ሰላማዊ ሰልፍ: “እግዚያብሔር ሲቆጣ ያደነቁራል!”

ይህ ፅሁፍ በዋናነት ነገ ሐምሌ 30/2008 ዓ.ም በተለያዩ ከተሞች ሊደረግ በታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ያተኩራል፡፡ በእርግጥ ሰላማዊ ሰልፍ በሕገ-መንግስቱ ዋስትና የተሰጠው የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት ነው፡፡ ይህንን የማያውቅ ባለስልጣን ያለ አይመስለኝም። አፄ ሚንሊክ “እግዚያብሔር ሲቆጣ ያደነቁራል!” አሉ ይባላል፡፡ ምክንያቱም፣ የእኛ ሀገር ባለስልጣናት ከሕዝቡ የሚሰጣቸውን ሃሳብና አስተያየትን ተቀብሎ ማስተናገድ ሽንፈት ስለሚመስላቸው አይቀበሉትም። ሆኖም ግን፣ መንግስት ሕገ-መንግስቱን እየጣሰ ዜጎችን ሕግ እንዲያከብሩ የመጠየቅ መብት እንደሌለው ለማሣየት እሞክራለሁ። 

እኔ ሰው ነኝ፣ መንግስት መዋቅር ነው። እኔ መንግስትን እቀይራለሁ እንጂ መንግስት እኔን አይቀይረኝም። ይህ እውነት ላይመስል ይችላል። በተለይ በኢትዮጲያ፣ ሀገር የመንግስትና በመንግስት እንደምትቀየር ተደርጎ በሚታሰብበት ሀገር አባባሉ ተቀባይነት ላይኖረው ይችላል። ነገር ግን፣ ሕይወት በእውነት እንጂ በእኛ እሳቤ አትመራም። በነባራዊ እውነታ መንግስት ይፈጠራል እንጂ አይፈጠርም። ሕዝብ ግን መንግስትን ይቀይራል፣ መንግስትን ይፈጥራል። ምክንያቱም፣ መንግስት ከሕዝብ ውስጥ ይወጣል እንጂ ሕዝብ ከመንግስት ውስጥ አይወጣም። መንግስት ያለ ሕዝብ ሕልውና የለውም። መንግስት የሌለው ሕዝብ ግን አዲስ መንግስት ይመሰርታል። 

የሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ እንደየግዜውና ሁኔታው ይቀያየራል። ሥራና አሰራሩን እንደ ሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ የሚቀይርና የሚያሻሽል መንግስት እድሜውን ይረዝማል። ከሕዝብ ፍላጎትና ምርጫ ጋራ አብሮ የማይሄድ መንግስት ግን በሌላ ይቀየራል። ምክንያቱም፣ መንግስት የተፈጠረው ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጥ እንጂ እንቅፋት እንዲሆን አይደለም። ሕዝቡ ለሚያነሳቸው የለውጥና መሻሻል ጥያቄዎች ምላሽ መሰጠት የተሳነው መንግስት ከሕዝብ ጋር ይጋጫል። ሕዝቡ አቤቱታውን እንዳይገልፅ የሚያግድ መንግስት ለውድቀት መንደርድር እንደጀመረ ይቆጠራል።     

መንግስት ማለት አስተዳደራዊ መዋቅር ነው። እንደ አስፈላጊነቱ መዋቅር ይቀየራል፥ ይሻሻላል። በመዋቅር ውስጥ ሰው ይገባል፥ ይወጣል። ሕዝብ ማለት “እኔ” ነኝ። እኔ አንድ ግለሰብ ነኝ ግን መንግስትን እሾማለሁ፥ እሽራለሁ። እኔ በአንድ ሀገር ፖለቲካ የለውጥና መሻሻል ሂደት መለኪያ ነኝ። የአምባገነናዊ ሥርዓት እና የዴሞክራሲ መለያ መስፈርት ነኝ። “Henry David Thoreau” እንዳለው እኔ የመንግስት ስልጣንና ኃይል ባለቤት ነኝ፡- 

“The progress from an absolute to a limited monarchy, from a limited monarchy to a democracy, is a progress toward a true respect for the individual. …there will never be a really free and enlightened state until the state comes to recognize the individual as a higher and independent power, from which all its own power and authority are derived, and treats him accordingly” Civil Disobedience 

እኔ ሰው ነኝ። እንደ ሰው፤ የእኔ መብት “ነፃነት” ነው፡፡ የእኔ ግዴታ የሌሎችን ሰዎችን ነፃነት አለመጋፋት ነው። በነፃነት ውስጥ፤ 1ኛ፡- የፈለኩትን ነገር የመስራት፥ የመናገር፥ የመፃፍ…. መብት፣ 2ኛ፡- በባዕድ መንግስት ወይም ሌላ ሰው ቁጥጥር ስር ያለመሆን መብት፣ እና 3ኛ፡- ራሴን-በራሴ የማስተዳደር፥ የመምራት ስልጣን አለኝ። መንግስት ማለት 1ኛ እና 2ኛ መብቶቼን እንዲያስከብርልኝ 3ኛ ላይ የተጠቀሰውን ስልጣን በውክልና የሰጠሁት አካል ነው። ስለዚህ፣ ነፃነቴን እንዲያስከብርልኝ በሕገ-መንግስቱ መሰረት በተፈጥሮ የተቸረኝን ራሴን-በራሴ የማስተዳደር ሥልጣን አሳልፌ ሰጥቼዋለሁ። ነገር ግን፣ የሰጠሁትን ስልጣን ተጠቅሞ መልሶ የእኔን ነፃነት ሲጋፋ መንግስት የገባውን ውል አፍርሷል። ስለዚህ፣ መንግስት ውል ሲያፈርስ እኔ ደግሞ ውክልናዬን አነሳለሁ። መንግስት ሕገ-መንግስቱን ካላከበረ እኔም ለመንግስት የሰጠሁትን ስልጣን አነሳለሁ። የእኔን ነፃነት የሚጥስ መንግስት በእኔ ላይ ስልጣን የለውም። 

