የኢህአዴግ ተሃድሶ መጀመሪያና መጨረሻ

በጦላይ የተሃድሶ ሥልጠና ማጠናቀቂያ ፕሮግራም ላይ በአካል ተገኝተው የነበሩት ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር፤ “እናንተ በዚህ የተሃድሶ ስልጠና ‘ታድሳችኋል’! አሁን የቀረው ደግሞ የመንግስት ተሃድሶ ነው። እኛም እንደ እናንተ ጥልቅ የሆነ ተሃድሶ ለማድረግ ተዘጋጅተናል!” አንዱ ከበስተኋላዬ አንዲህ ሲል ሰማሁት “ኧረ በለው…ምድረ ባለስልጣን እንደ እኛ በጦላይ ፍዳውን ሊቀምስ ነው!?”

እንደው ግን ለመሆኑ ይኼ “ተሃድሶ” የሚባለው ነገር ምንድነው?፣ መጀመሪያና መጨረሻው የት ነው?

በመሰረቱ አንድ ነገር የሚታደሰው ስለተበላሸ፤ እንደቀድሞ መደበኛ ተግባሩን ወይም አገልግሎቱን በሚገባ መስጠት ሳይችል ሲቀር ነው። መንግስት “ጥልቅ የሆነ ተሃድሶ ያስፈልገኛል” ካለ በእርግጥ በውስጡ የተበላሸ ነገር ስለመኖሩ ማረጋገጫ እየሰጠ ነው። ስለዚህ፣ ልዩነት ሊኖር የሚችለው በተሃድሶ አስፈላጊነት ላይ ሳይሆን “የት ተጀምሮ የት ይጠናቀቃል?” በሚለው ላይ ነው። ከዚህ አንፃር፣ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ አብዛኞቹ ባለድርሻ አካላት ግልፅ የሆነ አቅጣጫና ግንዛቤ ያላቸው አይመስለኝም፡፡ በዚህ ፅሁፍ መንግስት ሊደረግ ያታቀደው ጥልቅ ተሃድሶ የት ተጀምሮ የት መድረስ አንዳለበት በዝርዝር ለማየት እንሞክራለን፡፡

1ኛ) የተሃድሶ መጀመሪያ ራስን ማደስ ነው!

መንግስት እንደ ትምክህትና ጠባብ ብሔርተኝነት ያሉ ጥገኛ አመለካከቶችን በሀገሪቱ ለታየው አመፅና አለመረጋጋት ዋና መንስዔ እንደሆኑ በተደጋጋሚ ሲጠቅስ ይሰማል። እነዚህ የአመለካከት ችግሮች በአንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በገዢው ፓርቲ ውስጥም ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ባሉ አመራሮች ዘንድ እንደሚስተዋሉ ይገልፃል። በሌላ በኩል እንደ ጦላይ ባሉ የተሃድሶ ስልጠና ማዕከሎች የሚሰጠው ስልጠና በዋናነት እስረኞችን/ሰልጣኞችን በአመፅና ረብሻ ተግባራት እንዲሰማሩ ያደረጓቸው እነዚህ የተሳሳቱ አመለካከቶች ናቸው በሚል እምነት ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ ታዲያ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ “እኛም እንደ እናንተ ጥልቅ የሆነ ተሃድሶ ለማድረግ ተዘጋጅተናል!” ሲሉ መንግስት ሊያደርግ ያሰበው ተሃድሶም በተመሣሣይ የትምክህትና ጠባብ ብሔርተኝነት አመለካከቶች ላይ ያነጣጠረ እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡

በእርግጥ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በሀገራችን ለታየው አመፅና አለመረጋጋት ዋናው መንስዔ በአንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የሚስተዋለው የአመለካከት ችግር ሳይሆን በራሱ በመንግስት ዘንድ የነበረው የአመለካከት ችግር እና የሥራና አሰራር ክፍተት ነው። ችግሩ በተለያየ ደረጃ ያለው የመንግስት ሥራና አሰራር የዜጎችን እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ባለመከናወኑ ምክንያት የተፈጠረ ነው። ስለዚህ፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች ከታየው የአመፅና አለመረጋጋት ችግር በስተጀርባ ያለው የዜጎች የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ እንጂ የአመለካከት ችግር አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ከሕዝቡ ለሚነሱት ጥያቄዎች የድጋፍ ወይም ለዘብተኛ የሆነ አቋም የሚያራመዱ ግለሰቦች፣ እንዲሁም የገዢው ፓርቲ አባላትና አመራሮች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በትምክህተኝነት ወይም በጠባብ ብሔርተኝነት እየተፈረጁ ያሉበት ሁኔታ ነው ያለው። በገዢው ፓርቲ ለአመፁና አለመረጋጋቱ በመንስዔነት እየተጠቀሱ ያሉት የትምክህትና ጠባብ ብሔርተኝነት አመለካከቶች ከሕዝቡ እየተነሱ ላሉው የእኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ነፀብራቆች እንጂ በራሳቸው እንደ ችግር ሊጠቀሱ የሚችሉ አይደሉም። ስለዚህ፣ መንግስት የሌሎችን አመለካከት ለማስቀየር ከመኳተን ይልቅ የራሱን አመለካከት፣ ሥራና አሰራር ለማሻሻል ጥረት ቢያደርግ ይመረጣል፡፡

በአጠቃላይ፣ የኢህአዴግ ተሃድሶ ሀገሪቷን ያጋጠሟት ችግሮች በአንዳንድ ሰዎች የተሳሳተ አመለካከት አማካኝነት ሳይሆን በተሳሳተ የመንግስት ፖሊሲ፣ አሰራርና ሥራ አማካኝነት የተፈጠሩ መሆናቸውን አምኖ መቀበል ይጠይቃል፡፡ በዚህ መሠረት፣ የተሃድሶው የመጀመሪያ ተግባር መንግስት ስለ ችግሩ ያለውን አመለካከት መቀየር ይሆናል። በቅድሚያ ከሕዝቡ የሚነሱትን ጥያቄዎች እንደ ከዚህ ቀደሙ የተሳሳተ አመለካከት ውጤቶች ናቸው ብሎ ከመፈረጅ ሊቆጠብ ይገባል፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ አግባብነት ያላቸው የእኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች መሆናቸውን አመኖ መቀበል አለበት፡፡ ጥልቅ ተሃድሶ የሚጀምረው የመንግስትን የተሳሳተ አመለካከት በማደስ ነው፡፡ በአጠቃላይ፣ የተሃድሶ መጀመሪያ ራስን ማደስ ነው!

2ኛ) የተሃድሶ መጨረሻ ሕገ-መንግስቱን ማክበር ነው!

ከላይ ሀገሪቷ ያጋጠሟት ችግሮች በዋናነት በተሳሳቱ የመንግስት ፖሊሲዎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና ውሳኔዎች አማካኝነት የተፈጠሩ መሆናቸውን አይተናል፡፡ ከዚህ በመቀጠል፣ “የተሃድሶ መጨረሻ ምንድነው?” የሚለውን እንመለከታል፡፡

በመሠረቱ የዴሞክራሲያዊ መንግስት ህልውናው የተመሰረተው፣ የሥራና አሰራሩ አግባብነት የሚወሰነው ከሕገ-መንግስቱ አንፃር ነው፡፡ በኢትዮጲያም የመንግስታዊ ሥርዓቱ ዋስትና ያለው በዋናነት በሕገ-መንግስቱ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ፣ መንግስት ከዚህ በፊት፣ አሁንም ሆነ ወደፊት ተግባራዊ ያደረጋቸውና የሚያደርጋቸው ፖሊሲዎች፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና ውሳኔዎች በሙሉ ከሕገ-መንግስቱ አንፃር መቃኘት አለባቸው፡፡ 

በተቃራኒው የኢህአዴግ መንግስት ሀገሪቱ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትና የመስረተ ልማት መስፋፋት በስልጣን ላይ ለመቀየት እንደ ዋስትና ሲጠቅስ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ካለፈው አመት ጀምሮ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ግን “ከኢኮኖሚ እድገቱ እኩል ተጠቃሚ አልሆንም፣ በሀገሪቱ ያለው የሃብትና ስልጣን ክፍፍል ፍትሃዊ አይደለም” በሚል እሳቤ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ለምሳሌ፣ አንዳንድ የሕብረተሰብ ክፍሎች “በኢኮኖሚ እድገቱ ውስጥ የበይ-ተመልካች ሆነናል!” ወይም “በልማት ስም ያለ በቂ ካሳ ተፈናቅለናል” በማለት ለተቃውሞና አመፅ ወደ አደባባይ ወጥተዋል፡፡ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ፤ “የእናንተ ጥቅምና ተጠቃሚነት ቢረጋገጥም፣ ባይረጋገጥም ዓለም የመሰከረለት ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግበናል” እያሉ መደስኮር “በሰው ቁስል…” የሚሉት ዓይነት ነው፡፡

በማንኛውም አጋጣሚ ቢሆን የሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ ድንጋጌዎችና መርሆች መሸራረፍ የለባቸውም፤ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እኩል ሊከበሩ ይገባል፡፡ ማንኛውም ዓይነት የመንግስት ፖሊሲ፣ አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ ወይም ውሳኔ የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብትና ነፃነት የሚፃረር እስከሆነ ድረስ መንግስትን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እያሳጣውና የሕልውና መሰረቱን እየናደ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የኢህአዴግ መንግስት ላለፉት አስር አመታት የልማታዊ መንግስት አቅጣጫን በመከተል ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ከማክበርና ማስከበር ይልቅ ፈጣን የሆነ የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ ላይ ትኩረት ማድረጉ የሚታወቅ ነው፡፡

አንድ ማሣያ ለመጥቀስ ያህል፣ በኢፊዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 43 መሰረት ዜጎች የተሻለ የኑሮ ሁኔታና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት መብት አላቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ አንቀፅ 29 ዜጎች “የአመለካከት እና ሀሳብን በነፃ የመያዝና የመግለፅ መብት” እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን፣ በተለይ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የኢህአዴግ መንግስት ሲከተለው የነበረው የልማት አቅጣጫ አንቀፅ 43ን በአንቀፅ 29 የሚለውጥ – የልማት መብትን በፖለቲካዊ መብት ልዋጭ አድርጎ የሚያቀርብ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ፣ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በመሸራረፍ በከፊል ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር ሀገሪቷን አሁን ላይ ላጋጠማት የፀጥታና አለመረጋጋት ችግር ዳርጓታል፡፡ ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሕገ-መንግስቱን ያለ ምንም መሸራረፍ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም፣ መንግስት ሊያደርግ ያቀደው ተሃድሶ የመጨረሻ ግብ፤ ሕገ-መንግስታዊ መብቶችን የሚገድቡ አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች ማንሳት፤ በሕገ-መንግስቱ መሰረት ከተሰጠ ስልጣንና ኃላፊነት ውጪ የተሰሩ ሥራዎችና የተዘረጉ አሰራሮችን ማስተካከል፣ እንዲሁም በሁሉም የስልጣን እርከኖች ላይ ያሉትን ሥራዎችና አሰራሮች በሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ መርሆች ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ በማድረግ የዜጎችን የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን በማክበርና ማስከበር ላይ ማዕከል ሊያደርግ ይገባል፡፡ በዚህ መሰረት፣ የተሃድሶው መጨረሻ ሕገ-መንግስቱን ማክበርና ማስከበር ይሆናል!

በአጠቃላይ፣ ሊደረግ የታቀደው ተሃድሶ መጀመሪያው ኢህአዴግ ራሱን ማደስ ሲሆን መጨረሻው ደግሞ ሕገ-መንግስቱን ማክበርና ማስከበር ነው! ከዚህ ውጪ የሚደረግ ተሃድሶ የሀገሪቱን ዘርፈ-ብዙ ችግሮች ይበልጥ ከማወሳሰብ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories