ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የአባይ ወንዝን ለመጠቀም የደረሱት ስምምነት ሰነድ ሙሉ ቃል እና ማብራሪያ

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ ፍትሃዊ አጠቃቀም ላይ በቴክኒክ ኮሚቴ ደረጃ ሲያደርጉት የነበረውን ድርድር ወደ ፖለቲካ ኮሚቴ ከፍ በማድረግ ለወራት የዘለቀ ድርድር በሶስቱ አገራት ረዕሰ መዲናዎች ላይ ሲያካሂዱ ቆይተዋል።Photo - Al Sisis, Al Bashir, Hailemariam Desalegn signing a deal on Renaissance dam

እነዚህ ድርድሮችም ፍሬ አፍርተው አገራቱ የአባይ ወንዝን ዓለም አቀፍ መርህዎችን ተከትለው ለመጠቀም የሚያስችላቸውን ስምምነት ትናንት በሱዳን ካርቱም ተፈራርመዋል።

በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ፣ በግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱል ፋታህ ኤልሲሲ እና በሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር መካከል የተፈረመው ስምምነት ሶስቱንም አገራት እኩል ተጠቃሚ እና ዓለም አቀፍ መርህዎችን መሰረት ያደረገ ነው ተብሎለታል።

የዚህን ስምምነት ሰነድ ሙሉ ቃል ከአስረጅ ጋር እንደሚከተለው ቀርቧል።

መግቢያ

የግብፅ አረብ ሪፐብሊክ፣ የኢትዮጵያ ፌዴራሊያዊ ዴሞክራሲያ ሪፐብሊክ እና የሱዳን ሪፐብሊክ እየጨመረ የሚገኘውን ድንበር ተሻጋሪ የውሃ ሀብቶቻቸውን የመጠቀም ፍላጎትን መሰረት በማድረግ የናይል ወንዝ የግብፅ፣ የኢትዮጵያ እና የሱዳን ህዝቦች ህይወት እና ልማት ምንጭ የሆነ ሀብት መሆኑን በመገንዘብ ሶስቱ አገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ለተዘጋጁት ቀጣይ መርህዎች ይሰራሉ።

በዚህ የስምምነቱ የመግቢያ ክፍል ላይ ቀደም ሲል ግብፅ የናይል ወንዝ ለግብፃውያን የህይወት ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን ግን የቅንጦት ያህል ለመልማት ብቻ የሚፈልጉት አደርጋ የያዘችውን አቋም በመቀልበስ ናይል ለሶስቱም አገራት ዜጎች ህይወት እና ልማት መሰረት መሆኑን በእኩል እውቅና የሰጠ ነው።

1. የትብብር መርህ

– በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ ትብብር፣ የጋራ ፍላጎት፣ መልካም አሳቢነት፣ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ እና የአለም አቀፋዊ ህጎች መርህዎችን የተከተለ

– የታችኛውም ሆነ የላይኛው የተፋሰሱ ሀገራት ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው ተረድቶ በትብብር መስራት

በዚህ መርህ ውስጥ ቀደም ሲል በግብፃውያን ዘንድ የውሃ ፍላጎቱ በእነሱ ወገን ብቻ እንዳለ ተደርጎ የሚገለፀውን አቋም የቀየረ መሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ተናግረዋል።

በዚህ ስምምነት በተደረሰበት መርህ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ የየራሳቸው እያደገ የመጣ የውሃ ፍላጎት እንዳላቸው አውቅና በመስጠት የላይኛው እና የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ውሃ እንደሚያስፈልጋቸው ስምምነቱ አካቷል።

2. የአካባቢያዊ ትስስርና ዘላቂ ልማት መርህ

– የህዳሴው ግድብ ዓላማ ሀይል ማመንጨት፣ ለምጣኔ ሀብት እደገት አስተዋፅኦ ማድረግ፣ አከባቢያዊ ትብብርን መፍጠር፣ አስተማማኝ የሆነ የታዳሽ ሀይል በማመንጨት አከባቢያዊ ጥምረትን ማምጣት ነው።

የስምምነቱ ይህ ክፍል ኢትዮጵያ ግድቡን ሀይል ለማመንጨት እንደምታውለው የሚያስረዳ ሲሆን፥ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ጅማሬ ላይ እንደገለፀችው በአከባቢው ለሰፋፊ እርሻ የሚሆን መሬት ባለመኖሩ ለትላልቅ መስኖ መዋል የሚችልበት አድል የለውም።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሲያስረዱን ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያ በግድቡ የሚጠራቀመውን ውሃ ከሃይል ማመንጫነት ውጪ አትጠቀመም ማለት አይደለም።  ለምሳሌም በትናንሽ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች እየተሳቡ የሚለሙ መለስተኛ መስኖዎች፣ የዓሳ እርባታ፣ ቱሪዝም እና በአቅራቢያ የሚገኙ ከተሞች የሚፈልጉትን መጠቀምን ስምምነቱ ከግንዛቤ ያስገባ ነው።

3. ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርህ

– ሶስቱም ሀገራት በአባይ ወንዝ አጠቃቀማቸው ጉልህ ጉዳት ላለማድረስ ተገቢውን አካሄድ ይከተላሉ።

– ሆኖም ከሶስቱ አገራት መካከል በአንዱ ላይ ጉዳት ቢደርስ ያለምንም ስምምነት ጉዳቱን ያደረሰው አገር የዚያን ጉዳት መጠን ለመቀነስ ተገቢውን ስራ ያከናውናል፤ ሲመች ለመካስም ይወያያል።

ይህ የስምምነቱ ክፍል ለረዥም ጊዜ በግብፃውያን ዘንድ የነበረውን በወንዙ አጠቃቀም “ምንም ዓይነት ጉዳት አለማድረስ” የሚለውን አቋም ያስቀየረ ነው። በመሆኑም ሶስቱም አገራት በሌላኛው የተፋሰሱ አገር ላይ ጉልህ የሆነ ጉዳት ሳያደረሱ ወንዙን መጠቀም እንደሚችሉ እውቅና የሰጠ ነው።

በወንዙ አጠቃቀም አንዱ አገር በሌላው ላይ ጉልህ ጉዳት ቢያደርስ ሶስቱ አገራት ይነጋገራሉ፤ አስፈላጊውንም እርምጃ ይወስዳሉ፤ አስፈላጊም ከሆነ ለመካስ ይነጋገራሉ ይላል።

4. ፍትሃዊና ተገቢ የውሃ አጠቃቀም መርህ

– ሶስቱም ሀገራት በሀገራቸው ውስጥ የሚገኙ የጋራ ውሃቸውን በፍትሃዊነትና በአግባቡ ይጠቀማሉ።

– በፍትሃዊነት እና በአግባቡ በጥቅም ላይ ስለመዋሉም ለማረጋገጠ አገራቱ የሚከተሉትን መመሪያዎች ያጤናሉ።

ሀ. መልክዓ ምድር፣ የውሃ መልክዓ ምድር በውሃው ላይ ተመስርተው የሚኖሩትን፣ የዓየር ንብረት፣ ስነ ምህዳሩን እና ሁሉንም ተያያዥ የተፈጥሮ ነገሮች

ለ. የአባይ ተፋሰስ አገራትን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎትን

ሐ. በአባይ ተፋሰስ አገራት በወንዙ ላይ ሀይወታቸው የተመሰረተ ነዋሪዎች

መ. በአንዱ የወንዙ ተፋሰስ አገር የወንዙን ውሃ መጠቀም በሌላው የተፋሰሱ አገር ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ

ሰ. በወቅቱ እና በቀጣይ ሊኖር የሚችል የውሃ ተጠቃሚነት

ረ. የውሃ ምንጮችን መጠበቅ፣ ከጉዳት መከላከልና ማልማት እና ይህም የሚጠይቀው ወጪ

ሸ. ታቅዶ በሚውል ወይም ለተመረጠ የውሃ ፍጆታ ያለው ተነፃፃሪ አማራጭ እስከየትነት

ቀ. ለናይል ወንዝ ስርዓት የተፋሰሱ አገራት ድርሻ መጠን

በ. በእያንዳንዱ የናይል ተፋሰስ አገር የናይል ተፋሰስ ሽፋን የሚኖረው ደርሻ

5. ግድቡን የመሙላት እና የግድቡ ስራ ፖሊሲ መርህ

በግድቡ ፕሮጀክት ላይ ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ምክረ ሀሳብን እና የብሄራዊ የሶስትዮች የቴክኒክ ኮሚቴ የመጨረሻ ሪፖርትን ለመተግብር ፤

ሶስቱ አገራት የሶስትዮች ብሄራዊ የቴክኒክ ኮሜቴ እና ዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ጥናት ግኝቶች የሚያቀርቡትን ምክረ ሀሳብ በትብብር መንፈስ ሊጠቀሙ ይችላሉ፥ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ለማሳካት፤

ሀ. ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጎን ለጎን የግድቡን ውሃ የመያዝ ስራን አካሄድን በተመለከተ በሚቀርቡ አማራጮች ላይ የሚደረግ ስምምነት

ለ. የግድቡ ባለቤት በተለያዩ ጊዜያት እንደተመቸው በሚቀያይረው በግድቡ ስራ መመሪያ እና ዓመታዊ ስራ ፖሊሲዎች የሚደረስ ስምምነት

ሐ. ከታችኛው የተፋሰሱ አገራት የውሃ ክምችት ጋር ለማቀናጀት ሲባል በግድቡ ስራ ላይ ለውጥ የሚያመጣ አስቸኳይ ሁኔታ ሲፈጠር ለግብፅ እና ሱዳን ለማሳወቅ

– በዚህም መሰረት ሶስቱ አገራት በውሃ እና መስኖ ሚኒስትሮች በኩል ተገቢውን ስርዓት ያበጃሉ

– ዓለም አቀፍ የቴክኒክ ባለሙያዎች ኮሚቴ በግድቡ ላይ ጥናት ለማድረግ ዝግጅት ከሚጀምርበት ጊዜ ጀምሮ ከላይ በተጠቀሱት ነጥቦች ላይ ለመስራት የተቀመጠው የጊዜ ገደብ 15 ወራት ነው።

በዚህ የስምምነት ክፍል መሰረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴድሮስ አድሃኖም ሲያስረዱ ዓለም አቀፍ አማካሪ ኩባንያዎች የሚያቀርቡትን የጥናት ውጤት ሁሉንም ኢትዮጵያ የመቀበል ግዴታ የለባትም።

በመሆኑም የጥናት ውጤቱ በሶስቱም አገራት ላይ አስገዳጅ አይደለም። እናም ያልተቀበለቻቸውን የጥናት ውጤት ወደ ሶስትዮሹ የቴክኒክ ኮሚቴ በመውሰድ ተጨማሪ ውይይት እንዲደረግበት ማድረግ ትችላለች።

የቴክኒክ ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ መስማማት ካልቻለ በጉዳዩ ላይ ሶስቱ አገራት የሚያቀርቡትን ባለሙያዎች ምክር መጠየቅ ይችላሉ። በመጨረሻም ወደ አገራቱ መሪዎች ሊወስዱት ይችላሉ።

የውሃ አሞላሉን በተመለከተ ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ ሳይቆም ግድቡን በውሃ የምትሞላበትን የራሷን መመሪያ እና ህግ አዘጋጅታ ታቀርባለች።

በዓመት ውስጥም ውሃ በምን ሁኔታ እንደሚያዝ እና እንደሚለቀቅ እና አሰራሩን መለወጥ ስትፈልግ ማሳወቅ ብቻ ነው የሚጠበቅባት።

ኢትዮጵያ የግድቡን ውሃ  ስትለቅም ሆነ ተመሳሳይ ስራ ስታከናውን በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ጥፋት እንዳያደርስ ለጥንቃቄ የሚፈፀም ለጎረቤት የመጨነቅ ስሜትን የሚያሳይ መርህ ሲሉት ገልፀውታል።

6. መተማመንን የመገንባት መርህ

የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ የሚመነጭ ሀይልን እንዲገዙ ቀድሚያ ይሰጣቸዋል።

በዚህ የስምምነት ክፍል በዓለም አቀፍ ዋጋ ኢትዮጵያ ለግብፅ እና ለሱዳን የኤሌክትሪክ ሀይልን እንዲገዙ ቀድሚያ እንደምትሰጥ የሚገልፅ ሲሆን፥ ይህም ማለት ግን ግብፅ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ ሀይል ከሚገዙ አገራት ከፍተኛውን መጠን ያገኛሉ ማለት እንዳልሆነ ያስረዳል። ከፍተኛውን የሀይል መጠን የሚገዙት ሌሎቹ ጎረቤት አገራት ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለምሳሌ ኬኒያ።

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል የምትሸጥላቸውም ስትፈልግ እንጂ የመሸጥ ግዴታ በስምምነቱ አልተቀመጠም።

የኢትዮጵያን በራስ ሀብት የማዘዝ መብትን የሚያከብር መርህ መሆኑንም ዝርዝር ሰነዱ የያስረዳል ይላሉ።

7. መረጃ የመለዋወጥ መርህ

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ከሶስቱ አገራት የተውጣጡ አባላት ላለው የቴክኒክ ኮሚቴ ጥናት ለማድረግ የሚያስፈልጉትን መረጃዎች ያቀርባሉ።

8. የግድቡ ደህንነት መርህ

ሶስቱም አገራት እስካሁን ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ከዚህ ቀደም የሰጠውን ምክር ለመተግበር ያደረገችውን ጥረት ያደንቃሉ።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ከግድቡ ደህንነት ጋር በተያያዘ ያቀረበውን ምክረ ሀሳብ በመልካም ፈቃድ ትተገብራለች።

9. የሉዓላዊነት፣ የአንድነት እና የአገር ግዛት ሉዓላዊነት መርህ

የናይል ወንዝን በተቻለ መጠን ለመጠቀም እና ለመጠበቅ ሶስቱ አገራት እኩል ሉዓላዊነት፣ አንድነት እና የአገር ግዛት ሉዓላዊነትን መሰረት በማድረግ ተባብረው ይሰራሉ።

ይህ ኢትዮጵያ በግዛቷ ውስጥ ያላትን የውሃ ሀብት ካለማንም ጣልቃ ገብነት እንድትጠቀም ማረጋገጫ የሚሰጥ ነው።

በአጠቃላይ በሰው ሀገር ሀብት አጠቃቀም ላይ ገብቶ የማዘዝ ሰልጣንን ከነአካቴው የሚያስቀር መርህ ብለውታል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

10. ልዩነቶችን በሰላም የመፍታት መርህ

እነዚህን መርህዎች በመተርጎሙ እና በመተግበሩ ሂደት የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በመልካም ፈቃድ መርህ በንግግር እና በድርድር ይፈቷቸዋል።

በንግግሩ እና በድርድሩ የተሳተፉ አካላት ልዩነቶችን መፍታት ካልቻሉ ለሽምግልና ወይም ለንግግር ወደ አገራቱ ፕሬዚዳንቶች እና ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሊልኩ ወይም ሊጠይቁ ይችላሉ።

በዚህ የስምምነት ክፍል ልዩነቶች ሲፈጠሩ እንደሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጉዳዮችን ወደ ሶስተኛ ወገን ወይም ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት የመውሰድ ግዴታን አላስቀመጠም። በመሆኑም በጉዳዮች ላይ ልዩነቶች ሲፈጠሩ ሶስቱም አገራት በራሳቸው ቤት ውስጥ ተነጋግረው መፍታት ብቻ እንደሚጠበቅባቸው ያስረዳል።

*******************

ምንጭ፡- ፋና – መጋቢት 16፣ 2007

Content gathered and compiled from online and offline media by Hornaffairs staff based on relevance and interest to the Horn of Africa.

more recommended stories