛሬ በአለም ላይ በዕድገት የሰማይ ጥግ የደረሱ አገሮች ታሪካቸው የ20፣ የ30፣ የ40 ዓመታት ዕድሜ ነው፡፡ ሌላ ታሪክ የላቸውም፡፡ በዚያ ነው ራሳችንን መመዘን ያለብን እንጂ ወደቄየ ተመልሰን ሞቶ አፈር ከለበሰው ጋር ራሳችንን ዝቅ አድርገን ማወዳደር፣ በዚያ ራሳችንን ማሞኘት ይሆናል፡፡ ከዚህ ተነስተን ስናይ መስራት ያለብን፤ መድረስ ያለብ ደርሰናል ወይ ብላችሁ የጠየቃችሁ አልደረስንም፡፡ አልደረስንም ሣይሆን ትንሽ ነገር ነው የሰራነው ብዙ ነገር ይቀረናል ብለን ራሳችንን መመዘን አለብን፡፡ ብዙ ነገር ይቀረናል፡፡ ለምንድነው እዝያ መድረስ ያቃታን መሮጥ፣ መሄድ ሲገባን ለምን አዘገምን ብዙ ችግር ስላለብን ነው፡፡ ያንን በተሃድሶአችን ደጋግመን ስላየን አልደግመውም፡፡ እንናገራለን እንጂ የምንናገረው ነገር በሽታው ያለበት ሥፍራ የሚያክ አይደለም፣ በሽታው ያለበትን ሥፍራ የሚያድን አልነበረም፡፡”

———– 

“እርግጥ ነው ንግግራችን ትልቅ ነው፡፡ ከይቅርታ ጋር ምላሳችንን አርዝመን ብዙ ተናግረናል፡፡ የምላሳችንን ያህል እጃችን ሊደርስ አልቻለም፡፡ የችግሩን ሥፍራ አላየንም አልነካንም፣ አልወጋንም፤ እንጂ እራሳችንን ማየት ቀርቶብን አይደለም፡፡ እርስ በርስ መገማገም ተጨካክነን እርምጃም መውሰድ ቀርቶብን አይደለም፤ መውጋት ያለብንን ሥፍራ አልወጋንም፡፡ ለዚያ ነው ዛሬ ስራችን ጎዶሎ የሆነው፡፡ መንገድ ላይ የቀረነው ብዙዎቻችን ነን፡፡ ትላንት ያሰብነው ለህዝብ ተቆርቋሪነት አጥተን ረስተን መንገድ ላይ ጥለን ያለፍን አውላላ ሜዳ ላይ የቆምን ብዙዎቻችን ነን፡፡

አንዳንዱ የራሱን ጌታ ፈጥሮ የሚሰግድለት አለ፡፡ ጌታ መፍጠር ለምን ይመጣል? ለምን አስፈለገ? ለምን ተፈለገ? ለሰላም? የድርጅታችን መስመር ይህን ስለሚል? ህዝቡ ይሄን ስለሚፈልግ? አይደለም፡፡ በእርግጥ የድርጅታችን ችግር ነበር ወይ? የድርጅታን ችግር ነበር እውነት ነው፡፡ አንድ የሚያመን ሥፍራ እዚህ ጋር ነበር መደባበቅ ስለሌለብን ነው፡፡ ለምንድን ነው ተመልሰን የምንባላው? አንድ ህዝብ ነው ያለን፣ አንድ ሀገር ነው ያለን፣ አንድ አላማ ነው ያለን፡፡ ይህ ከሆነ ለምን እንከፋፈላለን? ለምን እንባላለን? ለምን ደባና ሸር አንደኛችን በሌላኛችን ላይ እንፈፅማለን?”

———– 

“የህዝባችን ችግር ሳይሆን የግል ጥቅም ችግር ስላለ ነው፡፡ ከህዝብና ከሀገር ጥቅም የግል ጥቅም ስላለ ነው፡፡ ሌላ አይደለም ሌላ ፍች የለውም ራስን ማስቀደም ስላለ ነው:: የራስ ጌታ ሲፈጥር ደግሞ በሄደበት ሁሉ ጉልበቱ ይብረከረካል፡፡ ወንበር ላይ መቀመጥ እንፈልጋለን ወንበር ላይ መቀመጥ ለስም መሆን የለበትም፡፡ በተቀመጥንበት ወንበር ላይ ወንበሩ የሚፈልገውን ሥራ መስራት ካልቻልን ወንበሩ የሚፈልገውን ውሳኔ መስጠት ካልቻልን ለስም ወንበር ላይ መቀመጥ ዋጋ የለውም፡፡ ስለዚህ የዚህ ዓይነት ችግሮች ስላሉብን ነው ከ27 ዓመት በኋላም መድረስ የሚገባን ሥፍራ ሳንደርስ ታግለን ለታገልንለት ህዝብ ጋር የተቃቃርነው ለዚህ ነው፡፡ ለዚህ ነው የተጨካከነው ሌላ አይደለም፡፡

አሁንም ህዝቡ የመጨረሻ እድል ሰጥቶናል በእውነት ሁሉ ነገር ድኗል ሁሉ ነገር ምላሽ አግኝቷል ሁሉ ነገር አልቆለታል ብለን የምናስብ ከሆነ ሞኝነት ነው፡፡ ራሳችንን ማሞኘት የለብንም ሀገር ሰላም ነው አዎ ሀገር ሰላም ነው፡፡ ግን ሰላም አይደለም፡፡ አጭር ዕድል ነው የሰጠን እንጂ ህዝቡ ሰላም አይደለም፣ እድል ሰጥቶናል የመጨረሻ ዕድል፡፡ እነዚህ ሰዎች ምን እንደሚሰሩ እንይ ብሎ እድል ሰጥቶናል፡፡ ይህን ማወቅ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በደንብ ማጤን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡”

———– 

“እንደ ድርጅት፣እንደ መንግስት እያንዳንዳችን ከገባንበት ጓዳ ውስጥ አንገታችንን ይዞ አውጥቶ የፈለገውን ነገር ሊፈጽምብን እንደሚችል እንዲህ አይነት እርምጃ ሊወስድብን እንሚችል አይተናል፡፡በፊልም ሣይሆን በተጨባጭ ውስጥ ኖረን አይተናል ይሄ ቲያትር አይደለም፡፡ ጎበዝ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ ወዲያና ወዲህ የምናይ ሰዎች ካለን ሌላ አማራጭ የለንም፡፡ የእኛ ጌታ ህዝባችን ነው፡፡ ለየክልላችን ህዝብ ነው፡፡ ሌላ ጌታ የለንም፡፡ ለሌላ ጌታ መስገድ የለብንም፡፡ ትልቅ ድርጅት አለን 4 ሚሊየን አባላት አሉን፡፡ አራት ሚሊየን ማለት በጣም ትልቅ ነው፡፡ በአለም ላይ አራት ሚሊዬን አባላት ያሉት ድርጅት ውስን ነው፡ እንደነ ቻይና ያሉት ካልሆነ በስተቀር ውስን ነው፡፡ በቁጥር አይደለም እንዲሁ በስም ብንናገር 50 ሚሊየን ህዝብ ነው እኮ ያለን፡፡ ይህን ይዘን ለምን እግራችን ብርክርክ እንደሚል ለምን እንደምንፈራ ለምን ወደ ጓዳ ተመልሰን አንገታችንን ደፍተን እንደምናጉረመርም አይገባኝም፡፡”

———– 

“አሁን ያለን ምርጫ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡ ደጋግመን ስንል እንደነበረው ማዳመጥ ያብን ማየት ያለብን ይሄንን ህዝብ ነው፡፡ ይሄ ህዝብ ሌላ አራማራጭ የለውም፡፡ እንደ ሥራው ክብደትና ድካም እያንዳንዱ ተቀብሎ ይሞክር ብለን አስረክበን ብንወጣም ደስ ይለን ነበር፡ ዛሬ እንደዚህ አይነት ምርጫ አለን? እስቲ ይቅርብን ሌሎችም ይሞክሩት፡፡ ሰባት አመት ሣይሆን 27 ዓመት የለፋንበት ስለሆነ፡፡ አንዳዶችን እንዲያውም ሰውነታችን የዛለ በመሆኑ ፡፡ ሌላው እስኪ ይየው ብለን እንደዚህ መቀባበል ቢቻል እንላለን፡፡ በዚህ መልኩ የተዘጋጀ ነገር ቢኖር ደስ ባለን ነበር፡፡ እውን በዚህ ደረጃ ይህ አለ ወይ ብለን ብንጠይቅ የለም፡፡ ራሳችንን ማታለል የለብንም፡፡ እኛም ደግሞ መሆን ያለብንን ሳንሆን ቀርተን እየተዉረገረግን በመሄድ፣እንዲሁ አስመስለን በመጓዝ ብቻ ረጅም መንገድ መሄድ እንችላለን ወይ ብለን ብንጠይቅ አንችልም፡፡መስቀለኛ መንገድ ላይ ነዉ ያለነዉ፣ራሳችንን ብቻ ሳይሆን ሀገርንም ልናጠፋ ስለምንችል፡፡ ሀገርንም ልናፈርስ እንችላለን፡፡ ሀገር እንደ ድንገት ሲፈርስ ደግሞ አይተናል ሩቅ ሳንሄድ ከጎረቤት ሀገር፡፡ በዕቅድ የሚፈርስ ሀገር የለም፡፡ ስለዚህ ያለን ምርጫ ቆም ብለን አሁንም ደጋግመን ስንል እንደነበረው ጥርሣችንን ነክሰን ከዚህ ህዝብ ጋር ሆነን ለህዝቡ መሥራት ነው ሊያዋጣን የሚችለዉ፡፡ ”

———– 

“ከዚህ በኋላ ትግሉ እጅግ መራር ነዉ፡፡ እኛ ታጋዮች ማወቅ ያለብን ምንድነዉ መራር የሚያደርገዉ የሚለዉ ነዉ፡፡ አንደኛ የተሰጠችን ጊዜ አጭር ናት፡፡ ሁለተኛ እኛ እንዳሻን ስንሠራ ዝም ብሎ ተኝቶ የሚያየንና የሚሰማን ህዝብ አይደለም ያለው፡፡ ህዝብ ማለት እኛ የምንቀመጥበት ዝምብሎ እንዲሁ ተሸክሞን የሚውልና የሚያድርንበር ሣይሆን ከሥር እሳት ያለው የሚፋጅ ወንበር ነው፡፡ እዚህ ወንበር ላይ ውለን ማደር የምንችለው ከሠራን ብቻ ነው፡፡ ካለበለዚያ በቁማችን ያቃጥለናል፡፡ ምንም አማራጭ የለንም፤ ስለሆነም ከእንግዲህ ወዲያ የምናደርገው ትግል መራርና ከባድ ነው ለዚያ ደግሞ ራስን አሳልፎ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ዝም ብለን መሥመር ውስጥ ገብተን ስለቆምንና ስለተጓዝን የሚያዋጣን አይመስለኝም፡፡ መራር ስለሆነ፡፡”

———– 

“ሌላው ሊታይና መገንዘብ የሚያስፈለገው እዚህ ሀገር ላይ የፌደራሊዝምን ሥርዓት ከመሠረቱት ውስጥ እኛ ትልቅ ድርሻ አለን፡፡ አንዳንዴ የፌደራሊዝም ሥራዓቱ ይቅርና በሀገር ምስረታ ያለንን ድርሻ ዘንግተን የሠራናቸውን ሥራዎች የምንተውበት ጊዜ አለ፡፡ ይህቺ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር እንድትፈጠር ይሄ ህዝብ (ኦሮሞ) ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ይሄንን የፌደራል ሥረዓት በመፍጠር ረገድም ሚና አለውው፤ በፌደሬሽኑ ውስጥ የሚገባንን ለማግኘት መታገል ማለትም ይሄው ነው፡፡ሥርዓቱን መፍጠር ብቻም ሳይሆን የፈጠርነው ሥርጭት ለህዝባችን የሚጠቅም፣ የሚበጅ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ ይሄንን ስንል በዚህ ፌደራሊዝም ሥርዓት ውስጥ ምንም አይነት ችግር አይገጥመንም ሁሉንም ነገር ቤታችን ውስጥ ተቀምጠን ይመጣልናል ብለን የምንጠብቅ ከሆነ ስህተት ነው፡፡ የጥቅም ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ ይህም በፌደሬሽን ውስጥ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ለጥቅማችን ታግለን ተከራክረን የዚህን ህዝብ ጥቅም ማስጠበቅና ማስከበር አስፈላጊ ነዉ፡፡ ይሄን ማለት ሌላ ነገር መሆን ማለት አይደለም፡፡

———– 

አንዳንዶቻችን እየተሳሳትን ያለነዉ እንዲያዉም እያሽቆለቆልን ማንነታችንን እየዘነጋን መጥተን ዬት እንደደረስን ታውቃላችሁ? ስለ ኦሮሞና ኦሮሞነት ማንሳት እንደ ወንጀል መታየት ጀምሯል እኮ፡፡ እንደ ጥፋት እንደ አውሬ እንደ ሌላ ነገር መወሰድና መታየት ጀምሯል፡፡ እኛ ለዚህ አይደለም የታገልነው፡፡ ምንግዜም ቢሆን በየትኛውም መድረክ ላይ ፊትለፊት ወጥተን መናገር ተገቢ ነው፤ ይገባናል፡፡ እኛ ካልተናገርን ማን ይናገርልናል? እኛ የዚህ ህዝብ ተወካይ ነን ካልን እኛ ካልተናገርንለት ማነው የሚናገርለት? ትግል ይሄ ነው? አንዳንዴ ችግር ያልሆነ ነገር እንደችግር የተወሰደ ይመስለኛል፡፡ ደግ ሴት ከወንድሟ ታረግዛለች እንደሚባለው አይነት ነገር ለመፍጠር እየተጓዝን ያለ ይመስለኛል፡፡ We don’t have to be shy! ለዚህ ህዝብ መብት ቆመን መታገል አለብን ካልን መታገል መቻል አለብን፡፡

ደጋግመን ተናግረናል መታገል ምንድነው ትርጉሙ? የህዝቡን ኑሮ መለወጥ ነው፡፡ ሌላ ነገር የለውም፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር ወዘተ አለ፡፡ የግል ባለሀብቶቻችንን ዘንግተናቸዋል፡፡ መቼ ወደ እኛ መጥተው ያውቃሉ? መች አቅርበናቸዉ፣አደራጅተናቸዉ እናውቃለን? በክልላችን የኢኮኖሚና የልማት ሥራ ራሳቸዉንመ ጠቅመው ሀገራቸውንም እንዲጠቅሙ፣ እንዲለዉጡ አድርገን እናውቃለን? እንደዚህ አይነት ዕቅድስ አለን? ብዙ ነገር ግን እናወራለን፡፡ እንደዚህ አይነት ነገር ሠርተን በተጨባጭ ካለን መሬት ላይ የት አለ? ስለዚህ ባለሀብቶቻችንን የግል ጥቅማቸውን ብቻ ሣይን ሀገርንም መጥቀም አለብን በሚል ዕምነት ከዝህ በኋላ በልማት ሥራዎቻችን ውስጥ አሣትፉን መሥራት አለብን፡፡ ያ ሲሆን ነው ኢኮኖሚ የሚቀየረው፡፡

———– 

እኛ በዕውቀታችን ሁሉ ነገር አሟልተን አይደለም ሀገር እየመራን ያለነው፡፡ በዕውቀት መታገዝ እና መረዳት አለብን፡፡ በአዲስ ሐሳብና በአዲስ ጥናት መደገፍ አለብን፡፡ በየጊዜዉ እየተቀያየረ በሚሄድ አለም ውስጥ እኛ ራሳችን መለወጥ የሚያቅተን ለምንድነው? ቶሎ ከዚያ ጋር ተላምደን እየተቀያየረ የሚሄደውን ሁኔታ ተረድተን መሥራት የሚያቅተን ለምንነው? በምሁራኖቻችን ስላልተደገፍን ነው፡፡ የእኛ ምሁራን፣ አዋቂዎችና ሐሳብ አፍላቂዎች ሊያግዙን ይገባል፡፡ ለእኛ ብለው ሳይሆን የዜግነት ግዴታ ስላለባቸው፡፡ ለዚያ ደግሞ እኛ በራችን ክፍት መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ እነሱን ጋብዘን ድርሻቸውን ሊወጡ የሚችሉበትን መድረክ፣ ሊረዱንና አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር መቻል አለብን፡፡ ይሁንና እነሱም ማዶ ተቀምጠው እኛን መውቀስ ብቻ ሳይሆን ማዶ ተቀምጠው ጉድለቶቻችንን ቆጥረው እኛን ማውገዝ ሳይሆን እኔስ ምን ሰራሁ ብለው ራሳቸውን ጠይቀው እኛን መደገፍና መርዳት አለባቸው፡፡

——

የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ፕረዝዳንት ክቡር አቶ ለማ መገርሳ በኦህዴድ 27ኛ የምስረታ በዓልን በማስመልከት በተዘጋጀ የፓናል ዉይይት ያደረጉትን ንግግር እና ቀጣይ አቅጣጫዎች  በሶስት ክፍሎች  አቅረቤላችሁ ነበር፡፡ የንግግራቸዉ ክፍልየመጨረሻዉ ክፍል  እነሆ!

“እኛ በዕውቀታችን ሁሉ ነገር አሟልተን አይደለም ሀገር እየመራን ያለነው፡፡ በዕውቀት መታገዝ እና  መረዳት አለብን፡፡ በአዲስ ሐሳብና በአዲስ ጥናት መደገፍ አለብን፡፡ በየጊዜዉ እየተቀያየረ በሚሄድ አለም ውስጥ እኛ ራሳችን መለወጥ የሚያቅተን ለምንድነው? ቶሎ ከዚያ ጋር ተላምደን እየተቀያየረ የሚሄደውን ሁኔታ ተረድተን መሥራት የሚያቅተን ለምንነው? በምሁራኖቻችን ስላልተደገፍን ነው፡፡ የእኛ ምሁራን፣ አዋቂዎችና ሐሳብ አፍላቂዎች ሊያግዙን ይገባል፡፡ ለእኛ ብለው ሳይሆን የዜግነት ግዴታ ስላለባቸው፡፡ ለዚያ ደግሞ እኛ በራችን ክፍት መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ እነሱን ጋብዘን ድርሻቸውን ሊወጡ የሚችሉበትን መድረክ፣ ሊረዱንና አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን አጋጣሚ መፍጠር መቻል አለብን፡፡ ይሁንና እነሱም ማዶ ተቀምጠው እኛን መውቀስ ብቻ ሳይሆን ማዶ ተቀምጠው ጉድለቶቻችንን ቆጥረው እኛን ማውገዝ ሳይሆን እኔስ ምን ሰራሁ ብለው ራሳቸውን ጠይቀው እኛን መደገፍና መርዳት አለባቸው፡፡”

——

“የግል ባለሀባቶቻችንን ዘንግተናቸዋል፡፡ መቼ ወደ እኛ መጥተው ያውቃሉ? መች አቅርበናቸዉ፣አደራጅተናቸዉ  እናውቃለን? በክልላችን የኢኮኖሚና የልማት ሥራ ራሳቸዉንመ  ጠቅመው ሀገራቸውንም እንዲጠቅሙ፣  እንዲለዉጡ አድርገን  እናውቃለን? እንደዚህ አይነት ዕቅድስ አለን? ብዙ ነገር ግን እናወራለን፡፡  እንደዚህ አይነት ነገር ሠርተን በተጨባጭ ካለን መሬት ላይ የትአለ? ስለዚህ ባለሀብቶቻችንን የግል ጥቅማቸውን ብቻ ሣይን ሀገርንም መጥቀም አለብን በሚል ዕምነት ከዚህ በኋላ በልማት ሥራዎቻችን ውስጥ አሣትፉን መሥራት አለብን፡፡ ያ ሲሆን ነው ኢኮኖሚ  የሚቀየረው፡፡

——

“የመጨረሻዉን ዕድል ሰጥቶን እንየዉ ብሎ ከሁሉም በላይ ይህንን በአል በዚህ መልኩ ተቀምጠን እንድናከብር ትልቁ ባለ ድርሻና ይህንን ሰላም ለሰጠን ህዝባችን ያለኝን ክብርና ምስጋና በናንተ ፊት ላቀርብ እወዳለሁ፡፡ ይህንን ሰላም ያጎናጸፈን መሳርያችን ወታደሮቻችን ወይም መዋቅራችን አይደለም:: ህዝባችን ነዉ ዕድሉን የሰጠን፡፡ ከሁሉም በላይ ይህንን ማወቅ ይገባናል፡፡ ለሰጠን እድል ደግሞ እውቅና ልንሰጠዉ ይገባናል፡፡ የሰጠን ዕድል ደግሞ የመጨረሻዉ ነዉ፡፡ የተለያየ ካርድ አይተናል፤ ቢሆንም ግን አሁንም የመጨረሻዉን ዕድል ሰጥቶናል፤ ይህ ትልቁ ዕድል ነዉ፡፡ በዚህ ዕድል ደግሞ አዉቀን መጠቀም የኛ ድርሻ ይሆናል፤ ቢሆንልንና ብዙ ነገር ብናወራ ጥሩ ነዉ፤ የሚድን ከሆነ አንዴ የወሰዱት መድሃኒት ነዉ የሚያድነዉ፤ ላለፉት ስድስት ወራት ብዙ ያወራን ስለሆነ በዚህ ሁኔታ ተደጋግፈን ተረዳድተን የምንሰራ ከሆነ እንለውጠዋለን የማይለወጥ  ነገር የለም፡፡ “

——

“እኛም ድርጅት የተባልነው ለለውጥ ነው እንጂ ለሌላ አይደለም፤ መታገል ያስፈለገን ለለውጥ ነው፡፡ ከሰራን እንለውጣለን፤ ከተቀመጥን እንጠፋለን፤  ሀገር እናጠፋለን፤ አሁንም ህዝባችን ያለዉ ችግር ብዙ ነዉ፡፡ እዉነት ነዉ ያስመዘገብነዉ ዉጤት አለ፤ በህዝባችን ዉስጥ ብዙ ችግር አለ፤ ብዙ የሚያሳፍሩን ነገሮች አሉ፡፡ ነገር ግን አንድ ቀን ለዉጥ ያመጡልኛል ብሎ ነዉ በተስፋ የሚጠብቀን፤ ስለዚህ ቁመን እንስራ፡፡ ትናንት ቃል እንደ ተገባባነዉ ቃል መገባባትና መማማል በቂ አይደለም ሰርተን መታየት ነዉ ያለብን፡፡ ሰርተን ተጨባጭ ለዉጥ አምጥተን ነዉ ማሳየት ያለብን፡፡ ይሄ ከሆነ ህዝባችን ማክበር ብቻ አይደለም በትከሻዉ ይሸከመናል፡፡ በታሪካችን ውስጥ አይተነዋል እስቲ 27 ዓመታት ወደ ኋላ ተመልሳችሁ አስታውሱ በሶስትና አራት ዓመታት ውስጥ  ጥሩ ነገር ስንሰራ ሕዝባችን ምን ያህል እንዳከበረን እናውቃለን፡፡ ይህንንም በተግባር አይተናል፡፡ አጣጥመን የማናውቀው ነገር አይደለም ከመስመራችን ወጥተን ማንቀላፋት ስንጀምር ደግሞ ምን ይህል እንደሚቀጣን አይተናል፡፡ ከዚህ በላይ ትምህርትና ልምድ የሚሆነን ነገር የለም፤ ስለሆነም ኑሮአችሁን በአቋራጭ የመለወጥ ፍላጎት ያላችሁ  ሰዎች ካላችሁ ከአሁን ወዲያ ይህ ቦታ በዚህ የሚመረጥ ቦታ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሁኔታው ለዚህ ምቹ አይደለም፡፡”

——

“ስለሆነም ይህንን በዓል ስናከብር የሕዝባችንን ችግር በማሰብ፤ ትናንት የነበርንበትን ጨለማና ችግር በማስታወስ ድክመታችንን በማስታወስና ከአሁን በኋላ የዚህን ሕዝብ ኑሮ እንዴት መለወጥ አንችላለን በማለት እያንዳንዳችን ምን መስራት እንዳለብን ትኩረት ሰተን ካየነው በዓላችን መልካም በዓልና በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ፈጣሪ ረድቶን ስኬታማ የሆነ ሥራ ሰርተን አንገታችንን ደፍተን በአዳራሽ ውስጥ ተሰብስበን ሳይሆን ከሕዝባችን ጋር ሜዳ ላይ ወጥተን ጨፍረን የምናከብረው ይሆናል፡፡ ስለሆነም በዚህ መልኩ እንስራ ከሰራን ደግሞ ለውጥ እናመጣለን፡፡ ለውጥ አስመዝግበን የምናውቅ ስለሆነ ይህንን በመስራት የዛሬውን ቀን በዚህ መልኩ በማስታወስ ሁላችንም ማለትም ሕዝባችንም በለሃብቶችም ምሁራንም የሀገር ሽማግሌዎችም አባገዳዎችም ተረዳድተን የህዝባችንን ኑሮ እንለውጥ እላለሁ ጥሪአችንን አክብራችሁ ጊዜአችሁን ሰጥታችሁን ስለተገኛችሁ አመሰግናለሁ፡፡”

——

ቸር እንሰንብት!

*********

Guest Author

more recommended stories