ኢትዪጵያን ከፈለክ መጀመርያ እኔን ፈልገኝ!

(ራማቶሀራ ዴርቶጋዳ)

ፅንፈኛው ወንድሜ! የልቤን ልንገርህ፤ ለዛሬ እንኩዋን ልብ ብለህ አድምጠኝ!

ሕመሜ ይመምህ፤ሃሳቤ ያሳስብህ፤ስጋቴ ስጋትህ ይሁን፤ጭንቀቴም ይጭነቅህ፡፡ እባክህንማ አንዴ ዦሮህን ስጠኝ፤ህሊናህን አንዴ ከነጎደበት የማንአለብኝነት፤የትዕቢትና የትምክህት ዓለም ላንዴም ቢሆን ገታ አርገህ መልሰውና እኔን እህትህን ስማኝ፡፡ምናልባት ዛሬ ባትሰማኝ ነገ በሚፈጠረው ሁኔታ ዕድሜ ልክህን ሊፀፅትህ የሚችል ከፍተኛ ችግር ሊከሰት ይችላልና ግድ የለህም ስማኝ!

አዎን! እኔም አንተም የአባቶቻችንን ታሪክና አገር እናውቃለን፤ባለፉት ስርዓቶች የኔም ያንተም ወገኖች የደረሰባቸውን ሁሉ እናውቃለን!!! እስኪ ስለዚህ ጉዳይ በግልፅ እናውራ::

ታድያ እኔ መሰረታዊ ናቸው የምላቸውን በገዢ መንግስታት ደረጃ በትግራይ ህዝብ ላይ የደረሱትን ሰብዓዊ ግፎች በወፍ በረር አስቃኝሃለው፤በዚህም ከውስጤ ያለው ቁስል ምን ያህል ያመረቀዘ እንደ ሆነ ላሳይህ እውዳለሁና ከቻልክ አንተም በኔ ቦታ ሆነህ ላፍታም ቢሆን አስበው! የታሪክን ሰበዝ ስንመዝ ግዜ ላለመፍጀት እንዲሁም የዚህ ፅሁፍ ዓላማው የኔን የእህትህን ስሜት በተቻለ መጠን ትጋራ ዘንድ ስንቅ የሚሆንህን መረጃ ማስጨበጥ ነውና ለውይይት ያህል ከሃ/ስላሴ ጀምሮ እስከ ደርግ ድረስ በትግራይ ህዝብ ላይ የተፈፀሙትን ዘግናኝ መንግስታዊ ግፎችን አንድ ሁለት እያልኩኝ አነሳልሃለው፡፡ ታድያ ወንድሜ! የምፅፈው ከልቤ ነውና አንተም ከልብህ አንብበህ ተረዳኝ፤የምፅፈው ለክርከርና ለሂሳብ ውርርድ አይደለምና!

እስኪ ወንድሜ! አንተን በመጠየቅ ልጀምር! እውነት ስለ አፄ ሀ/ስላሴ ያለህን ስሜት ምንድን ነው? በጎ ወይስ መጥፎ? ስለ ደርግስ? እውነቱን እንነጋገርና አንተና መሰሎችህ እኮ ሀ/ስላሴን ሞዓ አምበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ፤መንግሰቱን ደግሞ ጉዋዱ፤ቆራጡ፤አገር ወዳዱ፤ጀግና እያላችሁ የሌላቸውን የዘር ሃረግና መለኮታዊ ስልጣን ሰጥታችሁ ስታወድሱዋቸው ነው የምትኖሩት! ወንድሜ እኔና ወገኖቼ ደግሞ ንጉሱንም ሆነ ደርግን(መንግስቱን) የምንመለከታቸው በክፋታቸውና በጭካኔያቸው ነው፡፡ታውቃለህ እነዛ ወገኖቼ…የመጀመርያዎቹ ወያኔዎች ለምን ዓመፅ እንዳስነሱ! አዎን ጭቆና አንገሸገሸን ብለው ነበ፡፡መልስ አጡና ዓመፅ ተቀሰቀሰ፡፡ንጉሱ ግን ዓመፁን በዘዴ ማስቆም ሲገባቸው ጭራሽ ከባዕድ አገር (ከእንግሊዝ) ቦንብ ጣይ አውሮፕላኖችን አስመጥተው ህዝቡን አስጨረሱት፡፡ንጉሱ ድርጊታቸውና ጭካኔያቸው በዚህም አላበቃም! መቐለን ታቃት የለ….ያቺ “መቀሌ” እያልክ የምትጠራት….እርስዋንም በጠራራ ፀሓይ ከነ ህዝቦችዋ በጦር አውሮፕላኖች አርሰዋታል! እንግዲህ ይታይህ….አንድ አገርንና ህዝብን አስተዳድራለው ከሚል ወገን እንዲህ ያለው አረመኔነት በከተማ ህዝብ ላይ ሲፈፅም!Photo - Ethiopian nationalities with flag

ከዚህ ይህ ቀረሽ ከማይባል ጭፍጨፋ በመቀጠልም የትግራይ ህዝብ ዳግም አንገቱን ቀና እንዳያደርግ በሚል በስልታዊ መንገድ በድንቁርናና በድህነት እንዲኖር ተፈረደበት! ለዚህም ነው የትግራይ ህዝብ የልመና ተምሳሌት የሆነው! ወንድሜ እስኪ አስበው እኔን ምን እንደሚሰማኝ? እኔ የሚሰማኝ በወቅቱ የነበረው የህፃናት፤ሴቶችና ሽማግሌዎች የጣር ጩሀት ነው…..ሰቆቃ ነው….ሃዘን ነው…..ተስፋ መቁረጥ ነው……በገዛ አገር …አገር አልባ መሆንን ነው! እስኪ ይህን ስሜቴን በኔ ቦታ ሆነህ አስበው! እስኪ አስበው እኔና አንተ እንድ ገበታ ላይ ለምግብ ስንቀመጥ….አንተ ሞዓ አንበሳ ለብሰህ….እኔ ደግሞ ንጉሱ በወገኖቼ በማንነታቸው ምክንያት ብቻ ያደረሰባቸውን ግፍ እያሰብኩኝ….በውስጤ የታመቀ ህመም እየታመምኩኝ! ግን አስበሀው ታቃለህ..ለምን እኔና ወገኖቼ ለስርዓቱ ጥላቻ እንዳሳደርንስ ላፍታ ጠይቀህ ታቃለህ! ለነገሩ የደረሰብንን ማን ይንገርህ፤የተፃፈልህ ታሪክ ሁላ እኮ የተገለባበጠ ነው! ታድያ አሁን እኔ እህትህ ነገርኩህ እኮ! እስኪ አሁን እንኩዋን መለስ ብለህ የኔ ስሜት ይሰማህ፤ህመሜን ታመምልኝ፤ስቃዪን ተሰቃይልኝ! በኔ ቦታ ላፍታም ቢሆን ሁንና ይህ የሆነው ሁሉ ግፍ በኣማራው ክልል ህዝብ ላይ ቢሆን ኑኖ ምን ነበር የሚሰማህ!

እስኪ ወንድሜ አሁን ደግሞ ወደ ቅርቡና እጅግ የከፋው አሰቃቂ፤ከህሊና ሊጠፋ ከቶ ወደማይችለው የግፎች ሁሉ እናት የሆነውን መንግስታዊ ጭፍጨፋ ልውሰድህ፡፡ ደርግን ታቀው የለ! ያ መንጌ ቆራጡ!፤አገር ወዳዱ! እያልክ የምታሞካሸው! አዎን የሱንም ልንገርህ…..ዋናውን ብቻ! ዘርዝሬማ እንዴት እችላለው! ዓለም ላይ ያለው ቀለም ተሰብስቦም ቢሆን አይበቃም…..ያንን የ17 ዓመታት ህልቆ መሳፍርት ግፍ ለመፃፍ! እስኪ ወንድሜ አንዴ ልቦናህን ክፈትልኝማ…..ልወስድህ ነውና…..ወደ ሓውዜን( እግረ መንገድህ ግን ሓውዜን ማለት ምን እንደ ሆነ ልንገርህ…ሓወ-ዜን…የሁለት የትግርኛ ቃላት ድቀል ነው….*ሓው* እና *ባዜን*……የባዜን ወንድም ማለት ነው…..መቼም ባዜንን ታቀው የለ….ዝነኛው ያክሱም ንጉስ ነው…..ሓውዜንን ያስተዳደር የነበረው የእርሱ ወንድም ነበርና….ሃውዜን አሉዋት ከተማዋን)!

እንግዲህ ያ ቆራጡ መሪህ መንግስቱ በሃውዜን ህዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ በዜና ሰምተሀው ሊሆን ይችላል፡፡ግን የሆነው ሁሉ አንተንም ወገኖችህንም አልነካምና አንድም ቀን ትዝ ብሎህ እንደማያቅ እሙን ነው፡፡ እንግዲህ አስበው ከመንግስት አይደለም ከአማፂ ቡዱን እንኩዋን ሊጠበቅ በማይችል ሃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በሃውዜን ከተማ ፤ህዝብ በሞላበት፤ከሁሉም አቅጣጫ በተሰባሰበበት የገበያ ቀን ሆን ተብሎ በተሰጠው መንግስታዊ ትዕዛዝ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ እንዳይውል በተከለከለ የክላስተር ቦንብ በጠራራ ፀሓይ ህዝቡን በአውሮፕላን ፈጁት፤ከተማዋን ወደ ሬሳ ማዕከልነት ቀየሩዋት! በደቂቃዎች ውስጥ 2500 ሰዎች አለቁ፤ከ5000 በላይ ሰዎች አካለ ስንኩላን ሆኑ! ወንድሜ እስኪ ላፍታ ያህል የነበረውን በቃላት የማይገለፅ አሰቃቂ ትዕይንት አስበው፡፡አውነቴን ነው ወንድሜ! እስኪ ንገረኝ ምን ተሰማሕ! አስበውስኪ ይህ ድርጊት የተፈፀመው ባህርዳርና ጎንደር ቢሆን ኖሮ ምንድን ነበር የሚሰማህ! እኔ ደግሞ ምን እንደሚሰማኝ ልንገርህ! ሌላውን ተውውና እችን ቁራጭ ደብዳቤ ስጽፍልህ እንኩዋን ሁኔታውን በማሰብ ብቻ ከዓይኔ የእምባ ዘለላዎች ወርደዋል! በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በቴሌቪዥንም ሆነ በተለያዪ ሚድያዎች አይተህ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ሕፃን የሞተች እናቱን ጡት ሲጠባ፤ከተጣሉት ቦንቦች አንዱን እያንከባለለ ሲጫወትበት…….እስኪ አስበው ያ ህፃን ከነ እናቱ ካንተ ወገኖች ቢሆን ኖሮ! አዎን ያልተነካ ግልገል ያቃል አይደል የምትሉት…….ምንም ላይመስልህ ይችላል! አዎን እኛ ግን ባለፉት ሰርዓቶች በደረሰብን ከቃላት ኣቅም በላይ በሆኑ ግፎች ምክንያት ከውስጣችን የሰረፀ ህመምና ስቃይ አለ! ይህ ያለፈው ሰቆቃ መቼም እንዲደገም አንፈልግምና እንዳንተ ዓይነቶቹ ወንድሞቻችን ህመማችንን እንድትታመሙልን፤ስቃያችንን እንድትሰቃዪልን፤ጩሀታችንን እንድትጮሁልን፤ሃሳባችንን እንድታስቡልን፤ስጋታችንን እንድትሰጉልን እንፈልጋለን! አዎን ይህን ስታደርጉ ነው ከዚህ ቀጥሎ መምጣት ስላለበት የተሻለ መልካም ሂወት አብረን ቁጭ ብለን በመተማመን ስሜት መወያየት የምንችለው፤ስለ ሃቀኛ ሰላም፤ልማት፤ፍትህና ዴሞክራሲም ቢሆን ማሰብና መመካከር የሚቻለው ይህን ስሜት የጋራችን ስናደርገው ነው፡፡አዎን አብረን ስንስቅ፤አብረን እናለቅስ….አብረን ስንደሰት፤አብረን ስንጨነቅ ነው ስለ ሌላውም ማሰብና መመካከር የምንችለው፡፡

ወንድሜ አሁን ባንተና መሰሎችህ ያለው ነገር ግን እጅግ ስሜታችንን የሚነካ፤ህመማችንና ስቃያችን የሚቀሰቅስ ሁኔታ ነው ያለው! እኛን የገደለውን አንተ ካጀገንከው፤ካሞገስከው፤ካከበርከው! በተቃራኒው ደግሞ እኛ ከዛ ሁሉ መከራና ሰቆቃ ራሳችንን ነፃ ለማውጣት ያደረግነውን ትግል ደግሞ ካንቁዋሸሽከው፤ካጣጣልከው፤ካዋረድከው አልፎ ተርፎም የነዛን ገዳዪቻችን ትርፍራፊዎች ወደ ስልጣን ካላመጣሁኝ ብለህ ላይ ታች ካልክ አብሮ ገበታ መቀመጥ ይቅርና ባንድ አገርም መኖር አይታሰብም ነበር! ይሁንና አሁንም አብረን ባንድ አገር መኖር አይደለም አብረን ገበታውም ላይ አለን፡፡ከዛም አልፈን እንጋባለን፤እንዋለዳለን፤እንተሳሰራለን!!! ወንድሜ ይህ ሁሉ የሆነው የፈጣሪ ቸርነት ዋናው ሆኖ የትግራይ ህዝብ ከቂም በቀልና ጥላቻ የፀዳ መሰረቱ የማይናወጥ ኢትዪጰያዊነት ያመጣው ውጤት ነው!

ወንድሜ! ፅንፉን፤ጠርዙን፤ጥላቻውን፤ትዕቢቱን፤ትምክህቱን፤ ወዘተ ተወውና የኛ የወገኖችህን ስሜት፤ህመም፤ስቃይ፤ሃሳብና ስጋት ይሰማህ፤ ይግባህ! ታድያ ለሁሉም ግዜ አለውና እንዳይረፍድብህ! ግዜው አሁን ነው! አሁን ሃቁን ልንገርህ……..ግዜ የለህም!

ኢትዪጵያ……ኢትዪጵያ…..ኢትዪጵያ! ስትል…ሁሉን አጥተህ ብቻህን እንዳትቀር! ወንድሜ ኢትዪጵያ ማለት ጋራና ሸንተረሩ ሳይሆን ኢትዪጵያ ማለት እኔና አንተ ነን፤እኔና አንተ ካለን ኢትዪጵያም አለች፡፡ቃሉስ የሚለው መጀመርያ ፅድቁን እሹ ሌላው ይጨመርላችሁዋል አይደል! እኔ አንተን አንተም እኔን ስንመኝ ኢትዪጵያችንም ትኖራለች!!! ወንድሜ ኢትዪጵያ ያለኔና ያላንተ መቼም አትኖርም፤አንዳችን ከሌለን ኢትዪጵያም አትኖርም…………….. ኢትዪጵያችን እንድትኖር መጀመርያ እኛ እንኑር!

ኢትዪጵያ ለዘላለም ትኑር!

********

Guest Author

more recommended stories