የኢትዮጵያ መንግስትና “ኣርበኛዊ” ዲፕሎማሲ (እርምጃ)

በሳውዲ፣ የመን፣ ደቡብ ኣፍሪካና ሊብያ በኢትዮጵያውያን ላይ ችግር ባጋጠመ ጊዜ በቦታው የሌሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ መንግስት በነዛ ኣገራትና ቡድኖች ላይ እንዲወስደው የሚጠብቁት እርምጃ ኣርበኛዊ እርምጃ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ጥሎበት (በባህሪው) ኣርበኛዊ ዲፕሎማሲ ኣያራምድም፡፡ ቢያንስ መንግስት በኣንዳንድ ወገኖች የሚነሳበትን የ”ወኔ-ቢስነት” ክስ ለመከላከልና ለዜጎቹ እንደሚቆረቆር ለማሳየት ያክል እንኳን (ባያደርገዉም) በቴሊቪዥን ብቅ ብሎ ዘራፍና ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ኣይሆንለትም ወይም ኣያምንበትም፡፡ ይሄ ማለት ግን መንግስት ምንም ኣይነት እርምጃ ኣይወስድም ማለት ኣይመስለኝም ፡፡

በኢትዮጵያውያን ላይ ችግርና ጥቃት በደረሰ ቁጥር እኛ ዜጎች እንደምናሳየው ኣይነት ቁጣ የመንግስት ፊት (ግንባር) ላይ ባናየዉም በጊዜው እንደየሁኔታው የተሻለ የሚለው እርምጃ ይወስዳል የሚል ግምት ኣለኝ፡፡ ይሄንን ባህሪው ተቃዋሚዎቹ የፖለቲካ ነጥብ ለማስቆጠር ኣንዳንድ ደጋፊዎቹ ደግሞ የሚደግፉትን ፓርቲ/መንግስት ባህርይ በደንብ ካለመረዳት ኣሊያም በስሜትና ሃዘኑና ጥቃቱ በሚፈጥርባቸው ተፅእኖ ምክንያት መንግስትን ይወቅሳሉ፡፡ ለነገሩስ የኛን ስሜትና ምክር እየተከተለ እርምጃ የሚወስድ መንግስት ቢሆን ኖሮ ይሄኔ ከሱዳንና ግብፅ (በኣባይ ምክንያት)፣ ከሳውዲ ኣረቢያ (በዜጎች ምክንያት)፣ ከኤርትራ (በሄሊኮፕተር ምክንያት) እንዲሁም ከሌሎች ኣገሮች ጋር ጦርነት ውስጥ እንገባ ኣልነበር ?

የሰሞኑ የ ISIL ጉዳይ ግን ትንሽ ስሜትን ይፈታተናል፡፡ ድህነት ኣንገሽግሽዋቸውና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለመቀየር የሰሃራ በረሃን ኣቋርጠው የመሞትና የመትረፍ ኣጋጣሚው እኩል የሆነበትን የሜዲትራኒያን ባህር የጀልባ ጉዞ ለማድረግ የተዘጋጁትን ወጣት ወገኖች በኣደባባይ ኣንገታቸው ሲቀላና ሰረሸኑ ማየትን የሚያክል ዘግናኝ ነገር የለም፡፡ ህዝባችን በሃዘንም በቁጭትም ኣደባባይ ወጥቶ ሆ ቢል፣ እስቸኳይ የኣጸፋ እርምጃ እንዲወሰድ ቢጠይቅ ኣይገርምም፡፡ ጥያቄው ግን መንግስት ምን ኣይነት እርምጃ መውሰድ ኣለበት የሚለው ነው፡፡Photo - Islamic State killing Ethiopian Christians

ይህ ራሱን ISIL ብሎ የሚጠራ ቡድን የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ኣጠቃላይ የሰው ልጆች ጠላት ነው፡፡ ወጉ ደርሶን ዛሬ እኛጋ ቢመጣም ባለፉት በርካታ ወራት በዚህ ዘመን ይፈፀማሉ ተብሎ የማይጠበቁ ኣረመኔኣዊ ተግባራትን ሲፈፅም ታይቷል፡፡ ምእራባውያን ጋዜጠኞችን ያርዳል፣ ኣናሳ የኢራቅ ጎሳ ኣባላትን ይገድላል፣ ኣሁን ካለው የኢራቅ መንግስት ጋር ወግነዋል ያላቸው ሙሲሊም ኢራቃውያንን ያጠፋል፣ ግብፃውያን ክርስቲያኖችን ያርዳል፣ መንደሮችንና የታሪክና የስልጣኔ ማእከላትን ያወድማል፣ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችንም ይቀላል፡፡ ይሄ ቡድን የተለየ ጠላት የለዉም- ጠላቱ የሰው ልጅና ሰው ልጅ ስልጣኔዎች ናቸው፡፡

ይህ ኣረመኔኣዊ ቡድን እንዴት ተነሳ? የሰው ሃይሉና መሳሪያዎቹን ከየት ኣሰባሰበ? የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ቢኖሩም- ካለፈው ኣመት ጀምሮ ይሄንን ኣስከፊ ቡድን ለመዋጋትና እንዳይስፋፋ ለመከላከል በርካታ ኣገራት ሃይላቸውን ኣጠናክረው እየደበደቡት ይገኛሉ፡፡ ለወትሮው በሌላ ኣገር ጦርነት ዘው ብለው የማይገቡት እንደነ ኣውስትራሊያ፣ ካናዳና ኔዘርላንድስ እንኳን በዘመቻው ቀንደኛ ተዋናይ ሆነው በኣየር ድብደባው ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ የዚህ ቡድን ኣስከፊነት ኣሜሪካ ከቀንደኛ ጠላቷ ኢራን ጎን ሆና እንድትፋለማቸውም ኣሰገድዷታል፡፡ በነዚህ ከሰላሳ በላይ ሃያላን መንግስታት ሲካሄድ የቆየው ጥቃት ግን ቡድኑን ወደ ኣፍሪካ ከመዝለቅና እኛንም ሰለባ ከማድረግ ኣላገደዉም፡፡ ዛሬ ሊብያ ከገባ ነገ ሌሎች የፖለቲካና የፀጥታ ኣለመረጋጋት ያለባቸው ኣካባቢዎችም ሊጠቀሙባቸው እንደሚችል ማሳያ ነው፡፡

ስለዚህ ኢትዮጵያስ በዚህ ሰኣት ምንድንው ማድረግ የሚገባት? .….. እንደ ግብፅ የኣሮፕላን ጥቃት ማድረግ ለጊዜው የበቀል እርምጃ ወስጄኣለሁ ለማለት ያህል ካልሆነ ብዙ ውጤት የሚኖረው ኣይደለም፡፡ ኣንደኛ በንደነ ሊብያ ኣይነት ቦታዎች በኣይዲዮሎጂና በገንዘብ የሚመለምሏቸው ኣባላት ወይም ተባባሪወዎች ሊኖሩ ቢችሉም በወታደራዊ ጥቃት ልታጠፋቸውና ልትደመስሳቸው የሚችሉ የተደራጀ የሰው ሃይል ላይኖር ይችላል፡፡ የቡድኑ የጥፋት ኣላማ ኣስፈፃሚዎች ግድያውንና ውድመቱን ለማድረስ ግን በቂ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይሄንን ሁኔታ ያገናዘበ እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ በዛ ላይ ኣሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎቻችን እዛው ሊብያ ይገኛሉ፡፡ ተጨማሪ የዜጎች ህይወት እንዳይጠፋ መከላከልና የነሱን ህይወት ኣደጋ ውስጥ እንዳይገባ የሚያደርግ ስልታዊ እርምጃ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ማለት በቡድኑ ላይ የምንወስደው እርምጃ የኣለማቀፉ ጸረ- ISIL ዘመቻ ኣካል ሊሆን ይገባል፡፡

ከዛ በተጨማሪ ግን ይሄ ቡድን በኣካባቢያችን በምስራቅ ኣፍሪካ ምንም ኣይነት ቦታ እንዳያገኝና ተመሳሳይ ተግባራት እንይፈፅም ቀድሞ መከላከል ትልቁ የኢትዮጵያ የቤት ስራ መሆን ይገባል – ይሄም የኣካባቢውን ኣገሮችን በማስተባበር የሚፈፀም ነው፡፡ እዚህ ላይ እስካሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ የራሷ ግዛት ብቻ ሳይሆን ኣካባቢውን በሙሉ ከኣሸባሪዎች ለመከላከል የምታደርገው የተሳካ እንቅስቃሴ እውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ይህ የመከላከል እርምጃ በኣሁኑ ሰኣት ኢትዮጵያ ኣልሸባብ ላይ የምትወስደውን እርምጃ በማስፋፋት ሶማሊያንም እንደ ሊብያ መጠቀሚያ እንዳያደርጓት ኣስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

ከሁሉም በላይ ግን ለስደትና ለውርደት እየዳረገን ያለውን ድህነት መመከት ነው፡፡ ለዜጎቹ በቂ የስራ እድልና ኢኮኖሚ የሌለው መንግስት ዜጎቹን ወደዚህ ኣገር ኣትሂዱ ከሃገር ኣትውጡ ማለት ይከብደዋል፡፡ በንደዚህ ኣይነት የህይወትና የሞት መንገድ ውስጥ ተጉዘው የተሻለ ኑሮ እናገኛለን ብለው ለሚያስቡ በርካታ ወጣቶች ግን የሁኔታውን ኣስከፊነት ተከታታይ ኣስተምህሮ መስጠት የመንግስት ግዴታሊሆን ይገባል፡፡

********

Jossy Romanat

more recommended stories