ጉንጭን ማልፋት ይሻላል ከጦርነት

የ2ኛው ዓለም ጦርነት ሲነሣ የአንድ ሰው ስም አብሮ ይነሳል። በወቅቱ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት የዊኒስተን ቸርችል ስም። ይህ ታላቅ መሪ በሀገሩ እንግሊዝ ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣውን አደጋ በመመከት የቁርጥ ቀን መሪ መሆኑን አስመስክሯል። በዚህ ረገድ የዋለው ውለታ ለሀገሩ ብቻ አልነበረም። በተለይ በናዚ ጀርመን እና ፋሽስት ኢጣሊያ ቁጥጥር ስር ለወደቁት ሀገራት ጭምር ባለውለታ ነው። ከዚህ ውስጥ ሀገራችን ኢትዮጲያ አንዷ ናት። የፋሽስት ኢጣሊያን ወራሪ ሃይል ከሀገራችን ጠራርጎ በማስወጣቱ ረገድ ላበረከተው አስተዋፅዖ “ቸርችል ጎዳና” በሚል በስሙ መንገድ ተሰይሞለታል። ይህ ታላቅ መሪ በጦርነት ወቅት ለኢትዮጲያና ሌሎች የአለም ሀገራት ላደረገው ድጋፍ ዛሬም ሆነ ወደፊት ስሙ በክብር ይነሳል።

ዊኒስተን ቸርችል ሀገሩን በከባድ ጦርነት ውስጥ በመምራት ለድል እንዳበቃት ዘወትር ይነገራል። ነገር ግን፣ ይህ መሪ በ2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ካሳየው ጀግንነት በላይ፣ 3ኛው የዓለም ጦርነት እንዳይነሳ በማድረጉ ይበልጥ ጀግና ነው። በእርግጥ ይህ ሰው የጦርነት ሳይሆን የሰላም ጀግና ነበር። ለዚህ ደግሞ እ.አ.አ በ1954 ዓ.ም በአሜሪካ ነጩ ቤተ-መንግስት ያደረገውን ንግግር እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል። በንግግሩ ወቅት ቸርቺል እንዲህ ብሎ ነበር፤ “to jaw-jaw is always better than to war-war”። እኔ ደግሞ “ጉንጭን-ማልፋት ሁሌም ይሻላል ከጦርነት” በማለት ወደ አማርኛ መልሼዋለሁ።

በእርግጥ ዊንስተን ቸርችል በ2ኛው የዓለም ጦርነት ሀገሩን ለድል ያበቃው በጉንጭና የመንገጭላ ውጊያ አልነበረም። በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣን ድንገተኛ አደጋ ለመከላከል ጦር መሳሪያ እና መስዋዕት ይጠይቃል። የጀርመኑ አዶልፍ ሂትለር በእንግሊዝ ላይ የፈፀመው ወረራ፣ የኤርትራው ኢሳያስ አፍወርቂ በ1990 ዓ.ም (እ.ኢ.አ) በኢትዮጲያ ላይ ከፈፀመው ወረራ ጋር ተመሣሣይ ነው። ሁለቱም ሀገራት በሉዓላዊነታቸው ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመከላከል ያሳዩት ጀግንነትና የከፈሉት መስዋዕትነት በጣም ትልቅ ነው። በእንዲህ ያለ ሁኔታ፣ ምንም እንኳን የራሱ የሆነ አስተዋፅዖ ቢኖረው፣ ጉንጭን-ማልፋት ለድል አያበቃም። ነገር ግን፣ በዚህ ጦርነት ለድል ባያበቃም ሌላ ጦርነትን በማስቀረት ግን አማራጭ የለውም።

