በ9 ወር ግዙፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ የገነባን እኛ፤ በ5 ዓመት አንድ ፋብሪካ መገንባት ያቃተንም እኛ!

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በተመረቀው የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ላይ ተገኝተው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ያደረጉትን ንግግር የጀመሩትም እንዲህ በማለት ነበር፤ «የዛሬዋ ቀን ልዩ ናት»። አቶ ኃይለማርያም ይህንን ለማለት ብዙ ከበቂ በላይ ምክንያት አላቸው፤ ያስመረቁት በአገራችን አምራች ኢንዱስትሪ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን ግዙፍ ፕሮጀክት ነውና።

የሀዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ በውስጡ በርካታ ፋብሪካዎችን ያቀፈ ነው። የራሱ የሆነ የኤሌክትሪክና የውሃ አቅርቦትና ማሰራጫ ጣቢያ አለው። የሚጠቀመውን የሽንትቤት ውሃ ሳይቀር መልሶ በማጣራት ለአገልግሎት ያውላል። እስከ 10 ጊጋ ባይት የሚደርስ አቅም ያለው የፋይበር ኢንተርኔት መስመር ተዘርግቶለታል። ምንም ዓይነት ፍሳሽ ወደ አካባቢው አይለቅም።

Photo - Hawassa Industrial Park [Credit:AddisFortune]
Photo – Hawassa Industrial Park [Credit:AddisFortune]

ለ60 ሺ ሰዎች በሁለት ፈረቃ የሥራ ዕድል ይፈጥራል። 25 ሺ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች በግቢያቸው ውስጥ ሠራተኞች የሚከራዩአቸውን ቤቶች እንዲገነቡ ብድር ተመቻችቶላቸዋል። የቪዛ አገልግሎት ሳይቀር ሁሉም የመንግሥት ሥራዎች በፓርኩ ውስጥ ይከናወናሉ። ሌላም ሌላም የሀዋሳው ኢንዱስትሪ ፓርክ ገፅታ ነው። ይህንን በ420 ሺ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ የኢንዱስትሪ ፓርክ ገንብቶ ለማጠናቀቅ የፈጀው ጊዜ 9 ወር ብቻ ነው።

ለዚህም ነው አቶ ኃይለማርያም የዛሬው ቀን ልዩ ናት ማለታቸው። በተለይ እርሳቸው የሚመሩት መንግሥት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር ደፋ ቀና እያለ ባለበት በዚህ ወቅት የዚህ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክትን በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ገንብቶ ከዳር ማድረስ ትልቅ ድል ነው። ስለሆነም የትናንትናውን ዕለት በተመለከተ የሀገሪቱ ልዩ ቀን ነው ማለት በእርግጥም ተገቢ ነው።

ጥያቄው ያለውም እዚህ ላይ ነው። ባለፈው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ይገነባሉ ከተባሉት ሦስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ አንዱም አልተሳካም። የቦሌ ለሚውም ቢሆን ገና አሁን በስድስተኛ ዓመቱ እየተገባደደ ያለ ነው። በአምስት ዓመት ውስጥ አንድ ግንባታ ማሳካት የተሳነን እኛ፤ በአገራችን አይደለም በአፍሪካ ውስጥ በግዙፍነቱ ወደር የሌለውን የኢንዱስትሪ ፓርክ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ ገንብተን እዚህ ያደረስነውም እኛ ነን። ይህ እንዴት ይሆናል? ብሎ መጠየቅና አስፈላጊውን ልምድ መቅሰም ያስፈልጋል፡፡

መንግሥት ይህንን ግዙፍ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያሳካ የቻለበትን ምስጢር ይፋ አድርጓል። ምስጢሩ ከላይ እስከታች ያለው አስፈጻሚ በአንድ አካል አንድ አምሳል ተቀናጅቶ መንቀሳቀሱና ለወትሮ ትልቅ እንቅፋት የነበረውን ያልተገባ የአሰራር መንዛዛትን ማስወገድ መቻሉ ነው። በተጨማሪም የግንባታ ተቋራጮች ልየታ ታስቦበትና ተለፍቶበት የተከናወነ መሆኑ ነው።

ልብ ይበሉ! የዚህ ዓይነት ግዙፍ ፕሮጀክት በአጭር ጊዜ አጠናቀን ለአገልግሎት ስናበቃ ይህ የመጀመሪያችን አይደለም። ከዚህ በፊትም ከቦሌ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ የሚዘልቀውን መንገድ በታላቁ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ የበላይ ተቆጣጣሪነት በጣም በአጭር ጊዜ ሰርተን አጠናቀናል። በወቅቱም የተነገረው የስኬቱ ምስጢርም ባለድርሻዎች ተቀናጅተው መስራታቸው ነው ተብሏል።

ይህንን የግንባታ ቅንጅትም በሌሎች ግንባታዎች ላይ እናሰፋለን ተብሎ ተነግሮም ነበር። እንደውም በወቅቱ ከስድስት ኪሎ እስከ ፈረንሳይ ጉራራ እየተገነባ በነበረው ፕሮጀክት ላይ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎም በከተማዋ የመንገዶች ባለስልጣን በኩል ተነግሮ አድምጠናል፤ ዘግበናልም። ይህ መንገድ ግን ከተቀመጠለት የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜ አልፎ በምርጫ 2007 ወከባ በግድ የተጠናቀቀ ፕሮጀክት እንደነበረ ሁሉም የሚያውቀው ነው።

የሀዋሳውን የኢንዱስትሪ ፓርክና የቦሌውን የመንገድ ፕሮጀክት በጣም በአጭር ጊዜ ያጠናቀቀ ህዝብና መንግሥት እንዴት በአምስትና ስድስት ዓመት ውስጥ አንድ የስኳር ፋብሪካ ገንብቶ ማጠናቀቅ ተሳነው? መልሱ ቀላል ነው። በየደረጃው ያለው የአስፈጻሚ አካል ቁርጠኝነት ከአንገት ሳይሆን ከአንጀት ሲሆን እንዲህ እንደ አሁኑ ታምር መስራት ይችላል። ከዚህ ውጪ ግን ከላይ ባለው አመራር ቁርጠኝነት ብቻ ወይንም ከታች ባለው ፈጻሚ ትጋት ብቻ የትም መድረስ እንደማንችል ብዙም ርቀን ሳንሄድ የግንባታ ጊዜያቸውንና በጀታቸውን ቅርጥፍ አድርገው በልተው ዛሬም ድረስ በግንባታ ላይ ያሉት ፕሮጀክቶቻችን ይነግሩናል።

ስለሆነም ለስኬታችን የመዘዝነው የስኬት ሰበዝ በችግራችንም ላይ ሊደገም ይገባዋል። በስኬታችን ላይ በምንወዳደሰው ልክ በውድቀታችንም ላይ ልነወቃቀሰ የግድ ይለናል። የሀዋሳውን የኢንዱስትሪ ፓርክ በአጭር ጊዜ ከዳር ያደረሱ ግለሰቦችና ተቋማትን ለማመስገን የተዘረጉ እጆች በስኳር፣ በማዳበሪያ፣ በመንገድ፣ በቤቶችና መሰል ግንባታዎች ላይ አፈጻጸማቸው ዝቅተኛ በሆኑ አስፈጻሚዎችና የሥራ ተቋራጮች ላይም ለምን ሊሉ ይገባል። ይህንን ማድረግ ሲቻልም ጭምር ነው የሀዋሳውን የግንባታ ተመክሮ በአገር አቀፍ ደረጃ ባሉ ፕሮጀክቶቻችን ላይ መድገምና የህዳሴያችንን ጉዞ ማፋጠን የሚቻለው።

*******

* መጀመሪያ የታተመው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ Jul 14, 2016

Areaya Getachew (MA) is a public relations expert at a foreign embassy. He studied second degree at Addis Ababa University and was deputy editor in-chief of Addis Zemen newspaper.

more recommended stories