በቀውሱ የህዳሴን መንገድ ይቀይሱ – ለጠ.ሚ ኃ/ማሪያም

አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታን በግልፅ የተረዳ፥ የሚረዳ፥ የሚያስረዳ ማን ነው? እስኪ ትክክለኛ መረጃ ያለው፦ ሚዲያ፣ መንግስት ወይስ ህዝብ ነው? ሚዲያ እንዲኖር የሚወራ ወሬ መኖር አለበት፤ ወሬ ካለ ያወራል፥ ያስመስላል፣ ወሬ ባይኖር እንኳን ይፈጥራል። ለምሳሌ፣ ኢትዮጲያ እንደ EBC “በእድገት እየተመነደገች” አይደለም፣ እንደ OMN “በነውጥ እየተናጠችም” አይደለም፣ አሊያም እንደ FBC “ሁሉም ነገር በእቅድ የሚመራባት” ወይም እንደ ESAT “ሁሉም ነገር ወደ ጦርነት የሆነባት” ሀገር አይደለችም። እንደው በጥቅሉ ሲታይ፣ ለሚዲያ ፍጆታ ተብሎ የሚለቀቅ መረጃ በአብዛኛው ውሸትና ግነት የበዛበት ስለሆነ እውነታውን በትክክል አያሳይም።

ባለፈው ሳምንት፣ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከከፍተኛ የሀገሪቱ ምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት “መንግስት ዓይኑም፣ ጆሮውም፣ አካሉም በየቦታው መሆኑን በመጠቆም፣ በዚህ የተነሳም ከእናንተ የተሻለ መረጃ አለው” በማለት ተናግረው ነበር። እሳቸው እንዳሉት ከምሁራኑ የተሻለ መረጃ ሊደርሳቸው ይችላል። ነገር ግን፣ ለምሳሌ የባለፈው ዓመትን ምርጫ “100% አሸነፍን” የሚል መረጃ ሲደርሳቸው፣ “አሸነፍን” ሳይሆን “ህዝቡን አፈንን” ብለው ማሰብ ነበረባቸው። ምክንያቱም፣ በወቅቱ በህዝቡ ውስጥ የነበረው፣ ምርጫና አማራጭ በሌለበት የመታፈን ዓይነት ስሜት ነበር። በእርግጥ የሀገሪቱ መሪ ተመሣሣይ ግምት ቢኖራቸው ኖሮ ሀገሪቷ እንዲህ በድንገተኛ የህዝብ ተቃውሞና አመፅ ባልተናጠች ነበር።

እንደተባለው የመንግስት ዓይንና ጆሮና በየቦታው ቢሆንም፣ መንግስት አስተዳደራዊ መዋቅር እንጂ አካል የለውም። ለተቃውሞ አደባባይ ወጥቶ የቀረ፣ የታሰረ፣ አጥንቱ የተሰበረ ልጅ የለውም። መንግስት የተጎጂዎችን ቁጥር ይቆጥራል እንጂ የወላጅ እናት ሰቆቃን አይሳቀቅም። ሰዎች ያደረጉትን ይመለከት፣ የተናገሩትን ያዳምጥ ይሆናል፣ ነገር ግን፣ ተግባሩን ያደረጉበትን፥ ቃሉን የተናገሩበትን ስሜትን አይረዳም። ምክንያቱም፣ መንግስት መዋቅር እንጂ ስሜት የለውም።

እውነቱ በትክክል በሚዲያ ቢነገርም – ባይነገርም፣ ከተናገሩት ይልቅ የሆኑት ይበልጣል። መንግስት ክስተቱን ቢመለከትም – ባይመለከትም፣ ቃላቱን ቢሰማም – ባይሰማም፣…ከህዝብ በላይ እውነቱን አያውቅም። በአጠቃላይ፣ የተመለከቱት፣ የሰሙትና የተናገሩት ከሆኑት አይበልጡም። አሁን ሀገራችን ስላለችበት ሁኔታ ከህዝብ በላይ የሚያውቅ የለም። ስለዚህ፣ የመንግስት ድርሻ መሆን ያለበት ህዝብ በተቃውሞ አደባባይ ሲወጣ “እህ…” ማዳመጥ እንጂ በሃይል ለመቆጣጠር መሞከር የትም አያደርስም። መንግስት ህዝብን እንጂ ህዝብ መንግስትን መፍራት አቁሟል። እነዚህ ወጣቶች በምሬት ወደ አደባባይ የወጡት የነፃነትና ፍትህ ጥማት ከእስር ቤትና ሞት በላይ ስላስፈራቸው እንደሆነ ካወቅን እንቅስቃሴውን በሃይል ለመቆጣጠር መሞከር ከንቱ ድካም ነው።

ከላይ ያነሳሁትን ፅንሰ-ሃሳብ ይበልጥ ተጨባጭ ለማድረግ የእኔን የግል ገጠመኝ እንደ ምሳሌ ለማንሳት ፈለኩ። ጠ/ሚ ኃይለማሪያም እንደ ጠቅላይ ሚኒስተር 29 ሚኒስትሮችንና የ95 ሚሊዮን ህዝብ መሪ ናቸው። እኔ ደግሞ በምሰራበት ዩኒቨርሲቲ የአንድ ዲፓርትመንት ሃላፊ ስሆን የ9 መምህራንና የ350 ተማሪዎች መሪ ነኝ። ታዲያ አንድ ቀን ያጋጠመኝ ነገር “ይቺም ቂ* ሆና ለሁለት ተከፈለች” እንዲሉ፣ ይቺም ስልጣን ሆና ከስራ ባላደረቦቼ ስሜትና ምልከታ ጋረደችኝ አስብሎኛል።

ነገሩ እንዲህ ነው፣ የዲፓርትመንቱ መምህራን ስም ዝርዝር ተዘጋጅቶ በማስታወቂያ ቦርድ ላይ ሲለጠፍ ሁልግዜም 1ኛ ተራ ቁጥር ላይ የሚወጣው የአንድ መምህር ስም ብቻ ነው። እኔ ይህን ፍፁም አላስተዋልኩም፥ አሳስቦኝም አያውቅም ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን ግን፣ ስሙ የሚጠቀሰው መምህር ወደ ቢሮዬ መጣና፤ “ለምንድነው ሁልግዜ የእኔ ስም መጀመሪያ ላይ የሚፃፈው? በሁሉም ነገር ላይ ስሜ 1ኛ ላይ የሚፃፈው እኔ ላይ ምን የተለየ ነገር ስላለ ነው?” አለኝ። ስሙ በ“A” ፊደል የሚጀምር መምህር እሱ ብቻ እንደሆነ ስነግረው ግን በነገሩ ተገርሞ እየሳቀ ወጥቶ ሄደ። ነገሩ በጣም ስላስገረመኝ ሌላ ባልደረባዬን ጠርቼ ጉዳዩን አስተውሎት እንደሆነ ጠየቅኩት። እሱም፣ “በእርግጥ መጀመሪያ ላይ ገርሞኝ ነበር። በኋላ ላይ ግን ስማችንን በፊደል ተራ ቅደም ተከተል ስለምትፅፍን እንደሆነ ገምቼ..ከዚያ በኋላ ብዙም ትኩረት አልሰጠውትም” አለኝ። ነገሩ ይበልጥ አስገረመኝ።

ይቺህ ሚጢጢ ስልጣን እንኳን በአቅሟ የእኔ የ8 ዓመት ባልደረቦች ስለ ሥራዬና አሰራሬ ያላቸውን ስሜትና ምልከታ እንዳያጋሩኝ እንቅፋት ሆናለች። ከዚህ አንፃር ሲታይ እንደ ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ያሉ የሀገር መሪዎች ከሚመሩት ህዝብ የሰማይ ያህል ይርቃሉ። የመንግስት ዓይን፣ ጆሮና አካል ከህዝቡ ጋር እንደሆነ ቢናገሩም፣ እሳቸው እንደ ማንኛውም ሰው፤ ሁለት ዓይን፣ ሁለት ጆሮና አንድ አካል ብቻ ነው ያላቸው። ስለዚህ፣ በአብዛኛው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያውቁት፣ ሚንስትሮቻቸው፥ አማካሪዎቻቸው እና የደህንነት ሰዎች እንዲያውቁ የፈለጉትን ነው። በአጠቃላይ፣ የኢትዮጲያ ህዝብ መሰረታዊ ችግሮች ከጠቅላይ ሚኒስተሩ ዘንድ ሲደርሱ “ቁጥሮች” ናቸው። በመጨረሻም፣ እስከ የመንግስታቸው መውደቂያ ቅፅበት ድረስ ለጠ/ሚ ኃይለማሪያም የማይነገሯቸውን አንድ እውነት በመናገር ፅሁፌን ልቋጭ።

የተከበሩ ጠ/ሚ ሆይ፣ የሚመሩት መንግስትና ድርጅት ኪራይ ሰብሳቢነትን እንደ መልካም እሴት፣ ሙስናንን እንደ ደንብ ተቀብሎ፣ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ የዜጎች መብት መሆኑ ቀርቶ ለጥቂቶች የተፈቀደ ቅንጦት ሆኗል። በተለይ፣ ባለፉት አራት ወራት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል እየታየ ያለው አለመረጋጋትና ውጥረት በመንግስትና በድርጅቱ የአስተዳደር መዋቅር ውስጥ ወሳኝ የሆነ የአመራር ቀውስ ፈጥሯል። ይህ ደግሞ፣ እንደ የድርጅቱና የሀገሪቱ መሪ ዳግም የማያገኙት ምቹ አጋጣሚ ነው። ምክንያቱም፣ እንደዚህ ያለ ቀውስ በድርጅቱና በመንግስታዊ መዋቅሩ ውስጥ ያለውን፤ የኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ትብታብ ለመበጣጠስ፣ በተለይ ረጅሙ የጥቅም ሰንሰለት የታሰረበትን ችካል ከመዋቅሩ ውስጥ ለመንቀል ምቹ አጋጣሚ ፈጥሮልዎታል።

“Crisis is the best opportunity to miss” እንደሚባለው ሁሉ፣ ይሄም ቀውስ ድርጅቱ ኢህአዴግ’ን እና በአጠቃላይ መንግስትን ከፀጉሩ እስከ ጥፍሩ የተበተበውን የኪራይ ሰብሳቢነትና ሙስና ሰንሰለት ለመበጣጠስ፣ በፓርቲ ታማኝነት መስፈርት ተመልምለው የገቡና የጠራ የፖለቲካ አቋም፣ የአመራር ብቃትና ክህሎት የሌላቸውን አመራሮች ለማውረድና በአዲስ ለመተካት፣… ለመልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲ እንቅፋት የሆኑትን በማስወገድ ግልፅና አሳታፊ በማድረግ በአስተዳደር ሥርዓቱ ውስጥ፤ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ የሚያስችል ታሪካዊ አጋጣሚ ነውና ይጠቀሙበት!! የዛሬ 15 ዓመት፣ በ1993 ዓ.ም፣ የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የተፈጠረላቸውን ተመሣሣይ አጋጣሚ ተጠቅመው የኢትዮጲያን ህዳሴ ራዕይና አቅጣጫ ለመቀየስ በቅተዋል። ጠ/ሚ ኃይለማሪያም፣ እርሶዎም የተፈጠረልዎትን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ወደ የኢትዮጲያ ህዳሴ የሚወስደውን መንገድ ይቀይሱ…።

*********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories