ዶ/ር ነጋሶ:- “በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ስንመክር፣ ማስተር ፕላን ብሎ ታምራት ላይኔ አንድ ሀሳብ አመጣ”

(አለማየሁ አንበሴ – አዲስ አድማስ)

አንጋፋው የታሪክ ምሁርና ፖለቲከኛ የቀድሞ የኢፌዲሪ ፕሬዚንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ በሽግግር መንግስቱ ጊዜ የማስታወቂያ ጉዳይና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ነበሩ፡፡ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል መካከል ስለሚኖሩ ግንኙነቶች፣ኦሮሚያ እንዴት ከአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚ ትሁን እንደተባለ፣ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ከተሞች ድንበር መካለል ውሳኔናለምን ተግባራዊ እንዳልተደረገ፣ በሽግግር መንግስቱ ጊዜ ለውይይት ቀርቦ ስለነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላንና በመሳሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ቃለምልልስ አድርገዋል፡፡

በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 49(5) ላይ ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልዩ ተጠቃሚ ትሆናለች ሲባል በወቅቱ ምን ጥቅሞችን ታሳቢ ተደርጎ ነበር?

በወቅቱ በነበረው አርቃቂ ኮሚሽንም ሆነ በጠቅላላ ጉባኤ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገባንም።  ዝርዝሩ በሌላ ህግ እንዲገለጽ ነበር የተባለው፡፡ የህገ መንግስቱ ስራ በችኮላ ነው የተካሄደው፡፡ ዝርዝር ህጉን ማን ነው የሚያወጣው? አዲስ አበባ ነው ወይስ አዲስ አበባ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ስር ስለነበረች የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ነው? ለነዚህ ጥያቄዎች በወቅቱ መልስ ሳይሰጥ ነበር የታለፈው። ከዚያም በኋላ ይኸው 20 ዓመት ሙሉ ያ ዝርዝር ህግ አልወጣም፡፡ እሱ ሳይደረግ  ማስተርፕላን ላይ መንጠላጠሉ ነው ትልቁ ክፍተት፡፡ እስካሁን ድረስ ዝርዝር ህጉ አለመውጣቱ ትልቅ ጥፋት ነው፡፡

ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ታገኛለች የሚል አንቀፅ በህገ መንግስቱ ሲካተት ለምሳሌ ምን አይነት ጥቅሞች ነበሩ የታሰቡት?

አዲስ አበባ በኦሮሚያ እምብርት ላይ ነው ያለችው፡፡ ለአዲስ አበባ ግንባታ የሚውለው ድንጋይ የሚመጣው ከኦሮሚያ ነው፡፡ ውሃና መብራት የመሳሰሉትም ከኦሮሚያ ነው የሚመጡት፡፡ በአንፃሩ የአዲስ አበባ ቆሻሻ ደግሞ ወደ ኦሮሚያ ይሄዳል። ይሄን አዲስ አበባ ማሰብ አለባት፡፡ ከምታገኘው ገቢም ሊሆን ይችላል ለኦሮሚያ የምትጠቅመው። ኦሮሚያ ለአዲስ አበባ የተፈጥሮ ሀብቶች ምንጭ ናት። ይሄ ሀብት እንዴት ባለ መልኩ የኦሮሚያ ጥቅም ተጠብቆ ይተላለፍ የሚለውንም የሚያካትት ሊሆን ይችላል። በአዲስ አበባ ም/ቤት የኦሮሚያ ተወካዮች ሊኖሩ ይገባል የሚል ነገርም ነበር፡፡ የመሰረተ ልማት ጉዳይ የመሳሰለው አልተጠቀሰም ነበር፡፡

የአዲስ አበባንና የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችን ድንበር በማካለል በኩልስ በወቅቱ ምን ነበር የተወሰነው?

አንደኛ፤ በሽግግር መንግስቱ የማስታወቂያ ጉዳይና የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ሳለሁ የካቢኔ አባል ነበርኩ፡፡ ካቢኔውን የሚሰበስበው ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረው ታምራት ላይኔ ነበር። ያን ጊዜ በአዲስ አበባ ጉዳይ ላይ ስንመክር፣ ማስተር ፕላን ብሎ ታምራት አንድ ሀሳብ አመጣ። ካርታው ሲታይ የአዲስ አበባ ከተማ ተብሎ የተቀመጠው እስከ ፊቼ፣ አሰላ፣ አምቦ የመሳሰሉት የኦሮሚያ ከተሞች የሚደርስ ነበር፡፡ ይሄን ሲያመጣ ይሄማ አይሆንም፤ ወደ ድሮው የአዲስ አበባ ይዞታ መመለስ አለበት ተባለና ያ ማስተር ፕላን እንዲቀር ተወሰነ፡፡ በዚያው ቀረ፡፡

ከዚያ በኋላ አቶ መለስ ዜናዊ የሰበሰበን የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ የአዲስ አበባ ክልል ድንበር መወሰን አለበት አልንና ተነጋገርን፡፡ በወቅቱም በአፄ ኃይለሥላሴ ጊዜ ከነበረው የአዲስ አበባ ከተማ ስፋት ትንሽ በለጥ የሚል የክልል ይዞታ ይካለል ተባለ፡፡ በወቅቱም የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት የነበረው አቶ ሀሰን አሊና የአዲስ አበባ ከንቲባ አሊ አብዶ ኮሚቴ አቋቁመው ዳር ድንበር ማመላከቻ ድንጋይ እንዲተከል ተወሰነ፡፡ በዚህ ውሳኔ መሰረት ይሰራል ብለን ስንጠብቅ ነበር፡፡ እንግዲህ እኔ እስከማውቀው ድረስ የተባለው አልተፈፀመም፤ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በመሀከሉ የኢንዱስትሪ መስፋፋት መጣ፡፡ ቦታው የኦሮሚያ ሆኖ ቦታውን ማስተዳደር የሚገባው ኦሮሚያ መሆን ሲገባው አልሆነም፡፡ አሁን ለምሳሌ ጀሞ፣ ለገጣፎ የመሳሰሉት ቦታዎች ከአዲስ አበባ ጋር ያላቸው ድንበር ሳይወሰን ነው ዝም ብሎ ኢንዱስትሪው የተስፋፋባቸው፡፡ለምሳሌ ያኔ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ጽ/ቤት፣ ሣር ቤት አካባቢ ነበር፤ አሁን ግን ኦሮሚያ ክልል የነበረው ለቡ አካባቢ ነው ያለው። እንግዲህ ይሄ ሁሉ የሆነው ከ20 ዓመት በፊት ይከለላል የተባለው ድንበር ተግባራዊ ሳይደረግ እንዲሁ ዝም ብሎ ነው። ይሄ ነው ጭቅጭቅ እየፈጠረ ያለው፡፡ ድንበሩ አለመከለሉ፣ በዝርዝር ይገለፃል የተባለው ጥቅም አለመዘርዘሩም ትልቁ የችግሩ ምንጭ ነው፡፡

Photo - frm. President Negasso Gidada

ለምንድን ነው በአፋጣኝ ድንበሩን ማካለል ያልተቻለው? ከዚያ በኋላስ የድንበር ማካለል ጉዳይ ተነስቶ ያውቃል?

እኔ እንግዲህ ላለፉት 15 ዓመታት በኢህአዴግ ውስጥ አልነበኩም፡፡ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ውይይቶች ስለመካሄዳቸው አላውቅም፡፡ ያን ጊዜ ሀሰን አሊና አሊ አብዶ ድንበሩን እንዲያካልሉ ከተወሰነ በኋላ ይፈፀማል የሚል ግምት ነው የነበረኝ። ከዚያ በኋላ ሀሳቡ ይቀየር እንዲሁ ተድበስብሶ ይቅር አላውቅም፡፡

የአፄ ኃይለ ሥላሴን ማስተርፕላን ጠቅሰው ነበር። ማስተርፕላኑ የአሁኗን አዲስ አበባ የሚገልፅ ነው?

የኃይለ ሥላሴ ማስተርፕላን ዛሬ መጨቃጨቂያ የሆኑ ቦታዎችን በፍፁም አልነካም፡፡ ከተማዋንም ይሄን ያህል ለጥጦ ያስቀመጠ አይደለም፡፡ ዛሬ ተነስቷል የተባለውን የአርሶ አደሮች አካባቢም አይነካም፡፡ አሁን የተፈጠረው ችግር እንደኛ፣ የአመለካከት ጉዳይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ያሉ ሰዎች ምን ያህል ቅን ናቸው? ኦሮሚያን እያስተዳደሩ ያሉትስ ለዚህ ጉዳይና ለኦሮሚያ ክልል መብቶች ምን ያህል ይከራከራሉ የሚሉ ጥያቄዎችን ያስነሳል፡፡

እርስዎ የመንግሥት ካቢኔ አባል በነበሩ ጊዜ አዲስ አበባን ከኦሮሚያ ጋር የሚያስተሳስር የጋራ ማስተርፕላን የተነሳበት አጋጣሚ አለ?

በፍፁም የለም፡፡ ሁሉም ከተሞች በየራሳቸው ይጓዙ የሚል ነገር ነው የነበረው፡፡ እንደሚታወቀው የሽግግር ጊዜው ላይ አሁን ያለው የፌደራሊዝም ስርአት አልተዋቀረም፡፡ ስለዚህ አቶ ታምራት ላይኔ አቅርቦት ከነበረውና በተቃውሞ ውድቅ ከተደረገው ማስተርፕላን ውጪ እንዲህ ያለው እቅድ እኔ በመንግሥት አመራር ውስጥ ሳለሁ አልነበረም። የደርግን ማስተርፕላን አቶ ታምራት ማምጣቱን የኦሮሞ ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም በውቅቱ ተቃውመውት ነበር፡፡

በሽግግር መንግሥቱ ጊዜ በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩም ሆነ ከኢህአዴግ ውጪ የነበሩ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በአዲስ አበባ ከተማ ላይ የነበራቸው አቋም ምን ነበር?

ከኦነግም አቶ ዲማ ነገዎ ነበሩ፤ ከኦህዴድ እኔና ኩማ ደመቅሳ ነበርን፤ ሌሎች የፓርቲ አባል ያልሆኑ ኦሮሞዎችም ሆነ ከሌሎች ብሄረሰቦች የመጡ የካቢኔ አባላት፣ አዲስ አበባ የፌደራል ስርአቱ ሲቋቋም የኦሮሚያ ማዕከል ትሆናለች የሚለው አመለካከት ነበራቸው፤በግልፅ ባይወጣም፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር በኦሮሚያ ስር መሆን አለበት ግን የፌደራል መንግስት ይጠቀምባታል፤ባለቤትነቷ ግን የኦሮሚያ ነው የሚል ነገር ነበር፡፡ ክልሎች ሲቋቋሙ ፊንፊኔ የኦሮሚያ ዋና ከተማ ትሆናለች የተባለውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡

የአዲስ አበባና የኦሮሚያን ጉዳይ ከስረ መሰረቱ ያውቁታልና አሁን ውዝግብ ባስነሳው ማስተር ፕላን ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?

እንደኔ የመስፋፋቱ ጉዳይ በማን አስተዳደር ስር ሆኖ ነው የሚለው ይመስለኛል ጥያቄው፡፡ ባለፈው አመት ዋሽንግተን ነበርኩ፡፡ ከዋሽንግተን ዲሲ 10 ደቂቃ በማይሞላ ርቀት ላይ ኢርሲንግተን አለች፤በቨርጂነጂያ ግዛት ስር ያለች ከተማ ነች፡፡ ዋሽንግተንን ከዚህ ግዛት የሚለያት ወንዝ አለ፤ በቃ ያ ወንዝ ድንበሯ ነው፡፡ ባቡር፣ ኤሌክትሪክሲቲ፣ ስልክ፣ ውሃ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከተሞቹ የየራሳቸው ድንበርና አስተዳደር አላቸው፡፡ እንግዲህ ከዚህ ተነስተን እንደምንረዳው፣ ከተሞች ራሳቸው ናቸው ማቀድ ያለባቸው፡፡ ትልቅ ከተማ ለትንሽ ከተማ ማቀድ የለበትም፡፡ ሁሉም የየራሱን እቅድ አውጥቶ ድንበሩን ጠብቆ ተናቦ መስራት አለበት፡፡

ህገ መንግሥቱ አሁን ለተነሳው ጥያቄም ሆነ ተያያዥ ችግሮች መልስ የሚሰጥ ነው ይላሉ?

ህገ መንግሥቱ ተግባራዊ ምላሽ ሰጥቷል አልሰጠም በሚለው ላይ አንደኛ አንቀፅ 29 አለ፤ አንቀፅ 30፣ አንቀፅ 31 እና አንቀፅ 38 የሚደነግጉት የዲሞክራሲ ጥያቄዎችን ነው፡፡ በተለይ አንቀፅ 31 የመደራጀት መብት ነው፡፡ በአንቀፅ 38 ደግሞ የመምረጥና የመመረጥ  ጉዳይ በትክክል ተግባራዊ ሆኗል ወይ ካልከኝ አልሆነም፡፡ ኢህአዴግ ግን ሆኗል የሚል ምላሽ ነው የሚሰጠው፡፡ ከኢህአዴግ ፓርቲ ውጪ ሌሎች ፓርቲዎች የፈለገውን አመለካከትና አላማ ይዘው ለመደራጀት ይችላሉ የሚለው የህገ መንግስቱ አንቀፅ ተግባራዊ ሆኗል ወይ? ይሄም በግልፅ የሚታይ ነው፤ ተግባራዊ አልሆነም፡፡ ሌላው አንቀፅ 39 ነው፡፡ አንቀፁ የራስን እድል መወሰን እስከ መገንጠል ድረስ ይደነግጋል። እስካሁን ባየነው ግን ይሄ ህግ የማይተገበር ነው። መገንጠል ትክክል ነው አይደለም የሚለው የአስተሳሰብ ጉዳይ ነው፤ ህገ መንግስቱ ግን መገንጠልን ይፈቅዳል፡፡ እስካሁን በሰላማዊ መንገድ ክልሉን አሁን ካለው አደረጃጀት ልገንጥል ብሎ ህዝብን ለማደራጀት፣ ለማንቀሳቀስ የደፈረ አንድም ፓርቲ የለም፡፡ ከደረፈም የሚወሰድበት እርምጃ ሌላ ነው፡፡ እኔ ይሄን ጥያቄ በማነሳበት ጊዜ ብዙ ሰዎች #ነጋሶ ኦነግ ነው” ይላሉ። እኔ ግን ለዚህ ተሟጋች የሚያደርገኝ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ነው፡፡ እንጂ አንድ ክልል ልገንጠል የሚል ህዝበ ውሳኔ ቢያደርግ “መገንጠል አይበጅም÷ የኢትዮጵያ አንድነት ይሻላል” ብዬ ነው በተግባር የምመርጠው። የራስን መብት በራስ የመወሰን መብት መከበር አለበት በሚለው ዲሞክራሲያዊ መብት ላይ ግን ሳይሸራረፍ ተግባራዊ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በሌላ በኩል ከህገ መንግስቱ አንፃር ህዝብ የመወሰን መብቱ ተግባራዊ ተደርጓል ወይ ካልከለኝ አልተደረገም፤ህዝብ የመወሰን መብቱን ሙሉ ለሙሉ አላገኘም፡፡

********
Source: Addis Admass

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories