የ17 ዓመት ገደማ ወጣት ነው። በወሊሶ ከተማ የገረሱ-ዱኪ የመሰናዶ ት/ት ቤት የ11ኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን ትክክለኛ ስሙን አላውቅም። ስም መያዝ ስለማይሆንልኝ ሁሌ “ቀዮ!” እያልኩ እጠራዋለሁ። እስከ የትምህርት ሰዓት ድረስ ሱቅ ውስጥ ይሰራል። የትምህርት ሰዓት ሲደርስ ታናሽ ወንድሙ ይተካውና እሱ ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳል። ቀዮ ቀልጣፋና ጠንቃቃ ልጅ ነው። ትምህርቱ ላይም ጎበዝ እንደሆነ ታናሽ ወንድሙ ሲያወራ ሰምቻለኹ። ከዕድሜውም ትንሽ ቀደም ብሎ የበሰለ ይመስላል። ዘወትር ከሱቁ በረዳ ላይ ከሚቀመጥ ጎልማሳ ሽማግሌ ጋር ካልሆነ በስተቀር ከእድሜ እኩዮቹ ጋር ሱቁ በረዳ ላይ ተሰባስቦ ሲጫወት አይቼ አላውቅም።  ሰሞኑን ግን ነገሮች አየተለዋወጡ እንደሆነ መታዘብ ይቻላል። ለምሳሌ፣ በፈረቃ ይሰሩ የነበሩት ወንድማማቾች ሁለቱንም በተመሣሣይ ሰዓት ሱቅ አገኛቸው ነበር።

ዛሬም ሱቅ ሄጄ ነበር። ለወትሮው ገና ከሩቅ “ቀዮ” ስል ደስ በሚል ፈገግታ የሚቀበለኝ ልጅ ዛሬ አጠገቡ ቆሜ ስጠራው እንኳን አልሰማኝም። የ17 ዓመት ወጣት ሳይሆን የ71 ዓመት አዛውንት ሽማግሌ ይመስል፣ አገጩን በእጁ መዳፍ አስደግፎ አቀርቅሮ መሬቱን ያያል። በመጀመሪያ የሆነ ነገር በተመስጦ እያየ መስሎኝ ነበር። ከዛ፣ እኔም ወደ መሬት አቀርቅሬ የሆነ የሚንቀሳቀስ ነገር፣ በቃ…ጉንዳን ወይም ሌላ ነገር ፈለግኹ። ምንም እይታ ውስጥ የሚገባ ተንቀሳቃሽ ነገር የለም። ወደ እሱ ዞሬ ስመለከት፣ አሁንም እንደዛው እንደተተከለ ነው። እንደገና በእሱ እይታ አቅጣጫ አቀርቅሬ ማየት ጀመርኩ። ተሞልተው የተጣሉ የሞባይል ካርዶች፣ ተከፍተው የተጣሉ ቆርኪዎች፣ የማስቲካ ሽፋን ልጣጮች፣ የሲጋራ ቁሪዎች፣… ሌላ ምንም የተለየ እይታ የሚስብ ነገር የለም። ነገሩ ገርሞኝ፣ “ቀዮ” ብዬ ስጎነትለው ግዜ፣ ከእንቅልፉ እንደባነነ ሰው ግራ ተጋብቶ ተመለከተኝ? ትንሽ ቆየና “ወይኔ! በቃ ትምህርቴ ከንቱ ሆኖ ሊቀር ነው?” አለኝ። 

“ቀዮ” ላለፉት ሦስት ወራት መልስ ያልተገኘለትን ጥያቄ ነው የጠየቀኝ። በእርግጥ ህዳር 25/2008 ዓ.ም በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ የተጀምሮ፣ ከሳምንቱ ወደ 50ሺህ የሚጠጋ ህዝብ ያሳተፈ ተቃውሞ በወሊሶ ከተማ ከተካሄደ በኋላ መደበኛ የመማር-ማስተማር ሂደት ለተወሰነ ግዜ መቋረጡ የማይቀር ነበር። ለምሳሌ፣ በዚያን ሰሞን ከ2000 የካምፓሱ ተማሪዎች ውስጥ 300 ተማሪዎች ብቻ ቀርተው ነበር። ወዲያው ግን ከተማሪዎቹ ጋር ተከታታይ ውይይት ተደርጎ የ1ኛ ሴሜስተር ትምህርት ተጠናቆ አሁን 2ኛው ሴሜስተር ተጀምሯል። በከተማዋ ባሉት የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። በተለይ፣ ከታህሳስ ወር መጀመሪያ እስካለፈው የየካቲት ወር ድረስ ትምህርት አልነበረም ማለት ይቻላል። የ2ኛ ደረጃና የመሰናዶ ተማሪዎች የ1ኛ ሴሜስተር የማጠቃለያ ፈተና የተቀመጡት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ያልተሳካ ሙከራ ከተደረገ በኋላ ነው።

“ቀዮ” ከትላንት (ሐሙስ) በኋላ በወሊሶ ከተማ በሚገኘው የገረሱ-ዱኪ የመሰናዶ ደረጃ ት/ት ቤት ተማሪዎች “ላነሳናቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ አልተሰጠንም” በሚል ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ወስነዋል።በዚህ ምክንያት አንዳንድ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው መልቀቂያ እያወጡ ወደ ወልቂጤ፣ አዲስ አበባና ሰበታ የመሳሰሉ ከተሞች ሄደው እንዲማሩ እየላኩ እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ። ጉዳዩን ለማጣራት የት/ት ቤቱ መምህር ወደሆነ ጓደኛዬ ጋር ስልክ ደውዬ የነበረ ሲሆን ምላሹ በጣም አስደንጋጭ ነው። ወደ 500 የሚጠጉ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች በራሳቸው ግዜ ተሰብስበው “መስከረም 3/2009 እንገናኝ!” በማለት የዚህ ዓመት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ እንደወሰኑ ነግሮኛል። በተመሣሣይ፣ በወሊሶ ዙሪያ ካሉት ውስጥ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሦስት ት/ት ቤቶች ተቆጣጣሪ ወደ ሆነ ግለሰብ ደውዬ የነበረ ሲሆን፣ እስካሁን በ1ኛ ደረጃ ት/ት ቤቶች ትምህርት እንዳልተቋረጠ፣ ሆኖም ግን የመሰናዶና የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎች አቋርጠው ከተመለሱ እዚህም ተመሣሣይ ችግር ሊከሰት እንደሚችል ገልፆልኛል።

በቴክኒክና ሞያ እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የመማር-ማስተማሩ ከሞላ-ጎደል እየተካሄደ ነው። ሆኖም ግን፣ ለምሳሌ፡-ከአንድ ወር በፊት አከባቢ በወሊሶ ፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ የመማሪያ ክፍል ውስጥ ቦንብ (ወይም ቤት ውስጥ የተሰራ ፈንጂ) ፈንድቶ በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል። በተመሣሣይ፣ ከሁለት ሳምንት በፊት በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የወሊሶ ካምፓስ እና በፖሊ-ቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር-ግቢ ፊት-ለፊት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለመጀመር ሙከራ ተደርጎ ነበር። በቀናት ልዩነት ውስጥ በካምፓሱ ቅጥር ግቢ በሚገኘው ደረቅ የሳር-ድርቆሽ ባልታወቁ ግለሰቦች በእሳት ተለኩሷል። እነዚህና የመሳሰሉ ክስተቶች በተጠቀሱት ተቋማትም ቢሆን ሁኔታው አስተማማኝ እንዳልሆነ ያሳያል።

ከላይ በዝርዝር ለመግለፅ የሞከርኩት በዋናነት እንደ አንድ የወሊሶ ከተማ ነዋሪ፣ በከተማዋና በዙሪያዋ ስላለው ሁኔታ ነው። በሌሎች ቦታዎች ስላለው ሁኔታ በግሌ መታዘብ እና መረጃ ማሰባሰብ ሊያዳግተኝ ቢችልም፣ በተለያዩ የምዕራብ ሸዋ፣ አርሲና ሐረርጌ ከተሞች ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳለ መገመት ይቻላል። እርግጥ ነው። በአጠቃላይ፣ ሁኔታው በክልሉ ለተነሳው የህዝብ ተቃውሞ ከሚመለከታቸው አካላት ተገቢው ትኩረትና ምላሽ እንዳልተሰጠው የሚያሳይ ነው።

በእርግጥ ሁሉም ባለ-ድርሻ አካላት ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በሚያስችል መልኩ ተንቀሳቅሰዋል ማለት አይቻልም። የችግሩ መንስዔው በዋናነት ከመልካም አስተዳደር እጦት ጋር ተያይዞ በህዝቡ ውስጥ የተፈጠረ ብሶት እንደሆነ ተገልጿል። በተመሣሣይ፣ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚቻለውም የችግሩን መንስዔ በመለየት አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃ ሲወሰድ ነው።

መንግስት እንደ ወሊሶ ባሉ የክልሉ ከተሞች በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት በተከሰተው ያለመረጋጋት ምክንያት በሕይወትና ንብረት ላይ ለደረሰው ጉዳት ይቅርታ ጠይቋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ እንደ “ቀዮ” ያሉ የአከባቢው ወጣቶች ላለፉት ሦስት ወራት ትምህርታቸውን በሚገባ ሳይማሩ ቀርተዋል። በወቅቱ የነበረው አለመረጋጋት እንዳለ ሆኖ፣ የመማር-ማስተማር ሂደቱ እስካሁን ተቋርጦ የቆየው፤ በተለይ የ2ኛ እና የመሰናዶ ደረጃ ተማሪዎች “ጓደኞቻችን፣ አስተማሪዎቻችን፣ እንዲሁም ቤተሰቦቻችን ያላግባብ በጥይት ተገድለዋል፣ በሃይል ተደብድበዋል፣ በጅምላ ታስረዋል፣ …በዚህ ላይ መንግስት አስቸኳይ ምላሽ ይስጠን?” የሚል ጥያቄ አቅርበው የነበረ መሆኑና፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ከሚመለከተው አካል ተገቢውን ምላሽ ሳያገኙ በመቅረታቸው ነው።

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ፣ በወሊሶ ከተማ የሚገኙ የ2ኛና የመሰናዶ ደረጃ ተማሪዎች የዘንድሮን የትምህርት ዘመን ላለመማርና በቀጣዩ አመት መስከረም 03/2009 ዓ.ም ለመገናኘት ወስነዋል። በእርግጥ፣ መንግስት ችግሩን ተቀብሎ በአስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ ባለመውሰዱ ምክንያት፣ የእነዚህ ልጆች የትምህርት ዕድል እንዲህ በከንቱ ሲባክን ማየት በጣም ያሳዝናል። አሁንም ቢሆን ለመፍትሄ ግዜው አልረፈደም። በተለያየ ደረጃ ያሉ የመንግስት አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው፤ ከተማሪዎች፣ መምህራን፣ የተማሪ ቤተሰቦች እና ሌሎች ባለ-ድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል። 

በመጨረሻም፣ ከሦስትና አራት ወራት በፊት የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን መነሻ በማድረግ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲነሳ መንግስት “ፀረ-ዴሞክራሲ እና የመልካም አስተዳደር እንቅፋት” (farra dimokarsiin fi fara bulchisa gaarii) በሚል የኃይል እርምጃ ተወሰደ። ትላንትና መንግስት “ፀረ..” እያለ በሃይል ለመደምሰስ የሞከረውን ጥያቄ፤ ከ200 በላይ ሰዎች ከተገደሉና በሺህዎች የሚቆጠሩ ከታሰሩ በኋላ “ጥያቄው ዴሞክራሲያዊ ነው… ችግሩም በመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት የተፈጠረ ነው” ለማለት በቃ። ምላሽ አሰጣጡ ‘የህዝቡ ጥያቄ አግባብነት በሞተው ሰው ብዛትና በጠፋው ንብረት መጠን’ የሚመዘን ይመስላል።    
ዛሬ’ስ፣ ከቃል “ይቅርታ!” ባለፈ፤ በግፍ ለተገደሉና ለተጎዱ ተገቢውን ካሣ እንዲከፍል፤ በጅምላ የታሰሩትን እንዲፈታ፣… ስንት ህፃናትና ወጣቶች የትምህርት ዕድላቸውን “መሰዋዕት” ማድረግ አለባቸው?

************

8.552567237.9835033
Seyoum Teshome

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago