ወልቃይት እንኳን ህዝቡ መሬቱም ትግራዋይ ነው – ከታሪክ መዛግብት

(አስፋው ገዳሙ ([email protected]))

1/ መግቢያ

የኢትዮጵያ ክልሎች አወቃቀር ሁሉንም ኢትዮጵያውያን አብረውና ተከባብረው እንዲኖሩ የሚያስችል ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር፡፡ በተለያዩ ወቅቶች ኢትዮጵያን ያስተዳደሩ ገዢዎች ለህዝቡ ምቾት ሳይሆን ለራሳቸው በሚመች መልኩ ሃገሪቱን ሲስተዳድሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የአሁን መንግስትም ለራሱ በሚመቸው መልኩ እያስተዳደራት ይገኛል፡፡ ሆኖም ግን ብዙ ሰዎች፣ በተለይም የጎንደር ተወላጆች በደርግና በአጼ ሃይለስላሴ ወደ ነበረው አከላለል ካልተመለስን እያሉ ይገኛሉ፡፡ ይህ ጥያቄያቸው እንደ ድሮው ቋንቋው አማርኛ፣ ሰንደቅ ዓላማው ልሙጡ አረንጓዴ፣ ብጫ፣ ቀይ እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን ወልቃይትና ፀገዴም ወደ ጎንደር ካልተካለሉ እያሉ ይገኛሉ፡፡ ጥያቄው የተነሳበት ቦታ፣ ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ ግን አሁን ካለው አከላለል አንፃር ወደ መግባባት ሳይሆን ወደ ንትርክ የሚያመራ ነው፡፡ ወልቃይት በአማራ ክልል ስር ስለነበር ወደ አማራ ክልል ይመለስ የሚሉት ጥያቄ በዚህ የሚያበቃ አይመስለኝም፡፡ ቤንሻንጉል ጉሙዝም ወደ አማራ ካልተካለለ ሊባል ይችላል፡፡ ሲጀመርም የጌቶች ትእዛዝ እንጂ የህዝብ ጥያቄ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡

ሁለት እረኞች ራቅ ብሎ በሚገኘው አንድ ትልቅ ቋጥኝ ላይ የሆነ እንስሳ አሻግረው ያያሉ፡፡

አንዱ፡- እዛጋ ያለው እንስሳ ምንድነው?

ሁለተኛው፡- እኔ እንጃ፤ ግን አሞራ ሳይሆን አይቀርም፡፡

አንዱ፡- እንዴ! አሞራ ትላለህ እንዴ? ባክህ ጅብ ነው፡፡

ሁለተኛው፡- ኧረ ተው አሞራ ነው የሚሆነው፤ ጅብ ከመቼ ነው ቋጥኝ ላይ የሚወጣው?

አንዱ፡- በል ወደድክም ጠላህም ጅብ ነው፡፡

በዚህ የተነሳ አሞራ ነው፤ የለም ጅብ ነው እየተባባሉ ከቆዩ በኋላ ሁለተኛው እረኛ እሺ እንግዲህ ወደዛው ሄደን እናረጋግጥ ይላል፡፡ ሄዱ፡፡ ቋጥኙ አጠገብ ሲደርሱ እንስሳው በረረ – እውነትም አሞራ ነበርና፡፡ አንደኛው እረኛ ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹ይኽ እንስሳ ቢበርም ጅብ ነው››፡፡ የወልቃይት ጥያቄም – በእኔ እይታ ጥያቄ ሳይሆን ትእዛዝ ነው – ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ ወልቃይት መሬቱም ሆነ ህዝቡ ትግራዋይ ቢሆንም አማራ ነው የሚል ትእዛዝ፡፡ በዚች አጭር ፅሑፍ ይህን እንድል ያስቻሉኝን ምክንያቶች እንደሚከተለው አቀርባሎሁ፡፡

2/ የታሪክ መዛግብት ስለወልቃይት ምን ይላሉ?

ስለ ታሪክ ጠቃሚነት ሲወራ ሁሌም ቀድሞ የሚጠቀሰው የሮማ ትልቅ የህግ አስተማሪና ፈላስፋ እንደነበር የሚነገርለት ማርቁስ ቱልየስ ሲሰሮ ነው፡፡ሲሰሮ አንድ ሰው ከመወለዱ በፊት ያለውን ታሪክ ካላወቀ ዕድሜ ልኩን ህፃን ሆኖ እንደሚቀር ያትታል፡፡

‹‹To be ignorant of what occurred before you were born is to remain always a child. For what is the worth of human life, unless it is woven into the life of our ancestors by the records of history?›› ~Marcus Tullius Cicero(106-43 BC)

የእኛ ሃገር ታሪክ ግን የታሪክ አፃፃፍ ህጎች ተከትሎ ስለማይፃፍ ሃገራችን እኛ ከመወለዳችን በፊት የነበራት ምስል ጥርት አድርጎ ከማሳየት ይልቅ ያደበዝዘዋል፡፡ የታሪክ ፀሐፊዎቹ አንዴ መለኮታዊ ያደርጉታል አንዴም በዘመኑ ለነገሱ ሰዎች ሲባል እየቆራረጡ ያቀርቡታል…መፃፍ የነበረበት ሳይፃፍ ይቀራል፤ ያልነበረም ይጨመራል፡፡ በዚህ መክንያት የታሪክ መዛግብ የሚሉትን እንዳለ ከመጠጣት ይልቅ ነባራዊ ሁኔታዎችን ማገናዘብ ተመራጭ ይመስለኛል፡፡

ቢሆንም ግን ተክክለኛው ታሪካችን እስኪፃፍ ድረስ ያለውን እየጠቃቀስን መወያየት እንጂ ሌላ አማራጭ የለንም፡፡እንትና የተባለ ፈረንጅ የሚለው ትርክት እየመረረንም ቢሆን እንጠቀምበታለን፡፡

ስለወልቃይት ከተነሱት በመጠኑም ቢሆን ሚዛናዊ የሚመስል አፃፃፍ የተከተለው ዘ-አዲስ በሚል የብዕር ስም የተሰራጨው ፅሑፍ ነው፡፡ የፅሑፉ ዓለማ ወልቃይት ለሺህ ዓመታት ከትግራይ አስተዳደር ውጪ እንደነበር ለማሳየት ይሞክራል፡፡ ሆኖም ግን ሆን ብሎም ይሁን በስሕተት የዘለላቸው እውነታዎች አሉ፡፡

ዶክተር ገላውድዮስ አርኣያ በርባዳስ የተባለ ፅሐፊን ጠቅሰው የትግራይ ግዛት እስከ ሌማሊሞ ተራሮች ሊደርስ እንደሚችል ፅፈዋል:: ከቪኦኤ ባደረጉት ቃለ መጠይቅም ተናግሯል፡፡

‹‹[Tigray]…the kingdom has near circular shape; unless we wish to extend, as some maintain should be done, as far as the Lamalmon mountain range.››[1]

ሆኖም ግን የበርባዳስ ፅሑፍ ለትርጉም ክፍት ስለሆነ የህዝቡንና የአከባቢውን ባሕልና ቋንቋን መሰረት አድርጎ በተደረገው የክልሎች አወቃቀር ወልቃይት በትግራይ ክልል ውስጥ መሆኗን ሊገርመን አይገባም ይላሉ፡፡

‹‹All I have argued was that Wolkait, a Tigrigna entity, by all measure, would not be surprising if it becomes part of Tigray.>> [2]

የዶክተር ገላውድዮስ ፅሑፍ በዘመነ መሳፍ(17ኛ ክፍለ ዘመን) ሽረ ማእከላቸውን ያደረጉ ደጃዝማች ገላውድዮስ ወልቃይትና ሰራዬን(የኤርትራ ግዛት) ጠቅልለው ያስተዳድሩ እንደነበር ያወሳል፡፡በዘመነ ደጃች ውቤም ወልቃይት በትግራይ አስተዳደር ስር እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡በተጨማሪም ራስ ሚካኤል ስሑል ትግራይና ጎንደርን ጠቅልለው ያስተዳድሩ እንደነበር ይታወቃል…ዶክተር ገላውድዮስም በግልፅ አስቀምጠውታል፡፡

ዶክተር ገላውድዮስ ‹‹ትግሬ እንጂ ትግራይ ተከዘን ተሻግሮ አያውቅም›› የሚሉት መፈክር ከላይ ከተጠቀሱት ታሪኮች በተጨማሪ እንደሚከተለው ውድቅ አድርገውታል፡፡በዚሁ መረጃ መሰረት እንኳን ወልቃይት ቤገምድር(የቤጃ ምድር)ና ዋግ በትግራይ ይተዳደሩ እንደነበር ተጠቅሰዋል፡፡

‹‹Tigray, the most northerly province of Ethiopia; Almeida, who described it as in ancient times ‘the foundation and head’ of the entire Ethiopian monarchy, considered it still the ‘best part’ of the country, while Ludolf later described it as ‘the best and most fertile’ part of it.

The province began, Almeida says, at the twin Red Sea ports of Massawa and Hergigo, and extended south-eastwards along the coast as the tiny harbor of Defalo. Inland the province was bordered, from east to west, by the Dankali ‘Kingdom’, Angot, Doba, Begemdir and Semen. [Beckingham and Huntingford, Some Records of Ethiopia, pp. 14-15; J. Ludolf, A New History of Ethiopia, London, 1682, p. 13.8]>>

Both Beckingham and Ludolf do not say that Tekezze is the Western frontier of Tigray, and Ludolf especially, who had made extensive studies on Ethiopia, and who is credited as the founder of Ethiopian Studies, put Wag as one of the 27 prefectures (districts or regions) of Tigray.›› [3]

በተጨማሪም በራስ ወልደ ስላሴ(ሕንጣሎ ወይም እንደርታ ማእከላቸውን አድርገው ትግራይ የገዙ ነበር) ዘመን ትግራይ ክብ ሳይሆን የአራት መአዘን ቅርፅ(ትራፒዝዮም) እንደነበራትና ግዛትዋም እስከ ሰሜን ይደርስ እንደነበር ዶክተር ገላውድዮስም ሆነ ዘ-አዲስ በጠቀሱት መፅሐፍ ውስጥ ተዘግቧል፡፡

‹‹The kingdom of Tigre is bounded by the Belka, Boja, Takue, and several wild tribes of Shangalla on the north; by the mountains of Samen on the west; and by the Danakil, Doba, and Galla, on the east and south; comprehending and extent of about four degrees in latitude, and about the same in a longitudinal direction, and forming in shape the irregular figure of a trapezium.›› [4]

በተጨማሪም ራስ ወልደ ስላሰ ወልቃይትና ዋልድባን ያስተዳድሩ(ያስገብሩ) እንደነበር እንደሚከተለው መስከሯል፡፡

“Above Temben, to the westward of Axum, is situated the province of Shire, which forms a pretty sharp angle with the Tecazze in the latitude of 14º; and on the opposite side of the river extend still farther westward, the districts of Waldubba and Walkayt, both of which continue to pay tribute to the Ras”. [5]

ስለዚህ፣ በሆረን አፌርስ ዘአዲስ በሚል የብዕር ሰም ‹‹ወልቃይት ላለፉት ሺህ ዓመታት በትግራይ ስር ተዳድራ አታውቅም – የታሪክ ማስረጃዎች››“ [6] የሚለው ሙግት ተአማኒነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ለምሳሌ፣ ላስታ በትግራይ ግዛት ውስጥ ነበር፡፡አሁን ግን ወደ አማራ ክልል ተካልለዋል…የአከባቢው ሕዝብ የሚናገረው አማርኛ ስለሆነ፡፡ወልቃይትም እንዲሁ ወደ ትግራይ ቢካለል ነውር ያለው አይመስለኝም፡፡

‹‹Lasta is also classed with Tigre. This province which has also given its name to the kingdom, of which it now forms part, is bounded on the west by the Tchera-Agous, on the north by the Ejjon-Gall, on the south-east by Angot, and on the north by Bora and Ouofila›› (Routes in Abyssinia, page 187). [7]

ዘ-አዲስ ጎጃምን የአማራ ግዛት ነበር ቢልም ፀሐፊው ዋቢ ያደረገው መፅሐፍ ግን ጎጃም የአማራ እንዳልነበር ነው የሚናገረው፡፡

‹Amhara, properly so called, extends between the Rivers Ouahet and Bachelot, it is bounded on the west by the Nile, which separates it from Gojam, and on the east by Lasta and Ingot›› (Routes in Abyssinia, page 189). [8]

ናይል(አባይ) አማራና ጎጃምን የሚዋሰኑበት ወንዝ ከሆነ አማራና ጎጃም አንድ አይደሉም ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም ይኸው መፅሐፍ ወሎም አማራ እንዳልነበር ይናገራል (በገፅ 17፣103፣139-144፣174)፡፡

ዞሮ ዞሮ ግን ሚዛናዊነቱ አጠያያቂ ከሆነው ታሪክ ይልቅ በአሁኑ ሰዓት መሬት ላይ ያለው እውነታ ሚዛን ይደፋል፡፡ ህዝብን ለመሳደብ የሚዳዳቸው ሰዎች ‹‹ትግሬ እንጂ ትግራይ ተከዘ ተሻግሮ አያውቅም›› የሚሉት መፈክር በአሁኑ ሰዓት ያለው የአለማችን ሁኔታ ያላገናዘበ ስሜታዊነት ነው፡፡ የስደተኞች ሃገር እየተባለች የምትጠራው አሜሪካ የቀይ ህንዳውያን ስለነበረች የአሁኖቹ አፍሪካውያን፣ አውሮፓውያንና ኤዥውያን ሊኖሩባት አይገባም ማለት ጅልነት ነው፡፡ አውስትራልያም ቢሆን በአብዛኛው በአውሮፓውያን የተያዘች ነች…ለአቦርጅኖች ሲባል ግን እነዚህ አውሮፓውያን መኖር የለባቸውም ማለት አይቻልም፡፡ ወይም አቦርጅኖች እንጂ አውሮፓውያን መሆን አይችሉም ማለት አንችልም፡፡

3/ ‹‹ወልቃይት እንኳን ህዝቡ መሬቱም ትግርኛ ተናጋሪ ነው፡፡››

ሀ. የወልቃይት ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪ ነው – ትግራዋይ ነው፡፡

ይህን ያሉት የታሪክ ተመራማሪና ፀሐፊው መምህር ገበረኪዳን ደስታ ናቸው፡፡[9] የወልቃይት ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪ ነው፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፤መሬቱ የሚናገረው ትግርኛ ነው፡፡

ጎንደር በነበረው ዓመፅ ‹‹ትግሬ እንጂ ትግራይ ተከዜን ተሻግሮ አያውቅም›› የሚል መፈክር ሲስተጋባ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይህ ግን መሰረት የለውም፡፡ ስድብ ሌላ እውነታው ሌላ ነው፡፡

የሚከተለው ሰንጠረዥ እንደሚያመለክተው የወልቃይት፣ ፀለምቲና ፀገደ ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪ ነው…ትግራዋይ ነው፡፡ የህዝቡ ቋንቋ ብቻም ሳይሆን ባህሉና አኗኗሩም ትግራዋይ ነው፡፡ ለዛም ነበር ወደ ትግራይ የተካለለው፡፡

እውነተኛ የህዝብ ጥያቄ ከሆነ ጥያቄው መቅረብ የነበረበት ለመንግስት እንጂ ለትግራይ ህዝብ መሆን አልነበረበትም፡፡ አሁን ግን የትግራይ ህዝብ ተጠይቆ መልስ አልሰጥም እንዳለ ተቆጥሮ ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ ከአማራ ክልል እንዲወጣ ጥብቅ ትእዛዝ ተሰጥቶታል፡፡

Table - 1994 Census of Wolqait, Humera, Tigrai, Ethiopia
Table – 1994 Census of Wolqait, Humera, Tigrai, Ethiopia

የወልቃይት ተወላጁ አቶ መኮንን ዘለለውም ከኤስ.ቢ.ኤስ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የሚከተለው ምስክርነታቸውን ሰጥቷል፡፡ ‹‹መጀመርያ ማን ነበረ የሚለው ጥያቄ መልሱ ትግርኛ ነው፡፡ ወልቃይት ከመጀመሪያው ጀምሮ ትግሪኛ ተናጋሪ ነው፤ ወደ ወልቃይት የመጣው አማርኛ እንጂ ትግሪኛ አይደለም።አማርኛ የመጣው ደሞ በፖሊስ፣ በበለጠ ደሞ አዝማሪዎች መጥተው ነው ያስፋፉት፡፡››[10]

ለ. የወልቃይት መሬት ትግርኛ ተናጋሪ ነው፡፡

በወልቃይት ወረዳ የሚገኙ ጣብያዎች ስም ትግርኛ ነው፡፡ ትግርኛ የሚናገረው ህዝብስ ከትግራይ የፈለሰ ነው እንበል፣ የአከባቢው ስሞችስ ከየት መጡ? አከባቢውም ከትግራይ ፈልሷል ማለት ነው? የሄ ፈፅሞ ሊሆን የማይችል ነገር ነው፡፡ ህዝቡም ከባቢውም ትግራዋይ መሆኑን በግልፅ ትግርኛ እየመሰከረ ነው፡፡ህዝቡ እኛ ማንነታችንን እናውቃለን…ማንም እንዲነግረን አንፈልግም እያለ ነው፡፡ መሬቱም እንዲሁ ማይ ልሐም፣ማይ ፀብሪ፣ ማይ ጋባ፣ ማይ ሑመር፣ ማይ ጨዓ፣ ማይ ጥምቀት፣ ቓቓ፣ ዓዲ አርቃይ፣ ወዘተ. እባላለሁ እያለ ነው፡፡ ይህ ትግራዋይ ካልተባለ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡

Table - List of places in Wolqait, Tigrai, Ethiopia
Table – List of places in Wolqait, Tigrai, Ethiopia

የሚከተለው ካርታ ደሞ 1971 ዓ.ም የነበረው የህዝብ አሰፋፈር ያመለክታል፡፡ ካርታው የተገኘው ከሆርን አፌርስ ድረ ገፅ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

Map - Nationalities in northern Ethiopia in 1970s
Map – Nationalities in northern Ethiopia in 1970s

4/ የወልቃይት ጥያቄ መነሳት ያለበት የት ነው?

የኮንሶ ህዝብ በደቡብ ክልል ነው የሚገኘው፤የልዩ ዞን አስተዳደር ይገባኛል ጥያቄ ያነሳውም በደቡብ ክልል ውስጥ ነው፡፡የቅማንት ህዝብ በአማራ ክልል ይገኛል፤ የልዩ ዞን አስተዳደር ይገባኛል ጥያቄ ያነሳውም በአማራ ክልል ነው፡፡ጥያቄው የተፈታውም በዛው…በአማራ ክልል ነው፡፡

የወልቃይት ህዝብ የሚገኘው በትግራይ ክልል ነው፤ የማንነት ጥያቄ እያነሱ ያሉት ሰዎች ግን ጎንደር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ጎንደሬዎች የልቃይት ጥያቄን እንደ ሰበብ ተጠቅመው በትግራይ ተወላጆች ላይ የንብረት፣ የአካልና የሕይወት ማጥፋት ጥቃት ፈፅሟል፡፡ጎንደር ወስጥ ሰባት የትግራይ ተወላጆች እንደተገደሉ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ቤት ለቤት እየዞሩም ‹‹እስከዚህ ቀንና ሰዓት ጎንደርን ለቃችሁ ካልወጣችሁ እንደነ እንትና በላያችሁ ላይ ጋዝ አርከፍክፈን ነው በእሳት የምናጋያችሁ›› እያሉ ሽብርና ጣራ የነካው መርዘኛ ጥላቻቸውን ሲረጩ ከርሟል፡፡[11]

አቶ ውብሸት ሙላት የሕገ መንግሥት ኤክስፐርትና ‹‹አንቀጽ 39›› የተሰኘ መፅሐፍ ደራሲ ናቸው፡፡ አቶ ውብሸት ወልቃይትን አስመልክተው የሚከተለውን ብሏል፡፡

‹‹የወልቃይት ጥያቄ የተፈጠረው በአማራ ክልል አይደለም፡፡ የወልቃይት ሕዝቦች የአማራ የማንነት ጥያቄ የተነሳው በትግራይ ክልል ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ጥያቄው ሊፈታ የሚችለው በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥቱ ነው፡፡›› [12]

ሆኖም ግን የጎንደር ሽማግሌዎች ናቸው አስታራቂ መስለው ጥያቄውን ያቀጣጠሉት፡፡ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጎንደር ውስጥ ከሽማግሌዎች(ሽማግሌ ከተባሉ) ጋር በተደረገው ስብሰባ ‹‹የወልቃይት ህዝብ የወልቃይት ብቻ ሳይሆን የመላው አማራ እንዲሆን ነው የምንፈልገው›› ብሎ ሲናገር ተሰብሳቢዎቹ በጭብጨባ ቢቱን ሲያደምቁት አይተናል፡፡ እኛ አማራ እንጂ ትግሬ አይደለንም የሚለው አዋጅ ያሰሙት በመቐለ ከተማ ሳይሆን በአማራ ክልል ውስጥ በጎንደር ከተማ ነው፡፡ሽማግሌዎቹ ‹‹አማራ ነን ብሎ ለመጣ እንቀበላለን›› ነበር ያሉት፡፡ ሲያጠቃልሉም የአማራነት ጥያቄ መቀጠል አለበት በማለት በሚል ነበር፡፡ ጠንክሩ እኛም ከእናንተው ጋር ነን፤ በጉልበት፣ በገንዘብ እናግዛችኋለን ብለዋቸዋል፡፡ እናም ጥያቄው የጎንደር፣ ብሎም የመላው አማራ ጥያቄ መሆኑን ታወጀ፡፡[13]

ይህ አካሄድ ራሽያ የዩክሬን ግዛት የነበረችው ክርሚያን ወደ ራሽያ ግዛት ለመጠቅለል የተጠቀመቸው ስልት ነው፡፡ይህ ስልት እየተጠቀሙ ያሉትም ጎንደሬዎችና የብአዴን አመራሮች መሆናቸው ግልፅ ነው፡፡የአማራ ክልል ልክ እንደ ሻዕብያ ትግራይን ለመውጋት ታጥቀው የተነሱ ሰዎችን ጥገኝነት እየሰጠ ነው፡፡እነ ኮሎኔል ደመቀም የልብ ልብ ስለሰጣቸው ወደ አመፅ አመሩ፡፡አመፁም የትግራይ ተወላጆችን የንብረት ውድመት፣ የአካል ጉዳት እንዲሁም ሰባት ሰዎች እንደተገደሉ እነአልጀዚራ ዘግቧል፡፡በተጨማሪም፣ የትግራይ ተወላጆች ከአማራ ክልል ጠቅልለው እንዲወጡ የግዜ ገደብ መስጠት ሆነ፡፡

5/ ማጠቃለያ

ወልቃይት፣ ህዝቡም ሆነ መሬቱ ትግርኛ ተናጋሪ መሆኑን መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ይህ እውነታ የሆነ ፈረንጅ እንዲህ ብሎ ነበር፣ መፅሐፍ እንዲህ ይላል፣ እንዲሁም ህዝብን የሚያንቋሽሹ መፈክሮችን በማሰማት የሚቀየር ነገር አይደለም፡፡ይኼ ‹‹ቢበርም ጅብ ነው›› ዓይነቱ ክርክር ለሁላችንም የማይበጅ የጌቶች ትእዛዝ ስለሆነ ከወዲሁ ቢታረም የተሻለ ይመስለኛል፡፡ጎንደር ውስጥ ከሽማግሌዎች ጋር በተካሄደው ስብሰባ እንደ ተስማሙበት ጥያቄው መጀመርያ የጎንደር እንዲሆን ተስማሙ፤ የጎንድር ጥያቄ ደሞ የአማራ እንደሆነ ተስማምተው ነበር የተለያዩት፡፡የህም ጥያቄው የወልቃይት ሳይሆን የአማራ መሆኑን በግልፅ ተመልክተናል፡፡ሽማግሌዎቹም፣ በእነ ኮሎኔል ደመቀ የሚመራው ቡድንን ተበድላችኋል፣ ተጨቁናችኋል…ከጭቆናው ነፃ እናወጣችኋለን የሚል ሙሉ ድጋፍ ሰጥተዋቸዋል፡፡

References

[1] Ghelawdewos Araia. Beyond Ethnocentric Ideology and Paradigm Shift for a Greater Ethiopian Unity, April 20, 2016

[2] Ibid

[3] Ibid

[4] Henry Salt. (1816). A Voyage to Abyssinia: And Travels into the Interior of that Country page 378 and 381

[5] Ibid

[6] ወልቃይት ላለፉት ሺህ ዓመታት በትግራይ ስር ተዳድራ አታውቅም – የታሪክ ማስረጃዎች፣ ሆርን አፌርስ፣ June 8, 2016.

[7] Routes in Abyssinia (printed in 1867 G.C): 

[8] Ibid

[9] Memhir Gebrekidan Desta interview on Welkait-Tsegede, March 6, 2016.

[10] Interview with Mekonnon Zelelow – SBS Amharic, April 22, 2016.

[11] Ethiopia: Ethnic Tigrayans flee to avoid anti-government protesters, Al Jazeera English, , August 21, 2016.

[12] የተቃውሞ ሠልፎቹ ዘርፈ ብዙ ሥጋቶች፡ Ethiopian Reporter.

[13] Colonel Demeke Zewdu Addressing Welkait Committee Public Meeting in Gondar: , August 20, 2016.

*********

Guest Author

more recommended stories