ነፃነት የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ስለሆነ እንቅስቃሴው በሙሉ ከዚያ ጋር የተቆራጀ ነው። መብትና ግዴታ፣ ሕገ-መንግስትና የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ፣ ሀገርና መንግስት፣… የሁሉም መሰረታዊ ዓላማ የሰው ልጅን ነፃነት ማክበርና ማስከበር ነው። ከሰው በስተቀር የሚከበር መብት ያለው ሌላ አካል የለም። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን በሀገራችን እየወጡ ያሉ ሕጎችና አዋጆች መንግስትንና ባለስልጣናት “መብት እንዳላቸው” ታሳቤ ያደረጉ ናቸው። ነገር ግን፣ ይህ እሳቤ መሰረታዊ የመብት መርህን ይጥሳል። ምክንያቱም፣ መንግስት ግዴታ እንጂ መብት የለውም። የመንግስት ባለስልጣናት ቢሆኑም እንደ ግለሰብ ካልሆነ በስተቀር በሃላፊነታቸው ምንም የተለየ መብት የላቸውም። ስለዚህ፣ መንግስትና ባለስልጣናት፤ በመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ፣ “የመንግስት ሃላፊዎችን በሀሰት መወንጀልና ስም ማጥፋት” የሚለው፣ አዲስ በረቀቀው የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ፣ “ክብር ወይም መልካም ስም የሚያጎድፍ ጽሁፍ፣ …” …ወዘተ ባሉት የሕግ አንቀፆች ዜጎችን ለመክሰስ የሚያስችል ህጋዊ መሰረት የላቸውም።

ነፃነት የሌሎች ሰዎችን ነፃነት በማይጋፋ መልኩ በራሱ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት መንቀሳቀስ መቻል ነው። ስለዚህ፣ ማንኛውም ሰው የሌሎችን ነፃነት ሳይጋፋ በራሱ ነፃ ፍላጎትና ምርጫ መሰረት የመንቀሳቀስ መብት አለው። ይህ መብት ግን በተናጠል የተቀመጠ ሳይሆን የሌሎች ሰዎች መብትን ከማክብር ግዴታ ጋር የተጣመረ ነው። ለምሳሌ፣ የእኔ ፍላጎትና ምርጫ መብት የሌሎች ሰዎችን ነፃነት መጋፋት የለበትም። የእኔ መብት ለሌሎች ሰዎች ግዴታ ነው። የእኔ ግዴታ የሌሎች ሰዎችን መብት ማክበር ነው። በዚህ መሰረት፣ ነፃነት የመብትና ግዴታ ጥምርታ ነው።

የሰው-ልጅ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን የሚመራባቸው የሞራል ዕሴቶች እና የሥነ-ምግባር ደንቦች ፋይዳቸው በመብትና ግዴታ መካከል ያለውን ሚዛን መጠበቅ፣ የሰዎች ነፃነት ማክበርና ማስከበር ነው። በዚህ ዘመን የምንዳኝባቸው ሕጎች በዚህ ፅንሰ-ሃሳብ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። በመሰረቱ፣ ማንኛውም ሕግ ግዴታን በማስገደድ መብት ለማስከበር የተዘረጋ ስርዓት ነው። አንዱ የሌላውን መብት እንዳጋፋ፣ ወይም አንዱ ለሌላው ያለበትን ግዴታ በአግባቡ እንዲወጣ የሚደረግበት ስርዓት ነው። ስለዚህ፣ የትኛውም ሕግ የዜጎችን መብትና ግዴታ በማስከበር ለነፃነታቸው ዋስትና እንዲሆን ታስቦ የሚዘረጋ ነው። ሕግ የሚያስፈልገው ሰው በነፃነት ተግባራዊ እንቅስቃሴውን እንዲያደግ ለማስቻል ነው።

በነፃነት መርህ መሰረት፣ የሁላችንም መብት የእያንዳንዱ ግለሰብ ግዴታ መሆኑን አውቀን እና የእያንዳንዳችን መብት ሲከበር የሁላችንም መብት እንደሚከበር ተቀብለን ከተንቀሳቀስን ሕግ አያስፈልገንም። እያንዳንዱ ሰው ግዴታውን ሲወጣ የሁሉም ሰው መብት ይከበራል፣ ሁሉም ሰው ግዴታውን ሲወጣ የእያንዳንዱ ግለሰብ መብት ይከበራል። ነገር ግን፣ የሰው ልጅ በዚህ መልኩ ሌሎችን ማመንና በራሱ መተማመን ስለተሳነው፣ የመብትና ግዴታን “ሚዛን” የሚጠበቅ የጋራ ዋስትና አስፈለገው። ለዚህም የጋራ ሕግ አስፈላጊ ሲሆን፣ ሕጋዊ ስረዓት ለመዘርጋት ደግሞ ሦስት አካላት ያስፈልጋሉ፤ ሕግ አውጪ፣ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈፃሚ።  የሦስቱ አካላት ጥምር ውጤት ደግሞ “መንግስት” ነው።

መንግስት በዚህ መልኩ የዜጎችን ነፃነት ለማስከበር በሚል የተፈጠረ መዋቅር ነው። የመንግስት ኃላፊነት የመብትና ግዴታ ሚዛን እንዳይዛባ መጠበቅ ነው። በመሆኑም፣ የመንግስት ዋና ተግባር በተፈቀደለት የሕግ አግባብ መሰረት ሁሉም ዜጎች ግዴታቸውን እንዲወጡ በማድረግ ለመብታቸው ዋስትና ዋስትና መሆን ነው። ከዚህ በሕግ አግባብ ከተሰጠ ኃላፊነት ውጪ ሌላ ተግባር ለመፈፀም የሚያስችል መብት የለውም። መንግስት ከህዝብ የተሰጠውን ነፃነት የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት፥ ግዴታ ነው ያለበት የለውም። 

ሕግ ሁሉም ዜጎች ግዴታቸውን እንዲወጡ፣ በዚህም የሁሉም መብት እንዲከበር ለማስቻል የተዘረጋ ስርዓት ነው። ስለዚህ፣ ማንኛውም ዓይነት ሕግ የሚወጣው የዜጎችን ነፃነት ለማስከበር ነው። ህጋዊ መንግስት፣ እንደ መንግስት ሃላፊነት፥ ግዴታ እንጂ መብት የለውም።  በመሆኑም፣ መንግስት የሚያወጣው ሕግ የዜጎችን ነፃነት ለማስከበር ካልሆነ በስተቀር ሌላ ፋይዳ የለውም።

መንግስት ለዜጎች ነፃነት ጥበቃ የማድረግ ግዴታ እንጂ ነፃነታቸውን ለመገደብ የሚያስችል መሰረት የለውም። ስለዚህ፣ ማንኛውም የህግ ረቂቅ፤ ሲረቀቀና ሲፀድቅ፣ ሲተረጎምና ሲተገበር፣… በሁሉም አጋጣሚ አግባብነቱ ከሀገሪቱ ዜጎች ነፃነት አንፃር መመዘን አለበት። በዚህ መሰረት፣ ነፃነትን የሚገድብ፤ የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጥስ ማንኛውም ህግ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም። የሀገሪቱ ሕገ-መንግስት የዜጎቹን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ለማክበርና ለማስከበር ግዴታ እንዳለበት የሚያረጋግጥ የውል ሰነድ ነው። በሕገ-መንግስቱ መሰረት የተጣሉበትን ግዴታዎች ለመወጣት ጥረት ከማድረግ ባለፈ በሰነዱ ውስጥ የተጠቀሱትን የግለሰብ መብቶች በፍፁም መጋፋት አይችልም።

እንደ አለመታደል ሆኖ፣ በተለይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ በኢትዮጲያ እየወጡ ያሉ ህጎች በአብዛኛው የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የሚጥሱ ናቸው። ለምሳሌ፣ በመገናኛ ብዙሃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000፣ አንቀፅ 41፥ ተ.ቁ 2 እና አንቀፅ 43፥7 ላይ በተጠቀሰው መሰረት በመገናኛ ብዙሃን የመንግስት ኃላፊዎች በሀሰት መወንጀልና ስም ማጥፋት እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር (100,000) ቅጣት እንዳለው ይጠቅሳል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ከሳሽ ሆኖ የሚቀርበው በወንጀሉ ተጎጂ የሆነው ባለስልጣን ሳይሆን አቃቤ_ህግ ነው። ሌላው፣ አዲስ በውጣው የኮምፒውተር ወንጀል አዋጅ፣ በሰዎች ነፃነትና ክብር ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በሚለው አንቀፅ-6፥3 ላይ ተመሳሳይ ተግባር ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚያስቀጣ ይጠቅሳል። 

ሆኖም ግን፣ ከላይ ለመጥቀስ እንደተሞከረው፣ ማንኛውም መንግስት እንደ መንግስት ከህዝብ የተጣለበት ግዴታ እንጂ የራሱ የሆነ መብት የለውም። አንድ ባለስልጣን እንደ ማንኛውም የግለሰብ ካሉት ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተጨማሪ የመንግስት ኃላፊ ስለሆነ ሌላ መብት ሊኖረው አይችልም። ማንኛውም ባለስልጣን፣ እንደ መንግስት ኃላፊ፣ ህዝብን የማገልገል ግዴታ እንጂ የግለሰቦችን ነፃነት ለመገደብ የሚያስችል መብት ወይም ነፃነት የለውም።

በግል ሰብዕና፣ ሕይወትና ንብረት ላይ እስካልደረሰ ድረስ አንድን የመንግስት ባለስልጣን በኃላፊነቱ ዙሪያ በሀሰት ወይም በእውነት መረጃ ላይ ተመስርቼ ልከሰው፣ በዚህም የስም ማጥፋት ተግባር ልፈፅምበት እችላለሁ። ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን፣ ለሌሎች ሰዎች ያለብኝን ግዴታ በሕጋዊ መንገድ እንድወጣ ከማድረግ እና ለእኔና ለሌሎች የኢትዮጲያኖች ያለበትን ግዴታ ከመወጣት በዘለለ፣ በህዝቡ ዘንድ እንዲከበርለት የሚጠይቀው መብት የለውም። መንግስት እንደ መንግስት፣ ባለስልጣን እንደ ባለስልጣን በሚደርስባቸው የሀሰት ውንጀላና ትችት ምክንያት ክብሬና መልካም ስሜ ጠፍቷል ለማለት መብት የለውም። መንግስትና ባለስልጣናት ያላቸው ብቸኛ መብት በህዝብ የተጣለበትን ግዴታ በአግባቡ መወጣት። ይህን ማድረግ ያልቻለ ደግሞ አለመቻሉን ገልፆ ሃላፊነቱን በፍቃዳችን እንደሰጠነው በፍቃዱ መልቀቅ ይችላል። አሁን እየሆነ ያለው ግን መሆን ከነበረበት ፍፁም ተቃራኒ ነው። የኢህአዴግ መንግስትና ባለስልጣናቱ  የሌላቸውን መብት እየጠየቁ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን እየሸራረፉ ነው።

*************

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories