ዜጎች የሚፈሩት መንግስት ይወድቃል!

ነፃነት ለሰው ልጅ የተሰጠ ተፈጥሯዊ ፀጋ ነው። በነፃነት ማሰብ፣ መናገርና መፃፍ የሰው ተፈጥሯዊ ባህሪ፥ የሰውነት (የሰብዓዊነት) መገለጫ ነው። በመሆኑም፣ ነፃነት የሌለው ሰው ሰብዓዊ ክብሩን የተገፈፈ ነው። ሰዎችን በነፃነት ከመኖር፥ ከማሰብ፥ ከመናገር፥ ከመፃፍ፥… የሚያግዱ በሙሉ የሰው ልጅን ተፈጥሯዊ ባህሪ ለመግፈፍ የሚጥሩ ናቸው። የሰው ልጅ የተፈጠረው ከምንም ዓይነት እዳና እገዳ ነፃ ሆኖ ሕይወትን በነፃነት እንዲኖር ነው።

የሁሉም ሰዎች ነፃነት የሚከበረው የእያንዳንዱ ሰው ነፃነት ሲከበር ነው። እያንዳንዱ ሰው ግዴታውን በራሱ ከተወጣ የሁሉም ሰዎች ነፃነት ይከበራል። ነገር ግን፣ አንድ ሰው ግዴታውን በአግባቡ እንዲወጣ “ሌሎች ሰዎች ለእሱ ያለባቸውን ግዴታ በአግባቡ ይወጣሉ” ብሎ ማመን አለበት። ስለዚህ፣ ሕይወትን በነፃነት ለመምራት እያንዳንዱ ሰው ሁሉንም ሰዎች ማመን፣ ሁሉም ሰዎች ደግሞ እያንዳንዱን ሰው ማመን አለባቸው።

ሁሉም ሰው በራሱ ፍላጎትና ምርጫ በሚንቀሳቀስበት፣ በመነሳሳት፣ ለውጥና አደጋ የተሞላ የነፃነት ሕይወት ከፍርሃት ነፃ ሊሆን አይችልም። በዚህ ዓይነት ሕይወት ውስጥ እርስ-በእርስ መተማመን ሊኖር አይችልም። ይህ ያለመተማመን መንፈስ ደግሞ እርስ-በእርስ መፈራራትን ይፈጥራል። ነገር ግን፣ የነፃነት ሕይወት ሁሌም በለውጥና ስጋት የተሞላ ነው።

ምንግዜም ቢሆን ነፃነት ያለው ሰው ነፃነቱን እንዳያጣ ይፈራል። ስለዚህ፣ ሁሉም ሰዉ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ በሚንቀሳቀስበት የነፃነት ሕይወት ውስጥ እያንዳንዱ ሰው የሌሎችን እንቅስቃሴ በእርግጠኝነት መገመትና ማወቅ ማወቅ ይፈልጋል። አንድ ሰው ከጎኑ ያለን ሰው እንቅስቃሴ በራሱ ማወቅና መገመት ከተሳነው በውስጡ ያለመተማመን ስሜት ይፈጠራል።

ይህ ያለመተማመን ስሜት “እኔ ለሌሎች ሰዎች ያለብኝን ግዴታ በአግባቡ ብወጣ እንኳን እነሱ ለእኔ ያለባቸውን ግዴታ በአግባቡ ላይወጡ ይችላሉ” ከሚል እሳቤ የመነጨ ነው። ስለዚህ፣ “እኔ የሌሎችን መብት ባከብርም እነሱ ግን የእኔን መብት ላያከብሩ ይችላሉ” የሚል ፍርሃት በውስጡ ይፈጠራል። በዚህ መሰረት፣ በተወሰነ አከባቢ የሚኖሩ ሰዎች ማህበራዊ ግንኙነታቸውን የሚመሩበት የራሳቸው የሆነ ሕግና ሥርዓት ሊኖራቸው የግድ ይላል።

የሕግ ስርዓትን ለመዘርጋት ደግሞ ሦስት አካላት ያስፈልጋሉ። እነሱም፡- ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈፃሚ። እነዚህ ሦስት አካላት በጥምረት “መንግስት” ይባላሉ። የእነዚህ አካላት ድርሻና ኃላፊነት በግልፅ ተለይቶ የሚቀመጥበት የውል ሰነድ “ሕገ-መንግስት” ይባላል። በዚህ መልኩ የተወሰነ ጂኦግራፊያዊ ክልል ያለውና በአንድ መንግስት አስተዳደር ስር የሚገኝ ግዛት ደግሞ “ሀገር” ይባላል። በዚህ መልኩ፣ በአንድ የተወሰነ አከባቢ የሚኖሩ ሰዎች ነፃነትን ለማረጋገጥ እና ፍርሃትን ለማስወገድ ከእያንዳንዳቸው የበለጠ ኃይል ያለው መንግስት ፈጠሩ።

“የመንግስት ስልጣን” ማለት የዜጎችን ነፃነት እንዲያስከብር ከእያንዳንዱ ግለሰብ ላይ ተቆርሶ የተሰጠ መብት ነው። ምክንያቱም፣ እያንዳንዱ ዜጋ፤ አንደኛ፡- የሌላውን መብት ሳይነካ የፈለገውን ነገር እየሰራ፣ እየተናገረና እየፃፈ በሰላም በሀገሩ እንዲኖር፣ እና ሁለተኛ፡- በባዕድ ሀገር መንግስት ወይም በሌላ ሰው በኃይል ተገዢ እንዳይሆን ጥበቃና ከለላ እንዲያደርግለት ራሱን በራሱ የማስተዳደርና የመምራት መብቱን ለመንግስት በውክልና ሰጥቶታል። ስለዚህ፣ መንግስት ለዜጎች ነፃነት ጥበቃ የማድረግ ግዴታ እንጂ ነፃነታቸውን ለመገደብ የሚያስችል ስልጣን አልተሰጠውም።

በመሰረቱ ፍርሃትን ለማስወገድ የተፈጠረ አካል ሌላ ፍርሃት መፍጠር የለበትም። የሰው ልጅ ነፃነቱን ለማረጋገጥ ሲል ከነፃነቱ ላይ ቀንሶ የፈጠረው መንግስት ራሱ መልሶ ነፃነቱን ሊነፍገው አይገባም። መንግስት የዜጎችን ነፃነት የሚነፍግ ከሆነ የተፈጠረበት ዓላማ ስቷል። ተፈጥሯዊ ዓላማውን የሳተ ነገር ሁሉ ፋይዳ-ቢስ ነው። እንደዚሁም የዜጎችን ነፃነት የሚነፍግ መንግስት ፍይዳ-ቢስ ነው።

የመንግስት ሕልውና የተመሰረተው የዜጎችን መብትና ነፃነት በማክበርና በማስከበር ላይ ነው። የዜጎች መብትና ነፃነት የሚረጋገጠው ደግሞ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ነው። ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲኖር ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም የመንግስት አካላት፡- ሕግ አውጪዎች፣ ሕግ ተርጓሚዎች እና ሕግ አስፈፃሚዎች ሥራና ኃላፊነታቸውን ነፃና ገለልተኛ በሆነ መልኩ መወጣት አለባቸው። እነዚህ የመንግስት አካላት ሥራና ኃፊነታቸውን በነፃነት መወጣት ከተሳናቸው ግን የዜጎችን መብትና ነፃነት ማክበርና ማስከበር አይቻልም።

ፍርሃት በነገሰበት ሀገር በነፃነት ማሰብ ወንጀል ይሆናል፣ በነፃነት መናገር ከአመፅ ይቆጠራል፣ በነፃነት መፃፍ ለእስርና ስደት ይዳርጋል። የሀገሪቱን ዜጎች በነፃነት ከመኖር፥ ከማሰብ፥ ከመናገርና ከመፃፍ የሚያግድ መንግስት ከእድገት ይልቅ ውድቀትን የመረጠ ነው። እንደ ፈረንሳዊው ልሂቅ “Montesquieu” አገላለፅ፣ የዜጎችን መብትና ነፃነት በአግባቡ ማረጋገጥ የተሳነው መንግስታዊ ሥርዓት ተንኮታኩቶ ይወድቃል፡-

“The political liberty of the subject is a tranquility of mind arising from the opinion each person has of his safety. In order to have this liberty, it is requisite the government be so constituted as one man need not be afraid of another. When the legislative and executive powers are united in the same person, or in the same body of magistrates, there can be no liberty; … Again, there is no liberty, if the judiciary power be not separated from the legislative and executive. …As all human things have an end, the state we are speaking of will lose its liberty, will perish. Have not Rome, Sparta, and Carthage perished?” Baron de Montesquieu, The Spirit of Laws, trans. Thomas Nugent, 2 vols. Part 1: page151–162.

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories