የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት ላይ ያነጣጠረ መሰረተ ቢስ ውንጀላ እስከ መቸ?

(ታጋይ ካሕሳይ ቃሉ)

በዚሁ ወር መጀመሪያ ሳምንት በትግራይ ኦንሊይን (Tigray online) ድረ-ገፅ ላይ በአቶ እውነቱ ዘለቀ የተባሉ ፀሃፊ “ያን ያህል ወጥ መርገጥ ምን የሚሉት ድፍረት ነው”[PDF] በሚል ርእስና ቀደም ብሎ በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Gedu Andargachew; A fifth column on the loose” በሚል ርእስ በአቶ ብርሀነ ካሕሳይ ተፅፎ ለተዘረጋው ፅሁፍ መልስ ለመስጠት ታስቦ የወጣውን ፅሁፍ ተመለከትኩ፡፡ የፅሁፉ መነሻ የአቶ ብርሀነ ፅሁፍ ይሁን እንጂ አይጋ ፎረምና እሳቸው እየተጠቀሙበት ያለው የትግራይ ኦንላይን ድረ-ገፆች፣ የውራይና መፅሄት፣ በዋናነት ደግሞ የትግራይ ህዝብና መሪ ድርጅቱ ህወሓት ላይ ያነጣጠረ መሰረተ ቢስ ውንጀላ ሆኖ ነው ያገኘሁት::

በዚህ ሳያበቃ በተመሳሳይ ስም ደግሞ ከሶስት ቀን በኋላ በአይጋ ፎረም ላይ የወጣና “የግለሰቦችን ስም በማጠልሸት የህብረተሰቡ መሰረታዊ ችግሮች መፍትሄ ያገኝ ይሁን”[PDF] በሚል ርእስ ሃምሌ ወር በአይጋ ፎረም ለወጣው “የፖለቲካ ኤልኒኖ በኢህአደግ” በሚል ርእስ በአቶ ሰላምወርቅ በሚባሉ ፀሃፊ የለወጣ ፅሁፍ ምላሽ ለመስጠት የወጣ ፅሁፍን አነበብኩ::

የአቶ እውነቱ ፅሁፍ ብዙ ነገር የነካካ ስለነበረ ምናልባት የተወሰነ ነገር ይገኝበት እንደሆነ በማሰብ የተጠቀሱት ፅሁፎች በሙሉ ወደ ኋላ በመሄድ እውነታውን መፈተሽ የተሻለ እንደሆነ በማመን ሁሉም ለማየት ሞከርኩ፤ የነበረኝን እውቀትና ያገኘሁዋቸው ነገሮች ግን የተገላቢጦሽ ሆኑብኝ እናም ለዘመናት እየተዋሸና መልስ ስለማይሰጥበት እውነት እየመሰለ እየሄደ በመሆኑ ይህቺን ለመፃፍ ወሰንኩኝ::

በመጀመሪያ ግን መነሻ በሆነው የአቶ ብርሃነ ካሕሳይና አቶ ሰላምወርቅ ፅሁፎች ያለኝ አቋም ልግለፅ:: በመጀመሪያና ከሁሉም በላይ የአቶ ብርሀነ ፅሁፍ ማለትም በይዘቱ ላይ ያለው የትግራይ ህዝብ እምነትና ፍላጎት ያልሆነውን እንደተጠበቀ ሆኖ ሊነግሩን የፈለጉት ለኛ የትግራይና የአማራ ህዝቦች ከሆነ ለምን በእንግሊዝኛ ቋንቋ መፃፍ አስፈለጋቸው? ወይስ አማርኛና ትግርኛ መፃፍ አይችሉም ካልቻሉ ደግሞ ተወልደው አድገዋል እንዴት ሊባል ይችላል? ስለሆነም በኔ እምነት ለጊዜውም ቢሆን መምሰል ይቻል ይሆናል መሆን ግን አይቻልም:: ሌላው የአቶ ብርሀነ ችግር በአማራ ክልል እየታዩ ያሉ ችግሮች አንድ ሁለት ብለው አስቀምጠዋል ትክክል ነው ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ችግሮች በአገር ደረጃ የሚታዩና ለመፍታትም ጥረት እየተደረገ መሆኑ ሁላችን የሰማነው ነው:: ችግሩ ያለው በመፍትሄነት ያስቀመጡት ሃሳብ ላይ ልዩነት አለኝ:: ምክንያቱም የነዚህ ችግሮች መከሰት አቶ ገዱ ድርሻ ሊኖራቸው ካልሆነ እሳቸው ብቻ ናቸው ማለት አይቻልም::

ስለሆነም ችግሮቹ ከስረመሰረታቸው ለመፍታት የአቶ ገዱ ከስልጣን መውረድና ኣለመውረድ ብቻውን መፍትሄ አይሆንም ዋናው መፍትሄ ችግሮቹ የተያዙበት መንገድና የታያዘው አቅጣጫ ነው:: ኦህዴድ ስለወረዱ ብአዴንም መውረድ አለባቸው ከሆነ ትክክል አይደለም:: የየራሳቸው ነፃነት ያላቸው ድርጅቶች በመሆናቸው የሚወስዱት እርምጃም ሊለያይ ይችላል ዋናው ነገር ነገሮችን የሚይዙበት መንገድ በኢህአደግ ደረጃ በጋራ ያስቀመጡት አቅጣጫ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው::

ለኔ ትርጉም ያለው ጉዳይ ብአዴን ጉዳዩን የያዙበት መንገድ ችግሮቹን ከስረ መሰረቱ የሚፈታ መስሎ አልተሰማኝም ለዚህም ማሳያ የሚሆነኝ በሚከተሉት ነጥቦች ላይ ግልፅ አይደለሁም

1/ በቕማንት ህዝብ ማንነት ላይ በኢትዩጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የተሰጠው አቅጣጫና አቶ እውነቱም በፅሁፋቸው በሚገባ የገለፁት ችግር አፈታቱ ላይ ያለው ግልፅነት አሁን ደግሞ በተፈጠረው ግርግር የተዳፈነ መሆኑ

2/ ጎንደር ላይ የነበረው ሰልፍና የነበረው አላማ ፀረ ህገ-መንግስትና የአንድን ብሄር ማንነት የሚያንቋሽሽ ከመሆኑ በተጨማሪ መንግስት የለም የሚል መልእክት ያስተላለፈና ቀጥሎ የመጣው ብጥብጥና ውድመት የልብ-ልብ የሰጠ ሆኖ ሳለ ተጠያቂነት የሌለውና በሰላም የተጠናቀቀ እውቅና የሌለው ሰለፍ እየተባለ ሲወደስ መስማት በብአዴንና በክልሉ መንግስት ያለው አካሄድ በህገ-መንግስቱ ትግበራ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑ

3/ የወልቃይት ጉዳይ በተመለከተ የወልቃይት ህዝብ ምን ይላል ለጊዜው እንተወውና ችግር ካለም እንዴት መፈታት እንዳለበትና ማንን እንደሚመለከት በግልፅ በህገ-መንግስቱ ሰፍሮ እያለ የወልቃይት አስመላሽ ኮሚቴ ተብሎ በጎንደር የተደራጀ ሃይል ቢሮ ከፍቶ የጎንደር ህዝብ እየቀሰቀሰ ሰልፍ (ህገወጥ ሰልፍ) እስከማድረግ ሲሄድ ብአዴንና የክልል መንግስት ምን ሲያደርጉ እንደነበረ ሳይመለስ አሁንም ይህ ጉዳይ የአማራ ክልል ጉዳይ ሳይሆን የትግራይ ክልል ጉዳይ ስለሆነ እጃችሁን አንሱ በሚል ተግባብተው ከሄዱ በኋላም በክልል አጀንዳ ሆኖ መቀጠሉ:: ከዛም አልፎ በተሃድሶ ስብሰባ የትግራይ ክልል ካልመለሰው እስከ ፈደራል እንወሰደዋለን የሚል ዛቻ አዘል ውይይት እየተካሄደ መሆኑ::

4/ በክልሉ በተፈጠረው ብጥብጥ የደረሰው ጉዳት ለሁሉም ደርሷል ያሳዝናልም:: ግን እኮ የክልሉ መንግስና መሪ ድርጅቱ ተጠያቂ ናቸው:: የሚያሳዝነው ግን የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ሰዎችና ንብረታቸው እየታደነ ሲገደልና ሲቃጠል አልነበረም እንዴ? ከ8000 በላይ ትግርኛ ተናጋሪ አይደለም እንዴ የተፈናቀለው? ህዝብን በማገልገል ስራ የተሰማራው ሰላም ባስ አይደለም እንዴ የተቃጠለው? እና ይህ ህዝብ አገሬ ነው ወገኔ ነው ብሎ አይደለም እንዴ እዛ አከባቢ የሰፈረው? እና ለዚህ ይቅርታ አይጠየቅም እንደቀላል ነገር ይቅርታ ለመጠየቅ የሚያስችል ነገር አልሰራንም ተብሎ የታለፈው:: ዋናው ነገር የሞተውና የተባረረው ህዝብ ቁጥር ሳይሆነው የተገደለበትና የተባረረበት መንገድ ትግሬ ይውጣልን የሚል መፈክር ተይዞና ተቀስቅሶበት በመሆኑ እኮ ነው:: ብአዴንስ የወልቃይት የማይመለከተው አጀንዳ ከሚያደርግ የውስጥ ችግሩ በመፍታት ላይ ማተኮር አልነበረበትም? እዚህ ላይ ራሳቸው ተፈናቃዮቹ እንደገለፁት ወንድም የሆነው ሰፊው የአማራ ህዝብ የትግራይ ተወላጆች እንዳይጎዱ ያደረገው ትብብርና ኋላም ሽማግሌዎቹን ትግራይ ድረስ በመላክ ላሳየው ድጋፍ አሁንም በህዝቦች መሃል ያውን ትስስር እኛ ምንም ብናወራና ብንዘባርቅ ፍፁም የማይለያይ ስለመሆኑ የሚያስረግጥ እውነት መሆኑ እቀበላለሁ::

በአጠቃላይ እነዚህንና የመሳሰሉት የክልሉና የድርጅቱ ውስጣዊ ጉዳይ በማተኮር የነበሩት ፀረ ህገ-መንግስትና የጎራ መደበላለቅ ችግሮች በመፍታትና እስከጥግ ድረስ በመሄድ መለየት ለአማራ ህዝብ የዘላቂ ልማትና እድገት ዋስትና መስጠት ነበረበት ባይ ነኝ:: በመሆኑም አቶ ብርሃነ ያስቀመጡት የመፍትሄ ሃሳብ የታያቸው የመፍትሄ ሃሳብ ማስቀመጣቸው እንደ አቶ ተኮላ ባያስፈራኝምና እንደ አቶ እውነቱ ባያናድደኝም ቅድሚያ የሚመጣ ብቸኛ መፍትሄ ነው ብየ ግን አላምንበትም:: ምክንያቴ ደግሞ ላይ ለመግለፅ የሞከርኩትን ጉዳይ ሳይፈታ የሰዎች መቀያየር ብቻ ስለሚሆን የአቶ ገዱ መውረድና አቶ እውነቱ ወደ ስልጣን መምጣት ያው ስለሆነ:: እነዛ የጠቀስኩዋቸው ጉዳዮች እስካልተጣሩና ባለቤታቸው በሚለይና መበደላለቁን ሳይቀረፍ አቶ ገዱ የተገለፀው ሃጥያት በትክክል እጃቸው አለበት የለበትም ብሎ መከራከር ውሃ የሚቋጥር አይደለም:: በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ጉዳዮች ተጣርተው ባለቤታቸው እስካልታወቀ ደግሞ የክልሉ ፕረዚዳንት በመሆናቸው ብቻ ተጠያቂነታቸው ከሌላው ባለስልጣን እንደሚጎላ ሳይታለም የተፈታ (Guilty until proven innocent) ነው::

እስቲ አሁን ደግሞ የአቶ እውነቱ ሃሳቦች እውነት ካላቸው እንያቸው:: እዚህ ላይ የአቶ ተኮላ እምነትም ከአቶ እውነቱ የተለየ እንዳልሆነ መታወቅ አለበት:: አቶ ተኮላ የአቶ ብርሀነ ፀሁፍ እንጂ ጎንደር ሽንፋእና መተማ የሞተው ሰው አያስፈራቸውም ምክንያታቸው ባለውቅም::

አቶ እውነቱ ዘለቀ (ሌላ ካልሆኑ) ባለፈው አመት “የኢህአደግ አመራር መሰረታዊ ስህተቶች” በሚል አርእስት የፃፉት አይቼ ነበር በወቅቱ ሳነበው በተደጋጋሚ መልስ የተሰጠበት ደርጎችና ኢህአፓዎች ግን ምንም ያህል መልስ ቢሰጣቸው ነገርን መላልሰው በመቆስቆስ እውነት ለማስመስል አልመውና እምቢ ብለው ስለሚሰሩ ጊዜ ማጥፋት ነበር አሁንም ለዚሁ ፅሁፋቸው መልስ የመስጠት ሃሳብ የለኝም ሆኖም ፅሁፉ ከጅምሩ የተሳሳተ መሆኑ ለማሳየት የኢህአደግ ጥንካሬ ብለው ከገለፁት “ኢህአደግ በሽግግር መንግስት ምስረታ ወቅት ከኢሰፓና ኢህአፓ ውጪ ሌሎች ፓርቲዎች ጋብዘዋል” ይሉናል በወቅቱ የተጋበዙት ግን ከኢሰፓ ውጪ የነበሩት የታጠቁና ያልታጠቁ ፓርቲዎች (ኢህአፓም ጭምር) ነው ኢህአፓ በትእቢት ተወጥሮ ወያነ በጠራው ኮንፈረንስ አልሳተፍም ብሎ ቢቀርም:: ሃቁ ይሀ ሁኖ ሳለ የኢህአፓ ትእቢት ላለመቀበል ሲባል ኢህአፓ እንዳልተጠራ አድርጎ ማቅረብ የምን ታሪክ ማዛባት ነው::  የኢህአደግ ስህተቶች ተብለው የተጠቀሱትም ቢሆን ለኔ እንደሚገባኝ እነሱ ሳይሆን ከጅምሩ ጀምሮ በደርጎችና ኢህአፓዎች ሲነዛና ሲዘራ የነበረው በአንድ ብሄር ያነጣጠረ ዘረኛ የበሬ ወለደ ወሬና አሉባልታ በሚገባ እየተመከተ አዲሱን ትውልድ እንዳይበርዝ አለማድረጉና ችላ ብሎ ማለፉ ነው::

አቶ እውነቱ በአቶ ገዱ ላይ የተቀመጡት የግለ ሰቦች የግል አስተያየቶች በመቃወም የተሰማቸውና የሚያምኑበት መልስ መስጠታቸው መብታቸው ስለሆነ በምንም መለኪያ ስህተት አይሆንም:: በአቶ ገዱም ሆነ በራሳቸው ላይ እንዲደርስ የማይፈልጉት ያልተገባና ያልተጣራ የሚሉትን አይነት አስተያየት መስጠት ግን በዚሮ ማባዛት ነው:: አቶ ገዱ አቶ እውነቱ እንዳስቀምጧቸው መልአክ ኣይደሉም በሌላ በኩል አቶ ብርሃነ እንዳስቀመጧቸውም ሰይጣንም አይደሉም ሰው በመሆናቸው የፈፀምዋቸው ጉድለቶች ይኖራሉ ለወደፊቱም ከዚህ ነፃ አይሆኑም ዋና ነገር የተፈፀሙት ስህተቶች መታረማቸው ላይ ነው ትኩረት መደረግ የነበረበት::

የአቶ እውነቱ ሶስቱም ፅሁፎቻቸው ተመሳሳይ ናቸው በሳቸው እምነት በትግርኛ ተናጋሪ የሚባል ሁሉ ለኢትዮጵያ የማይጠቅምና የወረደ እንደሆነ አማርኛ ተናጋሪ እንኳ ቢሆን ትግራዋይ የሚለው እውነት የሚደግፍ ከሆነ ሰይጣን እንደሆነ ለማሳየት ሲባል ሰላምወርቅ የተባሉ ፀሃፊ ያስቀመጧቸው ሂሶች ከማስተባበል ይልቅ ፀሃፊው የትግራይ ተወላጅ ስለመሆናቸው ለማሳመን ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም ስለሆነም ይህ የቆየው የገዢ መደቦችና የኢህአፓዎች የትግራይን ስም የማጥፋት ዘመቻ አካል ስለሆነ በአቶ ብርሃነ ፅሁፍ መልስ ለመስጠት የተፃፈው ፅሁፋቸው ላይ ትኩረት በማድረግ አንዳንድ ነገር ልበል::

1/ አቶ እውነቱ በአማራ ክልል  የተፈጠረው ምስቅልቅሉ የወጣ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ የፈጠረው ህወሓትና አንዳንድ የትግራይ ተወላጅ ፀሃፊዎች እንደሆኑ ለዚህም ከጅምሩ ህወሓት በእጅጉ ዘረኛ የሆነ አስተሳሰብ ኮትኩቶ በማሳደግ ህይወት እንዲዘራበት ያደረገው ህወሓት ነው ይሉናል:: ይህ ፍፁም አዲስ ነገር የሌለበትና ኢህአፓዎች ሲፈጠሩ ጀምረው ስለ ብሄርህ ማሰብ ዘረኝነት ነው ብለው ሲከሱ የነበሩት አፋቸው የከፈቱበት ፖለቲካ ነው:: አማራ እንዲህ ሆነ፤ ትግሬ አገር የለውም ኦሮሞ እንደዚህ ነው እያለ ሲጮህ ጊዜውን የሚያሳልፈው ግን ህወሓት አለመሆኑንና ህወሓት ለአማራ ህዝብ ምኑ እንደሆነ ሰፊው የአማራ ህዝብ ስለሚያውቀው አውቆም በ36ኛ የብአዴን ልደት በዓል የደብረታቦር ህዝብ ያስቀመጠው እውነት ይመሰክራል:: ስለሆነም የእናቴ ቀሚስ ከመሆን አልፎ ውሃ አይቋጥርም::

2/ ባለፈው ጊዜ የተፈጠረው የስድስተኛ ክፍል መፅሃፍ ላይ የተከሰተው ስህትት ህወሓት ሆን ብሎ አደረገው ብለው ይከሳሉ (ኣቶ ተኮላም ደግመውታል) ይህ በማስረጃ ያልተረጋገጠ የስም ማጥፋት ዘመቻ መሆኑን ሳይታለም የተፈታና ወደ ትክክለኛ ማጣራት ተወስዶ መረጃው እንዳይገኝ የማሳሳት ጉዳይ ካልሆነ በወቅቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሃላፊ ኣማራ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ከ60% በላይ አማራ በሆኑበትና በመስሪያ ቤቱ የሚሰራ የትግራይ ተወላጅ ከ5% በማይበልጥበት መስሪያ ቤት እንዴት ብሎ ህወሓት እንደሰራው ግልፅ አይደለም ወይስ መፅሃፉ የታተመው መቀለ ነው ሊሉን ነው:: ይህም ጅራፍ ራሱ ገርፎ እንዳይሆን እኔ እንደሚመስለኝ በየቦታው የተሰገሰጋችሁ ኢህአፓዎች ራሳችሁ ሰራችሁት ከደበቃችሁት ደግሞ ፈትሻችሁ አወጣችሁት:: አረ ለመሆኑ በአማራ ክልል ህወሓትና የትግራይ ተወላጆች ይህ ሁሉ ለብጥብጥና ሁከት የዳረገ ስራ ሲሰሩ ይሀ ሁሉ 26 ዓመት የት ነው ተኝታችሁ የነበረው ለክልሉ ህዝብ ምንም አልሰራችሁም ማለት እኮ ነው:: እንደዚህ ከሆነ መፍትሄው ምን ይሁን ይላሉ?

3/ ሌላው በጣም አስገራሚና በትግራይ ህዝብና ተወላጅ ላይ ያላቸው ቅጥ ያጣ ጥላቻ የሚያሳየው በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊ የሆኑት ዶ/ር አዲሱ የሰዘነሩት ዘረኛ አባባላቸው ነው:: ዶ/ር አዲሱ የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ሃላፊ ስለሆኑ ኮሚሽኑ የደረሰበትን ድምዳሜ ለሾማቸው አካል ሪፖርት የማቅረብ ሃላፊነት ስላለባቸው አቀረቡና በአቶ እውነቱ ተከሰሱ እዚህ ላይ ኮሚሽኑ ለሚሰራቸው ስህተትና ስህተቱም እንዳለ ተቀብለው ሪፖርት ካቀረቡ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ዶ/ር አዲሱ ያውቃሉ ግን ያቀረቡት ሪፖርት “የክልሉ ባለስልጣናት የቅማንትን ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ጥያቄ ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መንገድ አላስተናገዱም አልፎም እንግልትና እስራት ታይቷል፤ የክልሉ የፀጥታ ሃይልም አድልዎ ፈፅመዋል” የሚል ነው ይህ ደግሞ እርስዎም በፅሕፉዎ ገልፀውታል ታድያ እዚህ ደርሶ ዶ/ር አዲሱ የሚያስወቅስ ምን ተገኘ:: ለመሆኑ ዶ/ር አዲሱ የኮሚሽኑ ሃላፊ በመሆናቸው የሚከሰሱ ከሆኑ በስድስተኛ ክፍል መፀሃፍ ላይ የተከሰተው ችግር በወቅቱ ሃላፊ የነበሩ አቶ ደመቀ፤ በአማራ ክልል የተከሰተው ችግር የክልሉ ፕረዚዳንት የሆኑ አቶ ገዱ ለምን አይከሰሱም ይላሉ አቶ እውነቱ? ነው ወይስ አማርኛ ተናጋሪ የፈለገው ቢያጠፋ አይከሰስም እያሉን ነው? ንጉስ አይከሰስም ሰማይ አይታረስም የሚለው የአባቶችዎ ብሂል ይዘው ከሆነ አይሰራም እንዳይመለስ ተቀብረዋል::

4/ አቶ እውነቱ የአቶ ብርሃነ ፅሁፍ ሲቃወሙ በመጨረሻ የወረደ እንደሆነ የብአዴን አባላትና የአማራ ህዝብ ቢሰማው ጥሩ ስላልሆነ የተወሰነ ብቻ እንደናገሩና ከወረደ ፅሁፍ ጋር መውረድ ትክክል እንዳልሆነ ይህም ለህወሓትና ለትግራይ ህዝብ እንደማይጠቅም ሊነግሩን ሞከሩ:: እስቲ መለስ ብለው ፅሁፍዎን ያንብቡት የትግራይ ተወላጆችና ህወሓት በአማራ ክልል የተፈጠረው ችግር እንዲፈጠር ምክንያት ሆነዋል፤ ህወሓት ጠባብ ፍላጎቱ ለማሟሟላት ሲል ዘረኛ አስተሳሰቡን ለማስረፅ ከቅማንት ህዝብ ጥያቄ ጀምሮ እስከ የስድስተኛ ክፍል መፅሃፍ የተፈጠረው ችግር ፈጣሪና ተጠያቂ ነው፤ በአጠቃላይ ከጎሳና ዘር ግጭት ውጪ ህወሓት/የትግራይ ህዝብ ለዚህች አገር ምንም አልፈየዱም እያሉን አይደለም ለዛውም ባልተጨበጠና አልፎም ራሳችሁ የሰራችሁትና ያጠፋችሁት በመለጠፍ::

5/ አቶ እውነቱና አቶ ተኮላ የአቶ ብርሃነ ፅሁፍ ስትቃወሙ ስለአማራ ክልል ምን አገባው ለአማራ ክልል ህዝብና መንግስት እንዲሁም መሪ ድርጅቱ ብአዴን መተው አለበት ብለችኋል፤ ከኛ በላይ ላሳር የሚለውን የእንስሳ አስተሳሰባችሁ ነው እንጂ ማንም ሰው የሚታየው ነገር መፃፉ ሃጢኣት ሆኖ አይደለም እንኳንና ኢትዮጵያዊ የውጭ አገር ዜጋም ቢሆን ሃሳብ ማቅረብ ይችላል ገምቢ ከሆነ ትቀበላለህ ካልሆነ ትተወዋለህ፤ በኔ እምነት በአቶ ብርሃነ ፅሁፍ የተጠቆሙት ትችቶች ሳይሆን ድምዳሜው ላይ ግን በድርጅቱና በፍርድቤት ጉዳይ በመግባት መዘበራረቅ አልነበረትም እላለሁ:: ለመሆኑ እናንተ እንደዚህ አላችሁ ስለወልቃይት ጎንደር ላይ ሁኖ መጮህ በአንድ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ የውስጥ ጉዳይ እጅ ማስገባትስ ምን የሚሉት ወጥ መርገጥና ድፈረት ብላችሁ ነው የምታዩት ለዛውም በባለስልጣናት ደረጃ:: ስለወልቃይት ህዝብ የሚቆረቆረው ጎንደሬ ነው ብላችሁ ነው የምታምኑት?

6/ ሌላዋ ትንሽ የምትመስል ግን ደግሞ ሆን ተብላ የራስዋ መልእክት ለማስተላለፍ በአቶ እውነቱ የተቀመጠች ድግሞ ህወሓት ብለው ለመጥራት ሲፈልጉ ህወሓት/ኢህአደግ ብለው የሚያስቀምጡት ብአዴን ብለው ለመናገር/መፃፍ ሲፈልጉ ደግሞ ብአዴን/ኢህደን ብለው ነው የሚፅፉትና ብአዴን ኢህአዴግ አይደለም እያሉን ነው ወይስ ምን ማለታቸው መሆኑ ስላልገባኝ በቀጣይ ፅሁፍዎ ማብራርያ እንዲሰጡኝ አስቤ ነው:: ምክንያቱ ብአዴን ኢህአደግ ነው ብለን አስበን ስለሆነ የምንናገረው ከውስጥ አዋቂዎች እነ አቶ እውነቱ ማብራርያ ያስፈልጋል::

በመጨረሻ አቶ እውነቱ በትግራይ ኦንላይን፤ በአይጋ ፎረምና በውራይና የማይረባ ፅሁፎች እያወጡ እንዳለሽቸገሩና ሚዛናዊነት እንደሚጎድላቸው ነው የነገሩን እነዚህ ድህረ ገፆች ግን የእርስዎ አንድ ብሄር የሚያንቋሽሽ ፅሁፍ ይዘው የወጡት የግልዎ አስተያየት ስለሆነ ለእርሰዎም እያስተናገዱ ነው:: በኔ እምነት ግን የወጡት ፅሁፎች ሃላፊነት ያለበት ፀሃፊው ይመስለኛል ሚዛን የማስያዝ ደግሞ ሁላችን በእውነትና በማስረጃ አስደግፈን በመወያየትና መልስ በመስጠት እንጂ ሁላችንም የመሰለንና ያመንበት የመግለፅ ህገ-መንግስታዊ መብታችን ነው:: እርስዎ የአቶ ብርሀነ ሃሳብ መንቀፍ በመሰልዎት እንደገለፁት እኔ ደግሞ የሁላችሁም በመሰለኝና በማምንበት የመግለፅ መብት አለኝ በቃ ከዚህ በዘለለ ስለየትግራይ ህዝብ/ተወላጅና መሪ ድርጅቱ መጥፎ ስም ሲሰጥ ትክክል ስለ አማራ ህዝብ/ተወላጅና መሪ ድርጅቱ ብአዴን መጥፎ ሲወራ የሚያንገበግብ መሆን አይችልም ለሁሉም እኩል ነው ሁሉም የነሱ ያልሆነ የፈጠራ ወሬ የደካሞችና አቅመ ቢሶች ተግባር ነው:: ስለሆነም እኔ በበኩሌ በትግራይ ህዝብ/ተወላጅና መሪ ድርጅቱ ላይ እንዲሆን የማልፈልገው በአማራ ህዝብ/ተወላጅና መሪ ድርጅቱ ብአዴን እንዲፈፀም አልፈልግም::

************

Avatar

Guest Author

more recommended stories