ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ምሁር የለም!

እስር ቤት ሳለሁ ፖሊሶች በተደጋጋሚ ሲጠይቁኝ የነበረውና በቀጥታ ለመመለስ የተሳነኝ ጥያቄ እንዲህ ይላል፡- “ከሰለጠንክበት የመምህርነት ሙያ ውጪ የፖለቲካ ፅሁፎችን እንድትፅፍና እንድታሳትም ማን ፈቀደልህ?” ይህን ጥያቄ ለመመለስ ያደረኩት ጥረት ፍሬ-አልባ ነበር። ይህ እንደ በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት ዴሞክራሲያዊ መብቴ፣ እንዲሁም በከፍተኛ ት/ት ተቋማት አዋጅ አንቀፅ 4(3) እና በአምቦ ዩኒቨርሲቲ መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 13(2) መሠረት ማህበራዊ ግዴታዬ ነው። የፖሊሶቹ ጥያቄ ግን ዴሞክራሲያዊ መብቴንና ማህበራዊ ግዴታዬን እንደ ወንጀል በሚቆጥር የተሳሳተ እሳቤ ላይ የተመሠረተ ነው። ስለዚህ፣ ለእንዲህ ያለ የተሳሳተ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ ራሱ ጥያቄውን ማስተካከል ነው፡፡ ነገር ግን፣ የእኛ ፖሊሶች ለጠየቁት ጥያቄ መልስ እንጂ ማስተካከያ አይሹም። 

በእርግጥ ሁሉም ፖሊሶች የማህብረሰቡ አካል ናቸው። በእነሱ ጥያቄ ውስጥ ያለው የተሳሳተ እሳቤ በአብዛኛው የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ በስፋት የሚንፀባረቅ ነው። እንደ እኔ በመምህርነት ወይም በሌላ የሙያ መስክ ከተሰማራ ሰው የሚጠበቀው “ሙያተኝነት” (professionalism) ነው። ምክንያቱም፣ እያንዳንዱ ባለሙያ በሰለጠነበት የሙያ መስክ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ይፈለጋል። ብዙውን ግዜ ከመደበኛ ሥራው በተጓዳኝ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አይበረታቱም። በተለይ ደግሞ ከፖለቲካ ጋር የሚነካካ ከሆነ ፍፁም ተቀባይነት የለውም። 

እንዲህ ባለ ማህብረሰብ ውስጥ የምሁራን ሚና ምን መሆን አለበት? በዚህ ዙሪያ “Edward Said” የተባለው ልሂቅ “Representations of an Intellectual” በሚል ርዕስ ጥልቅ ትንታኔ የሰጠ ሲሆን የምሁራንን (intellectuals) ችግር እንዲህ ሲል ይገልፀዋል፡- 

“The particular threat to the intellectual today, whether in the West or the non-Western world, is not the academy, nor the suburbs, nor the appalling commercialism of journalism and publishing houses. Rather the danger comes from an attitude that I shall be calling professionalism; that is, thinking of your work as an intellectual as something you do for a living, between the hours of nine and five with one eye on the clock, and another cocked at what is considered to be proper, professional behaviour – not rocking the boat, not straying outside the accepted paradigms or limits, making yourself marketable and above all presentable, hence uncontroversial and unpolitical and “objective”” Edward Said (1993): Representations of an Intellectual, Reith Lectures 1993

ከላይ እንደተገለፀው፣ ሙያተኝነት ወይም ፕሮፌሽናሊዝም (professionalism) በአብዛኞቹ የሀገራችን ምሁራን ዘንድ በግልፅ የሚስተዋል ችግር ነው። በእርግጥ ሙያተኝነት በራሱ እንደ ችግር ሊወሰድ አይገባም። እያንዳንዱ ባለሙያ በሰለጠነበት መስክ የሚጠበቅበትን አገልግሎት የመስጠት ሃላፊነትና ግዴታ አለበት። ስለዚህ፣ ሙያተኛ ከመደበኛ ሥራውና ከሙያ ስነ-ምግባሩ ውጪ ይሁን እያልኩ አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ እንደ አንድ የተማረ ሰው ሙያተኝነት የተጣለብንን ማህበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት ሊያግደን አይገባም ነው። በአጠቃላይ፣ ሙያና ሙያተኝነት እንደ መደበቂያ፣ ከኃላፊነት መሸሸጊያ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። 

አንድ የተማረ ሰው በሰለጠነበት ሙያ (profession) ስም ከሚፈፅማቸው ስህተቶች በጣም የከፋው መደበኛ ሥራውን በተለመደው መንገድ እየሰራ፣ በከረመ አስተሳሰብ አንድ ዓይነት ሃሳብ እያመነዠከ፣ በማህበራዊ ሕይወት ውስጥ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅበትን ድርሻ ሳይወጣ ሲቀርና፣ በዚህም ከማንኛውም ዓይነት ውዝግብና ፖለቲካ ነፃ ለመሆን ሲሞክር ነው። በዚህ መልኩ፣ “እኔ ከውዝግብና ፖለቲካ ነፃ ነኝ” እያሉ የሚመፃደቁ ምሁራን የተጣለባቸውን ማህበራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንደተሳናቸው በራሳቸው ላይ እየመሰክሩ ያሉ ናቸው። 

የተማረ ሰው ከመደበኛ ሥራው ባለፈ ያለበት ማህበራዊ ኃላፊነት ምንድነው? በተለይ እንደ ኢትዮጲያ ባሉ ሀገራት የብዙሃን ሕይወት በዘርፈ-ብዙ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የተተበተበ መሆኑ እርግጥ ነው። እነዚህን ችግሮች መቅረፍ የሚቻለው የማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል ሲኖር ነው። ከዚህ አንፃር ምሁራን ከመደበኛ ሥራቸው በተጓዳኝ አስፈላጊውን ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የበኩላቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል። “ይህን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንዲችሉ የምሁራኑ ሚና ምን መሆን አለበት?” የሚለውን አስመልክቶ “Edward Said” የሚከተለውን ትንታኔ ሰጥቷል፡-

“Every intellectual has an audience and a constituency. The issue is whether that audience is there to be satisfied, and hence a client to be kept happy, or whether it is there to be challenged, and hence stirred into outright opposition, or mobilised into greater democratic participation in the society. But in either case, there is no getting around authority and power, and no getting around the intellectual’s relationship to them. How does the intellectual address authority: as a professional supplicant, or as its unrewarded, amateurish conscience?” Edward Said (1993): Representations of an Intellectual, Reith Lectures 1993

እያንዳንዱ ምሁር በሙያዊ ገለልተኝነት ስም በስልጣን ላይ ላለ አካል ድጋፍ ሰጪ ሆኖ ከማገልገል ይልቅ በራሱ ሕሊና እየተመራ የተጣለበትን ማህበራዊ ኃላፊነት መወጣት ይጠበቅበታል። ሆኖም ግን፣ ምሁራን በተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ለውጥና መሻሻል ለማምጣት የሚያደርጉት ማንኛውም እንቅስቃሴ ከውዝግብና ከፖለቲካ ተፅዕኖ ነፃ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ፣ ምሁራን ከአወዛጋቢነትና ከፖለቲካዊ ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መልኩ ሚናቸውን መወጣት አይችሉም። 

በመደበኛው ሥራና አሰራር ላይ ብቻ ተወስኖ መቅረት ማህበራዊ ኃላፊነትን ካለመወጣት በተጨማሪ በስልጣን ላይ ካለው ኃይል ጋር በመተባበር በሕዝቡ ላይ በደል እንደመፈፀም ይቆጠራል። ምክንያቱም፣ ያለ ምሁራን ተሳትፎ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣት አይችልም። ምሁራን ራሳቸውን ከአወዛጋቢና ፖለቲካዊ ከሆኑ ተግባራት ባገለሉበት ሁኔታ ደግሞ ዘላቂ የሆነ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ማረጋገጥ አይችልም። 

ምሁራኑ ከፖለቲካው መድረክ ገለልተኛ በመሆናቸው ምክንያት ተጎጂ የሚሆነው በፖለቲካ ስልጣን ላይ ያለው አካል ጭምር ነው። ምክንያቱም፣ ዘላቂ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማት ማረጋገጥ የተሳነው ፖለቲካዊ ስርዓት ሕልውና ሊኖረው አይችልም። ስለዚህ፣ ምሁራን ከፖለቲካ ነፃና ገለልተኛ ከሆኑ በሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ የተሻለ ሕይወት የመኖር ተስፋ ይመነምናል። በዚህ መሰረት፣ በሙያተኝነት ስም አወዛጋቢና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነፃ ሆኖ ለመንቀሳቀስ መሞከር ፍፁም የሆነ አገልጋይነት እንጂ ትክክለኛ የምሁራን ባህሪ አይደለም። በአጠቃላይ፣ “ከፖለቲካ ነፃ የሆነ አገልጋይ እንጂ ምሁር የለም” ብሎ መደምደም የሚቻል ይመስለኛል። 

ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ወደሆነው ጥያቄ ስንመለስ፣ “ከሰለጠንክበት የመምህርነት ሙያ ውጪ የፖለቲካ ፅሁፎችን እንድትፅፍና እንድታሳትም ማን ፈቀደልህ?” ይላል። ነገር ግን፣ ፅሁፎችን መፃፍና በተለያዩ ድረገፆች ላይ ማሳተም የዜግነት መብቴ ብቻ ሳይሆን እንደ ተማረ ሰው የተጣለብኝን ማህበራዊ ግዴታ ለመወጣት ጥረት የማደርግበት መንገድ ነው። መጀመሪያ ላይ እንደገለፅኩት ለተሳሳተ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ ጥያቄውን ማስተካከል ነው። ስለዚህ፣ ለፖሊሶቹ ጥያቄ ትክክለኛው መልስ፤ “እንደ ተማረ ሰው ከመደበኛ ሥራህ ውጪ የተለያዩ ፅሁፎችን በመፃፍና በማሳተም መብትና ግዴታህን እንድትወጣ ማን ፈቀደልህ?” የሚለው ይመስለኛል። ከምር ግን በወቅቱ እንዲህ ብለው ቢጠይቁኝ ኖሮ መልስ አይኖረኝም ነበር።

***********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories