በአለም ላይ (በተለይም በአፍሪካ) የሚከሰቱ ግጭቶችን እንደ ወቅታዊ ክስተት በዜና ከመከታተል ባለፈ ጠለቅ ያለ የታሪክ ጥናት ያከሄደ ሰው አንድ ተመሳሳይ ሂደትን ማስተዋሉ አይቀርም፡፡ ይህም ሂደት ሁሉም የብሔር (የዘር) ግጭቶች ከፋ ደረጃ ከመድረሳቸው በፊት ጥቂት ልሂቃን ሆን ብለው ባቀናበሯቸው ደረጃዎች (steps) ውስጥ ማለፋቸው ነው፡፡

እነኝህ የጥላቻ/ግጭት መፍጠሪያ ደረጃዎች ከሞላ ጎደል በሁሉም ግጭቶች ውስጥ የሚተገበሩ ሲሆን የቆየ የታሪክ ቁርሾ መሰረት ባለበትም ሆነ ምንም የቁርሾ ትርክት በሌለበት ግጭቶችን የማጎልበት ወይም መፍጠር አቅም እንዳላቸው ቴቷል፡፡ የዚህ አይነት ግጭቶች አቀናባሪ ልሂቃን የጥላቻ ኢንጂነሮች አብዛኛውን ጊዜ በወጡበት ማህበረሰብ ዘንድ ያላቸውን ማንኛውም አይነት ተሰሚነት በመጠቀም በሚፈጥሩት የብሔር ጥላቻ/ግጭት ምክንያት እነሱ የብሔራቸው ጠበቃና መሲህ መስለው የሚወጡበት ሲሆን ይስተዋላል፡፡ በውጤቱም በፊት የነበራቸውን የፖለቲካ ቁመና (ተሰሚነት) አሳድገው ወደ ላቀ የመሪነትና የጥቅም ማማ ይወጣሉ፡፡

ያለፈው ወር በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በማስተር ፕላኑ እና በአከባቢያዊ መልካም አስተዳደር እጦት ላይ የተቀሰቀሰ የተማሪዎች ተቃውሞ በዋነኝነት በመንግስት የአያያዝ ድክመት (handling failure) የዜጎች ሕይወት የጠፋበት አሳዛኝ ወር ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ የተቃውሞ እንቅስቃሴ አነሳሱ ከወጣቶች ቢሆንም አንዳንድ ፖለቲከኞችና የዲያስፖራ ልሂቃን ዘግይተውም ቢሆን የተቃውም መሪ ሆኖ ለመወጣት ሲሞክሩ ታይተዋል፡፡

ከዲያስፖራ ልሂቃኑ ውስጥ የወቅቱ ፊት አውራሪ እንደ መድረኩ የተለያዩ ማንነት ይዞ በመቅረብ የሚታወቀው ጀዋር መሐመድ ነው፡፡ ሰውየው ከአንድነት አቀንቃኝ እስከ መገንጠል ሰባኪ ከዲሞክራሲ እስከ የሜንጫ ፖለቲካ ሁሉንም ሆኖ መተወኑን ያስታወሳል፡፡

ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነ ‹‹የአዲስ ገጽ›› መጽሔት ቁጥር አራት ላይ ያነበብኩት የጃዋር ቃለ መጠይቅ ሲሆን ባለፈው ወር በሶሻል ሚዲያ ሲያንፀባርቀው ከነበረው አስተሳሰብ ጋር ተደምሮ ዘንድሮም እንዳስለመደን አዲስ ፖለቲካ ይዞልን እንደተመጣ ስለተረዳሁኝ ነው፡፡

Photo - Jawar Mohammed

አዲሱ ፖለቲካ እስከ አሁን የሚነቅፋቸው የነበሩትን የኦሮሞን የፖለቲካ ድርጅቶቻችንና የቀኝ አክራሪ ፓርቲዎችን በመተው “ሀጎስ’ን በአዲስ ቀኝ ገዥነት የሚያስተዋውቅ ነው፡፡ ሰውየው በቃለመጠይቁ ‹‹ትግሬዎች ዜጋ ሌላው ተገዢ›› እንደሆኑ እና ይህንን ‹ቅኝ ግዛት› እንደሆነ ለማስመሰል (በንጽጽር) ያስምርበታል፡፡ ይህ የሚስተባበል አፍ ወለምታ ሳይሆን አዲሱ የፖለቲካ መንገዱ እንደሆነ የሚያስረግጥልን ደግሞ በፌስቡክ ጽሁፎች በኦሮሚያ የተሰማራውን (የኦሮሚያ ፖሊስ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሰራዊት) በደምሳሳው “የትግሬዎች ጦር’ “አግአዚ’ ወዘተ እያለ መጥራት መምረጡ ነው፡፡ ቤሰዓቱ በሚጽፏቸው አጫጭር ጽሁፎች የኢህአዴግ ድርጅቶች ሕወሐትን ከባለስልጣናት አባይ ፀሐዬን ከምናባዊ ባለሃብቶች ደግሞ “ሐጎስ’ን መምረጡ ደግሞ አዲስ ፖለቲካ መጀመሩን ያጠናክርልናል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት ሌላ ትርኢትና አገራዊ “የመፍትሔ ትንታኔ’ በዚሁ ሰው ሲቀርብ የሰማ ሰው በአዲሱ ፖለቲካ ግር መሰኘቱ አይቀርም፡፡ ይህ የጃዋር አካሄድ ግን የአንድ ሰሞን ሞቅታ ሳይሆን የአዲስ “ያልተሞከረ’ እስትራቴጂ ጀማሮ እንዲሆነ ይሰማኛል፡፡ ይህንን እስትራቴጂ ነው ከላይ የብሔር ግጭት/ጥላቻ ምህንድስና ብዬ የገለትኩት፡፡

የጥላቻ መሃንዲሶች የቁርሾ ፈጠራቸውን የሚያከናውኑባቸውን አላማዎችና ሊያሳኩ የሚሄዱባቸውን (የሚችሉባቸውን) መንገዶች በሚገባ ለመረዳት ከሚከተሏቸው ስሌቶች (ደረጃዎች) የተወሰኑትን መቃኘት ጠቃሚ ነው፡፡

የሴራ ትርክት ግንባታ (conspiracy theory building)

የሰራ ትርክት ባደጉም ሆነ ባላደጉ ማህበረሰቦች ዘንድ የሚታይ ክስተት ቢሆንም በራሳቸው ሕይወት የመወሰን አቅማቸው አነስተኛ የሆነ የውጭ አባላት ባላቸው ላቀ አቅም በመጠቀም የውስጥ ጉዳቶቻቸውን እንደሚወስኑ በሚያስቡ ግለሰቦችና ማህበረሰቦች ዘንድ በስፋት ይታያል፡፡

ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆን በእኛ አገር በሰፊው የሚዘወተር ለችግሮቻችን ሁሉ “ሲ.አይ.ኤ’ ን ወይም ግብጽን ተጠያቂ የማድረግ ልምድ ነው፡፡ በአረብ አገራት ህዝቦች ዘንድ ለተፈጥሮአዊ ችግር ሁሉ ሳይቀር “አይሁዶች’ የሚከሰሱበትን አግባብ ሌላ ማሳያ ነው፡፡

የብሔር ግጭት መሃንዲሶች እጅጉን ከሚያዘወትሯቸው ስልቶች አንዱና ዋነኛው “ሌላው ብሔር’ እያገዟቸው እንደሆነ መስበክን ነው፡፡ ለእነኝህ መሃንዲሶች ወጡበት ብሔር የተለያየ የፖለቲካ አመለካከትን እንደሚያስተናግድ ማመን ሕዝባቸውን “መከፋፈል’ እንደሆነ ይሰማቸዋል፡፡ ስለዚህ “ሕዝባቸው’ በሃሳብ “አንድ’ እንደሆነ እና በተለያ የፖለቲካ አመለካከት የተደራጁ የሕዝቡ ድርጅቶች የዛ ‹‹ሌላ›› ብሔር (ቅኝ ገዥ) ፈጠራ (ተለጣፊዎች) እንደሆኑ ይደሰኩራሉ፡፡

በማህበረሰባዊ ጉዳዮች እንኳን ሳይቀር መጥፎ ክስተቶችን “ለሌላው’ በማሸከም እራሳቸውንና እኛ የሚሉትን ሕዝብ የተጠያቂነት ታሪክን/ካባን (victimhood) ብቻ ያለብሱታል፡፡ ይህንንም በቁጭት ለበቀል ለማነሳሳት ይጠቀሙበታል፡፡

የጃዋር በቃለመጠይቁ ላይ ኦ.ህ.ዴ.ድን እና ብ.አ.ዴ.ንን የህወሓት “ዘበኞች’ አድርጎ መግለጽ የዚሁ የጠላት ሴራ ትርክት ግንባታ ማሳያ ነው፡፡

የመስዋዕት በግን መፍጠር (escapegoating)

‹የመስዋዕት በግ› ምንጩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሲሆን በእሳቤው መሰረት የመስዋዕት በጉ ከሕዝቡ መልካም ያልሆኑትን ነገሮች እንተሸከመ ተቆጥሮ የሚቃጠልበትና ያም ሕዝቡን በአዲስ ነፃ መንፈስ ወደ ፊት እንዲራመድ እንደሚያስችል የሚታመንበት ስርዓት ነው፡፡

በግጭት ኢንጂነሪንግ ውስጥ ዋነኛ ከሆኑት ስልቶች መሀከል ይህ አንዱ ነው፡፡ የጥላቻ መሃንዲሶች “ሕዝባቸው’ እንዳይተባበር ወይም “አሸናፊ’ እንዳይወጣ ወደ የሚጎትቱትን የታሪክ ልምድ ልዩነት (experience) እንዲሁም አከባቢያዊና ፖለቲካዊ የአስተሳሰብ ልዩነት ለማዳፈን ይረዳቸው ዘንድ ውጫዊ የሆነ “ጠላት’ ይፈጥሩለታል፡፡ ይህ ሕዝባቸውን “አንድ’ ለማድረግ የሚመረጠው አካል (ብሔር) ቢቻል ነባር ታሪካዊ ቁርሾን ተመስርቶ ሁኔታዎች ካልፈቀዱ ደግሞ አዲስና ወቅታዊ ሊሆን ይችላል፡፡

ለዚህ ጥሩ መሳያ የሞሆነን ሶሻል ሚዲያና ሌሎች አገራት ግጭቶች ውስጥ በተደጋጋሚ የሚታየው አንድ ብሔር አባላት የሆኑ ሰዎች በሌላ ብሔር ሰዎች/አባላት/ ወይም ወታደሮች እንደተገደሉ አድርጎ የሚያቀርብን ትርክት በሰቅጣጭ የሟቾች ምስሎች አስደግፎ ማቅረብ ነው፡፡

የተባለውን ግድያ የፈፀሙት ከመሟቾች ብሔር የወጡ ግለሰቦች ወይም ወታደሮች ቢሆኑ እንኳን “የመስዋዕት በግ’ ስልት ገዳዮቹ ከውጫዊ አካል “ሌላ ብሔር’ የወጡ መሆናቸውን የግድ ይላልና ትርክቱ እንደሚፈለገው ጥላቻን መፍጠር እንዲችል ተደርጎ ይቀናበራል፣ይሰራጫል፡፡

ማግለልና አካላዊ ጥቃቶች (discrimination and attacks)

የጥላቻ ኢንጂነሮች አማካኝነት በሕብረተሰብ ውስጥ ባሉት ስለሌሎች ያሉ ተዛቡ አመለካከቶች ላይ ተገነቡት “የሴራ ትርክት’ እና “የመስዋዕት በግ’ የመፍጠር ስልቶች በሚቀጥለው ደረጃ ከፍ ወደአለ ደረጃ እንዲያድጉ ያደርጋሉ፡፡

ከእነኝህ ቀጣይ ደረጃዎች አንዱ አግላይነት (discrimination) ነው፡፡ የማግለል ስልት በሰለጠነው አለም በጤናማ መልኩ (boycott) ተብሎ የሚተገበር ሲሆን አላማውም በሕብረተሰቡ ዘንድ የተወገዘ አስተሳሰቦች (ለምሳሌ ዘረኝነት) በሚያራምዱ/በሚደግፉ የንግድ ድርጅቶችና ታዋቂ ግለሰቦች ላይ ጫና በማሳረፍ ማረቅ ነው፡፡ በእኛም አገር ባለፈው ዓመት አርቲስት ቴዎድሮስ አፍሮ ያደረገው ንግግር ተከትሎ የደረሰበት ጫና ተነፃፃሪ ምሳሌ ነው፡፡

የብሔር ጥላቻ መሃንዲሶች የማግለል ጥሪዎችና ዘመቻዎች ግን በባህሪያቸው የተለዩ ናቸው፡፡ ከሰለጠነው የቦይኮት ስልት በተቃራኒ የማግለል ሰለባዎች የሚመረጡት አስተሳሰብ ሳይሆን በብሔር መስፈርት ነው፡፡ ማግለሉ “ከቅኝ ገዥዎች’ ጋር አብረው ከሚሰሩ ድርጅቶች የተወሰኑትን ብቻ መምረጥ አልፎ ተርፎም ማህበረሰባዊ፣ፖለቲካዊ ሚናቸው እምብዛም የሆኑ ተራ ግለሰቦችንና የንግድ ድርጅቶችን ሁሉ ማጠቃለሉ ከቦይኮት ይልቅ ለዘር መድልዎ (discrimination) ያመሳስላቸዋል፡፡

የዚህ ስልት ዋንኛ ግብ በሁለት ብሑሮች መካከል ያለው ቁሳዊና ማህበረሰባዊ ትስስሮች መበጣጠስ እና ለቀጣዩ ተግባራዊ ደረጃ አካላዊ ጥቃቶች አመቺ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ ሂደቶቹ ወደ ግጭት ከተሸጋገሩ የጥላቻ ኢንጂነሮች እቅድ ግብ መታ ማለት ሲሆን በግጭቱ መጠኑ ሊደርስ የሚችልበት ከፍተኛ ደረጃ ከሁኔታዎች በስተቀር መሃንዲሶችም ሆነ ሌላ ሊቆጣጠረው የሚቻል አይሆንም፡፡

መውጫ

የጥላቻ ወይም የግጭት ምህንድስና ብሎኬት በብሎኬት እየተገነባ የሚሄድና በልሂቃኑ ተከታዮች እና በአጠቃላይ ሕዝብ ዘንድ ቀስ በቀስ የመስረጽ አቅም ያለው አደገኛ ፖለቲካ ነው፡፡

በዚህ ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩትም በ “ሌላው’ ጥላቻ ላይ የሚገነባው ‹‹አንድነት›› ጤናማ የሆነ የማህበረሰብ መሰረት እንደማይፈጥርና ለዛ ብሔርም ሆነ አካል የማይጠቅመው እንደሆነ ነው፡፡ ከዚህ አትራፊ የጥላቻ ኢንጂነሮች ብቻ ናቸው፡፡ በተለይ እንደኛ አይነቱ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች በተተበተበበት ሀገር የህብረተሰቡ ለ “ሴራ ፖለቲካ” መመቸት፣ ለውስጣዊ ችግሩ ተጠያቂ ባዕድ አካል የመፈለግ ሰብአዊ ባህሪ እና የተከማቸብን የቁርሾ የታሪክ ትርክት ለዚህ አይነት አስቀያሚ ፖለቲካ በግብዓትነት ስለሚያገለግሉ ስልቱን አደገኛ ያደርገዋል፡፡

ለዚህ ብቸኛው መፍትሔ የተማረው አዲስ ትውልድ የጥላቻ ፖለቲካን ስልት መንገዶች ተረድቶ የልሂቃኑንን የጥላቻ ግንባታ ሲያመክን ሲሆን ሚዲያውም (እቺን መጽሄት ጨምሮ) እነዚህን ልሂቀን በልፍስፍስ ጥያቄዎች ከማለፍ ተቆጥበው ራሳቸውን እንዲገልጡ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡

***********
ይህ ጽሁፍ መጀመሪያ የታተመው በጥር 7፣2008 በ<አዲስ ገጽ> መፅሄት ቁጥር 5 ላይ ነው

Fetsum Berhane is an Ethiopian resident, economist researcher and a blogger on HornAffairs.

more recommended stories