ክቡር ጠ/ሚ ኃይለማሪያም ደሳለኝ በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ ከምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት የተነሱት ጥያቄዎችና የጠ/ሚ ምላሽ አሰጣጥ ከወትሮው ትንሽ ለየት ያለ መሰለኝ። ለነገሩ፣ “ከምሁራን ጋር ውይይት ሊያደርጉ ነው” ሲባል፤ “Who are these ’ምሁራን’?” ብዬ፣ በ’ከማን-አንሼ’ ትዕቢት ተወጥሬ ነበር። በውይይት መድረኩ የተሳተፉትን ሰዎች  ስመለከት ግን ትዕቢቴ ልክ በመርፌ እንደተወጋ ፊኛ ተነፈሰ።

ተሳታፊዎቹን ስመለከት የሀገሪቱ ታዋቂ ምሁራኖች፣ የዩኒቨርሲቲ ፕረዘዳንቶች እና እኔንም ያስተማሩኝ መምህራን ጭምር ናቸው። እኔ የምሰራበት ዩኒቨርሲቲ ፕረዘዳንት ሳይቀር በአዳራሹ የመጀመሪያ ረድፍ ተቀምጠዋል። ታዲያ እኔ ከእነዚህ ሰዎች እኩል ተቀምጬ በመድረኩ ብሳተፍ “የማያድግ ጥጃ ከበሬ ፊት ሣር ይግጣል!” ያስብላል። ከዚያ ይልቅ፣ በውይይት መድረኩ የመሳተፍ እድል ቢኖረኝ ኖሮ ለጠ/ሚ ሃይለማሪያም የማቀርባቸውን ጥያቄዎች አሰብኳቸው። በመድረኩ የተነሱትን ጥያቄዎችና ምላሾች ለመዳሰስ የተወሰነ ጥረት ካደረኩ በኋላ፣ “አጠር-አጠር አድርገኽ” የሚል በሌለበት፣ በውይይት መድረኩ ያልተጋበዙትን ምሁራን በራሴ ፍቃድ ወክዬ ጥያቄን  እንደሚከተለው አቀርባለሁ።

በእርግጥ ምሁራኑ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የብዙ ዓመት ልምድና ቆይታ ያላቸው ናቸው። እኔ የተማርኩባቸውን መፅሃፍት የፃፉ፣ ለምሳሌ እንደ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ያሉ ሰዎች ያሉበት ነው።  እነሱ ከ15-20 ዓመት በፊት በመምህርነትና ተመራማሪነት ሲሰሩ የነበሩ፤ የመመረቂያ ፅሁፋቸውን በመጀመሪያ ወረቀት ላይ ፅፈው ከዛ በታይፕ ያስመቱ ናቸው። የአሁኑ ትውልድ ግን መጀመሪያ ኮምፒውተር ላይ ከፃፈ በኋላ ነው ወደ ወረቀት የሚገለብጠው።

የሀገራችን የኢንተርኔትና ሞባይል አገልግሎት ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ፤ ከ1990 – 2000 ዓ.ም ድረስ በአብዛኛው እንደ መገናኛ መሣሪያ ሆነው ሲያገለግሉ የነበረ ሲሆን ከ2000 ዓ.ም በኋላ ግን ከመገናኛነት መሣሪያነት አልፈው በራሳቸው “የውይይት መድረክ” (Discussion Forum) ለመሆን በቅተዋል። ይህ በዋናነት ከማህበራዊ ድረገፆች (social networking sites) መምጣት ጋር የተያያዘ ነው። ነገር ግን፣ አብዛኛቹ በውይይት መድረኩ የተሳተፉ ምሁራን፣ ለምሳሌ “የመልዕክት ሳጥን” ሲባሉ ቀድሞ ወደ ሃሳባቸው የሚመጣው “P.O.Box”፣ አሊያም ደግሞ “E-mail Inbox” እንጂ “Facebook Inbox” እንዳልሆነ መታዘብ ይቻላል።

እንደ ኢትዮጲያ የዳበረ አቅምና ተደራሽነት፣ እንዲሁም ነፃና ገለልተኛ የሆነ ሚዲያ በሌለበት ሀገር የማህበራዊ ድረገፆች ሚና እጅግ ወሳኝ እየሆነ ነው። ነገር ግን፣ አብዛኞቹ ከጠ/ሚ ሃይለማሪያም ጋር በተደረገው ውይይት ተሳታፊ የነበሩት ምሁራን የዘመኑን ቴክኖሎጂ ለሥራ ካልሆነ በስተቀር፣ እንደ ፌስቡክ (facebook) እና ቲዊተር (twitter) ያሉ ማህበራዊ ገፆችን ለመጠቀም፣ እንዲሁም የራሳቸውን የጦማር ገፅ (blog) ከፍተው በሀገራችን ፖለቲካና ታሪክ ዙሪያ ሞያዊ ትንታኔ ለመስጠት ሲጠቀሟቸው ማየት የተለመደ አይደለም።

ክቡር ጠ/ሚ፣ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር፣ ማህበራዊ ድረገፆች ሀገራዊ መግባባትን ሆነ መለያየትን ለመስበክ፣ ታሪክን ለማስገንዘብ ሆነ ለማዛባት ከመደበኞቹ የህትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በተሻለ ምቹና ተደራሽ መድረክ ለመሆን በቅተዋል። ከእርስዎ ጋር ለመወያየት ከተጋበዙት ምሁራን ውስጥ አብዛኞቹ በማህበራዊ ደረገፆች ላይ ንቁ ተሳትፎ አያደርጉም። እነዚህ፣ መልዕክትን በፖስታ ሳጣን፣ የውይይት ሃሳብን በወረቀት ሲልኩ የነበሩ ሰዎች፣ የሃሳብ ብዙሃነትን ከማዳበር አንፃር የሚጠበቅባቸውን እንዳይወጡ የሚያግድ ሌላም የታሪክ ጠባሳ አለባቸው። ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም በተጨማሪ በደርግ የቀይ-ሽብር እሳት የተጠበሱና እስካሁን ድረስ ጠባሳውን እያዩ የሚፈሩ፣ “ፖለቲካ እሳት ነው” እያሉ ጠባሳውን እያሳዩ የሚያስፈራሩ ናቸው።

የደርግ አገዛዝ ሲወድቅ እኔ የ2ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩ። በወቅቱ ስለነበረው ጭቆና ከምናባዊ እሳቤ ባለፈ በተግባር አላውቅም። ከ2ኛ – 12ኛ ክፍል፣ ቀጥሎም በዩኒቨርሲቲ ተማሪነትና አስተማሪነት፤ ስለ ደርግ አምባገነናዊነት እና ጨቋኝነት፣ ስለ ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብት መከበር፣ ስለ ሕገ መንግስታዊ ሥረዓትና የሕግ-የበላይነት ተምሬያለሁ፥ አስተምሬያለሁ። ስለ ኢትዮጲያ በምናብ የማስበውን እንጂ በእውን የተገነዘብኩትን በነፃነት የመናገርና መፃፍ መብት የለኝም። ሌላው ቀርቶ፣ አንድ የሕግ ባለሞያ “ሕገ-መንግስቱ ሊሻሻል ይገባል” በማለቱ፣ በአንድ ወይም ሁለት ባለስልጣናት ሳይሆን፣ በሀገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት እንደ ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ግድፈት ተወስዶ ከሥራ ሲባረር እያየሁ፣ እንደ ሥርዓት “የሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱ ትርጉም ፋይዳ ምንድነው?” የሚል ጥያቄ እንዳነሳ ያደርገኛል። ይህ ልክ እንደ ቀድሞው ትውልድ ሁሉ፣ አዲሱ’ም ትውልድን በፍርሃት ቆፈን ውስጥ እንዲወድቅ ያደረገው ይመስለኛል።

ማህበራዊ ድረገፆች ዋና የውይይት መድረኮች እየሆኑ መምጣታቸውንና አብዛኞቹ የሀገሪቱ ምሁራን ደግሞ በእነዚህ መድረኮች በንቃት የመሳተፍ ልማድና ተሞክሮ እንደሌላቸው አይተናል። ነገር ግን፣ ሀገራዊ መግባባት እንዲሰፍን፣ የሃሳብ ብዙሃነት እንዲዳብር የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን (Political elites) በተለያዩ የውይይት መድረኮች ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን፣ ወቅታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካ አጀንዳዎች እና ታሪካዊ ውይይቶች በዋናነት የሚመሩት በተቃራኒ ፅንፍ (ጠርዝ) ላይ የቆሙ፣ በብሔርተኝነት እና አንድነት ፅንፈኛ ሃይሎች ናቸው። እነዚህ አካላት በጥቅሉ ጭፍን ደጋፊዎች ወይም ጭፍን ተቃዋሚዎች ናቸው። 

ፅንፈኝነት አንድን እምነትና አመለካከት ያለ በቂ ምክንያታዊ ግንዛቤ በጭፍን መቀበልና ማራመድ፣ ብሎም በሌሎች ላይ ለመጫን ጥረት ማድረግ ነው። ፅንፈኝነት የሕብረተሰቡ የጋራ የሆኑትን ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን መጠጊያና መሸሸጊያ አድርጎ የሚያድግ ቢሆንም፣ የፅንፈኝነት መሰረታዊ ምንጩ አንድና አንድ ነው፣ “ጭፍን አገልጋይነት” (Unquestioned Servitude)። የሀገሪቱን የፖለቲካ መድረክ፣ በተለይ በማህበራዊ ድረገፆች ላይ ቀዳሚውን ድርሻ የያዙት የብሔርተኝነት እና የአንድነት ፅንፈኞች ሁለቱም ለሚያራምዱት አክራሪ የሆነ የፖለቲካ አመለካከት ጭፍን አገልጋዮች ናቸው።

የብሔርተኝነት እና የአንድነት ፅንፈኛ ሃይሎች በዘረኝነትና ጥላቻ የታጨቁ ቃላት ሁለት ተቃራኒ ጥጎች ላይ ቆመው ከመወራወር ባለፈ፣ ብሔራዊ መግባባት ለማስፈን ወይም የሃሳብ ብዙሃነትን ለማዳበር ሲሰሩ አይታይም። በእርግጥ ሁለቱም የአንድ ሣንቲም ሁለት ገፅታዎች ናቸው፣ በአንድ ቦታና ግዜ ላይ ቆመው ወደ ተለያዬ አቅጣጫዎች የሚመለከቱ። ሁለቱም ስለአንድ ሀገር ህዝብና ታሪክ እያወሩ እርስ-በእርስ ግን የማይደማመጡ ናቸው።

የሀገሪቱ ምሁራን ዋና ድርሻ የነበረው ይህ ነበር፤ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ እና ታሪካዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ በመሳተፍና በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ ትንታኔ መስጠት፣ በዚህም አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል ከፅንፈኛ ሃይሎች እሳቤና አስተሳሰብ ነፃ ማውጣት ነው። የሃሳብ ብዙሃነት የሚዳብረው፣ ፅንፈኞችን በማስወገድ ሳይሆን በተጨባጭ ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ በመፍጠር፣ የሕብረተሰቡን የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና በማጎልበት ነው።

ክቡር ጠ/ሚ፣ ከእርስዎ ጋር ለመወያየት እድሉ ያልገጠመን ምሁራን መጠየቅ የምንፈልጋቸው ጥያቄዎች፤ በራሱ የማሰብ፥ የመናገርና የመፃፍ መብት የሌለው ምሁር የማህብረሰብን ግንዛቤ ለማዳበር እንዴት ብቁ ሊሆን ይችላል?  ከምክንያታዊነት ይልቅ ጭፍን ታማኝነትን በሚሸልምበት ሥርዓት ውስጥ የምሁር ድርሻ ከቶ ምንድነው? የሀገሪቱ ምሁራን፤ ግማሹ ካለፈ ጠባሳው ያላገገሙ፣ የተቀረው በፍርሃት ቆፈን የተለጎሙ ሆነው ሳሉ እንዴት ስለ ብሔራዊ መግባባት ማስተማር ይቻላቸዋል? የፖለቲካ መድረኩ፣ ከዕውቀት ይልቅ ጥላቻና ዘረኝነት በሚዘምሩ ድቀ-መዛሙርት ቁጥጥር ስር ውሎ እንዴት የሃሳብ ብዙሃነትን ማዳበር ይችላል?

***********

Seyoum Teshome

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

Recent Posts

ኪዳነ ኣመነ – እንደህዝብ አንድ ሆነናል ያስቸገረን የህወሓት አስተሳሰብ ነው

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 2 - ለውጥ…

5 years ago

ኪዳነ አመነ – ለትግራይ ታላቅነት ሼምለስ ሆነን እንሰራለን

ከብሔራዊ ባይቶ ኣባይ ትግራይ (ባይቶና) አመራር ኪዳነ አመነ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ ክፍል 1 - ለትግራይ…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ትዴት ኢትዮጲያዊ ማንነት ብቻ እንዳለ ነው የሚያምነው (video)

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለመጠይቅ (ክፍል 2)- ስለትዴት…

5 years ago

መኮንን ዘለለው – ኢሳት የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ ነው የሰራው (Video)u

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) አመራር መኮንን ዘለለው ከሆርን አፌይርስ ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ (ክፍል 1) -…

5 years ago

የበረከት ስምዖንና ታደሰ ካሳ መታሰር -ሕጋዊ ወይስ ፖለቲካዊ እርምጃ?

(የማነ ካሣ) እንደሚታወቀው አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ ታደሰ ካሳ (ጥንቅሹ) ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ…

5 years ago

ኣስተያየት በ’ኣብራክ’ ልብወለድ ድርሰት ላይ

(መርስዔ ኪዳን - ሚኔሶታ) ኣብራክ የተባለውን የሙሉጌታ ኣረጋዊ መጽሓፍ ኣነበብኩት። ኣገራችን ከሊቅ አስከደቂቅ በዘውጌ ብሄርተኝነት…

5 years ago