በነፃነት የመናገር፥ የመፃፍ፥ የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብት ያለኝ ሰብዓዊ ፍጡር ነኝ። መንግስት የመሬት ባለቤትነቴን እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነቴን ካላረጋገጠልኝ፣ ቋንቋና ባህሌን የማበለፅግበት እድል ከነፈገኝ፣ ተበድዬ ፍትህን ካልሰጠኝ፣…. ነፃነቴን ካላከበረልኝ፣ ውል አፍርሷል። ስለዚህ፣ “ሕገ-መንግስት ይከበር!” ብዬ ደጋግሜ ጮኼያለሁ። መንግስት የሰጠሁትን ስልጣን ተጠቅሞ የራሴን አመለካከት እንዳልይዝ እና ሃሳቤን እንዳልገልፅ የሚያግደኝ ከሆነ፣… ስለተናገርኩ የሚደበድበኝ፣ ስለፃፍኩ የሚያስረኝ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ሰለወጣሁ የሚገድለኝ ከሆነ… እኔም አምፃለሁ፥ እቃወማለሁ። በሕገ-መንግስቱ የገባውን ውል ሲያፈርስ እኔ እዳ የለብኝም። ስለዚህ፣ እኔም እንደ እሱ ውል አፈርሳለሁ። 

መንግስት “ሕገ-መንግስት ይከበር!” ብዬ ስጮህ በየግዜው ሕገ-መንግስቱን የሚጥስ አዲስ ሕግ የሚያረቅ ከሆነ፤ በሰላማዊ መንገድ ስለታገልኩ በሽብርተኝነት የሚከሰኝ፣ ሽብርተኝነትን ለመከላከል እያለ እኔን የሚያሸብረኝ ከሆነ፤ መብቴን እየጠየቅኩ ግዴታውን የማይወጣ፣ ግዴታዬን እየተወጣሁ መብቴን የማያከበር ከሆነ፤ እኔ እውነት እየጠየቅኩት እሱ ውሽት የሚነግረኝ ከሆነ፤ ንብረት ወድሞ-አልወደመም፣ ሰው ሞቶ-አልሞተም፣ ሰው ተርቦ-አልተራበም፣…እንደ ሰው ሰብዓዊነቴን፣ እንደ ዜጋ ዴሞክራሲያዊ መብቴን የማያከብር መንግስት በእኔ ላይ ስልጣን የለውም። ሕገ-መንግስት ሲጥስ ለእሱ የሰጠሁትን ስልጣን መልሼ ወስጄያለሁ። 

ከዚያ በኋላ ራሴን-በራሴ አስተዳድራለሁ፥ እመራለሁ። የሌላ ነፃነት ሳልጋፋ የፈለኩትን ነገር እሰራለሁ፥ እናገራለሁ፥ እፅፋለሁ። ከዚህ በኋላ የመንግስት ድጋፍና ውክልና አያስፈልገኝም። እኔን የሚያጠቃኝ ጠላት ሲመጣ ራሴን-በራሴ እከላከላለሁ። ነፃነቴን የሚጋፋ ሲመጣ አመፃለሁ፥ እቃወማለሁ፤ የጠላቴን መምጫ መንገድ ዘጋለሁ፥ ንብረቱን አወድማለሁ፥ በሰላም ወጥቶ እንዳይገባ አደርገዋለሁ። የእኔን መብት እስካላከበረ ድረስ ለእሱ ግዴታ የለብኝም። የእኔን ነፃነት የማያከብር አካል የሚከበር መብት የለውም። የእኔን ነፃነት ለማያከብር መንግስት ግዴታ የለብኝም። ኃላፊነቱን የማይወጣ መንግስት እኔን የማዘዝ ስልጣን የለውም። 

ማስታወሻ 

አንደኛ፡- ሰለማዊ ሰልፍ በሕግ-መንግስቱ አንቀፅ 30፣ ሁለተኛ፡- በሰላማዊ ሰልፉ የሚተላለፉ መልዕክቶችና መፈክሮች በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 29 መሰረት ለዜጎች የተፈቀዱ ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስለሆኑ፣ መንግስት የሕዝብን ሕይወትና ንብረት ደህንነት፣ እንዲሁም መደበኛ እንቅስቃሴ እንዳይስተጓጎል ከማድረግ ባለፈ ሰላማዊ ሰልፉ እንዳይካሄድ መሰናክል እንዳይፈጥር ለማሳሰብ የቀረበ ነው። አብዛኛውን ግዜ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም ተቃውሞና አቤቱታቸውን ለማቅረብ የሚያደርጉት ጥረት በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች ሲደናቀፍ ሰላማዊ ሰልፉ ወደ አመፅና ብጥብጥ ይቀየራል። ስለዚህ፣ መንግስት የዜጎችን ሕገ-መንግስታዊ መብት በመገደቡ ለሚፈጠረው ችግር ሙሉ ኃላፊነቱ የእሱ እንደሆነ አውቆ ከእዚህ ዓይነት ተግባር እንዲቆጠብ ለመጠየቅ እወዳለሁ።   

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories