የኢቢሲን የ50 አመታት ታሪክ ዘካሪ ዘገባዎችን እንደታዘብኳቸው

የትናንቱ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የዛሬው ኢቢሲ እነሆ 50 አመት ሞላው፡፡ ይህ አንድ ለእናቱ የሆነ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለፉት 50 አመታት ያለፈባቸውን ውጣ ውረዶችና የታሪክ ምዕራፎች መለስ እያለ እያስቃኘን ይገኛል፡፡ ያለፈውን መዘከር ለመጭው ትልቅ ስንቅ ብሎም ቆንጆ መስፈንጠሪያ ስለሚሆን ኢቢሲ ይሄንን ማድረጉ መልካም ነው እላለሁ፡፡

ይሁንና በዚህ ምልሰቱ ውስጥ ከጋዜጠኞቹ አሊያም ከኤዲተሮቹ ወይም ከሌላ ምክንያት የተነሳ እየተገደፉ ያሉ እንከኖች አልታጡም፡፡ ለአብነት ያህል ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ ባለፉት 50 አመታት ኢትዮጵያን የጎበኙ የተለያየዩ አገራት መሪዎች መኖራቸውን ይጠቅስና በዋናነትም በማለት ጋዜጠኛው በዘገባው በኢህአዴግ ዘመን ብቻ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ እንደ ቶኒ ብሌር አይነት መሪዎችን አስታውሶናል፡፡

በዚህ ዘገባ ላይ ያለኝ ትዝብት በአጠቃላይ በምልሰት ፕሮግራሞች ላይ እየታየ ያለ ነው፡፡ በንጉሱ ዘመን ኢትዮጵያን የጎበኘ የሌላ አገር መሪ የለም? በመንግሰቱ ዘመንስ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ እንደ ፊደል ካስትሮ አይነት መሪዎች አልነበሩምን? የእኛ መሪዎችስ ወደ ሌሎች አገራት አልሄዱም? ኢቲቪስ አብሮ አልተጓዘም? መልሱ ግልጽ ነው፡፡ ታዲያ ዘገባው ምን ሆኖ በኢህአዴግ ዘመን ብቻ የመጡ መሪዎችን ለማሳየት ቻለ? እነሱም ቢሆኑ በቅጡ አልተዘገቡም፡፡ የመጨረሻውን የኦባን ጉብኝት እንኳን ያላካተተ ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ያነሳ ፍጹም ባዶ ዘገባ ነበር፡፡

Image - Ethiopian Broadcasting Corporation 50th anniversary

በመሰረቱ የዚህ አይነት ዘገባ ዜና ተብሎ መቅረቡ በራሱ ትክክል አልነበረም፡፡ ምክንያቱም የዜና ባህሪያት የሌሉት የዶክመንተሪ አይነት ዘገባ ነው፡፡ ምናልባት ያ ዘገባ በዘጋቢ ፊልም መልኩ ታስቦበት ቢሰራ ወይንም በመዝናኛ ፕሮግራም በዝንቅ መልክ ቢቀርብ ይበልጥ አዋጭ ይሆን ነበር፡፡ ስለዚህ ተመሰሳይ ዘገባዎች ሲቀርቡ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል እላለሁ፡፡

ከዚህ ውጭ ልክ አሁን የአገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ኢህአዴግ ወይንም መንግስት የነካው ሁሉ መልካም ነገርም ቢሆንም እንትን የነካው እንጨት በማስመስል ዘላለም አለማቸውን እያንቋሸሹ እንዳሉት ሁሉ ኢቢሲም ከኢህአዴግ በፊት በነበሩት መንግስታት የተሰሩ መልካም ነገሮችን በምልሰት ፕሮግራሙ ለማሳየት ተስኖታል፡፡ ለምን? አንድ አባባል አለ “እናቴን ያገባ ሁሉ አባቴ ነው” የሚል፡፡ እንደተረቱ ሁሉ ኢትዮጵያን ያስተዳደረ ሁሉ መንግስት ነው! መንግስት የሆነ ሁሉ የእኛም መንግስት የኢቢሲም መንግስት ነው፡፡ ስለዚህ የታሪክ ምልሰቱ እነሱንም ይመለከታል ማለት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ አመክንዮ የሚቀርብ ከሆነ ኢቢሲ ገለልተኛነቱ በግልጽ ጥያቄ ውስጥ ይወድቃል፡፡ በዚህ አካሄድ ደግሞ ነገ ኢህአደግ ከስልጣን ዞር ሲል ኢቢሲ ዛሬ የሚዘግበውን መልካም ነገር ሁሉ በወዲያኛው 50 አመቱ ላይ ላያስታውሰው ነው ማለት ነው፡፡

“የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ” እንዳለ ከያኔው፣ ኢቢሰ በቀሩት ጥቂት ቀናት ቢያንስ በጥቂቱም ቢሆን ያለፉትን መንግስታት መልካም ስራዎች ለህዘቡ ያሳይ፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኞቹ በሚሰሯቸው የምልሰት ፕሮግራሞች ላይ አንዳንድ ስህተቶችን በድፍረት ወይንም በእንዝላልነት ሲፈጽሙ ታዝቤያለሁ፡፡ ለአብነት ያህል እሁድ እለት ማታ በቀረበው አንድ ዘገባ ላይ ጋዜጠኛው እንዲህ ሲል ጮክ ብሎ አንብቦልናል፡፡ ግብፅና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የተነሳ ባለፉት ሰባት ሺህ አመታት ግንኙነታቸውን መስርተው ቆይተዋል፡፡ (ቃል በቃል የተጻፉ አይደለም)

ልብ ይበሉ “ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የሶስት ሺ አመት ታሪክ ያላት ናት፣ አይደለም የ300 አመት ነው ታሪኳ የሚለው ክርክር መሬት ላይ ወርዶ ገና ባልሰከነበት አገር ጋዜጠኛው ኢትዮጵያን የሰባት ሺህ አመት ታሪክ ባለቤት አድርጓት ሌላ የክርክር ሀሳብ ጨምሯል፡፡

እዚህ ላይ የቱ ነው ትክክል? ወደሚል ሌላ የታሪክ ክርክር ውስጥ መግባት አልፈልግም፡፡ ነገር ግን የራሱ የኢቢሲ ስራ አስኪያጅ የነበሩት የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ኢትዮጵያ የ300 አመት ታሪክ ብቻ ነው ያላት እያሉ ስልጠና እንደሰጡ አስታውሳለሁ፡፡ እንግዲህ እኝህ ሰው ይመሩት የነበረው ቤት ጋዜጠኛ በዜናው ላይ ኢትዮጵያን የሰባት ሺህ አመት ባለጸጋ ማድረጉን እንዴት እንቀበለው?  

ለማንኛውም የዚህ አይነቱን ጉዳይ ልብ ማለት ያስፈልጋል ለማለት ነው እንጂ የኢቢሲ ጋዜጠኞች የመላዕክት ስብስብ ናቸው አይሳሳቱም ለማለት አይደለም፡፡ ሰዎች ናቸው ይሳሳታሉ፡፡

በአጠቃላይ ግን የኢቢሲ የምልሰት ዘገባዎች ፍጹም 50 አመት 50 አመት ሊሸቱኝ አልቻሉም፡፡ እኔ ኢቢሲን የማውቀው በኢህአዴግ ዘመን ነው፡፡ አሁን በምልሰት ዘገባዎቹ እያየሁ ያለሁትም በአብዛኛው የ25 አመት ታሪኩን ነው፡፡ ከ50 አመት እድሜው ውስጥ ወደዚህኛው መንግስት ያለው ዘመን አመዝኖ ነው እንዳይባል ዘመኑ እኩል ነው፡፡ እኩል ያልሆነው የጋዜጠኞቹ እይታ ይመስለኛል፡፡ ስለሆነም የታሪክ አንካሳ፣ የታሪክም ሸውራራ የለምና መለስ ተብሎ ታሪክ ሲዘከር መስፈርቱ መሆን ያለበት የጉዳዩ ክብደት እንጂ የታሪኩ ለመንግስት ያለው ቅርበት መሆን የለበትም፡፡

አዲስ ዘመኖንም በቀጣይ 75ኛ አመቱን በማክበሪያ ዋዜማ ላይ ነው፡፡ እነሱም ይሄን የኢቢሲን ስህተት እንደማይደግሙት እምነቴ ነው፡፡ “ብልህ ከሰው ሞኝ ከራሱ ይማራል” አይደል ብሂሉ እነሱም የኢቢሲን ስህተት ቁጭ ብለው ከደገሙት ሌላ ስህተት መሆኑ አይቀርም፡፡ አበቃሁ!
*************

Areaya Getachew (MA) is a public relations expert at a foreign embassy. He studied second degree at Addis Ababa University and was deputy editor in-chief of Addis Zemen newspaper.

more recommended stories