በኤርትራ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ መራዘም እና ለቀጠናው ያለው የሰላም አንድምታ

(Yohannes Gebeyehu)

እ.ኤ.አ. ሜይ 2009 የምስራቅ አፍሪካ በይነ-መንግስታት (ኢጋድ) በኤርትራ የጣለውን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ተከትሎ በተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በዛው ዓመት ዲሴምበር 23 ቀን በውሳኔ ቁጥር 1907 አማካይነት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ በኤርትራ ላይ ጣለ። ማዕቀቡ ወደ ኤርትራ የሚገቡ እና ከኤርትራ የሚወጡ የጦር መሳሪያዎችን እና ከጦር መሳሪያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቁሳቁሶችን የሚያግድ ውሳኔ ነው።

ውሳኔው በተመድ የሶማሊያ ጉዳይ ተቆጣጣሪ ቡድን ሪፖርት ግኝት መሰረት የኤርትራ መንግስት አልሻባብ ለተባለው እና ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው ለሚነገርለት አክራሪ እስላማዊ ቡድን የፖለቲካ፣ የፋይናንስ እና የሎጂስቲክ ድጋፍ እያቀረበች መሆኑ በመረጋገጡ የተላለፈ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ኤርትራ ከጅቡቲ ጋር በነበራት የድንበር ግጭት አለመግባባት ምክንያት ድንበር አካባቢ ያሉ የጦር ሰራዊቷን ከድንበሩ አስወጥታ ለድርድር ዝግጁ አለመሆኗን ተከትሎ የተጣለም እንደሆነ ውሳኔው ያመላክታል። ማዕቀቡ በ2009 እ.ኤ.አ. ከተጣለ በኋላ እየታደሰ እስከ 2016 የቆየ ሲሆን በ2016ም በተመድ የጸጥተው ምክር ቤት ውሳኔ ቁጥር 2317(2016) አማካኝነት ታድሷል።

የጦር መሳሪያ ማዕቀቡ አንድም ከኤርትራ እና ወደ ኤርትራ የሚገባውንና የሚወጠውን የጦር መሳሪያ እና ከጦር መሳሪያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ቁሳቁሶችን ለመግታት ሌላም የኤርትራ መንግስት የባህሪ ለውጥ እንዲያመጣ ለማድረግ እና የአካባቢውን ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ ታልሞ የሆነ ነው። ስለሆነም ማዕቀቡን ለመከለስ፣ ለማሻሻል ወይም ለማንሳት የታለመለትን ግብ በተለይም በኤርትራ ያለውን የባህሪ ለውጥ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት።

በዚህ መሰረት የኤርትራ መንግስት የባህሪ ለውጥ ባለማምጣቱ፣ የሶማሊያ እና የኤርትራ ተቆጣጣሪ ቡድን (ከዚህ በኋላ በጽሁፉ ውስጥ SEMG ተብሎ ይጠቀሳል) ወደ ኤርትራ ገብቶ የኤርትራው መንግስት አልሻባብን እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖችን እየረዳ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ እንዲችል አለመፍቀዱ የባህሪውን ግትርነት ማሳያ በመሆኑ፣ ተቆጣጣሪ ቡድኑ እንዲገባ ያልፈቀደው አሁንም ድረስ ለአሻባሪዎች ድጋፍ እያደረገ፣ ማዕቀቡን እየጣሰ፣ በኤርትራዊያን ላይ ብሔራዊ ባርነት ሊባል በሚችል መልኩ ጭቆናና ኢሰባዊ ዕርምጃ እያደረገ በመሆኑ፣  የጂቡቲ የጦር ምርኮኞችን በምን አይነት ሁኔታ እንዳሉ ለማረጋገጥ የሚያስችል መረጃን አልሰጥም በማለት ጠብ አጫሪነቱን እየቀጠለ በመሆኑ፣ ቀጠናውን የብጥብጥ እና የሽብር ማዕከል ለማድረግ የአካባቢውን ታጣቂ ቡድኖች አሁንም ድረስ እየረዳ መሆኑ በመረጋገጡ ማዕቀቡ ተራዝሟል። 

SEMG በኤርትራ የተጣለው ማዕቀብ በትክክል መተግበሩ አለመተግበሩን ወደ አገሪቱ ከሚገባውና ከሚወጣው የጦር ማሳሪ፣ የኤርትራ መንግስት አካባቢውን የማተራመስ አጀንዳውን መተው አለመተውን በማረጋገጥ፣ በኤርትራ ያሉ የማዕድን እና ሌሎች የሃብት ምንጮች የሚሰበሰበው ገንዘብ ታጣቂ ቡድኖችን ለመደገፍ መዋላቸውን በማረጋገጥ፣ የሰብአዊ መብት ረገጣ መቆሙን እና መሻሻል አለማሳየቱን ከነዚህ ጉዳዮች አንጻር ገምግሞ እንዲያቀርብ ነው የተዋቀረው።

የቡድኑ አባላት አወቃቀርን ስንመለከት የጦር መሳሪያ ባለሙያ(Arms expert) ከ እና ወደ ኤርትራ ያለውን የጦር መሳሪያ ፍሰትና ሁኔታ ለማወቅ፣ የቀጠናው እና የታጣቂ ቡድኖች ባለሙያ (regional expert and armed groups expert) ኤርትራ በቀጠናው የምታደርገውን የማተራመስ አጀንዳ ለመገምገም፣ የፋይናንስ እና የተፈጥሮ ሃብት ባለሙያ(finance expert እና natural resources expert) በቀጠናው የሚንቀሳቀሱ ታጠቂዎችን ለመደገፍ እና የጦር መሳሪያ ለመግዛት ያለውን የፋይናንስ ምንጭ ለመተንተን እና ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶች ማዕቀቡን ለመጣስ መጠቀም አለመጠቀሟን፣ የሰብአዊነት ባለሙያ(humanitarian expert)፣ የሰብዕዊ መብቶችን ሁኔታ ሪፖርት ለማጠናከር በሚያስችል ሁኔታ የተዋቀረ ነው።  

የማዕቀቡ መራዘም ለቀጠናው ያለው አንድምታ ምንድን ነው?

ማንኛውም ማዕቀብ እና በተለይም የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ውጤታማነት የሚለካው ማዕቀቡ የተጣለበት አገር የባህሪ ለውጥ ማምጣት ሲችል እና የተጣለው ማዕቀብ እውነትም ወደ አገሪቱ የጦር መሳሪያ መግባትን መከልከል ሲቻል ነው። ማዕቀቡ የኤርትራ መንግስት ለአለም ዓቀፍ ሰላም ጸረ መሆኑን የሚያሳይ፣ ወደ ኤርትራ ወይም ከኤርትራ መንግስት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ያለን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ፣ ወታደራዊ ስልጠና፣ የሎጅስቲክ ድጋፍን ወዘተረፈ የሚገታ፣ አገሪቱ በተለይም በስልጣን ላይ ያለው አስተዳደር ከአለም ማህበረሰብ መገለል እንዲደርስበት የሚያደርግ እና ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና ኢኮኖሚያው ቀውስን በኢሳያስ መንግስት እንዲፈጥር የታለመ እና የፈጠረ መሆኑ በግልጽ ይታያል።

በኤርትራ ላይ የተጣለው መዕቀብ የኤርትራው መንግስት የባህሪ ለውጥ ባለማምጣቱ ምክንያት ተራዘመ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም የኤርትራ መንግስት በማዕቀቡ ምክንያት የደረሰበትን ፓለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲዊ እና ወታደራዊ ቀውስ ግን ማየት ይቻላል። ኤርትራ ባልሞት ባይተጋዳይነት በራሷ ህዝብ ላይ የምታደርሰው በደል፣ ኢትዮጵያን እና ጅቡቲን ለማተራመስ የምታደርገው ጥረት፣ የአለም ማህበረ-ሰብን ከልክ ባለፈ ጥርጣሪ እየተመለከተች መምጣቷ የዚሁ ስነ-ልቦናዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ ቀዉስ ማሳያ ነው።

ይሁን እንጂ የማዕቀቡን ጥንካሬ ሊያዳክሙ የሚችሉ አንዳንድ ክስተቶችን ሁሉም አገራት በንቃት መከታተል እንደሚገባቸው ማዕቀቡን የጣለው የጸጥተው ምክርቤት በውሳቤው አመላክቷል። በዚህ ረገድ   ከኤርትራ ወደ ጣሊያን በከፍተኛ የአገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት ኃላፊዎች የተደረጉት ጉብኝቶችን፣ በተለያዩ ሚዲያዎች እና ለSEMG የደረሱት መረጃዎች ኤርትራ በእጅ አዙር ከዩክሬን የጦር መሳሪያ እየገዘች ስለመሆኑ የተገኙ መረጃዎች፤ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የየመን አማጺያንን ለመውጋት በሚል ሰበብ በኤርትራ ያደረጉት የጦር ሰፈራ፣ ቃጣር ጂቡቲንና ኤርትራን ለማስታረቅ በሚል የምታደርገው መውጣትና መግባት ማዕቀቡ በኤርትራ ላይ ያለው ተጽኖ እንዲቀጥን እና የኤርትራን መንግስት ባህሪን ከማሻሻል ይልቅ በእብሪት ልቡ እስኪ ፈነዳ ድረስ እንዲያብጥ የሚደርግ ብቻ ሳይሆን የጉዳዩን አሳሳቢነት የሚያመላክት መሆኑ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ብዙዎች የሚስማሙበት ነው።

ማዕቀቡ በኤርትራ ለውጥ አለመኖሩን በደንብ ያሳየ ነው። በውሳኔው ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት የታላቋ ብሪታኒያ እና አሜሪካ አምባሳደሮች ይህንኑ በደንብ አስቀምጠውታል. የእንግሊዙ አምባሳደረ Matthew Rycroft ስለኤርትራ ሲናገሩ “We don’t welcome the progress because nothing has changed,” ብለዋል።  የአሜሪካዋ አምባሳደር Isobel Coleman በበኩላቸው የእንግሊዙ አምባሳደር ያሉትን ያጠናከረ ነበረ። ከላይ የተጠቀሱት የሁለቱ ኃያላን መንግስታት እንዳስቀመቱት እውነተኛ ለውጥ በኤርትራ መጣ የሚባለው የኤርትራ መንግስት ሽብርተኞችን እና ታጣቂ ቡድኖችን ማገዝ ሲያቆም በዚህም ለአለም አቀፍ ሰላም እና መረጋጋት አደጋ መሆኑን ሲያቆም ነው።   

በዚህ ረገድ ያለው ዋና ጉዳይ በኤርትራ ያለው አስተዳደር ባህሪ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይቀየራል ወይ የሚለው እና የእውነተኛ ለውጥ ጥያቄ ከአስተዳደሩ መሪዎች ጋር በጥብቅ የተሳሰረ መሆኑ ነው። ኤርትራ የመሪዋ የኢሳያስ አፈወርቂ እና በበዙሪያቸው ያሉ ባለስልጣናት እርስት በመሆኗና አገሪቱን የሚያስተዳድራት ቡድን በከፍተኛ የተማከል የውሳኔ ዘዴ የታሰረ ከመሆኑ አንጻር አመራሮች ካልተለወጡ አስተዳደሩ ይለወጣል ማለት ዘበት ነው። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲው የኢሳያስ ፍላጎት እና ምኞት የሚገለጽበት ሲሆን የኢሳያስ ምኞት ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር በነበረው ‘የነጻነነት ጦርነት’ ቂም በቀል የተቀረጸና የአፍሪካ ቀንድን የማተራመስ ፍላጎትን እየገታች ያለቸውን ኢትዮጵያን ማተራመስን ቅድሚያ ሰጥቶ የሚንቀሳቀሰ የስነ-ልቦና ቀውስ ያለበት ነው። ውጭ ጉዳይ ፖሊሲው ነገሮችን ሁሉ በመሳሪያ እና በጦርነት እልባት ለመስጠት የሚፈልግ ነው። የፖሊሲው እይታም አመራሮች ለተቀረው አለም ባላቸው ቂም በቀል፣ የአፍሪካ ቀንድ ባለው አለመረጋጋት፣ በኤርትራ ውስጥ ጠንካራ መንግስት ለመመስረት ባሉት ተግዳሮቶች ፍራቻ የተከበበ ነው። በመከበብ ስሜት ውስጥ ያለ ፖሊሲ ደግሞ የከበበውን አለም ሁሉ በጠላትነት የሚፈርጅ ብቻ ሳይሆን በአዕምሮው ውስጥ የፈጠረውን የመከበብ ስሜት ለመፍታት መሳሪያን የሚያነሳ፣ ጦርነትን የሚያውጅ፣ ጠብ አጫሪነትን ቋንቋውና መግባቢያው የሚያደርግ ይሆናል ማለት ነው። የኤርትራው መንግስት ፖሊሲ መግለጫም እነኝሁ ናቸው።

ኤርትራ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ ለሚሹ ታጣቂ ቡድኖች የምታደርገው ድጋፍ፣ የጂቡቲን የጦር ምረኮኞች ሁኔታ መረጃ አልሰጥም ማለቷ፣ ከማዕድን የምታገኘውን ገንዘብ ለጦር መሳሪያ ግዥ በማዋል ማዕቀቡን ለመተላለፍ የምታደርገው ጥረት፣ የተመድ ተቆጣጣሪ ቡድን በኤርትራ ገብቶ ኃላፊነቱን እንዲወጣ አለመፈለጓ የኤርትራው መንግስት ባህሪውን ለመለወጥ ያለውን ፍላጎት በደንብ ሊያሳዩ ከሚችሉ ጉዳዮች በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።

የኤርትራ መንግስት አልሻባብን ከቃጣር በሚለቀቅ ገንዘብ፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻ አውጭ ግንባር(ኦብነግ)፣ የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ትህዴን)፣ የአርብኞች ግንቦት 7፣ የህዝቦች ትብብር ለነጻነትና ለዲሞክራሲ ለተባሉ ኢትጵያን ለማተራመስ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖችን እና በጂቡቲ የሚንቀሳቀሰውን pour la restauration de l’unité et de la démocratie (አንድነት እና ዴሞክራሲ አስመላሽ ግንባር) በመደገፍ ቀጠናውን ለማተራመስ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እና አጀንዳ እየቀጠለ መሆኑን ሪፖርቶች በግልጽ ያሳያሉ። ከላይ የተጠቀሱትን ታጣቂ ቡድኖች በፋይናንስ፣ በፖለቲካ፣ በሎጅስቲክ በመደገፍ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እየሰራ እንደሆነ መረጃወች ይጠቁማሉ።

በቅርቡ እንኳ 113 የሚሆኑ የግንቦት-7 አባላት በምዕራብ ትግራይ በኩል ሲገቡ መያዘቸው እና 15 የሚሆኑት መገደላቸው፣ 73 የሚሆኑት መማረካቸው የኤርትራ መንግስት ቀጠናውን የማተራመስ አጀንዳውን አለመተውን ብቻ ሳይሆን ይልቁንም በብርቱ እንደገፋበት የሚሳይ ጋህዳዊ ማስረጃ ነው።  የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ማዕከል ቀጠነውን ማተራመስ እንደሆነ ማሳያ ነው።

በዘርፉ ጥናት ያደረጉ አካላት ኤርትራ ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ቃጣር እና መሰል አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በጥርጣሪ ነው የሚመለከቱት። ኤርትራ ውስጥ የጦር ሰፈር የገነቡት አገራት እና ከኤርትራ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸው አገራት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ኢትዮጵያን “የክርስቲያን ደሴት” እንደሆነች የሚፈርጁ እና ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድን ለማስለም እና ቀይ ባህርን የአረብ እንዲሆን ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የምትገታ ደንቀራ አገር አድርገው የሚያምኑ መሆናቸው ጉዳዩን በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ የሚያደርግ ነው።

በኤርትራ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ ያላቸው እና በኤርትራ የጦር ሰፈር የመሰረቱ አገራት ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለውን አልሻባብንና ISIL የተባሉ የሽብር ቡድኖችን መደገፍ ብቻ ሳይሆን ቡድኖች በአምሳላቸው የተቀረጹ መሆኑ የታወቀ ሃቅ ነው። እነኝህ አካላት ቃጣር የምታደርገውን እስላማዊ አክራሪነትን የማስፋፋት አላማ የሚራምዱ እና የሙስሊም ወንድማማቾችን ርዕዮተ-ዓለም የሚወክሉ መሆናቸውን በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ምሁራን ይገልጻሉ። በዚህ ረገድ ጥናት እና ትንታኔ ያደረጉት ሩሲያዊው የፖለቲካ ተንታኝና ታዋቂው ጋዜጠኛ አንድሪው ኮሪብኮ የባህረ-ሰላጤው አገራት በኤርትራ ያላቸው የጦር ሰፈር በየመን አማጽያንን ለመዋጋት ካላቸው ፍላጎት እኩል የኢትዮጵያን ተጽዕኖ ለመቀነስ ብሎም አገሪቱን ለማዳከም ነው ማለት ማገነን እንዳልሆነ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

እንደ አንድሪው ኮሪብኮ ገለጻ በኤርትራ ያለው የጦር ሰፈር ኢትዮጵያን ለማደከምና በየመን አማጻያንን ለመዋጋት ያለመ እና በሁለቱም ወገን የተሳለ ጎራዴ ነው ይላሉ። ስለቃጣር ሲተነትኑ የቃጣር በኤርትራ መኖር በኢትዮጵያ ላይ የተቀነባበረ እና ሆን ተብሎ የታለመ (orchestrated, managed and ideologically induced chaos) አመጽ በመቀስቀስ የአፍሪካ ቀንድ የመጨረሻ የሰላም እድል (bastion of peace, security and stability) የሆነችውን ኢትዮጵያ ለማተራመስ ያቀደ ነው ይላሉ።    

ይህን ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግስት በጥበብ፣ በእውቀትና ትንታኔ ላይ በተመሰረተ የብሄራዊ ጥቅም፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ እና ዲፕሎማሲ እየመረው ስለመሆኑ የተለያዩ አመልካቾች አሉ። ኢትዮጵያ ለተቆጣጣሪ ቡድኑ የምትሰጣቸው መረጃዎች፣ ከኃያላኑ አገራት ጋር የምታደርገው የሰለጠነ ትብብር፣ የምስራቅ አፍሪካን ሰላም ለማስጠበቅ የምታደርገው ያላሰለሰ ጥረት፣ የኢትዮጵያ መንግስት ኤርትራን አስመልክቶ ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል ያለው የምንጊዜም ዝግጁነት፣ በኤርትራ የጦር ሰፈር ካላቸው አገራት ጋር ኢትዮጵያ ያላት ጥበብ የተሞላበት እንቅስቃሴ እና ዲፕሎማሲ ለዚሁ ማሳያ ነው።    

ኢትዮጵያ በኤርትራ እየሆነ ያለው ወሳኝ ብሔራዊ ጥቅሟን(vital national interest) የሚነካ መሆኑን በግልጽ ለአለም ማህበረሰብ፣ በኤርትራ  ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ አገራት እና ከኤርትራ ጋር ትብብር ላላቸው አገራት ማሳሰብ እንደቀጠለች መሆኗ ቀጠነውን በቅርበት የሚከታተሉ ይስማሙበታል። ድምጽን በድምጽ መሻር የሚችሉ የጸጥታው ምክር ቤት አባል አገራት ኢትዮጵያ ስታነጥስ፣ ታላቁ የአፍሪካ ቀንድ ጉንፋን እንደሚይዘው እና ለኢትዮጵያ አለመረጋጋት ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ነገር ሁሉ ለአለም አቀፍ ሰላም፣ መረጋጋት እና ደህንነት ያለውን አንድምታ መመልከት እንዳለበት የሚያሳይ ነው በኤርትራ ምድር ያለው ተጨባጭ ሁኔታ እና የኤርትራው መንግስት ባህሪ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሚያደርገው ዲፕሎማሲም ይህንኑ ለአለም ማህበረሰብ ለማሳየት ቀን ተሌት እየሰራ መሆኑን በተለይ የአገሪቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ያካተቱ የጉብኝት ልውውጦች ከባህረ-ሰላጤው አገራት ጋር መካሄዳቸው የዚሁ ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ መገለጫ ነው።

******************

* ፀሐፊው ዮሓንስ ገበየሁ በዚህ አድራሻ [email protected] ይገኛሉ፡፡

Avatar

Guest Author

more recommended stories