Photo - Battle of Normandy, WWII
Photo – Battle of Normandy, WWII

ዊንስተን ቸርችል በጦርነት ቆራጥ መሪ ቢሆንም፣ 3ኛው የዓለም ጦርነት እንዳይቀሰቀስ በማድረጉ ረገድ ያሳየው ጀግንነት ግን በ2ኛው የዓለም ጦርነት ካሳየው ጀግንነት እጅግ የላቀ ነው። ምክንያቱም፣ በ1ኛና 2ኛው የዓለም ጦርነቶች ወቅት በሰውና ንብረት ላይ የደረሰው ውድመትና ኪሳራ ተመልሶ ለ3ኛ ግዜ ቢደርስባት እንግሊዝ አሁን ካላት የብልፅግና ደረጃ ባልደረሰች ነበር። ለእኔ የዊንስተን ቸርችል ጀግንነት የሚመዘነው፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሰጠው አመራር በላይ፣ ከዚያ በኋላ ባሉት አመታት ሀገሪቱ ሌላ ትልቅ ጦርነት ውስጥ እንዳትገባ ባደረገው ነው።

ጦርነት እንዲቆም ከማድረግ በስተቀር ሌላ ምንም ጥሩ ነገር የለውም። ሆኖም ግን፣ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲሰነዘር ብቸኛ አማራጭ ይሆናል። ይሄን መቀልበስ ከተቻለ በኋላ ግን ጦርነት የመጀመሪያ መሆኑ ቀርቶ የመጨረሻ አማራጭ ይሆናል። በ1990 ዓ.ም የኤርትራ መንግስት በሀገራችን ላይ ወረራ ፈፅሟል። ይህ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት ማስከተሉ ይታወሳል። ከዚያ ቀጥሎ ባሉት አመታት፣ ልክ እንግሊዝ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እንዳደረገችው፣ ኢትዮጲያ ወደ ሌላ ጦርነት እንዳትገባ ማድረግ ይጠበቅብናል። ምክንያቱም፣ ጀግንነት በየግዜው ጦርነት ውስጥ ተዘፍቆ፣ በዜጎች የሕይወት መስዋዕትና በንብረት ውድመት አሸነፍኩ ብሎ ማቅራራት ሳይሆን ጦርነት እንዳይመጣ መከላከል መቻል ነው።

ከላይ የጠቀስኩትን አባብል ለመጀመሪያ ግዜ የሰማሁት በአንድ ትምህርታዊ የውይይት መድረክ ላይ ነበር። ተናጋሪዋ የቀድሞ የእንግሊዝ የሀገር ውስጥ ድህንነት ቢሮ ኃላፊ ስትሆን፣ ዘላቂ ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ የሚቻለው በንግግር ብቻ እንደሆነ አስረግጣ ትናግራለች። አያይዛም፣ ለመነጋገር ምንም አይነት ቅድመ-ሁኔታ ሊደረግ እንደማይገባ ትገልፃለች። በዚህ የውይይት መድረክ ላይ እንደገለፀችው፣ የእንግሊዝ የደህንነት መስሪያ ቤት፤ ከሰሜን አየር-ላንድ የሽብር ቡድን (አማፂ) ጋር፣ ከፍልስጤሙ ሃማስና ከሊቢያው መሃመድ ጋዳፊ ጋር ሳይቀር በሚስጥር ለመደራደር ይሞክሩ እንደነበር ተገልጿል። ምንም ያህል አምባገነንና ጨቋጭ ቢሆን፣ ኢሳያስ አፍወርቂ ከተጠቀሱት የባሰ ሊሆን አይችልም። ከእሱ ጋር በቀጥታ መነጋገር ባይቻል እንኳን በአመራር ደረጃ ያሉ፣ በሀገራቸው ለውጥና መሻሻል እንዲመጣ ከሚሹ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋር መነጋገር ይቻላል። ምክንያቱም፣ ከጦርነት አንፃር ሲታይ፣ መነጋገር ጉንጭን ከማልፋት በስተቀር ሌላ ምንም ጉዳት የለውም። ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ “to jaw-jaw is always better than to war-war” የሚለውን መርህ ለሀገር ሰላምና ድህንነት አስተዋፅዖው የላቀ ነው፡፡

**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories