ሰማያዊ ፓርቲ:- ነፃነት የማያውቅ አመራር ነፃ መሪዎችን ሲያባርር!

የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጥር 06/2008  ዓ.ም ባወጣው ዘገባ መሰረት “ሰማያዊ ፓርቲ አራት የምክር ቤት አባላቱን አባረረ” የሚለው ዜና በጣም አስገርሞኛል፡፡ የፓሪቲው የሥነ-ስርዓት ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ፣ አራት የምክር ቤት አባላት “የታሪክና የጎሣ ጥላቻ የሚቀሰቅስ፣ የኢትዮጲያን ህዝብና የተለያዩ የሀገራችንን መንግስታት ታሪኮች የሚያጎደፍ፣…” በአጠቃላይ ከፋፋይነት ያላቸው ፅሁፎችን በማህበራዊ ድረገፅ ላይ በማሰራጨታቸው፣ በከፍተኛ የሥነ-ስርዓት ጥሰት ክስ እንደተመሰረተባቸውና በዚህም ምክንያት ከፓርቲው መባረራቸውን ጠቅሷል፡፡  በተለይ “ከፍተኛ የሥነ-ስርዓት ጥሰት” በሚል የቀረበው ምክንያት ከማስገረምም አልፎ አስደንጋጭ ነው፡፡

አዲስ አድማስ በቀጣይ እትሙ ጥር 14/2008 ዓ.ም ይዞት በወጣው ዘገባ መሰረት ደግሞ፤ የፓርቲው የሥነ-ስርዓት ኮሚቴና የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን በአንድ ወገን፣ የፓርቲው ሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ በሌላ ወገን ሆነው አንዱ-ሌላውን “በህገ-ወጥነት” ይወነጅላል። እርግጥ በአዲስ አድማስ ላይ የተጠቀሰ ነገር ባይኖርም፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢ/ር ይልቃል ጌትነት “ውሳኔው ከፓርቲው መሰረታዊ ሃሳቦችና እምነቶች ተቃርኖ የተላለፈ ስለሆነ ተቀባይነት የለውም” በማለት ውሳኔው በፓርቲው የሥራ-አስፈፃሚ በኩል ተቀባይነት እንደሌለው በነገረ-የኢትዮጲያ ድረገፅ ላይ የሰጡትን አስተያየት አንብቤያለሁ፡፡ ይህም ቢሆን በቂ የሆነ ምላሽ ነው ለማለት አይቻልም፡፡

እዚህ ጋር መነሳት ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ፤ ስለ የሥነ-ስርዓት ኮሚቴው የአካሄድ ትክክለኝነት (“ኮረም” ያለመሟላት) ሳይሆን ስለክሱ አግባብነት ነው። ውሳኔው ከፓርቲው መሰረታዊ ሃሳቦችና እምነቶች ተቃርኖ የተላለፈ ብቻ ሳይሆን የአባላቱን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የገፈፈ፣ ፓርቲው የቆመላቸውን መሰረታዊ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች የጣሰና፣ ሰማያዊ ፓርቲ በህዝቡ ዘንድ ያለውን አመኔታ የሚያሳጣ ተግባር እንደሆነ በደንብ ሊሰመርበት ይገባል፡፡

እኔ እንደሚመስለኝ “ታሪክ አጉዳፊና ከፋፋይ” ለሚለው ክስ ዋና መነሻ የሆነው ፅሁፍ የፓርቲው የቀድሞው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ “ስለጎንደር ሲዘፈን ልቡ የሚሞቅ አንዳንድ የከተማ ሰው – ስለኦሮሞ ሲዘፈን ለምን ውስጡ እንደሚረበሽ አይገባኝም፡፡ … እንዲህ ያለ ሰው ስለ አንድነት ሲያወራኝ ውሰጤን ሬት ሬት ይለዋል…” በሚል በማህበራዊ ድረገፅ ላይ ያወጣው ፅሁፍ ነው።  ስለፅሁፉ ይዘት ያለኝን የግል ምልከታ ወደኋላ እመለስበታለሁ፡፡ ከዚያ በፊት ግን፣ በአራቱ የፓርቲው አባላት ላይ የተወሰደው እርምጃ አግባብነት በተወሰነ ደረጃ ለማየት እንሞክር።

አንድ የምክር ቤት አባል የተጠቀሰውን ዓይነት ፅሁፍ በማህበራዊ ድረገፅ ላይ ስላወጣና ሌሎች የተወሰኑ የምክር ቤት አባላት ደግሞ ሃሳቡን በተመሣሣይ መድረክ ማንፀባረቃቸው ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት በምን መልኩ አሳሳቢ ሊሆን ይችላል? ምን ያህልስ አሳሳቢ ቢሆን ነው በተግባሩ “በከፍተኛ የሥነ-ስርዓት ጥሰት” ሊያስከስስ የሚችለው? የምክር ቤት አባላትን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት የሚገድብ የፖለቲካ ድርጅት’ስ እንዴት ሆኖ “ለአትዮጲያ ህዝብ ነፃነት እታገላለሁ” ማለት ይችላል?

በመሰረቱ ሰው ምክንያታዊ ፍጡር ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ሰው የራሱ የሆነ አስተሳሰብና አመለካክት፣ ሃሳብና ግንዛቤ ይኖረዋል፡፡ በተመሣሣይ፣ እያንዳንዱ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የራሱ የፖለቲካ ግንዛቤና አመለካከት አለው፡፡ ይህን የተለየ ግንዛቤና አመለካከት ያለምንም ውጫዊ ተፅዕኖ በነፃነት የመግለፅ ተፈጥሯዊ መብት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ፣ ሰማያዊ ፓርቲ በጣም ብዙ አይነት የባህል፣ ስነ-ልቦና፣ የሞራል እሴት፣ ኑሮና አኗኗር ልዩነት ያለባት ኢትዮጲያን ቀርቶ፣ በአባላቱ መካከል ያለውን የግንዛቤና አመለካከት ልዩነት ለማስተናገድ ተስኖታል፡፡ በመሆኑም፣ የተወሰኑ የፓርቲው አመራር አባላት፣ በተለይ በሥነ-ስርዓት ኮሚቴው እና የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን አመራሮች ስለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ምንም ግንዛቤ ያላቸው አይመስለኝም፡፡

ማንኛውም ግለሰብ በማህበራዊ ድረገፆች አማካኝነት የተፈጠረውን ሃሳብን በነፃነት የመግለፅና በዚያውም ከብዙ ሰዎች ጋር የመወያየት መልካም እድል ለመጠቀም ሲል የተለያዩ ይዘት ያላቸው ፅሁፎችን ያወጣል፡፡ ፀኃፊው የፅሁፉን ይዘት፤ አውቆት ወይም መስሎት ወይም ደግሞ በስህተት ሊፅፈው ይችላል፡፡ ስለሚያውቀው ነገር ከፃፈ እውቀቱን እንጋራለን፣ ስለመሰለው ብቻ ከፃፈ መስሎት የነበረው ነገር እውነት ወይም ውሽት ስለመሆኑ ለማስረዳት፣ እንዲሁም በስህተት ፅፎት ከነበረ ደግሞ ስህተቱን ለማሳወቅ እድል ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ፣ በማህበራዊ ድረገፅ ሆነ በሌሎች መገናኛ ብዙሃን ስንፅፍ ሆነ ስንናገር፤ እናስተምራለን፣ እንማማራለን፣ እንማራለን፡፡

Photo - Yonathan Tesfaye Regassa facebook post Sept. 2015
Photo –  facebook post Sept. 2015

በመጨረሻም፤ “ስለ ጎንደር ሲዘፈን ልቡ የሚሞቅ አንዳንድ የከተማ ሰው – ስለኦሮሞ ሲዘፈን ለምን ውስጡ እንደሚረበሽ አይገባኝም፡፡ … እንዲህ ያለ ሰው ስለ አንድነት ሲያወራኝ ውሰጤን ሬት ሬት ይለዋል…” የሚለውን የአቶ ዮናታን ተስፋዬን ፅሁፉን እንደማሳያ በመውሰድ ስለሃሳቡ አጭር ነገር በማለት ፅሁፌን እቋጫለሁ፡፡

በቅድሚያ፣ የኢትዮጲያ ታሪክ  እንደ ማንኛውም ሀገር በበጎና መጥፎ ገፅታዎች የታጀበ ነው። በሚገባ ቦታ ያልሰጠነው የሉዓላዊነት/ነፃነት ትሩፋት እንደዋና በጎ የታሪክ ገፅታ የሚጠቀስ ሲሆን፣ በዚያኑ ልኩ፣ ሃሳባችንን ድንክዬ፣ አመለካከታችንን ቁንፅል ያደረገ ጭፍን እሳቤ ውስጥ መዘፈቃችን ደግሞ የታሪካችን መጥፎ ገፅታ አድርጌ እወስደዋለሁ። በተለይ ከጣሊያ ወረራ በኋላ “በብሔራዊ አንድነት” ስም በሀገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ላይ የተፈፀመው ተግባር የዚህ ታርካዊ ስህተት መገለጫ ነው፡፡ እዚህ ጋር ጉዳዩን ያነሳሁበት ምክንያት፣ የዮናታን ተስፋዬ ሃሳብና የሰማዊ ፓርቲ ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ እርምጃ የዚህ ታርካዊ ስህተት ጠባሳ ማሳያዎች ስለሆኑ ነው።

ስለጎንደር ሲዘፈን ልቡ የሚሞቅ ሰው፣ ሌላውም ሰው በጎንደር ስልት እንዲውረገረግ ይጠብቃል እንጂ የሚውረገረግበት የራሱ የሆነ ስልት እንዳለው አይገነዘብም፡፡ ስለኦሮሞ ሲዘፈን ውስጡን የሚረበሽ ከሆነ ግን እሱ እንደ ሌሎች መሆን ሳይችል ሌሎች እንደእሱ እንዲሆኑ የሚሻ ነው፡፡ እንዲህ ያለ አስተሳሰብ ያለው ሰው በበሰበሰ የፊውዳል ዘመን የአስተሳሰብ ባርነት ውስጥ ተዘፍቆ ያለ ነው። እንዲህ ያለ ሰው ስለ አንድነት ለማውራት የሞራል ሆነ የግንዛቤ ብቃት የለውም።

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው፣ የሰማያው ፓርቲ የሥነ-ስርዓት ኮሚቴ እና የኦዲትና ምርመራ ኮሚሽን በዚህ ዓይነት የአስተሳሰብ ባርነት ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች የተሰበሰቡበት ነው። ስለዚህ፣ ሰማያዊ ፓርቲ እነዚህን አባላት ስለተከተሉት የአካሄድ ስህተት ሳይሆን ያሉበትን የአስተሳሰብ ባርነት ተረድቶ  ከድርጅቱ አመራርነት ሊያገላቸው ይገባል።

አባላቱ በማህበራዊ ድረገፆች ላይ ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ ብቻ የሚከስና የሚያባርር አመራር ስለነፃነት ትርጉምና ፋይዳ ፍፁም ግንዛቤ የሌለው ነው። ሰማያዊ ፓርቲ ስለሀገሪቱ ዜጎች  ነፃነት እንዲከበር ከመጠየቁ በፊት፣ በቅድሚያ ከእንዲህ ያሉ ጭፍን አመራሮች ራሱን ነፃ ማውጣት አለበት። ይህን ማድረግ ከተሳነው ግን፣ ሰማያዊ ፓርቲ ነፃነትን የማያውቅ ነፃ-አውጪ ድርጅት ሆኖ እንዳይቀር እሰጋለሁ።
**********

Seyoum Teshome is a Lecturer at Ambo University Woliso Campus and head of Management Department. He was born in Arsi, Assela, in 1979 and studied Management at Harameya University and MBA at Mekelle University. He also blogs at http://ethiothinkthank.com

more recommended stories